Wednesday, December 31, 2014

ስለ ገና በዓል እና ጾም አንዳንድ ጥያቄዎች

 
(በብዙ አንባቢያን ጥያቄ በድጋሚ የታተመ)
 
የገና እና የጥምቀት በዓላት ሲደርሱ በምእመናኑ ዘወትር የሚጠየቁ ጥያቄዎች አሉ፡፡ እነዚህን እና መሰል የሕዝቡን የዘወትር ጥያቄዎች መልስ የያዘ የማያዳግም ጥራዝ ማውጣት ከሊቃውንት ጉባኤ የሚጠበቅ ነው፡፡ አብዛኞቹ ጉዳዮች አበው ቀድመው ሥርዓት የሠሩባቸው እና ማብራርያ ብቻ የሚያስፈልጋቸው ናቸውና፡፡ ለዛሬ ሦስቱን ብቻ እንመልስ፡፡

እንደ ሰው ወይስ እንደ እንስሳ

The Indian Folktales በተሰኝ ከዛሬ 100 ዓመት በፊት በ1919 እኤአ በታተመ መጽሐፍ ላይ እንዲህ ይላል፡፡
አንድ የሕንድ ጠቢብ ደቀ መዝሙሮቹን ሥራ እንዲሠሩ አዘዛቸውና ራቅ ብለው በከፍታ ቦታ ላይ ይመለከታቸው ጀመር፡፡ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ተመልሶ ደቀ መዝሙሮቹን ሰበሰባቸው፡፡ ከዚያም እንዲህ አላቸው ‹‹ከእናንተ መካከል የተወሰናችሁ እንደ ሰው የተወሰናችሁት ደግሞ እንደ እንስሳ ስትሠሩ ነበር›› ተማሪዎቹም ተገርመው ጠየቁት፡፡ መምህሩም ‹‹እንደ እንስሳ መሥራት ማለት አንድን ነገር መጎተት፣ መሸከም፣ መግፋት፣ ማዞር ወይም የሚደርስበት ቦታ ማድረስ ማለት ነው፡፡ ምን እየሠራ እንደሆነ፣ ለምን እየሠራ እንደሆነ፣ የሚመጣው ውጤት ምን እንደሆነ፣ ዓላማው ምን እንደሆነ አያስብም፡፡ በሥራው ላይም ከራሱ አስቦ አንዳች አይጨምርም፡፡ የዛሬ ሺ ዓመት አንድ ዝሆን የሠራውን ዛሬም ሌላ ዝሆን በተመሳሳይ መልኩ ይሠራዋል፡፡(አንድ ሊቅ ‹ዕብደት ማለት አንድ ውጤት እንደማያመጣ እየታወቀ በተደጋጋሚ መሥራት ነው› ብሎ ነበር) አያሻሽለውም፡፡ ምናልባት ከሰው በላይ ተሸክሞ፣ ስቦ፣ ገፍቶ፣ ቆፍሮ፣ ሮጦ፣ ደክሞ፣ ይሆናል፡፡ ያ ግን እንስሳውን ጠንካራ ያስብለዋል እንጂ ጎበዝ አያስብለውም፡፡ጉብዝና አእምሮ አለበት፡፡ እንደ እንደስሳ የሚሠሩ ሰዎች እንጂ እንደ ሰዎች የሚሠሩ እንስሳት የሉም የተባለውም ለዚህ ነው፡፡ 

Tuesday, December 30, 2014

በልዩ ቅናሽ የመጻሕፍት ሽያጭ ወር

ጥር
በልዩ ቅናሽ የመጻሕፍት ሽያጭ ወር
አግዮስ ኅትመትና ጠቅላላ ንግድ ሥራ ሐላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ያሳተማቸውን
የዲያቆን ዳንኤል ክብረትና የሌሎችንም መጻሕፍት፤ የንባብ ባህላችንን ለማሳደግ እና አንባብያንን ለማበረታታት፤ ከ25% እስከ 50% (ከሃያ አምስት እስከ ሃምሣ በመቶ) ቅናሽ በማድረግ፤

ከጥር 1 እስከ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ባሉት ቀናት ውስጥ ለአንድ ወር

የሚቆይ ልዩ የመጻሕፍት ቅናሽ ሽያጭ መርሐ ግብር አዘጋጅቷል፡፡

ቦታ፡- አግዮስ መጻሕፍት መደብር

አድራሻ፡- መገናኛ ለም ሆቴል አጠገብ፣ ማትያስ ሕንፃ ምድር ቤት (G – 06)
             ስልክ ቁጥር፡- 011 663 9902 / 0930098254

