Tuesday, August 26, 2014

ዝሆን

(ክፍል አንድ)
የዝሆን ሥዕል፣ ወሎ ገነተማርያም ቤተ ክርስቲያን
በሰው ልጆች የአደን፣ የጦርነት፣ የንግድ፣ የባሕልና የሃይማኖት ታሪክ ውስጥ ቦታ ካላቸው እንስሳት አንዱ ዝሆን ነው፡፡ ዝሆን ማደን የጀግንነት መገለጫ ሆኖ አዳኞቹን ሲያስመሰግንና ሲያስወድስ ኖሯል፡፡ በቀደምት ዘመናት በተደረጉ ጦርነቶችም ዝሆኖች የዛሬዎቹን ታንኮች ቦታ ተክተው አገልግለዋል፡፡ የአኩስሙ አብርሃ ከደቡብ የመን ወደ መካ ባደረገው የጦርነት ጉዞ አያሌ ዝሆኖችን ተጠቅሞ ስለነበር ዘመኑ ‹የዝሆኖች ዓመት› እየተባለ እስከ መጠራት ደርሶ ነበር፡፡ በበጥሊሞሳያን ዘመንም ግብጻውያን ከኢትዮጵያና አካባቢዋ ዝሆኖችን በመውሰድ ለጦርነት ተጠቅመውባቸዋል፡፡ 
የዝሆን ጥርስ ለጌጣጌጥ መሥሪያ መዋል የጀመረው ከክርስቶስ ልደት በፊት በነበሩ ጥንታውያን ሥልጣኔዎች ዘመን ነው፡፡ ይህ የዝሆን ጥርስ ንግድ ዝሆኖችን ከልዩ ልዩ አካባቢዎች እንዲጠፉና ዛሬም ቁጥራቸው እንዲመነምን ዋናውን ክፉ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡

