Thursday, August 28, 2014

ዝሆን (ክፍል ሁለት)


ዝሆኖች ለቤተሰባዊ ሕይወት ልዩ ቦታ አላቸው፡፡ የዝሆን መንጋ በእናት የሚመራ ነው፡፡ የሰው ልጅ ሴቶችን ወደ መሪነት ሳያመጣ፣ እነ ንግሥተ ሳባና ንግሥት ሕንደኬም ሀገር ሳይመሩ በፊት ዝሆኖች የእናቶችን መሪነት ተቀብለዋል፡፡ በዝሆኖች መንጋ ውስጥ ታላቅ መሆን ክብርንም ያመጣል ኃላፊነትንም ያስከትላል፡፡ እኛ ሀገር ብዙ ጊዜ ‹ታላቅነት› ክብርን ብቻ እንዲያመጣ ይታሰባል እንጂ ኃላፊነትን እንዲያስከትል አይፈለግም፡፡ በዝሆኖች ዘንድ ግን ታላቅ እናት ትከበራለችም፣ ኃላፊነት ትወስዳለችም፡፡

በማለዳ የዝሆኖች ውሎ ሲጀመር የዝሆን ቤተሰብ ለተግባር ሥምሪት ይወጣል፡፡ ብዙ ጊዜ አንድ ቤተሰብ ከ12 አባላት በላይ አይበልጥም፡፡ ይህም ልጆችንና የቅርብ ዘመዶችን ያካትታል፡፡ እናት ዝሆን ይህን ቤተሰብ በመምራት ወደ ምግብ ሥምሪት ስትነቃነቅ አመራርዋን የሚፈልጉ ሌሎች ዝሆኖች ይቀላቀሏታል፡፡ ወደ ረፋድ ላይ የመንጋው ቁጥር ወደ 25 ይደርሳል፡፡ ፀሐይ ልታቆለቁል ስታስፈራራ የመንጋው ቁጥር ወደ አንድ መቶ ያሻቅባል፡፡ ሲመሽ የመንጋው ቁጥር እየቀነሰና ሁሉም በየቤቱ እየገባ ይሄድና ወደ ቀደመው አሥራ ሁለት የቤተሰብ አባላት ይመለሳል፡፡ ይህ ሁሉ የሚመራው በአንዲት አረጋዊት ታላቅ እናት ነው፡፡
አንዳንድ የዝሆንን ጠባይ ያጠኑ ሊቃውንት ይህንን የዝሆኖች የዕለት ጉዞ ከሰዎች የዕለት ጉዞ ጋር አያይዘው አይተውታል፡፡ በየማለዳው ኑሮን ስንወጥን የምንጀምረው ከቤተሰባችን ነው፡፡ ወጣ ብለን ሠፈርተኛውን እናገኛለን፤ በመንገዳችንና በሥራ ቦታችን ደግሞ ከከተማው ነዋሪ፣ ከደንበኞች፣ ከሻጮች፣ ከተማሪዎች፣ ከገበያተኞች፣ ከተሳፋሪዎችና ከሌሎቹም ጋር እየተቀላቀልን ቁጥራችን እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ፀሐይ ወደ ማደሪያዋ ልትገባ ስትል በሄድንበት መንገድ ወደ ኋላ በመመለስ ቁጥራችን እየቀነሰ ይመጣና የመጨረሻ ማረፊያችን ቤተሰባችን ይሆናል፡፡

