Friday, November 29, 2013

አማርኛ በአንድ እግሩ

ባለፈው አንድ ዩኒቨርሲቲ ሄጄ አንድ ጓደኛዬ የነገረኝ አሳዛኝ ነገር ነበር፡፡ የአማርኛ መምህር ለመቅጠር የተሰጠው ፈተና ዩ፣ ዪ፣ ዬ እና ዮ ን መጻፍ ነበር፡፡ በጣም የሚገርመው ግን ከተፈተኑት አምስት የሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው መምህራን አንዱ ብቻ አሟልቶ ጽፏቸዋል፡፡ ወደፊት አማርኛን ማንበብና መጻፍ የሚችል ሰው ለማግኘት ሥዕለት ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ እስኪ ይኼንን ማስታወቂያ ተመልከቱት ‹ይከላከላል› ወይስ ‹ይከሳከሳል› - ተከላካይ ነው ቦክሰኛ?

Wednesday, November 27, 2013

የሙሴ እናት

እሥራኤልን ዐርባ ዓመት በበረሃ የመራ፣ ፈርዖንን ድል የነሣ፣ የኤርትራ ባሕርንም ለሁለት እንደ ድንጋይ የከፈለ ሰው ነው ሙሴ፡፡ እርሱን በተመለከተ አያሌ መጻሕፍትን ጽፈዋል፣ ፊልሞችን ደርሰዋል፣ ብዙዎችም በእርሱ ስም ተጠርተዋል፡፡ ሕዝብን ከባርነት የማውጣት፣ ለሕዝብ ብሎ የመከራከር፣ ለሕዝብ ብሎ ራስን የመሠዋት፣ ሕዝብን ከራሱ በፊት የማስቀደም፣ ሕዝብን በትዕግሥትና በጥበብ የመምራት፣ ለሕዝብ ብሎ ተከራክሮ ድል የማድረግ ተምሳሌት ነው - ሙሴ፡፡
ሙሴ ከወገኖቹ ጋር የኖረው ከተወለደ እስከ ሦስት ወር እድሜው ብቻ ነው፡፡ ያ ጊዜም ቢሆን ወገኖቹ በግብጻውያን እጅ ከባርነት በከፋ ስቃይ ውስጥ ገብተው የሚንገበገቡበት ጊዜ ነው፡፡ እንኳን ሌላውን ዓይነት ነጻነት ቀርቶ ልጅ ወልዶ የማሳደግ መብት እንኳን አልነበራቸውም፡፡ በተለይም ልጁ ወንድ ከሆነ፡፡ በምድርም ላይ እነርሱን ሊመለከት፣ ሊታደግና ሊራዳ የሚችል አንዳችም ኃይል አልነበረም፡፡ ዓለም እንደ ወስከንቢያ በላያቸው ላይ ተደፍታባቸው ነበር፡፡
ሙሴ ለዐርባ ዓመታት ያህል የኖረው በፈርዖን ቤተ መንግሥት ውስጥ የፈርዖን ልጅ ተብሎ፣ ግብጻዊነቱ እየተነገረው ነው፡፡ የተማረው የግብጽን ጥበብ፣ የበላው የግብጽን ምግብ፣ የሚያውቀው የግብጽን ቋንቋ፣ የኖረው ከግብጻውያን መኳንንትና መሳፍንት ጋር፣ የሚያየው የግብጻውያንን አማልክት፣ የተወዳጀው ከግብጻውያን ጠንቋዮችና አስማተኞች ጋር ነበር፡፡

Friday, November 22, 2013

ሊቃውንትን እናስታውሳቸው

እጨጌ ዕንባቆም የመናዊ

ልዩ መርሐ ግብር በደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት(መርካቶ) አዳራሽ
                                 ቀን -  ኅዳር 22 ቀን 2006 ዓም
                                 ሰዓት-  ከቀኑ በ8 ሰዓት

