Sunday, April 27, 2014

ዴር ሡልጣን፡- ዐሥር ነገሮች(ክፍል አራት)

5. መዝየም
ኢትዮጵያውያን አባቶችና ምእመናን በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም መንፈሳዊ ተጋድሎ ለመፈጸምና መንፈሳዊ ርስትን ለትውልድ ለማኖር ታላቅ መሥዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ ይህንን የዘመናት ተጋድሎ የሚያሳይ አንዳች ሙዝየም ግን የለንም፡፡ የገዳሞቻችንን ታሪክ፣ የተጻጻፍናቸውን ደብዳቤዎች፣ በየጊዜው ከሀገር ቤት የተላኩትን መጻሕፍትና ሌሎች ንዋያተ ቅድሳት፣ የዘመናቱን አሻራ የሚያሳዩ የሥዕልና የፎቶ ግራፍ መረጃዎች፣ ካርታዎች፣ ተጓዦችና ታሪክ ጸሐፊዎች የከተቧቸው ማስረጃዎች፣ በየዘመናቱ የተሰጡ ስጦታዎችን የሚያሳዩ መዛግብት፣ የተሾሙ ራይሶችንና ሊቃነ ጳጳሳትን የሚያሳዩ ዝርዝሮችና ፎቶዎች፣ የተሳላሚዎችን ሁኔታ የሚያሳዩ ፎቶዎችና መዛግብት የተከማቹበት፤ ከዚያም አልፎ የእናት ቤተ ክርስቲያንን ማንነት፣ ታሪክና ቅርሶች የሚያሳይ አንድ ታላቅ ሙዝየም በደብረ ገነት ኪዳነ ምሕረት ግቢ ውስጥ ወይም በአካባቢው ያስፈልገናል፡፡
ይህ ሙዝየም ሦስት ጥቅሞች ይኖሩታል፡፡ በአንድ በኩል ከሁለት ሺ ዓመታት በላይ ያስቆጠረውን የቅድስት ሀገር ርስታችንን ታሪክ በተጨባጭ የምናሳይበት፣ ከንግግር የዘለለ ማስረጃ እንዲኖረንና ያንንም ለዓለም ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንድናሳይ ያደርገናል፡፡ ከኢየሩሳሌም ከተማ አንዱ የቱሪስት መዳረሻ በመሆንም የኢትዮጵያውያንን የተጋድሎ ታሪክ ለጎብኝዎች እናሳይበታለን፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ኢየሩሳሌም የመላው ዓለም አማኞች መናኸሪያ በመሆኗ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ለማስተዋወቂያ ወሳኝ መድረክ ይሆናል፡፡ ቀደም ብለን እንዳየነው ኢትዮጵያንና ቤተ ክርስቲያንዋን በተለይ ለምዕራቡ ዓለም ያስተዋወቋት የኢየሩሳሌም(በተለይም የዴር ሡልጣን) ገዳማት አባቶች ነበሩ፡፡

