Tuesday, March 10, 2015

እየደመሰሱ መቅዳትለረዥም ዓመታት በአንድ ሬዲዮ ጣቢያ የሠራ ጋዜጠኛ ለአንድ ጥናት ወደ ጣቢያው ይሄዳል፡፡ ከ30 ዓመታት በፊት እርሱ ራሱ ያደረገው ቃለ መጠይቅ ነበር፡፡ ቃለ መጠይቁ የተደረገላት ሴት አሁን በሕይወት የለቺም፡፡ ለዚህ ነበር እርሷ የሰጠቺውን ቃል ፍለጋ ወደ ሬዲዮ ጣቢያው የሄደው፡፡ ያገኘው ግን የጠበቀውን አልነበረም፡፡ የተቀዳው ቃለ መጠይቅ የለም፡፡ ምነው? አለ ጋዜጠኛው፡፡ ‹‹ብዙ ካሴቶችን እየደመሰስን ቀድተንባቸዋል፡፡ በዚያ ምክንያት ያንን ቃለ መጠይቅ አሁን አታገኘውም›› አሉት፡፡ እርሱም በዚህ አዝኖ ወጣ፡፡

ለነገሩ እርሱ በካሴቱ አዘነ እንጂ ከኢትዮጵያ ታሪክ መገለጫዎች አንዱ እየደመሰሱ መቅዳት ነው፡፡ የሚመጣ መንግሥት ወይም ባለሥልጣን፣ ዐዋቂ ወይም ታዋቂ፣ ታሪክ ጸሐፊ ወይም ዐቅድ ነዳፊ ከእርሱ በፊት ለነበረው ነገር ዋጋ ሰጥቶ፣ የየራሱን ሥራ ከመሥራትና የዘመኑን አሻራ ከማኖር ይልቅ ያለፈውን መደምሰስ ይቀናዋል፡፡ 


ሀገር የማታልቅ ሕንጻ ናት፡፡ መሠረቷ ዛሬ አልተጣለም፡፡ መሠረቷ ከተጣለ ቆየ፡፡ እያንዳንዱ ትውልድ የየራሱን ድርሻ እየገነባ ይቀጥላል፡፡ የመጣው ሁሉ ባለው ላይ አዳብሮ፣ አሻሽሎ ወይም አሣምሮ የሚጨምር ከሆነ ሀገር እያደገች፣ እየበለጸገችም ትሄዳለች፡፡ የመጣው ትውልድ ሁሌም ከሥር ከመሠረቱ የሚያፈርሳት ከሆነ ግን ሀገር ባቢሎን ትሆናለች፡፡ ቅርስ እንጂ ሕይወት፣ ታሪክ እንጂ ዕድገት፣ ስም እንጂ ክብር አይኖራትም፡፡ ለጉብኝት እንጂ ለኑሮ አትሆንም፡፡ 

 ባቢሎን በታሪክ ቀድመው ከሠለጠኑ ሀገሮች ተርታ ነበረቺ፡፡ ነገር ግን የገዛት ሁሉ ከመሠረቷ እያፈረሰ እንደገና ሲሠራት፣ የመጣዉ ሁሉ እየደመሰሰ ሲቀዳባት ይሄው ዛሬም አላልፍላት ብሎ የጦር አውድማ ሆናለቺ፡፡ ስለ ኢራቅ ጥንታዊ ታሪክ የሚተረከውና የዛሬዋ ኢራቅ አይጣጣሙም፡፡ የመጡት ሁሉ በባቢሎን ካሴት ላይ እየደመሰሱ ሲቀዱ፣ መሠረት አልባ ጣራ ሊያቆመ ሲደክሙ፣ አሁን የመጡባት አሸባሪዎች ደግሞ ጨርሰው ታሪካዊ ቅርሶቿን በድጅኖ መናድ ጀመሩ፡፡ እየደመሰሱ መቅዳት ካንሰር መሆን ሲጀምር ይሄው ነው፡፡

ይኼ እፉኝታዊ ጠባይ ነው፡፡ እፉኝት የምትባል የእባብ ዘር አለች አሉ፡፡ አፈ ማኅፀኗ ጠባብ ነው፡፡ ከወንዱ ጋር ስትገናኝ የወንዱን አባለ ዘር ትቆርጠውና ወንዱ ይሞታል፡፡ ልጆቿን በማኅፀኗ ፈልፍላ ስትወልዳቸው ደግሞ ለመውጣት ስለማይችሉ ሆዷን እየቀደዱ እናታቸውን ገድለዋት ይወጣሉ፡፡ ልጆቹ ልጅ የሚሆኑት አባትና እናታቸውን ገድለው ነው፡፡ ያለፈውን ካልደመሰሱ መኖር አይችሉም፡፡
የመጣንበትንና የነበርንበትን ማንጠር ጠቢብነት ነው፡፡ መደምሰስ ግን እፉኝትነት፡፡ ማንጠር ማለት ደግሞ እንደ ቅቤ ነው፡፡ እናቶቻችን ቅቤ የሚያነጥሩት ለሁለት ነገር ነው፡፡ በአንድ በኩል ቅቤው ሲነጠር አንጉላው ተለይቶ ይቀራል፡፡ ቅቤውም ኮለል ብሎ ይወርዳል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቅመማ ቅመም በመጨመር በቅቤው ላይ ጣዕም ያክሉበታል፡፡ ወይም ቅቤውን ላቅ ወዳለ ሌላ የጣዕም ደረጃ ያሸጋግሩታል፡፡ ማንጠር ሲባል እንደዚሁ ነው፡፡ በታሪካችን፣ በባሕላችን፣ ወይም በልማዳችን ውስጥ እንደ አንጉላ ያሉ ነገሮች ተጨምረው ከሆነ በዕውቀትና ምርምር፣ በግልጽ ወይይትና ክርክር እሳት ላይ ጥዶ ማንጠር ነው፡፡ አንጉላውን ከለየን በኋላ ደግሞ በነበረው እሴታችን ላይ ሌላ እሴት መጨመር፡፡ 

