Friday, September 12, 2014

ሰነቦ

ነሐሴ 23 ቀን 2006 ዓም ማለዳ 10 ሰዓት ነው ከዕንቅልፌ የነቃሁት፡፡ ዲያቆን  ሙሉቀን ብርሃን ከጎንደር፣ ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ ከፍኖተ ሰላም መንገድ ላይ ይጠብቁኛል፡፡ ለመንገዱ የሚሆነውን የቱሪስት መኪና ያዘጋጀልኝ የኦሪጂንስ ኢትዮጵያ አስጎብኝ ድርጅት ባለቤት ሳምሶን ተሾመ ነው፡፡ ክብር ይስጥልኝ ብያለሁ፡፡ የምተርክላችሁን ታሪክ ስትጨርሱ ትመርቁታላችሁ ብየ አምናለሁ፡፡ የምጓዘው አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ ለማደርገው ጥናት ተጨማሪ መረጃዎችን ፍለጋ ነው፡፡
ሾፌራችን ደምስ ይባላል፡፡ ዝምታና ትኩረት ገንዘቦቹ የሆኑ፣ በሁሉም ነገር ለመንገድ የተዘጋጀ፡፡ ለተራራ ቢሉ ለቁልቁለት፣ ለበረሐ ቢባል ለደጋ የሚሆኑ መሣሪያዎችን ሸክፎ የያዘ ልምድ ያለው ሾፌር ነው፡፡


ዓባይ በረሐ መግቢያ ላይ
የምንጓዘው ከምድር ሥር ከሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎቻችን ወደ አንዱ ነው፡፡ በጎጃም በር በኩል ወጥተን ፍቼና ጎሐ ጽዮንን አቋርጠን በክረምት ውበቱ እጥፍ ድርብ ወደሚሆነው ዓባይ በረሐ መንደርደር ቀጥለናል፡፡ ዓባይ በረሐ የሚባል ቦታ መቼም አያልፍለት፡፡ አበሻ ቢሠራው፣ ጣልያን ቢሠራው፣ ጃፓን ቢሠራው መሬቱ እንደሆነ ድንጋይ ላይ እንዳስቀመጡት ሰው ሲንቀሳቀስ ይኖራል፡፡
ይንሸራተታል ተጠንቀቁ
ተሻገርንና ደጀንን አለፍናት፡፡ ከደጀን እስከ ደብረ ማርቆስ ያለው መንገድ በመሠራት ላይ ስለሆነ መኪኖቹን ሁሉ ለአካባቢው መንደሮች እጅ ሲያስነሣቸው ይውላል፡፡ አንዳንዱን መንገድ እንኳን መኪና ዝንጀሮም ያለ ስዕለት የሚወጣው አይመስልም፡፡ በግራ በቀኝ ሽው እልም እያሉ የሚከንፉት መኪኖች ሁሉ መዘጋጃ ቤት እንደ ረሳው ጎዳና በተቆፋፈረው መንገድ ላይ ሲደርሱ ለቆጠራ እንደወጣ እሥረኛ ሰልፍ ይይዛሉ፡፡ 
እኛም ስንችል ስንበር፣ ሳንችል ስንሰለፍ ደብረ ማርቆስን አልፈን ወደ ደምበጫ ማቅናቱን ተያያዝነው፡፡ ሙሉቀንና ስምዐ ኮነ ከአዲስ አበባ 360 ኪሎ ሜትር ርቀት ደምበጫ ላይ ነው የሚጠብቁን፡፡ እነርሱን ከምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት የቅርሳ ቅርስ ክፍል ኃላፊና ከደጋ ዳሞት ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ጋር አሳፍረን የባሕርዳርን መንገድ ትተን ወደ ቀኝ በመታጠፍ የፈረስ ቤትን መንገድ ተያያዝነው፡፡
ሰቀላ ማርያም ደን
ከፊት ለፊታችን የሰቀላ ማርያም ደን ጫፍና ጫፉን ገጥሞ በመካከሉ ሲያሳልፈን ሙሽራ ለመቀበል የወጣ የአዲስ አበባ ሚዜ ይመስል ነበር፡፡ በአንጀኒን በኩል አለፍንና ሰነቦ ተራራው ላይ ደረስን፡፡ መቼም የፈረስ ቤት የጠጠር መንገድ ከአንዳንዱ የአዲስ አበባ አስፓልት ይመረጣል፡፡ በስተግራችን ተራራውን ተደግፈን፤ በስተ ቀኛችን በረሐውን እያማተርን መኪናችንን ከአካባቢው ፖሊስ መጠበቂያ ጎን አቆምናት፡፡