ሦስተኛ ደግሞ ለገዳሙ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ይሆናል፡፡ የዓመቱን ፋሲካ ጠብቆ ጧፍ ከመሸጥ ይልቅ ራቅ አድርጎ አስቦ ታሪካችንን የሚያሳዩ ፖስት ካርዶችን፣ ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱና ስለ ኢየሩሳሌም ገዳማት የተጻፉ መጻሕፍትን፣ የጎብኝዎች መመሪያዎችን(Tourist Guide)፣ ኢትዮጵያዊ ትውፊት ያላቸው ቅዱሳት ሥዕላትን፣ የላንቲካ ዕቃዎችን(የሀገሪቱን ባሕል፣ የእምነት ሥርትዓቷንና ታሪኳን የሚያሳዩ ሰሐኖች፣ ቲሸርቶች፣ ኩባያዎች፣ የወግ ዕቃዎች፣  ጌጣ ጌጦች) ለቱሪስቶች በመሸጥ ከፍተኛ ገቢ ለማግኘት ያስችላል፡፡
እስካሁን በታየው ልማዳችን ዕቃ ቤት እንጂ ሙዝየም በብዛት የለንም፡፡ በሀገር ቤት እንኳን ያሉን ሙዝየሞች ከታሪካችንና ከቅርሳችን ጋር ሲወዳደሩ ዓባይን በጭልፋ የሚያስብሉ ዓይነት ናቸው፡፡ በኢየሩሳሌም የሚገኙ አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ሙዝየም ብቻ ሳይሆን የጥናትና ምርምር ተቋማት ጭምር እንዳሏቸው የኢየሩሳሌም የቱሪዝም መሥሪያ ቤት የሚያሳትማቸው የቱሪስት መርጃ መጻሕፍት ያሳያሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ የቅርብ ዘመን ታሪክ ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት እንኳን ቱሪስት እንደ ጎርፍ የሚፈስበት ሙዝየም አላቸው፡፡ ለተመራማሪዎችም ኢየሩሳሌምን የተመለከቱ መረጃዎችን በመሸጥ ገቢ ያገኛሉ፡፡
የአርመን ሙዝየም ሕንጻ
ወደ ኢየሩሳሌም ምእመናንን የሚያጓጉዙ ተቋማት ከገዳማቱ አስተዳደር ጋር በመመካከር ሊያከናውኗቸው ከሚገቡ ነገሮች አንዱ የሙዝየሙ ጉዳይ ነው፡፡ ‹ታሪክ እንደ ነጋሪው ነው› በሚል ያረጀ ብሂል ስለ ራሳችን ታሪክ ለእኛ እንኳን የሚገርመንን ዓይነት ያልነበረ ታሪክ እንደነበረ እየተደረገ፣ የነበረውም እየተዘነጋ እየቀረበልን መሆኑን ካየን ለቱሪስቶችማ ምን ሊነገር እንደሚችል መገመት ነው፡፡
የፍጥሞ ደሴት ገዳም ሙዝየም
ይህንን ሙዝየም እንዴት ባለ መንገድ ልናቋቁመው፣ ልናካሂደው ምን ምን እንዲሠራ ልናደርገው እንደምንችል በሚገባ በዓይን ዓይቶ ለመረዳት በግሪክ ፍጥሞ ደሴት የሚገኘውን የቅዱስ ዮሐንስ ገዳም መጎብኘቱ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ያም ካልተቻለ በኢየሩሳሌም አሮጌው ከተማ የሚገኙትን የአርመንንና የግሪክን ፓትርያሪኬት ሙዝየሞች ማየቱ በቂ ሊሆን ይችላል፡፡
6. ሴሚናሪ
