<<ስኩል ኦፍ ኖርዘርን ስታር›› ከሚባለው ውድ ትምህርት ቤቱ የአያቱ ሾፌር
ወደ ቤቱ ሲያመጣው ልቡ ከመኪናው ፍጥነት በላይ ነበር ወደ ቤቱ የሚሮጠው፡፡ ያየውንማ ለአያቱ መንገር አለበት፡፡ አያቱ እንዲህ
ታዋቂ አክተር መሆናቸውን አያውቅም ነበር፡፡ ፊልሙን ሲመለከት
አያቱን በመሪ ተዋናይነት በማግኘቱ ከትምህርት ቤት ጓደኞቹ ጋር በኩራት ነበር ያወራው፡፡ እነርሱም የታዋቂ ሰው የልጅ ልጅ
በመሆኑ ከፊልሙ በኋላ እንደ ንብ ነበር የከበቡት፡፡ ብዙዎቹ እንዲያውም በወረቀት ላይ አያቱን አስፈርሞ እንዲያመጣላቸው፣
ከተቻለም ፎቷቸውን እንዲሰጣቸው ለምነውታል፡፡
ቤቱ ሲገባ አያቱ የሉም፡፡ ደወለላቸው፡፡ እየመጡ መሆናቸውን ነገሩት፡፡ መክሰስ
ለመብላት እንኳን ሆድ አልቀረለትም፡፡ ይህን አስገራሚ ነገር ከአያቱ ጋር ማውራት እጅግ አጓጉቶታል፡፡ እየደጋገመ ‹ፐ›
ይላል፡፡ አባቱና እናቱ ራሳቸው ይህንን የሚያውቁ አልመሰለውም፡፡ ይህንን ነገር ያወቀ የመጀመሪያ ሰው እርሱ ብቻ ሊሆን
እንደሚችል ገምቷል፡፡ ‹ፐ›፡፡
አያቱ መጡ፡፡