Thursday, May 15, 2014

መሟላት

እሥራኤላውያን እንዲህ ይተርካሉ፡፡
በኢየሩሳሌም ከተማ የሚኖሩ ሁለት ወንድማማቾች ነበሩ፡፡ አንደኛው ባለ ትዳርና የቤተሰብ አስተዳዳሪ፣ ሌላኛው ደግሞ ላጤ ነበሩ፡፡ ሁለቱም የሚተዳደሩት በአንድ የእርሻ መሬት ነው፡፡ ጠንክረው በጋራ በመሥራት ያመርቱና ምርቱን በእኩል ይካፈላሉ፡፡ በሥራና በኑሮ ያላቸው መተጋገዝና መጠቃቀም ለአካባቢው ሰዎች ሁሉ እጅግ የሚያሰቀና ነበር፡፡ አንደኛው ለሌላኛው የሚያስበውን ያህል ለራሱ አያስብም ነበር፡፡
አንድ ቀን ላጤው ለባለ ትዳር ወንድሙ እንዲህ አሰበ፡፡ ‹‹ወንድሜ የቤተሰብ ኃላፊ ነው፡፡ ባለቤቱን፣ ልጆቹን፣ የባለቤቱን ወላጆችና የቤቱን ሠራተኞች ማስተዳደር አለበት፡፡ ምርቱን ከእኔ ጋር እኩል መካፈል የለበትም፡፡ እርሱ ከእኔ የሚበልጥ ምርት ማግኘት አለበት፡፡ ነገር ግን አሁን ከእኔ የተሻለ እህል ውሰድ ብለው አይቀበለኝም፡፡ ስለዚህ በሌላ መንገድ መርዳት አለብኝ፡፡››
አውጥቶ አውርዶም በጎተራ ካለው የእርሱ እህል እየወሰደ ማታ ማታ ተደብቆ በወንድሙ ጎተራ ውስጥ ለማስቀመጥ ወሰነ፡፡ ማታ ማታ ተደብቆ በመውጣት ከራሱ ጎተራ ወደ ወንድሙ ጎተራ እህል ይገለብጥ ነበር፡፡ ነገር ግን ጠዋት ጎተራውን ሲያየው እንኳንስ ሊጎድል ካለፈው የበለጠ ሞልቶ ያገኘው ነበር፡፡ ይህም እጅግ ይገርመው ነበር፡፡ ፈጣሪ በጎ ሥራዬን አይቶ እየባረከኝ ነው ብሎም አመሰገነ፡፡


