Wednesday, December 18, 2013

ምግብና ፖለቲካ

በየዓይነቱ የሚባል ምግብ መቼም ታውቃላችሁ፡፡ በጾም ጊዜ የሚዘወተር የሀገራችን ምግብ ነው፡፡ አንዳንድ ቦታ ሦስት ዓይነት ሲኖረው አንዳንድ ቦታ ደግሞ ሠላሳ ዓይነት አለው፡፡ ‹በየዓይነቱ› የሚለውን የምግብ ቤቶች መዝገበ ቃላት ሲተረጉመው ‹‹አንድ ቀይ የምሥር ወይም የሽሮ ወጥ በእንጀራው መካከል ጎላ ብሎ ይቀመጥና እነ አልጫ ሽሮ፣ እነ አልጫ ምስር፣ እነ ምጣድ ሽሮ፣ እነ ቃሪያ፣ እነ ስልጆ፣ እነ ቲማቲም ፍትፍት፣ እነ አበሻ ጎመን፣ እነ የፈረንጅ ጎመን፣ እነ ሩዝ፣ እነ ሱፍ ፍትፍት፣ እነ ቀይ ሥር፣ እነ ድንች ወጥ፣ እነ ተልባ ፍትፍት በዙሪያው አጅበው ይሰለፋሉ›› ማለት ነው ይላል፡፡
በያይነቱ ሕግም አለው፡፡ ባይጻፍም እኛ ‹የበያይነቱ ሕግ› ብለነዋል፡፡ በበያይነቱ ሕግ መሠረት በመካከል የሚቀመጠው ዋናው ወጥ በቀላሉ የሚገኝና የሚሠራ መሆን አለበት፡፡ ለዚህም ነው ወይ ምስር ወይም ሽሮ የሚሆነው፡፡ ርካሽነቱ የጥሬ ዕቃው ብቻ ሳይሆን በአንድ ትልቅ ድስት ውስጥ በቀላሉ በብዛት ሊሠራ የሚችል ማለትም ነው፡፡ ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ምሥርና ሽሮ ወጥ፣ በልቅሶ ቤትም ዕድሮች በብዛት ይዘዋቸው የሚመጡት፡፡  አንድ ድንኳን ሙሉ ለቀስተኛና ዕድርተኛ ለማብላት እንደ ቀይ ምስርና ሽሮ ወጥ የሚበቃ አይገኝም፡፡