                               የመግቢያ ካርዱን ይውሰዱ

  • ከየመን በ16ኛው መክዘ መጥቶ የደብረ ሊባኖስ አበ ምኔት ስለሆነውና አያሌ መጻሕፍትን ስለደረሰውና ስለተረጎመው እጨጌ ዕንባቆም የመናዊ ልዩ ዝግጅት በተለያዩ ሊቃውንትና ምሁራን ይቀርባል

  • በመርሐ ግብሩ ላይ ለመሳተፍ የመግቢያ ካርዱን 
  • ለም ሆቴል ማትያስ ሕንጻ ከሚገኘው አግዮስ መጻሕፍት መደብር፣ 
  • ከደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት(መርካቶ) ሰንበት ትምህርት ቤት ጽ/ቤት እና 
  • ከማኅበረ ቅዱሳን ጽ/ቤት ፊት ለፊት ከሚገኙ የመጻሕፍት ማከፋፈያ ሱቆች(የአርከበ ሱቆች) ማግኘት ይችላሉ፡፡
  • አስቀድመው የመግቢያ ካርዱን በመውሰድ አብረን ሊቃውንቱን እናስብ
አዘጋጆች
  • ምክሐ ደናግል ሰንበት ትምህርት ቤትና ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

Thursday, November 21, 2013

ዐፄ ምኒሊክ በአዲስ አቀራረብ

የወረዳው ሊቀ መንበር ለስብሰባው በሚገባ መዘጋጀታቸው ሲወራ ነው የሰነበተው፡፡ ሕዝቡን ለፀረ ሽብርተኛት ዘመቻ በሚገባ ማንቀሳቀስ አለብኝ ብለዋል አሉ፡፡ አንድም ሰው ከዚህ ስብሰባ መቅረት እንደሌለበት በየሰፈሩ ሲወራ ነበር፡፡
የስብሰባው ቀን ሕዝቡ እግር ኳስ የሚያይ መስሎ አዳራሹን ሞላው፡፡ ቦታ የጠበባቸውም በመስኮት በኩል ጉርድ ፎቶ የሚነሡ ይመስል አንገታቸውን ብቻ አስግገው ያጮልቃሉ፡፡ እስካሁን ማንም ሊቀ መንበር ያልተናገረውን ንግግር ሊያደርጉ ነው ስለተባለ ሰው ምን እንደሚናገሩ ለመስማት ጓጉቷል፡፡ በተለይ አንዳንዱ የወረዳው ነዋሪ እንደ ክትባት ለሁሉ የታዘዘ የሚመስል ተመሳሳይ ንግግር መስማት ሰልችቶታል፡፡ ተናጋሪዎች እንደ ኮካኮላ ጠርሙስ አንድ ዓይነት ሆነው  እንደ ተመረቱ ሁሉ እንኳን ቃሎቻቸው ሳሎቻቸው እንኳን ስለሚመሳሰሉ አንዳንዱ ‹ይህንን ንግግር የት ነበር የሰማሁት›› እስከማለት ደርሷል፡፡ አሁን የኛ ወረዳ ሊቀ መንበር ይህንን እንደ ኮንዶሚንየም መልክ የተመሳሰለ ንግግር ሰብረው ሪኮርድ ሊያስመዘግቡ መሆኑን ስንሰማ ተገልብጠን መጣን፡፡
አንድ በስብሰባው ውስጥ ያገኘሁት ሰው ‹‹እነዚህ ባለ ሥልጣናት ግን አንድ ዓይነት ቃላት ከየት ነው የሚያገኙት?›› ብዬ ስጠይቀው ምን እንዳለኝ ታውቃላችሁ ‹‹የባለ ሥልጣናት መዝገበ ቃላት›› የሚባል ያልታተመ መጽሐፍ አለ፡፡ከዚያ ብቻ ነው ቃላት መምረጥ የሚችሉት፡፡ እዚያ ውስጥ የንግግር ቅጽ አላቸው፡፡ ወረዳውን፣ ቀኑን፣ የተሰብሳቢዎቹን ዓይነትና የበዓሉን ስም ብቻ ትቀይርና ንግግሩን ትወስዳለህ›› ብሎ ቀለደብኝ፡፡