አሁን ከባዱ መንገድ ሊመጣ ነው፡፡ የምንወርደው ከምድር ሥር ወደ ታች ነው፡፡ በተራራው ወገብ እየታከክን፣ እንደ ዝንጀሮ ተንሸራትተን እንደ ጦጣ እየዘለልን መጓዝ ይጠበቅብናል፡፡ ዕቃዎቻችንን ሁሉ ሸከፍንና የማይቀረውን ቁልቁለት ተያያዝነው፡፡ ለጉልበት ፋታ የማይሰጠው ቁልቁለት መቅኔያችን ያለቀ እስኪመስለን ድረስ ያንተፋትፈናል፡፡ የገበሬዎችን እርሻና መንደር እያቆራረጥን፣ ወንዝና ገደሉን እየተሻገርን የተራራውን ሥር ለማግኘት እንኳትናለን፡፡
ውረድ- ወደ ሰነቦ
የተራራውን ወገብ ካለፍን በኋላ ዓለምን ተሰናብተናት ዓለምን ወደረሳና ዓለምም ወደረሳችው ክልል ወረድን፡፡ በጫካ የተሞላ፣ የፏፏቴ ድምጽ ከሩቅ የሚጣራበት፣ ወፎቹ በተሲዓት የሚዘምሩበት፣ የፋርስ ምንጣፍ የተነጠፈበት የሚመስል ሸለቆ ተቀበለን፡፡ እስካሁን ዋሻውን አላገኘነውም፡፡
ወደ ቀኝ ታጥፈን አንዲት ጅረት መሰል ውኃ ከተሻገርን በኋላ የግቢው መግቢያ በር ጋ ደረስን፡፡ ጭንቁ እዚህ ላይ ይጀምራል፡፡ እኔ ለራሴ ቁልቁለቱን ለመውረድ እንደ ቅቤ ቅል ስናጥ ስለቆየሁ ጉልበቴና እግሬ ተለያይተው ለየብቻ የሚሄዱ መምሰል ጀምረዋል፡፡ እዚህ ደግሞ ለከተማ ሰው የከበደ ቀኖና ጠበቀን፡፡ ከገዳሙ ክልል መግቢያ ጀምሮ በባዶ እግር ነው የሚገባው፡፡ ፊት ለፊት የማያቸው ደንጋዮች ሆያ ሆዬ እንደሚሉ ልጆች እጅብ እጅብ ብለው ቆመው፣ እንደ ፋስ መጥረቢያ የተሳሉ ናቸው፡፡ አንድ እግሬን የመግቢያው ርብራብ ላይ አሳርፌ ሁለተኛውን የት ላድርገው፡፡ በግራ በቀኝ የማያቸው ድንጋዮች እንደ ጥሬ ሥጋ ቆራጭ ቢላዋቸውን አሹለው ይጠብቁኛል፡፡ በብኾር ላይ ቆረቆር እንዲሉ ከተራራው ላይ ባለማቋረጥ የሚወርደው ውኃ አካባቢውን ስላራሰው እግሬ በብርዱ ወደ መደንዘዝ ደርሷል፡፡

መጨነቄን ያየው የቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪ የሆነው የዐቢ እንደ አቡነ ገሪማ አገልጋይ በግራ ጎኔ በኩል መጥቶ ደገፍ አደረገኝ፡፡ አይቀርምና እግሬን ወደ አንዱ ሹል ባልጩት ሰደድኩት፡፡ የእግሬ ድንዛዜና የባልጩቱ ስለት ተባብረው ዋጋዬን ሰጡኝ፡፡ ድምጽ እንደሰማች ዕንቁራሪት ዘልዬ ወደ ሌላው ድንጋይ ተሻገርኩ፤ እርሱም እንደ ጓደኞቹ በጠረባ አወራረደኝ፡፡ የዐቢ እየደገፈኝ፣ እኔ ጥርሴን ነክሼ እየዘለልኩ የውኃው ድምጽ እንደ ነጎድጓድ ከሚያስገመግምበት ሥፍራ ደረስን፡፡ ሰነቦ ተክለ ሃይማኖት፡፡