ሁለተኛው የበያይነቱ የሕግ ዐንቀጽ ደግሞ በወጥ ጭማሪ ጥያቄ ጊዜ ሊጨመር የሚችለው ዋናው ወጥ (ቀይ ሽሮው ወይም ምሥር ወጡ) ነው ይላል፡፡ እንጀራ ሲተርፍ ወይም እንጀራ ሲጨመር የወጥ ጭማሪ ቢጠየቅ ዋናውን ወጥ ማስጨመር ይቻላል፡፡
ሦስተኛው የበያይነቱ ሕግ በዋናው ወጥ ዙሪያ ለሚመጡት ዓይነቶች የቁጥር መጠን እንደሌላቸው ይደነግጋል፡፡ ሦስትም ሆኑ አሥራ ሦስት ችግር የለውም፡፡ ቁም ነገሩ ዋናውን ወጥ አጅበው በዙሪያው መኮልኮላቸው ነው፡፡ አራተኛውና እነዚህን በዙሪያው ያሉ ወጦችን የሚመለከተው ሕግ ደግሞ እነዚህ ወጦች ካለቁ አለቁ ነው ይላል፡፡ ዓይነት አይጨመርም፡፡ ዓይነት አለመጨመሩ ብቻ ሳይሆን በበያይነቱ ሕግ ዐንቀጽ አራት ንዑስ ዐንቀጽ አንድ መሠረት በምግብ ቤቱ ውስጥ ዋናው ወጥ አያልቅም እንጂ ዓይነት ሆነው የሚቀርቡት ወጦች ግን ሊያልቁ እንደሚችሉ ይደነግጋል፡፡ እንዲያውም በንዑስ ንዑስ ዐንቀጹ ላይ የዓይነቶቹ መጠን የምግቡ ሰዓት ሲጀመርና ሲያልቅ ሊለያይ እንደሚችልም ያስቀምጣል፡፡ ዋናው ወጥ ግን በብዛት ስለሚሠራ አያልቅም፡፡
አምስተኛው የበያይነቱ ሕግ ዐንቀጽ ዋናውን ወጥ አጅበው የሚቀርቡት ዓይነት ወጦች ‹ወጥ› ወይም ‹ዓይነት› የሚለውን ስም እስከያዙ ድረስ የፈለጉትን ዓይነት፣ መጠን፣ ቅርጽና ጣዕም ሊኖራቸው እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ ለምሳሌ ክክ ወጥ፣ ምጣድ ሽሮ፣ አልጫ ሽሮና አተር ፍትፍት በቅርጽና በስም ካልሆነ በቀር አንድ ዓይነት ናቸው፡፡ ዞሮ ዞሮ ያው ሽሮ ነው፡፡ ነገር ግን በየራሳቸው ስምና ቅርጽ ይዘው ‹ዓይነት› ሆነው መቅረብ እንደሚችሉ ‹የበያይነቱ ሕግ ይፈቅድላቸዋል፡፡
በበያይነቱ ሕግ ዐንቀጽ ስድስት መሠረት አንድ ምግብ ‹ዓይነት› ሆኖ የሚቀርበው በዋናነት ለመልኩና ቅርጹ እንጂ በውስጡ ላለው ይዘት እንዳልሆነ ይደነግጋል፡፡ ለዚህም ሳይሆን አይቀርም እነ አበሻ ጎመን፣ እነ ጥቅል ጎመንና እነ ኪያር እሳት ካደበናቸው የምግብ ይዘታቸው በሙሉ እንደሚጠፋ ቢታወቅም ቅሉ፣ ድብን ብለው በስለው ‹ዓይነት› ሆነው ለመቅረብ የቻሉት፡፡
በበያይነቱ ሕግ ዐንቀጽ ስድስት ንዑስ ዐንቀጽ ሦስት መሠረት ሁለት የበያይነቱ ወጦች የይዘትም ሆነ የቅርጽ ልዩነት ባይኖራቸውም ስማቸው ከተለያየ እንደ አንድ ወጥ ተመዝግበው መንቀሳቀስ ይችላሉ ይላል፡፡ አልጫ ምስርና ቀይ ምስር፣ አልጫ ድንችና ቀይ ድንች ቅርጻቸውም ሆነ ይዘታቸው አንድ ቢሆንም የስም ልዩነት ስላላቸው ግን ይኼው በዓይነትነት ተመዝግበው ቀጥለዋል፡፡
