Wednesday, February 25, 2015

ጠላ፣ ጥብስና ግድብ

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሲመኙት የኖረ፣ የትውልድን ሕልም እውን ያደረገ፣ በዘመናዊ ታሪካችን ውስጥ ሊጠቀስ የሚችል የዚህ ትውልድ ሥራ ነው፡፡ ‹ዓባይን መገደብ› ታላቅ ሐሳብ፣ ታላቅም ውሳኔ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከአካባቢው ሀገራት ጋር የምታደርገውን ውይይት ቋንቋውን የቀየረ፣ የግዮን ምንጩ ከኢትዮጵያ ተራሮች መሆኑን ከብራና አውርዶ መሬት ላይ የጻፈ ነው፡፡ 
 
ስለ ሕዳሴው ግድብ የሚሠሩት ማስታወቂያዎች ግን ፈጽሞ ግድቡን የማይመጥኑ፣ እንኳን ለዓባይ ግድብ ለኛ ቤት አጥርም የማይሆኑ፣ በውስጣቸው ምንም ዓይነት ሀገራዊ ርእይና ፍልስፍና የሌለባቸው፤ ከጠላና እንጀራ የማያልፉ ናቸው፡፡ እንዴው ግድቡ አፍ ስለሌለው እንጂ በስም ማጥፋትና በክብረ ነክ ወንጀል ይከስ ነበር፡፡  የታሪክ ባለሞያዎች፣ የፖለቲካ ጠበብት፣ የኪነ ጥበብ ልሂቃን፣ የእምነትና የባሕል ምሁራን፣ የሥነ ቃል አጥኒዎች፣ የሐሳብ መሪዎችና የሕዳሴ ኮከቦች መነጋገሪያ፣ መከራከሪያ፣ ሐሳብ ማራቀቂያ፣ ትውልድ መቅረጫ፣ ትውልድ ማነሣሻ፣ መሆን የነበረበት የሕዳሴው ግድብ የቀልደኞች ማቧለቻ ሲሆን እንደማየት ያለ የክፍለ ዘመኑ ርግማን የለም፡፡


እኔ እንዲያውም እነዚህ ግድቡን የማይመጥኑ ማስታወቂያዎች በግብጽ ነው እንዴ ስፖንሰር የሚደረጉት? እላለሁ፡፡ ግድቡኮ የግንባታ ሂደት ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥት ከአንድ ኮንትራክተር ጋር ተነጋግሮ የሚያጠናቅቀው፡፡ ዋናው ጉዳይ አስተሳሰቡ ነው፡፡ ለምን እንገነባዋለን? የምን ማሳያ ነው? ዓባይን እንገድባለን ስንል ምን ማለታችን ነው? ዓባይ በኢትዮጵያ እምነት፣ ታሪክ፣ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ባሕል ውስጥ ምን ቦታ ነበረው? አሁን ወደየትኛው ቦታ እየወሰድነው ነው? ዓባይን የመገደብ ሂደትና ስኬት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መፍጠሪያ መስፈንጠሪያ እንዲሆን ምን እንድርግ? እነዚህን ነው መተንተን፣ እነዚህን ነው መሥራት፣ እነዚህን ነው የሕዝብ ገንዘቦች ማድረግ፣ በእነዚህ ላይ ነው መግባባት ያለብን፡፡ ግድቡ መሠራት ያለበት በዜጎች ላይ ቀልደን ሳይሆን ዜጎችን በብቃት አሳምነን ነው፡፡  
 
ግድቡ ያልቃል፡፡ ወንዙም ይቀጥላል፡፡ የሚቀረው ታሪክና ሐሳቡ ነው፡፡ አሜሪካውያን በአሪዞናና በኔቫዳ መካከል የሚገኘውን የሁቨር ግድብን የሠሩት(እኤአ ከ1931-36) በችግር ወቅት ነው፡፡ ገንዘባቸው፣ ጉልበታቸውንና ዕውቀታቸው ሠውተው ነው የሠሩት፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ገንቢዎች ሕይወታቸው ከፍለውለታል፡፡ አያሌ አሜሪካውያን ዛሬ ግድቡን ለመጎብኘት ሲሄዱ ከግድቡ በላይ ስለ ግድቡ አሠራር የሚያሳየውን ሙዝየም መጎብኘት ነው የሚያስደስታቸው፡፡ ለምን ተገነባ? የዚያን ዘመን መሪዎችና ሕዝብ ምን ነበር ዓላማቸው? እንዴት ነበር የገነቡት? እነማን ምን ዓይነት መሥዋዕትነት ከፈሉ? ግድቡን ሲገደቡ አሜሪካን የት ማድረስ ነበር ሕልማቸው? ይህን ነው ሙዝየሙ የሚተርከው፡፡ የተሠው ዜጎችን፣ የቀን ራሽን እየተሰጣቸው የገነቡ አሜሪካውያንን፣ በአነስተኛ ክፍያ ለሀገራቸው የሠሩ ባለሞያዎችን ያሳያል ሙዝየሙ፡፡
 
ሁቨር ግድብ ለአሜሪካውያን ግድብ ብቻ አይደለም፡፡ የአልሸነፍ ባይነት መገለጫ፣ ሀገርን ከግል ጥቅምና ከጊዜያዊ ችግር በላይ አድርጎ ማሰቢያ፣ ብንወድቅ እንነሣለን፤ ‹ኢኮኖሚያችን ለጊዜው ቢወድቅም፣ እኛ ሕዝቦች ግን አልወደቅንም› የሚለውን የአሜሪካውያንን የዚያ ዘመን ፍልስፍና ማረጋገጫ ነው፡፡ ጽናታቸውንና የሀገር ፍቅራቸውን ማሳያ ነው፡፡ አስጎብኝዎቹ እንደሚሉትም ‹እንደ ሕዝብ አንወድቅም› የሚለውን ፍልስፍናቸው ማስመስከሪያ ነው፡፡ 
 
