ዶ/ር በርናንድ ብራድሊ አንደርሰን ልደቱ ቅድስት ካትሪን ደብር ጀማይካ ዉስጥ ነዉ፡፡ ወሩ መስከረም፣ ቀኑ 21፣ ዓመተ ምሕረቱ 1944፣ አቆጣጠሩ በአዉሮጳውያን፡፡ ቅድስት ካትሪን አጥቢያ ከእርሻዉ መካከል ነበር ያደገዉ፡፡ ዕድሜዉ ለትምህርት ሲደርስ ካሪቢያን ዉስጥ አንጋፋ ከሚባለዉና ከተከበረዉ ዎልማር የወንዶች ትምህርት ቤት ገባ፡፡ ወደ አሜሪካ ምድር የዘለቀው በ1960ዎቹ ሲሆን በዋሽንግተን ዲሲ ዝነኛዉ ሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ ማዕረግ የመጀመሪያዉን የባችለር ዲግሪ አገኘ፡፡ ከክፍሉ ቀዳሚ ሆኖም ወደ ሕክምናዉ የትምህርት ዘርፍ ተሻገረ፡፡ ቀን ቀን ትምህርቱን እየተከታተለ፤ ሌሊቱን እየሠራና ራሱን እየረዳ ትምህርቱን ቀጠለ፡፡
እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት ላይ በቀዶ ጥገና ሕክምና በከፍተኛ መዓርግ ተመረቀ፡፡ በትምህርትና በሥራ የበለጸገዉና ገና በለጋነቱ በትጋቱ የታወቀዉ፣ የቅርብ ጓደኞቹ በርኒ የሚሉት በርናንድ፤ የሕክምና ትምህርቱን ጨርሶ እንደተመረቀ ወደ ትዉልድ ሀገሩ ጃማይካ ተመልሶ በኪንግስተን የሕዝብ ሆስፒታል ማገልገል ጀመረ፡፡ ኪንግስተን የሕዝብ ሆስፒታል ነጻ ሕክምና የሚሰጥበት፣ ለተቸገሩና ዐቅም ለሌላቸዉ የሚለገስበት በመሆኑ ቀልቡን ገዛዉ፡፡ ወትሮም የሕክምና ሙያ ለአምሳያ ፍጡር የመድረስ መንፈስ አለዉና ከዶ/ር በርናንድ አንደርሰን ዉስጣዊ ተፈጥሮና ተልዕኮ ጋር ገጠመ፡፡ ዶ/ር አንደርሰን ሕሙማንን ከማከም በላይ ተተኪ ወጣቶችን ማስተማርና ማዘጋጀትን እንደ ቃል ኪዳኑ ነበር የሚያየዉ፡፡
እዚያም ጀማይካ ከሕክምናዉ ጎን ለጎን መምህር ሆኖ ብዙዎችን አሠልጥኗል፡፡ ዶ/ር በርናንድ የጃማይካ የሆስፒታል ተልዕኮዉን እንዳገባደደ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ተመለሰ፡፡ ነገር ግን ሀብትና ዕድሉ ወዳላቸዉ - ትርፍና ገንዘብ ወደሚጋበስባቸው ሆስፒታሎች ዓይኑን አላነሣም፡፡ እንዲያዉም የጤና ከለላና ሽፋን የሌላቸዉን ለመድረስ የሚችልበትን የቀድሞዉን ዲሲ ጄኔራል ሆስፒታል ነዉ የተቀላቀለዉ፡፡ ልዩ ተሰጥዖና ክህሎት ያለዉ ዶ/ር በርናንድ የሥራዉን ብቃትና የአመራር ችሎታዉን በዚያ ሆስፒታል ለማስመስከር ጊዜ አልወሰደበትም፡፡
በዲሲ ጄኔራል ሆስፒታል በሊቀ መንበርነትና የቀዶ ጥገና ዳይሬክተር በመሆን ሆስፒታሉ በሀገሪቱ ‹ዕዉቅና ያገኘ ሆስፒታል› ተብሎ እንዲጠቀስ ያደረገ ባለሙያ ነበር፡፡ ሲሠራ ውሎ ቢያድር ደከመኝ የማይል፣ ‹ሕሙማንን ማከም ተልዕኮዬ ነው› ብሎ የሚያምን ሰው ነበር፡፡ ዶ/ር በርናንድ አንደርሰን መኖሪያዉን በመሠረተባት የአሜሪካ ርዕሰ መዲና ዲሲ፣ በሮድ አይላንድ መንገድ ላይ የግል የሕክምና ክሊኒክ መሥርቶ በመደበኛዉ ሥራዉ ላይ አከለበት፡፡ ዶ/ር በርናንድ ክሊኒኩን ሀብት በበዛበት መንደር ሳይሆን የችግረኞቹን ቀየ ፈልጎና ይሁነኝ ብሎ ነበር ያቋቋመዉ፡፡ የመክፈል ዐቅም የሌላቸዉ ሕሙማንን በዚያ ክሊኒኩ በራሱ ወጪ ሕክምና መስጠቱን ዛሬ ድረስ በምስጋና የሚያነሡት ብዙዎች ናቸዉ፡፡
