Tuesday, July 29, 2014

እንደገና እንጋባ(የመጨረሻ ደብዳቤ)

ይኼ የመጨረሻዬ ደብዳቤ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ወይ እንደገና እንጋባለን አለበለዚያም እኅትና ወንድም ሆነን እንቀጥላለን፡፡ አሁን ‹እኅትና ወንድም ሆኖ መቀጠል›› ሲባል ቀላል ነገር ይመስላልኮ፡፡ የተለያዩ ባልና ሚስቶች ‹እኅትና ወንድም› ሆነው ለመቀጠል ሦስት ነገሮች ሳያስፈልጋቸው አይቀርም፡፡ ጠላትነትን ማጥፋት፣ ሌላ ዓይነት ወዳጅነትን መቀጠልና በአዲሱ መንገድ የሚመጡትን አስከፊ ነገሮች ሁሉ ለመቀበል መቻል፡፡ አንዳንድ ተጋቢዎች ሲለያዩ በጋብቻ ምትክ ጠላትነትን ተክተው ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ እንኳን ከዚህ በፊት አንድ ሆነው የኖሩና አንድ ሆነው ያደሩ፣ የተዋወቁም አይመስሉ፡፡ አንዱ ሌላውን ሲያስበው ያንገሸግሸዋል፡፡ ‹‹በለው በለው፣ ግደለው ግደለው› የሚለው ስሜት ይመጣበታል፡፡ ከፍቺ በኋላ ለሚፈጠሩ አሰቃቂ ወንጀሎች አንዱ ምክንያትም ይኼው ነው፡፡ ንብረት ክፍፍል ላይ ‹‹ይህንንማ አትገኛትም፣ አያገኛትም›› እየተባባሉ ምርኮ ስብሰባ የሚያስመስሉትም ለዚህ ነው፡፡
‹ሌላ ዓይነት ወዳጅነት› ያልኩሽ ቢያንስ ለመጠያየቅ፣ ተገናኝቶም ቢሆን ሻሂ ለመጠጣት፣ ስለ ልጆች ለመነጋገር፣ ቤተሰቦቻቸውን ለመጠያየቅ መግባባት ላይ መድረስ ማለት ነው፡፡ በትዳሩ ጉዳይ ለጊዜው ባይግባቡም ሌላ የሚያግባባቸው ነገር አያጡም፡፡ ትዳሩ ቢፈርስ እንኳን ትውውቁና ዝምድናው እንዲቀጥል ለማድረግ መጣር አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ አንዳቸው ስለሌላቸው ክፉ ላለማውራት፣ ምሥጢሮቻቸውንም ጠብቀው ለመኖር መስማማት ኑሮን ሰላማዊ ለማድረግ ሳይጠቅም አይቀርም፡፡ ይኼ ነገር ለሁለቱም ሰላማዊ ኅሊና ይሰጣቸዋል፡፡ ከጠብ ስሜት፣ ከበቀል መንፈስ፣ ያድናቸዋል፡፡ ስለ ሌላ ሰው በክፉ ማሰብ ከሚታሰብለት ሰው በላይ ክፉ አሳቢውን ይጎዳዋል፡፡ ለስንት በጎ ነገር ሊጠቀምበት የሚችለውን የኅሊና ጉልበት ለማይጠቅም ጠብና ሐሜት፣ ጥላቻና ክፋት እንዲጠቀምበት በማድረግ ውሳጣዊ ሰላሙን ያሳጣዋል፡፡ በሌላም በኩል ደግሞ በሰላም ተለያይተው በሰላም የሚኖሩ ተፋቺዎች በጠብ ከተለያዩት ይልቅ እንደገና ለመጋባት የቀና መንገድ ይኖራቸዋል፡፡ ለፍቺ ያበቃቸው ቁስል እንዲድን ዕድል ሰጥተውታልና፡፡ ከፍቺ በኋላ በክፉ በመፈላለግ ቁስሉ ይበልጥ እንዲያመረቅዝ አላደረጉትምና፡፡ 
