Wednesday, January 28, 2015

ከአኩስምና ከቻይና ግንብ በፊት
ማክሰኞ ለም ሆቴል አካባቢ ለመንገድ የተቆፈረ ገደል ውስጥ የገባው መኪና(ፎቶ ፡- ጽላት ጌታቸው)
ከግንባታዎች ጋር ተያይዞ እየደረሰ ያለው አደጋ አሳዛኝ እየሆነ ነው፡፡ ይኼ አደጋ በሦስት ነገሮች ምክንያት እየደረሰ ያለ ይመስለኛል፡፡ የመጀመሪያው ግንባታዎች ሲከናወኑ ተገቢ የሆነው ቅድመ፣ጊዜና ድኅረ ግንባታ ጥንቃቄ ስለማይወሰድ ነው፡፡ ታላላቅ ክሬኖች አገር ደርምሶ የሚሄድ ቋጥኝ አንጠልጥለው እየታዩ፣ በሥራቸው ሰውና መኪና እንዲያልፍ ይደረጋል፡፡ ለግንባታ ሠራተኞች በቂ የሆነ የአደጋ መከላከያ ሥልጠናና መሣሪያ አይሰጣቸውም፡፡ አማራጭ መንገዶችና የእንቅስቃሴ ቦታዎች ቀድመው ስለማይዘጋጁ ግንባታና ኑሮ ጎን ለጎን ይካሄዳል፡፡ መታጠር ያለባቸው ሳይታጠሩ፣ መሸፈን ያለባቸው ሳይሸፈኑ፣ መከደን ያለባቸው ጉድጓዶች ሳይከደኑ፣ ምልክት መደረግ ያለባቸው ቦታዎች ላይ ሳይደረጉ ግንባታዎች ይከናወናሉ፡፡ በዚህም የተነሣ በተገቢ ጥንቃቄ ሊተርፉ ይችሉ የነበሩ ሕይወቶች ይቀጠፋሉ፣ አካል ይጎድላል፣ ንብረት ይወድማል፡፡

Tuesday, January 20, 2015

ቁስል ተራ

click here for pdf
የመርካቶ ግርግር

ዛሬ ወደ ቢሮ እየመጣሁ በሬዲዮ ስለ አጭበርባሪ ልመናዎች እየሰማ ነበር፡፡ ራሳቸውን በሽተኛ አስመስለው ስለሚለምኑ ሰዎች፡፡ እጃቸውን አጣምመው፣ ሰውነታቸው አቁስለው፣ ዓይናቸውን  የጠፋ አስመስለው፤ ጀርባቸውን አጉብጠው ስለሚለምኑ ሰዎች፡፡ በአንዳንድ ሰዎች ላይ የሚታየው የጉዳት ምልክት ምንም ዓይነት ጥርጣሬን የማያመጣ ነው፡፡ 

በሰማነው ነገር ላይ እየተወያየን ስንመጣ መርካቶ ‹ቁስል ተራ› የሚባል ቦታ አለኮ አለኝ አንድ ሰው፤ ‹‹ምን የሚደረግበት›› ብዬ ጠየቅኩ፡፡ ‹‹ቁስል የሚሠራበት›› አለኝ፡፡ ‹‹እዚያ ትሄድና ገንዘብ ከፍለህ የምትፈልገውን ዓይነት ቁስል ይሠሩልሃል›› አለኝ፡፡ አይ መርካቶ! አለ ጸጋዬ ገብረ መድኅን፡፤ እስኪ የበለጠ የምታውቁ አካፍሉን፡፡   

Friday, January 16, 2015

ጎርፍና ግፍሰሚ ካጡ የሶማሌ ተረቶች አንዱ እንዲህ ይላል፡፡

አንድ ሰው የጠፋች የአካባቢው ግመል ፍለጋ ጫካ ይገባል፡፡ ከብዙ መከራ በኋላ ያቺን ግመል አግኝቶ ከተማ ገባና ግመሏን ለባለቤቱ ሳይመልስ ሐሳቡን ቀይሮ ራሱ ያልባትና ይጋልባት ጀመር፡፡ ግመሏን ከአውሬ ለማዳን ጫካ ገብቶ የነበረው ሰውዬ እርሱ ራሱ ግመሏን መውሰዱ ብዙዎችን አስገረማቸው፡፡ ትንሽ ቆየና ከዚያች ከአንዷ ግመል ወተት እያለበ በግመሏ ላይ ተቀምጦ እየዞረ ለአካባቢው ሰው ወተት መሸጥ ጀመረ፡፡ ነገር ግን የግመሏ ወተት በአንድ ጊዜ ሀብታም ሊያደርገው አልቻለምና ሌላ ነገር አሰበ፡፡ በወተቱ ውስጥ ውኃ እየጨመረ ቀላቅሎ መሸጥ፡፡ ‹‹ሰውም ምነው የሰውየው አመሉም ወተቱም ተቀየረሳ›› እያለ ዝም ብሎ ይገዛ ጀመር፡፡ (ይገዛ የሚለው ቃል ጠብቆ እንዳይነበብ አሳስባለሁ) 

Thursday, January 15, 2015

እሳት በዳጋ እስጢፋኖስ

በዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም ተነሥቶ የነበረው እሳት በደቅ ደሴት ሕዝብ፣ በገዳማውያኑና በፖሊስ ትብብር መጥፋቱ ተነገረ፡፡ እሳቱ ቁጥቋጦዎችን ከማጥፋት በቀር ደኑን እንዳላወደመው ተነግሯል፡፤ የደቅ ደሴት ሕዝብ ላደረገው አስቸኳይ ርብርብ ገዳማውያኑ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የክልሉ መንግሥትም ሄሊኮፕተር ለመላክ እስከመዘጋጀት ድረስ ያሳየውን ትብብር ገዳማውያኑና ሕዝቡ አድንቀዋል፡፡

Wednesday, January 14, 2015

ቀጣይ ዜና - እሳት በዳጋ እስጢፋኖስ


እሳቱ ከደኑ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ እንዳያልፍ መነኮሳቱ፣ ፖሊስና ሕዝቡ ቆርጠውታል፡፤ በአፈር ከተር በመሥራት የእሳቱን ተሻጋሪነት ቀንሰውታል፡፡ አሁን እሳቱን ለማጥፋት እየተረባረቡ ነው፡፡

እሳት በዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም


በጣና ሐይቅ ውስጥ በሚገኘው የዳጋ እስጢፋኖስ እሳት መነሣቱን የገዳሙ ምንጮች ተናግረዋል፡፤ እሳቱ የተነሣው ከደኑ አካባቢ ሲሆን ወደ ገዳሙ ገና አልደረሰም፡፡ የክልሉ ፖሊስ ወደ ቦታው በፍጥነት መድረሱ ተሰምቷል፡፡ አባቶች እሳቱን ቆርጦ ለመከላከል እየሞከሩ ነው፡፡ በሰው ኃይል ለመከላከል የማይቻል ከሆነ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ክልሉ ገልጦላቸዋል፡፡  

Tuesday, January 13, 2015

ጉርብትና
ጉርብትናችንን እንደ ጣይቱ ሆቴልና እንደ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያ ድርጅት  ጉርብትና አያድርግብን፡፡