Friday, February 6, 2015

ታሪክ ሠሪ ታሪክ አሻጋሪ ሲያገኝ

አበው ሲመርቁ ‹‹ወይ መልካም ልጅ፣ ወይ መልካም ደቀ መዝሙር ይስጥህ›› ይላሉ፡፡ የሚረከብህ ማለታቸው ነው፡፡ ብዙ ታሪክ ሠሪዎች ታሪካቸውን የሚያስተላልፍላቸው አጥተው ሳናውቃቸው ቀርተናል፡፡ ዛሬ ታሪካቸውን ከፍ አድርገን የምንናገርላቸው ታላላቆቻችን ታሪካቸውን የሚጽፍ፣ የሚጠብቅና ለትውልድ የሚያስተላልፍ ያገኙትን ነው፡፡ ስማቸውን ሰምተን ታሪካቸው ያጣን፣ ሥራቸው ደርሶን ታሪካቸው የጠፋብን አያሌ ጀግኖች አሉን፡፡ አንዳንድ አባቶች እንዲያውም ሰው ሲያጡ ታሪካቸውንና ቅርሳቸውን ለወንዞችና ለተራሮች በአደራነት ሰጥተው ነበር፡፡ ይሄው በየዘመኑ እየተቆፈረ የሚወጣው ቅርስ መሬት አደራ የተቀበለችውን እያስረከበች ነው፡፡

በዘመናዊ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ጎልተው ከሚጠቀሱት ታላላቅ ሰዎች መካከል ሊቀ ሊቃውንት መሐሪ ትርፌ አንዱ ናቸው፡፡ የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ትርጓሜ(1948)፣ የሐዋርያት ሥራ ትርጓሜ፣ የሰባቱ መልእክታትን ትርጓሜ፣ የዮሐንስ ራእይን ትርጓሜ(1951) ያገኘነው በእርሳቸው ድካም ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ‹ርትዕት ፍኖት ዘባስልዮስ በባሕረ ጣና›(1948)፣ ‹መጽሐፈ በቁዔት ዘጾም ወዘበዓል›(1946)፣ ቃለ ምዕዳን(1948)፣ መዝገበ ሃይማኖት(1950) ይህንንም መጻሕፍቱ በመጀመሪያ ገጻቸው ‹ከሊቀ ሊቃውንት መሐሪ ትርፌ› በማለት ያስታውሱናል፡፡ በዚያ ዘመን  ጵጵስና ከሊቅነት በኋላ የሚመጣ መዓርግ ነበርና ቅዱስ ሲኖዶስ እኒህን ታላቅ ሊቅ ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ ‹የጎንደርና የበጌምድር ጳጳስ› ብሎ በሐምሌ 12 ቀን 1952 ዓም ሾማቸው፡፡

ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ ባገለገሉባቸው ቦታዎች በሦስት ነገሮች ይታወቃሉ፡፡ የመጀመሪያው ሁለገቡ ሊቅነታቸው ነው፡፡ የሀገር ቤቱን ትምህርት አንድ ሳያስቀሩ የተማሩ ናቸው፡፡ በተለይም ደግሞ በሐዲስ ኪዳን ትምህርታቸው የሚጠቀሱ ሊቅ ናቸው፡፡ ከሀገር ቤቱ ትምህርት ባሻገርም ወደ ግብጽ ተሻግረው ለሦስት ዓመታት ያህል ተምረው ተመልሰዋል፡፡ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት አንድን አባት ‹ሊቅ› የምትለው በሦስት ነገሮች ነው፡፡ በኦርቶዶክሳዊ ሕይወቱ፣ በኦርቶዶክሳዊ ትምህርቱ እና በኦርቶዶክሳዊ ድርሰቱ፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ይህን ከሚያሟሉት መካከል አንዱ ናቸው - አቡነ ጴጥሮስ (1901- 1961 ዓም)፡፡ 

