Thursday, March 5, 2015

ፍቅር እስከ መቃብርን የጻፉት ‹‹ሐዲስ›› ናቸው ወይስ ‹‹ዓለማየሁ››?

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ
የሐዲስ ዓለማየሁ የባሕል ማዕከል 3ኛ ጉባኤ ላይ የቀረበ
‹‹አበሻ ባል ሚስቱ ስታረግዝ እርሱ ዕንቅልፍ አይወስደውም›› ይባላል፡፡ ስለምን ቢሉ የልጅ ስም ፍለጋ፡፡ ስም ደግሞ በአበሻ ምድር እንዲሁ አይወጣም፡፡ ቢቻል ከአያት፣ ካልተቻለም ከአባት ጋር የሚገጥም፣ ዘመኑንና ሁኔታውን የሚያሳይ፣ ተስፋንና  ምኞትን የሚያመለክት፣ አንዳንዴም ድጋፍንና ተቃውሞን የሚገልጥ መሆን አለበት፡፡ ‹ጅል እንደ ሠራው በርና መቃን የማይገጥም ስም ይዘህ. ይባላልኮ፡፡ በተለይ በሰሜኑ ማኅረሰብ ስም መጠሪያ ብቻ አይደለም፡፡ እንደ መዝገብ ታሪክን፣ እንደ ሚዲያ ሐሳብን፣ እንደ መጽሐፍ ፍልስፍናን፣ እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት እምነትን፣ እንደ ሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሞን የሚያሳይ  የመገናኛ መሣሪያ ጭምር ነው፡፡በደርግ ዘመን ተቆራጭና መዋጮ በዝቶ ሠራተኛውን መከራ ሲያሳየው፣ በባሕርዳር ጥጥ ፋብሪካ የነበረ በዛብህ የተባለ ወዛደር ለሁለት ልጆቹ ‹ተቆራጩ› እና ‹መዋጮው› የሚል ስም አወጣላቸው፡፡ የልጅ እናቱ በየአሥራ አምስት ቀኑ የልጆቿን ተቆራጭ ልትወስድ ስትመጣ ደመወዝ ከፋዩ ድምፁን ከፍ አድርጎ ‹ተቆራጩ በዛብህ› ‹መዋጮው በዛብህ› እያለ የሕዝቡን ተቃውሞ ሲገልጥ ኖሯል፡፡ በአብዮቱ ዘመን የተወለዱ ብዙ ልጆች ‹አብዮት› የሚለውን ስም በመያዝ ታሪክ መዝግበው አልፈዋል፡፡ ኀዘንን ለመርሳት ያስችላል የተባለውን ልጅ  ማስረሻ፣ ከመከራ በኋላ የተወለደውን አልፈነው፣ አልወልድም ካሉ በኋላ የተወለደውን እምቢ በል፣ ከሌላ ተረገዘ ተብሎ ሲታማ አባቱን መስሎ የተወለደውን ምስክር እያሉ መጥራት ከስም በላይ ጉዳይ ያለበት ነው፡፡ ከዐሠርት ዓመታት በፊትም ልጃቸው ‹ይገደብ ዓባይ› ብለው ትንቢት የተናገሩ ወላጆችም ነበሩ፡፡
እንኳን የልጅ ስም የውሻ ስም ከአንድ ጋዜጣ በላይ የሆነ ማኅበራዊ ጉዳይን ሲገልጥ ኖሯል፡፡
ሁለት ውሾች አሉኝ የማሳድጋቸው
አንዱ ሰምቶ መቻል ሌላው መተው ናቸው
የሚለው ሐሳብኮ ባለስሞቹ ውሾች ሊሸከሙት የሚከብዳቸው ነው፡፡ 
በጎንደር ከተማ በ1970ዎቹ መጀመሪያ የነበሩ አቶ ጨከነ የተባሉ አባት ለመጀመሪያዎቹ ሁለት ልጆቻቸው መንግሥቱና መልአኩ የሚል ስም አወጡ፡፡ ልጆቹም ‹መንግሥቱ ጨከነ› ‹መልአኩ ጨከነ› ተባሉ፡፡ ‹የእግዜር ታናሽ ወንድም› የተባለለት መልአኩ ተፈራ ሰምቶ ሊገላቸው ቢነሣ አገር ጥለው ጠፉ፡፡ ጠፍተውም ዝም አላሉም፡፡ የመከራው ዘመን ሲረዝም በፈጣሪም ተስፋ ቆረጡ መሰል ሦስተኛ ልጃቸውን ‹አምላኩ ጨከነ› ብለው ስም አወጡለት፡፡ 
እኒህ ዛሬ የምንዘክራቸው ሐዲስ ዓለማየሁ እንደሚተርኩልን በአንድ ወቅት እዚህ ምሥራቅ ጎጃም ሲመጡ ‹ኦክስጅን› የሚባል ስም ይሰማሉ፡፡ ገርሟቸው አባትዬውን ሲጠይቁት ትርጉሙን አያውቀውም፡፡ ‹ታድያ እንዴት አወጣህለት› ሲሉት ‹‹በአንድ ወቅት ደጃዝማች ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት እዚያ አካባቢ መጥተው ይህንን ቃል ሲሉት ሰማኋቸው፡፡ መቼም ከእርሳቸው አፍ ክፉ አይወጣም ብዬ ኦክስጅን አልኩት› ብሎ መለሰላቸው፡፡ 
እኛ አገር ስም ብዙ ነገር ነው፡፡
እንዲያውም ሰሞኑን አዲስ አበባ አንድ ስም ሰማሁ፡፡ ቆጥቡ፣ አስቀምጡ በሚባልበት ዘመን የተወለደች ስለሆነች መሰለኝ፤ ‹ባንኬ› ብለው ነው የሰየሟት፡፡ እነ ገንዘቤ፣ ንብረቴ፣ ሀብቴ አንድ ደረጃ አድገው ‹ባንኬ› ሆኑ ማለት ነው፡፡ ምነው ብዬ ብጠይቅ ሰውዬው ለ20/80ም ይሆን 40/60 የሚቆጥቡት ብር አጠራቸው፡፡ ደግሞ ጓደኞቻቸውና ዘመዶቻቸው ይህን ያህል ብር ቆጠብን ሲሉ ይሰማሉ፡፡ ስማቸው መልአኩ ነበርና ልጃቸው ‹ባንኬ መልአኩ› ብለው የኔስ ባንክ መልአኩ ነው ብለው ተጽናኑ አሉ፡፡ ደቡብ ወርጄ ደግሞ ‹መቶ ሃያ› የሚባል ስም ሰምቼ ነበር፡፡ መቼም በ120ው የጌታ ቤተሰብ ሰይመውት ነው ስል ለካስ ነገሩ ሌላ ነው፡፡ ‹‹በቴሌቭዥን 120 ፕሮግራም ሲጀመር ስለተወለደ ነው›› አሉኝ፡፡ 