በበያይነቱ ውስጥ እንደ ቃሪያ የሚያቃጥሉ፣ እንደ ምስር የሚጎረብጡ፣ እንደ ተልባ ፍትፍት የሚለሰልሱ፣ እንደ ሩዝ የአበሻ ምግብ ውስጥ ለምን እንደመጡ የማይታወቁ፣ እንደ ቲማቲም ፍትፍት የንጽሕናቸው ጉዳይ ሆድ ሲያጮኽ የሚውል፣ እንደ ስልጆና እንደ አተር ፍትፍት በአንድ ጉርሻ የሚያልቁ ምግቦችም እንዲካተቱ ሕጉ ይፈቅድላቸዋል፡፡
በበያይነቱ ሕግ ዐንቀጽ ዐሥር መሠረት ዛሬ አንድ ዓይነት ሆኖ የቀረበ ወጥ ነገ ተለያይቶ ሁለት፣ ሁለት ሆኖ የነበረም እንድ ሆኖ ለመቅረብ እንደሚችል ይፈቅዳል፡፡ ለየብቻቸው ሲቀርቡ የነበሩት ቀሪያ፣ ቲማቲምና እንጀራ ከቅርብ ዘመናት ወዲህ የቲማቲም ፍትፍት ተብለው ኅብረት መሥርተው መጥተዋል፡፡ ‹ሽሮ ወጥ› ተብለው አንድ ላይ የነበሩት ‹ሽሮ ፈሰስ›ና ‹ሽሮ ተጋቢኖ› ሆነው በየራሳቸው መጥተዋል፡፡
ይህን የበያይነቱን ሕግ አይተን እስኪ የሀገራችን የፖለቲካ ሕግና ባህል እንገምግመው፡፡ ፖለቲካችን ከበያይነቷችን ወይም በያይነቷችን ከፖለቲካችን ተወስዶ ሊሆን ከቻለስ?
በበያይነቱ ሕግ አንድ ዋና ወጥ እንዳለው ሁሉ በሀገራችንም አንድ አውራ ፓርቲ አለ፡፡ ሌሎቹ በመጠናቸው አነስ አነስ ያሉ ወጦች ዋናውን ወጥ አጅበው እንደሚቀመጡ ሁሉ በሀገራችን ያሉት ከብሔረሰቦች ቁጥር የበለጡት ፓርቲዎችም ይህን አውራ ፓርቲ አጅበው የሚኖሩ ናቸው፡፡ ይህ በበያይነቱ የሚገኝ ዋናው ወጥ ይኼው በያይነቱ ከተፈጠረ ጀምሮ ምስር ዋና ሆኖ የመካከሉን ዋና ቦታ እንደያዘው አለ፤ አንድም ዓይነት ሆኖ የገባ ወጥ ቦታውን እንዳልወሰደው ሁሉ በሀገራችንም ይኼው ዋናውም ወጥ ሆነ ዓይነቶቹ ዛሬም በዚያው ቦታቸው ናቸው፡፡
በበያይነቱ ሕግ ዋናው ወጥ ይጨመራል እንጂ ዓይነት አይጨመርም፡፡ በሀገራችን ፖለቲካም አውራው እየጨመረም እየተጨመረም ይኼዳል እንጂ ዓይነቶቹ ካለቁ አለቁ ነው፡፡ ስንት ፓርቲ ዓይነት ሆኖ በሆነ የምርጫ ዘመን ከመጣ በኋላ በሌላ ጊዜ ‹ጨምሩ› ስንል ‹አልቋል፤ ከፈለጋችሁ ምስር ጨምሩ› ተብለናል፡፡  በበያይነቱ ወጥ ዋናው ወጥ በትልቁ ሰታቴ ነው የሚሠራው፤ እንዳያልቅ፡፡ በሀገራችንም ዋናው ፓርቲ በትልቁ ነው የተሠራው፡፡ ወደ ዋናው ወጥ ሰታቴ የማይገባ እህል፣ የማይጨመር ውኃ፣ የማይደረግ ቅመም የለም፡፡ ችግሩ አንዳንዱ በሚገባ ያልተቀመመ፣ አንዳንዱ ‹ኤክስፓየር› ያደረገ፣ አንዳንዱ ምን ሳይጠቅም እንዲሁ የገባ፣ አንዳንዱ እንደ ሽንኩርቱ ያረረ፣ እየሆነ ነው ችግሩ፡፡ ወጥ ሠሪዎቹም ዋናው ዓላማቸው ወጡ እንዲሰፋ፣ እንዲበዛ፤ ከዚያም አልፎ ሌሎቹ ዓይነቶች ሲያልቁ ዋናው ወጥ እንዳያልቅ ማድረግ ነውና ያገኙትን የእህል ዓይነት ሁሉ እያስገቡበት ተቸገርን፡፡