ዶ/ር አንደርሰን ስሙ ሳይጠቀስ፣ ለታይታም ሳይደርስ፣ ለተማረበት ትምህርት ቤት የአንድ መቶ ሺህ ዶላር ስጦታ የቸረ ለጋስ ሰው ነዉ፡፡ ይህ እንዲያውም ለአብነት ያህል ተነሣ እንጂ ዶ/ር አንደርሰን ‹ቀኝህ ሲሰጥ ግራህ አይመልከት› የሚለውን በተግባር ያሳየ፣ ልዩ ጸጋ የተጎናጸፈ ሰዉ ነበር፡፡ ዶክተር በርናንድ አንደርሰን ሕሙማንን መከባከብና ማከም፣ ችግራቸዉን ተቸግሮ፣ ቋንቋቸዉን ተናግሮ አምላክ የሰጠዉን ችሎታና በሰዉኛ የሚችለዉን ማድረግ የሕይወት ተልዕኮዉ ያደረገዉ ገና አንድ ፍሬ ወጣት እያለ ነዉ፡፡
አንድ ቀን ከሰዉ ዘር መፍለቂያዋ ከጥቁር ሕዝብ መኩሪያ ሀገር ኢትዮጵያ፤ እነ ማርክስ ጋርቬ “ወደ ራሳችን እንመለስ” ወዳሉባት ጥንታዊት ምድር ሄዶ የማገልገል ሕልም ነበረው፡፡ ያ ሕልሙና ራእዩ ይሳካ ዘንድ የኑሮ አጣማጁ ሲስተር እማዋይሽ ምክንያት ሆነችና ከምድረ አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ ሐሳብ ፀነሰ፡፡
ስለ ኢትዮጵያ ማንበብ፣ ስለ ኢትዮጵያ መመራመር ይወድ
ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ስም በተጠራበት ቦታ ሁሉ መገኘት አይሰለቸውም ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ይመሰጣል፡፡ ለሌሎች ወገኖቹ መንገርና
ስለ ኢትዮጵያ እንዲያውቁ መጎትጎት ይወዳል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ማጥናት፣ ቤተ ክርስቲያን መሄድና ከአባቶች ጋር መወያያት
ያስደስተው ነበር፡፡ የትዳር ጓደኛው ሲስተር እማዋይሽ ደግሞ ይኼ ደግ ሰው ኢትዮጵያ መጥቶ ይህንን የተከፈተ ልቡን ለሀገሯ ሰው
ቢያስረክበው፣ ደግነቱን ቢያርከፈክፈው ትመኝ ነበር፡፤ መመኘትም ብቻ ሳይሆን ትጎተጉትም ነበር፡፡
‹‹ብዙ ጊዜ ሀገሬ ኢትዮጵያ ገብተን እንድንሠራ እነግረው
ነበር፡፡ እርሱም በዚህ ላይ አስቦ እንደሚወስን ይገልጥልኛል፡፡ ከብዙ ጊዜ በኋላ አንድ ማለዳ ‹ላንቺ አስደናቂ ዜና አለኝ› አለኝ፡፡ በጉጉት ጠበቅኩ፡፡ ‹ላንቺ ስል
ወደ ኢትዮጵያ ልሄድ ወሰንኩ› አለኝ፡፡›› ትላለቺ ሲሰተር እማዋይሽ ያንን ቀን ስታስታውሰው፡፡
