Friday, December 26, 2014

ብልጽግናና ባሕል


መንገድ አቋርጣለሁ፡፡ በእግሬ፡፡ ሁለት ጎልማሶች በመንገዱ ማቋረጫ ላይ ተገናኙ፡፡ ከሁለት አንዳቸው ቀድመው ወይም ተከትለው ማለፍ አለባቸው፡፡ ሁለቱም ቆሙ፡፡ ከዚያም አንዱ ሌላኛው ቀድሞ ያልፍ ዘንድ ጋበዘ፤ የተጋበዘውም ጋባዡ  እንዲያልፍ ለመነ፡፡ ግብዣው ጥቂት ደቂቃዎች ፈጀ፡፡ እኛም ከኋላ ያለነው ትኅትናቸውን አድንቀን በትዕግሥት ቆምን፡፡ በመጨረሻ አንደኛው እያመሰገነ አለፈ፡፡ ሌላኛውም ‹ምን አይደል›› እያለ አሳልፎ አለፈ፡፡ 

ደግሞ ሄድኩኝ፤ እነሆም በአንድ መስቀለኛ የአስፋልት መንገድ ላይ ደረስኩ፡፡ መኪኖቹ ከአራቱም አቅጣጫ ይመጣሉ፡፡ ሁሉም ወደ መስቀለኛው መጋጠሚያ ይገባሉ፡፡ አራቱም በአንድ ጊዜ ለማለፍ ይሞክራሉ፡፡ ነገር ግን አይችሉምና የመኪኖቹ አፍንጫዎቻቸው ተፋጥጠው ይቆማሉ፡፡ ለማለፍ እንጂ ለማሳለፍ የሚጥር አላይም፡፡ አራቱም በመስኮት ብቅ ብለው ‹ወደ ኋላ በልልኝ ልለፍ› ይላሉ፡፡ እነርሱ ሲከራከሩ ሌሎች ባለመኪኖችም ይመጣሉ፡፡ እንደ ዘንዶ ተጣጥፈው በአራቱ መኪኖች መካከል ለማለፍ ይሞክራሉ፡፡ እነዚያ ቀድመው የመጡትም ይናደዱና ወደ ፊት ገፍተው መንገዱን ያጠባሉ፡፡ በዚህ የተነሣም እነዚያም ከኋላ የመጡት በተራቸው ይቆማሉ፡፡ ሁሉም ቀድሞ ለማለፍ በሚያደርገው ፍትጊያ ሁሉም ይቆማሉ፡፡ እለፍ፣ እለፍ ተባብሎ መገባበዝ የለም፡፡ 


እየገረመኝ አልፋለሁ፡፡
አልፌም አንድ ያረጀ የዕድር ድንኳን የተጣለበት ጋ እደርሳለሁ፡፡ ድንኳኑ ለሁሉም አይበቃምና ከድንኳኑ ውጭ አግዳሚ ወንበር ላይ ሰዎች ተቀምጠዋል፡፡ ሌሎች ልቅሶ ደራሾ ሲመጡ ቀድመው ተቀምጠው የነበሩት ግር ብለው ይነሡና ወንበር ይለቃሉ፡፡ ‹ይቀመጡ አልቀመጥም› የግብዣ ግብግብ ይፈጠራል፡፡ በመካከል ገላጋይ ገብቶ እንግዳ ይቀመጣል፡፡ ‹ኖር› መባባል መልቶ ሰፍቶ ይከናወናል፡፡ ሰውን በአግዳሚዎቹ መካከል ለማሳለፍ ሁሉም እግሩን ያነሣል፣ ወይ ራሱ ይነሣል፡፡