ዝሆን በልዩ ልዩ ባሕሎችና ሃይማኖቶች ዘንድ የጥንካሬ፣ ወድቆ የመነሣት፣ ታላቅን የማክበርና የማስታወስ ተምሳሌት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ ላይ የምናገኘው የ‹ዐቢይ ነጌና የውርዝው ነጌያት› ምሳሌ ለዚህ ማሳያ ይሆናል፡፡ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍልም ‹ሔርማዝ› የሚለው ጥንታዊ የዝሆን መጠሪያ  ለ‹ጀግና› የሚሰጥ ስያሜ ሆኗል፡፡ በሀገራችን የአደን ታሪክ ውስጥ ከአንበሳ ገዳይ ቀጥሎ ክብር የነበረው ዝሆን ገዳይ መሆኑ ይነገራል፡፡
በሀገራችን ጥንታዊ ሥዕሎች ውስጥ የዝሆንን ሥዕል በስፋት እናገኛለን፡፡ በተለይም ከ15ኛው መክዘ በፊት የተሣሉ የግድግዳ ሥዕሎች ዝሆንን በየማዕዘናቱ ያስቀምጡታል፡፡ በወሎ እመኪና ልደታ ለማርያምና ገነተ ማርያም አብያተ ክርስቲያናት ግድግዳ ላይ የሚገኘው የ14ኛው መክዘና ከዚያ ቀደም ብሎ የተሳሉት የዝሆን ሥዕሎች ለዚህ ምሳሌ ሆነው ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡
የዝሆን ሥዕል፣ ወሎ እመኪና ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን
በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ ወደ ስድስት መቶ ሺ፣ በሕንድ ደግሞ ከ30 እስከ ሃምሳ ሺ የሚደርሱ ዝሆኖች እንደሚገኙ ይገመታል፡፡ 1.3 ሚሊዮን ይደርስ የነበረው የአፍሪካ ዝሆኖች ቁጥር አሁን ወዳለበት መጠን ያሽቆለቆለው እኤአ ከ1979-1989 ዓም ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እኤአ በ2007 ዓም በተደረገው ጥናት 1200 የሚደርሱ ዝሆኖች እንደነበሩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በዓለም እንደደረሰው የዝሆኖች እልቂት ሁሉ በ1980ዎቹ ብቻ 90 በመቶ የሚሆኑት የኢትዮጵያ ዝሆኖች ከምድረ ገጽ ጠፍተዋል፡፡
የጥንት ሰዎች የዝሆንን የተፈጥሮ ጠባያት በመረዳት ለእምነታቸው መግለጫ፣ ለሥነ ምግባራቸው ማስተማሪያና ለፍልስፍናቸው ማሳያ አድርገውት ነበር፡፡ በሕንድ፣ በፋርስና በመካከለኛው ምሥራቅ ከ8ኛው መክዘ ጀምሮ የታወቀው ‹የዝሆኑና የስድስቱ ዓይነ ሥውራን› ታሪክ በብዙ ጥንታውያን አስተምህሮዎች ውስጥ ለልዩ ልዩ ጥበብ፣ ፍልስፍናና ሞራል ማስተማሪያነት ውሎ ነበር፡፡
ዝሆን የጠንካራ ነገር ግን ተጣጣፊ ኩምቢ ባለቤት ነው፡፡ ይህ 150 ሺ ጡንቻዎች ያሉት የዝሆን ኩምቢ 600 ጡንቻዎችን ብቻ ከያዘው የሰው ዘር ጋር ሲነጻጻር ጥንካሬውን ማሳየት ይችላል፡፡ የዝሆን ኩምቢ ይህንን ያህል ጠንካራ ቢሆንም አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ግን የሚገባውን አገልግሎት ለመስጠት እንዲያስችለው ወደፈለገው አቅጣጫ ያጣጥፈዋል፡፡ ሰውም በአቋሙ እንደ ዝሆን ኩምቢ ጠንካራ መሆን አለበት፡፡ ነገር ግን አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ከነገሮችም ጋር አብሮ ለመጓዝ የሚችል፡፡ ጥንካሬው እንደ እንጨት ሳይሆን እንደ ብረት፡፡ እንጨት ይሰበራል እንጂ መተጣጠፍ አይችልም፡፡ ብረት ግን ጠንካራ ቢሆንም ተጣጣፊ ነው፡፡ የሰው ዓላማ ተጣጣፊ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ እንዲያ ከሆነ የመጣ ጎርፍ ሁሉ የሚወስደው፣ የበረታ ዱላ ሁሉ የሚነዳው ይሆናል፡፡ በሌላም በኩል ደግሞ ሰው እንደ ጅብራ የሚገተር፣ እንደ እንጨትም ደርቆ የሚቀር መሆን የለበትም፡፡ እንዲያ ከሆነ እኔ ብቻ ትክክል ነኝ፣ እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን የሚል ግለኝነት ይጠናወተዋል፡፡ ሰው እንደ ዝሆን ኩምቢ በዓላማው ጠንካራ ሆኖ፣ ደግሞም ዓላማውን ሳይለቅ አማራጮችንና የተሻሉ መንገዶችን ለማየት ዕድል የሚሰጥ፣ አመዛዝኖ ለመቀበልና ከተሻለው ነገር ጋር ለመራመድ የሚችል መሆን አለበት፡፡


