Tuesday, September 2, 2014

ዝሆን (ክፍል ሦስትና የመጨረሻው)

ዝሆኖች አንድ የታመመ ወይም የቆሰለ ወገን ካላቸው እስኪድን ድረስ ይከባከቡታል፡፡ ምግብ ያቀርቡለታል፤ ከአደጋም ይጠብቁታል፡፡ ለዚህ ሁሉ ድካማቸው በኩምቢ የሚገለጥ ‹እግዜር ይስጥልኝ› በቂያቸው ነው፡፡ አንድ ቀን ግማሽ ኪሎ ብርቱካን ይዘን የጠየቅነውን በሽተኛ ሁሉ ውለታችንን ካልመለሰ ለምንል ሰዎች ከእኛ የሚሻሉ እንስሳት መኖራቸውን ማወቅ እንዴት መልካም መሰላችሁ፡፡
ዝሆኖች ይቅር ባዮች ናቸው፡፡ ዝሆን አደጋ የደረሰበትንም ያደረሰበትንም አይረሳም ይባላል፡፡ ጊዜ ጠብቆ የመበቀል አመል አለው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ችግር የፈጠረባቸው ኅብረተሰብ ወይም ግለሰብ ሲከባከባቸውና ለእነርሱ መልካምን ነገር ሲያደርግ ከተመለከቱ በቀላቸውን ሁሉ ለመተውና ይቅር ለማለት ፈጣኖች ናቸው፡፡ ይቅርታ ለመበቀል አለመቻል አይደለም፡፡ አለመፈለግ እንጂ፡፡ ይቅርታ ከዐቅም ማጣት ሳይሆን ከዐቅም ማግኘት የሚፈጠር ነው፡፡ በዝሆኖች መንጋ መካከል ችግር ፈጣሪ ከተገኘና ከተቀጣ ሁሉም ዝሆኖች ያገሉታል፡፡ ተስተካክሎ ከመጣ ግን ኩምቢያቸው በማነካካት ይቅር ማለታቸውንና መተዋቸውን ይገልጡለታል፡፡ ከዚያ በኋላ አለቀ፡፡ ሰውን ‹እንስሳ› ብለን የምንሳደብ እኛ ለይቅርታ የተዘጋጀ ልብ የለንም ማለት ከዝሆን ያነስን ነን ማለታችን ነው፡፡