በዝሆኖች ላይ ጥናት ያደረጉ ሊቃውንት ለመሪነት የምትመረጠው ታላቅ እናት ሁለት ዋና ዋና ብቃቶች እንዳሏት አስተውለዋል፡፡ ጽናትና ችግርን የመፍታት ብቃት፡፡ ባለሞያዎቹ ‹ጽናት› ሲሉ ‹‹ችግርን የመቋቋም ችሎታ፣ ከፈተና ለመውጣት መንገዶችን የመተለም ዐቅም፣ ከችግር በአፋጣኝ ወጥቶ በአስቸኳይ ወደ ነበሩበት ጤናማ ሁኔታ ለመመለስ መቻልና ሳይረበሹ፣ ሳይደናገጡና ተስፋ ሳይቆርጡ ከችግሮች በኋላ አመራርን በብስለት ለመቀጠል መቻል› ማለታቸው ነው፡፡ የሀገራችንን የመልካም አስተዳደር እጦት ችግር ለመፍታትም እነዚህ ሁለቱ ችሎታዎች ያሏቸውን መሪዎች መመደብ ሳይኖርብ አይቀርም፡፡ ችግር ፈጣሪዎችን ሳይሆን ችግር ፈችዎችን፡፡ በሚከሰቱ ነገሮች ተደናግጠው መሥመራቸውን የሚስቱትን ሳይሆን ማዕበሉን ተቋቁመው ወደ ጥንት ግብራቸው ለመመለስ ዐቅም ያላቸውን፡፡
የዝሆንን መንጋ የምትመራው ታላቅ እናት እንዲሁ አትመረጥም፡፡ ሊመጣ የሚችለውን አደጋ ቀድማ የመገመት፣ የተሻለውን የምግብ ማግኛ ቦታ የማወቅ፣ ለግልገል ዝሆኖች ልምዷን የማካፈል፣ አስቸጋሪ ዝሆኖችን ሊታረሙ በሚችሉበት መንገድ የመቅጣት የካበተ ልምድ ያላት ናት፡፡ ብዙ ጊዜ መሪ እናቶች በጠባያቸው ጭምቶች፣ የተረጋጉ፣ ከግንፍልተኛነት የጸዱ እንደሆኑ ጥናቶቹ አሳይተዋል፡፡ የሚያስቆጡና ግብታዊ ርምጃ እንዲወሰድ የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ እንኳን ቀድማ የኃይልና የጉልበት ርምጃ ለመውሰድ አትቸኩልም፡፡ መንጋውን ማረጋጋትና ችግሩ ሳይከሰት ከፈተናው የሚወጣበትን መንገድ ማመላከትን ታስቀድማች፡፡ ግልገሎቹ ሲያጠፉም ማረምን እንጂ መቅጣትን የመጀመሪያ ተግባሯ አታደርገውም፡፡
ዝሆን ቆዳው ጠንካራ ነው፡፡ አያሌ ቆንጥሮችን፣ እሾህና አሜከላዎችን፣ ቁጥቆጦዎችንና ጥሻዎችን ያቋርጣል፡፡ ቅጠሎችን ለማግኘት ወደ ዛፎቹ ሲንጠራራ ከተጎረዱ ቅርንጫፎችና ካገጠጡ ቅርፊቶች ጋር ይታገላል፡፡ ይህንን ሁሉ እንዲቋቋም ፈጣሪ ለዝሆን ደንዳና ቆዳ ሰጥቶታል፡፡ የዝሆን ቆዳ እስከ አንድ ኢንች የሚደርስ ውፍረት አለው፡፡ ይህ የቆዳ ውፍረት ለሁለት ነገሮች ጠቅሞታል፡፤ በአንድ በኩል በመቧጨርና በመጎንተል ከሚመጡበት አደጋዎች ለመቋቋም በሌላ በኩል ደግሞ በመንገዱ ላይ የሚገኙ ቆንጥሮች እሾሆች፣ ቁጥቋዎችና ጥሻዎች እዚህመ፣ እዚያም ለሚፈጥሩበት ውጋትና ቡጭረት ትኩረት ሳይሰጥ መንገዱን እንዲቀጥል፡፡

ሰው እንደ ዝሆን ቢሆን እንዴት መልካም ነበር፡፡ በመንገድ ላይ ለሚገኙት ቁጥቋጦዎች፣ ቡጭሪያዎችና ውጊያዎች ሁሉ ተበሳጭተን፣ አልቅሰን፣ ተናድደን፣ መልስ ሰጥተን እንዴት እንችለዋለን፡፡ ታማን፣ ተሰደብን፣ ስማችን ጠፋ፣ ተነካን፣ እያልን በየዕለቱ የምንንገበገብ ከሆነ ወደ ዓላማችን መድረስ እጅግ ከባድ ይሆንብናል፡፡ ለዋናው ግብ ሲባል አንዳንዱን ነገር መሻገር፣ አንዳንዱን ነገር ችሎ ማለፍ፣ አንዳንዱን ነገር እንዳላዩ መሆን፣ አንዳንዱንም ነገር ቁብ አለመስጠት ይገባል፡፡ አቡነ ጎርጎርዮስ ታላቁ ‹ሥራህን ሥራ፤ አንበሳው ሲያጓራ ፍንክች አትበል፤ የሰይጣንን ውሻዎች ለመውገር አትቁም፤ ጥንቸሎቹን በማባረር ጊዜህን አታጥፋ፤ ዝም ብለህ ሥራህን ሥራ› ሲሉ የመከሩት ለዚህ ሳይሆን አይቀርም፡፡
ዝሆኖች ወገኖቻቸውን አይረሱም፡፡ የሞቱ ወገኖቻቸውን ከማይረሱ ጥቂት እንስሳት መካከል ዝሆኖች አንዱ ናቸው፡፡ የሞተበትን አካባቢ በተደጋጋሚ ይጎበኙታል፡፡ አንድ ዝሆን ከመንጋው ተለይቶ ለብዙ ጊዜ ቆይቶ ቢመለስ ልዩ የሆነ የደስታ አቀባበል ይጠብቀዋል፡፡ ኩንቢያቸውን በማነካካትና በማጠላለፍ አገላብጠው ይስሙታል፡፡ ጤንነቱን በሚጠይቅ መልኩ የሚያወጡት የተለየ ድምጽም አላቸው፡፡ ፍቅርና ደኅንነት ተሰምቶት ከመንጋው ጋር እንደገና እንዲቀላቀል እንጂ እንዲገለል አያደርጉም፡፡ እንዲያውም ሰዎች በዚህ ረገድ ሲቸግረን ያታያል፡፡ አንድን ያጠፋ ሰው መልሶ ለመቀበል፤ አንድን የበደለንን ሰው ይቅር ብሎ እንደ ቀደመው ለመሆን፣ ወይም አንድን ከወኅኒ ታርሞ የመጣን ሰው ደኅና ነው ብሎ ለመቀበል ይቸግረናል፡፡
(ይቀጥላል)