አቡነ ጴጥሮስ የሚታወሱበት ሁለተኛው ነገር ያለማቋረጥ ዞረው በማስተማራቸው ነው፡፡ የጎንደር ከተማ ለእርሳቸው የሥራ ማዕከል እንጂ የመቀመጫ ከተማ አልነበረም፡፡ እንዲህ እንዳሁኑ መኪና ባልነበረበት ጊዜ እስከ ሱዳን ድንበር ድረስ በእግርና በበቅሎ ዞረው አጥቢያዎችን ጎብኝተዋል፣ አስተምረዋል፣ ችግሮችን በቅርበት ፈትተዋል፣ አጥምቀዋል፣ አብያተ ክርስቲያናትንም ተክለዋል፡፡ በዚህ አገልግሎታቸው የተነሣም እጅግ አስቸጋሪ በሚባሉ ቦታዎች የሚኖሩ ምእመናን ሳይቀር ያስታውሷቸዋል፡፡ 

በጎንደር ስለ አቡነ ጴጥሮስ ሐዋርያዊነት የሚነገር አንድ ትርክት አለ፡፡ ብጹዕ አባታችን ያለ ዕረፍት ከጋራ ጋራ፣ ከቆላ ቆላ ሲዘዋወሩ የተመለከቱ አንድ አባት ‹‹አባታችን ምነው ጥቂት ቢቀመጡ›› አሏቸው፡፡ አቡነ ጴጥሮስም ‹አይ አባታችን ሂዱ እንጂ መች ተቀመጡ ተባልን›› ብለው መለሱላቸው ይባላል፡፡  
የአቡነ ጴጥሮስ ሦስተኛው መታወሻቸው ለገዳማዊ ሕይወት የነበራቸው ፍቅር ነው፡፡ በተለይም ዐቢይ ጾምንና ጾመ ማርያምን ከከተማ ወጥተው በታላላቅ ገዳማት ማሳለፍ ይወዱ ነበር፡፡ በመጨረሻው ሕይወታቸውም ዕለተ ዕረፍታቸውን የተረዱት ለዐቢይ ጾም ሱባዔ በማኅበረ ሥላሴ ገዳም በነበሩበት ጊዜ ነበር፡፡ እዚያ በሱባዔ ላይ እንዳሉ ዕረፍታቸው መድረሱን ዐወቁ፡፡ ወደ ጎንደር ተመልሰውም ሥራቸውን መልክ መልክ ማስያዝ ጀመሩ፡፡ በተለይም በየሀገሩ ሲዘዋወሩ ያሰባሰቧቸው ታሪካዊ ቅርሶች ለትውልድ ይተላለፉ ዘንድ ሁነኛ ሰው እንደሚያስፈልጋቸው ዐወቁ፡፡

አባ ሙሉ ሽታነህ በአቡነ ጴጥሮስ ዓይን የገቡት ያኔ ነበር፡፡ አባ ሙሉ አቡነ ቀሲሳቸው ናቸው፡፡ ዲቁናና ቅስና የሰጧቸው አቡነ ሚካኤል ሲሆኑ ቅኔና ቅዳሴን በሚገባ የተማሩ ሊቅ መነኮስ ናቸው፡፡ ደርቡሽ ያጠፋውን ኳንትቻ አርባዕቱ እንስሳ እንደገና ነፍስ የዘሩበት፣ አለፋ ወረዳ ያለቺውን ቼባ ማርያም እንደገና የገነቡ፣ በጉሙዝ አካባቢ ሐዋርያዊ ተልዕኳቸውን የፈጸሙ፣ የአንጋራ መድኃኔዓለምን ገዳም የእህል ችግር ለመፍታት በሬ በታንኳ ጭነው በመውሰድ ተአምር የሠሩ፣ የአቡን ቤት ገብርኤልን ባለ ታላቅ ሕንጻ አድርገው ካህናቱን ከልመና ያወጡ፣ የአባ ዝንግሪትን ድልድይ አስገንብተው ሕዝብን ያገናኙ፣ ከወጣት ጋር ወጣት፣ ከዐዋቂ ጋር ዐዋቂ ሆነው ለስብከተ ወንጌል የሚጣደፉ የጎንደር ፈርጥ ናቸው፡፡ 

