Monday, December 23, 2013

አምሳሉ፤ እንኳን ትሞት ትታመምም አይመስለኝ ነበር

 
ጌታቸው ኃይሌ
ኮሌጅቪል፤ ታኅሣሥ 12 ቀን፤ 2006 (12/21/2013)

ፕሮፌሰር አምሳሉ አክሊሉና እኔ አብሮ- አደግ አብሮ- ጎልመስ፥ አብሮ -አረግ ነን። 1947 . . የእንግሊዝ ፊደል አብረን ከቆጠርንበት ጊዜ አንሥቶ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ አንድ ዓይነት ትምህርት ለማስተማር እስከተቀጠርንበት ጊዜ ድረስ በቦታ እንኳን ሳንለያይ አብረን ነበርን። በዚህ አምላክ በመረቀልን ረጅም ጊዜ አንድ ቀንም አንዳችን ሌላውን ቅር የሚያሰኝ ቃል ከአፋችን መውጣቱ ትዝ አይለኝም። የተለያየ ጠባይ ያላቸው ሰዎች መፋቀር፥ መተሳሰብ፥ መረዳዳት፥ እንደሚችሉ የአምሳሉና የእኔ ወዳጅነት ምሳሌ ሊሆን ይችላል። ለጻፍኩት የሕይወት ታሪኬ ርእሱን የአምሳሉና የጌታቸው ታርክ ብለው የተገባ መሆኑን ያነበበው ሁሉ ሊገምት ይችላል። ረጅሙን በወንድማማችነት አብሮ የመኖር ሕይወታችንን ለማስቀረት ደርግና ሞት ሸመቁበት።


አምሳሉን በዚህ ረጅም ዘመን እንደማውቀው፥ ሞት ቀርቶ ሕመም ይደፍረዋል ብየ አልገመትኩም፤ እሱም አይገምትም ነበር። ሙሉ ጤነኛ ነበር፤ እኔ ሐኪም ቤት ስመላለስ፥ እሱ ሐኪም ቤቱን የሚያውቀው እንደኔ ያሉ ሕመምተኞችን ለመጠየቅ ሲሄድ ነበር። አምሳሉ ጤነኛ ብቻ ሳይሆን ሕይወቱ በተግባር የተመላ ነበር። ሥራ ሲወጥን፥ ሥራ  ሲያጣድፍ፥ ሥራ ሲፈጽም፥ እንቅልፍ አልነበረውም። ሲጫወት፥ ሲያጫውት ሁሉን ያስደስት ነበረ። በዚህ ሁሉ ምክንያት መቶ ዓመት ሳይሞላው ሊሞት ቀርቶ "ሆዴን ጎረበጠኝ" የሚል እንኳን አይመስለኝም ነበር። ግን በኢሳይያስ አፍ፥ "እስመ፡ ኢኮነ፡ ምክርየ፡ ከመ፡ ምክርክሙ፤ ወኢኮነ፡ ፍኖትየ፡ ከመ፡ ፍኖትክሙ።" (ሐሳቤ እንደ ሐሳባችሁ አይደለም፤ መንገዴም እንደመንገዳችሁ አይደለም።) የሚለው አምላክ ወንድሜን አምሳሉን፥ እሱ ባሰበው፥ እኛ ባላሰብንበት ዕለት ወሰደው። ሳንሰነባበት ተለያየን። ጽሎቴ ዕለተ ዕረፍቱን የመረጠለት አምላክ ለነፍሱ ከወዳጆቹ ማህል የተደላደለ ቦታ እንዲመርጥላት ነው።

አምሳሉ ሥራ የሚፈጸምለት ታታሪ ሠራተኛ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ብልህና አስተዋይ በመሆኑ ጭምር ነው። በብልህነቱ፥ በዐዋቂነቱ እቀናበት እንደነበረ ከእሱ በቀር ማንም አያውቅም። ሊሠሩ የሚገባቸውን ሥራዎች ማንም ሳያያቸው እሱ ቀድሞ ያያቸዋል። አምሳሉ በዘመኑ ሥልጣኔ በተራመዱት አገሮች በአንዱ ተወልዶ ቢሆን ኖሮ፥ በሀብትም ሆነ በሙያ በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉ ታዋቂዎች አንዱ ይሆን ነበር። ሲዘፍን፥ ቲያትር ሲሠራ፥ ያፈዝ ነበረ።