የዝሆን ኩምቢ
ዝሆን ሚዛናዊ ነው፡፡ ዝሆን በዓለማችን ትልቁ አጥቢ እንስሳ ነው፡፡ ክብደቱ እስከ ስድስት ሺ ኪሎ ግራም ይደርሳል፡፡ ይህንን ያህል ክብደቱን እስከ 3.3 ሜትር በሚደርሰው ቁመቱ ውስጥ ይይዘዋል፡፡ ይህንን ሁሉ ክብደት የያዘው ዝሆን ቅጠል በል መሆኑ የተነሣ የዛፎቹን ቁመት ተከትሎ ቀጭኔ በአንገቷ የምትደርስበት ቦታ ድረስ መድረስ የግድ ይለዋል፡፡ እዚህ ላይ ትልቁ ጥያቄ እንዴት? የሚለው ነው፡፡
የዝሆን አንዱ ችሎታ የሚለካው ለዚህ ጥያቄ በሚሰጠው መልስ ነው፡፡ ሁለት የፊት እግሮቹን ወደ ላይ በማውጣት በሁለት የኋላ እግሮቹ መሬቱን እንደ ችካል ተክሎ ይይዘዋል፡፡ ከዚያም ኩምቢውን እንደ ሰጎን አንገት በመምዘዝ የዛፉ ጫፍ ላይ ይደርሳል፡፡ ይህንን ተግባር ለማከናወን የሚችለው ዝሆን ሚዛናዊ ስለሆነ ነው፡፡ ክብደቱን፣ ቁመቱን፣ የነፋሱን ኃይል፣ የዛፎቹን ንቅናቄና የሚገነድሰውን ዛፍ ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሚዛኑን ሳያዛንፍ በሁለት እግሮቹ መጠበቅ ይችላል፡፡ ጠንካራ ሰው ማለትም እንዲህ ነው፡፡ ምንም ያህል ከባድ ኃላፊነት ቢኖርበት፣ ምንም ያህል አስቸጋሪ ሥራ ቢሠራ፣ ምንም ያህል ወደ ላይ ቢንጠራራ፣ ምንም ያህል እንደ ነፋስ ጠንካራ የሆነ ፈተናና ትችት ቢዘንብበትም ሚዛኑን ሳይስት ወደ ዓላማው መጓዝ አለበት፡፡ ለዚያ ደግሞ ሁለት ነገሮች ያስፈልጋሉ፡፡ እንደ ዝሆን ሁለት እግሮች ጸንተው የሚተከሉ መሠረታዊ እምነቶች፣ እንደ ሁለቱ የፊት እግሮችም ወደ ላይ የሚንጠራሩ ራእዮችና ግቦች ያስፈልጋሉ፡፡
ወደፊት ለመጓዝ ዛሬ የምንተከልበት፣ ተተክለንም የምንቆምበት ነገር ያስፈልጋል፡፡ ትናንት ላይ ሳይተከሉ ወደ ዛሬ፣ ዛሬ ላይ ሳይተከሉ ወደ ነገ መጓዝ አይቻልም፡፡ ማንኛውም አውሮፕላን በሰማይ ላይ ለመብረር ከፈለገ ማኮብኮቢያ ሜዳ ያስፈልገዋል፡፡ ወደ ነገ የሚጓዝ ማንም ቢኖር የሚተከልበት የትናንት ታሪክ፣ ባሕል፣ ቅርስና ጥሪት ያስፈልገዋል፡፡
ዝሆን የሚተኛው ለመነሣት እንዲመቸው ሆኖ ነው፡፡ መሬት ላይ ከወደቀ ለመነሣት ይቸገራል፡፡ ክብደቱ ትልቅ ነውና፡፡ ስለዚህም የሚተኛው ዛፍ ተደግፎ ነው፡፡ የዝሆን ዕንቅልፍ ፍጹም ዕንቅልፍ አይደለም፡፡ ለመነሣት ያኮበኮበ ዕንቅልፍ ነው፡፡ የሚተኛው ለመነሣት በሚችልበት መንገድ ነው፡፡ ሰውም ሞቱ ለትንሣኤ፣ ድካሙ ለብርታት፣ ዕረፍቱ ለሥራ፣ ኀዘኑ ለደስታ፣ ውድቀቱ ለመነሣት፣ ስሕተቱ ለእርማት፣ ማጣቱ ለማግኘት፣ ሕመሙ ለድኅነት በሚሆን መልኩ መሆን አለበት፡፡ እንዳይነሣ ሆኖ መውደቅ፣ እንዳይተርፍ ሆኖ መክሰር፣ እንዳይከብር ሆኖ መዋረድ፣ እንዳይፈታ ሆኖ መታሠር፣ እንዳይመለስ ሆኖ መሄድ፣ እንዳይታረቅ ሆኖ መጣላት የለበትም፡፡ የማርያም መንገድ መተው ያስፈልጋል፡፡ የአንድ ነገር መጨረሻ የሌላ ነገር መጀመሪያ መሆን አለበት፡፡ ከሥራ ማረፍ ለሌላ ሥራ መዘጋጃ፣ የዛሬ ዕንቅልፍ ለነገ ብርታት ኃይል መሰብሰቢያ፣ የዛሬ ሞት ለነገ ትንሣኤ መራመጃ መሆን አለበት፡፡
በዝሆን መንጋ ዘንድ ታላላቆች ወሳኝ ቦታ አላቸው፡፡ ይከበራሉ፤ ይሰማሉ፤ ይመራሉ፤ ያስተምራሉ፤ ትውልድም ቀርፀው ያፈራሉ፡፡ መንጋው ሲጓዝ መንገድ የሚመሩት፤ ለአዳጊዎች ልምዳቸውን የሚያካፍሉት፤ መንጋውን ከአደጋ የሚጠብቁት፤ ጥፋተኛውን ጎረምሳም የሚቀጡት ታላላቆች ናቸው፡፡ ታላላቆች የሌሉበት መንጋ እሥር ቤት እንደሰበረ ማፊያ ይሆናል፡፡ በአንድ ወቅት በደቡብ አፍሪካ ክሩገር ፓርክ ውስጥ የሚገኙ ዝሆኖች ቁጥራቸው ጨመረና ከፓርኩ ዐቅም በላይ ሆኑ፡፡ ቁጥራቸውን ከፓርኩ ዐቅም ጋር ለማመጣጠን እንዲቻል የተወሰኑትን ዝሆኖች ወደ ሌላ ፓርክ ለመውሰድ ተወሰነ፡፡ ዝሆኖቹ እንዲሄዱ የታሰበው በሄሊኮፕተር እየተንጠለጠሉ ነበር፡፡ ሄሊኮፕተሩ ትልልቆቹን ዝሆኖች ለመጫን ዐቅም ስላነሰው ወጣቶቹ ዝሆኖች እየተመረጡ ወደ ሌላኛው ፓርክ ተወሰዱ፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወጣቶቹ ዝሆኖች የገቡበት ፓርክ ተናወጠ፡፡ በፓርኩ ውስጥ የሚገኙት አውራሪሶች በየቀኑ ይገደሉ ጀመር፤ ዛፎች ይገነደሳሉ፤ ቁጥቋጦዎች ይተራመሳሉ፤ በዝሆኖቹ መካከል ጦርነት ተፈጠረ፡፡ በዚህም ምክንያት ዐቅመ ደካሞቹ እንስሳት ይጎዱ ጀመር፡፡ ነገሩ ያሳሰባቸው የፓርኩ ኃላፊዎች ሥውር ካሜራ ገጥመው ሁኔታውን መከታተል ያዙ፡፡ በመጨረሻም ወጣቶቹ ዝሆኖች የዚህ ሁሉ ችግር ፈጣሪዎች መሆናቸውን ደረሱበት፡፡ ሳይታሰብ አንድ ‹የዱርዬ ዝሆኖች ቡድን› ተመሥርቷል፡፡