እርሱም አንድ አስቀደመና ታንዛኒያን፤ ኬኒያን ሄዶ ጎበኘ፡፡ አፍሪቃ የምትቃትትበትን፣ ጫንቃዋን የያዛት የትላንቱ የቅኝ ዛር እንዳልለቀቃት አይቶ አዘነ፡፡ አስከትሎም ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ፣ የድህነቱና የችግሩን መክፋት ተመለከተ፡፡ ነገር ግን አዘነ እንጂ ሸሽቶ አልተመለሰም፡፡ ከአዉሮፕላኑ ሲወርድ አየሩን ሲምገዉ - ሕልሙን አስታወሰዉ፡፡ የሕክምና ተቋማቱን ሲጎበኝ ሕሙማኑ ተኮልኩለዉ ቢመለከት ልቡ ተሰበረ፡፡ አዲስ አበባ ታላላቆቹ የግልና የመንግሥት የሕክምና ተቋማት ከእነርሱ ጋር እንዲሠራ ለመኑት፡፡ እርሱ ግን ወደ ገጠሩ መቅረብ ወደ ድኻው መጠጋት ይወድ
ነበርና ከተሜዉን ጎብኝቶ ወደ ገጠሮቹ ሊመለከት አዘገመ፡፡ የሐኪም እጅ ማየት ቀርቶ መልኩና ገጹ የናፈቃቸዉ ወገኖች አጋጠሙት፡፡ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠዉ መጥተዉ ከየሆስፒታሉ ደጃፍ ተኮልኩለዉ አምላካቸዉን እየተማጠኑ፤ ከዕለታት አንድ ቀን የሐኪም እጅ እንዲነካቸዉ ሳምንታትን የሚጠብቁ ምስኪኖች ልቡን ነኩት፡፡ መንፈሱን ሳቡት፡፡ ጎንደርም በፍቅሯ ነደፈቺዉ፡፡ ቅርልኝ አለቺዉ፡፡ ዕድሜዉ ከግማሽ ምእተ ዓመት በላይ ለሆነዉ ለጎንደር ሆስፒታልና የሕክምና ኮሌጅ እጁን ሰጠ፡፡ ዶ/ር በርናንድ አንደርሰን የዋሽንግተን ዲሲዉን ስመ ጥር ሐኪም የጎንደር እጆች አቀፉት፡፡ ፋታና ዕረፍት አላስፈለገውም፡፡ ወትሮም ዕረፍቱ፣ ቀድሞም ምቾቱ ለሕሙማን መድረስ - ለተቸገረ ዋስ መሆን ነበረ፡፡ የቀናት ስምና ቁጥር ለዶ/ር በርናንድ ዋጋ አልነበራቸዉም፡፡ ከአጸደ ሥጋ እስከተለየበት ጊዜ ድረስ ለእርሱ ቀናት ማለት የሥራና ሰዉን የማገልገያ ጊዜያት ናቸዉ፡፡
ዶ/ር በርናንድ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የቀዶ ጥገና ትምህርት ክፍልን የተቀላቀለው በ1997 ዓም ነበር፡፡ ዶ/ር በርናንድ በኮሌጁና በሆስፒታሉ በነበረዉ ቆይታ የቅድመ እና ድኅረ ምረቃ ተማሪዎችን ከማስተማር ጎን ለጎን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ሕሙማንን በማከም ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ በተለይም የቀዶ ጥገና ሕክምና ትምህርት ክፍል ሥርዓተ ትምህርት በየጊዜዉ እንዲሻሻል የነበረዉ የላቀ ሚና ምንጊዜም በትምህርት ክፍሉ አባላት ኅሊና የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ዶ/ር በርናንድ ዕዉቅ ቀዶ ጥገና ሕክምና ባለሞያ እንደመሆኑ ያለዉን እጅግ ሰፊ ዕዉቀት፣ ክህሎትና ልምድ ለተማሪዎቹና ለሞያው ሰዎች በማካፈል በርካቶች በሞያዉ የተካኑ እንዲሆኑ ያለማሰለስ ሠርቷል፡፡ በተለይም የሆስፒታሉ የቀዶ ሕክምና ባለሞያዎች ብቻቸዉን ሊሠሯቸዉ የሚቸገሩ የጉበት ካንሰር፣ የጣፊያ ካንሰር፣ የልብና የደም ሥር፣ የመሳሰሉትን ቀዶ ጥገናዎች በማከናወን ሌሎቹ ልምድ እንዲቀስሙ ማድረጉ ለሞያዉ መጎልበት ከነበረዉ ከፍተኛ አስተዋጽዖ በተጨማሪ ሕሙማኑ ፈዉስ እንዲያገኙ ያደረገዉ ተኪ የለሽ ተግባር ከፈጣሪ የተላከ እስከመባል ያደረሰው ነበር፡፡
