ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን
ለዘመናት ሲመኙት የኖረ፣ የትውልድን ሕልም እውን ያደረገ፣ በዘመናዊ ታሪካችን ውስጥ ሊጠቀስ የሚችል የዚህ ትውልድ ሥራ ነው፡፡
‹ዓባይን መገደብ› ታላቅ ሐሳብ፣ ታላቅም ውሳኔ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከአካባቢው ሀገራት ጋር የምታደርገውን ውይይት ቋንቋውን የቀየረ፣
የግዮን ምንጩ ከኢትዮጵያ ተራሮች መሆኑን ከብራና አውርዶ መሬት ላይ የጻፈ ነው፡፡
ስለ ሕዳሴው ግድብ የሚሠሩት ማስታወቂያዎች
ግን ፈጽሞ ግድቡን የማይመጥኑ፣ እንኳን ለዓባይ ግድብ ለኛ ቤት አጥርም የማይሆኑ፣ በውስጣቸው ምንም ዓይነት ሀገራዊ ርእይና ፍልስፍና
የሌለባቸው፤ ከጠላና እንጀራ የማያልፉ ናቸው፡፡ እንዴው ግድቡ አፍ ስለሌለው እንጂ በስም ማጥፋትና በክብረ ነክ ወንጀል ይከስ ነበር፡፡
የታሪክ ባለሞያዎች፣ የፖለቲካ ጠበብት፣ የኪነ ጥበብ ልሂቃን፣ የእምነትና
የባሕል ምሁራን፣ የሥነ ቃል አጥኒዎች፣ የሐሳብ መሪዎችና የሕዳሴ ኮከቦች መነጋገሪያ፣ መከራከሪያ፣ ሐሳብ ማራቀቂያ፣ ትውልድ መቅረጫ፣
ትውልድ ማነሣሻ፣ መሆን የነበረበት የሕዳሴው ግድብ የቀልደኞች ማቧለቻ ሲሆን እንደማየት ያለ የክፍለ ዘመኑ ርግማን የለም፡፡