አምሳሉ ቀለመወርቅን በማግኘቱ ዕድለኛ የኖነውን ያህል እሷም አምሳሉን የመሰለ አጫዋችና አፍቃሪ የሕይወት ጓደኛ በማግኘቷ ዕድለኛ ነች። በአካል ቢለያዩም ትዝታውንና ጨዋታውን እያስታወሰች እንዳዲስ ስትስቅ እንደምትኖር እርግጠኛ ነኝ።  

አምሳሉ ቀለመወርቅን ለማግኘት ወዲያ ወዲህ ሲል እኔም ትንሽ ሚና ተጫውቻለሁ፤ ከመልካም ቤተሰብ የተወለደችና ጎልማሳ የምታፈዝ ቆንጆ ልጃገረድ ስለነበረች ለትዳር የሚመኟትና የሚፈልጓት ጥቂቶች አልነበሩም። አንዱ በተለየ ጓደኞቹን አስሰልፎ  ሊያስፈራራ ሲመጣ "አጭር ብትፈልግ አጭር፥ ረጅም ብትፈልግ ረጅም ሆነን መጥተንብሃልና የምትፈልገውን አሳየንና እናሳይ አልነው። ማን እንዳሸነፈ የአምሳሉና የቀለመወርው ልጆች ምስክር ናቸው።

እኔም እንደቀለመወርቅ በጨዋታው ሳስታውሰው እኖራለሁ። በትምህርት ገበታ ላይ ብቻ ሳይሆን አገር ለመጎብኘትም አብረን ብዙ ነገር አይተናል። ኪሳችን የተማሪ ኪስ ስለነበረ፥ አገር የምናየው መንገድ ላይ እየቆምን ባለመኪና ሲመጣ እየለመንን ነበር። የለማኝ መራጭ ስለሌለው፥ የቆመልን ሁሉ ይወስደናል። አንዳንድ ጊዜ ባለመኪናዎቹ ሁለት ሰው ስለማይወስዱ አውላላ ሜዳ ላይ እንለያያለን። ቀጠሯችን ባቡር ጣቢያ ነው። አንድ ቀን ባቡር ጣቢያ ስንገናኝ፥ "አምሳሉ፤ የዛሬው ጉዞህ እንዴት ነበር?" አልኩት።

"እረ እባክህ ተወኝ" አለ። "ምነው?" ብለው፥ "አንዲት ሴትዮ በዶቅዶቂት አሳፈረችኝ" አለኝ። "ታዲያ ምኑ ነው፥ እረ እባክህ ተወኝ የሚያሰኘው?" ብለው። "እንዳልወድቅ ትከሻዋን ነበር የያዝኩት፤ እንደሱ አይደለም፤ ወገቤን ያዝ" አለችኝ። ልንሄድበት ስንደርስ ልቀቀኝ ባትለኝ እዚያው ተጣብቄ ልቀር ነበር" አለኝ።

አይ አምሳሉ፤ ለካ አንተም እንደሌላው ነህ!! ግን የምንጽናናባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉን። በጤና ኖረሃል። መልካም ባለቤት፥ መልካም አባት፥ ታማኝ ወዳጅ ሆነሃል። የልጅ ልጅ ስመሃል። በዕውቀትህ የአገርህን ልጆች አገልግለሃል። ለስምህ ሐውልት ተክለሃል። የፈለከውን ለማድረግ አምላክ ዕድል ሰጥቶሃል። ክብሩ ይስፋ። ለዘላለሙ ሕይወት በሚኬድበት መንገድ የሄድከው የማይቀር ቢሆን ነው። ቤተሰብህን፥ ዘመዶችህን፥ ወዳጆችህን እግዚአብሔር ያጽናቸው። እንደኔ ምስጢረኛ አያሳጣቸው።

ምንጊዜም የማይረሳህ ወንድምህ
ጌታቸው ኃይሌ


13 comments:

 1. Thank you so much Mr Gatachew. I didn't know Mr Amesalu but I grew up with his book. God bless his family and you.

  ReplyDelete
 2. ******************************
  ማልቀስ ለከፋፋይ ለባንዳ ዘረኛው
  የገሀነብ እሳት ትንሽም ቢያበስለው
  አምላክ በአምሳሉ አክሊሉን የሰጠው
  ለሀገር ቅን አሳቢ ለትውልድ ለሠራው
  ሸልል ፎክር ሥለ ስመ ጥሩ ሰው
  አፈሩን ገለባ ነፍሱን ገነት ያግባው
  መልካሙ ሥሙ ከመቃብር በላይ ነው
  ልጅ ወዳጅ ዘመዱን ትውልዱን ያጥናው
  ሞተ እንዳትሉን ለቅሶም አያሻው አረፈ በለው!
  በለው!ከሀገረ ከናዳ

