Tuesday, July 29, 2014

እንደገና እንጋባ(የመጨረሻ ደብዳቤ)

ይኼ የመጨረሻዬ ደብዳቤ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ወይ እንደገና እንጋባለን አለበለዚያም እኅትና ወንድም ሆነን እንቀጥላለን፡፡ አሁን ‹እኅትና ወንድም ሆኖ መቀጠል›› ሲባል ቀላል ነገር ይመስላልኮ፡፡ የተለያዩ ባልና ሚስቶች ‹እኅትና ወንድም› ሆነው ለመቀጠል ሦስት ነገሮች ሳያስፈልጋቸው አይቀርም፡፡ ጠላትነትን ማጥፋት፣ ሌላ ዓይነት ወዳጅነትን መቀጠልና በአዲሱ መንገድ የሚመጡትን አስከፊ ነገሮች ሁሉ ለመቀበል መቻል፡፡ አንዳንድ ተጋቢዎች ሲለያዩ በጋብቻ ምትክ ጠላትነትን ተክተው ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ እንኳን ከዚህ በፊት አንድ ሆነው የኖሩና አንድ ሆነው ያደሩ፣ የተዋወቁም አይመስሉ፡፡ አንዱ ሌላውን ሲያስበው ያንገሸግሸዋል፡፡ ‹‹በለው በለው፣ ግደለው ግደለው› የሚለው ስሜት ይመጣበታል፡፡ ከፍቺ በኋላ ለሚፈጠሩ አሰቃቂ ወንጀሎች አንዱ ምክንያትም ይኼው ነው፡፡ ንብረት ክፍፍል ላይ ‹‹ይህንንማ አትገኛትም፣ አያገኛትም›› እየተባባሉ ምርኮ ስብሰባ የሚያስመስሉትም ለዚህ ነው፡፡

Saturday, July 26, 2014

ጳውሎስ ኞኞ (1926-1984)


አዘጋጅ፡- ደረጀ ትእዛዙ
ኅትመት፡- 2006 ዓም
የገጽ ብዛት፡- 308
ዋጋ፡- 84 ብር
ስለ ታላቁ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ፣ ደራሲና የታሪክ ሰው ጳውሎስ ኞኞ ታሪክ፣ ሥራዎችና ሀገራዊ አስተዋጽዖ የተጻፈ መጽሐፍ ነው፡፡ ደረጀ የጳውሎስ ጎረቤት ነበረ፡፡ ያደገውም እነ ጳውሎስ ሠፈር ነው፡፡ የልጅነቱ ትዝታ ስለ ጳውሎስ እንዲያጠና እንዳደረገው ይነግረናል፡፡ የጳውሎስን ሥራዎችና ስለ እርሱ የተጻፉ መዛግብትን አገላብጦ፤ ዛሬም በሕይወት ለታሪክ ቆይተው ያገኛቸውን የቅርብ ሰዎቹን አናግሮ ዙሪያ መለስ የሆነ ሥራ አቅርቦልናል፡፡ 