Monday, November 18, 2013

እሥረኛው ባለ ታሪክ

አንዳንዶች በድሎትና በምቾት ላይ ያገኙትን የሰላም ዘመን ምንም ሳይጠቀሙበት ‹ተወለዱ- ሞቱ› ተብለው ያልፋሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ስደታቸውን፣ እሥራቸውንና ግዞታቸውን፣ መከራቸውንና ሕመማቸውን የሀገርንና የወገንን ታሪክ ለመለወጥ፣ በሰው ልጅ ታሪክም ውስጥ ጉልሕ ቦታ ለመያዝ ሲጠቀሙበት ይታያሉ፡፡ እኛ ‹የመከራ በረከት› ፈረንጆች ‹blessing in disguise› የሚሉት ማለት ነው፡፡ ሰውን የሚጎዳው የደረሰበት ችግርና መከራ አይደለም፡፡ በዚያ ችግና መከራ ውስጥ ሆኖ የሚያየው ነገር ነው፡፡ ገነት ውስጥ ሆነው ሲዖልን ከሚያዩ ሰዎች ይልቅ ሲዖል ውስጥ ሆነው ገነትን የሚያዩ ሰዎች ይበልጣሉ፡፡ አንዳንዶች በመታመማቸው ምክንያት ታሪክ ሠርተዋል፡፡ አንዳንዶች በመታሠራቸው ምክንያት ታሪክ ሠርተዋል፤ አንዳንዶች በመሰደዳቸው ምክንያት ታሪክ ሠርተዋል፤ አንዳንዶችም በመቸገራቸው ምክንያት ታሪክ ሠርተዋል፡፡
ችግር ሁለት ነገሮችን ትወልዳለች፡፡ ጠቢባን ሲያዋልዷት ብልሃትን፣ ሞኞች ሲያዋልዷት ድህነትን፡፡
ችግርን ቀምሰዋት፣ በጥበብም አዋልደዋት ብልሃትን እንድትወልድ ካደረጓት የሀገራችን ሰዎች አንዱ ደጃዝማች ኃይሉ እሸቴ ናቸው፡፡ ዘመነ መሳፍንት ተብሎ በሚጠራው የሀገራችን ዘመን አብዛኛውን ዘመናቸውን ያሳለፉት የአስተዳደር፣ የጦርና የቀለም ሰው ደጃዝማች ኃይሉ እሸቴ የተወለዱት በ1746 ዓም አካባቢ ጥር 12 ቀን ነው፡፡ አባታቸው ደጃዝማች እሸቴ እናታቸውም ወ/ሮ ወለተ ራጉኤል ይባላሉ፡፡
ደጃዝማች ኃይሉ በዘመኑ እንደነበሩት የኢትዮጵያ የመኳንንት ልጆች ፈረስ ግልቢያውንና አደኑን እየተማሩ፣ የቀለም ትምህርቱንም ጎን ለጎን እያስኬዱ አደጉ፡፡ በዚህ መካከል ግን መጋቢት 11 ቀን 1760 ዓም አባታቸው ደጃዝማች እሸቴ በጦርነት ላይ ሞቱባቸው፡፡ ያኔም እድሜያቸው ወደ አሥራ አራት ዓመት ያህል ሆኗቸው ነበር፡፡ ወላጅ እናታቸው በ1755 ዓም የሞቱባቸው ኃይሉ እንደገና የአባታቸው በልጅነታቸው መሞት ኀዘኑን አጸናባቸው፡፡

Wednesday, November 13, 2013

ለዚህማ አልተፈጠርንም!