ቅቤን ማንም አያነጥረውም፤ ባለሞያ ይጠይቃል፡፡ አንጉላውን የማስወገጃ መንገዱ ራሱ ልዩ ሞያ ጠያቂ ነው፡፡አንጉላ መስሎን ቅቤዉን ጭምር እንዳያስወግደው እንደ ዶሮ ላባ ባለ ስስ ነገር እየለዩ ማንጠርን ይጠይቃል፡፡
ታሪካችንንና ባሕላችንን፣ ወጋችንንና ልማዳችንን ስንመረምርና አንጉላውን ስንለይ፣ እንደ ቅቤ አንጣሪው በሞያ መሆን አለበት፡፡ ስሜት ቦታ ሊያገኝ አይገባም፡፡ ቅቤ አንጣሪ ስሜት ውስጥ ከገባ ምች ይመታዋልና፡፡ አረሙን እንነቅላለን ብለን ስንዴውን ጨምረን እንዳንነቅለው ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ ለጊዜያዊ የፖለቲካ ፍጆታ ብለን የምንሠራቸው ሥራዎች አዙሪት ውስጥ እንዳይጥሉን ጉዳዩን የሞያና የዕውቀት ጉዳይ ማድረግ ይገባናል፡፡ ‹ዕውቀት አጠር፣ ስሜት መር› ከሆነው ጉዟችን ይልቅ ‹ዕውቀት መር፣ ስሜት አጠር› ወደሆነው ሥልጣኔ ካልወጣን በስተቀር እዚያው ጨለማው ውስጥ ስንኳትን እንኖራለን፡፡ 

ቅቤ አንጣሪ ሰው ሞያ ብቻ ሳይሆን ጥንቃቄም ያስፈልገዋል፡፡ ምች እንዳይመታው፡፡ የቅቤ ምች ያጠናግራል ይባላል፡፡ ቅቤውን በጥንቃቄ ያነጠረቺ ባለሞያ ናት ‹‹ቅቤ አንጣሪዋ እያለቺ ጎመን ቀንጣሿን ምች መታት› ብላ የተሳለቀቺው፡፡ ነባሩን ነገራችንን ስናነጥር ሞያ ብቻ ሳይሆን ጥንቃቄም ወሳኝ ነው፡፡ የዘመን ምች መትቶ እንዳያጠናግረን፡፡ ጎጠኛነት፣ የፖለቲካ ፍጆታ፣ የሥልጣን ፍቅርና ጊዜያዊ ጥቅም የሚባሉ ምቾች አደገኞች ናቸው፡፡ እነዚህ ምቾች የመቱት ሰው ቅቤውን በሚገባ ማንጠር ቀርቶ ሌላ በሽታ በራሱ ላይ ይጨምራል፡፡ ጤነኛ የነበረው አንጣሪ ተጣሞ፣ ዓይኑ ጠፍቶ፣ ፊቱ ቆሳስሎ ይወጣል፡፡ ከዚያ በኋላ እርሱ ያለፈው ታሪኩን ሁሉ የሚያየው በማንጠሪያ ዓይኑ ሳይሆን በተጠናገረ ዓይኑ ነው፡፡ 

አሁን በደምስሶ መቅዳት ሥራ ላይ የተሠማሩት ብዙዎቹ ወገኖቻችን ምች የመታቸው ናቸው፡፡ ዓይነ ልቡናቸውን ምች ስለ መታው ቅቤውንና አንጉላውን መለየት አልቻሉም፡፡ አንጉላ መስሏቸው ሁሉንም ነባር ቅቤ ሊያስወግዱ የቋመጡ ናቸው፡፡ የዛሬውን መንግሥተ ሰማያት ለማሰኘት የትናንቱን ሲዖል ማድረግ፣ የእነርሱን ዘመን የተድላ ዘመን ለማድረግ አላፊውን ዘመን የመከራ ዘመን ማድረግ፣ የአሁኑን አስተሳሰባቸውን ዘመናዊ ለማድረግ ያለፈውን ሁሉ ኋላ ቀር ማሰኘት የግድ ይመስላቸዋል፡፡ ያለፈው የተቀዳበትን ካሴት አዳምጠው ቀጥሎ የራሳቸውን ከመቅዳት ወይም አዲስ ካሴት ከመጠቀም ይልቅ ደምስሰው ካልቀዱ አይረኩም፡፡ አዲስ ሲሠሩ ከሚደሰቱት በላይ ነባሩን ሲያጠፉ የሠለጠኑ ይመስላቸዋል፡፡

ሰው በአንድ ቦታ ስለተሰበሰበ ብቻ ሀገር አይሆንም፡፡ እንዲያ ቢሆን ኖሮ እሥራኤላውያን አሜሪካና ፖላንድ መኖር ይበቃቸው ነበር፤ ለፍልስጤማውያንም ዮርዳኖስና ሊባኖስ የሚኖሩት የካምፕ ኑሮ በቂ ነበር፡፡  ሰፊ መሬት ብቻውንም ሀገርን አይመሠርትም፡፡ እንዲያ ቢሆን ኖሮ አንታርክቲካ ሀገር ይሆን ነበር፡፡ ሀገር ግን ከሰውም ከመሬትም በላይ ናት፡፡ ሰው በመሬቱ ላይ ሲኖር የሠራው ታሪክ፣ ያካበተው ባሕል፣ የደነገገው ወግና ሥርዓት፣ ያዳበረው ቋንቋ፣ ያመጣው ለውጥ፣ የፈጠረው ዘዴ፣ የገነባው ሥነ ልቡና፣ የተከተለው እምነት፣ የእርስ በርሱ መስተጋብር፣ ዓለምን የሚያይበት ርእዮተ ዓለም፣ ሥነ ቃሉ፣ ሌላም፣ ሌላም፣ ሌላም ተዋሕደው የሚፈጥሩት ነገር ነው - ሀገር፡፡ 
 