የሕዳሴው ግድብ ግን ‹የዚህ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ጎበኙት› ከሚለው ዜና በዘለለ ‹ስለምኑ› የማይወራለት፣ ፍልስፍናው የማይተነተንለት፣ ከግድቡ በላይ፣ ከአሸዋው፣ ከሲሚንቶውና ከብረቱ በላይ፤ ከጠጠሩና ከድንጋዩ ባሻገር ግድቡ ምንድን ነው? የሚለውን መግፍኤ ሐሳብ የሚናገርለት ያጣ ምስኪን ግድብ ነው፡፡ ልጆቻችን ነገ ግድቡን አይደለም የሚጎበኙት፡፡ እንዴት ተሠራ፣ ለምን ታሰበ፣ አባቶቻችን ምን ለውጥ ነበር ሊያመጡ ያሰቡት? የነበሩትን ተግዳሮቶች እንዴት አለፏቸው? የግድቡ መሠራትስ ምን የአስተሳሰብ፣ የአሠራር፣ የኢኮኖሚ፣ የባሕል፣ የዲፕሎማሲና የሀገር ገጽታ ለውጥ አመጣ? የሚለውን መመርመር ነው የሚፈልጉት፡፡ ከግድቡ ጀርባ የነበረውን የኢትዮጵያውያን ፍልስፍናና መንፈስ ነው የሚሹት፡፡  
 
ያ ሁሉ ቀረና፣ ጽድቁ ቀርቶ በወጉ እንኳን የሚኮንነው በማጣት …
 
ጭራሽ ሰሞኑን የምናያቸው ማስታወቂያዎች ደግሞ የግድቡን ሐሳብ አውርደው አውርደው ገንቦ ጠላና የብረት ምጣድ ጥብስ ላይ የሚጥሉ ሆኑ፡፡ ከዚህ በፊት ከጉንጭ የተረፈ ዳቦ በመብላት፣ በጎልማሶች ትምህርት ላይ በማሾፍ የተሠራውን ማስታወቂያ ስንታገሠው አሁን  ደግሞ  ‹ሕዳሴው ወርዶ ወርዶ› የጠላና የጥብስ መጨዋቻ ሆነ፡፡ ፀጉሯ እንኳን ወርዶ ወርዶ ‹ይጠቀለላል እንደ ሰርዶ› ነበር የተባለው፡፡ እንዴው ከዚህ የተሻለ ከፍ ያለ ሐሳብና የመንገሪያ መንገድ አጥተን ነው የግድቡን ሐሳብ በጋን ጠላና በብረት ምጣድ ጥብስ የምናሰቃየው? 
 
አሁን የሦስት ብር የስልክ ሎተሪን ለመግለጥ ‹መቼ ነው መብላት የሚጀመረው?›› ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል? መብላት ከተጀመረ ቆየ አይደለም እንዴ? መብላቱ አስቸግሮ አይደል እንዴ ፀረ ሙስና የሚባል መሥሪያ ቤት የተቋቋመው? አሁንኮ ሰው  መብላትንና መበላትን ለምዶት ‹ምናለ በልተው እንኳን ቢሠሩ› እያለነው፡፡›› የዐጸደ ሕጻናት አማርኛ ማስተማሪያ ይመስል ‹‹ጋን በጠጠር ይደገፋል›› የሚለውን አባባል ለማሳየት ጠላ የሞላ ጋን ማሳየት ያስፈልጋል? ግድቡ አሳዘነኝ፡፡ ‹እብድ የያዘው መልክ አይበረክትም› ማለት ይኼ ነው፡፡ 
 
ልጅቱ የሐር ነዶ የመሰለ ፀጉር ነው ነበራት አሉ፡፡ አልፈለገችውም፡፡ ፀጉር ቤት ገባችና ‹‹ቁረጭኝ›› አለቻት ፀጉር ሠሪዋን፡፡ ከከፈለቻት እርሷ ምን ተዳይዋ ልትመደምዳት ተነሣች፡፡ እዚያ ፀጉር ቤት ልትሠራ ገብታ የነበረች እናት ብትመክራትም ወጣቷ እምቢ አለች፡፡ ሴትዮዋም ‹‹ ይህን የመሰለ ፀጉር ማን እንዲህ ባለ ጭንቅላት ላይ ብቀል ብሎታል› አለች አሉ፡፡  

ሲሆን ‹በባሕል ትክክል ለመሆን› በዚህ ከፊሉ ሕዝብ በሚጾምበት ጊዜ የጥብስ ማስታወቂያ ባይኖር ጥሩ ነበር( የግድ መጠበስ ካለበት ወይም ጥብሱ በስፖንሰር የመጣ ካልሆነ)፡፡ ደግሞስ ከመቼ ወዲህ ነው ለገንቦ ጠላ የሚጋደሉ ጠጪዎች ሀገራዊ ለውጥ አምጥተው የሚያውቁት? ‹ዶሮ ብታልም ጥሬዋን› ሆኖ ካልሆነ በቀር፡፡ የሦስት ብር ሎተሪ ለማስቆረጥ በገንቦ ጠላ መጣላት አመልን በቴሌቭዥን መግለጥ ካልሆነ ምን ሊሆን ነው፡፡
 
ወይ ግድቡን ‹የሕዳሴ ግድብ› ብለን መጥራታችንን እናቁም፤ ወይ ማስታወቂያዎቻችን ግድቡን የሚመጥኑ ይሁኑ፡፡ ያን የመሰለ ታላቅ ሐሳብና የትውልድ ሥራ በገንቦ ጠላ፣ በብረት ምጣድ ጥብስ፣ በጉንጭ ሙሉ ዳቦ መቀለጃ አታድርጉት፡፡   

42 comments:

 1. ‹እብድ የያዘው መልክ አይበረክትም› ማለት ይኼ ነው፡፡
  you are the special one dani
  GOD bless you !!!