ጠበሉ ከቤተ ክርስቲያኑ በላይ ካለው ተራራ ላይ ነው የሚወርደው፡፡ በሦስት ቦታ ተጠማቂዎቹ ይገለገላሉ፡፡ ለሴቶች፣ ለወንዶችና ለካህናት የተዘጋጁ ናቸው፡፡ በሌሎች የመጠመቂያ ቦታዎች ለካህናት የተዘጋጀ የተለየ ቦታ አልገጠመኝም፡፡ በዚህ ሰነቦዎች ይመሰገናሉ፡፡ የቤተ መቅደሱ በር ከተራራው ሥር ይታያል፡፡ ዋሻው ግራና ቀኝ ተገንብቶ በበር ተዘግቷል፡፡ በስተ ግራ በኩል የካህናት መግቢያ ሌላ ሰርጥ አለ፡፡ ዋናው በር ተከፈተልንና ገባን፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ስትገቡ በስተግራ ይገኛል፡፡ መጀመሪያ ቅኔ ማኅሌቱን፣ በእንጨት በተከለለው ሥፍራ ደግሞ መቅደሱን የዋሻው ውስጥ ደግሞ ቅድስቱን ታገኛላችሁ፡፡ 
የመቅደሱ ግንብ
ከቤተ ክርስቲያኑ በስተ ቀኝ ማለቂያው የማይታወቅ የዋሻ  ውስጥ መንገድ ይገኛል፡፡ ያውም መንገዱ በውኃ የተሞላ ነው፡፡ አንዳንድ አገልጋዮች የአራት ሰዓት መንገድ ተጉዘው መጨረሻውን ሊያገኙት እንዳልቻሉ ገልጠውልናል፡፡ እንደ አካባቢው ቃላዊ ታሪክ ከሆነ ዋሻው ከደብረ ሊባኖስ ጋር ይገናኛል፡፡ ገዳሙ ‹ሰነቦ ደብረ ሊባኖስ ተክለ ሃይማኖት ገዳም› የተባለውም ለዚህ ነው ይላሉ፡፡
የገዳሙን የምሥረታ ጊዜ በትክክል ለማወቅ አልቻልኩም፡፡ አገልጋዮቹ ከሚተርኩት ትረካና በትረካቸው ውስጥ ከሚጠሯቸው ሰዎች ስንነሣ ግን ከግራኝ ዘመን ቀደም ብሎ የተተከለ መሆኑን ለመገመት ይቻላል፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታ የተተከለው በአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን(1674-1698ዓም) መሆኑን አንዳንድ የገዳሙ መዛግብት ያሳያሉ፡፡ አድያም ሰገድ ኢያሱ በዚህ ዋሻ ውስጥ አንድ መነኩሴ ጽላት እንደያዙ መስቀል ጨብጠው ዐጽማቸው እንደሚገኝ የሰሙትን ለማረጋገጥ ከጎንደር ተነሥተው መጡ፡፡ ሲመጡም የሰሙት ትክክል መሆኑን አዩ፡፡ ገዳሙን ገድመው፣ ርስት ሰጥተው አከበሩት፡፡ በወቅቱ 500 መነኮሳት ነበሩት(300 ወንዶችና 200 ሴቶች)፡፡
ወደ ዋሻው በዐለት ፍላጭ ላይ ጉዞ
አድያም ሰገድ ኢያሱ ያሠሩት የቤተ መቅደሱ ግንብ ፍርስራሹ አሁንም ይታያል፡፡ የመንበሩን ሥዕል ያሠሩት ወ/ሮ መለኮታዊት (ያረፉት በ1618 ዓም ነው) መሆናቸውን የገዳሙ ካህናት ይገልጣሉ፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የገዳሙ ትክል ከአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን ቀደም ይላል ማለት ነው፡፡ ወ/ሮ መለኮታዊት የነበሩት በዐፄ ሱስንዮስ ዘመን ነው፡፡ ካልሆነ ደግሞ በዐፄ ቴዎፍሎስ ዘመን የነበሩትና በ1701 ያረፉት መለኮታዊት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በአንዳንዱ የገዳሙ መጻሕፍት ላይ ከዐፄ ፋሲል የተሰጠ መሆኑን ስለሚገልጥ ታሪኩ ከአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን ቀደም ያለ መሆኑን ያሳየናል፡፡
የዋሻው ውስጥ መንገድ
ምሽቱን የአካባቢው ሕዝብ ከዝናብና ጭቃ ጋር እየታገለ ለክብረ በዓሉ ሲጎርፍ ነው ያመሸው፡፡ ያች ዋሻ ከአፍ እስከ ገደፏ ሞላች፡፡ ማኅሌቱ ሌሊቱን በሙሉ ከዋሻው ሲሰማ አደረ፡፡ ቅዳሴውን ያስቀደስነው ከታች ካለው ቅዝቃዜና ከጎን ከሚመጣው ብርድ ጋር እየታገልን ነው፡፡ ፈውስ ፍለጋ ከየቦታው የመጡት ሕሙማን እንደ ሰሊሆም መጠመቂያ ማለዳውን ይጠብቃሉ፡፡ ቅዳሴው እንዳለቀ የሚጀመረውን የዋሻ ውስጥ ጥምቀት፡፡
የሌሊት ማኅሌት
ቅዳሴው አብቅቶ ትምህርት ከተሰጠ በኋላ ለደመራ የሚበራውን ችቦ የሚያስንቁ አራት አምስት ችቦዎች በርተው መጡ፡፡ ሕዝቡም ወደ ዋሻው መንገድ ተሰባሰበ፡፡ ከግራ ከቀኝ በአገልጋዮች ተደግፌ ከተሳሉት የዋሻ ውስጥ ድንጋዮች ላይ እግሬን እያሳረፍኩ፣ በብርዱ የደነዘዘውን እግሬንም ትቼው የመጣሁ እስኪመስለኝ እየረሳሁ ከካህናቱ ጋር ወደ ዋሻው ውሳጣዊ ክፍል ገባን፡፡ በዐለቶች ላይ እንደ ጦጣ ተንጠላጥለን የጠበሉ ጫፍ ላይ ደረስን፡፡
ይህ አሁን ከፊታችን የሚታየው ጠበሉ ነው፡፡ ተጠማቂው ወገቡን በገመድ ይታሠርና ወደ ጠበሉ ይገባል፡፡ ወገቡን የሚታሠረው የዋሻው ጥልቀት ስለማይታወቅ ነው፡፡ አንድ ሰው አራት ሸንበቆ ተቀጣጥሎ ወለሉን እንዳልደረሰበት ነግረውኛል፡፡ በኋላ እንደገመትነው ጥልቀቱ ከ20 ሜትር በላይ ነው ማለት ነው፡፡ ጥልቀቱ ብቻ ሳይሆን የዋሻው መጨረሻም አይታወቅም፡፡ ቆርጦ ከሄደ መመለሻውን እንጃ፡፡ ‹ተክልየ ነው የሚይዙት›› ብለውኛል፡፡ እውነትም፡፡
በጨለማው ውስጥ ወደ ጠበሉ ጉዞ
ካህኑ መስቀል ይዘው እያጠኑ መጡ፡፡ ተጠማቂውም እየጮኸ ወገቡን በገመድ ታሥሮ ቀረበ፡፡ እርሳቸው ወደ ጠበሉ ዳር ገቡና ተጠማቂውን ጠሩት፡፡ ገባ፡፡ ታሪክ ተጀመረ፡፡ መስቀል ከመያዝና ጸሎት ከመድገም በቀር ካህኑ ምንም አላደረጉትም፡፡ እርሱ ግን መናገር ጀመረ፡፡ የተደረገበትን፣ ማን መድኃኒት እንዳደረገበት፣ ለምን እንዳደረገበት፣ ይለፈልፍ ጀመር፡፡ በአራት ጎረምሶች ተይዞ የገባው ጎልማሳ ኅሊናው ተመልሶለት ራሱ ከጠበሉ ወጣ፡፡ እንዲህ እያለ አንድ ሦስት ሰው ተጠመቀ፡፡
ካህኑ ወደ ጠበሉ ሲገቡ
ካህኑ በቃ አሉ፡፡ እንደሰማነው በወር አንድ ወይም ሁለት ቀን ወደ ዋሻው ጠበል ይገባል፡፡ እዚያ ገብቶ ሳይድን የሚወጣ የለም፡፡ ሕሙማኑም እነዚያን ሁለትና ሦስት ቀናት በተስፋ ነው የሚጠብቋቸው፡፡
በውኃው ላይ ወደ ጠበሉ ጉዞ
ከአንድ ሰዓት በኋላ ከዋሻው ወጣን፡፡ እኔም ከሹሉ ድንጋይ ላይ ዝናብ፣ ብርድና ጭቃ ተጨምረውበት እየዘለልኩና እየተደገፍኩ የገዳሙን ክልል ለቅቀን ወጣን፡፡ ወደ ማረፊያችን ገብተን ምሳ ከበላን በኋላ ከጫማችን ጋር ተገናኘን፡፡ ለካስ ጫማም ይናፍቃል፡፡