እያደነቅኩ አለፍኩ፡፡
የማልፍበት መንገድ በግራ በቀኝ ቤት ሠሪዎች አሸዋና ጠጠር፣ ድንጋይና ብረት አውርደውበታል፡፡ እዚህም እዚያም ተጀምረው ያላለቁ፣ አልቀው ደግሞ ሰው የገባባቸው ቤቶች አሉ፡፡ አሸዋውና ድንጋዩ፣ ጠጠሩና ብረቱ መሐል መንገድ ላይ ይቆለላል፡፡ ሰው በምን ይተላለፋል? መኪና በምን ያልፋል? ብሎ ነገር የለም፡፡ ሁሉም በቤቱ ፊት ለፊት ይደፋል፡፡ ሲብሰው ደግሞ መሐል መንገድ ላይ ሲሚንቶ ያቦካል፣ ድንጋይ ይፈልጣል፡፡ እዚያ ድንኳን ውስጥ የነበረው ‹ኖር› መባባል፣ በአግዳሚዎች መካከል ሰው ለማሳለፍ መከራ መቀበል፣ እንግዳ ሲመጣ ከመቀመጫ ተነሥቶ ክብር መስጠት በቤት ሠሪዎቹ ዘንድ የለም፡፡

ይህንንም አለፍኩት፡፡
እነሆም በኑሮ ደከም ያሉ ሰዎች ወደሚኖሩበት መንደር ደረስኩ፤ የቆርቆሮ ጣራና የቆርቆሮ ግድግዳ ወደሚበዛባቸው፡፡ አቡኪዎቻቸው በእድሜ ገፍተው በሞቱ የጭቃ ግድግዳዎች ወደተሠሩ፤ ተቃቅፈው እንደሚሄዱ የሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች ትከሻ ለትከሻ የተደጋገፉ ግድግዳዎች ወዳሏቸው ቤቶች መንደር፡፡ በዚያም ሳቋርጥ ‹‹ወ/ሮ እንትና ደኅና አደሩ፤ ምነው ሰሞኑን አላየሁዎትም› የሚል የጎረቤት ድምጽ ሰማሁ፡፡ ወ/ሮ እንትናም አብራሩ፡፡ እልፍ ስል ደግሞ ‹‹እ-ን-ት-ና፣ ቡ-ና-ው ፈ-ል-ቷ-ል› የሚል ዘለግ ያለ የግብዣ ጥሪ አዳመጥኩ፡፡ ደግሞ ልጆቹም ሰብሰብ ብለው በመንደሩ መካከል ከምትገኘው የእጣቢ መድፊያ መስክ ላይ አፈር ልሰው አፈር መስለው ይጫወታሉ፡፡ ውሾም ከልጆቹ ጋ ይዘላሉ፡፡
እነሆ ያንንም መንደር አለፍኩትና ከመንገዱ ማዶ ተሻገርኩ፡፡
ይኼ ደግሞ የባዕለ ጸጎች ሠፈር ነው፡፡ እያንዳንዱ ግን በአጥር ተከልሏል፡፡ ወደዚያ መንደር ለማለፍም እንደ መንግሥት መሥሪያ ቤት መታወቂያ ይጠየቃል፤ ወደ ውስጥ ስትዘልቁ እንደ ሙታን መንደር ጭር ያለ ነው፡፡ መስክ ላይ ተሰባስበው የሚጫወቱ ልጆች አታዩም፤ ሁሉም ወይ ጌም ላይ ናቸው ወይም ቲቪ እያዩ ነው፡፡ አለያም ግቢያቸው ውስጥ ናቸው፡፡ ወላጆቻቸውም ግቢ ግቢያቸውን ዘግተው አይጠያየቁም፡፡ እንዲያውም ጎረቤታቸው ማን እንደሆነ የማያውቁም አሉ፤ ከግቢያቸው ሲወጡ ‹‹ወ/ሮ እገሊት ደኅና አደሩ፤ ምነው ሰሞኑን አይታዩምሳ›› ብለው አይጠይቁም፡፡