  ReplyDelete
 2. ስላም ዲያቆን ዳኒ, እየተናደድኩም እየሳኩም ነው ያነበብኩት ዕይታህን.(ግብፆች ይሆን ማስታወቂያውን እስፖንሰር ያዳረጉት?) አባይን ለመገደብ የአገሬ እዝብ እንዴት ሆኖ ገንዘቡን እነደሚሰጥ እግዚሃብሔር ያውቀዋል
  በዚህ ደግ እዝብ ላይ በገንዘቡና በጊዜው ማሾፍ ተገቢ አይደለም እንበል!!!የሚያስተውል ልቦና ይሰጠን አሜን!!
  ዲያቆን ዳኒ እግዚሃብሔር ሰራህን ይባርክ አሜን!!!

  ReplyDelete
 3. Thank you D/n Daniel for writing about this.

  But, like all the good observations and critical view points we have seen and read everywhere, I am afraid that it will also fall on deaf ears. I don't think the "Woyane" govt will even care who disapproves their method of raising funds for this project. As long as the money flows in their pockets..
  When it stops and the "scaredy" people start to realize that most of it goes to the members of the Woyane govt, then even you D/n Daniel have to be afraid, because may be now you are having an influence on the general public opinion. And eventhough I am scared of the consequences, thet is all I wish and I pray for (all the hard) work you are putting into your web blog.

  I hope you will inspire more and more people to do the right thing for their country Ethiopia. As things are going down the hill right now, I don't think there will be much "Ethiopia" left at the end of this generation, unless the brave and true Ethiopians everywhere wake up and take the reins.
  May God protect Ethiopia and may HE give you the strength to keep on fighting for the right thing.
  God bless,

  ReplyDelete
 4. Dani:
  Many Thanks. This is actually what John the Baptist was doing.
  Others: Please be aware that Dani is not talking about Politics. Rather, he is telling the reality and the Truth that his Religion, Country and the public are expecting.

  ReplyDelete
 5. ከመቼ ወዲህ ነው ለገንቦ ጠላ የሚጋደሉ ጠጪዎች ሀገራዊ ለውጥ አምጥተው የሚያውቁት?

  ReplyDelete
 6. ከመቼ ወዲህ ነው ለገንቦ ጠላ የሚጋደሉ ጠጪዎች ሀገራዊ ለውጥ አምጥተው የሚያውቁት?

  ReplyDelete
 7. nice view but i see a little bit arrogance zer

  ReplyDelete
 8. በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የማስታወቅያ ሰዎቻችን ምን ያህል የማስታወቅያ እውቀት አላቸው ብለን ብንጠይቅ መልሱን ከስራቸው ማየት ነው።በሃገራችን የመገናኛ ብዙሃንን ቦታ ለመቆጣጠር የሚያስፈልጉ ዋና ዋና መስፈርቶች ድፍረት፣አድር ባይነት፣አዙሮ አለማሰብ፣እንደ ሱፐር ማን ራስን በየቦታው መክተት ፣በየጊዜው ኢንተርቪው አድራጊ ወይም ተደራጊ መሆን፣ትንሽ ማወቅ ብዙ ማውራት ብቻ መተው ይሻላል
  የማስታውቅያ ስራ ህዝብ አእምሮ ውስጥ አንድን ጉዳይ ተክሎ መሄድ ነው አላማው እንደየ ማስታወቅያው አይነት ደግሞ አስተዋዋቂውም የማስታወቂያው አስተሳሰብም የተለያየ መሆን አለበት ለነገሩ የሃገራችን አስተዋዋቂዎች እኮ ሊቆች ናቸው እግዚአብሄር ይመስገንና አላውቅም የሚለውን ቃል አያውቁትም አንድ ነገር ብዬ ልጨርስ ራሳቸው በሰሩት ፊልም ላይ እኮ ሰው ሳይቀይሩ ፮ ማስታወቂያ የሚሰሩ ናቸው ስለዚህ የአባይ ጉዳይ ለነሱ ከከረሜላ ማስታወቅያ የተለየ ነገር የለውም ለነሱ ዋናው ቁምነገር ካሜራው ፊት እንደባለ ውቃቢ አጔርቶ መመለስ ነው።ወደፊት የማያስብ ጭንቅላት ሳይዙ እንዴት አድርገው ወደፊት የሚቆይ ማስታውቅያ ይስሩ።
  ቸር እንሰንብት

  ReplyDelete
 9. Betam tekekel
  "Degmos kmeche wedihe naw Lgnebo tela Ymigadelu Hagerawi Lewete Ymiyametute"