ተጠማቂው በገመድ ታሥሮ ወደ ጠበሉ ኩሬ ሲገባ
ስንመጣ ቁልቁል ያየነውን አሁን ቀና ብለን ልናየው ነው፡፡ በትናንቱ መንገድ ላይ ዝናብና ጭቃ ተጨምሮበታል፡፡  የጫማዬ መልክና ቁመና ጠፍቶ ከተራራው ጋር እየታገልኩ መውጣት ቀጠልኩ፡፡ አንድ ጎኔን የዐቢ ደግፎኝ በአንድ እጄ መቋሚያ ይዣለሁ፡፡ የተጎረዱ መሬቶችን መዝለል፣ በጭቃው ተንሸራትቶ ወደ ኋላ መመለስ፣ ከፊት ለፊት እንደ ጅብራ የተገተረ ተራራን ማየት እንዴት አድካሚ መሰላችሁ፡፡ 
ተራራውን ከታች ወደ ላይ ሲያዩት
ይባስ ብለው ሙሉቀንና ስምዐ ኮነ እየጣሉኝ ወደ ተራራው ጫፍ መድረሳቸውን ሳይ የምደርስ አልመስልህ አለኝ፡፡ የዐቢ እኔን ደግፎ ተራራውን ለመውጣት ይፈጋል፡፡ የወረዳው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና የአካባቢው ካህናት ‹በርታ በርታ› ይላሉ፡፡ አሳብ የለሽ ሀብታሙ ደግሞ ከጎኔ ሆኖ ‹ምክርና ቡጢ ለሰጭው ይቀላል› ይላል፡፡ ልቤ እንደ ጾም ፍርፍር ፍርስ ልትል ነው፡፡

