click here for pdf
በተፈጥሮ ካልተገኙና ሰው ልጅ ከፈጠራቸው ከማይንቀሳቀሱ የሥልጣኔ
ውጤቶች አንዱ ከተማ ነው፡፡ ከተማ የአንድ ሕዝብ ሥልጣኔ የሚታይበትና የሚቀላጠፍበት ማዕከል ነው፡፡ በዚህም የተነሣ የሰው
ልጅን ታሪካዊ ሂደት በመመዝገብና የደረሰበትንም ሥልጣኔ በማሳየት ረገድ የከተማን ያህል የተሻለ ቦታ የለም፡፡ የጥንታዊ ሰዎችን
ሥልጣኔና ታሪክ የሚያጠኑ ባለሞያዎች የጉዞውን ሂደት የሚገልጡ መረጃዎችን የሚያገኙት በቁፋሮ ከሚገኙ ጥንታውያን ከተሞች ነው፡፡
በእነዚህ ጥንታውያን ከተሞች የሰው አነዋወር፣ ታሪክ፣ የመንግሥት አሠራር፣ የንግድና የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ ወግና ሥርዓት፣ እምነትና
ባሕል በተሰናሰለና ሥርዓት በጠበቀ መንገድ ይገኝባቸዋል፡፡
በአብዛኛው የገጠሩ ማኅበረሰብ ባልተሰባሰበ፣ አንድ ወገን በሆነ፣
ግልጽ የአኗኗር መርሕ፣ አስተዳደራዊ መዋቅር እምብዛም ባልተዘረጋበት መንገድ የሚኖር ነው፡፡ የከተማ ማኅበረሰብ ግን በተወሰነ
ቦታ፣ ከተለያየ ማኅበረሰብ ተውጣጥቶ፣ በአንድ ውሱን ሕግ እየተዳደረ፣ ለክዋኔዎች ቦታ ወስኖ(ለንግድ፣ ለአምልኮ፣ ለመንግሥት
አስተዳደር፣ ለመኖሪያ፣ ወዘተ) የሚኖር በመሆኑ የሥልጣኔ መገለጫዎች በከተሞች የሚገኙትን ያህል በገጠር አናገኛቸውም፡፡
ሐውልቶች፣ አደባባዮች፣ አብያተ መንግሥት፣ ሳንቲሞች፣ የኪነ ጥበብ ሕንጻዎች፣ የተደራጁ ገበያዎች፣ የውኃ መሥመሮች፣ የከተማ
መከለያ ግንቦች፣ የእምነት ማዕከሎች በከፍተኛ የሥልጣኔ ደረጃ ተሠርተው የምናገኛቸው በከተሞች አካባቢ ነው፡፡