  ReplyDelete
 10. ታላቅ መልእክት - ሰሚ ጆሮ ካገኘ

  ReplyDelete
 11. የማስታወቂያ ነገር ከተነሳ የራት ሰዓት እየተጠበቀ የሚቀርበው ገንዲና ከወሊዲ ጋር የተያያዘ ማስታወቂያ ምቾት አይሰጠኝም፡፡ሰዓት ቢመረጥለት፡፡
  ዳኒ ያነሳሀው ጉዳይ ግን ጥብሱ በጾም ባይሆን ከሚለው አመክንዮህ ውጭ ሌላው ዝርዝር ትችት አላሳመነኝም፡፡ማስታወቂያው ተደራሽ የሚያደርገው ከተማ ቀመስ የምንለውን ምሁር ብቻ አይደለም፡፡ከመሀይማናን ከህጻናት ጀምሮ ያለውን ተመልካች ነው፡፡ገጠሬውም አይረሳ፡፡ስለዚህ በተማረ ከተሜ ዐይን ብቻ አንየው፡፡
  መቼ ነው መበላት የሚጀመረው የሚለው ቃል የአመታት ጉጉታችን መገለጫ ነው፣ለጋኑ የሚደርገው የመደገፍ ተጋድሎም ሀገርን ተባብሮ የማቆም ምሳሌ ነው፣ጠጠሩ የጥረታችን(ማስታወቂያው እድሜና መሃይምናንን ታሳቢ ያደርጋልና ለምሁራን ላይጥም ይችላል)፣ቆፍጣናው ገበሬና ጎዳዳዋ እመቤት ፅዋውን መቅመሳቸው ደግሞ ተስፋው የሚጨበጥ መሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡ካላለባበስነው በስተቀር ጠላ በገጠሩ አርሶ አደር የስካር ምንጭ ሳይሆን የዘወትር የጥም መቁረጫና የወገብ መደገፊያ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡በተለይ በእኔና በዳኒ ሀገር በጎጃም ጠላ የስካር መጠጥ ሳይሆን በጥራት ተዘጋጅቶ የኃይል ምንጭ ነው፡፡ባጭሩ ከነፍልፍሎ 8100 ቀጥሎ ይሄኛው ማስታወቂያው ለእኔ ተመችቶኛል፡፡
  ይሄንን ጨርሰን ሌላ እንጀምራለ………..ን!!!!

  ReplyDelete
  Replies
  1. ይህ የከተሜና የገጠሬ ዕይታ ጉዳይ ሳይሆን ሐሳብን በትክክል ያለመግለጽ ጉዳይ ነው፡፡ በተጨማሪም ማስታወቂያ ውስብስብ ቅኔ መሆን የለበትም፡፡ ለ“መሃይማን”ም ሆነ ለ“ምሁራን”! የነፍልፍሉም ማስታወቂያ ቢሆን ሳቢነት የለውም፡፡

   Delete
 12. ማስታወቂያውን ማየት ነበረብኝ ከማንበቤ በፊት፤ አልተረዳሁክም(ቅሬታህን ልጋራ አልቻልኩም)

  ReplyDelete
  Replies
  1. ስለ ማሞ ቂሎ ለማወቅ የግድ እሱን በአካል ማግኝት ወይም ማየት አይጠበቅብህም ከመልክቱ ስዕሉን መሳለ ይቻል ይመስለኛል።

   Delete
 13. let the democratically elected leader do the job

  ReplyDelete
 14. Thank you Dn Daniel. No one chec it . They look the group not the ideas.

  ReplyDelete
 15. what an excellent and funny view it is!!! GOD bless u!!

  ReplyDelete
 16. ያልተማረ ለማናገር ደፋር ነው የሚከፋበትን አያውቅምና፡፡ እኔም በማስታወቂያው ተገርሚያለሁ ስለ አባይ ለማውራት እርቦት የሚጓመጅ ሰው ነው ማየት ያለብን ወይስ ሃገራዊ አንድነትን የሚገነባ፣ ስሜትን ወደ ልማት የሚያሸፍት፣ የዚህ ትውልድ በመሆን ለመጪው የሚዘከርታሪክን ማስተላለፍ፡፡ ጐበዝ እነ አፃ ቴውድሮስን፣ ሚኒሊክን የምንዘክረው በዛን ጊዜ በነበሩ ታሪክ ፀሐፊዎች በፃፋት፣ በገጠሙት ግጥምና በሰሩት ታሪክ ነው፡፡ እናንተ ባለማስታወቂያዎች ይኽ ትውልድ ሲያልፍ የሚቀረው ታሪክ ጠላና ጥብስ የሚጐማጅ ትውልድ ሆኖ እንዳይቀር አደራ፡፡ መንግስትም ቢሆን ኃላፊነቱንይወጣ፡፡

  ዲ/ዳንኤል ሀሳቤን በመግለፅህ በጣም ደስ በሎኛል

  አመሰግናለሁ፡፡ ፍቅሬ ከባ/ዳር

  ReplyDelete
 17. ጦም ባይሆን ኖሮ ‹‹አንጀቴን ቅብ አጠጣኸው›› እልህ ነበር፡፡ስለዚህ ‹‹አንጀቴን አራስከው›› እላለሁ! ዓይንን በጨው ማጠብ ለመድረክ በሚጋብዝብት ዘመን እና አገር ውስጥ ን እና መታገስ ነው፡፡ ደግነቱ ቴሌቪዥን ሥሩት ሰዎችአብረው ሪሞት ኮንትሮል መፈብረካቸው ያስመሰግናቸዋል፡፡ የቲቪ ሪሞት አንደ ኢትዮጵያ ሚያገለግልበት ሌላ አገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ሞዛዞቹ ሲመጡ ጥርቅም ለማድረግ ይመቸናላ! ስላካፈልከን ሃሳብ እድሜ ከጤና ያድልልን፡፡

  ReplyDelete
  Replies
  1. <>
   አገላለፁ ተመችቶኛል እውነትክን ነው ሳይደግስ አይጣልም አይደል የሚባለው?!

   Delete
 18. Daniel, I have a question to you.
  > At recent time,"Abay Damp" is it burning issue for our peoples ?
  > `why you are not talk about present hot issues ?

  ReplyDelete
 19. በሌሎች አገሮች ፡ በተማሩ ሰዎች የሚሰሩ ሥራዎች፡  እኛጋ በታማኞች ስለሚሰሩ፥  የስራው ውጤት "አላዋቂ ሳሚ ንፍጥ ይለቀልቃል" እንደሚባለው ሆንብንና ተቸገርን።

  አንድ የዘመኑ ባለስልጣን  " እኛ ታማኝነታቸውን እንጂ፡  ትምህርታቸውን አንፈልገውም" ብለው ያሉት፡  የማይዘነጋ አባባል ነው።

  ታማኞች ሆዳቸው ካልጎደለ አይናከሱም። ሰለዝህ ሆዳቸውን ሞልቶ ፡ ሰው የሚመስሉ ውሾች  ማትረፍ ይቻላል። ዋናው ነገር፡ አስበልጦ የሚከፍል ካገኙ ሊናከሱ ይችላሉና፡   በዓይነቁራኛ መጠበቅ ነው።

  ታማኞች ሰለወደፊት ታሪክ ቀርቶ፡  ስለነገም ለማሰብ፡  አቅሙ የላቸው!