ምንም እንኳን የገዳማቱ መነኮሳት የቀድሞ አባቶች ገዳሙን የጠበቁት ተምረው አይደለም ቢሉም አባባሉም ስሕተት ነው፣ ትምህርትም የግድ ነው፡፡ የቀድሞ አባቶች አልተማሩም የሚለው ብሂል ከሁለት ነገሮች የሚመነጭ ነው፡፡ አንድ ካለማወቅ ሁለትም ከንቀት፡፡ የቀድሞ አባቶች ለትምህርት ታላቅ ቦታ እንደነበራቸው ባከማቿቸው መጻሕፍት ብቻ እንኳን ማወቅ ይቻላል፡፡ እንኳን የክርስትና መጻሕፍት የአይሁድ፣ የግሪክ፣ የሂንዱስታንና የእስልምና መጻሕፍትን ሳይቀር ወደ ግእዝ እየተረጎሙ አስቀምጠውልናል፡፡ ተተኪዎቻቸው እንደነ እርሱ ዕውቀት ወዳጆች መስለዋቸው፡፡ ታላቁ ንጉሥና የዴር ሡልጣን ገዳም ባለ ውለታ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ‹‹መጽሐፈ ብርሃን›› በተሰኘው መጽሐፉ ‹‹እስመ ጽሙዐን ለትምህርት ብሔረ ኢትዮጵያ ኄራን - ምርጦቹ የኢትዮጵያ ሰዎች ትምህርትን የተጠሙ ናቸው›› እንዳለው ኢትዮጵያውያን ትምህርትን የተጠሙና ለዕውቀት ማንኛውንም ዓይነት ዋጋ የሚከፍሉ ነበሩ፡፡
ዛሬ ባለው ዓለም ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ቅኔ፣ ቅዳሴ፣ ዝማሬ፣ ትርጓሜና አቋቋም እጅግ አስፈላጊዎች ቢሆኑም ብቻቸውን ግን ወንዝ ሊያሻግሩን አይችሉም፡፡ ዛሬ በልዩ ልዩ የሀገራችንና የዓለም ቋንቋዎች ማስተማርና መጻፍ የሚያስፈልግበት፣ ጥንታዊ ሀብታችንን በዘመናዊ መንገድ ማቅረብ የሚጠየቅበት፣ ሕዝቡን ለመድረስ ልዩ ልዩ ሚዲያዎችን መጠቀም የግድ የሚልበት፣ ከትውልዱ ጋር ለመግባባትና የትውልዱን ጥያቄ ለመመለስ ሁለገብ ዕውቀት የሚያሻበት፣ ዘመን ነው፡፡
የኢየሩሳሌም ገዳማት አባቶችና እናቶች ከላይ በተጠቀሱት ነገሮች የሠለጠኑ፣ በሚገባ የታጠቁና በሁለት በኩል የተሳሉ ሰይፎች እንዲሆኑ ግድ ይላቸዋል፡፡ አንድም ‹‹መልክ ከእግዚአብሔር ሞያ ከጎረቤት›› ነውና ከጎረቤቶቻቸው ልምድ ለመቅሰም ስለሚችሉ፤ አንድም የትምህርት መርጃዎችን ከልዩ ልዩ ተቋማት ለማግኘት ቀላል ስለሆነ፤ አንድም በአንድ አካባቢ መኖራቸው በፈረቃ ለመማር ስለሚያስችላቸው፤ አንድም ልዩ ልዩ ቋንቋዎችን ለመማር ኢየሩሳሌም አመቺ በመሆኗ፡፡ ሌላው ቀርቶ በሀገር ቤት የሚገኙ መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶቻችንንም ከኢየሩሳሌም ትምህርት ቤት ጋር በማቀናጀት የተሻሉ ለሚባሉ ተማሪዎች ስኮላርሺፕ መስጠት ይቻላል፡፡
ዛሬ ዛሬ ከፍ አድርጎ ማሰብ እየጠፋ ነው መሰል የአባቶቻችን ሃሳብ አሜሪካና አውሮፓ መሄድ፣ ከግሪክ ንዋያተ ቅድሳት ማምጣት፣ ቤት መሥራት፣ ዘር መዝራት እየሆነ ነው፡፡ ነገ ቤተ ክርስቲያኒቱ ትፈልገኛለች፣ ነገ ወደ ኢትዮጵያ ኮሌጆች ሄጄ አስተምራለሁ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን እተረጉማለሁ፣ ሕዝቡን በወንጌል እደርሳለሁ፤ የመነኮስኩበትን ገዳም ኑሮና አሠራር አሻሽላለሁ፣ ቤተ ክርስቲያኔን በዓለም መድረክ አስጠራለሁ፣ ብሎ ከፍ አድርጎ የሚያስብ እያጣን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያናችን ጉዳት ነው፡፡
