Wednesday, September 4, 2013

ኑሮ በካንጋሮ ምድር(፪)

በአበሾቹ መንደር ፉት ስክሬይ በአንዱ የሐበሻ ሆቴል ቁጭ ብዬ አንድ ወገን ወደ እኔ መጣ፡፡ መጥቶም አልቀረ ወንበር ሳበና ቁጭ አለ፡፡
‹‹ዐውቅሃለሁ መሰል››
‹‹ይሆናል፣ የሰው መተዋወቂያው ብዙ ነው›› አልኩት፡፡
‹‹ዳንኤል ነህ አይደል›› አለኝ፡፡ አረጋገጥኩለት፡፡ እኔ በቀን አራት ጊዜ የሚፈራረቀው የሜልበርን አየር አልገባኝ ብሏል እርሱ ጃቦኒ ነው ያደረገው፡፡ ራሱን አስተዋወቀኝ፡፡ መጽሐፎቼን ማንበቡን ነገረኝ፡፡ መቼም በውጭ ሀገር ሰማሁ የሚል እንጂ አየሁ፣ እገሌ ነገረኝ የሚል እንጂ አነበብኩ የሚል ሰው ማግኘት ዋድላና ደላንታ ሄዶ ኦራል እንደማግኘት ብርቅ ነው፡፡ አመሰገንኩት፡፡
‹‹እንግሊዝኛ ብችል ኖሮ አንዳንዱን ጽሑፍ እተረጉመው ነበር›› አለኝ እየሳቀ፡፡
‹‹ታድያ ምን ችግር አለው፡፡ አውስትራልያ የእንግሊዝኛ ሀገር ናት፡፡ ተርጉመው›› አልኩት፡፡
‹‹እንደመጣሁ ቋንቋ ትምህርት ቤት ገብቼ ነበር፡፡ ለስደተኞች የሚሰጥ ኮርስ ስላለ ለመውሰድ፡፡ እንግሊዝኛና ብስክሌት በልጅነት ካልጀመሩት ጉድ ይሠራል››
ሳቅኩና ‹‹እንዴት?›› አልኩት››


