Thursday, November 21, 2013

ዐፄ ምኒሊክ በአዲስ አቀራረብ

የወረዳው ሊቀ መንበር ለስብሰባው በሚገባ መዘጋጀታቸው ሲወራ ነው የሰነበተው፡፡ ሕዝቡን ለፀረ ሽብርተኛት ዘመቻ በሚገባ ማንቀሳቀስ አለብኝ ብለዋል አሉ፡፡ አንድም ሰው ከዚህ ስብሰባ መቅረት እንደሌለበት በየሰፈሩ ሲወራ ነበር፡፡
የስብሰባው ቀን ሕዝቡ እግር ኳስ የሚያይ መስሎ አዳራሹን ሞላው፡፡ ቦታ የጠበባቸውም በመስኮት በኩል ጉርድ ፎቶ የሚነሡ ይመስል አንገታቸውን ብቻ አስግገው ያጮልቃሉ፡፡ እስካሁን ማንም ሊቀ መንበር ያልተናገረውን ንግግር ሊያደርጉ ነው ስለተባለ ሰው ምን እንደሚናገሩ ለመስማት ጓጉቷል፡፡ በተለይ አንዳንዱ የወረዳው ነዋሪ እንደ ክትባት ለሁሉ የታዘዘ የሚመስል ተመሳሳይ ንግግር መስማት ሰልችቶታል፡፡ ተናጋሪዎች እንደ ኮካኮላ ጠርሙስ አንድ ዓይነት ሆነው  እንደ ተመረቱ ሁሉ እንኳን ቃሎቻቸው ሳሎቻቸው እንኳን ስለሚመሳሰሉ አንዳንዱ ‹ይህንን ንግግር የት ነበር የሰማሁት›› እስከማለት ደርሷል፡፡ አሁን የኛ ወረዳ ሊቀ መንበር ይህንን እንደ ኮንዶሚንየም መልክ የተመሳሰለ ንግግር ሰብረው ሪኮርድ ሊያስመዘግቡ መሆኑን ስንሰማ ተገልብጠን መጣን፡፡
አንድ በስብሰባው ውስጥ ያገኘሁት ሰው ‹‹እነዚህ ባለ ሥልጣናት ግን አንድ ዓይነት ቃላት ከየት ነው የሚያገኙት?›› ብዬ ስጠይቀው ምን እንዳለኝ ታውቃላችሁ ‹‹የባለ ሥልጣናት መዝገበ ቃላት›› የሚባል ያልታተመ መጽሐፍ አለ፡፡ከዚያ ብቻ ነው ቃላት መምረጥ የሚችሉት፡፡ እዚያ ውስጥ የንግግር ቅጽ አላቸው፡፡ ወረዳውን፣ ቀኑን፣ የተሰብሳቢዎቹን ዓይነትና የበዓሉን ስም ብቻ ትቀይርና ንግግሩን ትወስዳለህ›› ብሎ ቀለደብኝ፡፡