ባለትዳሩም እንዲሁ ለብቻው ‹‹ወንድሜ እንደ እኔ አላገባም፡፡ ለወደፊትም ከባድ ኃላፊነት ይጠብቀዋል፡፡ ትዳር መመሥረት አለበት፣ልጆች መውለድ አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ አሁን የሚያገኘው ምርት በቂው አይደለም፡፡እኔ የራሴን ኑሮ አደላድያለሁ፡፡፡ እርሱ ግን ገና አዳጊ ነው፡፡ አሁን እርሱን የሚበልጠውን ምርት ውሰድ ብዬ ብነግረው አይቀበለኝም፡፡ ስለዚህ በድብቅ ልረዳው ይገባኛል›› ብሎ አሰበ፡፡
ወንድሙ ለእርሱ የሚያደርገውን ያላወቀው ባለ ትዳሩ ወንድምም ሊነጋጋ ሲል እየተነሣ ከራሱ ጎተራ ወደ ወንድሙ ጎተራ እህል ይጨምር ነበር፡፡ ጠዋት ሲነሣ ግን ጎተራው ሳይጎድል ያገኘዋል፡፡ ይህም ሁልጊዜ ይገርመዋል፡፡ መስጠቴን ተመልክቶ ፈጣሪ ነው የሞላልኝ እያለም ያመሰግን ነበር፡፡
እንዲህ እያደረጉ ለብዙ ጊዜ ከኖሩ በኋላ በአንድ ሌሊት አንደኛው እህሉን ተሸክሞ ወደሌላው ጎተራ ሲሄድ በድንገት መንገድ ላይ ተገናኙ፡፡ ሁለቱም በነገሩ ተገርመው ተቃቅፈው እየተላቀሱ የነበረውን ነገር ተነጋገሩ፡፡ ከበፊቱ ይልቅም ፍቅራቸው እጅግ ጸና፡፡ እግዚአብሔርም ተገኝቶ ለዚህ ፍቅራቸው መታሰቢያ እንዲሆን በእነርሱ የእርሻ ቦታ ላይ ቤተ መቅደሱ እንደሚሠራ ቃል ገባላቸው፡፡ ንጉሥ ሰሎሞን ታላቁን ቤተ መቅደስ በኢየሩሳሌም ውስጥ የሠራው በእነዚህ ወንድማማቾች የእርሻ ቦታ ላይ ነው ይባላል፡፡
ከፍቅር መገለጫዎች ዋናው መሟላት ነው፡፡ ታላቁ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ዘርዐ ያዕቆብ ሰው ማለት የሚሟላ ፍጡር ነው ይላል፡፡ ሙሉ እንዲሆን እንጂ ተሟልቶ አልተፈጠረም፡፡ ለመሟላት ሌላ ሰው ያስፈልገዋል፡፡ ሰው የፈለገውን ያህል የበቃ የነቃ ቢሆንም ሙሉ ሰው ለመሆን ግን ሌላ ሰው ያስፈልገዋል፡፡ ሰውን በመተቸት፣ ስሕተቱን በመግለጥ፣በመውቀስና ጎደሎነቱን በማሳየት ከምናርመውና ከምናስተካክለው በላይ የጎደለውን በመሙላት እናስተካክለዋለን፡፡ የምንወደው ሰው፣ የምናስብለት ሰው፣ የምናወቀው ሰው፣ ማለት የምናሟላው ሰው ማለት ነው፡፡
በወዳጅና ወዳጅ ባልሆነ መካከል ያለው አንዱ ዋና ልዩነት አብሮ ከመብላት፣ አብሮ ከመጠጣት፣ ልቅሶና ደስታ ከመደራረስ፣ ከመደዋወልና ከመጠያየቅ፣ ከመዛመድና አብሮ ከመኖር የሚመጣ አይደለም፡፡ ሰውን ለምን እናውቀዋለን? ለምንስ ማወቅ እንፈልጋለን? ለምንስ እንቀርበዋለን? ሰው ስለሆንን፣ የሚጠይቅ ኅሊና የሚያስብ ልቡና ስላለን ማወቅ የመጀመሪያው ነው፡፡ ይህንን መከላከል አንችልም፡፡ የግድ ከልዩ ልዩ ምንጮች ስለ አንድ ሰው እናውቃለን፡፡ ይህ ማወቅ ግን መተዋወቅን አይፈልግም፤ መቀራረብንም የግድ አያመጣም፡፡ ሁለተኛው ደግሞ መተዋወቅ ነው፡፡ ይኼኛው መቀራረብን ያስከትላል፡፡ መስተጋብርን ይፈጥራል፡፡ በዚህ መልኩ የምናገኘው መተዋወቅ ኃላፊነትን ይወልዳል፡፡ የመሟላትን ኃላፊነት፡፡
