Tuesday, December 2, 2014

የተሰበሰበ ድንች (ካለፈው የቀጠለ)
እኔና ባለቤቴ ልክ እንዳንቺ ሆነን ነበር፡፡ ነገራችን ሁሉ ችኮ ሆኖ፡፡ ያ ድሮ እንደ መልካም ሙዚቃ ጆሮሽን አዘንብለሽ የምትሰሚው የባልሽ ድምጽ ፍሬን እንደያዘ መኪና ድምጽ ሲሆንብሽ ይሰማሻል፡፡ ይናፍቅሽ የነበረው ድምጽ ሲደውል ሐሳብ ውስጥ ይጥልሻል፡፡ ደግሞ ምን ሊል ይሆን? ትያለሽ፡፡ ስልክ ከማንሳት ይልቅ ስልኩን ለመዝጋት ትቸኩያለሽ፡፡ ለመሆኑ ባል ማለት ምንድን ነው? ለእኔ ከባልሽ ጋር ብቻ የምታደርጊያቸው ነገሮች ስላሉ ነው፡፡ ከእርሱ ጋር ብቻ የምትቀልጃቸው፣ ከእርሱ ጋር ብቻ የምታወሪያቸው፣ ከእርሱ ጋር ብቻ የምትሠሪያቸው፣ ከእርሱ ጋር ብቻ የምትወስኛቸው፣ ከእርሱ ጋር ብቻ የምትባልጊያቸው፣ ከእርሱ ጋር ብቻ የምታኮርፊያቸው፡፡


ለአንቺ ብቻ የሚቀጸሉ፣ለአንቺ ብቻ የሚውሉ፣ ለአንቺ ብቻ የሚነገሩ፣ ለአንቺ ብቻ የሚገለጡ፣ ለአንቺ ብቻ የሚደረጉ፣ ለአንቺ ብቻ የሚሰሙ የተለዩ ነገሮች ከሌሉ ምኑን ሚስት ሆንሺው፡፡ ባልሽ ደግ፣ ሩኅሩኅ፣ ትዕግሥተኛ፣ የማይሰክር፣ ገንዘብ የማያባክን፣ ታማኝ፣ መልከ ቀና  ቢሆን እጅግ የታደልሽ ትባያለሽ፡፡ ይኼ ሁሉ ግን መልካም ሰውነቱን እንጂ መልካም ባልነቱን አያሳይም፡፡ ደግ ሰው፣ ቆንጆ ሰው፣ ትጉኅ ሰው፣ ፍጹም ሰው ያሰኘዋል እንጂ ብቻውን መልካም ባል አያሰኘውም፡፡

መልካም ባል ለመሆን በመልካም ሰውነት ላይ ሊጨመሩ የሚገባቸው ሌሎች የባልነት ነገሮች አሉ፡፡ በመልካም ባል ውስጥ ሚስትነት፣ በመልካም ሚስት ውስጥ ደግሞ ባልነት መኖር አለባቸው፡፡ መልካም ባል ማለት ሚስት መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ የሚረዳ፣ ሚስትነት በውስጡ ያለው ባል ማለት ነው፡፡ መልካም ሚስትም እንዲሁ፡፡ መልካም ባል ማለት የሚስትን ስሜት፣ ልብና ኩላሊት ለማወቅ የሚችል ማለት ሳይሆን ሊረዳውና ሊሰማው የሚችል ማለት ነው፡፡

እንዲህ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቼ ሳስበው ለካ እኛ ቤት ውስጥ የነበሩት ባልና ሚስት ጠፍተው አንድ ወንድና አንዲት ሴት ቀርተዋል፡፡ አብረው የሚኖሩ፣ አብረው የሚሠሩ፣ አብረው የሚያድሩ፣ አብረው የሚበሉ፣ አብረው ልጅ የሚያሳድጉ ሁለት ወንድና ሴት፡፡ ባለ ትዳሮቹ ጠፍተው ትዳሩ ቀርቷል፡፡ አንድ ነገር የሚመሠረተው፣ ለመመሥረቱ በሚኖረው ቀዳሚ ምክንያት ነው፡፡ ያ ምክንያት ነው ለዚያ ነገር የህልውናው ሞተር፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ምክንያቱ ይጠፋና ነገሩ ብቻውን ይኖራል፡፡ የምክንያቱ ሳይሆን ምክንያቱ የፈጠረው ተቋም ወይም ቡድን አባል ትሆኛለሽ፡፡