በበርናንድ ዘንድ ሥራ ሲያልቅ እንጂ ሰዓት ሲያልቅ ማቆም
አይታሰብም፡፡ አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፡፡ እርሱና ተማሪዎቹ ከጠዋት እስከ ማታ ቀዶ ጥገና ሲያደርጉ ዋሉ፡፡ ምሳ አልነበራቸውም፡፡
ልክ ፀሐይዋ ማቆልቆል ስትጀምር ጨረሱ፡፡ ጨርሰው ልብሳቸውን ሲያወልቁ ግን አንድ የገጠር ሰው አንኳኩ፡፡ ‹ወረፋ እየጠበቅኩ ነበር››
አሉ ረዳት ሐኪሙን፡፡ ‹‹አባቴ አሁንማ መሸ ነገ ይምጡ›› አላቸው፡፡ አማራጭ አልነበራቸውምና ከዘራቸውን አንሥተው ጉዞ ጀመሩ፡፡
በርናርድ ድምጽ ሰምቶ ወጣ፡፡ ረዳቱን ጠየቀው፡፡ ረዳቱም ያደረገውን ነገረው፡፡ በርናርድ አዘነ፡፡ ‹‹እንዲህ ነበር ያስተማርኩህ››
አለው ረዳቱን፡፡ ‹‹በል ቶሎ ተከትለህ ጥራቸው›› ሲል አዘዘ፡፡ ሰውየው ተጠሩና እንደገና ልብስ ተለብሶ ቀዶ ጥገናው ቀጠለ፡፡
ይኼ ረዳት ሐኪም ዛሬ ታዋቂ የቀዶ ጥገና ሐኪም ሆኖ እንዲህ አለ ‹‹ያንን ትምህርት ስላስተማረኝ ተመርቄ ሰው የማይደርስበት ገጠር
ገባሁ››፡፡
በርናርድ በሀገራችን በብቸኝነት የጉበት ካንሰርና ተዛማጅ በሸታዎች ቀዶ ሕክምና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል እንዲሰጥ ያደረገ የሞያ ቁንጮ የነበረ ታላቅ ሰዉ መሆናኑን መመስከር አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን እጅግ በጣም ተገቢም ነዉ፡፡
“እስመ በትኅትና ይትረከብ ልዕልና” እንዲል የሕክምናዉ ሊቅ እኔን እዩኝ ሳይል፣ አለሁ ብሎ ሳይፎክር፣ ዕወቁኝ ብሎ ሳያዉጅ፣ ካልተወለደበት ወገን መካከል አገለገለ፡፡ እንደ ሀገሬዉ ባሕል እጅ ነሥቶ ፣ በባላገሩ ምርቃት ተመርቆ፣ ለድኾችና ረዳት ለሌላቸው ዋርካና መጠጊያ ሆነላቸዉ፡፡ በፍቱን እጁ ዳበሳቸዉ፡፡ ለወትሮው አመሰገኑት፡፡ በሄደበት በተገኘበት ቤት ያፈራዉን ሰንቀዉ እያመጡ እግዚአብሔር ይስጥልኝ አሉት፡፡ አንድ ጊዜ እንዲህ ሆነ፡፡ አንዲት ምስኪን እናት
መጡ፡፡ እርሱም አከማቸው፡፡ ድህነታቸው ማግኘት ያለባቸውን ሕክምና አልከለከላቸውም፡፡ ከቅኖች ጋር አምላክ ይሠራልና ሴትዮዋ በበርናርድ
ታክመው ዳኑ፡፡ ከቀናት በኋላ ሊያመሰግኑት ወደ ሆስፒታሉ ተመለሱ፡፡ መርቀው መርቀው ጨረሱና ከጉንፋቸው እጃቸውን ሰድደው አንድ
ነገር አወጡ፡፡ ዐሥር ብር፡፡ ‹‹ሌላ ምንም የለኝም፤ በዚህ ግን ምሳ ብላበት›› ብለው ሰጡት፡፡ ሰው አክባሪው በርናርድ ዐሥር
