![]() |
የጉዞው መሥራቾች
|
ትናንት(እሑድ መጋቢት 13 ቀን 2007 ዓም) በጨጨሆ የባሕል ምግብ አዳራሽ በተደረገ
አንድ መርሐ ግብር ተጋብዤ ተገኝቼ ነበር፡፡ ‹ጉዞ አድዋ› ይባላል መርሐ ግብሩ፡፡
ከዛሬ 119 ዓመት በፊት
ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን በዓለም ታሪክ ያልተለመደ አዲስ ታሪክ ለመሥራትና ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገር የማይደረስበት ከፍታ
ላይ ለማስቀመጥ ሲሉ ከመላዋ ሀገሪቱ አንድ ሆነው ወጥተው፣ አንድ ሆነው ወደ አድዋ ዘምተው ነበር፡፡ ያኔ ብዙዎቹ የተጓዙት በእግራቸው
ጋራ ሸንተረሩን፣ አረሁን ገደሉን እየተሻገሩ በፍጹም ኢትዮጵያዊ ወኔና ሀገራዊ ፍቅር ነበር፡፡ ያ አንድነትና የሀገር ፍቅር ስሜት
ነበር ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችንን ሊደግሙት እንጂ ሊረሱት የማይገባ ታሪክ እንዲሠሩ ያደረጋቸው፡፡