በአንድ ጫካ ውስጥ አንድ ከሺ ዓመታት በላይ እድሜ የጠገበ ዋርካ ነበረ፡፡ ዋርካው
እጅግ ሰፊ፣ ውስብስብና ታላቅ ነው፡፡ በላዩ ላይ አዕዋፍ፣ በሥሩም እንስሳት ይጠለሉ ነበር፡፡ ከፊሉ ፍሬውን ከፊሉም ቅጠሉን
ይመገባሉ፡፡ ሌሎቹም ግንዱንና ሥሩን ፍቀው ይበላሉ፡፡ አንዳቸው ለሌላቸው እንስሳትና አዕዋፍ የጠቀሙበት፣ አንዳቸውም አንዳቸውን
የበሉበት ዘመን ነበር፡፡ አንዳቸው ከአንዳቸው ጋር የሚጋቡበት፣ አንዳቸውም ከሌላቸው ጋር የሚዋጉበት ዘመን አለ፡፡ ፈረስና
አሞራ ተጋብቶ ክንፍ ያለው ፈረስ ተወልዶ ነበር አሉ፡፡ ታላላቆቹ እንስሳት በልተዋቸው ዘራቸው የጠፉ እንስሳትም አሉ፡፡
እነዚህ እንስሳት አለመግባባታቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡ አንዳንዶቹ ወፍነት፣
አንበሳነት፣ ዝሆንነት፣ ድመትነት የሚባል ማንነት እንጂ እንስሳነት የሚባል ማንነት የለም ይላሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ እንስሳነት
የሚባል ማንነት እንጂ ወፍነት ወይም በግነት፣ ፍየልነት ወይም ጦጣነት የሚባል ማንነት የለም ብለዋል፡፡ ከዚህ የተረፉት ደግሞ
ሁለቱም አለ ይላሉ፡፤ እስካሁን ግን በአንዱም አልተስማሙም፡፡