Monday, September 22, 2014

እምቢታ (የቃቄ ወርድወት)

ደራሲ - እንዳለ ጌታ ከበደ
ዋጋ - 49 ብር
አታሚ - ኤች ዋይ ማተሚያ ቤት
እንዳለ ጌታ የጻፈውን እምቢታ መጽሐፍ ከአዲስ አበባ ወደ አውስትራልያ እየተጓዝኩ አውሮፕላን ውስጥ ነው ያነበብኩት፡፡ መጽሐፉ ለገበያ ሲቀርብ እንደማልኖር ስላወቀ ቀድሜ እንዳገኘው በማድረጉ አመሰግነዋለሁ፡፡ ይኼ በታሪክና በሥነ ቃል(ፎክሎር) ላይ የተመሠረተ ልቦለድ በአንዲት ብዙዎቻችን በማናውቃት ከዘመን የቀደመች ሴት ጀግና ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡
ቃቄ ወርድወት ትባላለች፡፡ በነገራችን ላይ ቃቄ የአባቷ ስም ነው፡፡ የእርሷ ስም ወርድወት ነው፡፡ በጉራጌ ባሕል የአባትን ስም ከልጅ የሚያስቀድም ጥንታዊ ሥርዓት ነበረ ማለት ነው፡፡ ምናልባትም በዕውቀቱ ስዩም ‹በኢትዮጵያ ከልጅ ስም በፊት የአባት እንደሚቀድም ማስረጃ አለኝ› ያለው አንዱ ይኼንን ሳይሆን አይቀርም ብዬ ገምቻለሁ፡፡ የመጽሐፉን ረቂቅ መመልከቱን መግቢያው ላይ ያሳያልና፡፡

