Wednesday, February 4, 2015

ወንድሟመቼም ከጓደኞቹ ጋር ምሳ እንደመብላት የሚያስደስተው ነገር የለም፡፡ ከየትም ቦታ ተሯሩጦ ወደ ቀጠሮው ቦታ ይመጣል፡፡ ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ ያቺ ያረጀች መኪናው ድንገት እየቆመች ብታስቸግረውም ቀጠሮውን ግን አይሰርዝም፡፡ አሁን የመኪና ማቆሚያ እየፈለገ ነው፡፡ አዲስ አበቤ ሁሉ ለሦስት ቀን ነነዌ ቅበላ ሀገሪቱን በቀንድ ከብት ሀብት አንደኛ ከመሆን ገፍትሮ ሊጥላት በየ ሥጋ ቤቱ ተጠቅጥቋል፡፡ መንገዱም አጥንት እንዳየ ጉንዳን በሚተራመሱ መኪኖች ተሞልቷል፡፡ እዚህ ነው ጓደኞቹ የቀጠሩት፡፡
በዋናው መንገድ በኩል ለመግባት ሞከረና ያለ ማስጠንቀቂያ የሚቆፈረው መንገድ ተዘግቶ አገኘው፡፡ እለፉም አትለፉም የማይል የአፈር ክምር መንገዱን ዘግቶታል፡፡ በታችኛው በኩል ዞረና መጣ፡፡ እንደ ደብረ ዕንቁ አንድ መውጫ ብቻ የቀረለት መንደር በግራ በቀኙ በቆሙት መኪኖች ተጣብቦ ጉርሻ እንዳነቀው ጉሮሮ ውጭ ነፍስ ግቢ ነፍስ ይላል፡፡ በወዲህና በወዲያ ምንም መቆሚያ አልተረፈም፡፡ 