ከዚያ በኋላ የምትኖሪው ወይም የምትንቀሳቀሽው ለምክንያቱ ሳይሆን በምክንያቱ የተነሣ ለተፈጠረው ተቋም ወይም ቡድን ይሆናል፡፡ ያ ተቋም የተመሠረተበትን ምክንያት ለመፈጸም ሲል የፈጠራቸው ሕጎች፣ ሥርዓቶች፣ ደንቦች፣ ባሕሎች፣ ልማዶች፣ ወጎች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች በሰው ውስጥ ሰርጸው የመኖር ዐቅም ስላላቸው፤ አንቺም ለእነዚህ እየተገዛሽ መኖር ትቀጥያለሽ፡፡ ያን ጊዜ ሕይወት አዙሪት ይሆንብሻል፡፡ ሥራ ስላለሽ ከቤት ትወጫለሽ፣ ቤት ስላለሽ ብቻ ተመልሰሽ ትመጫለሽ፤ ልጆች ስለወለድሽ ለእነርሱ ስትዪ ትዳርሽን ትቀጥዪዋለሽ፣ ባል ስላለሽ ብቻ አብረሽ ትተኛለሽ፤ የጋራ ጉዳይ ስላለሽ ብቻ ተነጋገሪያለሽ፤ እያለ ይቀጥላል፡፡

እኔ እንዳየሁት አንቺ በትዳር ውስጥ ስትሆኚና ትዳሩ አንቺ ውስጥ ሲሆን ይለያያል፡፡ አንቺ በትዳር ውስጥ ስትሆኚ፣ በውስጥሽ ምንም ስሜት ሳይኖርሽ፣ ነፍስሽ ምንም ሳይሰማት እንዴው ማድረግ ስላለብሽ ብቻ ስታደርጊው ነው፡፡ ምግብን ሆድሽ ብቻ ሲበላውና ኅሊናሽ ጭምር ሲበላው አይለያይም? ለመኖር መብላት ስላለብሽ ብቻ ስትበዪና ደስ ብሎሽ፣ ኅሊናሽ ረክቶ፣ ዘና ብለሽ ስትበዪ ማለቴ ነው፡፡ አንቺ በትዳር ውስጥ ስትሆኚ ለመኖር ብቻ ሲባል ምግብ እንደመብላት ነው፡፡ ትዳር በአንቺ ውስጥ ሲሆን ግን ሌላ ነው፡፡ ስትሄጂ፣ ስትሠሪ፣ ስትተኚ፣ ሲደክምሽና ስትበረቺ እንኳን ትዳርሽን ባሰብሽ ቁጥር አንዳች ልዩ የሆነ የደስታና የእርካታ ስሜት ሲሰማሽ፤ ገብተሸ ስትዋኚበት፣ ያወራችሁትን፣ ያደረጋችሁትን፣ የሆናችሁትን፣ ሌላው፤ ቀርቶ የተኳረፋችሁትን እንኳን እንደ ቤት እንስሳ መልሰሽ ስታመነዥኪው እንደ መልካም ጠጅ በኅሊናሽ ኩልል ብሎ ሲንቆረቆር፤ ከቤትሽ ስትወጭ ለመመለስ ስትቸኩዪ፤ ከባልሽ ስትለዪ ለመገናኘት ስትጣደፊ፤ ባልሽን፣ ልጆችሺን፣ ቤትሽን ይዘሺው ስትሄጂ - ያ ነው - ትዳር በአንቺ ውስጥ ሲኖር ማለት፡፡