እነዚህን የተሠራንባቸውን ነገሮች ነው ማንጠር የሚያስፈልገው፡፡ መጀመሪያ እንሰብስባቸው፣ እንመዝግባቸው፣ እንለያቸው፣እንዘግባቸው፣ እንቀርሳቸው፣ እንወቃቸው፡፡ ከዚያ እናጥናቸው፣ እንመርምራቸው፡፡ በመጨረሻም እናንጥራቸው፡፡ ገመዱ ውስብስብ ነው፡፡ ለዘመናት የተፈተለና የተገመደ፡፡ ርጋታ፣ ትዕግሥትና ጥበብ ይጠይቃል፡፡ ወስነን አይደለም ማወቅ ያለብን ዐውቀን ነው መወሰን እንጂ፡፡ አንዳንዴ መጀመሪያ እንወስናለን፣ ከዚያ እንሰይማለን፣ ቀጥለንም እንፈርጃለን፣ በመጨረሻም እንመታለን፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ግን ዕውቀት፣ ጥናትና ማንጠር ቦታ አይሰጣቸውም፡፡ እንዴው ዝም ብሎ ‹ስቅሎ ስቅሎ› ነው፡፡ ‹ትዕዛዝ ከበላይ፣ እግር ወደላይ› ይሆናል መመሪያው፡፡
 
በዚህ መንገድ ስንቱን እየደመሰስን ቀዳን፡፡ ስንቱን ነባር ዕውቀት ሳንጠቀምበት እንደ ገናሌ ወንዝ ፈስሶ ፈስሶ ቀረ፡፡ ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል የተባለው በራሳችን ላይ ደርሶ ብልሆቹ አውሮፓውያን የራሳችንን መጻሕፍት ሰብስበው፣ ባሕላችንን አጥንተው፣ ታሪካችንን ፈትሸው፣ ነባር ዕውቀቶችን መርምረው - በውስጣቸው ያገኙትን ጥበብ ለዘመናዊ ሥልጣኔያቸው ተጠቀሙባቸው፡፡ እኛ ግን እየደመሰስን ስንቀዳ፣ አንድም ትናንት ሳይኖረን ዛሬን እናቆማለን ብለን መከራ እናያለን፡፡ በጣም የሚገርመው ግን እኛ የትናንቱን ደምስሰን እየቀዳን፣ የነገዎቹ የኛን አይደመስሱም ብለን ማመናችን ነው፡፡ ይኼንኑ አሠራር አይደል እንዴ የምናቆያቸው፡፡   

58 comments:

 1. ሀገር የማታልቅ ሕንጻ ናት፡፡ መሠረቷ ዛሬ
  አልተጣለም፡፡ መሠረቷ ከተጣለቆየ፡፡ እያንዳንዱ
  ትውልድ የየራሱን ድርሻ እየገነባ ይቀጥላል፡፡
  የመጣው ሁሉ ባለው ላይ አዳብሮ፣ አሻሽሎ ወይም
  አሣምሮ የሚጨምርከሆነ ሀገር እያደገች፣
  እየበለጸገችም ትሄዳለች፡፡ የመጣው ትውልድ
  ሁሌም ከሥር ከመሠረቱ የሚያፈርሳት ከሆነ ግን
  ሀገር ባቢሎንትሆናለች፡፡ ቅርስ እንጂ ሕይወት፣
  ታሪክ እንጂ ዕድገት፣ ስም እንጂ ክብር
  አይኖራትም፡ great view dani

  ReplyDelete
 2. ዛሬውን መንግሥተ ሰማያት ለማሰኘት የትናንቱን ሲዖል ማድረግ፣ የእነርሱን ዘመን የተድላ ዘመን ለማድረግ አላፊውን ዘመን የመከራ ዘመን ማድረግ፣ የአሁኑን አስተሳሰባቸውን ዘመናዊ ለማድረግ ያለፈውን ሁሉ ኋላ ቀር ማሰኘት የግድ ይመስላቸዋል፡፡ ያለፈው የተቀዳበትን ካሴት አዳምጠው ቀጥሎ የራሳቸውን ከመቅዳት ወይም አዲስ ካሴት ከመጠቀም ይልቅ ደምስሰው ካልቀዱ አይረኩም፡፡ አዲስ ሲሠሩ ከሚደሰቱት በላይ ነባሩን ሲያጠፉ የሠለጠኑ ይመስላቸዋል፡፡

  ReplyDelete
 3. ዛሬውን መንግሥተ ሰማያት ለማሰኘት የትናንቱን ሲዖል ማድረግ፣ የእነርሱን ዘመን የተድላ ዘመን ለማድረግ አላፊውን ዘመን የመከራ ዘመን ማድረግ፣ የአሁኑን አስተሳሰባቸውን ዘመናዊ ለማድረግ ያለፈውን ሁሉ ኋላ ቀር ማሰኘት የግድ ይመስላቸዋል፡፡ ያለፈው የተቀዳበትን ካሴት አዳምጠው ቀጥሎ የራሳቸውን ከመቅዳት ወይም አዲስ ካሴት ከመጠቀም ይልቅ ደምስሰው ካልቀዱ አይረኩም፡፡ አዲስ ሲሠሩ ከሚደሰቱት በላይ ነባሩን ሲያጠፉ የሠለጠኑ ይመስላቸዋል፡፡

  ReplyDelete
 4. "እኛ ግን እየደመሰስን ስንቀዳ፣ አንድም ትናንት ሳይኖረን ዛሬን እናቆማለን ብለን መከራ እናያለን፡፡" በእውነት ትልቅ መከራ!

  ReplyDelete
 5. Dani, great view. Would have been even greater if you had used more examples. I am sure there are plenty of them out there.

  ReplyDelete
 6. ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል የተባለው በራሳችን ላይ ደርሶ ብልሆቹ አውሮፓውያን የራሳችንን መጻሕፍት ሰብስበው፣ ባሕላችንን አጥንተው፣ ታሪካችንን ፈትሸው፣ ነባር ዕውቀቶችን መርምረው - በውስጣቸው ያገኙትን ጥበብ ለዘመናዊ ሥልጣኔያቸው ተጠቀሙባቸው...................
  Geez PhD German Hager yisetal....Geez gin Ye-Amharic & Tigrigna Enatachew neew!
  ASazagn neew!