‹‹ሞከርኩትና ቋንቋውን ትቼ ፈገግታውን ብቻ ተምሬው ወጣሁ›› አለኝ፡፡
‹‹የትኛውን ፈገግታ?››
‹‹አለች የእነርሱ ፈገግታ፤ እንደ ፍሬቻ ብልጭ ድርግም የሚያደርጓት፡፡ ቢገባህም ባይገባህም ከሳቅክ ፈረንጅ ደስ ይለዋል፡፡ ታድያ ሥራ ስገባ ቢገባኝም ባይገባኝም ሳቅ ስል ከአፍንጫ በታች ከአገጭ በላይ በሆነ ፈገግታ ያጅቡኝ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ሥራዬን ከሠራሁ የእነርሱ እንግሊዝኛ ቢገባኝ ባይገባኝ ብዬ ተውኩላቸው፡፡ አንድ ቀን ግን ጉድ ሆንኩ፡፡›› ጉጉቴ ከሳቅ ጋር ጨመረ፡፡
‹‹አንድ አብሮኝ የሚሠራ ልጅ አለ፡፡ በጉሮሮ እንግሊዝኛው ሲያወራኝ ስቄ ነበር የማሳልፈው፡፡ ‹እንግሊዝኛንና ስደትን ስቆ ማሳለፍ ነው› የሚል ጓደኛ ነበረኝ፡፡ ታድያ አንድ ቀን ሥራ እየሠራን የሆነ ነገር ያወራኛል፡፡ ልብ አልሰጠሁትም፡፡ ሲጨርስ ቀና ብዬ በፈገግታ ሳየው ተናደደ፡፡ በማውቃት እንግሊዝኛ ‹‹ምን ሆንክ›› አልኩት፡፡ ‹‹እንዴት እናቴ ትናንት ሞተች ስልህ ትስቃለህ›› አይለኝም፡፡ እኔ ራሴ ደነገጥኩ፡፡ ቀዥቃዣ ፈረንጅ፤ እናቱ ሞታ እስኪ ከፍራሽ አስነሥቶ ሠለስት እንኳን ሳይደርስ ምን ያመጣዋል፡፡ እኛ ድሮ የተማርነውን ሁሉ አጣመው አጣመው ድምጻቸው ሊያዝልኝ አልቻለም፡፡ አሁን ሲገባኝ ግን እነርሱ የጉሮሮ እኛ የከንፈር እንግሊዝኛ ነው የተማርነው፡፡››
‹‹ደግሞ እንግሊዝኛ የከንፈርና የጉሮሮ የሚባል አለው?››
‹‹ታድያስ፡፡ እስኪ ስማቸው፡፡ እኛ ‹ዋተር› ብለን ረገጥ አድርገን ስንጠራ እነርሱ ‹ዋር› ብለው በአየር ላይ ያልፉታል፡፡ እኛ ‹ገርል› እየተባልን ጫን ብለን ስንናገር እነርሱ ‹ገ - ል› ብለው በስሱ ያቆላምጧታል፡፡› አሁን ያለን አማራጭ በአማርኛ እያለቀስን በእንግሊዝኛ መሳቅ ነው፡፡›› እኔ ግን በአማርኛ ሳቅኩ፡፡
‹‹ለምን ትምህርት ቤት አልሄድክም(ውጭ ‹አልገባህም› አይባልም) እዚያ የግድ ከቋንቋው ተናጋሪዎች ጋር ስትቀላቀል ትለምደው ነበር››
‹‹ድመት ጅራቷ የተቆረጠበት ቦታ ተመልሳ አትሄድም› ሲባል ሰምተሃል፡፡ እኛም መቀመጫችንን (እርሱ ሌላ ነበር ያለው) የተገረፍንበት ስለሆነ ነው መሰል ወጣ ስትል እዚያ አይመራህም፡፡ እንጂ እዚህ ሀገርማ ብትማር ብዙ ይረዱሃል፡፡ አየህ ድሮ እንማር የነበረው ለእንጀራ ነበር፡፡ እዚህ መጥተን ሳንማር እንጀራ አገኘን፡፡ ታድያ ለምን እንማራለን? ደግሞ በየስደተኛው ካምፕ ፀጉራችንንና ልባችንን ጨርሰን መጥተን ነው መሰል እዚህ ሀገር ማስታወስ የሚባል ነገር የለም፡፡ ቶሎ ትረሳለህ፡፡ 
‹‹ምን ያህል ጊዜ ቆየህ አውስትራልያ››
‹‹በሃሳብ ዘጠኝ ዓመት፣ በአካል አሥራ ስድስት ዓመት›› አለመረዳቴን ለመግለጥ አንገቴን ሊወድቅ እንደተዘጋጀ ብርጭቆ አወዛወዝኩ፡፡