ጉልበተኛነት ነውር ነው፡፡ በዝሆኖች ዘንድ ከባዱን ቅጣት የሚያስቀጣው በሌላው ወገን ላይ የኃይል ጥቃት ማድረስ ነው፡፡ ድብድብ ፈጽሞ ነውር ነው፡፡ በተለይም ወጣት ዝሆኖች ሲደባደቡ ከተገኙ መሪዋ እናት ዝሆን  ትቀጣቸዋለች፡፡ በቀላል ቅጣት ያልታረመ ጉልበተኛ ከመንጋው እስከመገለለ የሚደርስ ከባድ ቅጣት ሊጠብቀው ይችላል፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ ከእርሱ ጋር የሚሠማራ አያገኝም፡፡ ‹ዝሆኖቹ ሲጣሉ የሚጎዳው ሣሩ ነው› የሚለው አባባል ዱርዬ ዝሆኖችን ብቻ የሚመለከት ነው፡፡ ዝሆኖቹ ሣሩ እስኪጎዳ ድረስ በዝምታ የሚያዩ አይደሉም፡፡ ርምጃ ይወስዳሉ፡፡ በእነርሱ ዘንድ ሕግና ሥርዓት እንጂ ጉልበት ቦታ የለውም፡፡ ዐቅም ስላለህ፣ ጉልበት ስላለህ ወይም ታላቅ ስለሆንክ ወይም ደካማ ስላገኘህ ብቻ ተነሥተህ ቡጢህን ማሳረፍ አትችልም፡፡ በሥርዓት መቅጣት የመንጋው መሪ ድርሻ ነው፡፡ ማንም ጉልበት ያለው ሁሉ ተነሥቶ ጉልበቱን አይሞክርብህም፡፡ አንዳንዴ ጉልበተኛ የሚበዛው አለቃ ሲበዛ ነው፡፡ ሁሉም ቀጭ ሲሆን፣ ሁሉ አሣሪ ሲሆን፣ ሁሉም ፈራጅ ሲሆን፣ ሁሉም አስከፋይ ሲሆን፣ ሁሉም ሰጭና ነሽ ሲሆን ‹ምነው ዝሆን በሆንኩ› ያሰኛል፡፡
በዝሆን የአንዱ ችግር የሁሉም ነው፡፡ ችግርን በመረዳዳት ከሚወጡ እንስሳት ወገን ናቸው - ዝሆኖች፡፡ ‹የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ› ብለን እኛ ላለመስማት ምሳሌ ብናደርገውም የዝሆን ጆሮ ግን ለመስማትም ሙቀቱን ለማብረድም የሚረዳው አካል ነው፡፡ የዝሆን ጆሮ ከእግሩና ከኩምቢው ጋር ተጣምሮ ከሩቅ ድምጾችን ለመስማት ይችላል፡፡ እንዲያውም እጅግ በጣም ቀጭን አንድ ዝሆን ችግር ሲደርስበትና ርዳታ ሲፈልግ የሚያሰማው ልዩ የሆነ ድምጽ አለ፡፡ እያንዳንዱ ችግር በተለየ ድምጽ ነው የሚገለጠው፡፡ ያንን የሰማ ማንኛውም ዓይነት ዝሆን ለርዳታ ይንቀሳቀሳል፡፡ ለጠላት የተጋለጠውን፣ በአረንቋ የተያዘውን፣ ወንዝ ማቋረጥ ያቃተውን፣ መንገድ የጠፋበትን ለመርዳታ ከየአቅጣጫው የዝሆን መንጋ ይተማል፡፡ ተረዳድተው ከአደጋ ካተረፉት በኋላ ኩምቢ ለኩምቢ በሚደረግ መተሻሸት ብቻ ውለታው ይከፈላል፡፡ ‹እግዜር ይስጥልኝ› መሆኑ ነው፡፡ ያውም ከአደጋ የተረፈው ብቻ ሳይሆን ሁሉም ለአደጋ መከላከል የመጡ ዝሆኖች ችግሩን እንደራሳቸው ቆጥረው አጋና ይመታታሉ፡፡ የአንዱ ችግር የሁላችንም ነው ማለታቸው ነው፡፡ ‹አይመለከተኝም፣ አላውቀውም፣ ዘመዴ አይደለም፣ ምን ይከፈለኛል፣ በኋላ ጣጣ ቢመጣብኝስ፣ ከዚህ በፊት ለእኔ ማን ደረሰልኝ፣ ሁሉም ሥራው ያውጣው፣ ይኼ የእገሌ ድርሻ ነው› ለምንል ሰዎች ‹ወደ ዝሆን ተመልከቱ› የሚል ጸሎት ሳያሻን አይቀርም፡፡