ቃቄ ወርድወት በ1840ዎቹ አካባቢ ከጉራጌ ማኅበረሰብ የፈነጠቀች ኢትዮጵያዊት ኮከብ ነበረች፡፡ በሴቶች ላይ የነበረውን አድሏዊ ልማዳዊ ሥርዓት ለመታገል፣ በጋብቻ ሥርዓት ወንዶቹ ከሴቶቹ ይልቅ ሥልጣን ለማደላደል፤ ሴቶች ከለፉበት ትዳራቸው ያለ አንዳች ንብረት በፍቺ መባረራቸውን ለማስቀረት የታገለች ጀግና፡፡ ዛሬ እንኳን ለብዙ ኢትዮጵያውያን ሴቶች አስቸጋሪ የሆነውን ‹ሴት ልጅ ተመርጣ ብቻ ሳይሆን መርጣም ማግባት አለባት› የሚለውን ሐሳብ ይዛ የታገለች፤ ታግላም በራሷ ላይ የፈጸመች ጀግና ሴት ናት፡፡
በዚያ የሴቶች መብት፣ የጾታ እኩልነት የሚሉ ዘመናዊ ሐሳቦች ባልዳበሩበት፤ ለሴቶች መብት ቆመናል የሚሉ ተቋማት ባልነበሩበት ዘመን ከዘመኗ ቀድማ ችግሩን የተረዳች፤ የሴቶችን ችግር ለመቅረፍና እናቶቻችን ፍትሕ እንዲያገኙ ለማድረግ በጉራጌ ማኅበረሰብ ባሕል ከፍተኛው ሸንጎ እስከሆነው ኧጆካ አደባባይ ድረስ የተሟገተች ጀግና ናት፡፡
እንዳለ ጌታ የዚህችን የማናውቃትን ጀግናችንን የተጋድሎ ታሪክ ከልዩ ልዩ ምንጮች ሰብስቦ፣ ሥነ ቃሉን አስማምቶ፣ ከሀገራችን ታሪካዊ መዛግብት ጋር አዋሕዶ በልቦለድ መልክ አቅርቦልናል፡፡ ወጥ ልቦለዶች እያነሡ፣ የትርጉም ሥራዎች ቦታችንን እየወሰዱ ባሉበት ዘመን የራሳችንን ታሪክ መልሰን እንድናይ የሚያደርግ እንዲህ ያለውን ሥራ ማግኘት ለሥነ ጽሑፋችን አንድ እመርታ ነው፡፡
ሰው የሚያውቀውን ሲያቀርብ፣ የሚያቀርበውንም ሲያውቅ ደስ ይላል፡፡ የኖረበትን፣ የተሠራበትንና የተዋሐደውን ነገር ሲተርክ ከውስጡ ስለሚመነጭ ከዛፍ ሥር የሚመነጭን ውኃ እንደመጠጣት ይቆጠራል፡፡ አንድን ማኅበረሰብ በዕንግዳ ዓይን ማየት ተለምዶ የሚመስሉትን ነገሮች በሚገባ ለማንጠር ይረዳል፡፡ የውስጡ ሰው ለምዶት የሚያልፈውን ዕንግዳ ሰው ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ አንድን ማኅበረሰብ በውስጥ ሰው ማየት ደግሞ የሚያውቁትን፣ የኖሩበትንና ትርጉሙንም በሚገባ የሚያውቁትን ነገር እንደ ልብ ምት አዳምጦ ለማቅረብ ይረዳል፡፡ የቃቄ ወርድወት ታሪክ እንዲህ ሆኖ ነው የቀረበው፡፡ ማኅበረሰቡ የተሰፋበትን እያንዳንዷን ሰበዝ ታዩበታላችሁ፡፤ ያውም ሳይታወቃችሁ፡፡
የእንዳለ ጌታ መጽሐፍም የኖረበትንና ያጠናውን ማኅበረሰብ ያቀረበበት ስለሆነ ሁለት መቶ ዓመታትን ተሻግራችሁ ትነጉዱና ከቃቄ ወርድወት ጋር ለመብት ትታገላላችሁ፣ ጉራጌ ገብታችሁ ደመራ ታበራላችሁ፣ መስቀል ታከብራላችሁ፣ ክትፎ ትበላላችሁ፣ ከነገሥታቱና መኳንንቱ ጋር ትዋጋላችሁ፡፡ ኧጆካ ትወጣላችሁ፣ ጀፎረ ላይ ትቀመጣላችሁ፡፡
በጉራጌ ማኅበረሰብና በማዕከላዊው መንግሥት መካከል፣ በጉራጌ ማኅበረሰብና በሌሎች የአካባቢው ማኅበረሰቦች መካከል ፍቅርም፣ ጠብም፣ ጦርነትም፣ ዕርቅም ነበረ፡፡ እነዚህ ግንኙነቶች በማኅበረሰብ ውስጥ የሚፈጥሩትን አሉታዊና አዎንታዊ ነገሮች በእንዳለ ጌታ ዓይን ስናያቸው አንድን ታላቅ ማኅበረሰብ በመፍጠር ሂደት ውስጥ የተከናወኑ የሂደቱ መገለጫዎች እንጂ የቂም መቋጠሪያዎች ሆነው አናገኛቸውም፡፡ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ በሚገኙ ልጆች መካከል የሚኖር መጣላትና መዋደድ የልጆቹ የዕድገታቸው ሂደት አካል እንደሚሆነው ማለት ነው፡፡
በየአካባቢው የሚገኘውና የማናውቀው ታሪካችንና ባሕላችን እንዲህ ለነገዋ ሀገራችን መቀመሚያ በሚሆን፣ ያለፈውንም ለማወቂያና ለማረሚያ በሚያገለግል፣ በሌላ በኩል ደግሞ አቃፊ እንጂ አግላይ ባልሆነ መንገድ ቢቀርብልን የአንዱ አካባቢ ታሪክ የሁላችንም እየሆነ ‹የኢትዮጵያ› ስንል የሚጎድለን አይኖርም ነበር፡፡ አሁን አሁን ግን ‹የኢትዮጵያ› ስንል የሚጎድሉን ነገሮች አሉ፡፡ አንድም አንዳንዶች ‹የኼማ የራሳችን ብቻ ነው› ብለው ቆርጠው በማስቀረታቸው፣ አንድም ደግሞ ‹የኢትዮጵያ› የተባለው ነገር አንዳንዶችን አግልሎ በማስቀረቱ፡፡ ሁለቱም ግን እኩል ነው የሚጎዱት፡፡ የጉራጌ ክትፎ የሁላችንም እንደሆነው ሁሉ የየአካባቢው ሥነ ቃል፣ ታሪክ፣ ባሕልና ቅርስ እየወጣ የሁላችንም እየሆነ መሄድና ወደ ዋናው አካል እየተቀለቀለ፣ ለዋናው አካል ግንባታም አስተዋጽዖ እያደረገ መሄድ አለበት፡፡ ማግለልም መገለልም አንድ ናቸው፡፡
የአካባቢውን ሥነ ቃል፣ ታሪክና ባሕል ከምናገኝባቸውና የራሳችን ከምናደርግባቸው መንገዶች አንዱ ኪነ ጥበባዊ በሆነ መንገድ ማግኘታችን ነው፡፡ ‹የእገሌ ብሔረሰብ ታሪክና ባሕል› እየተባሉ ብቻ የሚወጡ፣ ሲጀምሩ ሌላውን አውግዘው፣ ኮንነውና ጠልተው የሚነሡ ‹መጻሕፍት› አጥሩን በአደገኛ አጥር ከማጠናከር ያለፈ ፋይዳ አይኖራቸውም፡፡ ቁስሉን ማሳየት እንጂ ማሻርም አይፈልጉም፡፡ ምናልባትም የጉዳዩ ባለቤት ነኝ ብሎ ከሚያስበው አካል በቀር የሌላውን ልብ ለመማረክም አይችሉም፡፡ ጎጣዊ ጀግና ከመፍጠር ባለፈ ሀገራዊ ጀግና አያስገኙም፡፡ በላይ ዘለቀን የጎጃም፣ ዐፄ ዮሐንስን የትግሬ፣ ቃቄ ወርድወትን የጉራጌ ብቻ አድርገው ለማስቀረት የሚያልሙ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያዊ ጀግና፣ ሀገራዊ ታሪክ፣ ሀገራዊም ማንነት ሊፈጠር የሚችለው እንዲህ የአንዱ አካባቢ ታሪክ የሌላው እንዲሆን አድርጎ በማቅረብና ለታሪኩና ሥነ ቃሉ ብቻ ሳይሆን ለአቀራረቡም ጭምር በመጨነቅ ነው፡፡ ‹ሲያዩት ያላመረ ሲበሉት ያቅራል› ይባል የለ፡፡ የእንዳለ ጌታን መጽሐፍ አንብቡት የምላችሁም ለዚህ ነው፡፡ በሞቴ አንብቡት፡፡  