ብሩን አመስግኖ ተቀበለና የዐሥር ብር ምግብ ወደሚሸጥበት ቦታ ሄዶ ምሳ በላላቸው፡፡
ለዚህ ነበር ድፍን ጎንደሬ እያለቀሰ የሸኘው፡፡ አንድ አልቃሽ ያወረደችው ሙሾ የጎንደርን
ስሜት ሳይገልጠው አይቀርም
የማን ዘመድ ሞተ አትበለኝ ሀገሬ
ጎንደር ሰው ሞቷታል እናላቅሳት
ዛሬ
በርናርድን የጎንደር ሰው የሚያውቀው የተሸከመ ሰው ሲያይ
ሸክሙን ተቀብሎ፣ በመኪናው ጭኖ ቤቱ ሲያደርስ፤ የተጎዳ ሰው ሲያይ ከመኪናው ወርዶ ችግሩን ሲጋራ፤ ወደ ሕክምና ያልመጣ ሰው መንገድ
ላይ ሲያገኝ አባብሎ አምጥቶ ሲያክም ነው፡፡ ከየሕክምናዉ ተቋም ተኮልኩለዉ የሚያያቸዉ ሕሙማን ቢያሳዝኑት - መጠለያ ለማሠራት ወጠነ፡፡ ሀገር አቆራርጠዉ ለሕክምና የሚመጡትን ለመታደግም ሆስፒታል አስገነባ፡፡ በአዞዞ በዶ/ር በርናንድና በባለቤቱ የተገነባዉ ይህ ሆስፒታልም ለአንድ መቶ ሕሙማን ማረፊያ መኝታ እንዲኖረዉ ተደርጎ የተገነባ ነዉ፡፡ ምንም እንኳን የሆስፒታሉን ሥራ ጀምሮ ለማየት ዶ/ር በርናንድ በሥጋ ቢለይም ስሙን የተከለበትን ራእይ ትውልዱ ያየዋል፡፡ አደራዉንም ይሰማዋል፡፡
ዶ/ር በርናንድ አንደርሰን የሕክምና ሊቅ ብቻ አልነበረም፡፡ ዘርፈ ብዙ ተሰጥዖም ነበረዉ፡፡ በሥነ ሕክምናዉ በጣፊያና በጉበት ሕመም ለሚሰቃዩ በልዩ ጥበብ ብልቶቹ የሚሠሩበትን ዘዴ በምስል ነድፎ የባለቤትነት (ፓተንት) ያለዉ ባለሞያ ነበር፡፡ ዛሬ መዝገብ የያዛቸዉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የባለቤትነት ዕዉቅና የያዘባቸዉ ሁለት መሣሪያዎች አሉት፡፡ የግጥም ስብስብ መጽሐፉ ርዕስ Limbic glimpses
ይሰኛል፡፡ ዲዛይን በማድረግም ልዩ ችሎታ ነበረዉ፡፡ ዛሬ በአዞዞ የቆመዉ ሆስፒታሉም የ ዶ/ር አንደርሰን ዉጥን ነዉ፡፡ አንዲትም ዕለት ቸል ብሎ ችግርን ለማለፍ የማይፈቅድ፣ ፊት ለፊት ገጥሞ ተፈጥሮን ለመግራት ሲሞክርና ሲለፋ የቆየ፤ ሙሉ ዕድሜዉን በጥድፊያ ሲሠራበት የኖረ ታላቅ ሰብእና ነበረው፡፡
ዶ/ር አንደርሰን ኢትዮጵያን ዐዉቋት ነዉ የወደዳት፡፡ መንፈሳዊ ሕይወቱንም ከጥንታዊዉ እምነቷ ጋር አዋሕዶት ነበር፡፡ ጊዜ ሲያገኝ ወደ ቁስቋም ማርያምና
ወደ ደብረ ብርሃን ሥላሴ መሄድ ያስደስተው ነበር፡፡ የክርስትና ስሙ ገብረ ሥላሴ ሲሆን የንስሐ አባትም ነበረው፡፡ ደግሞ እንደ
ቅዳሴ የሚወደው ነገር አልነበረም፡፡ ገና በሕይወት እያለ በዚያ በተራራ ላይ እቴጌ ምንትዋብ በተከሏት በደብረ ፀሐይ ቁስቋም ማርያም
ለመቀበር ምኞቱን ገልጦ ነበር፡፡ ‹ዛቲ ይእቲ ምዕራፍየ ለዓለም› ብሎ፡፡ በሕመም ተይዞ በአሜሪካን ሀገር እያለ፣ ከዚህ ዓለም ሊሰናበት
ሲደርስ ባለቤቱን ‹‹ወጭዉ የማይበዛብሺ፣ አንቺንም የማያደክምሽ ከሆነ ኢትዮጵያ፣ ጎንደር ቁስቋም ብቀበር እወድ ነበር›› ብሎ ተናገረ፡፡