የዝሆን አመራር
አንድ የጥናት ቡድን ተቀዋቁሞ የችግሩን መነሻ ማጣራት ሲጀምር ዋናው ጉድለት በዝሆኖቹ መካከል የሚመራና የሚፈራ ሽማግሌ አለመኖሩ መሆኑ ተደረሰበት፡፡ ወዲያውም የተወሰኑ ታላላቅ ዝሆኖችን እንደምንም ብለው ወደ ፓርኩ ሲያመጧቸው ሁሉም ነገር ሥነ ሥርዓት ያዘ፡፡ ‹መካሪ ዘካሪ አያሳጣ› ይባል የለ፡፡
በሰው ልጆችም ውስጥ ታላላቆች ተመሳሳይ ሚና አላቸው፡፡ ወላጆች ልጆችን፣ አያቶች የልጅ ልጆችን፤ ሽማግሌዎች መንደርተኞችን በባሕል፣ በእምነት፣ በሞራል ይመራሉ፡፡ አንዲት ሀገር ተው የሚል አባትና እናት፣ የሚያስታርቅ ሽማግሌ፤ ተሞክሮውን የሚያካፍል ታላቅ፤ ታሪክና ባሕል ዐዋቂ ጠቢብ፤ የሚፈራና የሚታፈር፣ የሚታይና የሚከበር ልዑል ዜጋ (Senior citizen) ከሌላት ሕግና ሥርዓት፣ ባሕልና ሞራል፣ የሀገርና የወገን ክብር ገደል ይገባሉ፡፡
ሀገር ከፍ ብለው የሚታዩ ኮከቦችን ትፈልጋለች፤ ትውልድ አርአያ የሚያደርጋቸው፡፡ ከጣት ጣት እንደሚበልጠው ሁሉ ከዜጋም ዜጋ ይከብራል፡፡ ለሀገር በዋለው ውለታ፣ ለትውልድ በሠራው ሥራ፣ በከፈለው መሥዋዕትነትና ባመጣው ውጤት ዜጋ ከዜጋ ይለያል፡፡ እንደ ብርሃ ድምቀት፣ እንደ ጥበቡ ምጥቀት ከዜጋ ዜጋ ይበልጣል፡፡ ‹ኮከብ እም ኮከብ ይኄይስ ክብሩ- ኮከብ ከኮከብ ክብሩ ይበልጣል› እንዲል፡፡ እነዚህ ዜጎች ናቸው የመንጋው አባቶችና እናቶች፡፡ ትውልዱን በሞራል፣ በባሕል፣ በእምነት፣ በሥራ፣ በሕግና በሥርዓት የሚቀርጹ፡፡ የሚፈራና የሚታፈር በሌለበት ሀገር የዱርዬ ቡድን መመሥረቱ አይቀሬ ነው፡፡ ሀገርን ሲዘርፍ፣ ዜጋን ሲገድል፣ ፍርድ ሲያጓድል፣ ድኻን ሲበድል፣ በሥልጣን ሲባልግ፣ በዘመድ ሲሠራ ምንም የማይመስለው፡፡ ነውሩ ክብሩ የሆነ፡፡ ‹እንብላት እንዝራት› ሲሉት ‹እንብላት› ብቻ የሚል ቡድን መፈጠሩ አይቀሬ ነው፡፡
(ይቀጥላል)