መተዋወቅ ለመሟላት ካልሆነ ስለ ሰዎች ያለንን ፋይል መቀነስ ያስፈልገናል፡፡ ዐወቅኩት፣ ቀረብኩት፣ እገሌንኮ ዐውቀዋለሁ፣ እቀርበዋለሁ ለማለት መተዋወቅ አያስፈልገንም፡፡ ግንኙነታችን መሟላትን የማያመጣ ከሆነ ዕውቀት መቀነስ ታላቅ ብልሃት ነው፡፡ ከሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት በሦስት መልኩ ብናደርገው ግንኙነታችን የታሰበበትና የተሟላ ይሆንልናል፡፡
የማናውቃቸው ሰዎች፡፡ እነዚህ ሰዎች ከኛ ጋር ለመተዋወቅም ሆነ በእኛ ለመታወቅ ዕድል የሌላቸው ወይም ዕድል የሌለን ናቸው፡፡ የሚበዙትም እነርሱ ናቸው፡፡ በማወቃችን የምናተርፈው ወይም የሚያተርፉት ነገር ከሌለ አለማወቃችን ምንም ጉዳት የለውም፡፡ ያገኙትን ሰው ሁሉ ስልክ የሚቀበሉ፣ ደግመው የማያገኙትን ሰው የሚተዋወቁ ሰዎች ሊያውቋቸው በማይገቡ ሰዎች ፋይላቸውን የሚያጨናንቁ ናቸው፡፡
ሁለተኛዎቹ የምናውቃቸው ሰዎች ናቸው፡፡ እነርሱ ሊያውቁንም ላያውቁንም ይችላሉ፡፡ ያ ደግሞ የእነርሱ ፋይል ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የሥራ ባልደረቦቻችን፣ ጎረቤቶቻችን፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ደንበኞቻችን፣ ዕውቀትን የምንሸምትባቸው ሰዎች፣ በልዩ ልዩ ምክንያት የምናገኛቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ከእነርሱ የምንፈልገው፣ ለእነርሱም የምንሰጠው ነገር ስላለ እናውቃቸዋለን፡፡ አንዳንዶቹንም ማወቅ የግድ ይለናል፡፡ ሌሎቹን ደግሞ አለማወቅ አንችልም፡፡ እነዚህን ሰዎች የግድ መቀራረብ፣ መተዋወቅ፣ ወይም የተለየ ተግባቦት መፍጠር ላያስፈልገን ይችላል፡፡ ግንኙነታችን አንድን ጉዳይ፣ ተግባር፣ ኃላፊነት፣ መሥመር ወይም ደግሞ ሁኔታ መሠረት ያደረገ ነውና፡፡
ሦስተኛው መተዋወቅ የሚባለው ነው፡፡ መቀራረብንና መግባባትን የሚያመጣው፡፡ በውስጡም መዋደድ ያለበት፡፡ ከላይ በሚገኙት ሁለቱ መውደድ እንጂ መዋደድ የለባቸውም፡፡ የማናውቃቸውንም ሰዎች፣ የምናውቃቸውንም ሰዎች ልንወዳቸው እንችላለን፡፡ ግንኙነት የሚያመጣው መዋደድ ግን ላይኖር ይችላል፡፡ እኛ ስለ እነርሱ እናስብ ይሆናል፣ እነርሱ ስለ እኛ እንዲያስቡ አይጠበቅምና መተሳሰብ ላይኖር ይችላል፡፡ በመተዋወቅ ውስጥ ግን ሦስቱም አሉ፡፡ መግባባት፣ መተሳሰብና መዋደድ፡፡ እነዚህ ሦስቱ ነገሮች ወዳጃዊ ኃላፊነትን ያስከትላሉ፡፡ አንዱ ለሌላው በጎ መሆን፣ ስኬትና ደኅንነት ኃላፊነት ይሰማዋል፡፡ ይህ ኃላፊነት ከመጠየቅ፣ ከመለመን ወይም ከመወትወት የሚመጣ አይደለም፡፡ ከመተዋወቅ የሚመጣ ራስ ወሰድ ኃላፊነት ነው፡፡