አሁን ሊቀ መንበሩ እየገቡ ነው፡፡ ሕዝቡ አጨበጨበ፡፡ ፕሮግራሙን የሚመራው ሰው ማይክራፎኑን ያዘና ‹አሁን ስብሰባችንን የምናከናውንበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡›› ሲል ሕዝቡ አጉረመረመ፡፡ ግራ ገባው፡፡ ‹ይህ ሕዝብ ባይገባው ነው›› ብሎ አዘነልን፡፡ ‹‹ወረዳችን በዕድገት እመርታ ላይ መሆኗን ታውቃላችሁ፡፡ ልዩ ልዩ ጽሕፈት ቤቶችና አጋር አካላት ተሳልጠው በመሥራታቸውና ሙስናንና ብልሹ አሠራን አስወግደን ልማታዊ አስተሳሰብን በማምጣታችን …›› ሕዝቡ ትዕግሥት አጣ፤ አንድ ጎረምሳ እንዲያውም ‹‹ይህንነን ንግግር የዛሬ ሦስት ዓመት ሰምተነው ነበር፡፡›› ሲል ተሰብሳቢው ሳቀ፡፡
አንደኛዋ ወይዘሮማ ‹‹ምነው መንግሥት በየቦታው ተዋንያኑን ብቻ ነው እንዴ የሚቀይራቸው? የፊልሙን ስክሪፕትስ ለምን አይቀይረውም፡፡ ያ ይሄዳል ይሄ ይመጣል፤ ፊልሙ ያው ነው፡፡›› ሳቅና ጭብጨባ አጀባቸው፡፡ ሰውዬው ግራ እንደገባው ነው፡፡ ‹‹ይህ ንግግር ከራሴ የወጣ ነው፡፡ ይህንን ማን ተናግሮት ነው የዛሬ ሦስት ዓመት የሰሙት›› አለ ተገርሞ፡፡ ‹‹ባክህ ሃርድ ዌሩ ነው እንጂ ሶፍት ዌሩ ያው ነው፡፡ ወይ አብዴት አድርጉት ወይ ቀይሩት››  ወጣቱ ሲናገር በዐዋቂነቱ ተጨበጨበለት፡፡
የወረዳችን ሊቀ መንበር አዝማሚያው ስለገባቸው ማይክራፎኑን ከፕሮግራም መሪው ተቀበሉት፡፡ ‹‹ወደ መጣንበት ጉዳይ ብንገባ ይሻላል፡፡›› ሲሉ አንድ ካህን ድምጻቸውን ከፍ አደረጉና ‹‹ልክ ነው ከተአምሩ መቅድሙ ረዘመብንኮ›› አሏቸው፡፡ ሊቀ መንበሩ ፈገግ ብለው ወረቀታቸውን ከቦርሳቸው አወጡ፡፡ አሁን ስፒል ቢወድቅ የሚሰማበት ዝምታ ተፈጠረ፡፡ የሰው ጆሮ እንደ ዲሽ ተዘረጋ፡፡
ሊቀ መንበሩ ንግግራቸውን ቀጠሉ፡፡ ‹ፈጣሪ በቸርነቱ እስካሁን ሀገር አስፍቶ ጠላት አጥፍቶ አኑሮናል› ብለው ሲጀምሩ ሕዝቡ ቀጣዩን እንኳን ሳይሰማ አጨበጨበ፡፡ የተከበራችሁ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት፣ የክፍለ ከተማ አመራሮች፣ የድርጅት ኃላፊዎች፣ የሥራ አስፈጻሚ አባላት፣ የወጣት ሊግ አመራሮች፣ የሴቶች ሊግ አመራሮች፣ የአነስተኛና ጥቃቅን አመራሮችና አባላት፣ የበጎ አድራጎት ድርጅት ኃላፊዎች፣ የአደረጃጀቶች ኃላፊዎች….. እያሉ እንደ ስም ጠሪ መምህር ወይም እንደ ሙሾ አውራጅ ሲዘረዝሩ ሊውሉ ነው ተብሎ ነበር የተጠበቀው፡፡
‹‹ድርጅታችንም እስካሁን በፈጣሪ ቸርነት፣ በታጋዮች መሥዋዕትነት፣ በአመራሩ ብስለትና በሕዝቡም ይሁንታ ይህንን ሀገር እየመራ መጥቷል፡፡›› ሲሉ ከጎኔ የነበሩት አንድ ሽማግሌ ‹‹ይኼ ነገር የሆነ የሆነ ነገር ሸተተኝ›› አሉኝ፡፡ በዚህ እድሜያቸው የሆነ ነገር ለማሽተት መቻላቸውን አደነቅኩና ‹‹ምን ሸተተዎት›› አልኳቸው፡፡ ‹‹ቆይ እስኪ ቀጣዩን እንስማው›› አሉ፡፡ እንደ ሬዲዮ አንቴና አንገታቸውን ወደ ላይ መዝዘው፡፡
ሊቀመንበራችን እንደ ቀጠሉ ናቸው ‹‹ደግሞም ሕዝባችን እስካሁን አሳፍሮን አያውቅም፤ ከእንግዲህም ያሳፍረናል ብለን አናምንም›› ሲሉ ጭብጨባው ቀለጠ፡፡ እኒያ ሽማግሌ ግን ወደ ላይ የዘረጉትን የአንገታቸውን አንቴና ወደ ውስጥ ሰበሰቡት፡፡ ከዚያም ራሳቸውን ወደ ቀኝና ግራ ወዘወዙ፡፡ ‹‹ይኼ የተከተፈ ንግግር ነው›› አሉ፡፡ በግራ በቀኝ፣ በፊት በኋላ የተቀመጡት ተሰብሳቢዎች ዘወር ዘወር እያሉ አዩዋቸው፡፡ ሊቀ መንበራችን ግን ቀጠሉ፡፡ ‹‹አሁን ግን አገር የሚያጠፋ፣ ገጽታ የሚለውጥ፣ ዕድገት የሚገታ፣ የሕዝብን ሰላም የሚያናጋ ጠላት መጥቶብናል›› ሽማግሌው አንገታቸውን አውልቀው መጣል ይፈልጋሉ መሰል ከአመድ እንደተነሣች አህያ ያርገፈግፉታል፡፡