‹በተወደደ ቁጥር ደንበኞቹን የሚጨመር ነገር ቢኖር ሥጋ ቤት ነው› ይላሉ አንድ በላተኛ የታጠቡትን እጃቸውን እያራገፉ ከሥጋ ቤት ወጥተው፡፡ ‹በዚህ የሥጋ ፍቅራችን የጾም ወቅት ባይኖር ምን ይውጠን ነበር› አሉ አብረዋቸው የወጡት ሰው፡፡ እርሱ ግን መሐል መንገድ ቆሞ ማቆሚያ ፍለጋ ያማትራል፡፡ ከኋላው ማለፊያ ያጡት መኪኖች እንደ ገጠር ሠርግ ጡሩንባቸውን ያንጣጡታል፡፡ ከፊት ለፊት ገበያቸው የቀረባቸው መኪና ጠባቂዎች ‹እባክህ እለፍ› ይሉታል፡፡ እርሱ ግን ‹አልበር እንዳሞራ ሰው አርጎ ፈጥሮኛል› እያለ ክንዱን መስኮት ላይ አስደግፎ ቆሟል፡፡
በመሐል ስልኩ ተደወለ፡፡ እኅቱ ነበረች፡፡ ‹‹ምጡ ሊጀምረኝ ነው መሰል ወገቤን እያመመኝ ነው› አለቺው፡፡ ‹‹አይዞሽ፣ በሦስተኛሽ ትጨነቂያለሽ እንዴ፤ ከፈለግሺኝ ደውዪልኝ›› አላትና ዘጋው፡፡ የእኅቱ ባለቤት ለሥራ ወደ ቻይና ሄዷል፡፡ አደራው ያለው እርሱ ጋ ነው፡፡ የጓደኞቹ ነገር ባይሆንበት አብሯት ቢሆን ነበር የሚመርጠው፡፡
አንድ የመኪና ጠባቂ መጣና ‹ቦታ ላሳይህ› አለው፡፡ ተከትሎት ነዳ፡፡ ወደ ውስጥ መግቢያ መንገድ ነው፡፡ ‹‹እዚህ ጋር አቁመው የሚገባ መኪና የለም› አለው፡፡ ስለሰለቸው ብቻ ወስዶ መንገዱን ዘጋና ገተረው፡፡ አንዳንድ ልጆች ‹እ ፍሬንድ ምነው መንገዱን ከረቸምሺውኮ› አሉት፡፡  ዝም ብሏቸው በሩን ቆልፎ ወደ ሥጋ ቤቱ ተጣደፈ፡፡ ማቆሙን አንጂ አቋቋሙን አላየውም፡፡ ከቀጠሮው ሠላሳ ደቂቃ አሳልፏል፡፡ ሥጋ ቤቱ ከጠጅ ቤት ጫጫታን ተውሶ ድብልቅልቁ ወጥቷል፡፡ ማን ምን እንደሚል አይሰማም፡፡ የሚሰማው የቢላዋ ፍጭት ብቻ ነው፡፡ ሁሉም ይጮኻል፣ ሁሉም ይሰማል፡፡ ሁሉም ግን አያዳምጥም፡፡  
በዓይኑ እያማተረ ፈለጋቸው፡፡ እንደ ሞባይል ሠሪ ሁሉም አጎንብሰው ያስነኩታል፡፡ በቅርጻቸው እንጂ በመልካቸው ለመለየት አልቻለም ነበር፡፡የመጀመሪያው ትእዛዝ ተጋምሶ ደረሰ፡፡ ከአራት አቅጣጫ በመጣለት ጉርሻም ከቡድኑ ተቀላቀለ፡፡
                            ***                    ****                    ***             ***            ***
እኅቱ ምጧ እየተፋፋመ መጣ፡፡ ምን እንደሆነ እርሷም አታውቀውም እንጂ ይኼኛውን እርግዝና ቀድሞም ፈርታዋለች፡፡ እንዳመማት ነው የከረመው፡፡ የበካር እርግዝና ይመስላል፡፡ ለወንድሟ ደወለችለት፡፡ ስልኩ ይጠራል፣ ግን አይነሣም፡፡ እየደጋገመች ደወለች፡፡ ለውጥ አልነበረውም፡፡ ሌላ መኪና ያለው ሰው ደግሞ አታውቅም፡፡ የመጨረሻ አማራጯ ይከታተላት የነበረው ሐኪም የነገራትን የስልክ ቁጥር መጠቀም ነበር፡፡ ወደ ሆስፒታሉ ደወለች፡፡ ስልኩን ያነሣው ሰው አምቡላንሱን በአስቸኳይ እንደሚልክላት ቃል ገብቶ አድራሻዋን ወሰደ፡፡