 ይህንን የገመገሙት፣ በመንፈሰ ትንቢትም የተመለከቱት አቡነ ጴጥሮስ ታሪካዊ ቅርሶቻቸውን በአደራ ለአባ ሙሉ አስረከቧቸው፡፡ ይህንን አደራ አባ ሙሉ ለሃምሳ ዓመታት ጠብቀዋል፡፡ መሣሪያ ይዘው በኃይል ሲያስፈራሯቸው፣ ገንዘብ ይዘው በወርቅ ሲደልሏቸው፣ ሥልጣንን ተጠቅመው አውጣ አግባ ሲሏቸው፣ ተንኮል ተጠቅመው ለስርቆት ሲያሸምቁባቸው፤ እርሳቸው ግን ጸሎት ከጥበብ ተጠቅመው ከግማሽ ምእት በላይ ጠብቀዋል፡፡ ወርቅን በምናኔ ድል አድርገዋል፡፡ ቅርሶቹን አልባሌ አስመስለው በማስቀመጥ ሌቦችን አታለዋቸዋል፡፡ ቤታቸው የገባ ሰው እንኳን ቡትቶ የተከማቸ እንጂ ቅርስ የተቀመጠ መሆኑን አያውቅም ነበር፡፡ እርሳቸውም ሌላ ቦታ እንዳስቀመጡት ነበር የሚያወሩት፡፡ በሥልጣንና በኃይል የሚመጣባቸውንም በሱባዔ ያሳልፉታል፡፡     
አባ ሙሉ ዐቅማቸው እየደከመ፣ እድሜያቸው እየጨመረ ሄዷል፡፡ ሁለት ጊዜ በአገልግሎት ላይ ወድቀው ዛሬ በክራንች ነው የሚጓዙት፡፡ የዛሬ 23 ዓመት በጎንደር ሳገኛቸው የነበራቸው የሃይማኖት ጽናትና ለሥራ ያላቸው ፍቅር ግን መቼም የሚሞት አይመስልም፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን መርዳት፣ ወጣቶችን ማበረታታት፣ ለቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጉ ግንባታዎችን በታማኝነትና በጥራት መሥራት፣ ገዳማትና ችግረኞች እንዲረዱ ማድረግ፣ የተጣሉትን ማስታረቅ፣ ዛሬም አልጋ ላይ ሆነው እንደገና ሊሠሩት የሚመኙት አገልግሎታቸው ነው፡፡ ሎሬት ጸጋየ ገብረ መድኅን በቴዎድሮስ ስንብት ላይ እንደገለጸው ‹ከሠሩት ነገር ይልቅ ያልሠሩት ይቆጫቸዋል››፡፡
አሥራ አንድ ሊቃነ ጳጳሳት በጎንደር ተፈራርቀዋል፡፡ አባ ሙሉ ግን ሳይቀየሩ ሁሉንም አገልግለዋል፡፡ የሁሉን ታሪክ ለግማሽ ምእተ ዓመት ሰብስበዋል፡፡ ወደ ፈጣሪያቸው ከመሄዳቸው በፊት ግን እነዚያን በተጋድሎ ያቆዩዋቸውን የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ንዋያተ ቅድሳት፣ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶች ለትውልድ ማስረከብ ፈለጉ፡፡ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤልሳዕም ሐሳባቸውን ተቀብለው ለቅርሶቹ ማስቀመጫ ሙዝየም እንዲሠራ አደረጉ፡፡ ሙዝየሙም ጥቅምት 26 ቀን 2003 ዓም አስመረቁ፡፡ አባ ሙሉም ለሃምሳ ዓመታት የጠበቋቸውን ቅርሶችም ሕዝብና መንግሥት ባለበት፣ ቤተ ክህነትና ምእመናን በተገኙበት በይፋ ለትውልድ አስረከቡ፡፡
ታሪክ ሠሪ እንዲህ ያለ ታማኝ ታሪክ አሻጋሪ ሲያገኝ ምንኛ ዕድለኛ ያደርገዋል፡፡ አባ ሙሉን ያብዛልን፡፡    

18 comments:

 1. አሜን ያብዛልን። ለአንትም እድሜና ጤና ይስጥህ ቃለ ሕይወት ያሰማህ።

  ReplyDelete
 2. Gonder lay eyalehu yihin tarik alawekim,Antenim sirahin geta yibarkilh,Laba Mulum edime yichemirilin.