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ የኢየሩሳሌም መነኮሳት የነበራቸውን ቦታ ባለፈው ጊዜ በመጠኑ ጠቅሰነዋል፡፡ የኢትተጵያ ታላላቅ ገዳማት አባቶች አብዛኞቹ ኢየሩሳሌም መጥተዋል፡፡ እዚህ ያዩትንና የሰሙትን ይዘው በሀገራቸው ተግብረውታል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትንና ንዋያተ ቅድሳትን ወደ ሀገር አምጥተዋል፡፡ ሌላው ቢቀር አፈሩንና የዮርዳኖስን ጠበል እየያዙ በመምጣት ከገዳሞቻቸው አፈርና ጠበል ጋር አዋሕደውታል፡፡ እንደ ቅዱስ ላሊበላ ያሉትም ምድራዊትና ሰማያዊት ኢየሩሳሌምን ከተመለከቱ በኋላ ‹ከመዝ ግበር› በተባሉት መሠረት የኢየሩሳሌምን አምሳል በሀገራቸው ሠርተዋል፡፡
ዛሬም ቤተ ክርስቲያን ከኢየሩሳሌም መነኮሳትና መነኮሳዪያት ብዙ ትጠብቃለች፡፡ በዕውቀት የበሰሉ፣ በቋንቋ የተካኑ፣ ዓለም ዐቀፋዊ ልምድ ያላቸው፣ በሁለት በኩል የተሳሉ ሆነው እንዲያገለግሏት፡፡ ለዚህ ደግሞ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሴሚናሪ ያስፈልጋል፡፡ የተቋሙን አመሠራረትና አሠራር ለመረዳት ከሌሎቹ ልምድ መቅሰም ነው፡፡ ወጭውን ለመሸፈን ደግሞ ምእመናን አንድም ሁለትም ተማሪ ስኮላርሺፕ እንዲሰጡ ማስረዳት ነው፡፡ ዛሬ ሰው ያጣንበት ዘመን ስለሆነ ሰው ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ለመርዳት ምእመናን ዝግጁ ናቸው፡፡ ብቻ የቆረጠ፣ የገባውና፣ ዓላማ ያለው ሰው ይኑረን እንጂ፡፡
አሁን አሁን በዓለም ዐቀፍ መድረኮች ቤተ ክርስቲያንን ወክሎ በብቃት ሊሳተፍ የሚችል ሰው እያጣን ነው፡፡ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል የእምነት ውይይት (Inter - church dialogue) ይደረጋል፤ በልዩ ልዩ እምነቶች መካከልም ውይይት ይደረጋል(Inter - faith dialogue)፣ የአፍሪካና የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ይደረጋል፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ጉባኤ ይደረጋል፤ በሌሎች የዓለም መድረኮችም የሃይማኖት አባቶች ይጋበዛሉ፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን በመተርጎም ሥራም ከግሪክ፣ ከዕብራይስጥ፣ ከላቲንና ዐረብ ጋር ማነጻጸር ይጠይቃል፤ ለዚህ ሁሉ ትምህርትና ሥልጠና ወሳኝ ነው፡፡ ለዚህ ነው ኢየሩሳሌም ላይ አንድ ደረጃውን የጠበቀ፣ ሰው ሊያፈራ የሚችል፣ ሴሚናሪ ይኑረን የምለው፡፡
(ይቀጥላል) 
ኢየሩሳሌም