  ReplyDelete
 3. ******************************
  ማልቀስ ለከፋፋይ ለባንዳ ዘረኛው
  የገሀነብ እሳት ትንሽም ቢያበስለው
  አምላክ በአምሳሉ አክሊሉን የሰጠው
  ለሀገር ቅን አሳቢ ለትውልድ ለሠራው
  ሸልል ፎክር ሥለ ስመ ጥሩ ሰው
  አፈሩን ገለባ ነፍሱን ገነት ያግባው
  መልካሙ ሥሙ ከመቃብር በላይ ነው
  ልጅ ወዳጅ ዘመዱን ትውልዱን ያጥናው
  ሞተ እንዳትሉን ለቅሶም አያሻው አረፈ በለው!

  ReplyDelete
 4. god bless him.....and long life for u ......ato amsalu balewletachen nebru ,minm neger belelebet beza zemen ke ferenji qunqa gar yagbabun ye ethioia lij neberu....

  ReplyDelete
 5. Professor Getachew, thank you for letting us know a little bit about an educator who taught millions with his timeless dictionary.

  ReplyDelete
 6. Thank u professor for your writing this short story of Dr.Amsalu Aklilu.Thank you.

  ReplyDelete
 7. ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ አረፉ
  ***************************
  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ)
  ለ33 ዓመታት ያገለገሉትና በተለያዩ መጽሐፎቻቸው
  የእንግሊዝኛ - አማርኛ መዝገበ ቃላትን ጨምሮ ታዋቂ
  የሆኑት ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ በ84 ዓመታቸው አረፉ::
  ከቅርብ ዓመት ወዲህ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት
  ሕክምናቸውን ሲከታተሉ የነበሩት ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ ከዚህ
  ዓለም በሞት የተለዩት ታኅሣሥ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. ነው::
  የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የሕዝብ ቤተ
  መጻሕፍት ወመዘክር የሳይንትፊክ ቡድን ዳይሬክተር ሆነው
  ለአንድ ዓመት (1954-55) ያገለገሉት ዶ/ር አምሳሉ፣ ከ1955
  ዓ.ም. ጀምሮ በጡረታ እስከተገለሉበት እስከ 1985 ዓ.ም. ድረስ
  በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
  ከሌክቸረርነት እስከ ተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማገልገላቸውን ገጸ
  ታሪካቸው ያመለክታል::
  በተለይ በግእዝ፣ በአማርኛና በዓረብኛ ቋንቋዎች እንዲሁም
  የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክን በማስተማር ይታወቃሉ::
  የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል
  ሊቀመንበር፣ የቋንቋዎች ጥናት ተቋም ዲን፣ የኢትዮጵያ
  ቋንቋዎችና ባህሎች አካዴሚ የቦርድ አባልም ሆነው ሠርተዋል::
  አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1997 ዓ.ም. የፊሎሎጂ (ጥንታዊ
  ጽሑፎች ጥናት) ትምህርት ክፍል ሲከፈት በድኅረ ምረቃ
  መርሐ ግብር ስለኢትዮጵያ ፊሎሎጂ፣ ስለግእዝና ዓረብኛ
  መዋቅር በኮንትራት አስተምረዋል::
  ዶ/ር አምሳሉን ስመጥር ካደረጓቸውና ካበረከቷቸው
  ትምህርታዊ የሕትመት ውጤቶች መካከል ‹‹እንግሊዝኛ
  አማርኛ መዝገበ ቃላት›› (ከጂ.ፒ. ሞስባክ ጋር /1966 ዓ.ም.)፣
  ‹‹የአማርኛ ፈሊጣዊ አነጋገሮች›› (ከዳኛቸው ወርቁ ጋር/1979
  ዓ.ም.) ‹‹የእንግሊዝኛና አማርኛ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መዝገበ
  ቃላት›› (ከኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዴሚ ጋር) ‹‹ጥሩ የአማርኛ
  ድርሰት እንዴት ያለ ነው?›› (ከደምሴ ማናህሎት ጋር/1989
  ዓ.ም.)፣ ‹‹አጭር የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ›› (ያልታተመ)፣
  ‹‹አማርኛ-ዓረብኛ መዝገበ ቃላት›› (ከሙኒር አብራር ጋር/1999
  ዓ.ም.)፣ ‹‹ግዕዝ መማሪያ መጽሐፍ Ge’ez Textbook›› (2003
  ዓ.ም.)፣ ‹‹የአማርኛና ሞክሼ ሆሄያት ጠንቅቆ ያለመጻፍ ችግርና
  መፍትሔ››(2002 ዓ.ም.)፣ በጀርመን ሐምቡርግ ዩኒቨርሲቲ
  በታተሙት ተከታታይ ‹‹ኢንሳይክሎፔዲያ ኢትዮፒካ››
  እንዲሁም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ጥናታዊ ጽሑፎችን
  አቅርበዋል::
  በቀድሞው አጠራር በወሎ ጠቅላይ ግዛት ደሴ ከተማ
  ነሐሴ 27 ቀን 1922 ዓ.ም. የተወለዱት ዶ/ር አምሳሉ፣ ከቄስ
  ትምህርት ቤት በኋላ መደበኛ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ
  ቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት የተከታተሉ ሲሆን፣ የመጀመሪያ
  ዲግሪያቸውን ከካይሮ ዩኒቨርሲቲ በነገረ መለኮት (ባችለር ኦፍ
  ዲቪኒቲ)፣ እንዲሁም ከካይሮው አሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ባችለር
  ኦፍ አርት በተመሳሳይ ዓመት በ1949 ዓ.ም. አግኝተዋል::
  የአማርኛ፣ ዓረብኛ፣ እንግሊዝኛና ጀርመንኛ ቋንቋዎች
  አዋቂ የነበሩት ዶ/ር አምሳሉ፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን
  ከጀርመን ቱቢንግ ዩኒቨርሲቲ በ1954 ዓ.ም. ሲያጠናቅቁ፣
  የመመረቂያ ድርሳናቸውን (ዲዘርቴሽን) የሠሩት በኦገስት
  ዲልማን የግእዝ መዝገበ ቃላት ላይ ነው::
  የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል
  አስተባባሪው ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣
  የዶክተር አምሳሉ አክሊሉ ሥርዓተ ቀብር ዛሬ (ታኅሣሥ 13
  ቀን 2006 ዓ.ም.) እኩለ ቀን (6 ሰዓት) በየካ ደብረ ሣህል ቅዱስ
  ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ይፈጸማል:
  ********************************
  http://www.ethiopianreporter.com/