ከታምሩ መቅድሙ እንዳይበዛ ብለን አሁን ተአምሩን መንገር እንጀምራለን፡፡
የሐዲስም አባት እንዲሁ የሆኑ መሰለኝ፡፡ ወላጆቻቸው ‹ዓለም አየሁ› ብለው ስም ሲያወጡላቸው አንዳች ተስፋ ነገር መሰነቃቸውን ያሳብቅባቸዋል፡፡ ለነገሩ ያ ዘመን  የተስፋ ዘመን ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በቴዎድሮስ የጀመረችውን ዝመና በምኒሊክ በኩል እውን እያደረገች የነበረችበት ዘመን፡፡ መኪና፣ ስልክ፣ ፖስታ፣ ዘመናዊ ትምህርት ቤት፣ የቧንቧ ውኃ፣ አዲስ ሆነው እየመጡ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ወደ አዲስ ሥልጣኔ እየገሠገሠች የነበረችበት ዘመን፡፡ ይኼን ዘመን ለታሪክ ካስቀሩልን መዛግብት መካከል የዚያ ዘመን ስሞች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እንደ ሐዲስ ዓለማየሁ አያት ያሉ ተስፋ ሰናቂዎች ‹ዓለም አየሁ› ብለው በልጆቻቸው ስም ዘክረውታል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ልጅ እምቢ ብሏቸው፣ እንደ ሐናና ኢያቄም፣ ወይም እንደ እግዚእ ኀረያ እና ጸጋ ዘአብ ሲናቁና ሲተቹ ኖረው የጀግና ልጅ አባት የሚሆኑ ጀግና ሲያገኙ ጊዜ ‹ዓለም አየሁ› ብለዋቸው ይሆናል፡፡ በኛ ትውፊታዊ ትርጉም ‹ዓለም› ብዙ ነገር ነዋ፡፡ ዓለም - ተድላ ነው፣ ተስፋ ነው፣ ኑሮ ነው፣ ሀብት ነው፣ ትዳር ነው፡፡
‹ዓለምሽ ዛሬ ነው ዛሬ
እህህ እቴ ሸንኮሬ›› እንዲል፡፡ 
ዓለምን መቅጨት፣ ዓለምን ማየት፣ ከዚህ ግጥም ጋር ለምስክርነት ተቆጥረዋል፡፡ ‹ዓለሜ› ሲል ደግሞ ሁለመናዬ የሚለውን ይተረጉም ዘንድ አለው፡፡ ‹‹የዓለም የሲሳይ ቤት ይሁን› ሲባልም ትርጉሙ ሁለመና ነው፡፡ የማይተነተን፡፡ በርግጥ የዛሬ ተጋቢዎች ‹‹እኔ በመሠረትኩት ትዳር፣ እኔ በሠራሁት ቤት - ዓለምና ሲሳይ ምን አገባቸውና የእነርሱ ቤት ይሆናል› ብለው ይሞግታሉ አሉ፡፡
ታድያ ተስፋ ተስፋን ወለደና አቶ ዓለም አየሁም ልጃቸውን ‹ሐዲስ› ብለው ጠሩት፡፡ አዲስ ዘመን፣ አዲስ ዓለም፣ አዲስ አበባ የሚባሉ ተስፋን የሰነቁ ስሞች በወጡበት ዘመን፡፡ የመታደስ፣ የመነሣት፣ የመሠልጠን፣ እንደ አዲስ የመጀመር ምኞት ሥግው በሆነበት ኢትዮጵያዊ ጊዜ ነበርና፣ እርሳቸውም ‹ሐዲስ ዓለም አየሁ› ብለው ትንቢት መሰል ስም ሰጡ መሰለኝ፡፡ ታድያ ለእኔ ፍቅር እስከ መቃብርን የደረሱት ልጅዬው ሐዲስ ሳይሆኑ አባትዬው አቶ ዓለም አየሁ ይመስሉኛል፡፡ ቢያንስ እርሳቸው ረቂቁን አውጥተው፣ ትልሙን ተልመው፣ ቅመሙን ቀምመው ለሐዲስ ሳይሰጡ አልቀሩም፡፡ እንገር ሲያጠጧቸው፣ ቅቤ ሲያውጧቸው፡፡ ፍቅር እስከ መቃብርና ሌሎቹም የሐዲስ ዓለም አየሁ ድርሰቶች - አዲስ ዓለም አየሁ ናቸው፡፡ 