‹‹ሱዳን ነበርኩ፡፡ ሱዳን ዘጠኝ ዓመት ቆየሁ፡፡ እዚያ እያለሁ በተስፋ አውስትራልያ ነበርኩ፡፡ ነገ ትሄዳላችሁ፣ አልቋል፤ ተጠናቋል፤ ፎርም ሙሉ፤ ተዘጋጁ፤ አሻራ ስጡ፤ ፎቶ ተነሡ ስንባል ዘጠኟን ዓመት ጠጣናት፡፡ እኛስ ይሁን በልጅነታችን ወጥተን ነው፡፡ አረጋውያን አባቶች ነበሩ እዚያ፡፡ ስደትና እብደት ካረጁ በኋላ አያምርም፡፡ የአብርሃም ቤት አዛውንቶች ሲባል ሰምተሃል?››
‹‹አልሰማሁም›› አልኩት፡፡
ቀጠለ፡፡ ‹‹እነዚህ አዛውንቶች ከ1966 ዓም ጀምሮ በኢዲዩ፣ በከፋኝ፣ በምናምን እየተደራጁ ሲዋጉ የኖሩ ናቸው፡፡ በኋላ ግን ሁሉም ነገር አልሆን አላቸው፡፡ አረጁ፡፡ መጀመሪያ በተለያዩ ቦታዎች፤ በኋላ ደግሞ አብዱል ረከም በሚባል የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ከሃያ ዓመታት በላይ በሱዳን አሳለፉ፡፡ በመጨረሻም ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት ወደ 350 የሚጠጉ አዛውንቶች አውስትራልያ መጡ፡፡ መንግሥት ጡረታ ይሰጣቸዋል፡፡ ቋንቋው ግን መከራ ያሳያቸዋል፡፡ ቤት የመጣ ፖስታ ለማንበብ፣ ከማኅበራዊ አገልግሎት ሠራተኞች ጋር ለመግባባት ችግር አለ፡፡ አውስትራልያ ብር እንጂ ቋንቋ አትረዳ፡፡
የዘመድ ሰላምታ ሲመጣ ደብዳቤ
አንብቡልኝ ብዬ ለሰው አስነብቤ - የሚል ዘፈን ትዝ ይልሃል (በዜማ ነው ያለልኝ) እዚህ ተወዳጅ ዜማ ነው፡፡››
‹‹እዚህ ሀገር ከሱዳን የመጡ ይበዛሉ ልበል፡፡››
‹‹ልክ ነህ፤ በተለይ በኢሕአፓና በኢዲዩ ጊዜ ወጥተው፤አሥርና ሃያ ዓመት ሱዳን ኖረው የመጡ ናቸው አብዛኞቹ፡፡ ያልተቀየጠ ንጹሕ የኢሕአፓ ዘር እዚህኮ ነው ያለው፡፡ ጓድ ሲባባሉ ትሰማቸዋለህ፡፡ 
‹‹ ለመሆኑ ግን ከወጣህ በኋላ ወደ ሀገር ተመልሰህ ታውቃለህ?››
‹‹አንድ ጊዜ ብቻ››
‹‹ምነው፤ ጥፊም ይደገማል ይባል የለ እንዴ››
‹‹ታክሲ ነጅ ከሆንክ መደጋገምህ አይቀርም››
ታክሲው አያደርሳቸው››
‹‹ትርፊክ እየጣስክ ትነዳ ትነዳና ነጥብ ትሰበስባለህ፤ ከዚያ ወደ ዘጠኝ አካባቢ ስትደርስ መንጃ ፍቃድህን ነጥቀው እንዳትነዳ ይሉሃል፡፡ እዚህ ሀገር እንዴት ትዘልቀዋለህ፡፡ ሀገር የናፈቀህ መስለህ ኢትዮጵያ ትሄድና አንድ ሦስት ወሯን ቅጣት እዚያ ታሳልፋታለህ፡፡ ‹ለዕረፍት የመጣ ፍቅር›› በሚለው ፋንታ ‹ለዕረፍት የመጣ ሾፌር›› የሚል ፊልም ሠርተህ ትመለሳለህ፡፡››
ቢሆንም አገር አይደል››
‹‹ወዳጄ ሀገር ቤት ደርሶ የመጣና ቤቱ የተቃጠለበት አንድ ነው››
‹‹እንዴት››
‹‹ሙልጭህን ነዋ የምትቀረው፡፡ እዚያ ዝንጥ እያለ የምታየው ዳያስጶራ ሁሉ ከሀገሩ ሲመለስ ስልክ አያነሣ፣ ከሰው አይገናኝ፣ ኢሜይል አይከፍት፤ ይመንናል፡፡ ከሆስፒታል መውጣት በለው፡፡ በተለይ ኢምፖርት ሊያደርጉ የሚሄዱትማ››
‹‹ምንድን ነው ኢምፖርት የሚያደርጉት››
(ይቀጥላል)
ካሮላይን ስፕሪንግስ፣ ሜልበርን፣ አውስትራልያ

34 comments:

 1. <<እንግሊዝኛና ብስክሌት በልጅነት ካልጀመሩት ጉድ ይሠራል›› የምትመች አባባል ናት፤

  ReplyDelete
 2. እያንዳንዱ ንግግርሩ እያሳቀኝ ነው ያነበብኩት በተለይ የሚገልጽበት መንገድ:: in person ደግሞ እንዴት አድርጎ እንደሚያወራው ሳስበው እንደገና ተመልሼ እስቃለህ:: ለማኛውም ደብሮኝ ነበር በጣም አዝናንቶኛል:: ባለበት ምስጋናዬ ይድረሰው ለሰውዬው ላንተም ስላቀረብክልን::

  ReplyDelete
 3. betam yazenanal yasetemeralem temechetogal !!!

  ወዳጄ ሀገር ቤት ደርሶ የመጣና ቤቱ የተቃጠለበት አንድ ነው›› Tekekel new !!!

  ReplyDelete
 4. እኔንም ሲያቀብጠኝ እንቅልፌ እንደመጠኝ አነበብኩልህና በሳቅ ፈርሸ ፈርሸ ጠላትህ እልም ይበል እንለፌ እልም አለ፡፡ መሳቅ ብቻ ሳይሆን በሳቅ ፈረስኩልህ፡፡
  ለአንተም ቸር ያሰማህ፡፡
  የጣና ዳሩ ነኝ!