  Thanks Dani

  ReplyDelete
 7. ግሩም የሆነ እይታ ! ጆሮ ያለው ይሰማ ልብ ያለው ልብ ይበል ."እየደመሰሱ መቅዳት" እንዳናድግ ያሰቀረን ትልቅ የአገር በሸታ ነወ. መቼም ይህንን ማድረጋችን አለማወቅ እና እራስ ወዳድነት ነው. ካለፈው የሚማር , ያለውን የሚያሰተካክል, ለነገ የሚያሰብ,እየደመሰሱ በመቅዳት የማያምን የአገር መሪዎች የሃይማኖት አባቶች እግዚሃብሔር ይሰጠን .ዲያቆን ዳኒ መድሃሂያለም ባለህበት ይጠብቅህ አሜን!!!

  ReplyDelete
 8. ግሩም እይታ በጣም ልብ የሚነካ!ኢትዬጵያ ትንሳሔሽን ያሳየን!ያ ጌዜ ይምጣ! ስምሸን ክብርሽን የሚያሰጠሩ ድንበርሸን የሚያሰጠብቁ ሁሉንም በአንድ ዐይን ማየት የሚችሉ ፈሪሃ እግዝሃብሔር ያለቸው እንደ ሙሴ እናት ጉበዝ ጀግና ሰው ይፈጠርብሽ! መድሃኒያለም ይጠብቅህ አሜን!!!

  ReplyDelete
 9. የእኔም ምኞቴ ይኸው ነበር፤ ነፍሳቸውን ይማርና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሩትን የለውጥ ዐቅድ በሚገባ ፈር የሚያስይዙበት፣ የተሠሩ በርካታ ስሕተቶችን የሚያርሙበት ጊዜ እንዲያገኙ ተመኝቼ ነበር፡፡

  ኢትዮጵያ ሀያ ዐመት ሙሉ በብዙ ማገዶ ስታበስለው የኖረችውን፣ ከአሁን አሁን በስሎ አውጥቼ በበላሁት ስትለው የነበረውን መንተክተክ የጀመረ ወጥ ሞት ከጉልቻው ላይ አንሥቶ ክንብል አድርጎ ደፋባት፡፡

  ወንድሞቼ፣ የተቃጠለው ማገዶ እንዴት ይቆጫል!
  በቃ ኢትዮጵያ ብስል መሪ እንዳማራት ልትቀር ነው ማለት ነው?

  ብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንዳሉት “ያለፍትሕ ሰላም፣ ያለ ይቅርታ ደግሞ ፍትሕ የለም፡፡”ና በውስጣችን የሚታዩትን የብሔርና የፖለቲካ ቁርሾዎች በይቅርታ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የምንተውበትና የምንለወጥበት ዐቅድ ያወጡልን ይኾናል፤ መንገዱንም ራሳቸው ይጀምሩት ይኾናል ብዬ ተስፋ አደርግ ነበር፡፡ በነበር ቀረ፡፡ አቡነ ቄርሎስ ያሉት ሐሰት የለበትም፡፡ ሞት ትልቅ መጽሐፍ ነው የሚያነብበው ጠፋ እንጂ፡፡

  ReplyDelete
 10. አይ ዳኒ ይሄ መንግስት እኮ ገና እየጀመረ ነው አማራን እና ኦርቶዶክስን ማጥፋት ከልማት አጀንዳው ቀዳሚ ነው ዋልድባ ፤ ዝቋላ ከዛማ ተረኛ ይቀጥላል ያው ሲኖዶሱ butorphanol ተወግቶ ተኝቷል ግን ዳኒ ሃገር ውስጥ ያሉት በመሄድ የራሳቸውን ግዴታ ይወጣሉ ከሃገር ውጭ ያለነውስ ምን ማድረግ እንዳለብን አቅጣጫ እንድታሳየን እንፈልጋለን ነገ በእግዝአብሄር እና በትውልድ ተወቃሽ እንዳንሆን አባቶቻችን በብዙ መከራና እንግልት ያስረከቡንን ገዳማት እኛ ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ አለብን።
  እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ

  ReplyDelete
 11. ሰውዬው ዶሮውን በጦም አርዶ ለምን አረድከው ቢባል ‹‹እሱ ነው ጠዋት እየተነሣ መንጋቱን የሚያሳብቅብኝ፣ አርፌ እንዳልተኛበት፡፡እርሱ ባይጮህ ኖሮ መንጋቱን ማን ያውቅ ነበር? ተኛህ ብሎስ ማን ይከሰኝ ነበር›› አለ አሉ፡፡ ከመንቃት ይልቅ ማንቂያውን ማጥፋት፡፡"

  ReplyDelete
 12. ያለፈው ኢትዮጵያዊ ትውልድ፡ ሰርቶት ባለፈው ታሪክ፡ የሚኮሩ የተለያዩ አገራት ዚጎችን ፡ በየአጋጣሚው በተለያዩ የዓለም አገራት ማግኘት የተለመደ ነው፡፡
  እንደ ዶ/ር በርናንድ በታሪኩ፡ እንደማግኔት ልባቸው የተሳበው፡ በስው ዘርነታቸው ብቻ አምነው፥ በሃገራችን ኖረው ፡ ሰብአዊ ታሪክ ሰርተው ያልፋሉ።

  ይህን ተአምረኛ ትውልድ የተካነው፡ የዛሬዎቹ ጎሳ ቆጣሪዎች፡ ለነገው ትውልድ፡ ማፈሪያ መሆናችን፡ እንዴት አሳዛኝ ነው!

  ReplyDelete
 13. Dr Adanom told us an Ethtiopian woman received 20 million dollar from Australia athlitics fedaration when Abebe gelaw critisize him, he changed his mind and Adanom blame a woman. the reason I mentioned this is our current leader teach us how to lie and use of power. They don't care about the people so they don't know about history. Thank you

  ReplyDelete
 14. wa lega yha aidele hulune ysazenew egzabeher lebanachewen ymaleselachw lela men yebalale!!

  ReplyDelete
 15. Hi, Dani I would like to give you some hint about your writing languche word. As we all know that most of our leader from Tigray region, they don’t understand Amharic very well so please write Tigrina to rich them . Thank you.

  ReplyDelete
 16. You are the one for this Yong generation thanks. Daniel!

