Thursday, September 25, 2014

ጨረቃና ጨለማ

በ1768 እኤአ የተጻፈና ጥንታዊ አባባሎችን የያዘ አንድ ‹‹AN ETHIOPIAN SAGA›› የተሰኘ መጽሐፍ ሳነብ ‹‹ጨረቃዋን እያየህ፣ ጨለማውን ግን እየተጠነቀቅ ተጓዝ›› የሚል ጥንታዊ ብሂል አየሁ፡፡ ይህ ለጥንቱ መንገደኛ የተሰጠ የጠቢብ ምክር ነው፡፡
የጥንቱ ተጓዥ ጤፍ በምታስለቅመው ጨረቃ መጓዙ ሁለት ጥቅሞች ይሰጡት ነበር፡፡ በአንድ በኩል በቀን ከሚገጥመው ሙቀትና የፀሐይ ቃጠሎ ይድናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መንገዱን በሩቁ ስለማያየው ‹ለካ ገና ብዙ መንገድ ይቀረኛል› እያለ መንፈሱ እንዳይደክም ያደርገዋል፡፡
በተለይም ደግሞ መንገደኞቹ በዛ ካሉ፣ ሰብሰብ ብለው በአንድ ቤት ታዛ ሥር ወይም በአንድ ዛፍ ጥላ ሥር ያርፉና በአራተኛው ክፍለ ሌሊት(ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት በኋላ) ተነሥተው የጨረቃዋን ብርሃን እየተከተሉ መጓዝ ነው፡፡ ያን ጊዜ  ነው እንግዲህ ‹ከጨለማው እየተጠነቀቁ፣ ነገር ግን ጨረቃዋን እያዩ›› የሚጓዙት፡፡

Monday, September 22, 2014

እምቢታ (የቃቄ ወርድወት)

ደራሲ - እንዳለ ጌታ ከበደ
ዋጋ - 49 ብር
አታሚ - ኤች ዋይ ማተሚያ ቤት
እንዳለ ጌታ የጻፈውን እምቢታ መጽሐፍ ከአዲስ አበባ ወደ አውስትራልያ እየተጓዝኩ አውሮፕላን ውስጥ ነው ያነበብኩት፡፡ መጽሐፉ ለገበያ ሲቀርብ እንደማልኖር ስላወቀ ቀድሜ እንዳገኘው በማድረጉ አመሰግነዋለሁ፡፡ ይኼ በታሪክና በሥነ ቃል(ፎክሎር) ላይ የተመሠረተ ልቦለድ በአንዲት ብዙዎቻችን በማናውቃት ከዘመን የቀደመች ሴት ጀግና ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡
ቃቄ ወርድወት ትባላለች፡፡ በነገራችን ላይ ቃቄ የአባቷ ስም ነው፡፡ የእርሷ ስም ወርድወት ነው፡፡ በጉራጌ ባሕል የአባትን ስም ከልጅ የሚያስቀድም ጥንታዊ ሥርዓት ነበረ ማለት ነው፡፡ ምናልባትም በዕውቀቱ ስዩም ‹በኢትዮጵያ ከልጅ ስም በፊት የአባት እንደሚቀድም ማስረጃ አለኝ› ያለው አንዱ ይኼንን ሳይሆን አይቀርም ብዬ ገምቻለሁ፡፡ የመጽሐፉን ረቂቅ መመልከቱን መግቢያው ላይ ያሳያልና፡፡

Friday, September 12, 2014

ሰነቦ

ነሐሴ 23 ቀን 2006 ዓም ማለዳ 10 ሰዓት ነው ከዕንቅልፌ የነቃሁት፡፡ ዲያቆን  ሙሉቀን ብርሃን ከጎንደር፣ ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ ከፍኖተ ሰላም መንገድ ላይ ይጠብቁኛል፡፡ ለመንገዱ የሚሆነውን የቱሪስት መኪና ያዘጋጀልኝ የኦሪጂንስ ኢትዮጵያ አስጎብኝ ድርጅት ባለቤት ሳምሶን ተሾመ ነው፡፡ ክብር ይስጥልኝ ብያለሁ፡፡ የምተርክላችሁን ታሪክ ስትጨርሱ ትመርቁታላችሁ ብየ አምናለሁ፡፡ የምጓዘው አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ ለማደርገው ጥናት ተጨማሪ መረጃዎችን ፍለጋ ነው፡፡
ሾፌራችን ደምስ ይባላል፡፡ ዝምታና ትኩረት ገንዘቦቹ የሆኑ፣ በሁሉም ነገር ለመንገድ የተዘጋጀ፡፡ ለተራራ ቢሉ ለቁልቁለት፣ ለበረሐ ቢባል ለደጋ የሚሆኑ መሣሪያዎችን ሸክፎ የያዘ ልምድ ያለው ሾፌር ነው፡፡