ከዲያቆን ዓባይነህ ካሤ

ኢትዮጵያውያን ደማቸው የዐረብን አስፋልት አቀለመው፡፡ ባንዲራውን በራሱ ላይ ሸብ ያደረገው የእማማዬ ልጅ የእኔ ጀግና ማንነቱን እየተናገረ በአናቱ ላይ የወረደውን የድንጋዩን ናዳ በሀገሩ ፍቅር ተቋቁሞ በክብር አሸለበ፡፡ ለእርሱ ከዚህ በላይ ሌላ ድል አልነበረምና፡፡ ድንጋዩስ እርሱን አሳርፎታል፡፡ ነፍሱን ይማርልን እንጂ! ባንዲራችን ግን እንደተመታች እንደታመመች ናት፡፡ እውን ይኽ የሆነው በእኛ ላይ ነው? 


ይህቺ ባንዲራ እኮ ጨርቅ አይደለችም፡፡ ያ በሳኡዲ መሬት ተወግሮ የሞተው ወንድሜ የኮራባት በሞቱ ጊዜ የለበሳት የክብሩ፣ የማንነቱ መገለጫ እንጂ፡፡ ማንም ባይደርስለት ባንዲራው ነበረችለት፡፡ በእርሷ ተጽናና፡፡ ሞተ አልለውም መሰከረ እንጂ፡፡ ባንዲራ ለብሶ መከራን መጋፈጥ የሰማእታት ወግ ነው፡፡ 

ዳግማዊ ሆሎኮስት በኢትዮጵያውያን ላይ? እንዴት እንዴት? ደግሞ በ ፳፩ኛው ክፍለ ዘመን፡፡ የሰውን ሕይወት የሚያስገብር ምን ጥፋት ተገኝቶ ነው ወይስ የሟርት መስዋእታቸው እኛ ነን፡፡ "ከሕግ አስከባሪው ፖሊስ" እስከ ዱርየው የእኅቶቻችን ክቡር ሰውነት እንደ ውሻ ሲጎተት ከማየት የሚዘገንን አረመኔነት ምን አለ? ይህ እኮ ንቀት ነው፡፡ ይህ እኮ ድፍረት ነው፡፡ ይህ እኮ የሀገርን ሉዐላዊነት መድፈር ነው፡፡ 

Tuesday, November 12, 2013

ዝክረ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራትና ፕሮፌሰር ዶናልድ ክራሚ

በኢትዮጵያ ታሪክ ጥናት ታላቅ ቦታ ያላቸውን ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራትንና ፕሮፌሰር ዶናልድ ክራሚን ለማሰብ ሰኞ ጥቅምት 18 ቀን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ መኮንን አዳራሽ መርሐ ግብር ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በወቅቱ የሁለቱም ደቀ መዝሙር የነበረው ዶ/ር ውዱ ጣፈጠ ያቀረበውን ማስታወሻ እንብቡት፡፡