ወገቧን እያመማት፣ ድካምም እየተሰማት አምቡላንሱን መጠበቅ ጀመረች፡፡ ዐሥር፣ ዐሥራ አምስት፣ ሃያ፣ ሠላሳ፣ ዐርባ ደቂቃዎች አለፉ፡፡ መልሳ ወደ አምቡላንሱ ደወለች፡፡ ያነሳው ሰውዬ ‹‹ይቅርታ አንድ ሰው መኪና አቁሞ መንገዱን ስለዘጋብን ነው፣ ትንሽ ታገሽን› አላት፡፡ ምን አማራጭ አለኝ ብላ ጠበቀች፡፡ ሕመሟ ሲበረታ ታክሲ እንዲጠሩላት ጎረቤቷን አስጠራቻቸው፡፡ ቤታቸው ከመንገድ ገባ ያለ በመሆኑ ዋናው መንገድ ድረስ በእግር መጓዝ ነበረባቸው፡፡
እርሳቸው ወደ ዋናው መንገድ ሲያዘግሙ እርሷም ወደ ድካምና ሽንፈት እያዘገመች ነበረች፡፡ መንገዱ ዳር ሲወጡ ሁሉም ባለ ታክሲዎች ለቅበላው ሥጋ ቤት ከትመዋል መሰል ትንንሾ ታክሲዎች የሉም፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ በቅበላ፣ በገብርኤል፣ በአርሴናልና ማንቸስተር የጨዋታ ቀናት ታክሲ ማግኘት ሕልም ነው፡፡ ትልልቆቹም እየሞሉ በኩራት ያልፋሉ፡፡ መቼም ትልልቅ ታክሲዎች ባዷቸውን ሲሆኑ የሚደርስባቸውን የመጠበቅ መከራ የሚበቀሉት ሲሞሉ  በኩራት ገልምጠው በማለፍ ይመስላል፡፡ እንደ መቆም ይሉና እንቁልልጭ ብለው እንደ መሸምጠጥ ይላሉ፡፡  
ጎረቤቷ ሲዘገዩባት ያለ የሌለ ኃይሏን አስተባብራ ወደ ሆስፒታሉ ደወለች፡፡ ስልኩን ያነሣው ሰውዬ ‹‹እባክሽ አንድ ምን እንደምለው የማላውቅ ሰው መንገድ ዘግቶ ጠፍቷል፡፡ እዚያ ሥጋ ቤት ሳይገባ አልቀረም፡፡ ሰው ልከን በታርጋ ቁጥሩ ብንፈልገውም ጫጫታው ነው መሰል ሊሰማን አልቻለም፡፡ በወዲያ በኩል ያለው መንገድ ደግሞ ተቆፍሯል፡፡ ከቻልሽ ሌላ መኪና ይዘሽ ነዪ›› አላት፡፡ ተስፋ ወደ መቁረጥ ልትገባ ስትል ጎረቤቷ ከቅበላ የተረፈች ታክሲ ይዘው መጡና ከቤት ሠራተኛዋና ከሹፌሩ ጋር አፋፍሰው ይዘዋት በረሩ፡፡
የሥጋ ቤቱ መንገድ እንደተጨናነቀ ነው፡፡ ቅበላውን ተቀብለው፣ ጾሙንም በሙዳ ሥጋ ይዘው የሚወጡት ተመጋቢዎች አልፋለሁ አታልፍም እየተነታረኩ ነው፡፡ የታክሲው ሾፌር ‹‹ኧረ እባካችሁ ወላድ ይዘን ነው›› እያለ በመስኮቱ በኩል ይለምናል፡፡ አንዳንዶቹ ጩኸቱን በመከራ ሰምተው ለመጠጋት ይሞክራሉ፡፡ ይገጩናል ብለው የፈሩ ሌሎች ደግሞ በጡሩንባ ድምጽ ያባርሯቸዋል፡፡ የሞተ አህያ ለመብላት አሞሮች የሚያሳዩት ትርዒት ይመስል ነበር፡፡
እንደምንም ብሎ የጎንና ጎን መመልከቻ መስተዋቱን እያጠፈ፣ በዔሊ ፍጥነት የውስጥ መንገዱን አለፈውና ወደ ሆስፒታሉ ለመግባት ወደ ግራ ሲታጠፍ መንገዱ ተዘግቷል፡፡ ከወዲያ ማዶ አንድ አምቡላንስ ቆሟል፡፡ ነጭ ገዋን የለበሱ የሆስፒታሉ ሰዎች ወዲያና ወዲህ ይራወጣሉ፡፡ ፖሊሶች መኪና አቋሚውን ቢያገኙት ሊቦጫጭቁት በሚደርስ ንዴት ውስጥ ናቸው፡፡ የትራፊክ ፖሊሶች ታርጋ ይፈታሉ፡፡ የታክሲው ሾፌር ደግሞ ‹አሳልፉኝ› እያለ ይጮኻል፡፡