  ReplyDelete
 5. ‹‹ወዳጄ ሀገር ቤት ደርሶ የመጣና ቤቱ የተቃጠለበት አንድ ነው››

  ReplyDelete
 6. I need the whole story soon

  ReplyDelete
 7. በጣም ነው የሳኩት በጣም ነው ደስ የሚለው። Thanks D.N Daniel

  ReplyDelete
 8. ስደትና እብደት ካረጁ በኋላ አያምርም፡፡

  ReplyDelete
 9. ”እብደት እና ስደት ካረጁ በኋላ አያምርም፡፡” እውነት ነው!

  ReplyDelete
 10. የተረገመ ተራኪ! የተረገመ ፀሐፊ! ! የተረገመ ዕውነት! !!

  ReplyDelete
  Replies
  1. የተረገመ ተራኪ! የተረገመ ፀሐፊ! የተረገመ ዕውነት!

   Delete
  2. Very interesting explanation. An explanation that comes from deep love.

   Delete
 11. Azenagn ena asetemari shega tshuf Amilak yebarikih abo Danii lanitem erjim edme ke tena gar MEDEHANIALEM yesetlih

  ReplyDelete
 12. ha ha ha, filfilu gar neber ende yemitawaraw, he seems comedian

  ReplyDelete
 13. Thank's Deacon Daniel Kibret.

  ReplyDelete
 14. ስልክ አያነሣ፣ ከሰው አይገናኝ፣ ኢሜይል አይከፍት፤ ይመንናል፡፡ ከሆስፒታል መውጣት በለው፡፡

  ReplyDelete
 15. nice history & funny

  ReplyDelete
 16. denke new yemeketlewn lemanbeb chekolku

  ReplyDelete
 17. Then ... / Keziyas ...

  ReplyDelete
 18. Still you didn't tell us why you go Australia. Do you live there or for limited time duration?

  ReplyDelete
 19. ምን ያገባሃል? አሁን ከሞላልህ ጥያቄ ይህን ትጠይቃለህ? እንደዚህ ዓይነት ጥያቄስ በአደባባይ ይጠየቃል?

  ReplyDelete
 20. like it.it's so funny!

  ReplyDelete
 21. ዳኒ አውስትራሊያ ምርጫ ላይ ናት:: እስኪ እግረ መንገድህን የሆነ ነገር በለን::

  ReplyDelete
 22. ሰላም ላንተ ይሁን የሚገርም ሰው ነው እውነታወችን አዋዝቶ ያለፈበትን ሁሉ አቅልሎ እና ስቆ የሚያሳልፍ ግሩም ስደተኛ ያለንበትን ህይወት በቀልድስላሳያችሁን አመሰግናለሁ ዳኒ ይቀጥል

  ReplyDelete
 23. ዱኔ የሰውየው አባባል አገርቤት ላለው ወገን ትምሕርት ሰጭ ይመስላል ። ኦጀን እሳት ወስጥ አስገብቸ ካልሞከርኩ አይነት ነገር ካልተፈለገ ።
  ለሁሉም በሰላም ይመልስሕ በርታ።

  ReplyDelete
 24. so so funny and meaning full article

  ReplyDelete
 25. what an habesha living there?

  ReplyDelete
 26. አየህ ድሮ እንማር የነበረው ለእንጀራ ነበር፡፡ እዚህ መጥተን ሳንማር እንጀራ አገኘን፡፡ ታድያ ለምን እንማራለን? ደግሞ በየስደተኛው ካምፕ ፀጉራችንንና ልባችንን ጨርሰን መጥተን ነው መሰል እዚህ ሀገር ማስታወስ የሚባል ነገር የለም፡፡ ቶሎ ትረሳለህ፡፡

  ReplyDelete
 27. በቅርብ ቀን ለሚከናወነው ለዓለም
  መጥፋትም ሆነ መዳን ኢትዮጵያ
  የመለኮት የፍርድ ምድር
  Ethiopia decides the redemption or destruction of the world that is upon us!
  Ethiopia is the origin and the salivation of the human race and all creation!

  ReplyDelete
 28. ታድያስ፡፡ እስኪ ስማቸው፡፡ እኛ ‹ዋተር› ብለን ረገጥ አድርገን ስንጠራ እነርሱ ‹ዋር› ብለው በአየር ላይ ያልፉታል፡፡ እኛ ‹ገርል› እየተባልን ጫን ብለን ስንናገር እነርሱ ‹ገ - ል› ብለው በስሱ ያቆላምጧታል፡፡›

  ReplyDelete