በፍቅር እስከ መቃብር ውስጥ ፊውዳሊዝም እየበሰበሰ፣ ሊሸከሙት ከሚቻለው በላይ እየሆነ ይታያል- በዚያ ውስጥ ጉዱ ካሣ - አዲስ ዓለም አየሁ ይላል፡፡ በድንጋይ ካብ እየመሰለ ሲፈርስ ይታየዋል፡፡ እንደ ሰብለና በዛብህ ያሉ አዳዲስ ትውልዶች፣ ቀደምቱ በቀረጸላቸው ፊደል ብቻ የማይጽፉ፣ ነባሩ በቀደደላቸው ቦይ ብቻ የማይፈሱ፣ የሚያፈተልኩ አዲስ ዓለመኞች ይታያሉ፡፡ ከፊውዳሉ ማኅጸን ውስጥ እንደ ጉዱ ካሣ ያሉ ፈንቅሎች፣ አይፈሬዎችና ለውጥ ፈላጊዎች እንደሚመነጩ - ሐዲስ ዓለም - አይተዋል፡፡ አንድ ሥርዓት እየበሰበሰ፣ ከሕዝቡ የልቡና ሸክም በላይ ሲሆን ያወጣቸው ሕጎችና አሠራሮች እንኳን ሊታደጉት እንደማይችሉ- በፊታውራሪ መሸሻ የደብረ ማርቆስ ክስና ፍርድ - አዲስ ዓለም አሳይተዋል፡፡ 
በነ አበጀ በለው ዐመጽ በኩል አይቀሬ የነበረውን የገበሬዎች እምቢ ባይነት አባታቸው ቀድመው ቢያዩት መስሎኝ - ልጃቸውን - ገና ምኑም ሳይወጠወጥ ስማቸው - ‹ሐዲስ ዓለም አየሁ› ያሏቸው፡፡ 
ደግሞም ‹ሐዲስ› ነገር ሁሉ ደግ አይደለምና የዚህች ሀገር ‹ክፉው› ሐዲስም ታይቷቸው ነበር አባትዬው፡፡ እንደነ አባ ሞገሴ ያሉ በሞራል የወረዱ፣ ተልዕኳቸውንም የሳቱ፣ ሥልጣን የያዘውን ብቻ ማወደስ ሥራቸው የሆነ መንፈሳዊ መሪዎች፣ በነ አቡነ ጴጥሮስ ቦታ እንደሚተኩ ታይቷቸዋል ልበል፡፡ በ65 – 66 ብቅ ያለው የእንቡጦቹ የአብዮት ሙሽሮች የወጣቶቹ የለውጥ ጉዞ፣ ከስኬት ሳይደርስ መንገድ እንደሚቀር ቢታያቸው አይደል እንዴ - ሰብለ ወንጌልንና በዛብህን ጎሐ ጽዮን ላይ ያስቀሯቸው፡፡ እንደነ በዓሉ ግርማ፣ እንደነ አቤ ጎበኛ፣ እንደነ ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት ያሉ ጉዱ ካሣዎች፣ እዚህች ሀገር ፍጻሜያቸው ለውጥ አምጥተው፣ በትውልዱ ዘንድ ከፍ ብለው መታየት ሳይሆን፣ ከለውጥ አምጭው ትውልድ ጋር አብሮ መሞትና መቀበር መሆኑን ቀድመው በትንቢት መነጽር ቢያዩም አይደል እንዴ ጉዱ ካሣን ከነ ሰብለና በዛብህ ጋር ጎሐ ጽዮን የቀበሩት፡፡ 