በልቅሶ ቤትም፣ በግብዣም፣ በድግስም፣ በቤታችንም፣ በየመሥሪያ ቤቱ ካፍቴሪያዎችም፣ በብዛትና በስፋት የምናገኘው ይኼንኑ ዋናውን ወጥ ሆነ፡፡ አንዳንዶች ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት ይህንን ዋናውን ወጥ መሥራት ቀላል፣ ብዙም ችሎታ የማይጠይቅ፣ ርካሽና በትልቅ ዕቃ የሚሠራ፣ ብዙም መሥዋዕትነት የማይጠይቅ ስለሆነ ነው ብለዋል፡፡
እንደ በያይነቱ ሁሉ የሀገራችን ፓርቲዎች የቁጥር መጠን የላቸውም፤ በብሔረሰቦች ቁጥር መጠን መስሎን ነበር፤ አሁንማ ከዚያም ቁጥር አለፈ፡፡ አንዳንዶቹ የበያይነቱ ወጦች በማንኪያ ተመጥነው የሚቀርቡት ከአንድ ጉራሽ እንደማያልፉ ሁሉ፣ አንዳንዶቹ ፓርቲዎች በዐሥር ሰው ይመሠረቱና ከአንድ ምርጫ ወይም ከአንድ ስብሰባ፣ አለፍ ካለም ከአንድ ሰላማዊ ሰልፍ አያልፉም፡፡ ቀይ ሽሮ፣ አልጫ ሽሮ፣ ሽሮ ፍትፍት፣ ክክ ወጥ፣ አተር ፍትፍት እየተባለ አንዱን ባቄላ ወይም አተር በዐሥር ዓይነት እንደሚያመጡት ሁሉ ከስማቸው በቀር የፕሮግራም፣ የግብ፣ የአደረጃጀትና የአካሄድ ልዩነት የሌላቸው ፓርቲዎች ሞልተውናል፡፡ ልዩነታቸው አንዱ አበበን ነጻ ሲያወጣ ሌላኛው ጫልቱን፣ ሌላኛው ደግሞ ኪሮስን የቀረውም ደንቦባን ነጻ ማውጣቱ ነው፡፡
በበያይነቱ ውስጥ እንደሆነው ሁሉ እንደ ቃሪያ አሠራራቸው የሚያቃጥል፣ እንደ ስልጆ የሚሰነፍጥ፣ እንደ ቀይ ሥር መልክ እንጂ  ይዘት የሌላቸው፣ እንደ ሩዝ እንዴት ፓርቲ ሊሆኑ እንደቻሉ ግራ የሚያጋቡ፣ እንደ ቲማቲም ፍትፍት ሆድ ማስጮህ እንጂ አእምሮ መገንባት የማይችሉ ፓርቲዎችም አሉን፡፡
በበያይነቱ ወጥ ውስጥ እንዳሉት የሐበሻ ጎመንና ጥቅል ጎመን፤ በፖለቲካው እሳት በመንተክተካቸው የተነሣ የምግብ ይዘታቸው የጠፋ፡፡ ቢበሏቸው የማይጠቅሙ፣ ቢተዋቸው የማይጎዱ ዓይነት ፓርቲዎችም አሉን፡፡ እንደ ቃሪያና ቲማቲም ለየብቻ ጀምረው እንደ ‹ቲማቲም ፍትፍት› አንድ ሆነው የመጡ፣ እንደ ‹ሽሮ ወጥ› እንደ ሆነው ጀምረው እንደ ሽሮ ፈስስና ሽሮ ተጋቢኖ ተለያይተው የቀጠሉ ፓርቲዎችም አሉን፡፡
በበያይነቱ ምግብ የምግብ ሰዓት ሲጀመር የነበሩት ዓይነቶች እያለቁ ሄደው በስተ መጨረሻ በያይነቱ ራሱ አልቆ ‹ምስር ወይም ሽሮ ነው ያለን› እንደሚባለው ሁሉ በሀገራችን ከሃያ ዓመት በፊት ምርጫና ዘመቻ ሲጀመር እንደ አሸን ፈልተው የነበሩት ‹በዴሕ› ና በ‹ዴድ› የሚጠሩ ፓርቲዎች አሁን የት እንደደረሱ የሚያውቅ የለም፡፡ ሁሉም ዓይነቶች አልቀው ዋናው ወጥ ብቻ ቀረ፡፡
እንግዲህ የኛ የፖለቲካ ሥርዓት በያይነቱ ምግባችንን ሳይመስል አይቀርም፡፡ ምናልባት ምግቡ ከፖለቲካው ይቀድማልና ፖለቲካው ከምግቡ አሠራሩን ቀድቶት እንደሆነ እስኪ እንመርምረው፡፡ ምናልባት በያይነቱን ብናስተካክለው ፖለቲካው ይስተካከል ይሆን?
ቸር ይግጠመን፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽት ላይ የወጣ ነው