ዝሆን አደጋን የመለየት ዐቅም አለው፡፡ በቅርብ ዘመናት የተደረጉ ጥናቶች ዝሆኖች አደጋን ቀድመው የመለየት ወይም ደግሞ አደጋዎችን ለይተው ተገቢ መፍትሔ የመስጠት ዐቅም እንዳላቸው አሳይተዋል፡፡ ከሁሉም ጋር አይጋጩም፤ ሁሉንም ንቀው አይተውም፤ ሁሉንም አይፈሩም፣ ሁሉንም አያባርሩም፤ ከሁሉም አይሸሹም፤ ከሁሉም ጋርም አይፋለሙም፡፡ የትኛው ዓይነት አደጋ ቀላል፣ የትኛውም አስጊ እንደሆነ ለይተው እንደ ሁኔታው ይቀበሉታል እንጂ፡፡
በኬንያ ማሳይና ካምባ የሚባሉ ጎሳዎች አሉ፡፡ ማሳዮች በዝሆን አደን የታወቁ ናቸው፡፡ ካምባዎች ደግሞ ዝሆኖችን ማደንን እንደነውር ይቆጥራሉ፡፡ ዝሆኖቹ ይህንን ሁኔታ አስተዋሉ፡፡ አደጋ የሚመጣበትንና የማይመጣበትን ማኅበረሰብ ለዩ፡፡ ሁለቱ ማኅበረሰቦች የሚኖሩበትን ክልልም ተረዱ፡፡ በመጨረሻም አያሌ ዝሆኖች ከማሳይ ጎሳ አካባቢዎች በመሸሽ ወደ ካምባ ጎሳዎች ክልል ገቡ፡፡ ጠቢባን እንዲህ ይላሉ ‹ብዙ ጊዜ ውድቀት የሚመጣው ምን ማድረግ እንዳለብን ባለማወቃችን ምክንያት አይደለም፤ ምን ማድረግ እንዳለብን የምናውቀውን ነገር ባለማድረጋችን እንጂ›፡፡ በችግር ውስጥ ተተብትቦ ከመነጫነጭ፣ ከማማረር፣ ከማላዘንና ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ከተቻለ አስቀድሞ ማወቅ፤ ካልተቻለም ከችግሩ በኋላ አመጣጡንና መንሥኤውን መለየት ያስፈልጋል፡፡ በችግሩ ላይ አጠንጥኖ ‹አይይ› እያሉ ቀንን ከመርገምና እንዴት እንደማይቻል ከማሰብ ይልቅ በግድግዳው መሐል ስንጥቅ፤ በግንቡ መካከልም ቀዳዳ መኖሩ ስለማይቀር ያንን መፈለግ እጅግ የተሻለው ነው፡፡ ለሁሉም በሽታ አንድ ዓይነት መድኃኒት እንደሌለው ሁሉ ለሁሉም ችግር አንድ ዓይነት መፍትሔ የለውም፡፡ መጀመሪያ ማጥናት፣ ከዚያም ማወቅ፣ ቀጥሎም በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ መወሰን፣ በመጨረሻም የወሰኑትን መፈጸም- ያ ነው መንገዱ፡፡
ዝሆኖች በጥቂት ያገኙትን በብዙ በመከባከብ እልፍ ያደርጉታል፡፡ ከአጥቢ እንስሳት ሁሉ የዝሆንን ያህል ረዥም ጊዜ የሚያረግዝ የለም፡፡ የእርግዝናዋ ወራት 22 ወራት ነው፡፡ አንድ ዓመት ከዐሥር ወር ማለት ነው፡፡ ያውም ደግሞ ቤተሰብ መምሪያ ያላወቀውን የቤተሰብ ምጣኔ ስለሚጠቀሙ ነው መሰል የሚወልዱት በአምስት ዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ዝሆኖች በጥቂቱ ያገኙትን በብዙ ክብካቤ ማበርከት ባይችሉበት ኖሮ የዝሆን ጥርስ አደን ተጨምሮበት ዛሬ ከምደረ ገጽ በጠፉ ነበር፡፡ ዋናው ጥያቄ ምን አለህ? አይደለም፡፡ እንዴት ይዘህ እንዴትስ ትጠቀምበታለህ? ነው እንጂ፡፡ ‹ከአያያዝ ይቀደዳል፣ ከአነጋገር ይፈረዳል› አይደል የሚባለው፡፡
ዝሆኖች በጭንቅ ያገኙትን ፍሬ በሚገባ በመከባከብ፣ ከአደጋ በመጠበቅ፣ ያንን ፍሬም ሥነ ሥርዓት አስይዘው በማሳደግ ዘራቸው እንዲቀጥል ያደርጋሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ የመንጋው አባላት ሁሉም እኩል ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አፍሪካውያን ‹አንድን ልጅ በብቃት ለማሳደግ መንደሩ ሁሉ ሊተባበር ይገባዋል - It takes a village to raise a child› የሚል አባባል አላቸው፡፡ ልጅን ለብቻ በብቃት ማሳደግ አይቻልም፡፡ ቤተሰብ ሲቀርጸው ማኅበረሰብ ካበላሸው፣ ትምህርት ቤት ሲያንጸው ሚዲያ ካፈረሰው፣ ሃይማኖት ሲያቃና ጫት ቤት ካጣመመው፣ ወላጅ ሲያለማው ጓደኛ ካጠፋው ፣ ልጅ ምን ፍሬ ይወጣዋል፡፡
በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ሳይሆን አይቀርም ቅዱሳት መጻሕፍት፣ ሥዕሎች፣ ተረቶች፣ የፍልስፍናና የጥበብ ማስተማሪያዎች ለዝሆን ቦታ የሰጡት፡፡ በሀገራችን ትርጓሜያትና በፊሳሎጎስ መጽሐፍ ዝሆን የማስተማሪያነት ቦታውን ይዟል፡፡ ብዙ ጊዜ ግን ከብሔራዊ ሎተሪ ዓርማነት ባሻገር ስንናገርለት አልታየንም፡፡ እስኪ ‹ሔርማዝ› እንሁን፡፡17 comments:

 1. ምንም እንኳ ዝሆን በቀለኛ ቢሆንም በቀል አድራጊው ከተስተካከለና መልካምነትን ካሳየ ይቅር ይለዋል፡፡ የእኛ በቀልስ እስከየት ነው፡፡ መጽሐፍ ግን በቀል የእግዚአብሔር ነው ይላል፡፡ ክፉ ላደረጉባችሁ በጉ መልሱ ለማለት፡፡ በቤተ መንግስቱ፣ በቤተክህነቱ ወዘተ አንዱ አንዱን ለማጥፋት የሚደረገው እሩጫ አቤት የት ያደርስ ይሆን፡፡ እንጃ…..፡፡ መልካም የሚሰራን ግለሰብ፣ ቡድን፣ ድርጅት… በማበረታት ለበጎ ነገር መጠቀም ሲገባ ለማነኳሰስ የሚደረገው ትግል አሰገራሚ ነው፡፡ ነገር ግን በግድግዳው መሐል ስንጥቅ፤ በግንቡ መካከልም ቀዳዳ አይጠፋምና ይህንን መልካም ስራ ከግብ ማድረስ ያስፈልጋል፡፡ ለሀገር፣ ለወገን ከሚያስብ የሚጠበቅ ነውና፡፡ የዝሆን ጀሮ ስጠን… ከሩቅ የምንሰማበትና መፍትሔ የምናዘጋጅበት፡፡ በርታ ዲ/ን ዳንኤል

  ReplyDelete
 2. ቤተሰብ ሲቀርጸው ማኅበረሰብ ካበላሸው፣ ትምህርት ቤት ሲያንጸው ሚዲያ ካፈረሰው፣ ሃይማኖት ሲያቃና ጫት ቤት ካጣመመው፣ ወላጅ ሲያለማው ጓደኛ ካጠፋው ፣ ልጅ ምን ፍሬ ይወጣዋል፡፡

  ReplyDelete
 3. amazing story,10q Dany!!!

  ReplyDelete
 4. Tnxs Dani God bless u.

  ReplyDelete
 5. Tnxs d.dani God bless u .

  ReplyDelete
 6. It is a wonderful view thanks D/n Daniel live long, may GOD bless you

  ReplyDelete
 7. ዝሆኖች በጭንቅ ያገኙትን ፍሬ በሚገባ በመከባከብ፣ ከአደጋ በመጠበቅ፣ ያንን ፍሬም ሥነ ሥርዓት አስይዘው በማሳደግ ዘራቸው እንዲቀጥል ያደርጋሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ የመንጋው አባላት ሁሉም እኩል ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አፍሪካውያን ‹አንድን ልጅ በብቃት ለማሳደግ መንደሩ ሁሉ ሊተባበር ይገባዋል - It takes a village to raise a child› የሚል አባባል አላቸው፡፡ ልጅን ለብቻ በብቃት ማሳደግ አይቻልም፡፡ ቤተሰብ ሲቀርጸው ማኅበረሰብ ካበላሸው፣ ትምህርት ቤት ሲያንጸው ሚዲያ ካፈረሰው፣ ሃይማኖት ሲያቃና ጫት ቤት ካጣመመው፣ ወላጅ ሲያለማው ጓደኛ ካጠፋው ፣ ልጅ ምን ፍሬ ይወጣዋል፡፡

  ReplyDelete
 8. ዝሆን ብትሆን ኖሮ ፡ ዳኒ የጻፈውን በድጋሚ ፡ አታስነብበንም ነበር !

  ReplyDelete
 9. እስኪ ‹ሔርማዝ› እንሁን፡፡ እውነት ነው እስኪ እንሞክር

  ReplyDelete
 10. Thanks d/n daniel a lot! GOD bless u!!!!!!!!!!!!!

  ReplyDelete
 11. ቃለ ህይወት ያሰማልን በእውነት ትልቅ ትምህርት ነው ያስተማርከን!!!

  ReplyDelete
 12. I cant express my all fillings....but I want to say fetary/GOD/ yabretahe,AMEN.

  ReplyDelete
 13. geta yezihonochen metesaseb yeseten lantem regem edemenena teru berilyant brain yeseteh

  ReplyDelete
 14. tsegawen yabizaleh wedu wendimachin

  ReplyDelete
 15. Very Interesting ዝሆኖች ይቅር ባዮች ናቸው፡፡ ዝሆን አደጋ የደረሰበትንም ያደረሰበትንም አይረሳም ይባላል፡፡ ጊዜ ጠብቆ የመበቀል አመል አለው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ችግር የፈጠረባቸው ኅብረተሰብ ወይም ግለሰብ ሲከባከባቸውና ለእነርሱ መልካምን ነገር ሲያደርግ ከተመለከቱ በቀላቸውን ሁሉ ለመተውና ይቅር ለማለት ፈጣኖች ናቸው፡፡

  ReplyDelete