  ReplyDelete
 8. ፕሮፌሰር አምሳሉ አክሊሉ የሰሩት ስራ እንዲህ በቀላል ቃላት ተገልጾ የሚተው ነገር አይደለም፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ነገር የሀገራችን ሚዲያዎች አልሰማንም አላየንም ማለታቸው ነው፡፡ አንድ ፈረንጅ ቢሞት ኖሮ ቢቢሲ እንዳለው ሲኤንኤን እንደነገረን እያሉ ያደነቁሩን ነበር፡፡ ነብይ በሀገሩ አይከበርም እንደተባለው፡፡

  ReplyDelete
 9. የኛ ሀገር ጋዜጠኞች የተጠበበቡት በአርሴናልና በማንቼ በቢዮንሴና በአንጀሊና ጆሊ እንጂ መች ቁም ነገር ባለው ሀገርኛ ጉዳይ ሆነና፡፡ አሳዛኝም አሳፋሪም ነገር ነው፡፡

  ReplyDelete
 10. አሳዛኝ አሳፋሪ ድርጌት ነው ።ለሞች ነፍስ ይማር።

  ReplyDelete
 11. እግዜር ይስጥልኝ ፕሮፌሰር ጌታቸው የእኚህን ዓዋቂ ታሪክ ስላሰሙን። እግዜር ይስጥልኝ ዳንኤል። አንት ባትኖር የዶ/ር አክሊሉን ሞትና ታሪክም አንሰማም ነበር። ድሮ እንኳን የኢትዮጵያ ሕዝብ ዓዋቂዎቹ ሲሞቱብት እያከበራቸው ይጽፋል የሚል እምነት ነበረኝ። አሁን ግን ጋዚጠኞቻችንን ታዝቤያቸዋለሁ። ሥራቸው ሁሉ ለገንዘብና ፖለቲከኞች ስለሆነ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞች የላትም ማለት ይቻላል።

  ReplyDelete