በአዲሱ መንገድ የሚመጡትን አስከፊ ነገሮች ሁሉ ለመቀበል ዝግጁ መሆን ሲባል መለያየቱ የሚያመጣቸውን አሳዛኝና አስከፊ ነገሮችም ለመቀበል ዐቅም ማግኘት ማለት ነው፡፡ ተለያይቶ መኖሩን፣ የሀብት መካፈሉን፣ የአንደኛው ወገን ከሌላ የጾታ ጓደኛ ጋር መታየቱን፣ ከልጆች መለየትን የመሰሉ ነገሮችን ‹አስፈላጊ ሰይጣን› ናቸው ብሎ ለመቀበል መቻል ነው፡፡ ይህንን ለመቀበል ዐቅም ያጡ ተፋቺዎች ትልቁን ትዳር አፍርሰው ለትንሹ ንብረት ሲሟገቱ፤ እንዴት እገሌን ከሌላ ጋር አየዋለሁ፣ እንዴት እገሊትን የእገሌ ሆና አያታለሁ እያሉ ደም ሲለብሱ፤ ቆይተውም ወደ በቀል መንገድ ሲገሠግሡ ይታያሉ፡፡ ለዚህ ነው ‹እኅትና ወንድም ሆነን እንቀጥላለን›› ያልኩሽ፡፡ እርሱም ዛሬ ዛሬ ለብዙዎቻችን እያስቸገረን ነውና፡፡
የመጨረሻው ደብዳቤዬ ነውና ‹ባለቤቴ› ስለሚለው ነገር እነግርሻለሁ ያልኩትን ነግሬሽ ልጨርስ፡፡ በግእዙ ‹በዐለ ቤት› ማለት ‹የቤት ጌታ፣ የቤት አለቃ› ማለት ነው፡፡ ‹ቤት› ደግሞ በምሥራቃውያን ባሕል ብዙ ነገርን የሚይዝ ነው፡፡ ቤት ነገድ ነው ‹ቤተ እሥራኤል እንዲሉ› ቤት ሀገር ነው ‹ቤተ አምሐራ›› ብለው እንዲጠሩ፡፡ ቤት  በማኅደሩ አዳሪውን ጠርተው ‹ነዋሪ› ማለት ነው፡፡ ‹‹ቤቶች›› እንዲሉ፡፡ ቤት ‹የቅርብ ዘመድ› ማለት ነው፡፡ ‹ቤተሰብ› እንዲሉ፡፡ ቤት ወገንን ያሳያል ‹ሥራ ቤቶች›  ሲል የቤት ውስጥ ሥራ የሚሠረቱትን አንድ አድርጎ እንዲገልጥ፡፡ ባለ ይዞታነትንና ባለሀብትነትንም ይገልጣል፡፡ ‹ባለቤት› ሲል ባለሀብት ማለት እንደሆነው፡፡ ቤት ልብስም ይሆናል ‹ቤተ እግር› ሲል ካልሲ፣ ገምባሌ ማለት ነውና፡፡ ቤተ እድ ሲልም ‹እጀ ጠባብ፣ እጅጌ፣ ቀለበት› ማለት ነው፡፡ የተሸለመ እልፍኝ ማለትም ይሆናል፡፡ ‹ቤተ አንስት› ሲል የተሸለመ የተጌጠ ቤት ማለት ነው፡፡
ባለትዳሮችም ‹ባለቤቴ› ሲባባሉ የቤቴ ጌታ፣ የቤቴ አለቃ፣ ወገኔ፣ ነገዴ፣ አብሮኝ የሚኖር፣ የቅርብ ዘመዴ፣ በአንድ አብረን የምንሠራ፣ የሀብቴ የንብረቴ ባለሀብት ባለይዞታ የሆነ፣ ጌጤ፣ ሽልማቴ፣ ልብሴ፣ ሞገሴ፣ እልፍኜ› ማለት ነው፡፡ በሌላም በኩል ‹ቤተ› ማለት ‹አደረ፣ ኖረ› ማለት ነው፡፡ ባለቤቴ ማለት ደግሞ አብረን የምናድር አብረን የምንኖር፣ ልቤ መኖሪያዋ፣ ማደሪያዋ ልቧ መኖሪያዬ፣ ማደሪያዬ የሆነ ማለት ነው፡፡ አንዳንድ ሊቃውንትም ‹ጉዳዩን በቤት በኩል ብቻ ሳይሆን በ‹በዐል› በኩልም ይፈቱታል፡፡ ‹በዐለ› - ከበረ፣ ከፍ ከፍ አለ፡፡ በዐለ - ቻለ፣ ዐወቀ፣ ሠለጠነ፣ ገዛ ማለት› ነው፡፡ ‹በዐለ መድኃኒት› ሲል መድኃኒት ያለው የሚያውቅ ማለት ነው፡፡ ‹በዐለ ሥልጣን› ሲል ሥልጣን ያለው ማለቱ ነው፡፡  ‹በዐለ ቤት› ሲል ‹የቤቱ ሠራዒ መጋቢ› ማለቱ ይሆናል፡፡ ባለቤቴ የሚለው ነገር እኩል ሥልጣንን፣ እኩል ባለሀብትነትን፣ እኩል አለቅነትንና እኩል መብትን ያሳያል፡፡ በእኔ ላይ ሥልጣን ያለው፣ ሥልጣን ያላት፣ እኔን የምታውቅ፣ በእኔ ላይ የሠለጠነ፣ የሠለጠነች፣ ማለት ነው፡፡
ለዚህ ይመስለኛል በባሕላችን ‹ከባለቤትዎ ጋር› እየተባለ ጥሪ የሚተላለፈው፡፡ ሰውየው ለብቻው ሙሉ አይሆንም፣ ሴትዮዋም ለብቻዋ ሙሉ አትሆንምና፣ ሥልጣንም የላትም የለውምና፣ ስጦታ እሰጣለሁ፣ ቃል እገባለሁ፣ ብትልና ቢል አይችልምና ሙሉ አድርገን እንጥራቸው ብለው ነው ‹ከባለቤትዎ ጋር› ብለው የሚጋብዙን፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ በአብርሐና አጽብሐ ዘመን ብቻ ነው ይባላል ሁለት ነገሥታት በአንድ መንበር የገዙት፡፡ ከአብርሐ አጽብሐ ወዲህ በትዳር ብቻ ይመስለኛል ሁለት ነገሥታት በአንድ መንበር የሚነግሡት፡፡ ይህንን በአንድ መንበር ሁለት ነገሥታት መንገሣቸውን ነው ‹ባለቤቴ፣ ባለቤቴ› እየተባባልን የምንጠራው፡፡
አንዱ ለሌላው ታዛዥ፣ ተገዥ ሆኖ፤ እርሱም በሌላው ላይ ገዥ፣ አዛዥ ሆኖ፣ የመኖርን ስልት ለማምጣት ነው ‹ባለቤቴ› ማለት፡፡ በፈቃድ መገዛትን፣ በፈቃድም ራስን መስጠትን ለማመልከት ነው ‹ባለቤቴ› ማለት፡፡ አንዱ የኔና ያንቺ ችግር ‹ብቻችንን ባለቤት እንሁን› እያልን ይመስለኛል፡፡ ሥልጣናችንን ስንጠቀመው ሌላውን ባለ ሥልጣን እየረሳን ስለሆነ መሰለኝ ችግራችን፡፡
እና እስኪ ከራስሽ ጋር ብቻ ተወያይና ለእኔም ባትጽፊልኝ ለራስሽ መልስ ስጭ፡፡ እኔ ለአንቺ፣ አንቺም ለእኔ ክፉ ብንሆን እንኳን የተሻልን ክፉዎች የምንሆን ይመስለኛል፡፡ ከማያውቁት መልአክ የሚያውቁት ሰይጣን ይባል የለ፡፡
በይ ደኅና ሁኚ፡፡ ምንም ብንለያይ ደኅና መሆንሽ ሁላችንንም ይጠቅማልና፡፡
© ሦስቱም ደብዳቤዎች በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ ወጥተዋል

