Monday, June 16, 2014

‹ትዕግሥት› - የቴሌ ሶፍትዌር

ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በእንግዶች ተጨናንቋል፡፡ በአዲስ አበባ ለሚዘጋጀው ዓለም አቀፍ ጉባኤ የሚመጡ እንግዶች አሁንም አሁንም የፍተሻውን መሥመር እያለፉ ሌሎች አገልግሎቶችን ለማግኘት ይሰለፋሉ፡፡ ብዙዎቹ የሞባይል ስልክ ለማግኘት የተሰለፉ ናቸው፡፡ የቪዛ አገልግሎት ለማግኘት እንኳን ያንን ያህል አልተሰለፉም፡፡ አንዳንዶቹ ያማርራሉ፣ አንዳንዶቹም ያመራሉ፡፡
ሰልፉ እየተቃለለ መጥቶ ሁሉም እንግዶች ወደየማረፊያቸው ተጓዙ፤ ጉባኤው የሚጀመረው ነገ ነው፡፡
በማግሥቱ የሀገሩም የውጭውም ሰው በአዳራሹ ከተተ፡፡ መርሐ ግብሩ እስኪጀመር ድረስ ንዴትና ብስጭት፣ ቁጣና ርግማን የተቀላቀለባቸው ንግግሮች ከእንግዶቹ እዚህም እዚያም ይሠነዘሩ ጀመር፡፡ ‹‹እንዴት ለሀገራቸው ሰው ብቻ የሚሠራ ስልክ ይሰጣሉ፤ ነውር አይደለም እንዴ›› ይላሉ እዚህም እዚያም፡፡ አንዳንዱ ስልኩን መሬት ላይ ቢፈጠፍጠው ንዴቱ የሚበርድለት ይመስል አሥር ጊዜ ይሠነዝረዋል፡፡ ወዲያው አንድ አካባቢ ሰዎቹ ከበው ቆሙ፤ ቀጥሎም ቁጣ ቀላቅሎ የሚዘንብ የውግዘት ዝናብ አወረዱ፡፡


