Sunday, September 1, 2013

አውስትራልያዊው ‹የቋራ ሰው›

የኢትዮጵያን ነጻነት ስናስብ ልንዘክራቸው የሚገቡ፣ ለሀገሪቱ ደማቸውን ያፈሰሱ፣ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የታገሉ፤ ለነጻነቷ ሲሉ ከገዛ መንግሥታቸው ጋር የተሟገቱ፣ ዕውቀታቸውንና ገንዘባቸውን የከሰከሱ አያሌ የሌላ ሀገር ሰዎች አሉ፡፡ በተለይ ዛሬ ኢትዮጵያዊነት ቆሻሻ እንደ ነካው ልብስ በሚገፋበት ጊዜ ለኢትዮጵያዊነታችን ዋጋ የከፈሉትን ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ሰዎች ማስታወስ ግድ ይለናል፡፡
እዚህ አውስትራልያ መጥቼ ካገኘኋቸው መጻሕፍት አንዱ ‹ተልዕኮ 101 - Mission 101› የተባለ ዱንካን ማክናብ(Duncan Mcnab) በተባለ ሰው የተጻፈ መጽሐፍ ነው፡፡ ማክናብ መርማሪ(detective) ፖሊስ፣ የግል የምርመራ ሥራ (Investigator) ባለሞያ፣ ደራሲና ጋዜጠኛ የነበረ አውስትራልያዊ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በእንግሊዝ ወታደራዊ ተልዕኮ ውስጥ በመሰለፍ ለኢትዮጵያ ነጻነት የታገሉ አራት አውስትራልያውያን ወታደሮች ታሪክ ቀርቧል፡፡ ከአራቱ አንዱ የዱንካን ማክናብ አጎት ነበረ፡፡