24 comments:

 1. God bless you Dn. Dani. erejim edme ketene gar lantana lemelaw beteseb yihun. Amen. I learn a lot as usual.

  ReplyDelete
 2. Just wow! it is a great definition with evidence ሰናይ ነው:: .ባለትዳሮችም ‹ባለቤቴ› ሲባባሉ የቤቴ ጌታ፣ የቤቴ አለቃ፣ ወገኔ፣ ነገዴ፣ አብሮኝ የሚኖር፣ የቅርብ ዘመዴ፣ በአንድ አብረን የምንሠራ፣ የሀብቴ የንብረቴ ባለሀብት ባለይዞታ የሆነ፣ ጌጠየ፣ ሽልማቴ፣ ልብሴ፣ ሞገሴ፣ እልፍኜ› ማለት ነው፡፡

  ReplyDelete
 3. ግሩም ነው። ጥሩ የሕይወት ማሳያ ደብዳቤዎች ናችው። ባለትዳር የሆንን እናውቃለን የምንል ባለ ትዳሮችም ደጋግመን ልናነበው ይገባል ባይ ነኝ። በትዳር ውስጥ አለመግባባት ሲኖር ችግሮቹን ሳናመዛዝን ወደ ውሳኔ እንገፋፋለን። እነዚህ ማመዛዘን የጎደላቸው ወሳኔዎች ናቸው ማኅበረሰብን ወደ ማኅበራዊ ቀውስ የሚያንደረድሩት። ዕድሜ ይስጥህ ዲያቆን ዳንኤል።

  ReplyDelete
 4. what a great message for a couples who are living in a marriage. Absolutely Absolutely needed to be re read .Thank you,D.Daniel . GOD Bless you and yr family.

  ReplyDelete
 5. ሰሚ ካለ ጥሩ ምክር ነዉ፡፡

  ReplyDelete
 6. Thank you so much Dn. Daniel Kibret. It was really a good lesson. May the Lord continue to bless you with His Wisdom.

  ReplyDelete
 7. I get a lot of lesson. God bless you.

  ReplyDelete
 8. ሰናይ ነው:: .ባለትዳሮችም ‹ባለቤቴ› ሲባባሉ የቤቴ ጌታ፣ የቤቴ አለቃ፣ ወገኔ፣ ነገዴ፣አብሮኝ የሚኖር፣ የቅርብ ዘመዴ፣ በአንድ አብረን የምንሠራ፣ የሀብቴ የንብረቴ ባለሀብት ባለይዞታ የሆነ፣ ጌጠየ፣ ሽልማቴ፣ ልብሴ፣ ሞገሴ፣

  ReplyDelete
 9. This comment has been removed by the author.

  ReplyDelete
  Replies
  1. Hi, Henok I am not Danial Kbret but I would like to answer your question. I think you are between six and ten years old otherwise you don't aks this kind of kids question. Dania wrote what he read or listen from other, he didn't discover this this expression so you have to ask whoever discovered this expression. In addition that example is not express 100% but people write to get the reader attantion. At the movement Devil is not better than an angel but he used to. When Adam did mistake Jissuse pay for him and he got merrsy but nobody want pay to Devil so he still in prison. One day he will be free. Further more you don't know all Devil so may be some of them are nice. We never met any Devil but we always give them a bad look. In addition that all Devil are white but our fathers and others are put them with black. We are black but devil is white so people alway follow what they hear without proof. Please give judgement after you meet with angel and devil. At the movement you never met both of them so don't try to fix our father and mother expression. It is true "ከማያውቁት መልአክ የሚያውቁት ሰይጣን ይሻላል''. If you know someone you know that about that thing then you will take your action.

   Delete
  2. I am sorry but it is your response that makes you look like even a toddler.
   1. You don't write what anyone says without analyzing the true meaning or the implication it has.
   2. You don't live by what you were in the past. What matter is what you are in present. Why would you bring the history of a devil? he was one of the angels. But now he is a devil.
   3. You have shallow knowledge about the religion you are following. From which religious book you came to understand that A DEVIL will set free? Are you introducing us a new religion? Our Church does not teach us this way.
   4. I am sorry (hahaha) but i don't know so far a good quality of a devil. You may tell me some time in the future.
   5. Our father gave bad picture (black, tail, horn, fire in his mouth, foul smell etc) of devil to reflect his bad characteristics. Just read "Sene (June) month Dersane Michael about Afomia's History" and then you will understand what a devil is.
   All in all your argument reveals your little knowledge or stupidity. If i were in your shoe i would try to become as much polite as possible to give an answer.
   Finally I know it is a saying. But my question is do we always use some sayings without taking into account the true implications the saying contains? Don't we have a better saying? For me it is giving an honor to a devil having a saying like this. Yes I can simply go over just like you and anyone else. But if you give yourself some thought of it ደስ የማይል ነገር አለዉ.

   Delete
 10. ዳኒ እባክህ እርሷም ምላሿን ብትጽፍልን መልካም ነበር:: ይሄን ሁሉ ሰምታ ምን ይሰማት ይሆን? ከነማን ጋር ትማከረዋለች? ለብቻዋ ጊዜ ወስዳ ታነበዋለች? ለጨቅላ ልጆቿ ታነብላቸው ይሆን? እንደው ምላሿ ምን ይሆን? እነ ማን ምን ይሏታል? የቤተ ዘመድ ጉባኤው ሽማግሌዎቹ ቤተሰቦቿና ጓደኞቿ? ሸሪአና መንፈሳዊው ፍርድ ቤት ምን አሉሽ? ፍርድ ቤቱና ጠበቆቹስ? እንደው የሴቶች ጉዳይ ማኅበራት ጋር ጎራ አላልሽም? እባክሽ የተሰማሽን አሰሚን ሕመምሽን እንታመም ችግርሽን እንቸገር ሀሳብሽን እንጋራ :: በፍጥነት መልስሽን ላኪ? ዳኒ እባክህ በምናብ ትከሻ ተጭነህ ካለችበት ሂድና በርቱዕ አንደበትህ መርምራት የልቧን ትንገረን ሴቲቱንም ጠይቃት::

  ReplyDelete
  Replies
  1. ዳኒ!!! እንደሁልጊዜው በፅሁፍክ ተምሬበታለሁ ለወደፊቱ ለኔም ሆነ በአካባቢዬ ለሚገኙት ሁሉ ለወደፊት የትዳር ህይወት ስንቅ እንደሚሆነን አምናለሁ፡፡ እኔም ግን የሚስትየዋን ምላሽ እጠብቃለሁ፤ የበለጠ እንደምማር አስባለሁና፡፡

   Delete
 11. Hello Danial on chapter two most of an Ethiopian people got mad when we read this part so could you ask us apologize for your mistake please.
  " ይኼው እንደምታዪው ለኢራቆች ሳዳምን ማስወገድ፣ ለሊቢያዎችም ጋዳፊን መግደል ቀላል ነበረ፡፡ የተሻለ ማምጣት ግን እንደ ማስወገዱ ቀላል አልሆነላቸውም፡፡"
  ያልካት አስገራሚ መልክት ነች!
  የትሻለ ነገር አይመጣምና ወያኔ ይግዛችሁ ይመስላል፡፡ ምንዋ ዲን ፥ እረ አይገባም፡፡
  የማያውቁትን ጉዳይ መተውን የመሰለ ነገር የለም፡፡
  አውቅሽ አወቅሽ ቢሏት መጽሀፍ አጠበች! እንዳይሆንብህ

  ReplyDelete
  Replies
  1. You just keep posting this nonsense comment again and again. Don't try to use "Ethiopian people" as a reference for your stupid understanding of the mentioned part.