ለካስ ከጉባኤው አስተናጋጆች መካከል አንዱን አግኝተውት ነው፡፡ ‹‹እንዴት ከስልክ ዐቅም የሀገር ሰውና የውጭ ትለያላችሁ፤ ሌላ ሀገርኮ ስልክ በሳንቲም ከሱቅ የሚሸመት ነው፤ የኛ ሳይሠራ እንዴት የናንተ ብቻ ተለይቶ ሠራ›› ባለሥልጣን እንዳጀበ መኪና ጥያቄው ተከታትሎ ወረደ፡፡ ‹‹ተአምኁ በበይናቲክሙ›› እንደተባለ አስቀዳሽ አንገቱን በአራቱም አቅጣጫ አዞረ፡፡ የቴሌውን ሰው ከሩቁ አየው፡፡ ክበቡን ጥሶ መሄድ ስለከበደው ሞባይሉን አወጣና በማዶ ለሚያየው የቴሌ ሹም ደወለ፡፡ ‹‹የደወሉላቸው ደንበኛ ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጭ ናቸው›› ስትለው ደንግጦ ዘጋው፡፡ እንግዶቹ በእንግሊዝኛ የምትለውን ቢሰሙ ጭራሽ ያብዳሉ ብሎ ፈራ፡፡ ‹‹ይኼ ታላቅ ስብሰባ የሚደረግበት አዳራሽ ራሱ ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጭ ነው ማለት ነው›› አለና አፈረ፡፡ ታድያ የቱ ነው ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውስጥ የሆነው? ለመሆኑ ይኼ ቴሌ የመሠረታቸው ‹የአገልግሎት ክልል› እና ‹ከአገልግሎት መስጫ ውጭ የሆነ ክልል› በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ያገኙ ክልሎች ናቸው? ቴሌስ የራሱን ክልል መመሥረት ይችላል እንዴ? ስንት ባልና ሚስት ‹የት ሄደህ ነበር፣ የት ሄደሽ ነበር› እየተባባለ የተጣላው ያቺ የቴሌ ሴትዮ ‹‹ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጭ ናቸው›› እያለች የሌለ ነገር አውርታ አይደል እንዴ?
አስተናጋጁ ይቅርታ ጠየቀና የቴሌውን ሹም ሊጣራ ሄደ፡፡ ‹‹እርሱ የቴሌ ባለሞያ ነው፤ ጠይቁት›› ብሎ ሹልክ ብሎ  ከክበቡ ወጣ፡፡ ወደ መድረኩ ሲያቀና ‹‹እንኳን እኔ አለቆቹ የማያውቁትን ጥያቄ ያዘንቡብኛል እንዴ›› ወደ መድረኩ ሲወጣ የቴሌውን ሹም የከበቡት እንግዶች የላምበረትን አውቶቡስ ተራ ጠሪዎች የመሰለ መዓት ድምጽ ሲያወርዱበት ሰማ፡፡ ‹‹ቻለው እንግዲህ፤ ኔት ወርኩ ያልቻለውን እናንተ ቻሉት›› አለ በልቡ፡፡
‹‹እንዴት ትናንትና የገዛነው ስልክ እስከ ዛሬ አይሠራም፤ የተሳሳተ ሲም ካርድ ነው የሰጣችሁን፤ አታላችሁናል፤ ገንዘባችንን መልሱ›› እንደ ሲሚንቶ አቡኪ ከየማዕዘኑ እንደ አሸዋ የበዛ ጥያቄ ጣሉበት፡፡ ፈገግ ለማለት ሞከረ፡፡ ፈረንጅ ፈገግታ ይወዳል የሚባለው ትዝ ብሎት፡፡ ‹‹ችግራችሁ ይገባኛል፡፡ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ አገልግሎቱን እንድታገኙ እናደርጋለን፤ ለተፈጠረው ችግር ይቅርታ እንጠይቃለን›› ሲል አሁኑኑ መፍትሔ አምጣ የሚል ወጣሪ ገጠመው፡፡ የሚያደርገውን ሲያጣ ስልኩን አወጣና ‹‹አንዴ ኃላፊውን ላናግረው›› አለና ደወለ፡፡ ‹‹የደወሉት ቁጥር የተሳሳተ ነው›› ስትለው እንግዶቹ እንግሊዝኛውን እንዳይሰሙ ሰግቶ እዘጋለሁ ሲል ጭራሽ ድምጽ ማጉያውን ከፈተውና አሰማቸው፡፡ ሰሚዎቹ ጎል እንደገባበት ስታዲዮም አንድ ላይ ጮኹ፡፡