በዚህም ተገረምኩ፤ አለፍኩም፡፡
እነሆም ሰዎች ታክሲ ለመሣፈር ወረፋ የያዙበት ቦታ ደረስኩ፡፡ ረዥም ሰልፍ፡፡ ልጆች፣ ወጣቶች፣ አረጋውያን፣ በከዘራ የሚሄዱ፣ ጎንበስ ብለው መሬት መሬት የሚያዩ፣ ጥላ የያዙ፣ በወረቀት ፀሐይን የሚከልሉ፣ ሁሉም ተሰልፈው የታክሲውን መምጣት ይጠባበቃሉ፡፡ ቆምኩና አየኋቸው፡፡ ታክሲዎቹ በመጡ ቁጥር የቻሉትን ሰው ይጭናሉ፡፡ በዚያ ፀሐይ ጨዋነታቸው ይነበባል፡፡ ራሳቸው ተራ አስከባሪዎች ከሚፈጥሩት ግርግር በቀር ግርግር ለመፍጠር የሚቻኮል ያንን ያህል ሰው የለም፡፡

ይህንንም አይቼ አለፍኩ፡፡
አለፍኩና ወደ አንድ ማደያ ዘንድ ደረስኩ፡፡ የነዳጅ ወረፋው የመንገዱን ጥግ የመኪና መሸጫ አስመስሎታል፡፡ ወደ ማደያው አካባቢ ሸውደው ለማለፍ የሚሞክሩ፤ አልፈው የሚሄዱ መስለው በሰው ሰልፍ የሚገቡ፣ ያንን ረዥም ሰልፍ እያዩ ሌላ ሰልፍ የሚፈጥሩ፣ መኪናቸውን አቁመው ጓደኛቸውን የሚያስገቡ ባለመኪኖች ይታያሉ፡፡ ከመኪኖቻቸው ውስጥ የብልግና ስድቦች ይወጣሉ፤ ይወራረፋሉ፤ ታክሲ እንደሚጠብቁት ሰዎች ፀሐይና አቧራ አያገኛቸውም፤ ከታክሲ ጠባቂዎቹ በላይ ግን ትዕግሥት የለሾች ናቸው፡፡ በመካከል ነዳጅ አልቋል ሊባል እንደሚችል ያውቃሉ፤ ነገር ግን ከኋላቸው የተሰለፉት ሰዎች ድካም ምንም ሳይመስላቸው ከነዳጅ ታንከራቸው በተጨማሪ በጀሪካቻኖቸው ይሞላሉ፡፡

እነሆ ይህንንም ታዝቤ አለፍኩ፡፡
አሁን ግን ዝም ብዬ አላለፍኩም፤ ያሳስበኝ ጀመር፡፡ እንዴው የኛ በጎ በጎ ባሕላችን በድህነት ላይ ነው እንዴ የተመሠረተው? አልኩ፡፡ በድሃው ማኅበረሰብ አካባቢ የምናያቸው የመከባበር፣ የመተባበር፣ የመጠያየቅ፣ የመረዳዳት፣ የመተሳሰብ ባሕሎች የተሻለ ገቢ ያለው ማኅበረሰባችን ላይ ሲታዩ ወይ ጠፍተዋል ወይም ቀንሰዋል፡፡ የዘመዶቻቸውን ልጆች እንደራሳቸው አድርገው የሚያሳድጉ ክቡራን ወላጆችን በብዛት የምናየው ድሃው ወገናችን ዘንድ ነው፡፡ የአንድ ሰው ጉዳይ አሳስቦት የት ነበርክ? ብሎ የሚየጠይቀው፣ ያለውን ተካፍሎ ለመብላት የሚተጋው፣ ጉርብትናው የሚያምረው፣ መከባበሩ ሞልቶ የሚፈሰው እዚህ ደሃው ወገናችን ላይ ነው፡፡

የተሻለ ኑሮና ዕውቀት ያለው ጋ ስትሄዱ ግለሰባዊነት፣ ብቸኛነትና ድንበርተኛነት ሠፍኖ ታዩታላችሁ፡፡ የማይለብሳቸው ብዙ ልብሶች አሉት፣ ግን አይሰጥም፤ የማይመገበው ትርፍ ምግብ አለው ግን፤ ግን አይመጸውተውም፡፡ ታላላቅ ግቢ አለ፤ ነገር ግን ተረት የሚያወሩ፣ ባሕል የሚያስተምሩ አክስቶች፣ አጎቶችና አያቶች አይኖሩበትም፡፡