ትዳር ስንጀምር ትዳር ውስጣችን ገብቶ ነበር፡፡ ስንቆይ ግን እኛ እንገባና እርሱ ይወጣል፡፡ ያኔ ነው ‹መነጋገር› መነጋገር ብቻ የሚሆነው፡፡ መነጋገር የፍቅር መግለጫ፣ በነፍስ የመዛመድ ምልክት፣ በሐሳብ የመገናዘብ ማሳያ መሆኑ ይቀርና መነጋገር መነጋገር ብቻ ይሆናል፡፡ እኔም እንዲህ ሆኖብኝ ብዙ ጊዜ ተቸገርኩ፡፡ ስነጫነጭ፣ ስብሰከሰክ፣ ስማረርና ስቆርጥ ስቀጥል ኖርኩ፡፡ አንድ ቀን እንደ ድንገት ጋብቻን ስለማደስ የተጻፈ መጽሐፍ አገኘሁ፡፡ በፈረንጆቹ ባሕል ጋብቻን ማደስ (marriage renewal) የተለመደ ባሕል ነው፡፡ ለምን ወደ እኛ አንቀይረውም ብዬ አሰብኩ፡፡

በዚያ መጽሐፍ ላይ አንድ ቁም ነገር አየሁ፡፡ ከትዳር ልምድ ያገኘሺውን ነገር ተጠቅመሽ አዲስ የቃል ኪዳን ሰነድ አዘጋጂ ይላል፡፡ ለባለቤቴ ወሰድኩና አሳየሁት፡፡ ሲያነበው ወደደው፡፡ ያ ነገር ምክንያት ሆነንና ስለትዳር ማደስ አወራን፡፡ እኔም የራሴን እርሱም የራሱን ሰነድ አዘጋጀ፡፡ በቃል ኪዳን ሰነዱ ሞዴል ላይ ያለፈውን የትዳር ዘመን፣ ባለፈው ዘመን በክፉም በደጉም ለቆየንባቸው ዘመናት ለፈጣሪ ምስጋና፣ ለፈጠርናቸው ስሕተቶች ይቅርታ፣ ከዚያ ደግሞ ለወደፊቱ በትዳራችን እንድናደርግ የምንፈልገውን ነገር ይዘረዝራል፡፡ እኔ የርሱን እርሱም የእኔን ልናዘጋጅ ተስማማን፡፡ ባሌ ምን ቢሆንልኝ እንደምፈልግ ለብዙ ጊዜ አሰብኩበት፤ እርሱም አስቦበታል፡፡

ያዘጋጀነው ሰነድ ከትዳራችን ምን እንደምንፈልግና፣ ምን እንደማንፈልግ ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነበር፡፡ ትዳራችንን የፈተሽንብት መልካም አጋጣሚ ሆነልን፡፡ ሁለታችንም በተዘጋጀልን ሰነድ ላይ መጠነኛ ማሻሻያ ከማድረግ ያለፈ አልተጓዝንም፡፡ አሁን በስለናል፤ ከልምድ ብዙ ነገር አግኝተናል፤ በፊት በትዳር ውስጥ እናስባቸው ያልነበሩ ነገሮችን ማሰብ ጀምረናል፤ ተፈታትነናል፤ ተዋውቀናልም፡፡ አንዳችን የሌላችንን በማዘጋጀታችን የተነሣ ነገሮች በዝርዝር ቀርበው ነበር፡፡ አናደርግም የምንለው፣ እናደርጋለን የምንለው ቁልጭ ብሎ ቀርቧል፡፡

በጣም የሚገርምሽ ነገር ችግር የማይመስሉን ነገሮች ሁሉ በሌላችን ተነቅሰው ሲመጡ ችግር መሆናቸውን ለመረዳት አስችሎናል፡፡ ቀላል የሚመስሉ፣ እንደዋዛ የምንዘላቸው፣ ነገር ግን ሌላችንን የሚያናድዱና የሚያሳዝኑ ነገሮች ሁሉ መጡ፡፡  በፈጣሪ ፊት ቆምንና ሁለታችንም እንደገና ቃል ገባን፡፡ እንደገናም ተጋባን፤ ለትዳራችን አዲስ እሴት ጨመርንለት፣ እንደገና የመኖሪያ ምክንያታችንን አደስነው፤ እርሱ ወደ እኔ፣ እኔም ወደ እርሱ ውስጥ ገባን፡፡ ትዳራችንም ወደ እኛ ገባ፡፡ ያንን ሰነድ በየጊዜው እያየሁ ራሴን አረጋግጥ ነበር፡፡ ቃሌን እየጠበቅኩ ነውን? እል ነበር፡፡ እንደ አዲስ ተጋቢ ነበር የሚሰማኝ፡፡