‹‹እኛም ብሔር ብሔረሰቦች ፊታቸውን ወደ ልማት ማዞራቸውን፣ ሀገራችንም በአንጻራዊ ሰላም ላይ መሆኗን ተመልክተን፤ ዐቅማችንንም ለልማት እንጂ ለሌላ ነገር ማዋል የለብንም ብለን ዝም ብንለው፤ ደግሞ እያለፈ እንደ ዘንዶ አደጋ ማድረስ ጀመረ››፡፡ ሽማግሌው የአንገታቸው አልበቃ ብሏቸው በጫማቸው መሬቱን ይፎግሱ ጀመር፡፡ ‹‹አሁን ግን ሕዝባችንን አጋዥ አድርገን ሀገራችንን አሳልፈን አንሰጥም በማለት ተነሥተናል፡፡ ሕዝባችን ሆይ እስካሁን የበደልንህ አይመስለንም፡፡ አንተም አልበደልከንም፡፡ ዐቅም ያለህ በዐቅምህ እርዳን፤ ዐቅም የሌለህ ለሚስትህ/ለባልሽ፣ ለእምነትህ ስትል መረጃ በመጠቆም እርዳን፡፡›› አሁን ሽማግሌው እጃቸውን ከእጃቸው ጋር ማፋተግ ጀመሩ፡፡ ሊልጡት ነው እንዴ፡፡ ‹‹ወስልቶ ከዚህ ዘመቻ የቀረ ካለ ግን ይጣላናል፡፡ አንተወውም፤ ድርጅታችንን፤ እንምረውም››
‹‹ኦህ›› አሉ ሽማግሌው፡፡
‹ለዚህ አማላጅ የለንም፡፡ ፀረ ሽብር ዘመቻችን ተጀምሯልና የሀገራችን ሰው በዚሁ ወቅት በየራስህ ከትተህ እናግኝህ፡፡››
ሕዝቡ አጨበጨበ፡፡ ጭብጨባውም ረዘመ፡፡
ሽማግሌው ማንም ሳይቀድማቸው ተሥፈንጥረው ተነሡ፡፡
‹‹እሽ አባቴ›. አሉ ሊቀመንበሩ፡፡ ሽማግሌው ወኔ ይዟቸው የተነሡ መስሏቸው፡፡
‹‹ይህ ንግግር የማን ነው?›› አሉ፡፡ እየተንቀጠቀጡ፡፡ ሰው አጉረመረመ፡፡
‹‹እንዴት ማለት›› አሉ ሊቀ መንበሩ፡፡
‹‹ይህ ንግግር ዐፄ ምኒሊክ ለዐድዋ ዘመቻ ከተናገሩት ንግግር የተወሰደ አይደለም?›› አሉ ሽማግሌው፡፡
‹‹ነው›፡፡ ግን ሬሚክስ አድርጌ በአዲስ አቀራረብ ነው ያመጣሁት፡››
‹‹ምኑን ነው ሬሚክስ ያደረጉት››
‹‹ከዓላማዬ ልጀምርልዎት፡፡ የቀድሞ መሪዎችን ንግግር እንዲህ ሬሚክስ እያደረግን ካላቀረብነው ይረሳሉ፡፡ ትውልዱ አያስታውሳቸውም፡፡ ይህንን ያደረግኩት ለምኒሊክ ክብር ብዬ ነው፡፡ አላዩም ዘፋኞቻችንን፤ የቀድሞ ዘፋኞችን ዘፈን ሬሚክስ እያደረጉ በአዲስ አቀራረብ ሲያቀርቡ፡፡ እኔም እንደዚያው ነው ያደረግኩት፡፡ ሬሚክስ ያደረግኩት ደግሞ የምኒሊክን ባላባታዊ አስተሳሰብ ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ጋር ነው፡፡ በአዲስ አቀራረብ ያልኩት ንግግሩን ልማታዊ፣ ሕዝባዊ፣ ፌዴራላዊ፣ ብዝኃነትን የያዘ አድርጌ ነው ያቀረብኩት፡፡›› አሉ ሊቀ መንበሩ፡፡
‹‹እና ዐፄ ምኒሊክን በአዲስ አቀራረብ አቀረቧቸው ማለት ነው›› አሉ ሽማግሌው፡፡
‹‹አዩ አባቴ ማዘመን ማለት ይኼ ነው፡፡ ታሪክን ማረም ይገባል፡፡ አዲስ መፍጠር ካልተቻለ የነበረውን ሬሚክስ እያደረጉ በአዲስ አቀራረብ ማቅረብ ነው፡፡ ሕዝቡም የሚወደው ይኼንን ነው›› አሉና ወደ ሕዝቡ ሲመለከቱ ጎረምሶቹ ‹‹ሼባው አቦ ተወና፣ እኛ ተመችቶናል›› አሏቸው ሽማግሌውን፡፡
ሽማግሌውም ‹‹በጦርነት ያልጠፋች ሀገር በሬሚክስ መጥፋቷ ነው በሉኛ›. ብለው ተቀመጡ፡፡ በአዲስ አቀራረብ በሬሚክስ ላስደሰቱን ለሊቀ መንበራችን ግን ጭብጨባው ቀለጠላቸው፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት የወጣ ነው