37 comments:

 1. Thanks Daniel, always amazing and insightful writing.

  በበያይነቱ ሕግ ዋናው ወጥ ይጨመራል እንጂ ዓይነት አይጨመርም፡፡ በሀገራችን ፖለቲካም አውራው እየጨመረም እየተጨመረም ይኼዳል እንጂ ዓይነቶቹ ካለቁ አለቁ ነው፡፡ ስንት ፓርቲ ዓይነት ሆኖ በሆነ የምርጫ ዘመን ከመጣ በኋላ በሌላ ጊዜ ‹ጨምሩ› ስንል ‹አልቋል፤ ከፈለጋችሁ ምስር ጨምሩ› ተብለናል፡፡

  Yimechih

  ReplyDelete
 2. Thanks D/Daniel it is a nice view.God gives an eagle eye to you.

  ReplyDelete
 3. አንዳንዶቹ የበያይነቱ ወጦች በማንኪያ ተመጥነው የሚቀርቡት ከአንድ ጉራሽ እንደማያልፉ ሁሉ፣ አንዳንዶቹ ፓርቲዎች በዐሥር ሰው ይመሠረቱና ከአንድ ምርጫ ወይም ከአንድ ስብሰባ፣ አለፍ ካለም ከአንድ ሰላማዊ ሰልፍ አያልፉም፡፡