15 comments:

 1. ምነው ሰዎች ከዝሆኖች ብንማር፡፡ አይ ዝሆን እስኪ ለዓለም ይህንን ስበክ ምናልባት በአንተ ስብከት እንመለስ ይሆን ማን ያውቃል፡፡ ስውንማ ሰው ሰብኩት፣ አስተምሮት አልሰማ፣ አልመለስ ብሏል፡፡ ሴቶች እናቶቻችን. እህቶቻችን ወደ ሹመተ ሲመጡ ለቁጥር ማሟያ እናዳንጠቀምባቸው ሴቶችም ይህንን ሲቀበሉ ኃላፊነታችሁን ተጠቀሙበት ሌላ ምን ይባላል፡፡ አይ ሰው…………….. ጥሩ እይታ ነው ዳ/ነ ዳንኤል ፡፡በርታ

  ReplyDelete
 2. ሥራህን ሥራ፤ አንበሳው ሲያጓራ ፍንክች አትበል፤ የሰይጣንን ውሻዎች ለመውገር አትቁም፤ ጥንቸሎቹን በማባረር ጊዜህን አታጥፋ፤ ዝም ብለህ ሥራህን ሥራ

  ReplyDelete
 3. ምነው ሰዎች ከዝሆኖች ብንማር፡፡ አይ ዝሆን እስኪ ለዓለም ይህንን ስበክ ምናልባት በአንተ ስብከት እንመለስ ይሆን ማን ያውቃል፡፡ ስውንማ ሰው ሰብኩት፣ አስተምሮት አልሰማ፣ አልመለስ ብሏል፡፡ ሴቶች እናቶቻችን. እህቶቻችን ወደ ሹመተ ሲመጡ ለቁጥር ማሟያ እናዳንጠቀምባቸው ሴቶችም ይህንን ሲቀበሉ ኃላፊነታችሁን ተጠቀሙበት ሌላ ምን ይባላል፡፡ አይ ሰው…………….. ጥሩ እይታ ነው ዳ/ነ ዳንኤል ፡፡በርታ

  ReplyDelete
 4. ድንቅ የዝሆን ተፈጥሮ-ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡

  ReplyDelete
 5. እስቲ ከድቃቃይቱ ጉንዳን ኣልማር ብለናልና ከግዙፉ ዝሆን እንማር መቼም የኛ ነገር በትልቅ ካልታየ ኣልገባ እያለን ተቸግረናልየኛ ትውልድ መጨረሻው??ወንድማችን እግዚኣብሄር ይባርክልን ቀጥልበት ምን ይሳነዋል ታሪካችንን ይቀይርልን ይሆናል???

  ReplyDelete
 6. "በሚከሰቱ ነገሮች ተደናግጠው መሥመራቸውን የሚስቱትን ሳይሆን ማዕበሉን ተቋቁመው ወደ ጥንት ግብራቸው ለመመለስ ዐቅም ያላቸውን፡፡" as we all know if 1997 election happned our country never change. At the movement we see train, condeminium, Abay, new road,

  ReplyDelete
 7. Dikon Daniel egziabher yebarkeh. betam astamari yohon meleket new. betame new yewedekut. lemtegberem emokeralhu