ዝክረ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራትና ፕሮፌሰር ዶናልድ ክራሚ
ዉዱ ጣፈጠ( ዶ/ር)
ከተማሪዎቻቸው አንዱ
ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራትና ፕሮፌሰር ዶናልድ ክራሚ ሁለቱ በዩነቨርስቲ የትምህርት ቆይታዬና ብሎም በህይወቴ ላይ ቀና ተፅእኖ ያሳደሩ ታላቅ መምህሮቼ ነበሩ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የቅድመ-ምረቃ የታሪክ የአራተኛ ዓመት ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ ከፕሮፌሰር ታደሰ ጋር የመጀመሪያን ትውውቅ አደረግን፡፡ ለቅድመ ምረቃ (ለቢ.ኤ.) ዲግሪ ማóóያ የምረቃ Òሁፍ ምርምር ለማድረግና ውጤቱንም ለመፃፍ እንድችል እርሳቸው አማካሪዬ ሁነው ተመድበው ነበር፡፡ በወቅቱ እርሳቸው የማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ስለነበሩ እርሳቸውን አግኝቶ ለማነጋገር ትንሸ ችግር ፈጥሮብኝ ነበር፡፡ ከትንሸ መመላለስ በኋላ አግኝቸ ራሴን ሳስተዋውቅ ትኩር ብለው እየተመለከቱ በርጋታ አዳመጡኝ፡፡ ከዚያም እስኪ ወደ ሌላ ነገር ከመግባታችን በፊት የራስህን ታሪክ፤ የቤተሰብህን፤የአስተዳደግህንና የትምህርትህን ነገር ግለፅኝ ብለው ጠየቁኝ፡፡ በጊዜው ይህ ሁሉ ምን ያደርጋል ብየ በየዋህነት ራሴን ጠይቄ ነበር፡፡ የርሳቸው አካሄድ የገባኝ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነበር፡፡
  ለቅድመ ምረቃ የምርምር ስራ የሰራሁበት ርእስ ስለ ራጉኤል አብያተ ክርስቲያናት ታሪክ ነበር - እንጦጦና አዲስ አበባ መርካቶ ስለሚገኙት መንትያ አብያተ ክርስቲያናት፡፡ ፕሮፌሰር ታደሰ  በጣም ረጋ ያሉ፤ በተመስጦ የሚያዳምጡ፤ ቀስ ብለው የሚናገሩና እንዲህ አይነቶቹን ዋና ዋና ፍሬ ነገሮች አስተውለሀዋል ብለው በማስታወሰ መንገድ የሚያሳዩ ነበሩ፡፡ በዜያ ጊዜ እኔን ለመሰለው ገና ጀማሪ በማበረታታትና በሚቀጥለው ጊዜ ስንገናኝ አዲስ መረጃ እንደምታመጣ ተስፋ አለኝ ብለው የሚሸኙ ነበሩ፡፡ የሚያውቁትን መረጃ ጠቅሰው ፈልግ የሚሉ፤ መረጃ ሊሰጡ የሚችሉና ያውቃሉ ብለው የሚገምቷቸውን ሰዎችን ስም የሚነግሩና ሲቻልም የሚያስተዋውቁ ነበሩ፡፡

Monday, November 11, 2013

‹የዜግነት ክብር›

ኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ሲዘመር ከሚያነሣቸው ነጥቦች መካከል ‹የዜግነት ክብር› የሚለው የተለየ ስሜት ይሰጠኛል፡፡ ለአንዲት ሀገር ሰው ትልቁ ዋጋው ‹የዜግነት ክብር› ነው፡፡ ሀገር አለኝ ብሎ ማሰብ፤ የሚያስብልኝ፣ የሚጮህልኝ መንግሥት አለኝ ብሎ ማመን፤ የእኔ ጉዳይ ጉዳዩ የሆነ አካል አለ ብሎ መመካት፡፡
እንዲህ እንደ ሰሞኑ ያለ፣ በሳዑዲ እየተፈጸመ እንዳለው ነገር ያለ ስናይና ስንሰማ ደግሞ ‹የዜግነት ክብር› መዝሙር ብቻ ይሆንብናል፡፡ ‹ኢትዮጵያዊ ማለት› ብለን ልንተረጉም ይቸግረናል፡፡ ማንም  የአራዊት ጠባይ ያለው ሁሉ ተነሥቶ መንገድ ላይ ደሙን የሚያፈሰው፣ እግሩን የሚቆርጠው፣ የሚደበድበውና በፈለገበት ቦታ የሚያሥረው ከሆነ፣ ይህማ እንኳን የዜግነት ክብር የስደተኛነት ክብርም አላገኘም ማለት ነው፡፡ ሀገር አልባ ጂፕሲዎች ከሚደርስባቸው ግፍ በላይ ባለሀገሩ ኢትዮጵያዊ ከደረሰበትማ ‹የዜግነት ክብር› የቱ ላይ ነው፡፡ ደግሞስ በአንድ ኢትዮጵያዊ ላይ ሰው መሆኑን የሚያጠራጥር ከዚህ በላይ ምን ሊደርስበት ይችላል፡፡
ይህ ነገር ሁለት ነገሮችን እንድናስብ ማድረግ አለበት፡፡
1.   የመንግሥት አካላት በየሀገሩ ያሉትን ዜጎቻችንን ለማወቅ፣ ለመከታተልና መብታቸውን ለማስከበር ያላቸውን ብቃት
2. እንዲህ ዓይነት ነገር በሌላ ጊዜና በሌላ ሀገር እንዳይደገም ልናደርገው የሚገባንን ዘላቂ መፍትሔ
የዜግነት ክብር የሚኖረው አንድ ዜጋ የትም ቦታ ቢኖር የዜግነት መብቱ እንዲከበርለት፣ በዜግነቱ እንዲኮራና የዜግነቱንም ግዴታ እንዲወጣ ሲደረግ ነው፡፡
ይህ የዜግነት ክብር እንዲጠበቅ መንግሥት፣ የዲፕሎማቲክ ሚሽኖች፣ የዲያስጶራ ማኅበረሰቦችና ጠቅላላው ሕዝብ ከዚህ ጊዜ የተሻለ የመንቂያ ጊዜ አያገኙም፡፡ ይህንን ለማሰብ እስከዛሬ የፈሰሰው ደም በቂ ካልሆን፤ የሚያስፈልገን የስንት ሰው ደም ይሆን?