  ReplyDelete
 4. "በበያይነቱ ሕግ ዋናው ወጥ ይጨመራል እንጂ ዓይነት አይጨመርም፡፡ በሀገራችን ፖለቲካም አውራው እየጨመረም እየተጨመረም ይኼዳል እንጂ ዓይነቶቹ ካለቁ አለቁ ነው፡፡ ስንት ፓርቲ ዓይነት ሆኖ በሆነ የምርጫ ዘመን ከመጣ በኋላ በሌላ ጊዜ ‹ጨምሩ› ስንል ‹አልቋል፤ ከፈለጋችሁ ምስር ጨምሩ› ተብለናል፡፡ በበያይነቱ ወጥ ዋናው ወጥ በትልቁ ሰታቴ ነው የሚሠራው፤ እንዳያልቅ፡፡ በሀገራችንም ዋናው ፓርቲ በትልቁ ነው የተሠራው፡፡ ወደ ዋናው ወጥ ሰታቴ የማይገባ እህል፣ የማይጨመር ውኃ፣ የማይደረግ ቅመም የለም፡፡ ችግሩ አንዳንዱ በሚገባ ያልተቀመመ፣ አንዳንዱ ‹ኤክስፓየር› ያደረገ፣ አንዳንዱ ምን ሳይጠቅም እንዲሁ የገባ፣ አንዳንዱ እንደ ሽንኩርቱ ያረረ፣ እየሆነ ነው ችግሩ፡፡ ወጥ ሠሪዎቹም ዋናው ዓላማቸው ወጡ እንዲሰፋ፣ እንዲበዛ፤ ከዚያም አልፎ ሌሎቹ ዓይነቶች ሲያልቁ ዋናው ወጥ እንዳያልቅ ማድረግ ነውና ያገኙትን የእህል ዓይነት ሁሉ እያስገቡበት ተቸገርን፡፡"
  ልክ ብለሀል ዳኒ፥ በየአይነት ምግባችንና ፖለቲካችን ብዙ የሚያመሳስላቸው ነገር አለ። እንግዲህ አይነት ለማስጨመር ሲሹ በጭራሽ የሚባለው አንደኛው ምግብ አቅራቢው የዘረጋው ስርዓት (ህግጋቶቹ)፣ ሲቀጥል ደግሞ ተመጋቢው ምግብ አቅራቢው ከሚያቀርብለት ባለፈ በራሱ ፍላጎት ተመርቶ የመረጠውን አይመገብም። ሽሮ ወይንም ምስርን በዋናነት ስለቀረበለት እንዲሁ ተቀብሎ ሲመገብ ለምዶት ይኖራል እንጂ፣ ምስር የጨጓራ ጠሩ እንደሆነ እያወቀ ምስሩ ይቅር ሳይል በየአይነት የሚያዝና የሚመገብ ጥቂት አይደለም። የበየአይነትን ህግ ያወጣው ምግብ አቅራቢው ነው፥ እውነት ነው ምስርና ሽሮ በማህበራዊ ህይወታችንም ከተለያዩ ምክንያቶች አንፃር የተለመደ ነው (በተለይ በሀዘን ቤት)። ነገር ግን ከሀዘን ቤት ውጪ ላሉ ማህበራዊ መስተጋብሮች ላይ የበየአይነቱ ህግ በተወሰነ መልኩ ይቀየርና የምግብ አቅራቢው አውቅልሀለው ባይነትም ይቀርና፣ ተመጋቢው የራሱን ምርጫ መሰረት አድርጎ የመረጠውን፣ የሚወደውን፣ ይጠቅመኛል የሚለውን በማንሳት ይመገባል። “ብፌ” ይባላል፥ ይህ በሰፊው ሀገራችን ሲለመድ፥ ማንም ሰው የወደደውን ይመገባል፣ የሚስማማውን መርጦ ይመገባል። ዋና የሚባለው ምግብ እኛ የምንወደውና የምንመርጠው ይሆናል። ደጋሹ ለሁሉ እንዲበቃ አድርጎ ይስራው እንጂ፣ ዋናው የተመጋቢው ምርጫ ይሆናል።
  ፖለቲከኞቻችን ከምግብ ወስደውት ከሆነ ስርዓቱን ወደ “ብፌ” ዘወር እንዲሉ እመክራለሁ። የጣፈጠ እና የተስማማ ብቻ ወደሚበላበት

  ReplyDelete
 5. ምናልባት በያይነቱን ብናስተካክለው ፖለቲካው ይስተካከል ይሆን? I like the whole Idea.

  ReplyDelete
 6. Good article! and i like your blog background!

  ReplyDelete
 7. መልካም አስተውለሃል ወንድሜ። እግዚአብሔር ይጠብቅህ።

  ReplyDelete
 8. In this text:
  Number of በየዓይነቱ=2
  Number of በያይነቱ=27
  sum=29= ዋናው ወጥ


  ReplyDelete
 9. ዳኒ ቃለ ፖለቲካ ያሰማልን
  ግን በየአይነቱ ወይስ በያይነቱ
  አውራ ፓርቲ ወይስ አውራ ዶሮ እኛ ያለን

  ReplyDelete
 10. Woow excellent view


  በበያይነቱ ውስጥ እንደሆነው ሁሉ እንደ ቃሪያ አሠራራቸው የሚያቃጥል፣ እንደ ስልጆ የሚሰነፍጥ፣ እንደ ቀይ ሥር መልክ እንጂ ይዘት የሌላቸው፣ እንደ ሩዝ እንዴት ፓርቲ ሊሆኑ እንደቻሉ ግራ የሚያጋቡ፣ እንደ ቲማቲም ፍትፍት ሆድ ማስጮህ እንጂ አእምሮ መገንባት የማይችሉ ፓርቲዎችም አሉን፡፡