በዛብህ አዲስ አበባ ሩፋኤል ነበር የመጣው፡፡ ሰብለንም ሊያመጣት ያሰበው አዲስ አበባ ሩፋኤል ነበር፡፡ ሩፋኤል ደግሞ ፈታሔ ማኅፀን ነው፡፡ የጦቢትን ዓይንም የገለጠ እርሱ ነው፡፡ ‹‹በዓለ መድኃኒትም›› ይባላል፡፡ በዛብህ ግን ማኅፀን ፈቺውንና በዓለ መድኃኒቱን አየው እንጂ አላገኘውም፣ ተሳለመው እንጂ አልተሾመበትም፡፡ ይህቺ ሀገር አንዱ የሚያስፈልጋትኮ የኪነ ጥበብ፣ የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማሲ፣ የዕውቀት፣ የጥበብ፣ የፖለቲካ፣ የለውጥ፣ የሰብአዊነትና የእምነት ጀግኖች ትወልድ ዘንድ ፈታሔ ማኅፀን ነው፡፡ የሚያዋልድ፣ ከምጥ የሚያሳርፍ፡፡ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ አካባቢያዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ዕውቀታዊ፣ ተቋማዊ ሕመሞቿ እንዲድኑ በዓለ መድኃኒት ያስፈልጋታል፡፡ የትውልዱም ዓይን ከጫትና ከሐሺሽ፣ ከፊልምና ዳንስ፣ ከውጭ ሀገርና ከስደት፣ ላቅ ያለ ነገር እንዲያይ እንደ ጦቢት ዓይን ገላጭ ያሻታል፡፡ በዛብሃዊው ሰብላዊውና  ጉዱ ካሣዊው ትውልድ ግን ገና አላገኘውም፡፡ ጎሐ ጽዮን ላይ ቀረ፡፡ ይህን ይሆን አባትዬው ‹ሐዲስ ዓለማየሁ› ያሉት፡፡ ‹በሩቅ አይቶ የሚሳለም ግን የማያገኝ› ትውልድ የሚኖርባትን ኢትዮጵያ አይተው፡፡  ጎሐ ጽዮን - ጽዮን ኢትዮጵያ አይደለችም እንዴ፡፡ የጽዮን ሀገር ናትና ኢትዮጵያ፡፡ ‹‹በስመ ኀዳሪ ይፄውእ ማኅደር - እንዲል በአዳሪዋ በጽዮን ስም ማደሪያዋ ኢትዮጵያም ጽዮን ተብላ ተጠርታለች፡፡ - የጽዮን ጎሕ - እዚያ ነው አዳዲስ ለውጠኞች የተቀበሩት፡፡ አብዮት ልጇን ትበላለች እንዲል መሆኑ ነው፡፡ ብዙዎቹ በዛብሆችና ሰብለዎች፣ ብሎም ጉዱ ካሣዎች - የጽዮን ጎሕ ውስጥ ነው የተቀበሩት፡፡ ዓባይ በረሃ ሳይወስደቸው፤ ግን ሳይሻገሩት፣ አፋፍ እያስቀራቸው፡፡ የጽዮን ጎሕ ውስጥ ገብተው ቀሩ፡፡ ችግሩ ደግሞ ደጀንና ጎሐ ጽዮን ከመለያየታቸው ላይ ነው፡፡ ደጀን ማዶ ጎሐ ጽዮን ማዶ፤ በመሐል በረሃ፡፡ ደጀኑ ሕዝብ ጎሑን አይከተል፣ ወይ ጎሑ ደጀኑን አያስከትል፡፡ ጎሕና ደጀን ለየብቻቸው ይሄዱና ደጀኑ ለውጥ አምጭዎችን ጎሐ ጽዮን ላይ ቀብሮ ዝም ይላል፡፡ ይህን ነው ያዩት - ዓለም አየሁ፡፡
ራሳቸው ሐዲስስ ቢሆኑ ይህንን ዐርባ ዓመት የተቀመጠ የጎጃም ጠላ የመሰለ ልዩ ድርሰት እንዳልደረሱ ተቆጥረው ባለፉት ዘመናት ጎሐ ጽዮን ላይ ተቀብረው አልነበር እድሜያቸውን የጨረሱት፡፡ አባትዬው የጻፉትን ድርሰት ልጅዬው ፊልሙን በቁም አልሠሩትም እንዴ፡፡    
ምርቅና ፍትፍት፣ ግርድና ምርት፣ ጥሬና ብስል የሚጋፉባትን፤ ደጀንና ጎሐ ጽዮን የተለያዩባትን - አዲሷን ኢትዮጵያ አይተው ነው- ሐዲስ ብለው የሰየሟቸው፡፡ እስመ ስሙ ይመርሖ ኀበ ግብሩ እንዲል፡፡ 
 