አራቱ ኃያላን - የምረቃ መርሐ ግብርTuesday, November 5, 2013

የሌለውን ፍለጋ - ክፍል ሁለት

click here for pdf
በይምርሐነ ክርስቶስ ጣራ ላይ የሚገኘው የዳዊት ኮከብ
ባለፈው ሳምንት ተስፋዬ ገብረ አብ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ ያነሣቸውን ነጥቦች ማየት ጀምረን ‹የሦስቱን ተክለ ሃይማኖቶች› ጉዳይ ለዛሬ አቆይተነው ነበር፡፡ እንቀጥል፡፡
1)        የሰባተኛው መክዘ ተክለ ሃይማኖት
ተስፋዬ የጠቀሳቸው የሰባተኛው መክዘ ተክለ ሃይማኖት የሉም፡፡ እስካሁንም እንደርሱ ፈጠራቸውን የሚናገሩ እንጂ ማስረጃ ያመጡ አልተገኙም፡፡ ይህንን ነገር መጀመሪያ ያነሣው የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ገድለ ተክለ ሃይማኖትም ስለ ጽላልሽ (ኢቲሳ) ተክለ ሃይማኖት እንጂ ስለ ሰባተኛው መክዘ ሌላ ተክለ ሃይማኖት አይናገርም፡፡ ገድለ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ ልዩ ልዩ ቅጅዎች ቢገኙም ሁሉም ግን በተወለዱበት ቦታ፣ በተወለዱበት ዘመን፣ በወላጆቻቸው ስም፣ በሠሯቸው ሥራዎችና በገዳማቸው ላይ የሚተርኩት ታሪክ ተመሳሳይ ነው(Encyclopedia Aethiopica, Vol., IV,.P.833) በአንድ ወቅት ታላቁን የታሪክና የኢትዮጵያ ጥንታውያን መዛግብት ሊቅ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን ስለዚህ ጉዳይ ስጠይቃቸው ‹አለኝ ያለ ማስረጃውን ያምጣ፣ የለም የምንለው ፈልገን ልናመጣ አንገደድም›› እንዳሉት አለን የሚሉት እስኪያመጡ ድረስ የምናውቀውን ይዘን እንቀጥላለን፡፡
2) መራ ተክለ ሃይማኖት የሚባል ንጉሥ ነበረ፡፡ እንደ ደብረ ሊባኖስ ዘሺምዛና(ኤርትራ) እና ደብረ ሐይቅ መዛግብት ከሆነ መራ ተክለ ሃይማኖት የዛግዌ ሥርወ መንግሥት መሥራች ንጉሥ እንጂ ‹ቄስ› አልነበረም፡፡ የዛግዌን ዘመን በተመለከተ የተጻፉ የዛግዌ ቅዱሳን ገድሎች(ፔሩሾ የጻፈውን የገድለ ላሊበላ መቅድም መመልከት) ይህንን አይነግሩንም፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን የዛግዌን ታሪክ ያጠኑት ሊቃውንት(ለምሳሌ E. A. Wallis Budge, A History of Ethiopia, London, 1928; Sergew Hable Sellassie, Ancient and Medieval Ethiopian History) መራ ተክለ ሃይማኖት ቄስ ነበረ አይሉንም፡፡ የላስታ ትውፊትም ይህን አይናገርም፡፡ በላስታ አድባራትና ገዳማት የሚሳሉት ቅዱሳን አራቱ ነገሥታት ናቸው (ቅዱስ ላሊበላ፣ ቅዱስ ሐርቤ(ገብረ ማርያም)፣ ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስና ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ)፡፡ ከእነዚህም ክህነትና ንግሥናን እንደያዘ የሚነገረው ይምርሐነ ክርስቶስ ነው፡፡ ተስፋዬ እንዲሆን የሚፈልገውን ብቻ ነው የነገረን፡፡ 
ስለዚህም በገድለ ተክለ ሃይማኖት የሦስት ሰዎች ገድል ተቀላቅሏል የሚለን ማስረጃ አልባ ሕልም ነው፡፡ 