17 comments:

 1. አንድን ማኅበረሰብ በውስጥ ሰው ማየት ደግሞ የሚያውቁትን፣ የኖሩበትንና ትርጉሙንም በሚገባ የሚያውቁትን ነገር እንደ ልብ ምት አዳምጦ ለማቅረብ ይረዳል፡፡

  ReplyDelete
 2. Di. Daniel Ejeg betam enamesegnhalen weketawi yehone menebeb yalebet tsufe stie lay post bemadregeh tedestenal
  metsehafun alanebebenewim bante tekuwaminet ena mereje akebaynet lemanbeb gagtenal.enanebewalen yechin yeset tagay ema limduwan mewsed alebin yawim minm neger baltemechachebet gize .yeset mebtin lemaskebet yetenesach set tagaye enakeberatalen esuwa baskemetechew ashara new ahun tinsh tinsh ye set mebet mekeber yetejemerew eske kirb gize deres meret be wurse enqwan leset lij bewurse aytelalefe neber gin esuwa betalechw ashara ahun tinsh emrta asaytoal . bedgami enamesgnalen Di. Daniel . Geta erejem edeme ena tena yesteh enlalen.

  ReplyDelete
 3. EGZIABHERE YESETILIN , BECHER KE AUSTRALIA TEMELES, EDMEY YESTEH

  ReplyDelete
 4. ቁስሉን ማሳየት እንጂ ማሻርም አይፈልጉም ፡፡ ለምን

  ReplyDelete
 5. MARYAMIN DANIYA KAGERBAT ASLKA ANBEWALW HULGIZA AKBRHALEW

  ReplyDelete
 6. Bemigeba anebewalew belehegn new

  ReplyDelete
 7. I READ IT. IT IS IMPRESSIVE. ENDALEGETA YOU DID A GREAT JOB. PLEASE KEEP IT UP.

  ReplyDelete
 8. ሰው የሚያውቀውን ሲያቀርብ፣ የሚያቀርበውንም ሲያውቅ ደስ ይላል፡፡

  ReplyDelete
 9. One comment: there is a difference between 'የቃቄ ወርድወት' and 'ቃቄ ወርድወት' when u use the first it doesn't suggest the father's name come first; rather ወርድወት is the daughter of 'ቃቄ'-so it is better to refer her as 'የቃቄ ወርድወት'. If Bewketu has any evidence, regarding the existence of such naming in Ethiopia this is not the one

  ReplyDelete
 10. ኢትዮጵያዊ ጀግና፣ ሀገራዊ ታሪክ፣ ሀገራዊም ማንነት ሊፈጠር የሚችለው እንዲህ የአንዱ አካባቢ ታሪክ የሌላው እንዲሆን አድርጎ በማቅረብና ለታሪኩና ሥነ ቃሉ ብቻ ሳይሆን ለአቀራረቡም ጭምር በመጨነቅ ነው፡፡

  ReplyDelete
 11. ኧረ አትሙት ወንድሜ፤እንኳንስ ተጻፈ እንጂ ማንበብ ማን ይጠላል፡፡

  ReplyDelete
 12. ሰው የሚያውቀውን ሲያቀርብ፣ የሚያቀርበውንም ሲያውቅ ደስ ይላል፡፡

  ReplyDelete
 13. ሰው የሚያውቀውን ሲያቀርብ፣ የሚያቀርበውንም ሲያውቅ ደስ ይላል፡፡

  ReplyDelete
 14. ደራሲ እንዳለ ጌታ እጅግ የማደንቀው ደራሲ ነው፡፡ እንቢታንም አንብቤ ተደስቸበታለሁ፡፡ ሆኖም ግን ምነው የጉራጌን ታሪክ ከሥር ሲተርክልን የጎንደሩን ታሪክ አቀዳደመው? አፄ ሱስንዮስን እና አፄ ፋሲልን……፡፡

  ReplyDelete
 15. ዳኒዬ ገዝቼ እስካነበው ቸኩያለሁ።

  ReplyDelete
 16. .....በአንድ ቤተሰብ ውስጥ በሚገኙ ልጆች መካከል የሚኖር መጣላትና መዋደድ የልጆቹ የዕድገታቸው ሂደት አካል እንደሚሆነው ማለት ነው፡፡

  ReplyDelete