እነዚያን የመንደር ሐኪሞች፣ እነዚያን እጆቻችንን አሽተው ያዳኑን ወጌሾች፣ እነዚያን ሐረግሬሳ በጥሰው፣ ስሚዛ ጨምቀው ያዳኑንን የመንደር እናቶችን አስቡና የአሁኑን የሕክምና ሥነ ምግባር አስቡት፡፡ ጠዋት ከዕንቅልፍ ብንቀሰቅሳቸው፣ በምሳ ሰዓት ብንሄድባቸው፣ በእኩለ ሌሊት ብንጠራቸው ለመንደሩ ሰዎች የነበራቸው ትጋት፤ ዛሬ ከዘመናዊ የሕክምና ተቋማት ለምን ተወሰደ? ይበልጥ ባወቅንና ይበልጥ ባገኘን ቁጥር ይበልጥ ጨዋነት ይጠፋብናል ማለት ነው? ከጉልት ሻጮች ይልቅ በሱፐር ማርኬቶች፣ ከመንደር ሱቆች ይልቅ በገበያ አዳራሾች ለምን ማጭበርበሩ በዛ?

ከተለያየ ጎሳና ነገድ ይበልጥ ተዋሕዶ፣ ተጋብቶና ተዛምዶ የምናገኘው የትኛውን ኅብረተሰብ ነው? ከውስኪ ቤትና ከጠጅ ቤት ኢትዮጵያን የሚያሳየን የትኛው ነው? በሀገር ቤት ከሚኖረውና በውጭ ከሚኖረው የትኛው ነው ጠባቡ? በአውቶቡስ ከሚሄድና በአውሮፕላን ከሚሄደው የትኛው ነው የሚገባበዘው? የትኛውስ ነው የሚጨዋወተው?   

ባደግንና በተለወጥን ቁጥር፣ ዕውቀትና ሀብትም ባፈራን ቁጥር፣ የኑሮ መደባችንም በተቀየረ ቁጥር እነዚያን የኛ ናቸው የምንላቸውን ወጎች፣ ልማዶች፣ ሥነ ምግባሮችና ባሕሎች እየተውናቸው እንሄዳለን ማለት ነው? ሥልጣኔና ብልጽግና የበጎ ባሕል ማጥፊያ ናቸው እንዴ? ኢትዮጵያዊ የምላቸው ባሕሎች፣ ወጎችና ልማዶች ካልተማረው ይልቅ በተማረው፣ ከሀብታሙ ይልቅ በደሃው ማኅረሰብ ዘንድ ይበልጥ የሚከበሩትና የሚጠበቁት ለምንድን ነው? ይበልጥ በበለጸግን ቁጥር፣ ይበልጥስ በተማርን ቁጥር ይበልጥ ኢትዮጵያዊነታችንን እንለቃለን ወይስ?31 comments:

 1. God bless your pen:)! Eye of the eagle, thanks Dan!

  ReplyDelete
 2. that's incredible idea,,,,, the more we develop the more we lose our culture and our religion.

  ReplyDelete
 3. ኢትዮጵያዊ የምላቸው ባሕሎች፣ ወጎችና ልማዶች ካልተማረው ይልቅ በተማረው፣ ከሀብታሙ ይልቅ በደሃው ማኅረሰብ ዘንድ ይበልጥ የሚከበሩትና የሚጠበቁት ለምንድን ነው? ይበልጥ በበለጸግን ቁጥር፣ ይበልጥስ በተማርን ቁጥር ይበልጥ ኢትዮጵያዊነታችንን እንለቃለን ወይስ? be tikikil ethiopia wust iye hone new zare yetemarut nachew mekefafelin, meleyayetin iyazemu yalut mastewalun yisten inji!!!