16 comments:

 1. Thanks Dani? Minewu ye Eyerusalem Neger absekesekehsa???? Lezih hulu lalkewu neger meftihew mejemeria kewust 1 enhun:: Tenkara sinodos(lehaymanotu erasun asalfo lemestet erasun zigju yaderege "Abat".....) yasfelgal:: Papasat be federal yemidebedebubat bete-chrstian alfa hida ante yemtlewun neger ayidelem mesrat lemasebm tchegeralech:: lemanignawum Ante Egziyabher yaqebelehn kemenager(kemetsaf) atbozn. yemisema joro yalewu yisma lib yalewu yastewul:: God bless you bro!

  ReplyDelete
 2. ብቻ የቆረጠ፣ የገባውና፣ ዓላማ ያለው ሰው ይኑረን !!!

  EGZIABHER asteway libona yisten!!!

  Dani, egziabher yabertah!!!

  ReplyDelete
 3. አንተ ትጽፋለህ እኛ እንመገባለን የተትረፈረ በረከት ምን ልበል ቃላት ጠፋብኝ አጠረኝ እንዲሁ ብቻ እግዚአብሔር ይጠብቅህ ወላዲትአምላክ አትለይህ የተደበቀ ገድላቸውን እንድናውቅ ያደረክላቸው (አራቱ ኃያላን) የቅዱሳን ፀሎት አይለይህ፤

  ReplyDelete
 4. ከኢየሩሳሌም ከተማ አንዱ የቱሪስት መዳረሻ በመሆንም የኢትዮጵያውያንን የተጋድሎ ታሪክ ለጎብኝዎች እናሳይበታለን፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ኢየሩሳሌም የመላው ዓለም አማኞች መናኸሪያ በመሆኗ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ለማስተዋወቂያ ወሳኝ መድረክ ይሆናል፡፡እንዴት ደስ ይላል!

  ReplyDelete
 5. Good job Dn. Daniel K

  ReplyDelete
 6. We need a leader who can organize and work hard all those things happen.

  ReplyDelete
 7. ዳኔ አንኳር አንኳሩን እየተናገርከው ነው፤ ሐበሻ ድሐረ ገጽ ላይ የጻፎ አባት ግን በቅን መንፈስ ይሕን ኦንዴያነቡት እማጸናለሁ ። አይኔን ግንባር ያረገው ካልተባለ በስተቀር የገዳሙ እሙሆየች የኑሮ ሁኔታ በሁሉም መልኩ ቅድሚያና ቦታ ሊሰጠው ይገባል። ሕንጻ ቤፈርስ ታሪክ ተረካቤ አባቶችና ምእመን ይሰሩታል ፤ ነፍስ ሲኦል ስትገባ ማን ያወጣታል??? እኔ ባልተገባ በኯልታፋ አንደበቴ የምለውን ብያለሁ ። ንሰሐ ነውና ሊሎቻችሑም ብታክሉበት መልካም ነው ። ዝናብ ከላይ ወደታች ሲዘንብ መልካም ነው ፣ከታቾ ወደላይ ሲሆን ግን ይፍቱኝ ይባሩክኝ ግድ ነው። ሐቁ እንዳለ ሁኖ ስለ ድፍረቴ ይቅርታ።

  ReplyDelete
 8. ዛሬ ዛሬ ከፍ አድርጎ ማሰብ እየጠፋ ነው መሰል የአባቶቻችን ሃሳብ አሜሪካና አውሮፓ መሄድ፣ ከግሪክ ንዋያተ ቅድሳት ማምጣት፣ ቤት መሥራት፣ ዘር መዝራት እየሆነ ነው፡፡ ነገ ቤተ ክርስቲያኒቱ ትፈልገኛለች፣ ነገ ወደ ኢትዮጵያ ኮሌጆች ሄጄ አስተምራለሁ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን እተረጉማለሁ፣ ሕዝቡን በወንጌል እደርሳለሁ፤ የመነኮስኩበትን ገዳም ኑሮና አሠራር አሻሽላለሁ፣ ቤተ ክርስቲያኔን በዓለም መድረክ አስጠራለሁ፣ ብሎ ከፍ አድርጎ የሚያስብ እያጣን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያናችን ጉዳት ነው፡፡

  ReplyDelete
 9. Excellent suggestions! However, the implementation of these suggestions needs good leadership and committed leaders. Do we have church leaders who can think at this level? Or can they allow the young and educated leaders to work on these? I would say we have more blockers than facilitators, and more intelligent followers than leaders. While they bite and beat each other years, decades and centuries pass. You have said what should be. Thanks