30 comments:

 1. A very nice view! The dictionary of the Authority.

  ReplyDelete
 2. እንደ ኮንዶሚንዬም መልክ፣የተመሳሰለ ንግግር ሰብረን ሪኮርድ ሊያስመዘግቡ መሆኑን ስንሰማተገልብጠን መጣን። አሁን ግን አገር የሚያጠፍ የህዝብ ን ሰላም የሚያናጋ ጠላት መጥቶብናል። ሽማግሌው አንገታቸውን አውልቀው መጣል ይፈልጋሉ። የባለ ሥልጣናት መዝገበ ቃላት የሚባል ያልታተመ መጽሐፍ አለ ከዚያብቻነው ቃላት መምረጥ የሚችሉት። ኦህ አሉ ሽማግሌው ይኼ ነገር የሆነ የሆነ ነገር ሸተተኝ አሉ ። ለዚህ አማላጂ የለንም ። ደግሞ እያለፈ እንደ ዘንዶ አደጋ ማድረስ ጀመረ። አሁን ግን ህዝባችንን አጋዥ አድርገን ሀገራችንን አሳልፈን አንሰጥም በማለት ተነስተናል ። ህዝባችን ሆይ እስካሁን የበደልንህ አይመስለንም????????????? አንተም አለበደልከንም ምን አቅም ኑሮት ይበድላል የለት እንጀራ ብቻ እያሰበ ስደተኛ ሆኗል ።ዕቅም ያለህ በአቅምህ እርዳን ዕቅም የሌለህ ለሚስትህ /ለባልሽ ለእምነትህ ስትል መረጃ በመጠቆም እርዳ ። ወስልቶ ከዚህ ዘመቻ የቀረ ካለ ግን ይጣላናል ።የኢትዮጵያ የክተት አዋጂ የነጋሪቱ ድወል በሳውዲ አረቢያ ለተጠቁ ለሞቱ ወገኖቻችን ለተደፈሩት እህቶቻችን ድምጹ ያስተጋባል ያልሰማህ ስማ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚያብሔር ትዘረጋለች የተባለው አሁን ነው ተነስ ያጠባቻቸው ሲነክሱዋት ልጆችዋ ሲክዷት ወንበር ሲፈልጉ የትኛውን ህዝብ ተቀምጦ ሊመራበት ይሆን ልጆቻ ደማቸው ደመከል ሆኖ ሲቀር የኢትዮጵያ ልጆች ተነሱ አምላካችን ከኛ ጋራ ነው አትፍሩ ።ደም መላሽ መንግስት ባይኖረን የሰማይ አምላክ በውሀ አጥለቀለቀው ዛሬም የአባቶቻችን አምላክ ከኛ ጋራ ነው አትፍራ ።አትነሳም ወይ አትነሳም ወይ በሳውዲ የወደቀው ህዝብ ያንተ አይደለም ወይ ተነስ ተነሰ ተነስ ከበላይ ነኝ።ኢትዮጵያ ለዘለአለም ትኑር።።።።።።