እያመመው ፈገግ አለና ‹‹ሶሪ›› ብሎ ቀና ሲል የስብሰባው መጀመር ገላገለው፡፡ እንግዶቹ ወደመቀመጫቸው ሲያመሩ እርሱም አንገቱን ደፍቶ ወደ ቢሮው ገባ፡፡ ‹‹ምን ዓይነት መከራ ነው፡፡ ባለፈው ጊዜ ከስድስት መቶ ቦታዎች ስድሳውን ሠርተን ጨርሰናል ተብሎ ተነገረ፤ ሰውም ‹ጤፍ እየዘራን ነውና ራብህን ቻለው ማለት ነው› ብሎ ተረተብን፡፡ አሁን ደግሞ ምን ሊባል ነው፡፡ ያ የመሥመር ስልክ ይሻለን ነበር፡፡ በሞባይል የተላከ ቴክስትና በፖስታ የተላከ መልእክት እኩል እየደረሱ ቴሌ ምን ያደርጋል?
ስልኩን አነሣና ወደ ዋናው ቢሮ ደወለ፡፡
‹‹ኧረ ሰው ሊበላን ነው አንድ ነገር ይደረግ›› አለ በማዶ ላለው ሰውዬ፡፡
‹‹ገና ምኑን አይተህ ከዘጠና ሺ በላይ የሆኑ ደንበኞች ያወጡት ሲም ካርድ ሊሠራላቸው አልቻለም፡፡ ሲስተሙ ተበላሽቷል››
‹‹ታድያ መፍትሔው ምንድን ነው?››
‹‹እኛም አለቆቻችንን ስንጠይቅ ‹በቃ ታገሡ በሏቸው› ነው ያሉን››
‹‹እነዚህኮ ነገ ተሰብስበው ወደ ሀገራቸው ይሄዳሉ››
‹‹አገራቸው ከገቡ በኋላ በአድራሻቸው እንልክላቸዋለን›› ሣቀ፡፡
‹‹ታድያ ለምን ሸጥንላቸው››
‹‹እና ኢትዮጵያ የሞባይል ሲም አትሸጥም ይባል? ይኼማ ለገጽታችን ጥሩ አይደለም››
‹‹የኢትዮጵያ ሞባይል አይሠራም መባሉስ ገጽታ ይገነባል?››
ስልኩ ተዘጋ፡፡
የጉባኤው የመጀመሪያ ክፍል አብቅቶ እንግዶቹ የሻሂ ግብዣ ላይ ናቸው፡፡ መድረክ አካባቢ የነበሩት ባለ ሥልጣናትም ወደ እንግዶቹ መጥተው አብረው ሻሂ መጠጣት ጀመሩ፡፡ ሁለት ባለ ሥልጣናት ክብ ሠርተው ወደሚገኙ እንግዶች መጡና ተቀላቀሉ፡፡ ሁለቱም ራሳቸውን አስተዋወቁ፡፡ አንደኛው የቴሌ ዋናው ሰው ነበሩ፡፡ ‹የሰው ሁሉ ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል› እንዲል መጽሐፍ ሁሉም ዓይናቸውን በእርሳቸው ላይ ተከሉ፡፡ ሁሉም ቅሬታውን አዘነበ፡፡ ባለ ሥልጣኑም ራሳቸውን እየነቀነቁ ሰሙና ስልካቸውን አወጡ፡፡ ደወሉ፡፡
‹‹ቴሌፎኑ ለጊዜው ጥሪ አይቀበልም፣ ወይም ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጭ ነው›› ሲል ሰሙት፡፡ እንደገና ወደ ሥራ አስኪያጁ ሞከሩ ‹‹የደወሉት ቁጥር አገልግሎት ላይ ያልዋለ ነው፡፡›› የቴሌው ሥራ አስኪያጅ ቁጥር እንዴት አገልግሎት ላይ አልዋለም፤ እነዚህ ሰዎች ጠንቋይ ይመስል ለረሳቸው አያውቁም እንዴ›› ብለው ፈገግ አሉና ለመጨረሻ ጊዜ ሌላ ኃላፊ ጋ ደወሉ ‹‹ይህንን ጥሪ ለማድረግ የሚያስችል በቂ ሂሳብ የለዎትም›› ስትል ደነገጡና ‹‹ዋት፣ ይኼኮ ካርድ የሚሞላበት ስልክ አይደለም፤ ምን ማለቷ ነው›› የከበቧቸው ሰዎች የሚሉት ነገር አልገባቸውም፡፡
‹‹የሚመለከታቸውን ላናግር ነበር፤ የኔም ስልክ ግን እንደናንተው አይሠራም፤ ከመታገሥ በቀር ሌላ አማራጭ የለንም›› አሉ፡፡
‹‹እስከ መቼ ነው ግን የምንታገሠው? ስብሰባውኮ ነገ ያልቃል››
‹‹ልክ ናችሁ ብዙ ስብሰባዎችም እንዲሁ በትዕግሥታችን ነው ያጠናነቅናቸው››
‹‹ታግሠን ግን ምን ይገኛል››
‹‹ስብሰባው ያልቅና አገራችሁ ትገባላችሁ፤ ያን ጊዜ ሲም ካርድ ለምን አልሠራም? ማለት ታቆማላችሁ፤ ጥያቄውን መመለስ ካልተቻለ ሌላው አማራጭ ጥያቄውን እንዳይጠየቅ ማድረግ ነው››
ምሽት ላይ ስብሰባው ሲያልቅ መሬቱን የሞላው የተወረወረ ሲም ካርድ ነው፡፡ ለጽዳት ሠራተኞች ግን ሠርግና ምላሽ ሆኖላቸዋል፡፡

© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው

13 comments:

 1. ‹‹ቴሌፎኑ ለጊዜው ጥሪ አይቀበልም፣ ወይም ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጭ ነው›› ‹‹የደወሉት ቁጥር አገልግሎት ላይ ያልዋለ ነው፡፡››ዳኒ በአንድ ወቅት የሆነ ቦታያነበብኩ ትዝ አለኝ፡፡ "ቴሌ አለ ኮሚኒኬሸን የለም ኔት አለ ወርክ የለም ሀላፊ አለ ስራ የለም"፡፡

  ReplyDelete
  Replies
  1. ሞኝዎትን ይፈልጉ ! የሙባረክ መንግስት ግብጽ ውስጥ የቀለጠው ፡ ኮምኒኬሽን አሳድጎ ነው።
   መንገደኛው

   Delete
  2. Poor communication poorly informed society the government get to play with the poor longer. Well thought my friend. The only good thing is Ethiopia's fate relies on God and only on God. This Zelans shall pass soon.

   Delete
 2. እና ኢትዮጵያ የሞባይል ሲም አትሸጥም ይባል? ይኼማ ለገጽታችን ጥሩ አይደለም››
  ‹‹የኢትዮጵያ ሞባይል አይሠራም መባሉስ ገጽታ ይገነባል?››

  ReplyDelete
 3. ቴሌ አለ ኮሚኒኬሸን የለም ኔት አለ ወርክ የለም ሀላፊ አለ ስራ የለም"፡፡

  ReplyDelete
 4. We live it, we know it, we say it. we cry it. We didnit get it.You write it, you say it but you will not get it. They lie many times. They promise many times. They anounce many times. They change contructor many times. They have been worked many times but still we didn't get it.

  ReplyDelete
 5. ዳንየ እምየ አገሪ ባጋጠማት የሰልክ አገልግሎት ሁዋላ ቀርነት ባዝንም ፤ ባሕር ማዶ ላለነው የዋጋ መናሩም አስመርሮናል። ሲሰተካከል ለዚሑም ቦታ ሰጥተው ቤያሻሽሉት መልካም ነበር።

  ReplyDelete
 6. ‹‹ስብሰባው ያልቅና አገራችሁ ትገባላችሁ፤ ያን ጊዜ ሲም ካርድ ለምን አልሠራም? ማለት ታቆማላችሁ፤ ጥያቄውን መመለስ ካልተቻለ ሌላው አማራጭ ጥያቄውን እንዳይጠየቅ ማድረግ ነው››

  ReplyDelete
 7. በሞባይል የተላከ ቴክስትና በፖስታ የተላከ መልዕክት እኩል እየደረሱ ቴሌ ምን ይሰራል?

  ReplyDelete
 8. ay tele!!!! ay tele!!! andegnawen baysera yeshalal ahunema yametuben tata internet tetekemu belew wey anetekem wey santibachenen alaterefn endihu mezref tejemerualko be tele telewoch ebakachu genzeb mezref becha sayhon agelgelotunem asebubet

  ReplyDelete
 9. በትክክል እይታህ የንስር መሆኑን ለመመስከር የሚያስችሉኝን እይታዎችህን አብሬ አይቻለሁ...በመጸሐፍሕ ምረቃ/ድሬ ዳዋ/ ተገኝቻለሁ በርከት ያሉ ስብከቶችህን አድምጫለሁ በሥራዎችህ በተለይ የራስን ሰዎች ማክበር በኔ በኩል የሚያስመሰግንህ መሆኑን በአክብሮት እና በትህትና እየገለጽኩ ማሕበርህን ደግሞ የማልወደው መሆኑን አልደብቅህም፡፡ሞክሼህ ከድሬ ደዋ

  ReplyDelete
 10. ሞኝዎትን ይፈልጉ ! የሙባረክ መንግስት ግብጽ ውስጥ የቀለጠው ፡ ኮምኒኬሽን አሳድጎ ነው።
  መንገደኛው

  ReplyDelete
 11. ''teff eyezeran new erabhen tages''.

  ReplyDelete