ይህንንም ብሎ ታኅሣሥ 23 ቀን 2007 ዓም ሁለት ልጆቹን ትቶ ዐረፈ፡፡
ሲሰተር እማዋይሽና ወዳጅ ዘመዶቹም ቃሉን አክብረው አስከሬኑን ወደ ጎንደር አመጡት፡፡ የዐርባ አራቱ
ታቦት ካህናት አንድ ሆነው ወጥተው፣ ድፍን የጎንደር ሕዝብ ከአድያም ሰገድ ኢያሱ ወዲህ አልቅሶት በማያውቅ ልቅሶ ወደ ቁስቋም ሸኘው፡፡
ታሪኩ፣ ሥራዉና ውለታዉ ግን የብዙዎች ቤት ውስጥ ገብቷልና ይኖራል፡፡
‹ለዓለም ይሄሉ› እንዲል፡፡
Egziabher amlak nefsun ke degagochu Abatochachin Abrham, Yishak ena Yaekob Ategeb yanurlin
ReplyDeleteበበርናንድ ዘንድ ሥራ ሲያልቅ እንጂ ሰዓት ሲያልቅ ማቆም አይታሰብም፡፡
ReplyDeleteበርናርድን የጎንደር ሰው የሚያውቀው የተሸከመ ሰው ሲያይ ሸክሙን ተቀብሎ፣ በመኪናው ጭኖ ቤቱ ሲያደርስ፤ የተጎዳ ሰው ሲያይ ከመኪናው ወርዶ ችግሩን ሲጋራ፤ ወደ ሕክምና ያልመጣ ሰው መንገድ ላይ ሲያገኝ አባብሎ አምጥቶ ሲያክም ነው፡፡
ዲ/ን ዳንኤል እግዚአብኤር ይስጥልኝ፡፡……. አብዝቶ
እግዚአብሔር ለበዓል ያልሰገዱ ሰባት ሺዎች ዛሬም አሉት፤፤ የዶክተርን ነፍስ በገነት ያሳርፍልን፤፤
ReplyDeleteዳንየ ፣ በዋሽንግተን ዲሲ 16 ኛው መንገድ በሜገኝ ምካኢል ቤተክርስቲያን ለዜህ የአገራችን ብርቅየ ፣ ግሩም ሰው ብዙ ሕዝብ በተገኙበት ሥርዓተ ፍትሐት ሴደረግ እኔም የ ድርሻየን ፣ አልቅሸ ሸኝቸ ነበር ።ነገር ግን እንዳንተ ያለ ትልቅ አዋቂ ሰው ፣ትልቅ ሴኖር ፣ሴሰራ፣ሴያስተምር፣ወዘተ ነው እንጂ ያሰበውን ሳይጨርስ ፣የጀመረውን ሳይቋጭ ፣ጣል እርግፍ አርጐ ሴያልፍ ፣ለአገርና ፣ለወገን ፣ጉዳት መሆኑ ይረዳል ።ለዜህም ነው ለአንተው ፣ ለወንድሜ ዲ/ዳንኤል ክብረት ብዕር ፣ ምሰጋናየ ይድረስ ማለት የፈለኩ ። ምንም እንኳን ሐዘኑ ፣የኢትዩጵያ ፣ሕዝብ ብሎም የሞላው ጎንደር ቤሆንም ፣ ለባለቤቱ ፣ለምታኮራዋ እህታችን ሴስተር ፣እማዋይሽ ገሪማ በድጋሚ መጽናናቱን እንዲሰጣት ፤ ሁላችንም በጾሎት እንድናስባት ፣በእግዜአብሔር ስም አደራ እላለሁ ።
ReplyDeleteዳንኤል! ዶ/ር አንደርሰንን በሚገባ ስላስተዋወቅኸው ምስጋናዬ የላቀ ነው፡፡ ዶ/ር አንደርሰንን በቤተሰባዊ ዝምድና ለአጭር ጊዜም ቢሆን የማወቅ ዕድሉ ስለነበረኝ ቀደም ሲል ስለእርሱ ከሰማሁት፣ በጥቂቷ የዕውቅና ጊዜዬ ከተረዳሁትና በዓይኔም ካየሁት ተነስቼ ታላቅ ሰውነቱን ለመመስከር እችላለሁ፡፡ አንተ የገለጽካቸውን መልካም አስተዋጽኦዎቹንና ድንቅ ባሕሪውን ሳነብ ግን ብዙ ሳላውቀው በማለፉ በእጅጉ ቆጨኝ፡፡ እንደዚህ ያለ የእውነት “ሰው” የሆነ ሰው ሲያልፍ ሐዘንና ቁጭቱ ከባድ ነው፡፡ የበለጠ የሚቆጨው ግን እኛ፣ “ባለ-አገሮቹ”፣ የዶ/ር አንደርሰንን፣ የካርልሐይንዝ ቦምን፣ የዶ/ር ካትሪን ሐምሊንን፣ የፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስትና ቤተሰቦቻቸውን፣ … ያህል ኢትዮጵያዊነት አጥተን ለአገር ተቆርቋሪነታችን ድራሹ ጠፍቶ ለአገራችን ባዳ መሆናችን ነው፡፡ ልቦናችን ወደ ምንጫችን የሚመለስበት ቀን አብዝቶ ይናፍቀኛል፡፡
ReplyDeleteየዚህን መልካም ሰው ነፍስ ልኡል እግዚአብሔር ከቅዱሳኑ ጋር ይደምረው! አንተንም ይህን ለነገርከን እግዚአብሔር አምላክ ቃለ ሕይወት ያሰማህ እድሜ ከጤና ጋር ይስጥህ!!! ...... በዚያን ግዜ አንባቢ ሁሉ ያስተውል.......
ReplyDeleteThank you! ደግሞ እንደ ቅዳሴ የሚወደው ነገር አልነበረም፡፡
ReplyDeleteDani Endet Atafteh Tsafikew... Egziabher Yistih
ReplyDeleteዶ/ር በርናንድ ነፍስ ይማር ብለናል፠ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ይሰጥልን፠ጌታ ሆይ አንተ ያሰተማርከንን ስራ ሰርተው አልፈዋል ነፍሳቸውን በገነት አኑርልን፠ ተተኪ ዶክተሮች እግዚአብሔር የሰጣቹን ጥበብ ተጠቀሙበት፠ጥሩ አሰተማሪ ሆነው አልፈዋል፠ኢትዬጵያ መቼም አትረሳዎትም! የምንችለውን እናድርግ !አድናቂቂዎች ብቻ አንሁን!ሊደረግላት የሚገባት አገር ነው ያለን፠ሁሉንም የምትወድ ሰሟ የሚያምር ! ኢትዬጵያ!
ReplyDelete፠ዲያቆን ዳኒ መድሃኒያለም ይባርክህ አሜን!!!
Dani, what a nice selfless humanity is this?
ReplyDeleteኢትዮጲያዊነቴን በሃሳብ ብቻ ጨረስኩት፡፡ እባክህ አምላኬ ከእምነት ጋር የተግባር ሰው አድርገኝ፡፡
ReplyDeleteVery impressive story. He was really human. Thank you Dn . Daniel.
ReplyDeleteኢትዮጲያዊነቴን በሃሳብ ብቻ ጨረስኩት፡፡ እባክህ አምላኬ ከእምነት ጋር የተግባር ሰው አድርገኝ፡፡
ReplyDeleteGreat! this is a MAN from whom our country should take a lesson from. Nowadays, Ethiopians are not allowed to work in other Regions of their OWN COUNTRY.
ReplyDeleteዲ/ን እንደምን የታደለ ሰው አስተዋወከን። ማመንና መታመንን ፈጽሞታል። ቤተሰቡን ይባርክልን።
ReplyDeleteየሕክምናዉ ሊቅ እኔን እዩኝ ሳይል፣ አለሁ ብሎ ሳይፎክር፣ ዕወቁኝ ብሎ ሳያዉጅ፣ ካልተወለደበት ወገን መካከል አገለገለ፡፡
ReplyDeleteGod bless you Diakon!!!