   ሁሉም ሰው እንዳንተ እውነታን በጠማማ ትርጉሙ አይረዳም፡፡ ምሳሌው የፖለቲካን አጀንዳ መሰረት አርጎ የተፃፈ ሳይሆን እንደ ሰውና ማህረሰብ ነገሮችን በቅንነት በበጎነት ለዘላቂ ጥቅም መፍትሔ ለመፈለግ በመትጋት ላይ እንድናተኩር ለማሳሰብ ነው፡፡ በራስ ወዳድነት እና እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ ሰማይና ምድር ይገለባበጥ የሚል አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ አቋም በግላዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ሀይማኖታዊ ህይወታችን ውስጥ ማራመድ ከጥቅሙ ጉዳቱ ነው የሚያይለው የሚለውን መሰረታዊ እውነታ ለማስረዳት የቀረበ አገላለፅ ነው፡፡
   Therefore, don't comment this as if u represent us Ethiopians and in effect suggesting we have a small brain as you to understand a simple article in the worst narrow form.
   And leave Daniel Kibret to mention his own view as an individual.

   Delete
  2. ምን ይደረግ ብለህ ነዉ ሰዉ እኮ ማሰብ የሚፈልገዉን ብቻ ነዉ ማሰብ የሚፈልገዉ፡፡ አሁን ከፓለቲካ ጋር ምን ያገናኘዋል?

   Delete
  3. Either you're twisted-minded, or you can't read and understand what's written. It talks about “bringing something or someone better when removing someone or something.”Please read and understand the whole paragraph. If you can't, here is what the paragraph says:
   “…ችግሩ ችግሩን ማወቃችንና ማውገዛችን አልነበረም፡፡ በሌላ፣ እኛ ዘመናዊና የተሻለ በምንለው መፍትሔ አለመተካታችን ብቻ ነው፡፡ አንድ ቤት ውስጥ ያለውን ዕቃ ‹ኋላ ቀር ነው› ብለን አስወጥተን ጥለን ቤቱን ወና ብናደርገው የአይጥ መጨፈሪያ ነው የሚሆነው፡፡ አንድን የኖረ መፍትሔ አስወግደን በሌላ ካልተካነውም ችግሩን ያለ መፍትሔ ነው የተውነው፡፡ አንድን ነገር ማስወገድ ማለት በተሻለ ነገር መተካት ማለት አይደለም፡፡ መተካትም እንደማስወገድ ቀላል አይደለም፡፡ ይኼው እንደምታዪው ለኢራቆች ሳዳምን ማስወገድ፣ ለሊቢያዎችም ጋዳፊን መግደል ቀላል ነበረ፡፡ የተሻለ ማምጣት ግን እንደ ማስወገዱ ቀላል አልሆነላቸውም፡፡”
   Furthermore, please just speak for yourself when you say “upset, since you’re not representing us as far as Daniel’s article is concerned.