  ReplyDelete
 20. በመጀመሪያ ሰማይን ያለ ምሰሶ ምድርን ያለካስማ በጥበቡ ላቆመ÷ ለእኛ ልጆቹ ኃጢያት ስርየት በቀራንዮ አደባባይ የደም ዋጋ ለከፈለ÷ ጥንተ ጠላታችንን ላሸነፈልን÷ ጠባቂ መልዓክትን ላኖረልን÷ ዕልፍ ዓዕላፋት ቅዱሳንና ሰማዕታትን አርአያና ምሳሌ ላዘጋጀልንና የቅድስና ዋጋቸውን አምነን በስማቸው ውሃ በመስጠት እኛም ዋጋቸውን እንድናገኝ ለፈቀደልን÷ የመዳናችን ምክንያት የሆነች ንጽህይተ ንጹሃን እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን በቅዱስ ዮሐንስ በኩል ለዓለም ሁሉ እናት አድርጎ ለሰጠን÷ መዳናችን በእሱና ከእሱ በኩል ለሆነው ÷ ዘመንን (ሰዓታትን)ለፈጠረው አልፋና ዖሜጋ አምላክ በፈጠረው ሰዓታት ሁሉ ያለማቋረጥ በቅድስና የተቀደሰ ምስጋና ይድረሰው። አሜን።

  ሰላም ላንተ ይሁን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት። እግዚአብሄር ከፈተና ይሰውርህ ያጽናህ። (መቼም ኃጥዕ ቢመርቅ ምን ዋጋ አለው እንጂ ብዙ ብዙ በመረቅኩህስ ነበር። ብቻ እሱ ፈቃዱ ሆኖ ዛሬም ነገም እያፀና ይመርቅህ። አሜን።)

  ዲያቆን ዳንኤል የተለያየ አይነት አገልግሎት ላይ በመፋጠን ጊዜ ሊያጥርህ እንደሚችል ብረዳም ስስታም ሆኜ ተጨማሪ ግልጋሎትን ከአንተ ተመኘሁ።

  ዲያቆን ያለኝን ጥያቄ በዚህ አደባባይ (blog) ላይ አልጠይቅህም። ምክንያቱም አደባባዩ ላይ ከቀረቡ አስተማሪና ገንቢ ሃሳቦች ጋር ምንም ግኑኝነት የሌላቸው ነገርግን የራሴን ህይወት እንዳርምና ከአስመሳይ መንፈሳይነት እንዴት ልላቀቅ እንደምችል÷ እንዲሁም መንፈሳዊና ግብረገባዊ ጥያቄዎች ሲኖሩኝ እየጠየቅሁህ አምላክ ጊዜና ቦታ በፈቀደልህ ወቅት ትመልስልኝ ዘንድ መልካም ፈቃድህ ቢሆንና እሺ ብትለኝ addism_eng@yahoo.com ላይ "ሰላም ነህ አዲስ?" ብለህ ከአደባባዩ ጀርባ ብታገኘኝ... በጣም ደስ ይለኛል። ልቦናህን እሱ በፈቃዱ ያራራልኝና!!!

  በጎ የምትሰራበት ዘመንህን እየባረከ ያርዝምልህ። አሜን።

  አዲስ ነኝ።

  ReplyDelete
 21. እሺ ዳኒ መቼም የማታስታውሰን ነገር የለም
  የማስታወቂያውን ነገር ተወው ፡ግን ይሄ ምስኪን ህዝብ ከሚበላው የሚዘለው የበለጠበት ፡እውነት በዜና እንደምናየው ደስ ብሎት ነው ደሞዙን የሚያዋጣው ? ምነው እነ የዘመኑ የሀገር ቤቱ አልበቃ ብሎአቸው በውጭ አገር ካስቀመጡት ትንሽ ቢያዋጡና ይህን ደሞዙ ሳይነካ ቢኖርበት
  ኧረ እግዚአብሄር ያያል ቆንጠጥ አድርጎም አሳይቶናል
  አመሰግናለው ዳኒ መተንፈሻ ስላዘጋጀህልን
  እድሜህን ያርዝመው

  ReplyDelete
 22. እናመሰግናለን ወንድማችን :-ሰሙኑ የምናየው የባሰ ሆነዋል ።ዓባይን የመሰለ የማንነት ጉዳይ ይዘን ሦስት ብር ለማገዝ ወዴት መሄድ እንዳለብን
  ሳናውቅ ግራ የሚያጋባ ማስታወቂያ እያየን ነው ሚድያዎች አረ እባካቹ.....

  ReplyDelete
 23. I am afraid that dani will be turned to be arrogant.... i like it except some arrogance unlike the previous dani.

  ReplyDelete
 24. ከመቼ ወዲህ ነው ለገንቦ ጠላ የሚጋደሉ ጠጪዎች ሀገራዊ ለውጥ አምጥተው የሚያውቁት?

  ReplyDelete
 25. Dn. Daniel,
  What!?
  First, I am a regular reader of your blog page. I do not enjoy your article about advertisements being made about Nile Dam. Why? It seems to me you want to ignore the main issue and want to focus on minor ones. All Ethiopians care about Nile river. As you stated it, it is one of our vital resources. We all are happy to use Nile to generate power, for irrigation, tourist attraction and the like. The question is how to make sure we will get these benefits from Nile. The current dam construction process on Nile is not started for the values you briefly mentioned in your article. Leave alone the general public, Ethiopians with special skills, who can contribute for the successful completion of the dam, were not engaged in the process. Without too much details, the government is carrying out the dam construction purely for political purpose and to prosper (Not the nation) themselves in the process. I do not think you miss this fact. So, how do you dare to ignore the main issue and focus on minor issues. Please always remember, many people have respect for you and use this gift of God in a very ethical and Christianity way. Otherwise …….
  Thank you

  ReplyDelete
 26. ‹‹ ይህን የመሰለ ፀጉር ማን እንዲህ ባለ ጭንቅላት ላይ ብቀል ብሎታል› አለች አሉ

  ReplyDelete
 27. እግዚአብሔር አንተን፣ የዘመናችን ዕንቁ መምህራችንን ያቆይልን፣ ግን ዳኒ ስለግድቡ አስፈላጊነትና ሀገራዊ አንድምታ ምን አለበት ትንሽም ቢሆን ቀደም ብለህ ጽፈህ ቢሆን የበለጠ ሙሉ ሆን ነበርእግዚአብሔር አንተን፣ የዘመናችን ዕንቁ መምህራችንን ያቆይልን፣ ግን ዳኒ ስለግድቡ አስፈላጊነትና ሀገራዊ አንድምታ ምን አለበት ትንሽም ቢሆን ቀደም ብለህ ጽፈህ ቢሆን የበለጠ ሙሉ ሆን ነበር

  ReplyDelete
 28. ዳኒ ከዚህ ቀደም እንዳልከው ይመስለኛል:: የሚመጥን ነገር ለመሥራት መጀመሪያ ስለምን እያወራን እንደሆነ መገንዘብ አለብን:: እነርሱን እንተዋቸውና ይህ ግድብ ምንድን ነው ለእኛ? የኃይል ማመንጫ ብቻ? ኧረ ይሄ ነገር ከዚያም ያለፈ ልዩ ትእምርታችን ነው:: ይህ ሕዝብ ተዋሕዶ የኖረ ከደሟደም፣ ከሥጋዋ ሥጋንና ከነፍሷ ነፍስ ነስተን:: ያቃተን መተቃቀቡ ነው:: አንዳችን አንዳችንን መጠበቁ ማክበር መከባበሩ የመስጠት የመቀበል ባሕሉ:: ለዚህ ደግሞ እየገነባነው ያለውን ዓይነት በርካታ ግንባታዎች የሚያስፈልጉን ይመስለኛል::
  የግድቡን ሥራ ዓይነት በርካታ የጋራ ቅርሶች ያስፈልጉናል:: በአንድነት የምንዘምርላቸው፣ የምንፈክርላቸው፣በስማቸው የምንምልባቸው፣ የጋራ ጀግኖች ያስፈልጉናል:: በብሉይ ታሪካችን ብቻ ሳይሆን ሁሌም የምንኮራባቸውና ኪዳናችንን የሚያድሱ በየዘመናቱ የሚገነቡ አዳዲስ መገለጫዎች አዳዲስ ታሪኮች ሊኖሩን ይገባል:: የሕዳሴው ግድብ ያ ነው::
  አሁን የተያያዝነው ታሪካዊ የቅርስ ግንባታ ነው:: ቅርስ ከዘመን ርቀቱ ከታሪካ ዊፋይዳው ቀድሞካበረከተውና ከሚያዘክረው ትናንት የተነሳ ቅርስ ሆኖ ይጎበኛል፣ ይጠበቃል፣ ይወደዳል፣ ይከበራል:: አሁን የምንገነባው ቅርስ ግን ከዚህ ይለያል:: እየተገነባ የሚቀረስና የሚጎበኝ የቅርስ ግንባታ::

  ራእያችንን እየገነባንነው:: የእርቅ የአንድነት የመተባበርና የሰላማችን ሐውልት እየቆመነው:: በወንዝ በጎጥ በጎሳ እየተከፋፈለ በጠላትነት ይተያይ ይጋደል ይጣላ ደም ይቃባ ደም ይመልስ የነበረ ሕዝብ ግንባታ ላይ ነው:: ይህን ሕዝብ በልዩነት ውስጥ ባለው አንድነት ተውቦ በሕብረት ቆሞ ሲዘምር ማየት እንዴት ያምራል::

  የሌሎችን ሳይሆን የራሳችንን ደም የገበርንበት የጋራ ሐውልት ካለን ይህ የመጀመሪያችን ይመስለኛል:: ጊዜችንን ገንዘባችንን ዕውቀታችንን የተጠቀመ ያስተባበረን እንዲህ ያለ ሐውልት ኖሮን ያውቅ ይሆን? ይህ ሐውልት የትናንት ድላችን አይደለም:: የሰማእታትም አይደለም:: የሙታንም የገዳዮችም አይደለም:: የሕዳሴያችን ሐውልት ነው:: ያለፈውንም ያለውንም የሚመጣውንም ሕዝብ የሚያስተሳስረው ሐውልት:: ያለፈውን ቁጭቱን የተወጣንበት ያለውን ያዋሀድንበት የሚመጣውን ያማማልንበት ድንቅ ምልክት:: ሕዝባችን እንቆቅልሹን የሚፈታበት፣ ሰምና ወርቁን የሚያስማማበትና በተዓቅቦ የሚዋሐድበት ሐውል ተስምዕ /የምስክር ሐውልት/ ነው::

  አሁን ይህን ቅርስ ግንባታ ላይነን! ጽንሱ ሳይጨነግፍ ሕልሙም ሳይመክን እንደ ጀመርን ከጨረስነው ኢትዮጵያችን በሦስት የተገመደ ፈትል ትሆናለች:: አትበጠስምም:: ብሔር ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና ኢትዮጵያ በሚቀያየረው ሥርዓተ መንግሥት ውስጥ ተዋሕደውና ተጠባብቀው ይነጉዳሉ አይናናቁም አይነጣጠሉም፣ አይበጣጠሱም፣ አይገዳደሉም፣ . . . ይልቁንም እንደ አካል ብልቶች አንዳችን ያለሌላችን ከንቱ መሆናችንን ተረድተን ዚአከ ለዚአየ እየተባባልን እንተጋገዛለን:: ይህ ነው ትልቅ የነበርንበት ጥበብ ትልቅም የሚያደርገንም የስኬት ጎዳና::