ለሌላው ሕይወት የማይገደን ወይም ኃላፊነት የማይሰማን ከሆነ የተሻለው መንገድ ዕውቀት መቀነስ ነው፡፡ ለምን እንቀራረባለን? ለምን እንወያያለን? ለምንስ የማንሸከመውን የሰው ‹ውስጥ› እናውቃለን? ለምንስ የማንጋራውን የሰው ችግር እናውቃለን? ለምንስ የማንሞላውን ጉድለት እንሰማዋለን? ለምንስ የማናክመውን ቁስል እንመረምረዋለን? አንዳንድ ሰው አመል ሆኖበት ‹‹ይህ ነገር አይመለከተኝም፣ ይህ ነገር ልሸከመው አልችልም፣ ይህንን ነገር መስማት የለብኝም፣ ይህ ነገር የሰውየው የራሱ ብቻ ነው›› ማለት አይችልም፡፡ በሁሉም ነገር ውስጥ ይገባል፣ ሁሉም ነገር ይመለከተኛል ይላል፣ ሁሉንም ነገር በዝርዝር ያውቃል፣ የሁሉም ሰው ጓዳ ዘው ይላል፡፡ ነገር ግን ምንም ዓይነት ኃላፊነት አይወስድም፡፡ ከማወቅና ሲወራ አብሮ ከማውራት፣ ባስ ሲልም ‹ገመናን ከማጋለጥ› ያለፈ ሚናም የለውም፡፡ መሸሽ እንዲህ ካለው ሰው ነው፡፡
የሰሎሞን ቤተ መቅደስ በእነዚህ በመሟላት በሚኖሩ ወንድማማቾች እርሻ ላይ እንደተገነባው ሁሉ የኛም የትዳር፣ የወዳጅነት፣ የጓደኛነት፣ የሥራና የጉርብትና መቅደሳችን በመሟላት ላይ ቢመሠረት ኖሮ፣ ተባብሮ ከመውደቅ ተባብሮ ወደ ማደግ፣ ተያይዞ ከመጠፋፋት፣ ተያይዞ ወደ መመንደግ፤ ጥሎ ከማለፍ ይዞ ወደማለፍ ይሸጋገር ነበር፡፡ ይኼው ሦስቱንም ታላላቅ እምነቶች(እስልምና፣ ይሁዲነትንና ክርስትና) አስተሳሥሯል የሰሎሞን መቅደስ፡፡ ሁሉም እዚያ ቦታ አለው፤ ልብም አለው፡፡ ሁሉም እዚያ ይጸልያል፤ ሁሉም ያንን ቦታ ያከብራል፡፡ መግባባትን ከመነጋገር በላይ ይበልጥ የሚያጠነክረው ‹መሟላት› ነው፡፡ አብሮ መኖርን አብሮ ከመሥራት በላይ ‹መሟላት› የተሟላ ያደርገዋል፡፡ ወዳጅነትን አብሮ ከመብላት በላይ ‹መሟላት› ያጸናዋል፡፡
መሟላት መጓደልን የሚያጠፋ ነው፡፡ በመሟላት የሚኖሩ ወዳጆች የሚሞሉትን ያህል ይሞላላቸዋል፡፡ ሳያጎድሉ መስጠት የሚቻለው በመሟላት ነው፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ተረት እዚህ ላይ ትዝ አለኝ፡፡ በወዳጁ ሀብት የሚቀና አንድ ጎረቤት ከወዳጁ አሞሌ ጨው ይበደራል፡፡ብድሩን ክፈል ሲባል ‹‹አሞሌውኮ ድንጋይ ሆነብኝ›› ብሎ ይመልሳል፡፡ ያ ጎረቤትም ተንኮሉን ቢያውቅም የሚያደርገው ስላልነበረው ዝም ብሎ ኖረ፡፡ አንድ ቀንም ‹እባክህ ሴት ልጅህ ባለቤቴን የድግስ ሥራ ታግዛት›› ብሎ ለመነውና የጎረቤቱን ሴት ልጅ ወሰደ፡፡ ልጂቱም ትመጣለች ተበላ ብትጠበቅ በዚያው ቀረች፡፡ ልጂቱን የወሰደው ጎረቤትም ‹‹ልጂቱማ ዝንጀሮ ሆነችብኝ›› ብሎ መለሰ፡፡ ያም ድሮ በአሞሌው ላይ የሠራውን ያውቅ ነበርና ውጦ ዝም አለ፡፡
ከብዙ ጊዜ በኋላ ሁለቱም ጠዋት ከብት አውጥተው ሲያሠማሩ ተገናኙ፡፡ አስቀድሞም ልጁ ዝንጀሮ ሆነች የተባለበት አባት እንዲህ ብሎ አንጎራጎረ፡-
‹‹ወይ ዘንድሮ ወይ ዘንድሮ
ልጄ ሆነች ዝንጀሮ››
አሞሌው ድንጋይ የሆነበትም
‹‹ወይ ጉባይ ወይ ጉባይ
አሞሌ ሆነ ድንጋይ››
ሲል መለሰ፡፡
የልጂቱ አባትም
‹‹አሞሌስ አለ ከጎታ
የልጄን ነገር እንዴታ›› ሲል ጠየቀ፡፡
የአሞሌው ጌታም፡-
‹‹አሞሌስ ካለ ከጎታ
ልጂቱም አለች ካጎቷ›› ሲል አበሠረው ይባላል፡፡ ስንሟላ እንጂ ስንባላ አናድግም፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው፡፡