አንድ አልፎ ሂያጅ ሽማግሌ ግን ግራ ቀኙን ሲያዳምጡና ሲቃኙ ቆዩና ‹‹ሰው ማለትኮ ለሚፈጽመው ነገር አንዳች ምክንያት ያለው፣ የሚሠራው ነገር ሊያስከትል የሚችለውን ነገር ቀድሞ አስቦ የሚሠራ ፍጡር ማለት ነው፡፡ የሚያደርጉት ነገር ምን ሊያስከትል እንደሚችል የማያስቡ፣ በዚህም የተነሣ ኃላፊነት ሊሰማቸው የማይችል እንስሳት ብቻ ናቸው፡፡ እስካሁን እንደ ሰው የሚኖሩና የሚያስቡ እንስሳት አልተገኙም፤ እንደ እንስሳት የሚኖሩና የሚያስቡ ሰዎች ግን በብዛት አሉ፡፡ ኃላፊነት ሁለት ዓይነት ነው፤ የሹመት ኃላፊነት አለ፡፡ ለሥራና ለአገልግሎት የሚሰጥ፡፡ ዋናው ግን እርሱ አይደለም፡፡ ዋናው ሁለተኛው ነው፡፡ ሰው በመሆን ምክንያት ብቻ የሚመጣ ኃላፊነት፡፡ ሰው ስለሆንክ ብቻ ነገሮችን ሁሉ በኃላፊነት ስሜት እንድታከናውን የሚያስገድድህ የሰውነት ኃላፊነት አለብህ፡፡አንድን ፈረስ ከነ ጋሪው ብትለቅቀው ልክ እንደዚህ ሰውዬ አንዱ ቦታ ላይ ይቆማል፡፡ የቆመበት ምክንያት ሣር ስላገኘ ብቻ ነው፣ ወይም ጥላ፡፡ አለቀ በቃ፡፡ በመቆሙ የሚያመጣውን ነገር እንዲያስብ አይጠበቅበትም፡፡ ኃላፊነት የማይሰማቸው ሰዎችም እንደዚህ ፈረስ ናቸው፡፡›› አሉና እየተራገሙ ሄዱ፡፡
ሁለት ነርሶች መጡና እርጉዟን ተሸከሟት፡፡ ግርግሩን ሲያደምቅ የነበረው ሁሉ ከፊት ከኋላ ከቀኝ ከግራ ደግፎ መንገድ ዘግቶ የቆመውን መኪና አሻገራት፡፡ አምቡላንሱ እንደምንም ፊቱን መልሶ ይዟት ወደ ሆስፒታሉ ሸመጠጠ፡፡
መንገድ ዘግቶ በቆመው መኪና ዙሪያ ፖሊሱ፣ መኪና ጠባቂው፣ በልቶ ተመላሹ፣ ወሬ ጠምቶት የቆመው አላፊ አግዳሚ ወጉን ጮክ እያለ ይሰልቃል፡፤ አንዳንዱ ያወግዛል፤ አንዳንዱ ባለ መኪናው ሲመጣ ሊፈጠር የሚችለውን እየገመተ ይተነትናል፤ሌላው ደግሞ መወሰድ ስላለበት ርምጃ ሐሳብ ይሰጣል፤የባሰበትም ‹አይ አበሻ› እያለ ራሱን ጨምሮ ይረግማል፡፡ በዚህ መሐል የታጠቡበትን እጅ እያፍተለተሉ አንድ አምስት ጎልማሶች ጮክ ብለው እያወሩ መጡ፡፡ አንዱ ከመካከላቸው ነጠል ብሎ ሰዎቹ ወደተሰበሰቡበት አቀና፡፡ የተሰበሰቡት የርሱን መኪና ከበው መሆኑን፣ ፖሊሶቹ መቁነጥነጣቸውን ሲያይ አንዳች ክፉ ነገር ሸተተው፡፡
‹‹አንተ ነህ ባለ መኪናው›› አለ የትራፊክ ፖሊሱ፡፡
‹‹አዎ›› ሲለው ምን ሊመጣ ይሆን ብሎ እያሰበ ነበር፡፡
‹‹መንጃ ፈቃድህን ከመንገድ ላይ ነው እንዴ ያገኘኸው›› አለው ፖሊሱ፡፡
ባለ መኪናው ዝም አለ፡፡
ከግራ ከቀኝ የስድብና የርግማን መዓት ይወረወርበታል፡፡ ጓደኞቹ ሁኔታውን አይተው መጡ፡፡ 
‹‹በል አስነሣና ወደ ፖሊስ ጣቢያ›› አለው ፖሊሱ፡፡ ጓደኞቹ የተፈጠረውን ነገር ከከበቡት ሰዎች እየጠያየቁ ነው፡፡ መኪናውን ለማስነሣት በሩን ከፈተ፡፡ ጥሎት የሄደውን ስልኩን አንሥቶ ሲያየው ከሃያ በላይ አምላጭ ስልክ አለው፡፡ ፖሊሱ እያጣደፈው እንደምንም ያመለጡትን ስልኮች አየ፤ አብዛኛው የእኅቱ ነው፡፡ ግራ ገባው፡፡