  ReplyDelete
 3. ‹‹በጦርነት ያልጠፋች ሀገር በሬሚክስ መጥፋቷ ነው በሉኛ›. ብለው ተቀመጡ፡፡

  ReplyDelete
 4. ‹‹የባለ ሥልጣናት መዝገበ ቃላት›› የሚባል ያልታተመ መጽሐፍ አለ፡

  ReplyDelete
 5. Replies
  1. የአጼ ሚኒሊክ የአደዋ ጦርነት የክተት አዋጅ አና የጸረ አሸባሪነት ዘመቻ ሪሚክስ ሊደረጉ አይችሉም ሁለቱ የተለያዩ ናቸውና፡፡
   የአደዋ ጦርነት ጠላት ሳንፈልገው እቤት ድረስ መጥቶ ካልወጋዋችሁ በማለቱ የታወጀ የክተት አዋጅ ነው፡፡አሸባሪነት ግን በሀገራችን ተንከባክበን ያሳደግነው ልጃችን ነው፡፡ስለዚህ ሁለቱ ሪሚክስ ለደረጉ አይችሉም፡፡

   Delete
 6. ‹‹በጦርነት ያልጠፋች ሀገር በሬሚክስ መጥፋቷ ነው በሉኛ

  ReplyDelete
 7. i like this guy the way of his expression. The issue he touched upon invites for more discussion. keep it up Dani.

  ReplyDelete
 8. you made your point like all the time

  ReplyDelete
 9. የባለ ሥልጣናት መዝገበ ቃላት›› የሚባል ያልታተመ መጽሐፍ አለ::

  ReplyDelete
 10. ‹‹ባክህ ሃርድ ዌሩ ነው እንጂ ሶፍት ዌሩ ያው ነው፡፡ ወይ አብዴት አድርጉት ወይ ቀይሩት››

  ReplyDelete
 11. ወቅታዊና በጣም ወሳኝ የዓይናማ ሰው ዕይታ፤
  ውድ ወንድማችን ዲ/ን ዳንኤል በርታልን

  ReplyDelete
 12. ያስተሳሰብ ነጻነት ሲኖር የተለያየና አዲስ ንግግር ይኖራል፡፡ አሁን ግን ሠው ያስተሳሰቡን ለመናገር በበላዩ ፍላጎት ጥገኛ ስለሆን አዲስ ነገር የለም ወደፈት ከተቻለ ሣቅም ይኮረጃል ፡፡ በቁም መምት ይህ ነው፡፡Shebelaw