Tuesday, July 22, 2014

እንደገና እንጋባ

(ሁለተኛ ደብዳቤ)
ምን ብዬ ጠርቼሽ ልቀጥል
ለካስ እስካሁን የተዋደዱና የተጣሉ ሰዎች የሚጠራሩበት የቅጽል ስም እንጂ የተለያዩ፣ ግን ያልተጣሉ ሰዎች የሚጠራሩበት የቅጽል ስም የለንም፡፡ መቼም አንዳንዱን  ነገር የምንረዳው ሲገጥመን ብቻ ነው፡፡ በኑሯችን ውስጥ የሚጎድሉ፣ ነገር ግን ልብ የማንላቸው ጥቃቅን ነገሮች ብቅ የሚሉት ታላላቅ ነገሮችን አጥተን ቦታው ክፍት መሆኑን ስናረጋግጥ ብቻ ነው፡፡ ‹ውዴ› ብዬ እንዳልጠራሽ ተለያይተናል፤ ‹አንቺ ምናምን› ብዬ እንዳልጠራሽ ደግሞ እኔና አንቺ ተለያይተናል እንጂ ልቤና ልብሽ መለያየቱን እንጃ፡፡ ብቻ ለማንኛውም ዝም ብዬ ሐሳቤን ልቀጥል፡፡
ሰሞኑን ካንቺ ለመጨረሻ ጊዜ ተለያይቼ ከሌላ ሰው ጋር ስለ መኖር ሳስብ ነበር፡፡ ነገር ግን እስከ ዛሬ አስቤያቸው የማላውቅ ሐሳቦች ወደ ልቡናዬ እየመጡ ይሞግቱኝ ጀምረዋል፡፡ አንዱ ሞጋች እንዲህ አለኝ፡፡ ወደህ፣ ፈቅደህ፣ አፍቅረህ ካገባሃት፣ አብረሃትም ለዚህን ያህል ዓመት ከኖርካት፣ ከምታውቅህና ከምታውቃት፣ ካነበበችህና ካነበብካት ሴት ጋር አብረህ ለመኖር ካልቻልክ ከሌላዋ ጋር አብረህ ለመኖርህ ምን ዋስትና አለህ? ይህችንምኮ ያገባሃት አንተው ነህ፤ እንደ ጥንቱ ወላጆችህ አጭተውልህ ቢሆን ኖሮ በእነርሱ ታመካኝ ነበር፤ ያመጣሃትም የተጣላሃትም አንተው ነህ፤ ለእኔ የተሻልሽው አንቺ ነሽ ብለህ፤ ዐውቄሻለሁ፤ ተስማምተሽኛል ብለህ ያገባሃት አንተው ነህ፤ ያስገደደህ አካል አልነበረም፤ እንዲህ ብለህ ካገባሃት ሴት ጋር መኖር ለምን አቃተህ? እንዲህ ብለህ ካገባሃት ሴት ጋር መኖር ያቃተህ ሰው ከሌላዋ ጋር ለመኖርህ ምን ዋስትና አለህ?

Tuesday, July 15, 2014

ኡመተ ፈናን ኡመተ ቀሽቲ ዲሬ ዳዋ

(አርቲስቱና ሽቅርቅሩ የድሬዳዋ ሕዝብ)

ደራሲ፡- አፈንዲ ሙተቂ
የገጽ ብዛት፡-191
ዋጋ፡- 46 ብር
የኅትመት ዘመን፡- 2006 ዓም
አፈንዲ ሙተቂ ያበረከተልንን መጽሐፍ አነበብኩት፡፡ ከአዋሽ ወዲያ ማዶ ያለውን ሀገራችንን ሙልጭ አድርገን ለማወቅ የሚጎድለን ነገር መኖሩን የምንረዳው የእርሱን መጽሐፍ ስናነብ ነው፡፡ እንኳን እንደ እኔ በጎብኝነት የሚያውቀው ቀርቶ ተወልጄበታለሁ አድጌበታለሁ የሚለው ሁሉ የቀበሌ መታወቂያውን እንደገና እንዲያወጣ የሚያደርግ መጽሐፍ ነው፡፡
ሰው የሚያውቀውን ሲጽፍ ወይም የሚጽፈውን ሲያውቅ እንዲህ ያለ መጽሐፍ ይገኛል፡፡ ባሕሉ አልቀረ፣ ትውፊቱ አልቀረ፣ አባባሉ አልቀረ፣ ታሪኩ አልተዘለለ፣ መልክዐ ምድራዊ መረጃው አልተዘነጋ፣ አፈ ታሪኩ ቦታውን አልሳተ፣ ሁሉም በመልክ በመልኩ ተሰድሮ እንደ መልካም የወታደር ሠልፍ የቀረበበት መጽሐፍ ነው፡፡