  ReplyDelete
 4. kale hiwot yasemalin memhir. yemiyasgerimim, yemiyasazinim naw. lemanignawim egziabher yirdan

  ReplyDelete
 5. I was expecting that you will say something about those who lost their lives in Bahirdar, at least "nefis yimar".
  This is not politics but sharing the grief

  ReplyDelete
 6. ''ሥልጣኔና ብልጽግና የበጎ ባሕል ማጥፊያ ናቸው እንዴ?
  የተሻለ ኑሮና ዕውቀት ያለው ጋ ስትሄዱ ግለሰባዊነት፣ ብቸኛነትና ድንበርተኛነት ሠፍኖ ታዩታላችሁ፡፡ የማይለብሳቸው ብዙ ልብሶች አሉት፣ ግን አይሰጥም፤ የማይመገበው ትርፍ ምግብ አለው ግን፤ ግን አይመጸውተውም፡፡ ታላላቅ ግቢ አለ፤ ነገር ግን ተረት የሚያወሩ፣ ባሕል የሚያስተምሩ አክስቶች፣ አጎቶችና አያቶች አይኖሩበትም፡፡''
  Dani, yekduean amlak yitebkih!!!

  ReplyDelete
 7. very very Nice view, Dn. Daniel.

  ReplyDelete
 8. antew ande endalkew fikrachin kebado akufada newa

  ReplyDelete
 9. hiwetan asalfa yemsete talaqe sew new lala menem malet alclem dani

  ReplyDelete
 10. yezemenu talqe sew neh

  ReplyDelete
 11. ይበልጥ በበለጸግን ቁጥር፣ ይበልጥስ በተማርን ቁጥር ይበልጥ ኢትዮጵያዊነታችንን እንለቃለን ወይስ?

  ብልፅግና በተለያየ መንገድ ይመጣል፡፡ አንድም በላብ ወዝ አሊያም በዚህ ዘመን በዚች ምስኪን ሀገር በስፋት እንደሚታየውና ያልገባበት እንደሞኝ የሚታይበት በሰይጣናዊ መንገድ ማለትም በሌብነትና በባዕድ አምልኮ የሚመጣ ነው፡፡
  በላብ ወዝ የተገኘ እግዚአብሄር ስላለበት መልካም ሲደረግበት እያየን ነው፡፡የነብስ ዋጋም ያሰጣል፡፡
  በሌብነት የተገኘ እግዚአብሄር ስለሌለበት ሰዎች ስግብግብ፡ ለኔ ብቻ፡ (Self confined) ሲሆኑ ይታዩበታል፡፡ በዚህኛው የተገኘ ስጡ ስጡ አይልም፡፡ ቢሰጥም /ብትሰጥም በጎ ላድርግበት ቢልም /ብትልም ያው ያለውን ይዞ ይሄዳል፡፡ ምንጩ ሰይጣን ነውና፡፡
  • መንግስት ሌባ
  • ባለስልጣን ሌባ
  • ግልገል ሹመኛ ሌባ
  • ኢንቬስተር ነኝ ባይ ሌባ
  ስለዚህ እንደምን ሃብት ሲያገኙ መልካም ያድርጉ ፡፡ አንቺ ሀገር የድንግል ማርያም ልጅ እግዚአብሄር የሆነ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ይጎብኝሽ፡፡ የበቀለብሽን እንክርዳድ ይንቀልልሽ፡፡ አዚምሽን ይግፈፍልሽ፡፡ ከማህፀንሽ ወጥተው የሚነክሱሽን እንዳልሆንሽ ያደረጉሽን ልብ ይስጥልሽ፡፡ አሜን

  ReplyDelete
 12. adegena atir,kifu wusha, keswu gar lalemegenangt kenetsfu yanoralu. TERET YEMMWORU, WOG YEMIYAOGU AKISTOCH SIMETU ZEBENACHW BET YELUM EDLU ADRGUCHHWAL. KALHONE ZEBU WUSHAW TELKO NEW YALE YILAL .LIJOCHACHW MECHAWT BIFLGU
  ENATOCHACEW GIBA BET BILW EJOCHACHWN GOTEW YASGEBALU. NEGE KESEW, KEWOGEN ,KEBETESB GAR YEMYIGENANGN LIJ YASDIGALU.
  YEMCHRSAHA TIFATU YEWOLAJOCH.

  ReplyDelete
 13. Very good observation Daniel. We can learn from others without abandoning our good cultural assets!