21 comments:

 1. እኛስ በዱርዬ ቡድን መተራመስ የጀመርነው ከ 1974 ዓ/ም እኤአ ጀምሮ አይደል? ምነው የኛንም ዱርዬዎች ቪዲዮ ተክለው ቢያጠኑልን!

  ReplyDelete
  Replies
  1. seifemichael zeejereAugust 30, 2014 at 4:21 AM

   ወንድሜ ሆይ በ2014 እ.አ.አ ጀምሮ ስልጣኑ ቢሰጥህ ዱርዬ ላለመሆንህ ምን ማረጋገጫ አለን፡፡ ምክንያቱም ከ1974 ዓ.ም ጀምሮ ሀገሪቱን ሲመሩ የነበሩትና አሁንም እየመሩ ያሉት ምንም ጥሩ ጎናቸውን ላለማየት አይንህን ከልለህ በአንተ አይን ዱርዬ ከተባሉ ወይም ካልካቸው አንተና መሰሎችህ ስልጣን ላይ ብትወጡ ዱርዬ የማይላችሁ ይኖራል ብለህ ታስባለህ? ይህ ከሆነ ደግሞ አንተ እኔን ዱርዬ ሰትለኝ እኔ አንተን ዱርዬ ስልህ ዘመናችን ያልቃል፡፡ ለንስሀ እንኳን ሳንበቃ ወደመቃብር እንወርዳለን፡፡ ስለዚህ ወንድሜ ሆይ የሚበጀን ስለዝሆን የተፃፈውን ሌላ ሰው እያሰብን ሌላው እንዲማርበት ሳይሆን የተፃፈው ለኔና ላንተ ነውና እኛ እንማርበት፡፡ የገባንን ያህል ለሌላው እንዝራ፡፡ ያንጊዜ የዱርዬ ብዛቱ እየቀነሰ ይመጣል፡፡ ምክንያቱም ቁጥሩን የምናበዛው እኔና አንተ ተደምረንም አይደል? ወንድሜ ሆይ በ2014 እ.አ.አ ጀምሮ ስልጣኑ ቢሰጥህ ዱርዬ ላለመሆንህ ምን ማረጋገጫ አለን፡፡ ምክንያቱም ከ1974 ዓ.ም ጀምሮ ሀገሪቱን ሲመሩ የነበሩትና አሁንም እየመሩ ያሉት ምንም ጥሩ ጎናቸውን ላለማየት አይንህን ከልለህ በአንተ አይን ዱርዬ ከተባሉ ወይም ካልካቸው አንተና መሰሎችህ ስልጣን ላይ ብትወጡ ዱርዬ የማይላችሁ ይኖራል ብለህ ታስባለህ? ይህ ከሆነ ደግሞ አንተ እኔን ዱርዬ ሰትለኝ እኔ አንተን ዱርዬ ስልህ ዘመናችን ያልቃል፡፡ ለንስሀ እንኳን ሳንበቃ ወደመቃብር እንወርዳለን፡፡ ስለዚህ ወንድሜ ሆይ የሚበጀን ስለዝሆን የተፃፈውን ሌላ ሰው እያሰብን ሌላው እንዲማርበት ሳይሆን የተፃፈው ለኔና ላንተ ነውና እኛ እንማርበት፡፡ የገባንን ያህል ለሌላው እንዝራ፡፡ ያንጊዜ የዱርዬ ብዛቱ እየቀነሰ ይመጣል፡፡ ምክንያቱም ቁጥሩን የምናበዛው እኔና አንተ ተደምረንም አይደል?