እንዳየሁት ከሆነ ትዳርና አትክልት በየጊዜው ካልተከታተሉት አረም ይበቅልበታል፡፡ ሲብስም አትክልቱ ይጠፋና አረሙ መታየት ይጀምራል፡፡ ያኔ ነው እንጨት እንጨት የሚለው፡፡ ጎበዝ ሰው ቶሎ ብሎ ያርምና አትክልቱ እንዲያብብ ያደርገዋል፡፡ እንደገና መኮትኮት፣ እንደገና ማዳበሪያ ማድረግ፣ እንደገና አፈር መከለስ፣ እንደገና ውኃ ማጠጣት፣ እንደገና አጥር ማጠር ይጠይቅ ይሆናል፡፡ ድሮ አፈር አድርጌ ነበር፣ ማዳበሪያ ነበረው፣ አጠጥቼው ነበር፣ ኮትኩቼው ነበር አይሠራም ወዳጄ፡፡ አንዳንዴም እርሻው ብቻ ቀርቶ ተክሉ ሊጠፋ ይችላል፡፡

እና እስኪ ቆም ብለሽ ተመልከቺው፤ እንደገና መጋባት፣ ጋብቻውን እንደገና ማደስ፣ ለአዲሱ ሰብእናሽ አዲስ ሐሳብ መፈለግ፣ አሁን ለደረስሽበት ነገር አዲስ ቃል ኪዳን መግባት ያስፈልጋችሁ ይሆናል፡፡ ትዳርሽ አርጅቶ ይሆናል፡፡ ትዳር ይፀነሳል፣ ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ያረጃል፣ ዝም ካሉትም ይሞታል፡፡ ጀግኖች ደግሞ እንዳያረጅና እንዳይሞት እንደ አዲስ ያድሱታል፡፡ አንቺም ትዳርሽ እንደ ንሥር አድሽው፤ ያለበለዚያ መጀመሪያ ያረጃል፤ ከዚያም ከባሰ ይሞታል፡፡ እሳትን እንጨት ላይ እያለ መልሶ ማቀጣጠል መልካም ነው፤በእንጨትነቱ ካልተደረሰም እንጨቱ ከሰል ሲሆን ቶሎ መድረስ ነው፤ ከሰሉ አመድ ከሆነ በኋላ ግን እንደገና ማቀጣጠል አስቸጋሪ ነው፡፡ ›› ነበር ያለቺኝ፡፡

አሁን  ሳስበው እርሷ ያለቺኝ ሳይሻል አይቀርም፡፡
‹እውነትሽ ነው› አለቺ ጓደኛዋ ‹‹ሁላችንም ብንሞክረው ሳይሻል አይቀርም››
ዑራኤል የኤሌክትሪክ ሱቆች ጋር ደርሼ ተለየኋቸው፡፡ እነርሱ ግን ቀጠሉ፡፡
ፍራንክፈርት አውሮፕላን ጣቢያ

27 comments:

 1. እጅግ ግሩም ጽሁፍ ነው ነገር ግን በዚህ መልኩ ሊሸነፉ የሚችሉ ወንዶች እንዳሉ ሁሉ የማይቻሉ ወንዶች ስላሉ ችግርን ከትዳር አጋራቸው ጋር ከማየት ከመነጋገር ይልቅ የራሳቸውን ዘመድና እናት እያስገቡ የደረሱ ልጆቻቸውን እየተው ቤተሰባቸው ቤት ገብተው የሚቀመጡ ባሎች ስላሉ የማንበብ ልምድ ካላቸው ይሄ ለነሱ ጥሩ ትምህርት ይሆናቸዋልና ልብ ሰጥቷቸው ወደ ራሣቸው ቢመለከቱ በተለይ ለሚያኮርፉና ሚስት ወይም ሴት ምንም የማታውቅ ለሚመስላቸው ባሎች

  ReplyDelete
  Replies
  1. It is for both genders( male or female).

