በድምጽና
ምስል ለመከታተል እዚህ ይጫኑ
አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር በዋናው በር በኩል ወደ አውራ ጎዳናው
ይወጣል፡፡ ጥቂት እንደተጓዘ ደግሞ እዚያ አካባቢ ቆመው አላፊ አግዳሚውን ከሚላከፉ ጎረምሶች ጋር ይጨቃጨቃል፡፡ ጭቅጭቁ በምን
እንደተጀመረ ማናችንም አላወቅንም፡፡ እነዚያ ጎረምሶች ግን በመምህሩ ላይ ‹ሙድ› ይዘውበታል፡፡ ‹እሺ - - ሊቁ› እያሉ
በስድብ ጠረባ ይረፈርፉታል፡፡ እርሱ ደግሞ ስድቡን አልቻለበትም፡፡ ‹‹ያልተማራችሁ፣ ማይሞች፣ ከስድብ በቀር ሌላ የማታውቁ፣
ደደቦች›› ይላል ሥሩ እስኪገታተር ድረስ በቁጣ፡፡ በትከሻው ያንጠለጠለው ቦርሳ ይወዘወዛል፣ መነጽሩም ልውደቅ ልውደቅ ይላል፡፡
‹‹እሺ ሊቁ፣ ለምን ላፕቶፕሺን ከፍተሺ ዕውቀት አትጭኝብንም›› እያሉ ጎረምሶቹ
ይሳሳቁበታል፡፡እርሱ ይበግናል፡፡ ‹ኤፍ ብቻ ነው እንዴ ቦርሳሽ ውስጥ የያዝሺው፤ በናትሺ አንድ አምስት ኤ የለሽም››
ይሉታል፡፡ እርሱ ይንዘፈዘፋል፡፡ ‹‹አንድ ሁለት ኤ ብትሰጭን ቸብ አርገን በርጫ እንገዛበት ነበር›› ይሉታል፡፡ ሰው
እየተሰበሰበ፣ እየከበበው ይሄድና የጎረምሶቹን ስድብ እንደመዝናኛ ቆጥሮት አብሯቸው ይሳሳቃል፡፡ እርሱን ኮሜዲ ፊልም እንደሚሠራ
ተዋናይ ቆጥረውት በነጻ ይኮመኩማሉ፡፡ ጎረምሶቹ አንድ ተረብ በወረወሩ ቁጥር ከብቦ የተሰበሰበው ‹አስገቡለት› እያለ እንደ
ጎጃም ልቅሶ ያጅባቸዋል፡፡