34 comments:

 1. Replies
  1. ዳኒ እ/ግ ይጠብቅህ እስኪ ከሁሉ ጠብቆህ ለቤተክርስቲያናችን ላዲሱ ትውልድ ተስፋ ያድርግህ ።ምን እላለሁ ሌላማ ።ቃለ ህይወትበያሰማህ።

   Delete
  2. ዳኒ መልካም ነው ያለከው እዳንተ አስተዋይ ልጂ ይኑራት ቤተክርስቲያናችን ።

   Delete
  3. ዳኒ ይበል ብለናል።ግን እኛ ይገባን ብለህ ነው? እ/ግ አምላክ የማዳመጫ ልቦናን ይስጠን እጂ አነተ ብቻ እንኳን ስንቱን የተጣመመውን ታቃናው ነበር እንኳን እማማ ስንት ልጆች እያሏት ።እስኪ በቃ ይበለን።

   Delete
 2. Comment mestetun ene lijemrew meselegn..
  D/n Daniel tiru anbabi neh, Ye Ethiopia lij honeh enditketil efelgalehu, Ethiopia n keafu sayley bewust silerasu enji silela yemayasib endemathon tilk tesfa alegn. Beahunu aqamih ketil. Thank you,

  ReplyDelete
 3. Replies
  1. Dani, amlak yesera zemenun yabzaleh,

   Delete
 4. trew glasa new sem megalech aydele

  ReplyDelete
 5. እስመ ስሙ ይመርሖ ኀበ ግብሩ እንዲል፡፡

  ReplyDelete
 6. ግሩም እይታ በጣም ልብ የሚነካ!ኢትዬጵያ ትንሳሔሽን ያሳየን!ያ ጌዜ ይምጣ! ስምሸን ክብርሽን የሚያሰጠሩ ድንበርሸን የሚያሰጠብቁ ሁሉንም በአንድ ዐይን ማየት የሚችሉ ፈሪሃ እግዝሃብሔር ያለቸው እንደ ሙሴ እናት ጉበዝ ጀግና ሰው ይፈጠርብሽ!ዲያቆን ዳኒ የዝቋላ ነገር እንዴት ሆነ? መድሃኒያለም ይጠብቅህ አሜን!!!

  ReplyDelete
 7. Dear Dn. Daniel. it is very appreciable analysis, keep doing so. As stated in the bible, wisdom is God, he gives this wisdom for those who fear and follow him. We need so many Daniels to teach and to creat ethical generation.
  Stay safe and blessed!

  ReplyDelete

 8. ጥሩ ብለሃል፧ መድሐኔአለም ይርዳሕ።  ReplyDelete
  Replies
  1. ጤና ይስጥልኝ ዲ/ን ዳንኤል!