በተስፋ፣ ከታች ወደ ላይ
ተመስገን የተራራው መጨረሻ ላይ ደረስኩ፡፡ የቀደሙኝን ሁሉ መንገዱ ዳር መኪናው ጋ አገኘኋቸው፡፡ ጫማየን አውልቄ በፌስታል ጠቅልየ መኪናው ላይ ጣልኩት፡፡ ከዚያም ወደ ኋላ ተመልሼ የመጣነውን ተራራ አየሁት፡፡ 
ሸለቆው ከሩቁ
ድካሙ ሲቀነስ ውበቱ አሁንም አለ፡፡ ከእኔ እናንተ ትበረታላችሁና ሰነቦን እዩት፡፡ በተለይ ከአኩስምና ላሊበላ በጎንደርና ባሕርዳር በኩል የምትመጡ ተጓዦች ጎራ ብትሉ ቅርብ ነው፡፡ ሌሎቻችሁም ዛሬ ሄዳችሁ ነገ መምጣት ትችላላችሁና ተነሥታችሁ ሂዱ፡፡ ውጣ ውረዱ ራሱ እንዴት ልዩ ትዝታና በረከት መሰላችሁ፡፡ ደኅና እንሰንብት፡፡
ተራራው ላይ ደረስን

63 comments:

 1. Thank you so much Dani, I never heard this place before. I love it the way present. Espacially the photo section was fabilous. God bless you and your family.

  ReplyDelete
 2. Beye ametu wode gedamu yemiderge guzo ale ?

  ReplyDelete
 3. በጣም ነው የጓጓሁት ዳኒ እግዚአብሔር ሲፈቅድ አየወዋለሁ፡፡ አንተንም እግዚአብሔር ይባርክህ የማናውቀውን ቦታ እና ታሪካችንን እያሳወከን ነው፡፡

  ReplyDelete
 4. God bless u Dn Dani........nice diary and very interesting......and am glad to be there.

  ReplyDelete
 5. ቃለ ህይወት ያሠማልን

  ReplyDelete
 6. Dani, lemehedm eko memeret yasfelgal! fetari hulachininm yifkedilin!!!!

  ReplyDelete
  Replies
  1. Amennnnnnnnnnnnn!!!!!!!!!!!!!!!!!

   Delete
 7. very interesting story and place !!!

  ReplyDelete
 8. ካህኑ መስቀል ይዘው እያጠኑ መጡ፡፡ ተጠማቂውም እየጮኸ ወገቡን በገመድ ታሥሮ ቀረበ፡፡ እርሳቸው ወደ ጠበሉ ዳር ገቡና ተጠማቂውን ጠሩት፡፡ ገባ፡፡ ታሪክ ተጀመረ፡፡ መስቀል ከመያዝና ጸሎት ከመድገም በቀር ካህኑ ምንም አላደረጉትም፡፡ እርሱ ግን መናገር ጀመረ፡፡ የተደረገበትን፣ ማን መድኃኒት እንዳደረገበት፣ ለምን እንዳደረገበት፣ ይለፈልፍ ጀመር፡፡ በአራት ጎረምሶች ተይዞ የገባው ጎልማሳ ኅሊናው ተመልሶለት ራሱ ከጠበሉ ወጣ፡፡ እንዲህ እያለ አንድ ሦስት ሰው ተጠመቀ፡፡

  ReplyDelete
 9. Thank you D.Daniel you are trying to help us know that we don't know ,at this point I really didn't get what you want to say.

  ReplyDelete
  Replies
  1. He introduced us this church because it is not famous. I has more than 400 years age but most people don't know the church. If still don't understand please post me, your phone and I will explain to you. Meskerem from Doro Mankiya Sefer.

   Delete
 10. amazing god belss you!

  ReplyDelete
 11. enteresting story&place.GOD bless you deacon Daniel.

  ReplyDelete
 12. Yemetemekiyawen Ken mawok Yichalal? kehedu ayker endenetemek.
  God bless you!

  ReplyDelete
 13. Betam guaguchakehu. Egziabher yisitilin.

  ReplyDelete
 14. ዲ.ን ዳኒኤል አብሬህ የተጓዝኩ ያህል ነው የደከመኝ ' ደስምያለኝ ፡፡ ያንተ እግሮችህ መቆምና መራመድ ሲያቅታቸው እኔም በሃሳብ ደከመኝ ለማየት በረከቱን ለመካፈል ጓጓሁ ዳኒ ጡሩ የጉዞ ማስታዎሻ ነው ፡፡ አነተ በአካል ጎብኝተህ/ተጉዘህ እኛንም በማስታወሻህ አኩል አስጎበኸን፡፡ ጥናትህንም እሱ ሰመያዊ ሚስጢር ግለጦ ያናግርህ ፡፡ የተክለሃየማኖት ፀሎትና በረከት ለሁላችንም ይድረሰን ቃለ ህይወትን ያሰማልን ' በድሜ በፀጋ ይጠብቅልን 'በአገልግሎትህ ያጥናልን አሜን ፡፡