‹‹አንዴ ልደውል›› አለው ፖሊሱን
‹‹ባክህ ወደ ጣቢያ ሂድ፤ ስንት ችግር እንደፈጠርክ እዚያ እንነግርሃለን›› አለው ፖሊሱ፡፡
‹‹እኅቴ ስለሆነች ነው›› አለ፡፡
‹‹እዚህ መኪናውን ገትረህ የስንቱን እኅት ስታስለቅስ ነው የቆየኸው፤ ባክህ ንዳው›› አለ ፖሊሱ፡፡
ቁልፉን ተረክ አድርጎ አስነሣው፡፡ ልቡ ግን በድንጋጤና በሥጋት እንደ ጥምቀት ከበሮ ይመታል፡፡ ፖሊስ ጣቢያ ሲደርስ ፖሊሱ ቁጣው አልበረደም ነበር፡፡
‹‹እንዴት አንተ የሆስፒታል መንገድ ትዘጋለህ?›› አለው በንዴት
‹‹አላወቅኩም ነበር›› ብሎ መለሰለት፡፡
‹‹እንዴት ነው የማታውቀው፤ ምልክት ማየት አቅቶህ ነው››
‹‹ስለቸኮልኩ ልጆቹ አቁመው ሲሉኝ አቆምኩት››
ጣቢያ ያሉት ሁሉ ከራሱ ውጭ ግድ የሌለው፣ ለሌላው የማያስብ፣ ሥርዓት የለሽ፣ ማን አለብኝ ባይ ጎረምሳ አድርገው ገመቱት፡፡ ለማስረዳት ብዙም አልጣረም፡፡ ልቡ ከእኅቱ ጋር ነበር፡፡ ጣጣውን በግማሽ ሰዓት ውስጥ ጨርሶ ቅጣቱን በቀሪው ግማሽ ሰዓት ተቀጥቶ፣ ወደ እኅቱ ደወለ፡፡ አንድ ሴትዮ አነሡና ‹‹ሐኪሞቹ አትግቡ ስላሉ ሰው አታናግርም›› አሉት፡፡ ጎረቤቷ ነበሩ፡፡
‹‹የት ነው ያለቺው›› ሲል ጠየቃቸው፡፡ ቦታውን ሲነግሩት እዚያው አካባቢ ነበር፡፡ ከፖሊስ ጣቢያ በር ላይ የቆመውን ፖሊስ ሲጠይቀው ‹‹ቅድም ያንን ሆስፒታል ዘግተህ አይደል እንዴ የቆምከው›› አለው፡፡ ሌላ ነገር ከመከሰቱ በፊት አመስግኖት ወጣ፡፡ ልቡ ግም ገጭ ይላል፡፡ መኪና አቁሞ በነበረበት መንገድ በኩል ወደ ሆስፒታሉ ሲገባ መንገደኞቹ በሙሉ መኪናውን የለዩት ይመስል በክፉ ዓይን ነበር የሚያዩት፡፡ መኪናውን ግቢው ውስጥ ሲያቆም ብዙዎች ይጠቋቆሙበታል፡፡ ወደ ሕንፃው ገባና የእኅቱን ስም ጠርቶ የአልጋ ክፍሏን ጠየቀ፡፡ ከመስኮቱ ኋላ ያለቺው ልጅ ቁጥሩን ነገረቺውና ‹‹የበደልካትን ልትክሳት ነው እንዴ›› አለቺው፡፡
‹‹ለምን እክሳታለሁ›› አለ ገርሞት
‹‹አንተ አይደለህ እንዴ መንገድ ዘግተህ አምቡላንስ የከለከልካት›› አለቺው በዓይኗ እየገረፈች
‹ዋት?› አለና ወደ ደረጃው በሩጫ ወጣ፡፡ ልቡ ከደረቱ ውጭ ያለ መሰለውና በእጁ ዳሰሰው፡፡
የሠፈሩ ሰው በሩ ላይ ከብቧል፡፡ ማንም በበጎ አልተቀበለውም፡፡
ጎረቤቷን ሴትዮ ፈለገና ‹‹እንዴት ናት›› አላቸው
‹‹ሐኪሞቹ ደኅና ናት ብለዋል›› አሉት፡፡
‹‹ምነው ባሰባት እንዴ››
ጎረቤቷ በኀዘን መሬት መሬት እያዩ ‹‹ምን አንድ የተረገመ ሰውዬ የሆስፒታሉ መንገድ ላይ መኪናውን አቁሞ አምቡላንሱስ በየት ይምጣ፣ እርሷን በታክሲ ስናመጣት በየት ትግባ፡፡ በዚህ የተነሣ አደጋ ውስጥ ልትወድቅብን ነበር፤ መድኃኔዓለም አተረፈልን፤ አንተም ስልክህን አታነሣውም›› አሉና ቀና ሲሉ  እርሱ የለም፡፡ የመጀመሪያውን ርግማን እንደሰማ አእምሮውን ስቶ ተንሸራትቶ ወድቋል፡፡