   Delete
 2. '' ከትዳር ልምድ ያገኘሺውን ነገር ተጠቅመሽ አዲስ የቃል ኪዳን ሰነድ አዘጋጂ ይላል '' የማይተማመን ባልንጀራ በየወንዝ ዳር ይማማላል እንዳይሆን ትዳር ሲሰጥ ከላይ ነው መሠረቱ ከፀና ደግሞ ጐዶሎን በጐዶሎ መሙላት እንደሆነም ጭምር አምኖ መግባት ነው ደግሞም መነጋገር ከሌለ መሞራረድ እንደሌለ የቀበጣችሁ ሲቶች ሁሉ ተረዱ

  ReplyDelete
 3. Anonymous November 27, 2014 at 3:58 PMDecember 2, 2014 at 1:15 PM

  Be Kifl 1 Anonymous November 27, 2014 at 3:58 PM biye comment yaderegkut new.
  Yihe tsihufih - Koyet kalut tsihufochih Bolo le Tidar, beqirbu degmo Endegena Engaba bileh beteketatay ketsfkew tsihuf gar endihum keleloch alfo alfo sile tidar kemitanesachew tsihufochih gar yetetemesaselebign neger ale. Lezia new meselegn almesetegnm. Beterefe gin berta.

  ReplyDelete
 4. Very Interesting and educating Story
  Thank You D. Daniel

  ReplyDelete
 5. Thank you so much Dani, I will try to apply in my life.

  ReplyDelete
 6. tadiya ketemesaselebik ehe eho be netsa yemitagenegew migib new enji kefle yemitageniw aydelem endegena demo migib wun yidegemal eko .

  ReplyDelete
 7. I like it but I was waiting God support to rebuild the marriage. If there is no God, there is no satisfaction so pray to God to have peace, happiness, love and satisfaction.” እኔ የርሱን እርሱም የእኔን ልናዘጋጅ ተስማማን፡፡ ባሌ ምን ቢሆንልኝ እንደምፈልግ ለብዙ ጊዜ አሰብኩበት፤ እርሱም አስቦበታል፡፡” This may work for temporary but to have permanent love, pray to God and please don’t waste your time by looking for other people fault. I don’t mean I undermined your idea but we don’t have to try to bring love without God. God is the foundation of my house. Kebede Tafesse from Addis Ababa and God bless Ethiopia.

  ReplyDelete
  Replies
  1. Thank you so much bro. God bless you.

   Delete
 8. እንደገና መጋባት፣ ጋብቻውን እንደገና ማደስ፣ ለአዲሱ ሰብእናሽ አዲስ ሐሳብ መፈለግ፣ አሁን ለደረስሽበት ነገር አዲስ ቃል ኪዳን መግባት ያስፈልጋችሁ ይሆናል፡፡ ትዳርሽ አርጅቶ ይሆናል፡፡ ትዳር ይፀነሳል፣ ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ያረጃል፣ ዝም ካሉትም ይሞታል፡፡ ጀግኖች ደግሞ እንዳያረጅና እንዳይሞት እንደ አዲስ ያድሱታል፡፡ አንቺም ትዳርሽ እንደ ንሥር አድሽ

  ReplyDelete
 9. Wey yetesebesebe dinch....! Tebetno kemiqer yishalewal ..........

  ReplyDelete
 10. Great view & Thankyou Dakon Dani.May God bless you and your family!

  ReplyDelete
 11. Thank you Daniyee !! it was interesting.keep the good work Boss man.

  ReplyDelete
 12. I was waiting to read the second part and guess what, wait worthy.

  ReplyDelete
 13. ለሕወታችን አስተማሪናጠቃሚ ነገር ነው ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡

  ReplyDelete
 14. ‹‹ለአንቺ ብቻ የሚቀጸሉ፣ለአንቺ ብቻ የሚውሉ፣ ለአንቺ ብቻ የሚነገሩ፣ ለአንቺ ብቻ የሚገለጡ፣ ለአንቺ ብቻ የሚደረጉ፣ ለአንቺ ብቻ የሚሰሙ የተለዩ ነገሮች ከሌሉ ምኑን ሚስት ሆንሺው፡፡››ችግሩ እዚህ ላይ ነው ፤ ለአንቺ (ለአንተ) ብቻ የሚሆን ባል (ሚስት) የለም እንዲያው እንደ እንስሳው ሁሉም ነገር የጋራ መገልገያ ነው የሆነው፡፡ ባልና ሚስት ድሮ ቀረ ተረተረት በድሮ ጊዜ መልካም ባልና ሚስት ነበሩ ሲኖሩ ሲነሩ እኛን ወለዱ ነው ነገሩ ዘመዴዋ አሁን ያሳዝናል ነገሩ ሁሉ ጭምልቅልቅ ብሏል፡፡ እንጃ ልጇቻችን ……