በተለይ ‹አራቱ ኃያላንን ላልገዛችሁ ይኼ መልካም አጋጣሚ ነው

የትልቁ ዋርካ ትልቁ ቅርንጫፍ
ታኅሣሥ 19 ቀን 2007 ዓም በቤተ ክርስቲያን ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ከታወቁት ሊቃውንት መካከል አንዱን አጥተናል፡፡ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታየን፡፡ ስለ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በመቆርቆር፣ በማስተማርና በመጻፍ የምናውቃቸው፤ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከጫፍ እስከ ጫፍ ያገለገሉ፤ በተለይም ለወጣቱ ትውልድ ጥያቄዎቹን በመመለስና አስረግጠውም በማስረዳት የምናደንቃቸው ነበሩ፡፡
ዜማ፣ አቋቋም፣ የአማርኛ ሰዋስው፣ ቅኔና የግእዝ አገባብ፣ ብሉይ፣ ሐዲስ፣ ነገረ መለኮት፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ በዘመናዊ ትምህርት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የተማሩ መሆናቸውን ስናይ፤ በአንባቢነታቸው ጥንታውያንና ዘመናውያን መጻሕፍትን የሚያገላብጡ ብቻ ሳይሆኑ በላዔ መጻሕፍት እንደነበሩ በሌሎቹ ሊቃውንት ሲመሰከርላቸው፤ በምሥራች ድምጽ ሬዲዮ ትምህርት በመስጠት፣ በታሪክና ድርሰት ክፍል ለዐሥር ዓመታት በማገልገል፤ የመዝሙር ክፍልን በመምራት፣ የዜና ቤተ ክርስቲያንን በምክትልና በዋና አዘጋጅነት  በማገልገል፣ እንዲያውም ጋዜጣውን የጋዜጣ መልክ በማስያዛቸው በ1962 ዓም መሸለማቸውን  እያዘከርን የተጓዙበትን የዕውቀት ጎዳና ስንመረምር ያጣነው አንድ ሰው ብቻ ባለመሆኑ፡-
አራት ሰው ሞተ ተቀበረ ዛሬ
ድጓ ጾመ ድጓ መዋሥዕት ዝማሬ
ተብሎ ለሊቁ የተገጠመው ሙሾ ለእርሳቸውም ይስማማቸዋል እንላለን፡፡ 

Friday, December 26, 2014

ብልጽግናና ባሕል


መንገድ አቋርጣለሁ፡፡ በእግሬ፡፡ ሁለት ጎልማሶች በመንገዱ ማቋረጫ ላይ ተገናኙ፡፡ ከሁለት አንዳቸው ቀድመው ወይም ተከትለው ማለፍ አለባቸው፡፡ ሁለቱም ቆሙ፡፡ ከዚያም አንዱ ሌላኛው ቀድሞ ያልፍ ዘንድ ጋበዘ፤ የተጋበዘውም ጋባዡ  እንዲያልፍ ለመነ፡፡ ግብዣው ጥቂት ደቂቃዎች ፈጀ፡፡ እኛም ከኋላ ያለነው ትኅትናቸውን አድንቀን በትዕግሥት ቆምን፡፡ በመጨረሻ አንደኛው እያመሰገነ አለፈ፡፡ ሌላኛውም ‹ምን አይደል›› እያለ አሳልፎ አለፈ፡፡ 

ደግሞ ሄድኩኝ፤ እነሆም በአንድ መስቀለኛ የአስፋልት መንገድ ላይ ደረስኩ፡፡ መኪኖቹ ከአራቱም አቅጣጫ ይመጣሉ፡፡ ሁሉም ወደ መስቀለኛው መጋጠሚያ ይገባሉ፡፡ አራቱም በአንድ ጊዜ ለማለፍ ይሞክራሉ፡፡ ነገር ግን አይችሉምና የመኪኖቹ አፍንጫዎቻቸው ተፋጥጠው ይቆማሉ፡፡ ለማለፍ እንጂ ለማሳለፍ የሚጥር አላይም፡፡ አራቱም በመስኮት ብቅ ብለው ‹ወደ ኋላ በልልኝ ልለፍ› ይላሉ፡፡ እነርሱ ሲከራከሩ ሌሎች ባለመኪኖችም ይመጣሉ፡፡ እንደ ዘንዶ ተጣጥፈው በአራቱ መኪኖች መካከል ለማለፍ ይሞክራሉ፡፡ እነዚያ ቀድመው የመጡትም ይናደዱና ወደ ፊት ገፍተው መንገዱን ያጠባሉ፡፡ በዚህ የተነሣም እነዚያም ከኋላ የመጡት በተራቸው ይቆማሉ፡፡ ሁሉም ቀድሞ ለማለፍ በሚያደርገው ፍትጊያ ሁሉም ይቆማሉ፡፡ እለፍ፣ እለፍ ተባብሎ መገባበዝ የለም፡፡ 