  እንግዲህ የኛ የፖለቲካ ሥርዓት በያይነቱ ምግባችንን ሳይመስል አይቀርም፡፡ ምናልባት ምግቡ ከፖለቲካው ይቀድማልና ፖለቲካው ከምግቡ አሠራሩን ቀድቶት እንደሆነ እስኪ እንመርምረው፡፡ ምናልባት በያይነቱን ብናስተካክለው ፖለቲካው ይስተካከል ይሆን?

  ReplyDelete
 11. ስንት ፓርቲ ዓይነት ሆኖ በሆነ የምርጫ ዘመን ከመጣ በኋላ በሌላ ጊዜ ‹ጨምሩ› ስንል ‹አልቋል፤ ከፈለጋችሁ ምስር ጨምሩ› ተብለናል.........ልዩነታቸው አንዱ አበበን ነጻ ሲያወጣ ሌላኛው ጫልቱን፣ ሌላኛው ደግሞ ኪሮስን የቀረውም ደንቦባን ነጻ ማውጣቱ ነው፡፡ እውነት ነው ላማንኛውም ካሁን ቡሃላ በየዓይነቱን ስበላ ይህን ፖለቲካ ማስታወሴ አይቀርም kb

  ReplyDelete
 12. ሌሎቹ በመጠናቸው አነስ አነስ ያሉ ወጦች ዋናውን ወጥ አጅበው እንደሚቀመጡ ሁሉ በሀገራችን ያሉት ከብሔረሰቦች ቁጥር የበለጡት ፓርቲዎችም ይህን አውራ ፓርቲ አጅበው የሚኖሩ ናቸው፡፡ ይህ በበያይነቱ የሚገኝ ዋናው ወጥ ይኼው በያይነቱ ከተፈጠረ ጀምሮ ምስር ዋና ሆኖ የመካከሉን ዋና ቦታ እንደያዘው አለ፤ አንድም ዓይነት ሆኖ የገባ ወጥ ቦታውን እንዳልወሰደው ሁሉ በሀገራችንም ይኼው ዋናውም ወጥ ሆነ ዓይነቶቹ ዛሬም በዚያው ቦታቸው ናቸው፡፡

  ReplyDelete
 13. ፣ እንደ ምስር የሚጎረብጡ ....
  ...ይህ በበያይነቱ የሚገኝ ዋናው ወጥ ይኼው በያይነቱ ከተፈጠረ ጀምሮ ምስር ዋና ሆኖ የመካከሉን ዋና ቦታ እንደያዘው አለ፤ አንድም ዓይነት ሆኖ የገባ ወጥ ቦታውን እንዳልወሰደው ሁሉ በሀገራችንም ይኼው ዋናውም ወጥ ሆነ ዓይነቶቹ ዛሬም በዚያው ቦታቸው ናቸው

  ReplyDelete
 14. Dear Dn Dani
  Previously this beyaynetu has been served only on fasting days but now it is only being served in non fasting days. In the same token our politics has been engulfing only those who do not have education or money but now the riches and so called educated are now being engulfed and directed by the main party. Great perspective and thanks

  ReplyDelete
 15. twe back, le Woyane yehe teshufe ashemude nwe. Woyanene BANDAWOCH bilhe Likachwen mengire nwe !!!
  Kifuwoch lagire ayasibu, lemanim gedyelelachwe. ye Fireon lejoche.
  Bizu lile nibire Tastawes endihone the former primenister Melse zenawe eyalagitubien sininadied, yas digmou simu balhulet misimer Patriyaric MR Paulose betam nibire metelawe Mote yam Mote, ahunem yemikilduben hulum yemotalu COMING soon very soon....

  ReplyDelete
 16. ሽሮ በየአይነት ትወዳልህ ማለት ነው?