  ReplyDelete
 10. ዋናው መሠረታዊው ችግር እኮ ይህ ነው፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ የሕገ ወንጌልን አስተምህሮ በሕገ ልቡና አስተዳደር ነው እየመራችው ያለችው፡፡ ከአብነት ትምህርት ቤቶቻችን ጥሩ ካህን ይወጣል፤ የትምህርቱ ይዘት ይህ ነውና፡፡ ከአብነት ትምህርት ቤቶች ጥሩ አስተዳዳሪ ወይም ሥራ አስኪያጅ መጠበቅ ግን ስንዴ ዘርቶ የወይን ምርትን እንደመጠበቅ ነው፡፡ ይህንን ስል ግን እነዚህ ክህነት ብቻ የተማሩ አያስተዳድሩ እያልኩ አይደለም፡፡ የሚጎድላቸውን ክህሎቶች ማሟላት ይጠበቅባቸዋል ለማለት ነው፡፡ አሁን ያለው ያለው ሁኔታ ግን ምዕመኑ ከካህናቱ እጅግ የተሻለ ማሰብ የቻለበት ነው፡፡ ለዚህም ነው አንዳንድ ምእመናን እነርሱ ይቀድሱ፤ እኛ ራሳችንን በራሳችን እናስተዳድር ማለት የጀመሩት፡፡ ለዚህ እኮ ነው ምእመናን ራሳቸውን በማህበር በማደራጀት ገንዘብ እያዋጡ በተናጥል መንቀሳቀስ የጀመሩት፡፡ ዋናው ችግር የአስተዳዳሪዎቻችን የእውቀት የክህሎትና የልምድ ማጣት ነው፡፡ በልመና ያደገ ልጅ ለሚገጥመው ችግር ሁሉ የሚጠቀመው መፍትሔ ያው መለመን ነው፡፡ አንተን ግን እግዚአብሔር ይርዳህ!

  ReplyDelete
 11. ከወ/ት ታህሳስ አብቧል
  ለተከበርከው ውድ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት
  እንደሚታወቀው መልካም ነገርና ሃሳብ ሁሉ ከመንፈስ ቅዱስ ስለሆነ በዚህ ዘመን ይህንን የተቀደሰና ቅንነት የተሞላውን ሃሳብ ያነሳሳህን እግዚያብሔርን ከሁሉም በፊት አመሰግናለሁ። ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም። ሁላችንም ያቅማችንንና የምንፈልገውን ያህል አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠባቅብናል። በዋንኛነት ምንም የማይቸግረን “ቅን” ልቦና ይኑረን።
  ወንድማችን ዳንኤል በአቀረበው ሃሳብ ላይ ተጨማሪ ሃሳቦችን ማዋጣትና ማዳበር ያስፈልጋል። በመቀጠልም ወደ ተግባር ለመግባት ይረዳን ዘንድ በትጋት መጸለይ። ሁላችንም እንደምንስማማው ለእግዚያብሔር ምንም የሚሳነው ነገር የለም። እኛ የማናውቃቸው ነገር ግን እግዚያብሔር የሚያውቃችው እጅግ ብዙ መልካም መሪዎች/ሰዎች አሉ። ለሁሉም ሰው የተሰጠው ጸጋና መክሊት አለው። በተሰጠን ጸጋና መክሊት እየሰራንበት መሆኑን እለት ተእለት እራሳችንን መጠቅ ይገባናል። የእጃችን 5 ጣቶች በመጠን ፣ በቅርጽና በስያሜም እንኳን ቢለያዩ በህብረት ሆነው ስራ ሰርተው ምግባችንን ወደ አፋችን እያቀበሉ/እያጎረሱ ያኖሩናል፡፡ ሁላችንም በተሰማራንበት መስክ፣ ባለን አቅምና እውቀት፣ እንዲሁም በምንችለው ነገር ሁሉ ለመርዳት መዘጋጀት ይጠበቅብናል። ሁሉን በልግስና መስጠት የሚችለው አማላካችን እግዚያብሔር ቅን ልቦናን ይስጠን።
  ወንድሜ ዳንኤል ” ሰው ያስባል እግዚያብሔር ይፈጽማል “ በሚለው አባባላችን መሰረት በርታ። በዘወትር ጸሎቴ አስብሃለሁ። ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሲጀመር በምችለው ለመሳተፍና ለመርዳት በዚህ አጋጣሚ ቃል እገባለሁ።
  እግዚያብሔር ይርዳን።