  ReplyDelete
 8. ሰውም ሞቱ ለትንሣኤ፣ ድካሙ ለብርታት፣ ዕረፍቱ ለሥራ፣ ኀዘኑ ለደስታ፣ ውድቀቱ ለመነሣት፣ ስሕተቱ ለእርማት፣ ማጣቱ ለማግኘት፣ ሕመሙ ለድኅነት በሚሆን መልኩ መሆን አለበት፡፡ እንዳይነሣ ሆኖ መውደቅ፣ እንዳይተርፍ ሆኖ መክሰር፣ እንዳይከብር ሆኖ መዋረድ፣ እንዳይፈታ ሆኖ መታሠር፣ እንዳይመለስ ሆኖ መሄድ፣ እንዳይታረቅ ሆኖ መጣላት የለበትም፡፡ የማርያም መንገድ መተው ያስፈልጋል፡፡ የአንድ ነገር መጨረሻ የሌላ ነገር መጀመሪያ መሆን አለበት፡፡ ከሥራ ማረፍ ለሌላ ሥራ መዘጋጃ፣ የዛሬ ዕንቅልፍ ለነገ ብርታት ኃይል መሰብሰቢያ፣ የዛሬ ሞት ለነገ ትንሣኤ መራመጃ መሆን አለበት፡፡

  ReplyDelete
 9. ሰውም ሞቱ ለትንሣኤ፣ ድካሙ ለብርታት፣ ዕረፍቱ ለሥራ፣ ኀዘኑ ለደስታ፣ ውድቀቱ ለመነሣት፣ ስሕተቱ ለእርማት፣ ማጣቱ ለማግኘት፣ ሕመሙ ለድኅነት በሚሆን መልኩ መሆን አለበት፡፡ እንዳይነሣ ሆኖ መውደቅ፣ እንዳይተርፍ ሆኖ መክሰር፣ እንዳይከብር ሆኖ መዋረድ፣ እንዳይፈታ ሆኖ መታሠር፣ እንዳይመለስ ሆኖ መሄድ፣ እንዳይታረቅ ሆኖ መጣላት የለበትም፡፡ የማርያም መንገድ መተው ያስፈልጋል፡፡ የአንድ ነገር መጨረሻ የሌላ ነገር መጀመሪያ መሆን አለበት፡፡ ከሥራ ማረፍ ለሌላ ሥራ መዘጋጃ፣ የዛሬ ዕንቅልፍ ለነገ ብርታት ኃይል መሰብሰቢያ፣ የዛሬ ሞት ለነገ ትንሣኤ መራመጃ መሆን አለበት፡፡

  ReplyDelete
 10. ወይ አለመታደል! ከሌላው አገር ህዝብ በፊት ሰልጥኖ የነበረው የአክሱም ዘመን ትውልድ ፡ ዛሬ በሱ ቦታ ተተክተን ፡ በዝሆን አኗኗር የምንቀናውን ቢያይ ምን ይል?

  ReplyDelete
 11. ሰው እንደ ዝሆን ቢሆን እንዴት መልካም ነበር፡፡ በመንገድ ላይ ለሚገኙት ቁጥቋጦዎች፣ ቡጭሪያዎችና ውጊያዎች ሁሉ ተበሳጭተን፣ አልቅሰን፣ ተናድደን፣ መልስ ሰጥተን እንዴት እንችለዋለን፡፡ ታማን፣ ተሰደብን፣ ስማችን ጠፋ፣ ተነካን፣ እያልን በየዕለቱ የምንንገበገብ ከሆነ ወደ ዓላማችን መድረስ እጅግ ከባድ ይሆንብናል፡፡ ለዋናው ግብ ሲባል አንዳንዱን ነገር መሻገር፣ አንዳንዱን ነገር ችሎ ማለፍ፣ አንዳንዱን ነገር እንዳላዩ መሆን፣ አንዳንዱንም ነገር ቁብ አለመስጠት ይገባል፡፡ አቡነ ጎርጎርዮስ ታላቁ ‹ሥራህን ሥራ፤ አንበሳው ሲያጓራ ፍንክች አትበል፤ የሰይጣንን ውሻዎች ለመውገር አትቁም፤ ጥንቸሎቹን በማባረር ጊዜህን አታጥፋ፤ ዝም ብለህ ሥራህን ሥራ› ሲሉ የመከሩት ለዚህ ሳይሆን አይቀርም፡፡

  ReplyDelete
 12. Replies
  1. dani keniser kelelo sele Zihon selesaf bet des yemil neger new "egizihaber bandem belelam yasetemiral sew gen ayasetewelem'' Thank you again.

   Delete
 13. ዝሆን እስኪ ለዓለም ይህንን ስበክ ምናልባት በአንተ ስብከት እንመለስ ይሆን ማን ያውቃል፡፡

  ReplyDelete