  Haileluel

  ReplyDelete
 14. pls donot post copy & paste

  ReplyDelete
 15. ወዳጄ ይህ እይታህ በጣም ተገቢና ወቅታዊ እንዲሁም በጣም አነጋጋሪ ነው። እውነት ለመናገር ስልጣኔ የራስን ባህል ፣ ወግና እምነት ባጠቃላይ ማንነትን እንኳን መለወጥ መሸርሸር አይገባውም ምክንያቱም የኛነታችን መገለጫዎች ናቸውና። ይህ ጉዳይ በሕብረተሰቡም ሆነ በመንግስት ትኩረት ካጣ ከራርሟል ብል ማጋነን አይሆንብኝም።
  አንድ ምሳሌ ላንሳ ፤ የዛሬ ፩፯ ዓመት ገደማ በአንድ የመንግስት መስሪያ ቤት ስብሰባ የማኔጅመንት መመሪያ የሚል መጽሃፍ ላይ ውይይት ተደርጎ ነበር። በዚያ ዕለት ከአዠንዳው ያላነሰ አነጋጋሪ ጥያቄ ተነሳና ቤቱን ከሁለት ከፈለው እሱም የመጽሃፉ ርዕስ ላይ ያተኮረ ሲሆን ማኔጅመንት የሚለውን የእንግሊዘኛ ቃል አማርኛ ጠፍቶለት ነወይ የሚል ነበር። በጊዜው ትኩረት ላላገኝ እችላለሁ ብዬ ሳመነታ ያነሳሁት ጥያቄ ባልጠበቅኩት ሁኔታ ከመድረኩም ተቀባይነት አግኝቶ ወደፊት በምናሳትማቸው መሰል ሰራዎች ሁሉ ጥንቃቄ እንዲደረግበት በማሳሰብ ስብሰባው መጠናቀቁ ት ዝ ይለኛል።

  ስለዚህ ወዳጄ ስጋት ህን እጋራለሁ ቢሆንም ማህበረሰባችን፣ የሚመለከተው የመንግስት አካልና የመገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ይህን መሰል የማህበረሰብ ድህረ ገጾች ብዙ ሚና ይጠበቅባቸዋል የሚል እምነት አለኝ። ያኔ ስልጣኔና ብልጽግና የዚህ ዓይነት ችግር ፈጣሪነታቸውን ሙሉ ለሙሉ ባይተውዃን መቀነሳቸው አይቀርም የሚል ግምት አለኝ።

  ReplyDelete
 16. ራሳቸው ተራ አስከባሪዎች ከሚፈጥሩት ግርግር በቀር ግርግር ለመፍጠር የሚቻኮል ያንን ያህል ሰው የለም፡ D/n Daniel Tera askebariwoch bayinoru eneza yeteselefu sewoch sijemer ayiselefum nefse tur bitiwedik enkuwan regito yemiyalf hizib new yemiselefew silezih Tera askebariwoch endene betam limesegenu yigebachewale benesu birtat new tax agigniten wedeminfeligibet yeminihedew.

  ReplyDelete
  Replies
  1. Ay wondimie, tera askebariwoch kemefeterachew befit eko ye Addis Ababa hzb le Anbesa Awutobis siselef yeneberena sne-sreat yemiawuk hizb new. Tera askebariwoch lehz bilew yemiaskebru endaymeslih, lerasachew santim lemelkem ena le poletica sra yetesemaru nachew. Chirash yesu musna new zaries yemereren. Yemifelgutin asalfew yasgebutal.

   Delete
 17. ምናልባት ፈጣሪ ሥልጣኔ ይቅርባቹህ ያለን ለዚህ ይሆን? እውነቴን እኮ ነው። እስኪ ስኬሉን አሳድገን እንየው፣ በጣም ሠልጥነን ግን በጣም ከፍተን። እኔ በራሴ ላይ ብዙ ለውጥ አይቻለው። የተሻለ ስኖር ለበጎነት ቦታ እያጣሁ ነው(Displacement?)። ለሁሉም ተመልክተህ እንድመለከት ስለረዳኸኝ አመሰግናለው። ፈጣሪ በስራህ አይለይህ።መልካም የገና በዓል ከመላው ቤተሰብህ ጋር!