Friday, September 5, 2014

ጳጉሜን - አምስት፣ ስድስት፣ ሰባት

የመግቢያ ማስታወሻ
በጽሑፉ ውስጥ በግእዝ ቁጥሮች በቅንፍ ውስጥ የተጻፉት ሐሳቡን እንዲወክሉ ብቻ ነው፡፡ በኋላ (ቁጥር ፭ ተመልከት ቢል ያንን ሐሳብ መልሶ ለማየት እንዲረዳ ነው፡፡
የኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር ለየት ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ጳጉሜ የምትባል አሥራ ሦስተኛ ወር ስላለችን ነው፡፡ የቤት ኪራይና የወር ደመወዝ የማንከፍልባትና የማንቀበልባት፤ መብራትና ውኃ ግን ከነሐሴ ወር ጋር ጨምረው የሚያስከፍሉባት፤ ሲሻት አምስት፣ ሲያስፈልጋት ስድስት፣ ስትፈልግ ደግሞ ሰባት የምትሆን ወር ናት፡፡ እንዲያውም ከአሥራ ሁለቱ የኢትዮጵያ ወሮች ጳጉሜ በብዙ መንገድ የተለየች ናት፡፡
በአንድ በኩል በጣም ትንሿ ወር ናት፡፡ ሲቀጥልም ወርኃዊ በዓላት የማይውሉባት ወር ናት፡፡ እንዲያም ሲል ደግሞ ከሌሎች ወሮች በተለየ የቀኖቿ መጠን የሚቀያየሩ ብቸኛ ወር ናት፡፡ ከሌሎች የኢትዮጵያ ወሮች በተለየም ስሟ ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ወር ናት፡፡ በሁለት ዘመናት መካከልም እንደ መሸጋገሪያ የምትታይ ወርም ናት፡፡  

Tuesday, September 2, 2014

ዝሆን (ክፍል ሦስትና የመጨረሻው)

ዝሆኖች አንድ የታመመ ወይም የቆሰለ ወገን ካላቸው እስኪድን ድረስ ይከባከቡታል፡፡ ምግብ ያቀርቡለታል፤ ከአደጋም ይጠብቁታል፡፡ ለዚህ ሁሉ ድካማቸው በኩምቢ የሚገለጥ ‹እግዜር ይስጥልኝ› በቂያቸው ነው፡፡ አንድ ቀን ግማሽ ኪሎ ብርቱካን ይዘን የጠየቅነውን በሽተኛ ሁሉ ውለታችንን ካልመለሰ ለምንል ሰዎች ከእኛ የሚሻሉ እንስሳት መኖራቸውን ማወቅ እንዴት መልካም መሰላችሁ፡፡
ዝሆኖች ይቅር ባዮች ናቸው፡፡ ዝሆን አደጋ የደረሰበትንም ያደረሰበትንም አይረሳም ይባላል፡፡ ጊዜ ጠብቆ የመበቀል አመል አለው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ችግር የፈጠረባቸው ኅብረተሰብ ወይም ግለሰብ ሲከባከባቸውና ለእነርሱ መልካምን ነገር ሲያደርግ ከተመለከቱ በቀላቸውን ሁሉ ለመተውና ይቅር ለማለት ፈጣኖች ናቸው፡፡ ይቅርታ ለመበቀል አለመቻል አይደለም፡፡ አለመፈለግ እንጂ፡፡ ይቅርታ ከዐቅም ማጣት ሳይሆን ከዐቅም ማግኘት የሚፈጠር ነው፡፡ በዝሆኖች መንጋ መካከል ችግር ፈጣሪ ከተገኘና ከተቀጣ ሁሉም ዝሆኖች ያገሉታል፡፡ ተስተካክሎ ከመጣ ግን ኩምቢያቸው በማነካካት ይቅር ማለታቸውንና መተዋቸውን ይገልጡለታል፡፡ ከዚያ በኋላ አለቀ፡፡ ሰውን ‹እንስሳ› ብለን የምንሳደብ እኛ ለይቅርታ የተዘጋጀ ልብ የለንም ማለት ከዝሆን ያነስን ነን ማለታችን ነው፡፡