   Delete
 2. Certainly true! Thank you Dn Daniel as usual!
  Abera

  ReplyDelete
 3. Thanks, Dani
  deep looking as usual!

  ReplyDelete
 4. ‹እንብላት እንዝራት› ሲሉት ‹እንብላት› ብቻ የሚል ቡድን መፈጠሩ አይቀሬ ነው፡፡

  ReplyDelete
 5. የሚፈራና የሚታፈር በሌለበት ሀገር የዱርዬ ቡድን መመሥረቱ አይቀሬ ነው፡፡ ሀገርን ሲዘርፍ፣ ዜጋን ሲገድል፣ ፍርድ ሲያጓድል፣ ድኻን ሲበድል፣ በሥልጣን ሲባልግ፣ በዘመድ ሲሠራ ምንም የማይመስለው፡፡ ነውሩ ክብሩ የሆነ፡፡ ‹እንብላት እንዝራት› ሲሉት ‹እንብላት› ብቻ የሚል ቡድን መፈጠሩ አይቀሬ ነው፡፡

  ReplyDelete
 6. Great advice for me and this generation.Thank you!!!

  ReplyDelete
 7. እግዚአብሔር አምላክ እውቀትህን ያስፋልህ

  ReplyDelete
 8. እግዚአብሔር አምላክ እውቀትህን ያስፋልህ

  ReplyDelete
 9. Wow it is interesting point but it looks to me impossible idea. We divided to many parts, so we don’t want to hear other idea. However we hear always without asking question.

  ReplyDelete
 10. Hi, Danni thank you so much. For the next chapter please write what action we will take when the old elephant disturb the Pease. Our country problem is the old elephant not the young elephant. Most of the old elephant came from the forest, so it is difficult for us to deal with them

  ReplyDelete
  Replies
  1. እንዲህ ከሆነማ ችግራችንን በሚቀጥሉት 30 - 40 ዓመታት ተፈጥሮ ታስወግድልናለች!

   Delete
 11. ወንድማችን እግዚኣብሄር ይባርክህ።እስቲ ከ ድቃቃይቱ ጉንዳን ካልተማርን ከ ግዙፉ ዝሆን ኣርኣያ እንውሰድ

  ReplyDelete
 12. Astaraqi ayetfa lehager lewgwn,melkam tmehert new,
  weqtawi, yaqoywlen yetbeqelen.

  ReplyDelete
 13. tnx so much,,,zere will b no 2morrow with out...!!!