  ReplyDelete
 17. ጤና ይስጥልኝ ዲ/ን ዳንኤል

  ዛሬም እይታህን አደንቃለሁ ጥሩ አድርገህ እንደ ባለሙያዋ ቅቤ አንጣሪ ከሽንህ (ጋዳ ለጾሙ) ነው የመገብከን። የኢትዮጵያ አምላክ ለደምሳሾች ልቦና ይስጥልን።
  "....አዲስ ሲሠሩ ከሚደሰቱት በላይ ነባሩን ሲያጠፉ የሠለጠኑ ይመስላቸዋል፡፡"
  ቸር ተመኚው
  ብላቴናው

  ReplyDelete
 18. ሀገር የማታልቅ ሕንጻ ናት፡፡ መሠረቷ ዛሬ
  አልተጣለም፡፡ መሠረቷ ከተጣለቆየ፡፡ እያንዳንዱ
  ትውልድ የየራሱን ድርሻ እየገነባ ይቀጥላል፡፡
  የመጣው ሁሉ ባለው ላይ አዳብሮ፣ አሻሽሎ ወይም
  አሣምሮ የሚጨምርከሆነ ሀገር እያደገች፣
  እየበለጸገችም ትሄዳለች፡፡ የመጣው ትውልድ
  ሁሌም ከሥር ከመሠረቱ የሚያፈርሳት ከሆነ ግን
  ሀገር ባቢሎንትሆናለች፡፡ ቅርስ እንጂ ሕይወት፣
  ታሪክ እንጂ ዕድገት፣ ስም እንጂ ክብር
  አይኖራትም፡

  ReplyDelete
 19. Many Thanks Dani,

  ADWA, which is the proud of Africa ,is Now replaced with TPLF. Ethiolecom and ETV can witness this.

  ReplyDelete
 20. ዳንየ ምን ብየ እንደማወራ አይገባኝም …ብቻ አንተን እግዚአብሔር ይጠብቅህ ፡፡የሚያጠፉ ሰዎችም ሳያውቁ የሚያጠፉ አይመስለኝ ኅሊናቸው ያውቀዋል፡፡የእጃቸውን ያገኛሉ፡፡ግን ይህች ሀገር ታሳዝነኛለች፡፡ እንደ እኔ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ታሪኩን መሰነድ አለበት የተወሰኑ አካላት ሓላፊነት አድርጎ ማለፍ የለበትም ኢትዮጵያዊ መልኩን የሚጠብቅ ….ነውና

  ReplyDelete
 21. ወንድሜ ዲያቆን ዳንኤል ሰላነሳኸዉ ሀሳብ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ በአንድ ወቅት በ FM ራዲዮ ጣቢያ የሰማሁት ዜና ሳሰታዉሰዉ ሁልጊዜም ይገርመኛል፡፡ ከብዙ አመታት በፊት ተሰብስበዉ የተቀመጡ ስለ ጥንታዊት ኢትዮጲያ ብዙ የሚያወሩ መጻህፍት በጨረታ መሸጣቸዉ ሲነገር ሰምቼ ነበር የተሸጡበት ምክንያት ከሃላፊዎች ሲጠየቅ ደግሞ ለአሁኖቹ መጻህፍቶች ቦታ ለማስለቀቅ ነበር ያሉት፡፡ በእነሱ እምነት ከታሪክ አንጻር ከቀደሙት የታሪክ ማጣቀሻዎች የአሁኖቹ ተሸለዋል ማለት ነዉ፡፡ ታሪክ ማለት እንዲሀ ነዉ??? ታሪክ የሚለካዉ በምን ይሆን??? አንድ ለ ኢትዮጲያ ታሪክ ተጠሪ የሆነ መንግስታዊ ተቋም በይፋ እንዲህ ታሪክን ከደመሰሰ ነገ ይቺ ጥንታዊ ሀገር ምን ታሪክ ሊኖራት ይችላል??? የታደለ ተዉልድ ታሪክ ይሰራል ያልታደለ ትዉልድ ታሪክ ይደመስሳል

  ReplyDelete
 22. ዛሬ ዛሬ እየደመሰሱ የራስን መቅዳት ብቻ አይመስለኝም ያለው፣ የቀድሞውን መልካም ይሁን ክፉ ደምስሶ መልካሙን አጥፍቶ ክፉውን አጉልቶ መቅዳት ያለ ይመስለኛል፤

  ለትውልድ በሽታን ማውረስ ከባድ ነው፤ የተበላሸ ታሪክ ማለት በዘመኑልክ ተበላሽቶ እንደተቀመጠ ምግብ ማለት ነው፡ በቆየ ቁጥር መርዛማ ሰው በጥናትም አይደርስበትምና ለሚበላው ደሞ ገዳይ ሆኖ ያገዳድላል ቂም በቀል ያስቋጥራል።

  ልዑል እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክልን!

  ReplyDelete
 23. መምህር...ዲ/ዳንኤል፡- መቼም ይህ ጽሑፍ ዓላማ አለው...አዋቂ ለመባል፣ ዝናህን ለመጨመር ብለህ የፃፍከው አይመስለኝም! ሥልጣንና ኃይል ላይ ያሉት ቢተገብሩት ይጠቅማል...የመሚመጠጡተትመም አሀሁነን የያለወውነን በመደምሰስ ሳይሆን በማንጠር ብቻ ተጠቅሞ ቀጣይ እንዲያደርገው ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ዓለም አሰራሯ (Political philosophy) ለዚህ የተመቸ ስላልሆነ፤ ወይ ሥልጣን መልቀቅ...ወይ የዓለም አሰራሯን በከፊል እንኳን መጠቀም ግድ ትላለች፡፡ Unless the one holding the power have some special ability to resist and protect those who are against his just and perfect governance.

  ReplyDelete
 24. Let God be with you!!!

  ReplyDelete
 25. you always tell as the reality we are going through. we never ask ourselves why and how some thing was done.
  thanks Dn

  ReplyDelete
 26. ሰላም ዲያቆን ዳንኤል
  አመሰግናለው መልካም ዕይታ ነው፤ በርግጥ የሃሳብህ መነሻ የተደመሰሰ ቃለ መጠይቅ ነው። ግንኮ ሥራቸው ሳይነጠር፤ የግድፈት አንጉላቸው ሳይለይ፤ በሀገር ደኅንነት ስም የስንት ሰው ሕይወት ተደምስሷል በሀገራችን ታሪክ?