  ReplyDelete
 13. ዳኒ፡- እንደዋዛ ያነሳኸው ጉዳይ በጥልቀት ላየው ሰው ብዙ ቁምነገር እንዳለው አስባለሁ፡፡ የምላስና የአመራር ግንኙነት በሀገራችን ምን ይመስላል? የሌሎች ሀገሮችን ተሞክሮ ብዙ ባላውቅም በኛ ሀገር፣ በኛ ዘመን ሥልጣን የሚይዙት ተናጋሪ የሆኑ(ምላስ ያላቸው) ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ስለዚህ ሥልጣን ለመያዝ የግድ ምላስን ማሰራት፣ ብዙ ማውራት(ውሸትንም ጨምሮ) ያስፈልጋል፡፡ ሰዎች ሥልጣን ለመያዝ ለምን ይሽቀዳደማሉ?ካልን በአብዛኛው የግል ህይወታቸውን ለመቀየር፣ይህም የሚሆነው በህገወጥ መንገድ በሚገኝ ገቢ እንጂ የሥልጣኑ ቦታ የሚፈቅደውን ህጋዊ ደመወዝ በማግኘት ብቻ አይደለም፡፡ ሥልጣን ለመያዝ የገዢው ፓርቲ አባል (የፖለቲካ ሰው) መሆንም አንዱ ወቅቱ የሚጠይቀው መስፈርት ነው፡፡የገዢው ፓርቲ ሰዎች ከፌዴራል እስከ ክልል ተደጋጋሚ ቃላት መጠቀም ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ ለንግግር ከተሰጠው ከፍተኛ ግምት የተነሳ እነርሱም በተራቸው ከፍተኛ ግምት የሚሰጡት ለተናጋሪ ሰዎች ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የዘመኑ ባለሥልጣኖች በሙስና ተዘፍቀው በየመድረኩ ግን ቃላትን መደርደር ብቻ ነው ሥራቸው፡፡ሀገሪቱም አላድግ ያለችው በሙሰኞች አመራሮችና የሥራ ኃላፊዎች ዘረፋና ራስ ወዳድነት ነው፡፡የምላስ መዘዝ ምን እንደሆነ ሳያውቁ ውሸትን ሲዋሹ ህሊናቸውን አይቆረቁረውም፡፡መናገር የቻለ ብቻ ለምን ሥልጣን ይሰጠዋል?ምግባሩ መታየት የለበትም? ምላስ የሌላቸው ጥሩ ምግባር ያላቸውና የመስራት ችሎታ ያላቸው የሉም? አልበርት አንስታይን መናገር አይወድም ይባላል፤አንድ ቀን በስብሰባ ላይ አንድ ቃል ብቻ ተናገረ፣ በአጠገቡ የተቀመጠውን ሰው ‘’እባክህ መስኮቱን ዝጋው’’አለ፡፡ስለዚህ ሀገርን የሚያሳድገው ሥራ የሚሠራ ጭንቅላት (ከንጹህ ኅሊና ጋር)፣ ከደም የነፃ እጅና ታማኝነት እንጂ ቀባጣሪ ምላስ እንዳልሆነ ባለፉት 40 ዓመታት አይተናል፡፡ ከሃይማኖት አንጻርም ሲታይ የምላስ መዘዝ ብዙ ነው፡፡በራዕየ ማርያም መጽሐፍ ላይ እመቤታችን በሲኦል ያሉትን ነፍሳት እንደሀጢአታቸው ዓይነት በተለያየ ፍርድ ውስጥ እንዳሉ ልጅዋ ኣሳይቷት ከነዚህም ውስጥ በምላሳቸው ተንጠልጥለው የተሰቀሉ ነፍሳት አዝና አልቅሳለች፡፡እነዚህ እንግዲህ በምላሳቸው የበደሉ መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡ከዚህ ያድነን፡፡ጻድቁ አባ በርሱማ መላ ዘመናቸውን እግዚአብሔርን አገልግለው የእረፍታቸው ቀን ሲደርስ ጌታ ተገልጾ አረጋጋቷቸዋል፡፡ ነፍሳቸው ከመውጣትዋ በፊት ደቀመዝሙራቸውን መቁረጫ(ቢለዋ) አምጣልኝ አሉት፤ ከዚያም ምላሳቸወን ቆርጠው ጣሉት በዚያው አርፈዋል፡፡ ይቺን ምላስ መዘዝዋን መፍራት ጠቃሚ ነው፡፡

  ReplyDelete
 14. It is interesting and informative.

  ReplyDelete
 15. Dn. Daniel
  You are an excellent observant. To avoid boredom, it is quite essential at least to rephrase others wordings. As much as possible we need to stick to our style of presentation, because ours is not bad!