33 comments:

 1. ቃላቶች ያጥሩኛል:ወንድማችን ዲ/ን ዳንኤል እግዚአብሔር እድሜና ጤና ይስጥህ::

  ReplyDelete
 2. Egziabher ejochihin yibark, Dani. Berta

  ReplyDelete
 3. that is right,
  ስንሟላ እንጂ ስንባላ አናድግም፡

  ReplyDelete
 4. ስንሟላ እንጂ ስንባላ አናድግም

  ReplyDelete
 5. እውነት ነው ስንሟላ እንጂ ስንባላ አናድግምና ፍቅር የተባለ እግዚአብሔርን ይዘን በፍቅር እንጓዝ፡፡ ዲ/ን ዳኒኤል እግዚአብሔር ይባርክህ

  ReplyDelete
  Replies
  1. እውነት ነው ስንሟላ እንጂ ስንባላ አናድግምና ፍቅር የተባለ እግዚአብሔርን ይዘን በፍቅር እንጓዝ፡፡ ዲ/ን ዳኒኤል እግዚአብሔር ይባርክህ

   Delete
 6. መግባባት፣ መተሳሰብና መዋደድ፡፡ እነዚህ ሦስቱ ነገሮች ወዳጃዊ ኃላፊነትን ያስከትላሉ፡፡ አንዱ ለሌላው በጎ መሆን፣ ስኬትና ደኅንነት ኃላፊነት ይሰማዋል፡፡

  መምህር ዳንኤል እግዚአብሔር እድሜና ጤና ይስጥህ::