   Delete
 12. ዲን ዳኒ - ሁሌም ጥሩ ነጥቦችን ስለምታነሳ እግዚአብሔር እስከቤተሰቦችህ ይባርክህ! እኔ አንተ ከጻፍኸው ተጨማሪ የሰዎችን አስተያየት ማንበብ በጣም ያስደስተኛል፡፡ ምክንያቱም የሰዎችን አስተሳሰብ፣ አረዳድ፣ አተረጓጎም፣ መልስ አሰጣጥና ከግል ህይወታቸው ጋር በማገናኘት ወይም የውስጥ ስሜታቸውን በሚፈልጉት ምልክ አጋጣሚውን በመጠቀም የሚያነሱት ነጥብ ሁሌም ለእኔ አስተማሪ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ አስተያየት ሰጭዎችም ሃሳባችሁ በራሳችሁ ልክ ስለሆነ ቀጥሉበት እላለሁ፣ አንዱ ከሌላው መማማር ይቻላል፡፡ ሁሉም ሃሳብ ልክ ነው ልዩነቱ ሰዎችን የማሳመንና ሌሎች በሚረዱት መልክ ማቅረብ አለመቻል ነው፡፡
  በዚህ ጽሁፍ ላይ ሁለት ነጥቦች ተደጋግመው ስለተነሱ የግሌን አስተያየት ልጽፍ ፈለግሁ፡፡ 1ኛው "ይኼው እንደምታዪው ለኢራቆች ሳዳምን ማስወገድ፣ ለሊቢያዎችም ጋዳፊን መግደል ቀላል ነበረ፡፡ የተሻለ ማምጣት ግን እንደ ማስወገዱ ቀላል አልሆነላቸውም፡፡" ይህ አረፍተነገር ከዚህ ላይ የቀረበው እኔ እንደተረዳሁት ማፍረስ ወይም ማስወገድ ቀላል መሆኑንና ማሻሻል ወይም መጠገን ከባድ መሆኑን የሚያሳይ ነው እንጅ ሌላ ትርጉም ያለው አይመስለኝም፡፡ “contextual meaning” ለመረዳት እንሞክር፡፡
  2ኛው ነጥብ ደግሞ - "ከማያውቁት መልአክ የሚያውቁት ሰይጣን ይሻላል'' ይህ አባባል ብዙ ጊዜ ይባላል፡፡ አባባሉ ግን ሁለቱን ለማወዳደር አይደልም፡፡ ነገር ግን የምታውቀው ግን ክፉ የሆነ ነገር እንደ ጸባዩ ትይዘዋለህ፣ የማታውቀው ግን በጎ ነገር ለመልመድና እንደጸባዩ ለማሰተናገድ ትቸገራለህ ለማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አብሮ የኖረ ሰራተኛ፣ ጓደኛ፣ የአካባቢ ሰው ….. ..ወዘተ ክፉ ሆነው ግን ካወቅናቸው በተለመደው መንግድ መመለስ እንችላለን፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ምን እንደሚፈልጉ ስለ ምናውቅ የሚፈልጉትን ነገር በማድረግ ወይም በመስጠት ሳንጣላ ያለክርክር መመለስ እንችላልን፡፡ ነገር ግን የማናውቀው ከሆነ በተለያየ መልኩ ላንግባባ እንችላለን፡፡ ይህን አባባል በተለይ በሃገራችን የገጠሪቱ ክፍል ብዙ ጊዜ ሰዎችን በትዳር፣ በግብርና በጋራ ለማምረት፣ በጉርብትና እና በድንበር ሲጣሉ ላማስታረቅ፣ ለማስማማት፣ አብረው እንዲሰሩ ለማድረግና አብረው እንዲቀጥሉና ተስማምተው እንዲኖሩ ለማድረግ የሚጠቀሙበት አባባል ነው፡፡ ብዙ ትረጉም ስላለው ምናልባት ሌሎችን ሊቃውትን መጠየቅ ይበጃል፡፡
  አበራ