  ReplyDelete
  Replies
  1. ምናልባት ፈጣሪ ሥልጣኔ ይቅርባቹህ ያለን ለዚህ ይሆን?
   incredible view,my bro/sis!!!

   Delete
 18. seifemichael zeejereDecember 31, 2014 at 5:11 AM

  እንዴው የኛ በጎ በጎ ባሕላችን በድህነት ላይ ነው እንዴ የተመሠረተው? አልኩ
  ውድ ወንድሜ ዳንኤል ዛሬ ሁሌ የሚያብሰለስለኝን ርእስ አነሳህልኝ፡፡ ማህበራዊነት፣ በሀገራዊ ጉዳዮች ግንባር ቀደም ተሳታፊነት፣ ባህል አክባሪነት ለደሀው የተተወ ነወይ ያልከው አሁን እየታየ ባለው ሁኔታ እጅግ የሚመስል ነው፡፡ ሀገርህ ተደፈረ ሲሉት ዳር እስከ ዳር የሚነሳው ደሀው ነው፡፡ የኢትዮጵን ባንዲራ ምልክት በእጁ አስሮ የሚዞረው ደሀው ነው፡፡ የሀገር ፍቅር ተነስቶ ሲዘፈን የሚያለቅሰው ያው ደሀው ነው፡፡ ትምህርትና ሀብት እንባ ያደርቃል እንዴ? ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ትጫወታለች ሲባል መንገዱን ሁሉ ማልያ በማልያ ደረገው ደሀው ነው፡፡ ለነገ ጨዋታ አለ ሲባል በስቴድየም ብርድ ሲጠጣው የሚያድረው ፀሓይ ሲከካው የሚውለው ይኸው ደሀው የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ደሀ ደግሞ ጨዋ ደሀ ነው፡፡ የሀብታሙ ቤት ሲቃጠል ቢያይ እራሱን አቃጥሎ ለማጥፋት የሚተባበር፣ በጠጠር የምትሰበር መስተዋት በምትከለል መስኮት የተቀመጠውን ወርቅ ከጀርባው አድርጎ ነገር ግን የተራበ አንጀቱን ለማራስ ስሙኒ ከፊት ለፊት ቁጭ ብሎ የሚለምን ነው፡፡ ርቦት ይሞታል እንጂ መስኮቱን ሰብሮ ወርቁን ዘርፎ አይበላም፡፡ ይህንን የሀገሬን ደሀ ሳስብ እጅግ ያኮራኛል፡፡ ምክንያቱም በስራ ምክንያት ወደ ኬንያ ናይሮቢ ሄጄ የወርቅ ቤቶች በስንት የብረት በሮች ታጥረው እንደሚሰሩ ሳይ እጅጉን ይገርመኛል፡፡ ታዲያ በሀገራችን ያሉ ሀብታሞችና ምሁራን ይህ ደሀ ሰላም እንደማይነሳ አውቀው አብረን እንድናድግ እንስራ እና ይለፍለት ብለው በሚሊዮን የሚቆጠር ግብር ባያጭበረብሩ ምናለበት፡፡ በኮንትሮባንድ ነግደው፣ ስልጣን ተከራይተው እንደ ልብ እቃቸውን እያስገቡ ገንዘብ እያገኙ እስኪያስታውካቸው ባይበሉበትና ባይጠጡበት ምናለበት፡፡ የተማሩ የሚባሉ መሃንዲሶቻችን ቢያንስ ሙያቸውን እክብረው በተሰራ ማግስት የሚፈረፈር አስፋልት የሚሰበር ድልድይ ባይሰሩልን ምናለበት፡፡ የተማሩ የፖለቲካ ልሂቆቻችን የማይረባ ነገር ፈጥረው ባያጫርሱን ምናለበት፡፡ ገና ከሃይለስላሴ ጊዜ ጀምረው ወደ ውጪ ለትምህርት ሄደው ሲመጡ በፖለቲካ ተደራጅተው ያንኑ ደሀ ተጠቅመው ሲጫረሱና ሲያጫርሱን ዛሬም ድረስ ያንን የመጨራረስ ፅዋ እየጋቱን በየመንገዱ ግዳይ እንድንጥል የሚያደርጉን እና ወደ ትውልዱ ለማስተላለፍ የሚጥሩት ምን ሆነው ነው፡፡ እንደ ደሃው ወገኔ መዋደድ እንፈልጋለን፡፡ ጎረቤት ለጎረቤት በደስታ እና በሀዘን መካፈል እንፈልጋለን፡፡ አንዳንዶቻችን ብንማርም ሀብት ብናገኝም የዚህ የማህበራዊ ትስስር ፍቅር ከሀገር እንዳንወጣ አድርጎናል፡፡ በአለም ላይ ከኛ የበለጠ ሀገር የሌለ አስመስሎብናል፡፡ በበኩሌ የሚያስደስተኝ ምን ጠፋህ መባባል፣ ደስታና ሀዘንን መካፈል፣ በበዓላት ሽር ማለት እና እንኳን አደረሰህ መባባል ወዘተ.. እባካችሁ የተማራችሁም ሀብት ያፈራችሁም በባህላችን እና በሀገራችን እንኩራ እንጂ አንሸማቀቅ፡፡ የጥላቻ እናትና አባቶች እንዲሁም እንዳይደርቅ ወን ከሌት የምትሰሩት ምሁራን መጨራረስ፣ መገዳደል በሬሳ ላይ መረማመድ በናንተ ይብቃ፡፡ ሃይማኖትና ባህል የለሽ ልታደርጉት የነበረው ህዝባችሁ ኮሚኒስት አልሆንም ብሎ እንዳሳያችሁ አሁንም ባህሌን አልተውም ጥላቻን አልቀበልም ይላችኋል፡፡ ግን ድሆች ሀብታም ስትሆኑ ትናንትን አትርሱ፣ ባህልንና ሀገርን አትርሱ፡፡ በተከፈተ ቤት እንጂ በተዘጋ በር ለመኖር አታስቡ፡፡