  አሁንም ትውልድ በቁሙ እየተደመሰሰ ነው፤ መነጠር ያለበት ሃሳብ እና ምልከታ አንጉላ እየተባለ እየተነቀፈ፤ "ምች" የመታው ዐይንና አይምሮ፤የወጣቱን፤ የዜጎቹን ዐይንና አይምሮ "ምች" እያስመታ ነው።
  መፍትሔውን አንተው ጠቁመኸዋል፤ በ"ምች" ያልተጠናገረ ዐይን እና አይምሮ!
  መልካም ሳምንት

  ReplyDelete
 27. Thank you Dani
  We are always busy on deleting our forefathers positive contributions our generations.that is why we always name our country "Adisitua ETHIOPIA"

  ReplyDelete
 28. You expressed our history in a good way
  Thank you Dani

  ReplyDelete
 29. ከትናንቱ መማር አቅቶን ዛሬ ደግሞ ኢሕአዴግ የሠራውን ሁሉ ሳያነጥሩ ሊደመስሱና ሌላ ሊቀዱ የሚቋምጡ ብዙ ናቸው፡፡

  ReplyDelete
 30. አንድ ሰው ለአባቱ በአሮጌ ሰፌድ፣ለሱና ለልጁ ጀግሞ በሸከላ ሰሃን ሲየቀርብ ያየው ልጅ ለምን ብሎ ቢጠይቅ አያትህ ስላረጀ ይሰብረዋል ብዬ ነው አለው። ልጁም በል ሰፌዱን በደህና ቦታ አስቀምጠው አለው፣ አባት ለምን? ቢለው ስታረጅ በሱ እንዳቀርብልህ ብሎ መለ። በሰፈርከው መስፈሪያ መሰፈር የሏል እንዲህ ነው! ይህችንም ታሪክ የቀበለኝ ዲ/ዳንኤል ክብረት ነው።እኔ ደግሞ አጋፈርኳት-እንዳጋፋሪ

  ReplyDelete
 31. አንድ ሰው ለአባቱ በአሮጌ ሰፌድ፣ለሱና ለልጁ ጀግሞ በሸከላ ሰሃን ሲየቀርብ ያየው ልጅ ለምን ብሎ ቢጠይቅ አያትህ ስላረጀ ይሰብረዋል ብዬ ነው አለው። ልጁም በል ሰፌዱን በደህና ቦታ አስቀምጠው አለው፣ አባት ለምን? ቢለው ስታረጅ በሱ እንዳቀርብልህ ብሎ መለ። በሰፈርከው መስፈሪያ መሰፈር የሏል እንዲህ ነው! ይህችንም ታሪክ የቀበለኝ ዲ/ዳንኤል ክብረት ነው።እኔ ደግሞ አጋፈርኳት-እንዳጋፋሪ

  ReplyDelete
 32. ለጉብኝት እንጂ ለኑሮ አትሆንም
  በጣም ትክክለኛ አባባል የዋሾዎች አገር በፍፁም የእግዚአብሄርን ስም የማይጠራ መንግስት ያላት አገር ሆነችብን ፡እረ በየገዳሙ ላሉ አባቶች አሳውቁልንና እግዚኦ ለምህረትህ ይበሉልን

  ReplyDelete
 33. በጣም የሚገርመው ግን እኛ የትናንቱን ደምስሰን እየቀዳን፣ የነገዎቹ የኛን አይደመስሱም ብለን ማመናችን ነው፡፡ ይኼንኑ አሠራር አይደል እንዴ የምናቆያቸው፡፡

  ReplyDelete
 34. ye metanibetin na ye nebernibetin manter tebibnet new::
  medemses gin efegninet ::
  << Ewuket ater: simet mer> ke honew guzuachin yilik < Ewuket mer : simet ater > wede honew silitane kal wotan besteker eziyaw chelemaw wust sinkuatin eninoralen:
  gotegninet: ye poletika fijota: ye siltan fikir na giziyawi tikim ye mibalu michoch adegegnoch nachew:: enezih michoch ye metut sew kibewun be migeba manter kerto lela beshita be erasu lay yichemiral::
  yalefew ye tekedabetin kaset adamtewu ketilo ye rasachewun kemekdat weyim addis kaset kemetekem yilik demsisew kalkedu ayrekum:: addis siseru ke midesetut belay nebarun siyatefu ye seletenu yimeslachewal::
  Ewunwt eko new sewoch ye hualaw kelele yelem yefitu:: ye egna wedfit endemayidemses min wastina alen? mikniyatum egna yetekedawun eyedemesesin kemetan ye mimetaw tiwuldim ye egna yetekedawun eyedemeses ye erasun yikedabetal::
  silezih hulachinim be teleyaye erken(dereja) yalen sewoch ke ezih sthuf (Article) enmar::
  emebete mariyam timesgen endih yemiyastemir ena ye mimekir sew sele setechin, egnam yetemarnewun egziabher belibonachin yasadribin :: Deacon Daniel, egziabher amlak rejim edme ke tena gar yistih.

  ReplyDelete
 35. what a nice view dani may God bless you u r always teaching us and adivce as tanks alot, you r a true teacher of this generation....missing your nxt view.