  ReplyDelete
 15. ቃለ ሕይወት ያሰማልን ዳኒ
  ሰነቦን በ1982 ዓ.ም. አካባቢ አንጀኒ አፈር ጥበቃ ምርምር ፕሮጀክት ሥሰራ አውቀዋለሁ። ያን ጊዜ እኔ ወደዚያ ቦታ ስሄድ በዓፄ ሚኒሊክ ማኅተም ከጂማ ተ/ሃይማኖት የተበረከተ የብራና ስንክሳር ከሌላ ታላቅ የብራና መጽሐፍ ጋር በተሰረቀ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተአምራት ከብቸና ተይዞ ሲገባ ደርሼ ስደነቅ በወቅቱ እዚያ ያገኘኋቸው አንድ ሰው ደግሞ ቀደም ሲል ታቦቱም ተሰርቆ በሳምንቱ ሰራቂውን አባይን አላሻግር ብሎ ወደፊት ለመሄድ አቅቶት ወደኋላ መልሶ ካህናቱ ለምዕመናኑ ምን እንደሚሉ ግራ ተጋብተው ሳሉ ሌባው ተሸክሞ አንደደረሰና እንደተናዘዘ ታቦተ ህጉም ወደ መቅደሱ የገባበትን ተአምራት አጫውተውኛል።
  ቃለ ሕይወት ያሰማልን ዳኒ
  ሰነቦን በ1982 ዓ.ም. አካባቢ አንጀኒ አፈር ጥበቃ ምርምር ፕሮጀክት ሥሰራ አውቀዋለሁ። ያን ጊዜ እኔ ወደዚያ ቦታ ስሄድ በዓፄ ሚኒሊክ ማኅተም ከጂማ ተ/ሃይማኖት የተበረከተ የብራና ስንክሳር ከሌላ ታላቅ የብራና መጽሐፍ ጋር በተሰረቀ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተአምራት ከብቸና ተይዞ ሲገባ ደርሼ ስደነቅ በወቅቱ እዚያ ያገኘኋቸው አንድ ሰው ደግሞ ቀደም ሲል ታቦቱም ተሰርቆ በሳምንቱ ሰራቂውን አባይን አላሻግር ብሎ ወደፊት ለመሄድ አቅቶት ወደኋላ መልሶ ካህናቱ ለምዕመናኑ ምን እንደሚሉ ግራ ተጋብተው ሳሉ ሌባው ተሸክሞ አንደደረሰና እንደተናዘዘ ታቦተ ህጉም ወደ መቅደሱ የገባበትን ተአምራት አጫውተውኛል።

  ዓለማየሁ ብርሃኑ ከአ.አ.

  ReplyDelete
 16. ገዳም መሄድ ለፅድቅ ከሚመስለው ሰው ጋር እየኖርን እንዲት እንየው ለበረከት መሆኑ ገና እስኪገባው ድረስ እግዚአብሄር ይመስገን ልባችንን ተራራ ላይ አውጥተህ እንደመለስከው ይቆጠራልና እናመሰግናለን

  ReplyDelete
  Replies
  1. I don't get it waht do you want to say? Are you menafk?

   Delete
  2. Yes he is menafik. Two thinking's in one mind or two tongs in one mouth

   Delete
 17. betam des yilalale kalehiwet yasemalen

  ReplyDelete
 18. betam new des yemilew kalehiwet yasemalen

  ReplyDelete
 19. የአባታችን በረከት በሁላችንም ላይ ይደርብን፡፡አሜን!!!

  ReplyDelete
 20. ውጣ ውረዱ ራሱ እንዴት ልዩ ትዝታና በረከት መሰላችሁ፡፡

  ReplyDelete
 21. tadiqu yebeletun yegeletsuleh Yetebaberunm hulu Amlak Tekle Hayimanot Abizitew yesetachew.

  ReplyDelete
 22. ዳን እውነት አንተ እግዚአብሔር ይወድሀል፡፡ ይህ የክርሳትናችን አንዱ ክፍል ነውና ያኮራናል፡፡እኛ ያላየነውን በምናባዊ እይታ በደንብ አስመልክተህናልና እግዚአብሔር ይባርክህ፡፡

  ReplyDelete
 23. እግዚኣብሔር በስራህ ሁሉ አይለይህ!

  ReplyDelete
 24. ዳኒ፡-ሰነቦ ተክለሃይማኖትን- ከ አስራ ሦስት ዓመታት በኋላ እንደገና ስላስታወስከኝ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ክረምት እንዲህ አንተ በሄድክበት ወቅት በጸመ-ፍልሰታ ጊዜ ለሁለት ሳምንታት ያህል ቆይቻለሁ፡፡ አዎ! ያ ቦታ ለእኔ አሁንም ሌላ ዓለም ነዉ፡፡ የከተማዉ ኑሮ ለሰለቸዉ ሰዉ፤ እንዲህ ዓይነት ቦታ መሄድ ምናልባትም የጠፋ ማንነታችንን ፈልገን ለማግኘት አቋራጭ መንገድ ይመስለኛል፡፡ እዉነት ነዉ ዳኒ ሁሉም ነገር እንዳልከዉ ነዉ፤ዳገትና ቁልቁለቱ እንዲህ ቀላል አይደለም፡፡ ዳኒ ዳገትና ቁልቁለቱ፤ቁርና ብርዱ እንዲህ ቢያስቸግርህም አንድ ቀን ግን ይህ ሁሉ ይናፍቅሀል፡፡ ያ ሁሉ ነገር አሁን ዛሬ ከአስራ ሦስት ዓመታት በኋላ ስታስታዉሰኝ ከምር ዉስጤን ሞረሞረኝ፤ሁሉ ነገር ዉል አለኝ፤በፍቅር ነደድኩኝ……….እፍፍፍፍፍ………የከተማ ኑሮ እንዲህም ይሰለቻል!!!