  በሀገራችን ታሪክ ሳይጠናቀቅ በብዙ ሕዝብ የተጎበኘ ቅርስ ካለ የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ቀዳሚው ሳይሆን ይቀራል? ከዚህ የሚልቅ የእርቅና የመተሳሰብ ሐውልት የትአለ? ከዚህ ቀደም እየገደልን ስንፎክር ከገነባናቸውና ሞተውብን ስናዝን ካቆምናቸው ሐውልቶች በላይ የሚናገር የሚዘምር የሚደምቅ ግንባታ ላይ ነን:: አሁን እያነባን ሳይሆን እንደ ሀገራችን ገበሬ እየዘመርን የምንገነባው የጋራ ርእይ አለን:: ርእይ ይገነባል:: ርእይ ርእይን ይወልዳል:: የርእይ ግንባታ አይጠናቀቅም:: “ይህንን ጨርሰን ሌላ እንገነባለን” ግንባታው ይቀጥል:: በአንድነት እየፈተሉ የሚገምዱን በተአቅቦ የሚያዋሕዱን ብዙ ግንባታዎች ያስፈልጉናል:: መንገዱም፣ ባቡሩም፣ ሕንጻውም፣ ልማቱም ሁሉ ሃገር የሚገመድበት የሀር ፈትል ነው::

  የሀገራችን ልማትና ግንባታ ሁሌም አንድነት አብሮነት መተባበርና መዋሐድ፥ መፈቃቀድን፣ መተማመንን፣ መግባባትና መወያየትን ይጠይቃሉ:: ካለዚያ ውኃ በወንፊት እንደመያዝ ነፋስንም እንደመጎሰም ያለ ከንቱ ድካም ነው:: በዚህ መሠረት ላይ የሚገነባ አንድነት ከፉከራው ከሽለላውና ከቀረርቶው በላይ ያዋሕደናል:: በመፈክር የሚመጣ አንድነት ቢኖር ኖሮ ዛሬም ስለአንድነት መዋሐድና መተቃቀብ ባላወራን ነበር:: መንግሥትና መገናኛ ብዙኃን እገዛ አድራጊዎች እንጂ የተዋሕዶአችን ዋናመሠረት ሊሆኑ አይችሉም:: በማኅበራዊ መስተጋብር በምናደርገው ግንኙነት እየሰጠን የምንቀበላቸው ገንዘብ ያደረግናቸው ማንነቶች አሉ:: እነዚህናቸው መሠረቶቹ:: ከአመጋገባችን፣ ከአለባበሳችን፣ ከቋንቋችን፣ ከባሕላችን፣ ከእምነታችን የምንወራረሳቸው ያለመጠፋፋት በመጠባበቅ እንድንኖር የሚያግዙን የመሠረተ ኢትዮጵያዊነት ባሕርያችንን አምኖ መቀበልና መጠበቅ ይኖርብናል:: የሕዳሴውን ግድብ የመሠሉ ብዙ መተሳሰሪያ ውሎችም ያስፈልጉናል::
  ዛሬ ክትፎን የጉራጌ ብቻ የሚለው፥ በሃገር ልብስ መሽቀርቀርን የዚህና የዚያ አካባቢ ብቻ የሚያደርገው ማንነው? ይህንን ግን መንግሥት አልለገሰንም:: ሕዝብ ነው ፈጣሪው:: አሁንም ሕዝብ ለሕዝብ የምንቀባበላቸው የምንመጋገባቸው በርካታ እሴቶች አሉን:: ተዋሕደን የምንተቃቀብ ከሆነ ብቻ:: ያለነው ይህን ስኬት መፍጠር ከቻልን የመከባበር ዕጣናችን የሚያውዳቸው፣ የጋራ ልማት ሽቱአችን የሚጠራቸው ብዙ ሕዝቦች አሉና:: በመጠባበቅ እንዋሐድ!!!


  ReplyDelete
 29. In general i don't like the advertisement.b/c it have vast conversation to transform the idea.

  ReplyDelete
 30. I wish all the best & long live for you!!!

  ReplyDelete
 31. i m feel comfort with you comment, nice!! Daniel we respect you!

  ReplyDelete
 32. nice comment, i satisfied ,Abay is every thing for us but...

  ReplyDelete

 33. It is what we observe too!!

  God Bless you D/n Daniel!!

  ReplyDelete
 34. ዲ. ዳኒ እግዚአብሔር ይስጥህ የውስጤን ነው የገለፅክልን እየቀረቡ ያሉት ማስታወቂያዎች የህዳሴ ግድቡንም ግድቡን የሚገድበውን ህዝብም ፈፅሞ አይወክልም ምክንያቱም ኑሮ የኑሮ ውድነትን ተቋቁሞ ከአቅሙ በላይ ገንዘቡን አውጥቶ የህዳሴውን ግድብ የሚገድበውን ህዝብ ላይ ችግሩ ላይ፣አኗኗሩ ላይ፣ ባህሉ ላይ፣ የት/ት አሰጣጥ ላይ እና እና የመሳሰሉት ላይ እየቀለዱ ማስታወቅያ መስራት በጣም የሚያሳዝን ነው። ከዚህ በተጨማሪ ሁሌ የምሰማው የማስታወቅያቸው መጨረሻ<< አንዴ ጀምረናል እንጨርሰዋለን>> የሚለው አባባል ማስፈራሪያ ነው፣ ማስጠንቀቂያ ነው፣ ዛቻ ነው፣ ወኔ አነሳሽ ነው ወይስ ምንድን ነው? ምንም ልገባኝ ያልቻለ አባባል ነው። ወኔ አነሳሽ ነው እንዳል አቀራረባቸው ማስፈራሪያ ነው የሚመስለው ማስፈራሪያ ነው እንዳልል የሚቀርበው በኢትዮጵያ ቋንቋ ነው ብቻ ምንም የማይገባ ነው ምን ይባላል ማስታወቂያ የሚሰሩት ላይ እግዚአብሔር ማስተዋልን እና ማገናዘብን ይስጣቸው። ሌላው የማስታወቂያን በተመለከተ ከላይ አንድ አንባቢ የወሊድ መቆጣጠሪያ ማውታወቂያ ሰዓት ቢቀየር የሚል አስተያየት ሰጥቶ አንቢያለው እኔ የምለው 30 ጊዜ <> እያሉ የሚጨቀጭቁን የህዝብ ብዛት ይህን ያክል ስጋት ውስጥ ከቶናል እንዴ በዚህ ሚዲያ የህዝብ ብዛት ሃይላችን ነው ብሎ እየቀረበ በዚሁ ሚዲያ ሌላ የሚምታታ ነገር ብቻ .....