  ReplyDelete
 19. ዲ/ን ዳንኤል ክብረት
  እግዚአብሔር የአገልግሎት ዘመንህን ያስረዝምልን፤ይባርክልን፡፡ ከዚህ በመቀጠል እኔ የታዘብኩትን ትንሽ ልጠቁምህ፤ ብዙ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ጉአደኞች አሉኝ ነገር ግን ስማቸውን አሁን አላውቅም ለምን ቢባል ስማቸውን እየቀየሩ፤ የሚገርመው የእነሱን ብቻ በሆነ የሚቀይሩት የአባታቸውን ጭምር እንጂ፡፡ ቆይ እናትና አባት ባወጡት ስም መጠራት ያሳፍራል እንዴ? አመሰግናልሁ፡፡

  ReplyDelete
 20. ባደግንና በተለወጥን ቁጥር፣ ዕውቀትና ሀብትም ባፈራን ቁጥር፣ የኑሮ መደባችንም በተቀየረ ቁጥር እነዚያን የኛ ናቸው የምንላቸውን ወጎች፣ ልማዶች፣ ሥነ ምግባሮችና ባሕሎች እየተውናቸው እንሄዳለን ማለት ነው? ሥልጣኔና ብልጽግና የበጎ ባሕል ማጥፊያ ናቸው እንዴ? ኢትዮጵያዊ የምላቸው ባሕሎች፣ ወጎችና ልማዶች ካልተማረው ይልቅ በተማረው፣ ከሀብታሙ ይልቅ በደሃው ማኅረሰብ ዘንድ ይበልጥ የሚከበሩትና የሚጠበቁት ለምንድን ነው? ይበልጥ በበለጸግን ቁጥር፣ ይበልጥስ በተማርን ቁጥር ይበልጥ ኢትዮጵያዊነታችንን እንለቃለን ወይስ?


  ReplyDelete