  ReplyDelete
 25. ዳኒ፡-ሰነቦ ተክለሃይማኖትን- ከ አስራ ሦስት ዓመታት በኋላ እንደገና ስላስታወስከኝ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ በጸመ-ፍልሰታ ጊዜ ለሁለት ሳምንታት ያህል ቆይቻለሁ፡፡የከተማዉ ኑሮ ለሰለቸዉ ሰዉ፤ እንዲህ ዓይነት ቦታ መሄድ ምናልባትም የጠፋ ማንነታችንን ፈልገን ለማግኘት አቋራጭ መንገድ ይመስለኛል፡፡ ያ ሁሉ ነገር አሁን ዛሬ ከአስራ ሦስት ዓመታት በኋላ ስታስታዉሰኝ ከምር ዉስጤን ሞረሞረኝ፤ሁሉ ነገር ዉል አለኝ፤በፍቅር ነደድኩኝ……….እፍፍፍፍፍ………የከተማ ኑሮ እንዲህም ይሰለቻል!!!

  ReplyDelete
 26. ዲ/ን ዳንኤል እግዚአብሔር ከመላው ቤተሰብ ጋር ረጅም እድሜ እና ጤና ይስጣችሁ እኔ በበኩሌ የማላውቀውን ታሪክ ነው ያስተማርከኝ/ያስጎበኘኸኝ/ የተክልዬ በረከት በሁላችንም ላይ ይደርብን!!
  እግዚአብሔር ጉልበትህን ይባርክ!!
  እግዚአብሔር ይስጥልን!!

  ReplyDelete
 27. እፍፍፍፍፍ………የከተማ ኑሮ እንዲህም ይሰለቻል!!!

  ReplyDelete
 28. ...ዓለምን ወደረሳና ዓለምም ወደረሳችው ክልል ...

  ReplyDelete
 29. Abet Danni, Tariku yimestal. Yigermhal botaw eko ene tewelje yadeghubet akababi new. hulet gize heje lemayet mokrealehu. Ahun yanten zegeba sanebew gin fitsum addis bota meselegn.
  Egziabher yistiln, qalehiwot yasemalin, egnanm abertton yetsadikun bereket lemaggnet yabqan !

  ReplyDelete
 30. egziabhiar ybarkeh!

  ReplyDelete
 31. በአዲስ ዓመት አዲስ ነገር ለማየት ያበቃን አምላከ ቅዱሳን ክብር ምስጋና ይግባው! ዲ/ን ዳንኤልና ልዑኮችህም በረከታችሁ ይድረስን! አሜን!

  ReplyDelete
 32. ለሁም ነገር እግዚአብሔር ይመስገን፡፡

  ዲ/ን ዳንኤል ምን እንደምልክ አላውቅም እግዚአብሔር ይባርክህ እንዲህ ያለ ቦታ ለመሄድ የአምላክ ፍቃድና መታደል ያስፈልጋል ቦታው የአለም ጫጫታ የማይሰማበት ከእግዚአብሔር ጋር ብቻ የምንነጋገርበት መሆኑ እኔ እንኳን ሳነበው በጣም በተመስጦ ስወጣ ስወርድ ነበር አንተንም ትብብር ያረጉልህን እድሜ ከሙሉ ጤና ጋር ያድላችሁ መጨረሻውን ያሳምርልህ፡፡

  ስንዱ ተስፋዬ

  ReplyDelete
 33. Egziabher yestilen Dn Daniel yaglegelot zemnon yebarekelen.

  ReplyDelete
 34. May God bless your service! We are expecting a lot from you.

  ReplyDelete
 35. dani i am appreciate always your talent

  ReplyDelete
 36. ዳኒ እጅግ በጣም ነው የወደድኩት፡፡ እንደዚህ ያለ ቦታ ለማየት መመረጥ ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር ይስጥህ፡፡ አሜን!

  ReplyDelete
 37. ዳኒ እጅግ በጣም ነው የወደድኩት፡፡ እንደዚህ ያለ ቦታ ለማየት መመረጥ ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር ይስጥህ፡፡ አሜን!