Monday, November 4, 2013

ከኢትዮጵያ ውጭ ለምትኖሩ

ብዙዎቻችሁ ከኢትዮጵያ ውጭ ምትኖሩ አንባብያን አዲሱን መጽሐፍ ባላችሁበት ለማግኘት ጠይቃችኋል፡፡ ያለው አማራጭ በ dkibret@gmail.com ኢሜይል ላኩልን፡፡ በኢሜይላችሁ ያላችሁበትን አድራሻ አብራችሁ ላኩልን፡፡ የመላኪያውን ዋጋ ጠይቀን እንነግራችኋን፡፡ ከዚያም የመጽሐፉንና የመላኪያውን ዋጋ በባንክ በኩል ከላካችሁ መጽሐፉን በነጠላም ሆነ በብዛት እንልክላችኋለን፡፡ አስቀድመን በመላክም ከሀገር ቤቱ አንባቢ እኩል እንድታነቡ እናደርጋለን፡፡
መልካም ንባብ፡፡ 

Saturday, November 2, 2013

አራቱ ኃያላን - አዲስ መጽሐፍ - በቅርብ ቀን

click here for pdf
በቅዱሳት መጻሕፍት ዕውቀትና በቤተ ክርስቲያን ትምህርት የበሰሉ፣
ዘረኝነትንና ጠባብነትን እስከ መጨረሻው የተዋጉ፣
የፍቅር መሥፈርታቸው ሰው መሆን ብቻ የሆነ፣
ቤተ ክርስቲያን የቤተ መንግሥቱ ጥገኛና ተቀጽላ እንዳትሆን በብርቱ የተጋደሉ፣
ለእምነታቸውና ለአቋማቸው ሲሉ ከነገሥታቱ ጋር ፊት ለፊት የተገዳደሩ፣
ከእሳት፣ ከግርፋት፣ ከአራዊት፣ ከዘንዶ፣ ከግዞት፣ ከስደት ጋር ተጋፍጠው እምነታቸውን ያስከበሩ፣
ነገሥታቱ በተሳሳተ መንገድ ሲሄዱ እንደ ዮሐንስ መጥምቅ ያለ ፍርሃት የገሰጹ፣
በመላዋ ኢትዮጵያ ለስብከተ ወንጌል የተሠማሩ፣
ቤተ መንግሥትን ለሥልጣንና ለጥቅም ሲሉ ከተጠጉ ሥጋውያን ካህናት ጋር በእምነትና በጽናት ያደረጉት ትግል፤
ምንኩስና መንኖ ጥሪት(ሀብት ንብረትን መተው) ነው ብለው የተሰጣቸውን የማባበያ ገንዘብ፣ ወርቅና ርስት ላለመቀበልና       ሃይማኖታዊ ነጻነታቸውን ለመጠበቅ ያደረጉት ተጋድሎ፣