21 comments:

 1. ልትሞት ነው ብዬ ፈርቼ ነበር፡፡ ምንም እንኳን መሞቷ ቢያሳዝንም አስተማሪነቱ የበለጠ ይሆን ነበር፡፡ ያም ቢሆን ግን ተምረንበታል፤ እናመሰግናለን፡፡

  ReplyDelete
  Replies
  1. ልትሞት ነው ብዬ ፈርቼ ነበር፡፡ ምንም እንኳን መሞቷ ቢያሳዝንም አስተማሪነቱ የበለጠ ይሆን ነበር፡፡ ያም ቢሆን ግን ተምረንበታል፤ እናመሰግናለን፡፡

   Delete
 2. Thank you for your Educating article

  ReplyDelete
 3. የሚያደርጉት ነገር ምን ሊያስከትል እንደሚችል የማያስቡ፣ በዚህም የተነሣ ኃላፊነት ሊሰማቸው የማይችል እንስሳት ብቻ ናቸው፡፡ እስካሁን እንደ ሰው የሚኖሩና የሚያስቡ እንስሳት አልተገኙም፤ እንደ እንስሳት የሚኖሩና የሚያስቡ ሰዎች ግን በብዛት አሉ፡፡
  thank you Dani

  ReplyDelete
 4. Betam yemiyasazin, yemiyaschenik, Yemiyasfera ena yemiyabesach neger new yetekesetew. ye hod neger hod yikortal honena negeru hod amlaku ye ihtun tiri chila bilo wede misaw hede. gin mechereshachew min hone ? huletum esuas beselam tegelagelech ? esus endet hone ke wedeke behuala? le manignawum astemari tsuf new. e/r asteway libona yisten. Deacon Daniel. e/r yistih lezih astemari tsufih. Eyobel Dejen

  ReplyDelete
 5. At least he know it is his mistake, had a remorse. But in this world, most people do not admit their mistakes, that is why it is getting complicated ...

  ReplyDelete
 6. ልብ ሰቃይ አጨራረስ፣ አእምሮ ነክ ትምህርት::
  If there was an ending, how do you imagine it? Will she forgive him?

  ReplyDelete
 7. የሚገርም እይታ ነው፠ ሳነበውእያዘንኩ ማርያም ማርያም እያልኩ አነብኩት፠እንደ ሰው ተፈጥረን እንደ ሰው ማሰብ አቃተን፠ ፈሪሃ እግዚሀብሔር እራቀን፠ራሰ ወዳድነት በዛ,አቤቱ የልቦናችችንን አይን አብራልን፠ዲያቆን ዳኒ የአገልግሎት ዘመንህን ይባርክልህ፠አሜን!