  ReplyDelete
 16. አዲስ መፍጠር ካልተቻለ የነበረውን ሬሚክስ እያደረጉ በአዲስ አቀራረብ ማቅረብ ነው፡፡

  ReplyDelete
 17. አንዳንድ ሰዎች አባታችን ሆይ እንዲህ ይጸልያሉ አሉ፦

  ''ውዳሴ ዘመንግሥተ ቢቸግር''

  አባታችን ሆይ
  በቤተመንግስትህ የምትኖር
  ስምህ በክፉ አይነሳ
  መንግስትህ ትጽና
  ፈቃድህ ለአሽከሮችህ እንደሆነች
  እንዲሁም ለእኛ ትሁን
  የእለት ጉርሻችንን ስጠን ዛሬ
  ጥፋታችንንም ይቅር በለን
  እኛም የበደልንህን ይቅር እንደምንል
  አቤቱ ወደ እስር ቤት አታግባን
  ዳኛና ሕግ ያንተ ናትና
  ስደት እስር ጭቆና
  ለዘላለሙ ዓሜን!


  የሚዲያ ዳሰሳ ጋዜጠኞች ሆይ መንግሥት ሞቶልናል ደክሞንናል በሳውዲ ለተደረገውም ሁሉን አድርጓል አላችሁን? አንተ ጋዜጠኛ ሆይ በሳውዲ እናትህ ብትሞት ኖሮ መንግስት ሁሉን አድርጎልኛልና ደግ አደረክ ትለው ነበረን? እህት ወንድምህ ቤተሰብህ ቢሞት ምን ትል ይሆን? አፍ ሲዋሽ ሆድ ይታዘባል አሉ!


  ኢትዮጲያዊያን ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ከሳውዲ ተባረዋል አላችሁን። ከኢትዮጲያዊያን ውጪ የትኛው ዜጋ ነው የተደፈረ የታረደ? ሽንጣችሁን ይዛችሁ ለተከበረው መንግስታችን የምትከራከሩ ጋዜጠኞች ሆይ ሬሳ በታቀፉ ቤተሰቦች ላይ ማፌዝ አይሆንምን? ለሆድ ሳይሆን ለህሊና የሚኖር ማን ነው?

  እስኪ ጅል ልሁንና የጅል ጥያቄ ልጠይቅ! ETV መንግሥት እዚህ ጋ ስህተት ሰርቷል የሚለው መቼ ይሆን? ደም ከደም ስር ጋ የሚጋጨው መቼ ይሆን እንደማለት ይሆንብኛል። ሁለቱም መቼም አይሆኑምና! BBC የሀገሪቱን መንግስት ይሞግታል ስህተቱንም ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። ETV ደግሞ ከላይ እንዳየነው ውዳሴ ዘመንግስተ ቢቸግር ያሰማናለ! በ ETV ከሳውዲ መጣሁ ያለች ዜጋ ኤምባሲ ባይደርስልን ኖሮ እዚህ ባልቆምን ነበር ስትል ፎጋሪው ETV አሳየን። ሲኦል ይከርቸምላችሁና የመንግስት ኤምባሲ ግን ክርችም ብሎ ተዘግቷል። እዛጋ ዜጋ የኤምባሲ ያለህ እያለ ይጮሃል እዚጋ ውዳሴ ዘመንግስተ ቢቸግር ይቀርባለ!  ReplyDelete
 18. enquan kalachew yejachew enkisikase andayinet now

  ReplyDelete
 19. ያስተሳሰብ ነጻነት ሲኖር የተለያየና አዲስ ንግግር ይኖራል፡፡ አሁን ግን ሠው ያስተሳሰቡን ለመናገር በበላዩ ፍላጎት ጥገኛ ስለሆን አዲስ ነገር የለም