ያለፈው ኢትዮጵያዊ ትውልድ፡ ሰርቶት ባለፈው ታሪክ፡ የሚኮሩ የተለያዩ አገራት ዚጎችን ፡ በየአጋጣሚው በተለያዩ የዓለም አገራት ማግኘት የተለመደ ነው፡፡
ReplyDeleteእንደ ዶ/ር በርናንድ በታሪኩ፡ እንደማግኔት ልባቸው የተሳበው፡ በስው ዘርነታቸው ብቻ አምነው፥ በሃገራችን ኖረው ፡ ሰብአዊ ታሪክ ሰርተው ያልፋሉ።
ይህን ተአምረኛ ትውልድ የተካነው፡ የዛሬዎቹ ጎሳ ቆጣሪዎች፡ ለነገው ትውልድ፡ ማፈሪያ መሆናችን፡ እንዴት አሳዛኝ ነው!
የሀገራችንን ገፅታ በበጎ መልኩ ለመለወጥ ስንት "በርናንድ" ያስፈልገን ይሆን?
ReplyDeleteእጅግ በጣም የሚገርሙ እና የሚያሳዙኑ ዶክተር ናቸው። ፈጣሪ ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልን። ቸሩ መድሃኒዓለም ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጆቻቸው መጽናናትን እንዲሁም ለጎንደር ሕዝብ ደግሞ ምትክ ሊሆን የሚችል ሐኪም ይስጥልን።
ReplyDeleteYagerachin hakimoch kezih talak sew memar alebachew
ReplyDeleteEsm betehtena yetrekeb lielena!abetu deg sew atatfaben!
ReplyDeletewendemache betam enamsegenalen edeme ketena yestelen.
I am a G12 student.I want to be a doctor and this is the type of doctor I want to be.Thank u dani.this is really inspirational I will copy this short biographie and it will be my courage when I become weak.THANK U AGAIN!!!!
ReplyDeleteየዚህን መልካም ሰው ነፍስ ልኡል እግዚአብሔር ከቅዱሳኑ ጋር ይደምረው! Daniyiee አንተንም ይህን ለነገርከን እግዚአብሔር አምላክ ቃለ ሕይወት ያሰማህ እድሜ ከጤና ጋር ይስጥህ!
ReplyDeleteነፍስ ይማር አንተም ይህን የመሰለ ታላቅ ሰው ስላስተዋከን የቅዱሳን አምላክ ይጠብህ
ReplyDeleteነፍስ ይማር አንተም ይህን ታላቅ ሰው ስላስተዋወከን የቅድሳን አምላክ ይጠብቅህ
ReplyDeleteአንድ ቀን ከሰው ዘር መፍለቂያዋ ሀገር ሄዶ የማገልገል ህልም ነበረው ብለሃል፡፡ ቤተክርስቲያን ያስተማረችን የሰው ዘር የፈለቀው ከእግዚአብሔር እጅ በኤድን ገነት መሆኑን ነው እንጂ ከሉሲ መሆኑን አይደለም፡፡ እንዲህ አይነት አገላለጽ ከቤተክርስቲያን አባቶችና ከሰባክያነ ወንጌል ስሰማ ያሳዝነኛል፡፡ እባካችሁ ነገር አሳመርን እያላችሁ ከወንጌል የሚጋጭ እምነት አትርጩብን፡፡ ዶክተሩን ግን ነፍሱን ይማርልን፡፡ አሜን፡፡
ReplyDeleteYemigerm new!!! Fetari bizu bernandochin yadilen. I wish for Dr. Paradise place.
Deletethank you for your link
ReplyDeleteNefs yimar.Talak sira yesera,besiraw behuletum alem Hiyaw new.Thank u for sharing this valuable history of good servant of people.
ReplyDeleteAmazing and inspiring story. Thank you for sharing this
ReplyDeleteThis is exactly the definition of a true and real man . We need real physicians or Doctors. Be on the right side of GOD D/r Bernand !!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!
ReplyDeleteThis is exactly the definition of a true and real man. W e need real physicians or Doctors. Be on the right side of GOD D/r Bernand!!!!!!!!!!!!
ReplyDeleteእግዚ አብሔር ነፍሡን በገነት ያኑረው አሜን
ReplyDeleteእግዚ አብሔር ነፍሡን በገነት ያኑረው አሜን
ReplyDeleteቃለ ሕይወት ያሰማህ።
ReplyDelete