  ReplyDelete
 15. no words Dani u r talking about my life waw thank you

  ReplyDelete
 16. Thank you, Dn. Daniel, This is a touchy and reflection of the real life style of spouse relation ship. I can say every one of us goes through this cycle, Let's start to views towards our self and try to repaint from our mistake, respect our marriage relation ship, be loyal, sharing ideas, open for discussion, not to be fault finder ,love each others with the help of GOD.

  ReplyDelete
 17. ትዳርና አትክልት በየጊዜው ካልተከታተሉት አረም ይበቅልበታል፡፡ ሲብስም አትክልቱ ይጠፋና አረሙ መታየት ይጀምራል፡፡ ያኔ ነው እንጨት እንጨት የሚለው፡፡ ጎበዝ ሰው ቶሎ ብሎ ያርምና አትክልቱ እንዲያብብ ያደርገዋል፡፡ እንደገና መኮትኮት፣ እንደገና ማዳበሪያ ማድረግ፣ እንደገና አፈር መከለስ፣ እንደገና ውኃ ማጠጣት፣ እንደገና አጥር ማጠር ይጠይቅ ይሆናል፡፡ ድሮ አፈር አድርጌ ነበር፣ ማዳበሪያ ነበረው፣ አጠጥቼው ነበር፣ ኮትኩቼው ነበር አይሠራም ወዳጄ፡፡

  ReplyDelete
 18. ግሩም ጽሁፍ ነው፣ እንደዚህ አይነት ጽሁፎችን ማንበብ በጣም ጠቃሚ ነው፣ ነገር ግን አንድ ሰው ከዛሬ ጀምሮ ቅን መሆን አለብኝ፣ መልካም ስራ መስራት አለብኝ ብሎ ወስኖ ለመስራት ስለተነሳ ብቻ ማድረግ ይችላል እንዴ? አረ እኔ ብዙ አንብቤአለሁ፣ ካገኘሁት እውቀት ብዙ ሰውንም መክሬያለሁ ..መቼ ብልሀቱ ጠፋኝና! መተግበር ተሳነኝ እንጂ! ያለእኔ አንዳች ልታደርጉ አትችሉም አይደል ያለው አምላካችንስ? ሁሉም እግዚአብሄር ሲፈቅድ ነው የሚሆነው! መልካምን ነገር ማወቅ ብቻ ሳይሆን መፈጸምም እንድንችል እግዚአብሄር ሀይል ይስጠን፣ አምላክ እድሜና ጤና ይስጥልን ወንድማችን!!!

  ReplyDelete
  Replies
  1. ሁሌ በፈጣሪ ስር መደበቅ :'(

   እሱ የከፍተውን ጉሮሮ ፡ ሳይዘጋው አያድርም!

   ፈጣሪ ጭንቅላት የሰጠን ለጌጥ አይደለምኮ ፡፡ በዛ ላይ ጥረህ ግርህ እንጀራህን ብላት ብሏል፡፡
   በራሳችን ባንቀልድ ጥሩ ነው።

   Delete
 19. ትዳርና አትክልት በየጊዜው ካልተከታተሉት አረም ይበቅልበታል፡፡ ሲብስም አትክልቱ ይጠፋና አረሙ መታየት ይጀምራል፡፡ ያኔ ነው እንጨት እንጨት የሚለው፡፡ ወንድሜ ትክክለኛ አባባል ነው፡፡ እግዚአብሔር እድሜና ጤናውን አብዝቶ ይስጥህ፡፡

  ReplyDelete
 20. Is there any one who specifically elaborate 'መልካም ባል ለመሆን በመልካም ሰውነት ላይ ሊጨመሩ የሚገባቸው ሌሎች የባልነት ነገሮች አሉ፡፡ ' i am not clear with this statement
  thanks

  ReplyDelete
 21. ለሕወታችን አስተማሪናጠቃሚ ነገር ነው ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡

  ReplyDelete
 22. I will apply today and will tell for all of my friends now . . . Lovely idea

  ReplyDelete