  ReplyDelete
 7. ውብሸት ተክሌMay 15, 2014 at 6:04 PM

  ዛሬ ቀኑ ምን እንደሆነ አላውቅም ድብርት ጥሎቢኛል፤ የግንቦት ወር ለኢትዮጵያውያን ምንድን ነው ? ታሪክን የኃሊት ለመመልከት ሞከርኩኝ፤ በግንቦት ወር በኢትዮጵያ ታሪክ መፈንቅለመንግስት፤ በቅሎቤት ፍንዳታ፤ አዲስ አበባ በተኩስ ስትታመስ ታንክና ወታደር አብረው ሲጋዩ ወዘተ በሐሳቤ ድቅን አለቢኝ ባሩድ ባሩድ ሸተተኝ አማትቤ ሌላ ነገር ለማሰብ ሞከርኩኝ፡፡ የቀድሞ ነገስታት ዛሬ ደግሞ አዝማሪ ምን አለ ብለው ይጠይቁ ነበር፤ እኔ ደግሞ ዳንኤል ክብረት ዛሬ ደግሞ ምን አለ ብዬ ጠየኩኝ፤ ይህንንም ጦማር አነበብኩኝ በጣምም ገረመኝ በጣምም ደነቀኝ “እንዲህ ያለ ፍቅር እንዴት ያለ ፍቅር ነው” አለ ሊቁ አባ ሕርያቆስ፤ በዚህ ዘመን ግን እንዲህ ያለ ፍቅር መተሳሰብ ይኖራል ? አይመስለኝም የፈለገ ሰው እንደ ፈላስፋው ዲዮጋን በጠራራ ፀሐይ ፋኖስ አብርቶ ከተማውን ያስስ እግሩም እስኪቀጥንም ከአገር አገር ይዙር አይደለም የዚህን ያህል ፍቅር የእንጥፍጣፊ እንጥፍጣፊ አያገኝም፤ እንኳን እንደ ዛሬው 14 ትናንሽ ሆነን “አንድ ኢትዮጵያ አንድ ሕዝብ ሆነንም ሳለ አልተዋደድንም” ለማንኛውም ዛሬ ቀኑን ሙሉ ይዞኝ የነበረው ድብርት ይህን ጽሑፍ ሳነብ እንደ ጉም በኖ እንደ ጢስ ተኖ ጠፋሊኝ እኔም አስተያየቴን ጻፍኩኝ ኮምፕዩተሬን ዘግቼም ከቢሮ ወጣሁኝ፡፡ ዕድሜ ይስጥህ፤ ልጆችህ ይባረኩ፤ የሰጠህን ዕውቀት አያጉልብህ፤ የሰጠህን ጸጋ አይንሳህ፡፡

  ReplyDelete
 8. እግዚአብሔር ቃለ ሕይዎት ያሰማልን፡፡

  ReplyDelete
 9. it is so interesting.

  ReplyDelete
 10. ስንሟላ እንጂ ስንባላ አናድግም፡፡

  ReplyDelete
 11. ምን ይባላል ዲያቆንዳንኤል እውነት ነው ስንሟላ እንጂ ስንባላ አናድግም መድሃኒዓለም እድሜና ጤና ይስጥህ እኛንም አንባቢ ብቻ ሳይሆን ተግባሪም ያድርገን አንብበን ሰምተን አይተን ለመለወጥ ያብቃን

  ReplyDelete
 12. አቤት መታደል! አሁንም ፀጋውን ያብዛልህ፤ፍቅርን ሳይሆን ጥላቻን፣አንድነት ሳይሆን መለያየትን፣መቻቻልን ሳይሆን መጠፋፋትን ለሚሰብኩና ለሚቀሰቅሱ ትምህርት ነውና ቀጥልበት
  እንደ ጠቀስኩት እኩይ ተግባርን ለሚሰሩና ለሚያስቡትም እግዚአብሄር ማስተዋልን ይስጣቸው፡፡እስከዛሬ የነበረው አብሮነታችን እንዲቀጥል ሁላችንም የበኩላችንን እንወጣ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !

  ReplyDelete
 13. betam des yemile ababale new egiziabhere yakoyih

  ReplyDelete
 14. It is so interesting. GOD bless you Dn. Daniel.

  ReplyDelete
 15. It is great. GOD Bless you.

  ReplyDelete
 16. ለመሟላት የገዛ ጭንቅላትን ማሰራትና ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ለብዙዎቻችን ከዚህ ይልቅ የሚያባሉንን ማመን ይቀለናል፡፡