Tuesday, December 9, 2014

ራትን ቁርስ ላይ

አፍሪካውያን ቀደምት አያቶቻችን እንዲህ የሚል ትንቢት አዘል አባባል ነበራቸው፡፡ ‹‹የዚህ ትውልድ ትልቁ አደጋ ራታቸውን በቁርስ ሰዓት ለመብላት መፈለጋቸው ነው››፡፡ ሰው እንደ መላእክት አይደለምና በሂደት እየበሰለ፣ በሂደት እየተገነባ፣ በሂደትም የበለጠ እየተማረ የሚሄድ ፍጡር ነው፡፡ ይኼ ደግሞ የመንፈስ፣ የአካል፣ የስሜትና የአእምሮ ዕድገትና ለውጥን ይጠይቃል፡፡ ሰው ሲወለድ ለማደግና ለመለወጥ ከሚያስችል ዐቅም ጋር ነው፡፡ ይህንን ዐቅም ተጠቅሞ ለማደግና ለመለወጥ ግን ልምድ፣ ትምህርትና የሰውነት ግንባታ ያስፈልጉታል፡፡ ልምድ የሚባለው ከተወለደ ጊዜ ጀምሮ በሕይወት ውጣ ውረድ የሚደርስበት ተሞክሮ ነው፡፡ ይህም የሕይወት ተጋድሎ ይባላል፡፡ ትምህርት ከሰዎች፣ ከትምህርት ቤት፣ ከመጻሕፍት፣ ከአካባቢውና ከሌሎችም የዕውቀት ምንጮች የሚያገኘው ጥበብ ነው፡፡ የሰውነት ግንባታ የሚባለው ደግሞ በምግብና በእንቅስቃሴ የሚያበለጽገውን አካል ነው፡፡

እነዚህ ነገሮች የሚመጡትና የሚከናወኑት በሂደት ውስጥ በመሆኑ ሰዎች ለተለያዩ የኑሮ ደረጃዎች የሚበቁበት ጊዜ ይለያያል፡፡ በልጅነት፣ በወጣትነት፣ በዐዋቂነትና በአረጋዊነት ጊዜ የሚከናወኑት ተግባራት በዚያው በየዘመናቸው እንዲከናወኑ የሚያስገድዱት ሰዎች እነዚህን ነገሮች ለማከናወን የብስለታቸው ደረጃ እንደ ዕድሜያቸውና በዚያ ዕድሜ የተነሣ እንደሚያገኙት ልምድና ዕውቀት ብሎም አካላዊ ዝግጁነት ስለሚለያይ ነው፡፡ የልጆች ጋብቻንና የልጅነት ጊዜ ወሊድን የምንቃወመው፣ ጋብቻም ሆነ ወላጅነት የሚፈልጓቸው የመንፈስ፣ የአካል፣ የስሜትና የአእምሮ የዕድገት ደረጃዎች ስላሉ ነው፡፡

Tuesday, December 2, 2014

የተሰበሰበ ድንች (ካለፈው የቀጠለ)
እኔና ባለቤቴ ልክ እንዳንቺ ሆነን ነበር፡፡ ነገራችን ሁሉ ችኮ ሆኖ፡፡ ያ ድሮ እንደ መልካም ሙዚቃ ጆሮሽን አዘንብለሽ የምትሰሚው የባልሽ ድምጽ ፍሬን እንደያዘ መኪና ድምጽ ሲሆንብሽ ይሰማሻል፡፡ ይናፍቅሽ የነበረው ድምጽ ሲደውል ሐሳብ ውስጥ ይጥልሻል፡፡ ደግሞ ምን ሊል ይሆን? ትያለሽ፡፡ ስልክ ከማንሳት ይልቅ ስልኩን ለመዝጋት ትቸኩያለሽ፡፡ ለመሆኑ ባል ማለት ምንድን ነው? ለእኔ ከባልሽ ጋር ብቻ የምታደርጊያቸው ነገሮች ስላሉ ነው፡፡ ከእርሱ ጋር ብቻ የምትቀልጃቸው፣ ከእርሱ ጋር ብቻ የምታወሪያቸው፣ ከእርሱ ጋር ብቻ የምትሠሪያቸው፣ ከእርሱ ጋር ብቻ የምትወስኛቸው፣ ከእርሱ ጋር ብቻ የምትባልጊያቸው፣ ከእርሱ ጋር ብቻ የምታኮርፊያቸው፡፡