5. መዝየም
ኢትዮጵያውያን አባቶችና ምእመናን በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም መንፈሳዊ ተጋድሎ
ለመፈጸምና መንፈሳዊ ርስትን ለትውልድ ለማኖር ታላቅ መሥዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ ይህንን የዘመናት ተጋድሎ የሚያሳይ አንዳች
ሙዝየም ግን የለንም፡፡ የገዳሞቻችንን ታሪክ፣ የተጻጻፍናቸውን ደብዳቤዎች፣ በየጊዜው ከሀገር ቤት የተላኩትን መጻሕፍትና ሌሎች
ንዋያተ ቅድሳት፣ የዘመናቱን አሻራ የሚያሳዩ የሥዕልና የፎቶ ግራፍ መረጃዎች፣ ካርታዎች፣ ተጓዦችና ታሪክ ጸሐፊዎች የከተቧቸው
ማስረጃዎች፣ በየዘመናቱ የተሰጡ ስጦታዎችን የሚያሳዩ መዛግብት፣ የተሾሙ ራይሶችንና ሊቃነ ጳጳሳትን የሚያሳዩ ዝርዝሮችና
ፎቶዎች፣ የተሳላሚዎችን ሁኔታ የሚያሳዩ ፎቶዎችና መዛግብት የተከማቹበት፤ ከዚያም አልፎ የእናት ቤተ ክርስቲያንን ማንነት፣
ታሪክና ቅርሶች የሚያሳይ አንድ ታላቅ ሙዝየም በደብረ ገነት ኪዳነ ምሕረት ግቢ ውስጥ ወይም በአካባቢው ያስፈልገናል፡፡
ይህ ሙዝየም ሦስት ጥቅሞች ይኖሩታል፡፡ በአንድ በኩል ከሁለት ሺ ዓመታት በላይ
ያስቆጠረውን የቅድስት ሀገር ርስታችንን ታሪክ በተጨባጭ የምናሳይበት፣ ከንግግር የዘለለ ማስረጃ እንዲኖረንና ያንንም ለዓለም
ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንድናሳይ ያደርገናል፡፡ ከኢየሩሳሌም ከተማ አንዱ የቱሪስት መዳረሻ በመሆንም የኢትዮጵያውያንን
የተጋድሎ ታሪክ ለጎብኝዎች እናሳይበታለን፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ኢየሩሳሌም የመላው ዓለም አማኞች መናኸሪያ በመሆኗ
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ለማስተዋወቂያ ወሳኝ መድረክ ይሆናል፡፡ ቀደም ብለን እንዳየነው ኢትዮጵያንና ቤተ ክርስቲያንዋን
በተለይ ለምዕራቡ ዓለም ያስተዋወቋት የኢየሩሳሌም(በተለይም የዴር ሡልጣን) ገዳማት አባቶች ነበሩ፡፡