  ReplyDelete
 35. ዲ. ዳኒ የውስጣችን ስለተናገርክልን በጣም ነው የምናመሰግንህ። አምላክ ከዚህ በላይ የምተሰራበት ረጅም እድሜ ከጤና ጋር ይስጥህ፤ የያዝከውን አካሄድ አይቀይርብህ ማስተዋሉን ከጥበብ አቆራኝቶ ይስጥህ።
  ለህዳሴው ግድብ የማይመጥን ማስታወቂያ መሰራቱ ሁሉንም የከነከነ ነገር እንደሆነ አስተያየት ከሰጡ ሰዎች ማየት ችለናል። በዚህ ምስኪን ህዝብ ላይ በዓይኑ በጆሮው መቀለዳቸው ሊበቃ የሚገባ ጉዳይ ነው። ማስታወቂያው ለህዳሴው ግድብ ብቻ ሳይሆን ለህዝቡም የማይመጠ ነው ዲሽን የሰሩት ይመስገኑ እንጂ አማራጭ ባይኖር ችግር ነበር። ደግሞ ዲሽ ገጣሚዎች አሳብ ገብቶዋቸዋል አሉ ሊሰሩ ሲሄዱ ዕቃቸውን ደብቀው ነው የሚሄዱት፣ ጣራ ላይ ሆነው ፖሊስ ካዩ ዘለው ነው የሚወርዱት እየተሳቀቁ ነው የሚሰሩት የሚል ነገር facebook ላይ አንብቤ ነበር እውነት ከሆነ የምንሰራው ነገር ግራ ገብቶናል ማለት ነው።
  ሌላው ነገር ደግሞ የህዳሴው ግድብ ጉዳይ የሁላችን ጉዳይ ሆኖ ሳለ ግድቡን ለመገደብ ተብሎ እየተሰበሰበ ያለው ገንዘብ አሰባሰብ ምንም ሊገባኝ አልቻለም ህዝቡ በግል አቅሙ ይፍቀድ አይፍቀድ ሳይታወቅ በጅምላ ስበሰባ ላይ 2 ሰዎች ደግፈው ተናገሩ ተብሎ ሁሉም ሰው ላይ ይፀድቃል የግል ጉዳይ ሁኔታ አይገናዘብም ደግሞም አንድ ዙር ያልተሳተፈ እያለ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዙር እንዲሳተፍ ይደረጋል። ይህን ስል ተሳትፎውን እየተቃወምኩ አይደለም አንድ አይነት አሰራር መኖር አለበት የሚለውን ለማጠየቅ እና የህዝቡን ችግር ቀርቦ መጠየቅ አለበት ለማለት ነው። ለህዳሴው ግድብ የሚወጣ የቦንድ ሽያጭ ቁጣባ እንመሆኑ ማንም ሰው ገንዘቡን በመቆጠብ የህዳሴውን ግድብ መገደብ የሚጠላ ሰው ይኖራል ብዬ አላስብም አቅም የማነስ ጉዳይ የኑሮ ውድነት ጉዳይ አስጨንቆት ይመስለኛል ቅሬታው ደሞዙን ስንቱ ጋር ይበታትነው ቀለብ፣ የቤት ኪራይ፣ የቤት ቁጠባ፣የአባይ፣ ታክስ፣ በእያንዳንዱ የሚገዘው እቃ ላይ ቫት፣ ትራንስፖርት፣ በረከት የሌለው የስልክ ካርድ፣ የት/ቤት ክፍያ ወዘተ ምኑ ቅጡ ችግር ማውራት ይሆንብኛል እንጂ ተዘርዝሮ አያልቅም። አሁን አሁን ሳስበው የደሞዛችን ግማሽ ፐርሰንት የሚወስደው ታክስ እና ከእያንዳንዱ የምንጠቀምበት ነገር ላይ የሚቆረጠው ቫት ነው። በጣም የሚከብድ ነግር ነው ከአንድ ሰራተኛ የደሞዙ አንድ ሶስተኛ በላይ መቆረጥ የለበትም የሚለው ህግ እንዴት ነው የሚታየው? ከዚህ ተጨማሪ ደግሞ የቤት ኪራይ ራሱ የአንድ ሰው ደሞዝ ሆናል በደባል የምኖራው ኑሮ መቼ ነው የሚያበቃው መቼ ነው ራሳችንን ችለን የምንኖረው????

  ReplyDelete
 36. አመልን በቴሌቭዥን መግለጥ ካልሆነ ምን ሊሆን ምን ሊላ ሊሆን ነው

  ReplyDelete
 37. ድንቅ እይታ ነው ጌታ አእይንተ ልቡናህን ያብራልህ እናሰግናለን ፡፡

  ReplyDelete