  ReplyDelete
 38. በአማን ነጸረSeptember 24, 2014 at 10:30 AM

  ሠናይ እገሪሆሙ ለእለ ይዜንው ሠናየ ዜና፡፡

  ReplyDelete
 39. D.daniel ebakeh betransport endet adrgen mehed endeminchil bitinegren

  ReplyDelete
 40. ዳንኤል በጣም ጥሩ የጉዞ ማስታወሻ በመስጠትህ እጅግ ደስ ብሎኛል፡፡ እንዲህ በረከት ያለበትን ቦታ ለማየት እንችል ዘንድ ጥሩ መልእክት አስተላልፈህልናልና በጣም አመሰግንሃለሁ፡፡ አምላክ እስከ ሕይወት ፍጻሜህ ድረስ በቤቱ ያበርታህ፡፡

  ReplyDelete
 41. ዳንኤል በጣም ጥሩ የጉዞ ማስታወሻ በመስጠትህ እጅግ ደስ ብሎኛል፡፡ እንዲህ በረከት ያለበትን ቦታ ለማየት እንችል ዘንድ ጥሩ መልእክት አስተላልፈህልናልና በጣም አመሰግንሃለሁ፡፡ አምላክ እስከ ሕይወት ፍጻሜህ ድረስ በቤቱ ያበርታህ፡፡

  ReplyDelete
 42. እግዜአብሄር ይባርክህ ዕድሜህን ያርዝምልን

  ReplyDelete
 43. እግዜያብሄር ይባርክህ ዕድሜህን ያርዝምልን

  ReplyDelete
 44. እግዜአብሄር ይባርክህ እድሜህን ያርዝምልን

  ReplyDelete
 45. እግዚአብሄር ይስጥህ፡፡

  ReplyDelete
 46. ውድ ወንድማችን እግዚአብሄር ይባርክህ ፡፡ ይህ ገዳም የአያቶቸ ሀገር ነው ሰው እንዲያየው ሁሌም እመኝ ነበር ዛሬ ይህን እደል ለአንባቢዎችህ በማሳወቅህ መልካም ስራ ሰርተሃል ፡፡ እበካችሁ ሌሎቻችሁም እዩት ፡፡ ሙሉተስፋ ነኝ ከቡሬ

  ReplyDelete
 47. yehenenema mayeti albene! dekame endehone sewtute yeresal. kalhiwoti yasemalene!

  ReplyDelete
 48. እግዚአብሔር ይባረክህ ፡፡ ያለ ድካም በረከት የለምና የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ ለማየት ያብቃን፡፡ እግዚአብሔር ይባረክህ ፡፡ ያለ ድካም በረከት የለምና የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ ለማየት ያብቃን፡፡

  ReplyDelete
 49. I am glad to be there Dani. ለነገሩ በአካል አልሄድኩም እንጂ ያንተን ፅሁፍ እያነበብኩ ደርሼ ተመለስኩ እግዚአብሄር ይባርክህ ያኑርልን እሺ!!

  ReplyDelete
 50. በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
  ዲ/ን ዳኒ በመጀመሪያ የከበረሰላምታየን እያቀረብኩ ለምትሰራውስራሁሉ አምላከቅዱሳን እንዲያበረታህ እና መልካሙን ልቦና እንዲያዲል በመማጸንነው
  በመጀመሪያ ጹሑፉን ስመለከተዉ አልቅሻለሁ.፤እጅግ አዝኛለሑ ምክንያቱም አሁን ከወቅቱጋር ያለዉን ሁኔታ ስመለከተው በጣም አሳዝኖኛል … ቅኝ ገዝ የሚለው ቃል መቼም ቢሆን አንተንም ሳያሳዝንህ እንደማይቀር አልጠራጠርም …ሆኖም ግን በማህበሩበኩል ያሉትን ጉድለቶች በአንዲንት እና በጋራ በዉይይት መፍታት የሚለዉን ወሳኝ ነገር መውሰድ እንዳለብን ይስማኛል ፡፡!!!
  በዚህቀዳዳ ተሐዲሶ መናፍቃን ገብተው የጥሎማለፍ የኳስጨ ዋታሜዳ ለማድረግ የሚሸርቡት ገመድ ሁላችነንም የሚሰማን ዳይ መሆን እነዳለበት መውሰድ አለብን …
  ለአንዲት ቅዲስት ቤተክርስቲያን ሁላችንም በጸሎት መረባረብ እንዳለብን ይሰማኛል፡፡!!!
  አምላችን እግዚአብሔር በኁሉም ነገር ይርዳን አሜን…፡፡!!!

  ReplyDelete
 51. Egziabher befekdina egnam edilun agigniten binhedina yebereketu tekafay endeyadergen yemedhanialem fekad yihunilin.........KALE HIWOT YASEMALIN.....

  ReplyDelete
 52. ዳኒዬ በጣም እናመሠግናለን።እኔ ቦታዉን ከ፰ ዐመት በፊት አይቸዋለሁ።በዉነት በሚገባ ዳግም ያየሁት ያህል አስታወስከኝ።ሊታይ የሚገባዉ ቦታ ነዉ።በፀበሉ የዳኑ ብዙ ሠዎች አዉቃለሁ።

  ReplyDelete
 53. wow!!!!! betam des yilal. ene tewelije yadekut ezaw senebo new. beye ametu(yearly) nehase 24 yenigse beal ale ena metachihu yebereketu tesatafi endithonu be egziabher sim asasibalehu. Le d.daniel egziabher selamina tena yistilin.

  ReplyDelete
 54. wwwwwwww fetari lemayet yabkagne

  ReplyDelete