  ReplyDelete
 36. ሀገር የማታልቅ ሕንጻ ናት፡፡ መሠረቷ ዛሬ
  አልተጣለም፡፡ መሠረቷ ከተጣለቆየ፡፡ እያንዳንዱ
  ትውልድ የየራሱን ድርሻ እየገነባ ይቀጥላል፡፡
  የመጣው ሁሉ ባለው ላይ አዳብሮ፣ አሻሽሎ ወይም
  አሣምሮ የሚጨምርከሆነ ሀገር እያደገች፣
  እየበለጸገችም ትሄዳለች፡፡ የመጣው ትውልድ
  ሁሌም ከሥር ከመሠረቱ የሚያፈርሳት ከሆነ ግን
  ሀገር ባቢሎንትሆናለች፡፡ ቅርስ እንጂ ሕይወት፣
  ታሪክ እንጂ ዕድገት፣ ስም እንጂ ክብር
  አይኖራትም፡ great view dani
  ግዚክስ

  ReplyDelete
 37. አንድም ትናንት ሳይኖረን ዛሬን እናቆማለን ብለን መከራ እናያለን፡፡ በጣም የሚገርመው ግን እኛ የትናንቱን ደምስሰን እየቀዳን፣ የነገዎቹ የኛን አይደመስሱም ብለን ማመናችን ነው፡፡ ይኼንኑ አሠራር አይደል እንዴ የምናቆያቸው፡፡ በእውነት በጣም ትልቅ አባባል ነው ሰሚ ከተገኘ። ቃለ ህይወት ያሰማህ!!!

  ReplyDelete
 38. you are a hypocrite !

  ReplyDelete
 39. dani tebarek tebarek tebarek

  ReplyDelete
 40. ሰላምህ ይብዛ ዲያቆን ዳንኤል። ሰላም ላንተ ይሁን። ከአረዳዴ መስመር ስቼ ካልሆነ "የመጣው ትውልድ ሁሌም ከሥር ከመሠረቱ የሚያፈርሳት ከሆነ ግን ሀገር ባቢሎን ትሆናለች፡፡ ቅርስ እንጂ ሕይወት፣ ታሪክ እንጂ ዕድገት፣ ስም እንጂ ክብር አይኖራትም፡፡ ለጉብኝት እንጂ ለኑሮ አትሆንም፡፡" በማለት የገለጽከውን እንደሚከተለው ቢገለበጥ ለመልእክቱ ስምሙ ይሆናል የሚል አመለካከት አለኝ።

  "የመጣው ትውልድ ሁሌም ከሥር ከመሠረቱ የሚያፈርሳት ከሆነ ግን ሀገር ባቢሎን ትሆናለች፡፡ ሕይወት እንጂ ቅርስ ፣ ዕድገት እንጂ ታሪክ ፣ ዝና እንጂ ክብር አይኖራትም፡፡ ለኑሮ እንጂ ለጉብኝት አትሆንም፡፡" ከተሳሳትሁ እታረማለሁ። እግዚአብሄር ስራህን ይባርክ። ያበርታህ።

  አዲስ ነኝ።

  ReplyDelete
 41. Daniel! You have raised & reviewed vital issues. Let God bless you more wisdom. We expect that a lot will be learned from this essential literature.

  ReplyDelete
 42. What a golden paper i read...bertalin wendimachin.Biro gebiche yemejemeria siraye hulem yanten tsihufoch manbeb new

  ReplyDelete
 43. ዛሬውን መንግሥተ ሰማያት ለማሰኘት የትናንቱን ሲዖል ማድረግ፣ የእነርሱን ዘመን የተድላ ዘመን ለማድረግ አላፊውን ዘመን የመከራ ዘመን ማድረግ፣ የአሁኑን አስተሳሰባቸውን ዘመናዊ ለማድረግ ያለፈውን ሁሉ ኋላ ቀር ማሰኘት የግድ ይመስላቸዋል፡፡ ያለፈው የተቀዳበትን ካሴት አዳምጠው ቀጥሎ የራሳቸውን ከመቅዳት ወይም አዲስ ካሴት ከመጠቀም ይልቅ ደምስሰው ካልቀዱ አይረኩም፡፡ አዲስ ሲሠሩ ከሚደሰቱት በላይ ነባሩን ሲያጠፉ የሠለጠኑ ይመስላቸዋል፡፡

  ReplyDelete
 44. Hi, Dani I live in USA, some media talked about you. They said that " You work for current goverment with under cover agent" Is this true or false?

  ReplyDelete
  Replies
  1. ሰላም ወንድሜ በውጭ ሀገር ያለኸው። "Under cover agent for the government" ይሉሃል አንዳንድ ሚድያዎች እና እውነት ነው ወይስ ሃሰት ብለህ ወንድማችንን ዲያቆን ዳንኤልን ጠይቀኸዋል። ጊዜና ቦታ ፈቅዶለት ዲያቆን ጥያቄህን ይመልስልህ ዘንድ ምኞቴ ነው።

   ይሄ "ለመንግስት መስራት" ወይም "አለመስራት" የሚለው ነገር ብንወያይበት መልካም አጋጣሚ መስሎ አገኘሁት (በነገራችን ላይ የዲያቆን ዳንኤል ጽሁፍ አንጓ መልእክት ከዚህ ጋር ምንም ግኑኝነት የለውም)።

   በቅድሚያ ለፓርቲ መስራትና ለመንግስት መስራት አይለያዩም ወይ? ለሃገራችን ታዲያ እንዴት ነው መስራት የምንችለው? መቼም እኛ የምንደግፈው ፓርቲ ስልጣን ከያዘ ብቻ የሚል ቀልደኛ ይኖር ይሆን እንዴ?

   ወንድሜ (ጠያቂው ከUSA) የአሜሪካ ዜግነት ካለህኮ ዜግነቱን ለማግኘት የገባኸው መኻላ እናት ሃገሩን ከሃዲ አያስብልህም እንዴ? ኤጀንትነት ታዲያ ምንድን ነው ከዚህ የበለጠ? ዲያቆን ዳንኤል ቢፈልግ ኤጀንት ቢሆን ባይሆን ምርጫው ወይም መብቱ የእሱ አይደለም ወይ? ለምን የሚያስተምሩንን የሚመክሩንን የማይገናኝ ነገር እየለጠፋችሁ ቀና ሰው ከአደባባዩ ለማጥፋት ትዳክራላችሁ?