Thursday, July 10, 2014

እንደገና እንጋባ

ይህንን ደብዳቤ ስጽፍ ፊት ለፊቴ የቤተሰባችንን ፎቶ ግድግዳው ላይ እያየሁ ነው፡፡ ‹‹ይናገራል ፎቶ›› አሉ፡፡ አቤት በፎቶማ እንዴት ያምርብናል፡፡ ፎቶ ላይ ያለው ፈገግታ እንዲሁ ትዳር ውስጥም ቢቀጥል እንዴት ጥሩ ነበር፡፡ ግርም ይላልኮ፡፡ፎቶ አንሺዎች ሁሉ ከአንድ እናት የተወለዱ ይመስል ለምንድን ነው በግድ ‹‹ፈገግ በሉ›› የሚሉት፡፡ በቃ ፎቶ ማለት ደስታን ማሳያ ብቻ ነው እንዴ፡፡ የከፋው ሰው ፎቶ አይነሳም ማለት ነው፡፡ አንዳንድ ፎቶ አንሺዎችና ቪዲዮ ቀራጮችኮ በገዛ ሠርጋችን ተዋንያን ያደርጉናል፡፡ እንደ ራሳችን ሳይሆን እንደ እነርሱ ፈቃድ ያስኬዱናል፣ ያሳስሙናል፣ ያስተቃቅፉናል፣ ያሰልፉናል፣ ያጣምሙናል፣ ያቃኑናል፡፡ እነርሱ ግን የፊልም ዳይሬክተር ናቸው ወይስ የሠርግ ቪዲዮ ቀራጮች? እኛስ ሙሽሮች ነን ወይስ ተዋንያን?
ከተለያየን ጀምሮ ይህንን ፎቶ ደጋግሜ እያየሁ ደጋግሜ አስባለሁ፡፡ ለብቻ መሆን አንድ የሚጠቅመው ነገር ቢኖር የማሰቢያ ጊዜ መስጠቱ ነው፡፡ ሰው ለመኖር ለካ ከምግብና መጠለያ እኩል የማሰቢያ ጊዜም ያስፈልገዋል፡፡ እንዲሁ ስንዞር፣ እንዲሁ ስንወጣና ስንወርድ፣ እንዲሁ ቀዳዳ ለመሙላት ወዲህ ወዲያ ስንል፣ እንዲሁ ጠዋት ወጥተን ማታ ስንገባ አይደል እንዴ የኖርነው? አሁን ሳስበውኮ የኑሮ ወንዝ ወደወሰደን ፈሰስን እንጂ አስበን አልኖርንም፡፡

Wednesday, July 2, 2014

ድኻው ምን አረገ

ሰሞኑን ከአንድ ሰው ‹የማጭበርበር› ነገር ጋር በተያያዝ ከዚህም ከዚያም አስተያየት ይሰጣል፡፡ አብዛኞቹ የመገናኛ ብዙኃንም ትኩረታቸውን በሰውዬው ላይ አድርገው እንዴት እንዲህ ሊያደርግ ቻለ? ለምን እንዲህ አደረገ? ምን ነክቶት ነው? እያሉ ጉዳዩን ከማኅበረሰብ ሳይንስ፣ ከሥነ ልቡና፣ ከእምነትና ከባሕል አንጻር እየተነተኑ ይገኛሉ፡፡
እኔ ግን ይህን ጉዳይ ስከታተል ትዝ የሚለኝ አንድ የሀገራችን ተረት ነው፡፡ ሰውዬው መንገድ ላይ ሲሄድ በሩ ወለል ብሎ የተከፈተ ቤት ያገኛል፡፡ ለጥቂት ቆም ብሎ ሁኔታውን ሲያይ ማንም በአካባቢው ዝር የሚል አልነበረም፡፡ ነገሩ የተከፈተ በር ብቻ ሳይሆን ‹የተከፈተ ዕድልም› የሆነለት ሰውዬ የተከፈተው ቤት ውስጥ ዘው ብሎ ይገባል፡፡ማንም አልነበረም፡፡ ወዲያና ወዲህ እየተንጎራደደ ቤቱን ቃኘና ዓይኑ ያረፈበትን ዕቃ ይዞ ላጥ አለ፡፡ መንገድ ላይ ያዩት ሰዎች የሚያውቁትን ዕቃ አንድ ሰው ይዞ ሲሸመጥጥ በማየታቸው ይጠራጠሩና ያስቆሙታል፡፡ ፖሊስም በነገሩ ይገባበታል፡፡ ሰውም ከዚህም ከዚያም ይወርድበታል፡፡