  ReplyDelete
 20. ‹ፈጣሪ በቸርነቱ እስካሁን ሀገር አስፍቶ ጠላት አጥፍቶ አኑሮናል›
  ከዓላማዬ ልጀምርልዎት፡፡ የቀድሞ መሪዎችን ንግግር እንዲህ ሬሚክስ እያደረግን ካላቀረብነው ይረሳሉ፡፡ ትውልዱ አያስታውሳቸውም፡፡ ይህንን ያደረግኩት ለምኒሊክ ክብር ብዬ ነው፡፡
  የሚገርማችሁ ነገር በቅርቡ አንድ የዩንቨርስቲ መምህር ሲቪክስ ሲያስተምር አፄ ሚኒልክን ዘመናዊ ስልጣኔን በማስገባታቸው ሲወቅሰቸው በመስማቴ በጣም ነው የገረመኝ፡፡ ለመሆኑ ይህ ትውልድ እውነት አፄ ሚኒልክን የመውቀስ ሞራልና ብቃት አለው ? ምን ሰርቶ ?

  ReplyDelete
 21. ‹‹በጦርነት ያልጠፋች ሀገር በሬሚክስ
  መጥፋቷ ነው በሉኛ›. ብለው ተቀመጡ፡፡ በአዲስ አቀራረብ
  በሬሚክስ ላስደሰቱን ለሊቀ መንበራችን ግን ጭብጨባው
  ቀለጠላቸው፡፡

  ReplyDelete
 22. ‹‹የባለ ሥልጣናት መዝገበ ቃላት›› የሚባል ያልታተመ መጽሐፍ አለ

  ReplyDelete
 23. አንደኛዋ ወይዘሮማ ‹‹ምነው መንግሥት በየቦታው ተዋንያኑን ብቻ ነው እንዴ የሚቀይራቸው? የፊልሙን ስክሪፕትስ ለምን አይቀይረውም፡፡ I like it bravo d

  ReplyDelete
 24. አንደኛዋ ወይዘሮማ ‹‹ምነው መንግሥት በየቦታው ተዋንያኑን ብቻ ነው እንዴ የሚቀይራቸው? የፊልሙን ስክሪፕትስ ለምን አይቀይረውም፡፡

  ReplyDelete
 25. አንደኛዋ ወይዘሮማ ‹‹ምነው መንግሥት በየቦታው ተዋንያኑን ብቻ ነው እንዴ የሚቀይራቸው? የፊልሙን ስክሪፕትስ ለምን አይቀይረውም፡፡ ያ ይሄዳል ይሄ ይመጣል፤ ፊልሙ ያው ነው፡፡›› ሳቅና ጭብጨባ አጀባቸው፡፡ ሰውዬው ግራ እንደገባው ነው፡፡ ‹‹ይህ ንግግር ከራሴ የወጣ ነው፡፡ ይህንን ማን ተናግሮት ነው የዛሬ ሦስት ዓመት የሰሙት›› አለ ተገርሞ፡፡ ‹‹ባክህ ሃርድ ዌሩ ነው እንጂ ሶፍት ዌሩ ያው ነው፡፡ ወይ አብዴት አድርጉት ወይ ቀይሩት›› ወጣቱ ሲናገር በዐዋቂነቱ ተጨበጨበለት፡፡

  ReplyDelete
 26. አንደኛዋ ወይዘሮማ ‹‹ምነው መንግሥት በየቦታው ተዋንያኑን ብቻ ነው እንዴ የሚቀይራቸው? የፊልሙን ስክሪፕትስ ለምን አይቀይረውም፡፡ ያ ይሄዳል ይሄ ይመጣል፤ ፊልሙ ያው ነው፡፡›› ሳቅና ጭብጨባ አጀባቸው፡፡ ሰውዬው ግራ እንደገባው ነው፡፡ ‹‹ይህ ንግግር ከራሴ የወጣ ነው፡፡ ይህንን ማን ተናግሮት ነው የዛሬ ሦስት ዓመት የሰሙት›› አለ ተገርሞ፡፡ ‹‹ባክህ ሃርድ ዌሩ ነው እንጂ ሶፍት ዌሩ ያው ነው፡፡ ወይ አብዴት አድርጉት ወይ ቀይሩት›› ወጣቱ ሲናገር በዐዋቂነቱ ተጨበጨበለት፡፡

  ReplyDelete
 27. በዊልቸር ከሚገፋ ፖለቲካ፤ዘመን ተሻጋሪው ታሪካችን ይሻላል!

  ReplyDelete