   ለኔ አንድ ሰው እያራመደ ያለው አመለካከት ከተስማማኝ እንዲሁም አመለካከቱን ለሌሎች ወገኖች ለማስተላለፍ የሚጠቀምበት መንገድ የሌሎችን የሃሳብ ወይም የአመለካከት መንገድ በተጽእኖ የማይዘጋ ከሆነ ለመንግስት መስራቱ ወይም ለግል የሚያመጣው ልዩነት ምንድን ነው? ያለማጋነን ዲያቆን ዳንኤል የሚመክረንን የሚያስተምረንን መንግስት ከልቡ የሚያምንበት ከሆነ መንግስታችንን አላወቅነውም ነበር። በመሃይማን ሲሰደብ ሲከሰስ ነበረ ማለት ነው ለኔ። ስለዚህም የእስካሁኑ መንግስትን ያላገዝንበትጊዜ መቃጠሉ ይብቃና የመንግሥትን ሃሳብ ለማስፈጽም እንትጋ (ቀልድ አይደለም)። ፓርቲን መደገፍ ሌላ መንግስትን ማገዝ ሌላ።

   ጊዜው የጥላቻ ፖለቲካን ዕለት በዕለት በመደስኮር የአመለካከት ለውጥ ልናነብርበት የምንችልበት ጊዜ ላይ አይደለም ያለነው። ሁሉም ያመነበትን እንዲሰራ ነጻ ፍቃድ ልንሰጥ ይገባናል እንጂ እኔን ካልመሰልከኝ በቃ ሰላይ ነህ ማለት በፍጹም አይገባም። የዘር ፖለቲካን ለመከላከል ዘረኛ መሆንን አይጠይቅም። የሚያስፈልገው ልክ እንደ ዲያቆን ዳንኤል ያመኑበትን ሃሳብ ለህብረተሰቡ በተገኘው ሚዲያ በመጠቀም ሃሳቡን በግልጽ ቋንቋ በማስገንዘብ በጎ ሃሳቦቹ እጅና እግር ተፈጥሮላቸው መሬት ላይ ወርደው ተግባራዊ የሆነ እንቅስቃሴ እንዲያደረጉ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል እንጂ ኤጀንት ነህ ደጋፊ ነህ ጠላት ነህን መባባልን ምን አመጣው? ነው ወይስ በመገዳደል መፍትሔ የሚመጣ መስሎት ሲጫረስ የኖረውና ዛሬም በእኛ ትውልድ ላይ ያደረ ቂሞቹን ማወራረድ የሚፈልግ የ ያ ትውልድ አባል አለ እንዴ?

   ስለሆነም ወንድሜ ዳንኤል እውነት ያንተን ምክር የሚሰሙ የተወሰኑ ቱባ ባለስልጣናት ካገኘህ ለሃሳቦችህ ተግባራዊነት ከተንቀሳቀሱ አገር በበጎ ትለወጣለችና ከፈለግህ መንግስትን ማገዝ አይደለም ኢህአዴግን ቢሆን ተቀላቅለህ ወይም ሌላ ጠንካራ አቋም ያለው ተወዳዳሪ ፓርቲ መስርትና (እምነትህ ከፈቀደልህ) አገራችንን በተሰጠህ ጸጋ አገልግላት።

   በመጨረሻም ፈጥሮ የሚያወራ የሚያወራውንም ተባለ ብሎ መልሶ የሚዘግብ አሉባልተኛና እርባና ቢስ የሆነ ማህበረ ሚዲያ ወረረንኮ። መረጃ አቀባይ ሳይሆን የሃሰተኛ ወሬዎች መፈልፈያ ሚዲያ በዛብን። ጥላቻን በጥላቻ፣ እሾህን በእሾህ፣ ዘርን በዘረኝነት ሊዋጋ የተነሳ ሚዲያ... ስለዚህ "እንዲህ ይሉሃል አሉ በሚዲያ እውነት ነው ሃሰት?" ሲባል ስለየትኛው ሚዲያ እያወራን እንደሆነ መለየት ይኖርብናል።

   አዲስ ነኝ።

   Delete
 45. Dani yayehibet menged bizu astemirognal.Idme yistilign.

  ReplyDelete
 46. ሺበሺ አድማሴMarch 19, 2015 at 4:03 PM

  የትኛውም ሀገር ቢሆን በአ ድ ቀንና በአንድ ስርወ መንግስት ተመስርታና አድጋ አታውቅም በቅብብሎሽ እንጂ እኔ ብቻ ነኝ አዋቂ ማለት ሀገሪቱንና ህዝቡን ችግር ላይ ከመጣል በስተቀር ጠቀሜታ የለውም ለአሁኑ ገዢዎቻችን ልቦና እግዚአብሄር ይስጣቸው

  ReplyDelete
 47. I feel very much privileged and gratitude to have access to such enormous issues day-in and day-out by a great thinker and observer. Stay Blessed!!!

  ReplyDelete
 48. Sle ewunet Dani, yich tsihuf satasnetrh atqerm. Betam yeneterech tsihuf nat.

  ReplyDelete
 49. የመጣንበትንና የነበርንበትን ማንጠር ጠቢብነት ነው፡፡ መደምሰስ ግን እፉኝትነት፡፡ ማንጠር ማለት ደግሞ እንደ ቅቤ ነው፡፡ እናቶቻችን ቅቤ የሚያነጥሩት ለሁለት ነገር ነው፡፡ በአንድ በኩል ቅቤው ሲነጠር አንጉላው ተለይቶ ይቀራል፡፡ ቅቤውም ኮለል ብሎ ይወርዳል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቅመማ ቅመም በመጨመር በቅቤው ላይ ጣዕም ያክሉበታል፡፡ ወይም ቅቤውን ላቅ ወዳለ ሌላ የጣዕም ደረጃ ያሸጋግሩታል፡፡ ማንጠር ሲባል እንደዚሁ ነው፡፡ በታሪካችን፣ በባሕላችን፣ ወይም በልማዳችን ውስጥ እንደ አንጉላ ያሉ ነገሮች ተጨምረው ከሆነ በዕውቀትና ምርምር፣ በግልጽ ወይይትና ክርክር እሳት ላይ ጥዶ ማንጠር ነው፡፡ አንጉላውን ከለየን በኋላ ደግሞ በነበረው እሴታችን ላይ ሌላ እሴት መጨመር፡

  ReplyDelete
 50. ሳይደመስሱ ለምቅዳት:

  http://www.sewasew.com/

  ReplyDelete