  ReplyDelete
  Replies
  1. በአስተያየትዎ ከሞላ ጎደል እስማማለሁ፡፡ ያከራከሩ ሐሳቦችንም ለማጥራት በመሞከርዎ አመሰግናለሁ፡፡ ነገር ግን ከአስተያየትዎ ውስጥ የማልስማማበትን አንድ ነጥብ አንስተዋል፡፡ "ሁሉም ሐሳብ ልክ ነው ልዩነቱ ሰዎችን የማሳመንና ሌሎች በሚረዱት መልክ ማቅረብ አለመቻል ነው፡፡" ብለዋል፡፡ ይህንን ሐሳብዎን በሁለት ምክንያቶች እቃወማለሁ፡፡
   አንደኛ፡- ይህ ሐሳብ እርስዎ ራስዎ ከፍ ብለው ካነሱት ሌላ ሐሳብ ጋር ይጣረሳል፡፡ በአስተያየትዎ መጀመሪያ ላይ "… አስተያየት ሰጪዎችም ሐሳባችሁ በራሳችሁ ልክ ስለሆነ ቀጥሉበት…" ብለው ነበር፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡ ጤነኛ አዕምሮ ያለው ማንም ሰው የሚያስበው ሐሳብ ለራሱ ትክክለኛ ሐሳብ ነው፡፡ ያሰበውን ሐሳብ ይፋ ከማድረጉ በፊት አምኖበትና ትክክል ነው ብሎ ስለወሰደው፡፡ ይህ ሐሳብ ግን ዝቅ ብሎ ካለውና ከላይ ከጠቀስኩት ሐሳብዎ ጋር አይገጥምም፡፡ ምክንያቱም የአንድ ሰው እውነት የሁሉም ሰው እውነት አይደለምና፡፡
   ሁለተኛ፡- የምናስበው ሐሳብ ሁሉ ልክ ነው ማለት ስህተት ወይም ውሸት አይደለም ማለት ነው፡፡ እውነታው ግን ይህ አይደለም፡፡ ሰይጣናዊ ሐሳቦች ልክ ናቸው ብለን ልንቀበል እንችላለን? በፍጹም! ዓለምን ያወኩና ያጠፉት የነሂትለርና የነሙሶሊኒ ሐሳቦች ልክ ስለነበሩ ነው ወይ ሚሊዮኖች የተጨፈጨፉት? አይደለም፡፡ እነሱ ይህንን ሐሳባቸውን ከመመካከርና ከመማማር ሸሽገው "እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን" በሚል ዕብሪት የፈጸሙት የግፍ ሥራ ውጤት ነው፡፡ "ተው! ይህ መንገዳችሁና ሐሳባችሁ ልክ አይደለም" የሚላቸውን ሁሉ ጠላት አድርገው በመፈረጅ ለዘመናት የማይሽር ቁስል በዓለማችን ላይ ትተው ለስም የማይበቃ ሞት ሞቱ እንጂ ሐሳባቸው ትክክል ሆኖ አልወጣም፡፡ ሁሉም ሐሳብ ለአሳቢው ብቻ እንጂ ሁልጊዜ ለሌላው ልክ ሊሆን እንደማይችል ከዚህ ምሳሌም በላይ በዘመናችን ብዙ አስረጂዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የሐሳቡ ባለቤት አፈ-ቅቤ ሊሆንና መድረኩ ከተገኘም ሰዎችን በሐሳቡ ሊያሳምን ይችላል፡፡ ሐሳቡ ወደተግባር ሲለወጥ ግን ውጤቱ ጥፋት ከሆነ፣ ችግሩ የአፈጻጸም ብቻ ሳይሆን የሐሳቡ መሠረትም የሚሆንበት ዕድል ሰፊ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ በጥቅሉ፣ የአንድ ሐሳብ ሁሉን አቀፍ ትክክለኛነት በአሳቢው የማስረዳት ወይም የማሳመን ብቃት ላይ ሳይሆን፣ በሐሳቡ ውጤት ላይ የሚመሠረት ነው ባይ ነኝ፡፡

   Delete
 13. dani le eyitawochih hulu yenisir aynich yisth.

  ReplyDelete
 14. ለትዳር መስማማትና መግባባት ብሎም መቻቻል ያስፈልጋ ግን ሁልጊዜ እኔ ትክክል ነኝ የሚለው አባባል ይመስለኛል የሚያጣላው እንጂ ኢኮነሚንም በመስራት ይሞላል ግን ያለው ነገር ሁለቱም ወገኖች ጐዶሎ ፖርት አንዳላቸው ቢያምኑ ጥሩ ነው የኔን ጐዶሎ እሱ ሊሞላ የሱን ጐዶሎ እኔ ልሞላ ይመስለኛል ትዳር ማለት ፡፡

  ReplyDelete
 15. I do not why this word we used so many time.
  "kemiawkut melak ye miawkute setan yeshalale"
  Setan be menem neger teshelo ayawekem. Le bete christian lege yeha ababal teru aydelem. Metefo neger hulem metefo naw. Daniel please do not use such kind of word. We love you!

  ReplyDelete
 16. By the way Danie? Did your Wife read this article??? what did she say???hmmmmmmm

  ReplyDelete