  ReplyDelete
 17. ዲ/ን ዳንኤል፡፡ አዎ ልክ ብለሀል፤ እኛም ሳናውቀው ቀርተን አይመስለኝም ግን እንዴት ወደ ተግባር እናምጣው; የተቸገርነው ይህንን ይመስለኛል፡፡ ትናንት ማምሻ የገጠመኝን ላካፍልህ፡፡ ደብረ ዘይት ለስራ ጉዳይ ሄጄ ስመለስ መናኸሪያ ለመድረስ ታክሲ ውስጥ ገባሁ፡፡ ኪሴን ስዳብሰው የታክሲ ሂሳብ ሶስት ብር ቢሆንም ያለኝ ዝርዝር ሁለት ብር ብቻ ነው፡፡ ረዳቱን የመቶ ብር ዝርዝር ስጠኝ ለማለት ከብዶኝ ስሳቀቅ ከጎኔ ያለቸው ተሳፋሪ እኔ ልሙላልህ አትቸገር አለችኝ፡፡ በመሀል ግን ረዳቱ ዘረዘረልኝ፡፡ በልጅቱ ደግነት ተማርኬ የእሷንም ሂሳብ ከፍዬ ደስ እያለኝ ወረድኩ፡፡
  ከአምስት ቀን በፊት ጀርመን ሀምቡርግ ውስጥ ከተወሰኑ አፍሪካውያን የስራ ባልደረቦቼ ጋር ነበርን፡፡ የሄድንበትን የስራ ተልዕኮ ጨርሰን ወደ አየር ማረፊያው ለመሄድ ባቡር ጣቢያ ሆነን መስመራችንን በመፈለግ በዚህ ነው በዚያ ነው ስንባባል እዛው ሀገር ነዋሪ የምትመስል አንዲት ኢትዮጵያዊት ሰምታን ኖሮ መጥታ ወደ ኤርፖርት ለመሄድ መጠቀም ያለባችሁ የባቡር ቁጥር ይሄን ነው ብላ አመላክታን ሄደች፡፡ እኛም አመስገነን ምክሯን ተቀበልናት፡፡
  ይህ ኢትዮጵያዊ ባህላችን ከተረት ተረት ወጥቶ ወደ ቀደመ ማንነቱ የሚመለስበት ጊዜ ለብዙዎቻችን ይናፍቀን ይመስለኛል፡፡ እንዳልከው ማንም በራሱ ምሉዕ የሆነ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ መፍረስ ያለባቸውን ያበጀናቸውን ድንበሮች አፍርሰን እንድንሞላላ ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡ ቀጣዩን የተዋዛውን ቁም ነግርህን እንጠብቃለን፡፡ በርታ፡፡

  ReplyDelete
 18. amlaki melkamun menged ymiran .

  ReplyDelete
 19. ዛሬ ቀኑ ምን እንደሆነ አላውቅም ድብርት ጥሎቢኛል፤ የግንቦት ወር ለኢትዮጵያውያን ምንድን ነው ? ታሪክን የኃሊት ለመመልከት ሞከርኩኝ፤ በግንቦት ወር በኢትዮጵያ ታሪክ መፈንቅለመንግስት፤ በቅሎቤት ፍንዳታ፤ አዲስ አበባ በተኩስ ስትታመስ ታንክና ወታደር አብረው ሲጋዩ ወዘተ በሐሳቤ ድቅን አለቢኝ ባሩድ ባሩድ ሸተተኝ አማትቤ ሌላ ነገር ለማሰብ ሞከርኩኝ፡፡ የቀድሞ ነገስታት ዛሬ ደግሞ አዝማሪ ምን አለ ብለው ይጠይቁ ነበር፤ እኔ ደግሞ ዳንኤል ክብረት ዛሬ ደግሞ ምን አለ ብዬ ጠየኩኝ፤ ይህንንም ጦማር አነበብኩኝ በጣምም ገረመኝ በጣምም ደነቀኝ “እንዲህ ያለ ፍቅር እንዴት ያለ ፍቅር ነው” አለ ሊቁ አባ ሕርያቆስ፤ በዚህ ዘመን ግን እንዲህ ያለ ፍቅር መተሳሰብ ይኖራል ? አይመስለኝም የፈለገ ሰው እንደ ፈላስፋው ዲዮጋን በጠራራ ፀሐይ ፋኖስ አብርቶ ከተማውን ያስስ እግሩም እስኪቀጥንም ከአገር አገር ይዙር አይደለም የዚህን ያህል ፍቅር የእንጥፍጣፊ እንጥፍጣፊ አያገኝም፤ እንኳን እንደ ዛሬው 14 ትናንሽ ሆነን “አንድ ኢትዮጵያ አንድ ሕዝብ ሆነንም ሳለ አልተዋደድንም” ለማንኛውም ዛሬ ቀኑን ሙሉ ይዞኝ የነበረው ድብርት ይህን ጽሑፍ ሳነብ እንደ ጉም በኖ እንደ ጢስ ተኖ ጠፋሊኝ እኔም አስተያየቴን ጻፍኩኝ ኮምፕዩተሬን ዘግቼም ከቢሮ ወጣሁኝ፡፡ ዕድሜ ይስጥህ፤ ልጆችህ ይባረኩ፤ የሰጠህን ዕውቀት አያጉልብህ፤ የሰጠህን ጸጋ አይንሳህ፡፡