  ReplyDelete
 3. Great Father, Thank You

  ReplyDelete
 4. ይህንን የገመገሙት፣ በመንፈሰ ትንቢትም የተመለከቱት አቡነ ጴጥሮስ ታሪካዊ ቅርሶቻቸውን በአደራ ለአባ ሙሉ አስረከቧቸው፡፡ ይህንን አደራ አባ ሙሉ ለሃምሳ ዓመታት ጠብቀዋል፡፡ መሣሪያ ይዘው በኃይል ሲያስፈራሯቸው፣ ገንዘብ ይዘው በወርቅ ሲደልሏቸው፣ ሥልጣንን ተጠቅመው አውጣ አግባ ሲሏቸው፣ ተንኮል ተጠቅመው ለስርቆት ሲያሸምቁባቸው፤ እርሳቸው ግን ጸሎት ከጥበብ ተጠቅመው ከግማሽ ምእት በላይ ጠብቀዋል፡፡ ወርቅን በምናኔ ድል አድርገዋል፡፡ ቅርሶቹን አልባሌ አስመስለው በማስቀመጥ ሌቦችን አታለዋቸዋል፡፡

  ReplyDelete
 5. Aba mulu yasadegugne abati nachew gin yihin kidisnachwun alawukim. behewot eyalu mesimate asidesitognal. keriu zemenachwen yibariklachew

  ReplyDelete
 6. አሜን ያብዛልን!የሚደነቁ አባት ፀሎታቸው በረከተቸው አይለን፠የሚወዷትን ኢትዬጵያ ትንሳሔ ያሳያቸው፠ጌታ ሆይ ያባቶችን ልብ ክፈት እንደ ቅዱሰ ፓውሎስ የቤተክርስቲያን ብርሐን አድርጋቸው፠እኛንም ታሪክ ሰሚ ብቻ ከመሆን አድነን፠ስራ ሰርቶ ፍሬ ለማፍራት እንድንችል ቅዱሰ ፈቃድህ ይሁን! ዲያቆን ዳኒ እመብርሐን አትለይህ አሜን!

  ReplyDelete
 7. ታሪክ ሠሪ እንዲህ ያለ ታማኝ ታሪክ አሻጋሪ ሲያገኝ ምንኛ ዕድለኛ ያደርገዋል፡፡ አባ ሙሉን ያብዛልን፡፡ thank you dannie

  ReplyDelete
 8. ...አንድ አባት ‹‹አባታችን ምነው ጥቂት ቢቀመጡ›› አሏቸው፡፡ አቡነ ጴጥሮስም ‹አይ አባታችን ሂዱ እንጂ መች ተቀመጡ ተባልን›› ብለው መለሱላቸው ይባላል፡፡ ሹመት ከፈጣሪ ሲሆን እንዲህ ነው። ፈጣሪንም ሆነ ሰውን ለማገልገል የተመረጣችሁ የኚህን አባት ልብና ጽናት ይደርባችሁ። ወንበራችሁን መቀመጫ ብቻ እያደረጋችሁ ስራና ሃላፊነታችሁን እባካችሁ አትዘንጉ።

  ReplyDelete
 9. Waaaw gorgeous!!!! Betam des yilal

  ReplyDelete
 10. papapapapa gud new yesew hiwot

  ReplyDelete
 11. አንድ አባት ‹‹አባታችን ምነው ጥቂት ቢቀመጡ›› አሏቸው፡፡ አቡነ ጴጥሮስም ‹አይ አባታችን ሂዱ እንጂ መች ተቀመጡ ተባልን›› ብለው መለሱላቸው ይባላል፡፡ ሹመት ከፈጣሪ ሲሆን እንዲህ ነው።

  ReplyDelete
 12. ይህን አርቲክል እያነበብኩ በአእምሮዬ የሆነ ነገር ተመላለስብኝ። ምን መስላችሁ?! አልነግራችሁም! እንድነግራችሁ ከፈለጋችሁ ጦቢያን(ሀገሬን) መልሱልኝ!

  ReplyDelete