  ReplyDelete
 12. ዛሬም ቤተ ክርስቲያን ከኢየሩሳሌም መነኮሳትና መነኮሳዪያት ብዙ ትጠብቃለች፡፡ በዕውቀት የበሰሉ፣ በቋንቋ የተካኑ፣ ዓለም ዐቀፋዊ ልምድ ያላቸው፣ በሁለት በኩል የተሳሉ ሆነው እንዲያገለግሏት፡፡ ለዚህ ደግሞ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሴሚናሪ ያስፈልጋል፡፡ የተቋሙን አመሠራረትና አሠራር ለመረዳት ከሌሎቹ ልምድ መቅሰም ነው፡፡ ወጭውን ለመሸፈን ደግሞ ምእመናን አንድም ሁለትም ተማሪ ስኮላርሺፕ እንዲሰጡ ማስረዳት ነው፡፡ ዛሬ ሰው ያጣንበት ዘመን ስለሆነ ሰው ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ለመርዳት ምእመናን ዝግጁ ናቸው፡፡ ብቻ የቆረጠ፣ የገባውና፣ ዓላማ ያለው ሰው ይኑረን እንጂ፡፡ አባባልህ ተመችቶኛል

  ReplyDelete
 13. ዲ/ን ዳንኤል
  በዚህ ሁሉ ጥረትህ እና ድካምህ ውስጥ የእግዚአብሔር እርዳታ እንዳልተለየህ አምናለሁ፡፡ ሰው ምንም እንኳን የድካሙን ፍሬ ከሰው ባይጠብቅም እንደቤተክርስቲያን ግን ይህን ምልከታ እና ገንቢ ሀሳብ ተመልክቶ ለተሸለ ነገ ለመጠቀም የተሰናዳ አካል አለ ወይ ስል ድካምህ ከንቱ እንዳይቀር እሰጋለሁ፡፡ እርግጥ ነው በመቁረጥ ተስፋ ለማስቆረጥ አይደለም፡፡ የአንተ ድርሻ ደግሞ ማጥናት ፤መመራመር፤ግኝት እና መፍትሔ ማቅረብ ነው፡፡ ይህን ካደረግህ ድርሻህን ተወጥተሀል፡፡ የችግሩን አጣዳፊነትና የጉዳዩን ክብደት በመገንዘብ የሚመለከተው የጠቅላይ ቤተ ክህነት አካል ጉዳዩን ከተገነዘቡት የቤ/ክ አካላት ጋር በእኩል ገጽ ላይ ይገኝ ይሆንን ብዬ ሳስብ ያስፈራኛል፡፡ ለሁሉም መድኃኒዓለም አይለየን፤ ድንግል ማርያም ትከተለን፡፡ ቃለ ህይወት ያሰማልን፡፡ቀጣዩንም እንጠብቃለን፡

  ReplyDelete
 14. መምህር የነገርከን የጻፍክልን ነገሮች በጣም አስፈላጊ ናቸው ግን እንዴት ይህንን ሊሰራ የሚችለው ክፍል ይንን ነገር ቢያውቁ መልካም ነው

  ReplyDelete
 15. መምህር ስለ ኢየሩሳሌም ያነሳሀቸው ሀሳቦች መልካም እና ጠቃሚ ናቸው ይህንን የታሪክ አደራ መቼም ለአለው ትውልድ ነው እናም ታዲያ አንተ ስለዚህ ጉዳይ እራስክ ይዘከው በተለያየ ቦታ ያሉትን ሰዎች እና የሚመለከተውን ክፍል በማነጋገር አንተ ብትይዘው መልካም ነው እኛ በሙሉ ቃል ከጎንህ እንሁንና በዬ አስባለው:: አለበለዚያ እስኪ ተፈጻሚነቱ ምን ሊሆን ይችላል ብለህ ታስባለህ?
  ህይወት

  ReplyDelete
 16. hulem bastemarinetih misgana yigebahal.

  ReplyDelete