  ReplyDelete
  Replies
  1. " ካልደፈረሰ አይጠራም " ይሉ አይደል አበዉ

   Delete
 20. አሜን እግዚአብሀሔርበጎ ህሊናን ያድለን

  ReplyDelete
 21. ወየው ጉድ እንኳን ከራሱ ጎተራ ለሌላው ሊሞላ ከተመቸው ሌላውን እየደቀደቀ ለመረማመጃ ባልተጠቀመበት !

  ReplyDelete
 22. ሰላምታዬ ባለህበት ይድረስህ
  እኔ ግን ከዚህ ጹፍ የተማርኩት ይህንን ታሪክ ሆኖ የቀረውን ታሪካችንን እኛው እራሳችን መመልስ እንችላለን ነው ይህ ማለት እኔ ዛሬ እራሴ ከተለወጥኩ እና ለሌላው ሙሌት ከሆንኩ ሌላው ደግሞ ለእኔ በእጥፍ ይሞላል ይህንን የሚያደርገው ደግሞ በውስጡ ያለው ፍቅር ነው እና ይህንን ብንለምድ::

  ReplyDelete
 23. May God help us to fill the empty in each other! God bless you Dn. Daniel!

  ReplyDelete
 24. Your spirit is like a father who is out looking for his lost childeren;and congera you are finding us!you are my guru

  ReplyDelete
 25. ለሌላው ሕይወት የማይገደን ወይም ኃላፊነት የማይሰማን ከሆነ የተሻለው መንገድ ዕውቀት መቀነስ ነው፡፡ ለምን እንቀራረባለን? ለምን እንወያያለን? ለምንስ የማንሸከመውን የሰው ‹ውስጥ› እናውቃለን? ለምንስ የማንጋራውን የሰው ችግር እናውቃለን? ለምንስ የማንሞላውን ጉድለት እንሰማዋለን? ለምንስ የማናክመውን ቁስል እንመረምረዋለን? አንዳንድ ሰው አመል ሆኖበት ‹‹ይህ ነገር አይመለከተኝም፣ ይህ ነገር ልሸከመው አልችልም፣ ይህንን ነገር መስማት የለብኝም፣ ይህ ነገር የሰውየው የራሱ ብቻ ነው›› ማለት አይችልም፡፡ በሁሉም ነገር ውስጥ ይገባል፣ ሁሉም ነገር ይመለከተኛል ይላል፣ ሁሉንም ነገር በዝርዝር ያውቃል፣ የሁሉም ሰው ጓዳ ዘው ይላል፡፡ ነገር ግን ምንም ዓይነት ኃላፊነት አይወስድም፡፡ ከማወቅና ሲወራ አብሮ ከማውራት፣ ባስ ሲልም ‹ገመናን ከማጋለጥ› ያለፈ ሚናም የለውም፡፡ መሸሽ እንዲህ ካለው ሰው ነው፡፡

  ReplyDelete
 26. you are the especial one!

  ReplyDelete