  ReplyDelete
 17. ‹‹አንድ ቀይ የምሥር ወይም የሽሮ ወጥ በእንጀራው መካከል ጎላ ብሎ ይቀመጥና እነ አልጫ ሽሮ፣ እነ አልጫ ምስር፣ እነ ምጣድ ሽሮ፣ እነ ቃሪያ፣ እነ ስልጆ፣ እነ ቲማቲም ፍትፍት፣ እነ አበሻ ጎመን፣ እነ የፈረንጅ ጎመን፣ እነ ሩዝ፣ እነ ሱፍ ፍትፍት፣ እነ ቀይ ሥር፣ እነ ድንች ወጥ፣ እነ ተልባ ፍትፍት በዙሪያው አጅበው ይሰለፋሉ›› ማለት ነው ይላል፡፡

  ReplyDelete
 18. በያይነቱ ሕግም አለው፡፡ ባይጻፍም እኛ ‹የበያይነቱ ሕግ› ብለነዋል፡

  ReplyDelete
 19. really an insightful article. God bless you.

  ReplyDelete
 20. denk eyeta dani berta

  ReplyDelete
 21. ምናልባት በያይነቱን ብናስተካክለው ፖለቲካው ይስተካከል ይሆን? I

  ReplyDelete
 22. በበያይነቱ ወጥ ዋናው ወጥ በትልቁ ሰታቴ ነው የሚሠራው This is the main and core problem of Ethiopian politics.which mines as you know the main party always active and defend the other party to live as his ዋናውን ወጥ አጅበው እንደሚቀመጡ other wise if they are cross the border the main party has all authority that can say they are terrorist or give any plate . the opposite party are also a grate problem to plan and strategical problem to seat their vision there fore አንዳንዶቹ ፓርቲዎች በዐሥር ሰው ይመሠረቱና ከአንድ ምርጫ ወይም ከአንድ ስብሰባ፣ አለፍ ካለም ከአንድ ሰላማዊ ሰልፍ አያልፉም these is always confer table for the law that written in the heart of main party ዋናው ወጥ አያልቅም እንጂ ዓይነት ሆነው የሚቀርቡት ወጦች ግን ሊያልቁ እንደሚችሉ ይደነግጋል፡፡and stretch their hands in every aspect of the country either regional, political Juridical etc...and they call it them selves as AWRA PARTY Tank you God and His Mother bless you!!!

  ReplyDelete
 23. ዳኒ ችግር የለም ፣ የጾሙ ወራት እስኪፈጸም ብቻ ስለሆነ እንችለዋለን። ጾሙ ሲፈታ የሚያጠግበውን ቁርጥ እንበላለን። እንደምታውቀው አበሻ ሆዬ ሥጋ ካገኘ በየዓይነቱን ከነአካቴው አይሻውም። የዚህን ያህልም የታገስነው ጾም ወዳዶች በመሆናችን ነው።

  ReplyDelete
  Replies
  1. በውነት በውነት ምጡቅ ቅኔ ዘረፍክ !!!

   Delete
  2. great saying!!!!!!!!!!
   deep interpretation!!!!!!!!!!

   Delete
  3. አዎ
   እስከመቼ ድረስ ጸጉር ተበጥሮ
   መቀስ የት ይገኛል ቁርጥ ነው ዘንድሮ

   Delete
 24. ire tewu gomen betena.msr um ketekeka hod aynekam.ine yemiyasferagn timatimu new .

  ReplyDelete
 25. ከፈለጋችሁ ምስር ጨምሩ

  ReplyDelete
 26. ድንቅ ንጽጽር፡፡ ምናልባትም በተመሳሳይ የአመለካከት ጐዳና ላይ ያለ ህዝብ በሁሉም ዘርፍ አካሄዱ ተመሳሳስ መሆኑን ማረጋገጫ ሳንሆን አልቀረንም፡፡

  ReplyDelete