   እጅግ በጣም ደስ የሚል እይታና አቀራረብ ነው። በቦታውም የተገኘውን ታዳሚ ምን ያህል እያዝናናህ እንዳቀረብከው በቴሌቪዥን አይቼዋለሁ። ስለዚህ የአጓጉል ሰዎችን ያልተገባ ትችትና አካሄድ ወደጎን እየጣልክ እይታህን ቀጥልበት ለማለት እወዳለሁ። ለዚህም ፈጣሪ ይረዳህ ዘንድ ጸሎቴ ነው። በርታ!!!
   በዚሁ አጋጣሚ በስማቸው ሃሳብና አስተያየት የማያቀርቡ ሰዎች የብዕር ስም ቢኖራቸው ጥሩ አይመስልህም?

   ቸር እመኛለሁ!

   ብላቴናው

   Delete
 9. ሰላም ዲ ዳንኤል ስለዝቋላ ገዳማችን ወቅታዊ ሁኔታ ንገረን እንጂ

  ReplyDelete
 10. ሰላም ዲ ዳንኤል ስለዝቋላ ገዳማችን ወቅታዊ ሁኔታ ንገረን እንጂ

  ReplyDelete
  Replies
  1. You souldn't ask him about this topic. the goverment want to creat some fight . Ignore it and you will see when time solve it.

   Delete
 11. ዳኒ ግሩም አድርገህ መጽሐፉን በተለየ መንገድ አይተኸዋል፣ ተንትነኸዋልም።እግዚአብሔር ጸጋውን ይብዛልህ።

  ReplyDelete
 12. ፍቅር እስከ መቃብርን የደረሱት ልጅዬው ሐዲስ ሳይሆኑ አባትዬው አቶ ዓለም አየሁ ይመስሉኛል፡፡

  ReplyDelete
 13. እነኋ ሊቅ ይተነትነዋል! ሥምን በምስጢር በሚሰይመው ዘንድ ትርጉም የሚሰጥ ሥራ ነውና! ዲያቆን እግዚአብሔር ይጠብቅልን!!

  ReplyDelete
 14. ግን እውነተኛው ፍቅር እስከመቃብር ያለ ይመስላችኋል ?
  መፅሀፉን አይደለም

  ReplyDelete
 15. ጥሩ ስሞች እንዳለ ሁሉ መጥፎ ስሞችም አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ድፋባቸው፡ ደምስሳቸው፡ ደመላሽ፡ ውቃው፡ አሸብር፡ መርዙ፡ ወዘተ. እነዚህን ስሞች ለልጆቻችን ከማወጣት ብንቆጠብስ

  ReplyDelete
 16. ዳኒ ምናልባትም የዚህች አገር የቅርብ ቀን ተስፋ የቤተክርስቲያን የቁርጥ ቀን ልጅ ከሚሆኑት አንዱ እና ዋነኛው ትመስለኛለህ፡፡
  አምላክ በነገሮች ሁሉ አብዝቶ ይባርክህ ክንድህን ያበርታው፡፡

  ReplyDelete
 17. ጥሩ እይታ ቀጥልበት...

  ReplyDelete
 18. ዲ/ን ዳኒ
  አንተም ድንቅ ድርሰት አስነበብኸን። እናመሰግናለን።
  እግዚአብሄር ያበርታህ አሜን።

  ReplyDelete
 19. ዲ/ን ዳንኤል
  በጣም ደስ ይላል ቀጥልበት

  ReplyDelete
 20. Egziabher yabertah Dn. Daniel

  ReplyDelete
 21. tsihufocheh astemari ena dess yemilu naachew dani enamesgenalen

  ReplyDelete
 22. መጸሀፉን ከአንበቡክት እረጅም ግዚ ነበር በውጋየሁ ተራኪነት ነፍስ ዘርቶንት በእውን እንድናየው አርጎን ነበር የአንተም እይታ ጥሩ ነው የረሳዋቸውን እንዳስታውስ አርጎኛል ።

  ReplyDelete
 23. Keep it up! I love your views

  ReplyDelete
 24. አቤት መባረክ ብትባረክ እኮ ነው ጌታ እግዚአብሔር ይህን የመሰለውን ፀጋ ያደለህ

  ReplyDelete
 25. መጻሕፍትን እንድትገልጥልን አንተን ለኛ የሰጠን እግዚአብሔር ይመስገን!

  ReplyDelete