  ReplyDelete
 14. Thank you wendimachin enameseginalen egiziabiher
  yibarkih

  ReplyDelete
 15. Egzhabher balhe ewket lay abzto ychemirlh

  ReplyDelete
 16. አንድ የጥናት ቡድን ተቀዋቁሞ የችግሩን መነሻ ማጣራት ሲጀምር ዋናው ጉድለት በዝሆ ኖቹ መካከል የሚመራና የሚፈራ ሽማግሌ አለመኖሩ መሆኑ ተደረሰበት፡፡ ወዲያውም የተወሰኑ ታላላቅ ዝሆኖችን እንደምንም ብለው ወደ ፓርኩ ሲያመጧቸው ሁሉም ነገር ሥነ ሥርዓት ያዘ፡፡ ‹መካሪ ዘካሪ አያሳጣ› ይባል
  የለ፡፡
  በሰው ልጆችም ውስጥ ታላላቆች ተመሳሳይ ሚና አላቸው፡፡ ወላጆች ልጆችን፣ አያቶች የልጅ ልጆችን፤ ሽማግሌዎች መንደርተኞችን በባሕል፣ በእምነት፣ በሞራል ይመራሉ፡፡ አንዲት ሀገር ተው የሚል አባትና እናት፣ የሚያስታርቅ
  ሽማግሌ፤ ተሞክሮውን የሚያካፍል ታላቅ፤ ታሪክና ባሕል ዐዋቂ ጠቢብ፤ የሚፈራና የሚታፈር፣ የሚታይና የሚከበር ልዑል ዜጋ (Senior citizen)
  ከሌላት ሕግና ሥርዓት፣ ባሕልና ሞራል፣ የሀገርና የወገን ክብር ገደል
  ይገባሉ፡፡

  ReplyDelete
 17. ዝሆን የሚተኛው ለመነሣት እንዲመቸው ሆኖ ነው፡፡ መሬት ላይ ከወደቀ ለመነሣት ይቸገራል፡፡ ክብደቱ ትልቅ ነውና፡፡ ስለዚህም የሚተኛው ዛፍ ተደግፎ ነው፡፡ የዝሆን ዕንቅልፍ ፍጹም ዕንቅልፍ አይደለም፡፡ ለመነሣት ያኮበኮበ ዕንቅልፍ ነው፡፡ የሚተኛው ለመነሣት በሚችልበት መንገድ ነው፡፡ ሰውም ሞቱ ለትንሣኤ፣ ድካሙ ለብርታት፣ ዕረፍቱ ለሥራ፣ ኀዘኑ ለደስታ፣ ውድቀቱ ለመነሣት፣ ስሕተቱ ለእርማት፣ ማጣቱ ለማግኘት፣ ሕመሙ ለድኅነት በሚሆን መልኩ መሆን አለበት፡፡ እንዳይነሣ ሆኖ መውደቅ፣ እንዳይተርፍ ሆኖ መክሰር፣ እንዳይከብር ሆኖ መዋረድ፣ እንዳይፈታ ሆኖ መታሠር፣ እንዳይመለስ ሆኖ መሄድ፣ እንዳይታረቅ ሆኖ መጣላት የለበትም፡፡ የማርያም መንገድ መተው ያስፈልጋል፡፡ የአንድ ነገር መጨረሻ የሌላ ነገር መጀመሪያ መሆን አለበት፡፡ ከሥራ ማረፍ ለሌላ ሥራ መዘጋጃ፣ የዛሬ ዕንቅልፍ ለነገ ብርታት ኃይል መሰብሰቢያ፣ የዛሬ ሞት ለነገ ትንሣኤ መራመጃ መሆን አለበት

  ReplyDelete
 18. የሚፈራና የሚታፈር በሌለበት ሀገር የዱርዬ ቡድን መመሥረቱ አይቀሬ ነው፡፡ ሀገርን ሲዘርፍ፣ ዜጋን ሲገድል፣ ፍርድ ሲያጓድል፣ ድኻን ሲበድል፣ በሥልጣን ሲባልግ፣ በዘመድ ሲሠራ ምንም የማይመስለው፡፡ ነውሩ ክብሩ የሆነ፡፡ ‹እንብላት እንዝራት› ሲሉት ‹እንብላት› ብቻ የሚል ቡድን መፈጠሩ አይቀሬ ነው፡

  ReplyDelete