  ReplyDelete
 8. Betam newu yemiyasaznew Egzabhire mastewal libonawun yisten legedialeshe sewche.

  ReplyDelete
 9. ስንቶቻችን የሚጠበቅብንን አለማድረጋችን ብቻ ሳይሆን ለስንቱስ ችግር ፈጠርን?

  ReplyDelete
 10. ‹‹ሰው ማለትኮ ለሚፈጽመው ነገር አንዳች ምክንያት ያለው፣ የሚሠራው ነገር ሊያስከትል የሚችለውን ነገር ቀድሞ አስቦ የሚሠራ ፍጡር ማለት ነው፡፡

  ReplyDelete
 11. ጊዜያዊ ደስታን ከሃላፊነት አስበልጦ መንቀሳቀስ ለእንደዚህ ያለ ከፍ ላለ ፀፀት መዳረግን ያመጣል።

  ReplyDelete
 12. I don't blame him, most of the hotel or restaurant build without parking space, it is difficult to drive Inaddition that he gets permission from unknown person. We have to focus on the solution instead of blaming each other. I know most Ethiopian poor and they don't have car but we have to give respect for rich people. We are Ethiopian.

  ReplyDelete
  Replies
  1. What do you mean "respect for rich people"? What's your solution? I thought you use wrong premisese first no parking spot, so where he park and second he got permission from someone to park wrong parking lot.

   Delete
 13. Are you getting your feet wet in short fiction?

  I get the message on being responsible Driver...scratch that...responsible person

  ReplyDelete
 14. የሚያደርጉት ነገር ምን ሊያስከትል እንደሚችል የማያስቡ፣ በዚህም የተነሣ ኃላፊነት ሊሰማቸው የማይችል እንስሳት ብቻ ናቸው፡፡ እስካሁን እንደ ሰው የሚኖሩና የሚያስቡ እንስሳት አልተገኙም፤ እንደ እንስሳት የሚኖሩና የሚያስቡ ሰዎች ግን በብዛት አሉ፡፡

  ReplyDelete
 15. የሚገርም እይታ ነው፠ ሳነበውእያዘንኩ ማርያም ማርያም እያልኩ አነብኩት፠እንደ ሰው ተፈጥረን እንደ ሰው ማሰብ አቃተን፠ ፈሪሃ እግዚሀብሔር እራቀን፠ራሰ ወዳድነት በዛ,አቤቱ የልቦናችችንን አይን አብራልን፠ዲያቆን ዳኒ የአገልግሎት ዘመንህን ይባርክልህ፠አሜን!

  ReplyDelete
 16. ታሪኩ የቀረበበት መንገድ የበለጠ አስተማሪ እንዲሆን ያደረገዉ ይመስለኛል፡፡

  ReplyDelete
 17. Is it a true story? Or just your fiction? It is a bit confusing. The way you try to bring such important issue through novel truly sucks! I could simply write a critic article than trying to create a story. Or else, tell us if it is a true story. I thing novel is not your thing.

  ReplyDelete
 18. የሚያደርጉት ነገር ምን ሊያስከትል እንደሚችል የማያስቡ፣ በዚህም የተነሣ ኃላፊነት ሊሰማቸው የማይችል እንስሳት ብቻ ናቸው፡፡ እስካሁን እንደ ሰው የሚኖሩና የሚያስቡ እንስሳት አልተገኙም፤ እንደ እንስሳት የሚኖሩና የሚያስቡ ሰዎች ግን በብዛት አሉ፡፡
  thank you Daniየሚያደርጉት ነገር ምን ሊያስከትል እንደሚችል የማያስቡ፣ በዚህም የተነሣ ኃላፊነት ሊሰማቸው የማይችል እንስሳት ብቻ ናቸው፡፡ እስካሁን እንደ ሰው የሚኖሩና የሚያስቡ እንስሳት አልተገኙም፤ እንደ እንስሳት የሚኖሩና የሚያስቡ ሰዎች ግን በብዛት አሉ፡፡

  iግዜክስ

  ReplyDelete
 19. Teru astmari new enamsgenalen!!

  ReplyDelete