በዚህ መጽሐፍ ላይ ከአራቱ ወታደሮች ጋር ታሪኩ ተያይዞ የቀረበ አንድ ሌላ ሰው አለ፡፡ ይህ ሰው የተወለደው እኤአ ኖቬምበር 25 ቀን 1877 ዓም በደቡብ ብሪዝበን(አውስትራልያ) ነው፡፡ አያት ቅድመ አያቶቹ ትንግርታዊ ጉዞ የሚወዱ(adventurers) ነበሩ፡፡ አያቱ ከእንግሊዟ ዌልስ በ1800ዎቹ ነበር ወደ አውስትራልያ የገባው፡፡ በምሥራቅ አውስትራልያ ከ117ሺ ሄክታር በላይ መሬት የነበረው ሀብታም አሳራሽ ነበረ፡፡ በኋላ ግን ወደ እንግሊዝ ተመልሶ በሄርፎርድ ሻየር ኑሮውን ቀጠለ፡፡ ልጁን አርኖልድንም በአዳሪ ትምህርት ቤት አስተማረው፡፡
በ1896 አርኖልድ እንግሊዝን ተወና ወደ አውስትራልያ መጥቶ በቤተሰቡ እርሻ ላይ መሥራት ጀመረ፡፡ በከተማ በሚገኘው ዘመናዊ ቤት ከመኖር ይልቅ በገጠር በነበረው የገበሬዎች ቤት ውስጥ በመኖርና አኗኗሩን ሁሉ እንደ ገበሬዎቹ በማድረግ የተለየ ሕይወት የመኖርን ዘይቤ እንደ አያቶቹ ተካነበት፡፡ ‹ቋረኛው› አርኖልድ ዊንሆልት እንግዲህ የዚህ ሰው ልጅ ነበር፡፡
ዊንሆልት ሲፈጥረው የትግል ሰው ነው፡፡ መከራ ባለበት ቦታ ገብቶ መታገል የሚወድ፡፡ በ1899 እኤአ በደቡብ አፍሪካ የቦር ጦርነት ሲፈነዳ የቤተሰቡን ሀብት ትቶ እንዲያውም ለፈረስ መግዣ እንዲሆነው የተወሰነውን ሽጦ በኩይንስ ላንድ ጦር ወስጥ በመመዝገብ በ1900 ወደ ደቡብ አፍሪካ ሄደና ለለስምንት ዓመት በውጊያ ላይ ቆየ፡፡ ጦርነቱ ሲፈጸምም ወደ አውስትራልያ ተመልሶ የቤተሰቡን ሀብት ማስተዳደር ጀመረ፡፡ ከሀብቱ ጎን ለጎን በኩዊንስ ላንድ ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ለግዛቲቱ ሕግ አውጭ ምክር ቤት በ1909 ተመርጦ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ በ1913 እኤአ ወደ አፍሪካ ተመልሶ በደቡብና በደቡብ ምእራብ አፍሪካ ውጊያዎች ላይ በፈቃደኛነት ተሳትፏል፡፡ እንዲያውም በናሚቢያ በረሃ እያለ በአንበሳ እስከ መነከስ ደርሶ ነበር፡፡
በዚህ መካከል በ1928 ዓም ሞሶሎኒ ኢትዮጵያን ወረረ፡፡ ዊንሆልት ይህ ነገር በጣም ነበር ያሳሰበው፡፡ በአንድ በኩል የኢትዮጵያ መወረር፤ በሌላ በኩል ሞሶሎኒ በአፍሪካ ለነበሩ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛቶች አደጋ መሆኑ ልቡን ገዝቶታል፡፡ ጦርነቱን በቅርብ ለመረዳት እንዲችል የብሪዝበኑ ኮርየር ሜይል ጋዜጣ የጦርነት ሪፖርተር አድርጎ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ እንዲልከው አደረገ፡፡ በኖቬምበር 22 ቀን 1935 እኤአ ከአውስትራልያ ወደ አፍሪካ በመርከብ አመራ፡፡ በኤደን በኩል አድርጎ ጅቡቲ፣ በጅቡቲ በኩልም በባቡር ተሣፍሮ አዲስ አበባ ገባ፡፡ ኢምፔሪያል ሆቴልም ዐረፈ፡፡
አርኖልድ ዊንሆልት
ዊንሆልት በኢትዮጵያ አርበኞች የአልበገር ባይነት ውጊያ መንፈሱ ተማርኮ ነበር፡፡ እርሱ በደቡብ አፍሪካ፣ በናሚቢያና በአንጎላ የተዋጋው የደፈጣ ውጊያ ስልት በኢትዮጵያ አርበኞች ሲተገበር ማየቱ እንዲቀላቀላቸው ይገፋፋው ነበር፡፡ ዊንሆልት ስለ ደፈጣ ውጊያ አንብቧል፣ ሠልጥኗል፤ በተግባርም ሠርቶበታል፡፡ የደፈጣ ውጊያም ይማርከዋል፡፡ ይህንን የአርበኞች ውጊያ ለመረዳትና ለመዘገብ ግን አልቻለም፡፡ ጣልያኖች ጋዜጠኞች ከአዲስ አበባ እንዲወጡ አይፈቅዱም ነበር፡፡
ዊንሆልት ይህ ነገር መንፈሱን አላረካው ሲል የቀይ መስቀል ሾፌር ሆኖ በመቀጠር ወደ ገጠሮች ለመሄድ ወሰነ፡፡ በ1936 እኤአ የፈለገውን ሥራ አገኘው፡፡ በዚህ ሥራው አማካኝነት በአዲስ አበባ ለነበረው የእንግሊዝ ሌጋሲዮን መረጃ ከማቀበሉም በላይ ጦርነቱን በቅርብ ለመረዳትም ቻለ፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ጦርነቱ ዜና መሆኑ አበቃ፡፡ ዊን ሆልትም ወደ አውስትራልያ ተመለሰ፡፡
ዊንሆልት በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን ጠባይ ባይደሰትም የኢጣልያ ወረራ ግን ትክክል አልነበረም ብሎ ያስብ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበሩት ኃያላን ሀገሮች ለኢትዮጵያ ጥያቄ ተገቢ መልስ አለመስጠታቸውም አሳዝኖታል፡፡ ይህንን ስሜቱን ኮርየር ሜይል ለተሰኘው ጋዜጣ እየጻፈ ቢልክም ዋና አዘጋጁ ግን ለማተም ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ዊንሆልት ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሞሶሎኒንና የእንግሊዙን ጠቅላይ ሚኒስትር ቻምበርላይንን ያወግዝ ነበር፡፡ ጋዜጦች የነፈጉትን ዕድል የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ይወጣ ነበር፡፡ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስለ ኢትዮጵያ ይናገራል፡፡
በ1937 እኤአ ዊንሆልት አውስትራልያን ለቅቆ እንደገና ወደ የመን አመራ፡፡ በየመን ዋና ከተማ ኤደን ያገኛቸውን የእንግሊዝ ታላላቅ ወታደራዊ ባለ ሥልጣናትንም ኢትዮጵያን ለማገዝ እንግሊዝ ጦር ማዝመት እንዳለባት መወትወት ጀመረ፡፡ በተለይም የአርበኞችን የደፈጣ ውጊያ በመጠቀም ጣልያንን ሰላም መንሣትና በመጨረሻም ማስወጣት አለብን የሚለውን ሃሳቡን በተደጋጋሚ ለማሳመን ይጥር ነበር፡፡ የየመን ቆይታው አልሳካ ሲለውም ወደ ለንደን አምርቶ ከእንግሊዝ የዲፕሎማሲና ወታደራዊ ባለሥልጣናት ጋር በሃሳቡ ተነጋገረ፡፡ ማንም ግን ትኩረት ሊሰጠው አልወደደም፡፡ ዊንሆልት በዚያ እያለ ታዋቂዋ የኢትዮጵያ ወዳጅ ሲልቭያ ፓንክረስት ለምታሳትመው New Times – Ethiopian News ዋና የጽሑፍ አበርካች ሆኖ ነበር፡፡
 በተለይም በአፕሪል 16 ቀን 1938 እንግሊዝና ጣልያን ‹የአንግሎ ጣልያን› ስምምነትን ሲፈራረሙ ዊንሆልት በጣም አዘነ፡፡ ለንደንንም ለቅቆ ወደ የመን ተመለሰ፡፡ ከየመንም አገሩ አውስትራልያ ገባ፡፡ በየሄደበት ሁሉ ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ መናገርና መቀስቀስም ዋና ተግባሩ ሆነ፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይም የመተዳደርያ ሥራውን እስከ ማስረሳት አደረሰው፡፡
በዚህ መካከል እንግሊዝና ጀርመን እየተቃቃሩና ወደ ጦርነት እያመሩ ሄዱ፡፡ የአውስትራልያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሮበርት ሜንዝየስም በጀርመን ላይ ጦርነት ዐወጀ፡፡ ዊንሆልት ይህንን እንደ መልካም አጋጣሚ ወሰደው፡፡ ፊቱንም ወደ አፍሪካ ለመመለስ እንዲችል አበቃው፡፡ ሴፕቴምበር 27 ቀን በ1935 እኤአ በ62 ዓመቱ ከአውስትራልያ ለቅቆ ወደ ሲንጋፖር፣ ከዚያም ወደ ኤደን አመራ፡፡ በዚያም አንድ አፓርትመንት ተከራይቶ ዐረብኛና አማርኛ የሚችል ተርጓሚ ቀጠረ፡፡ ለሲልቭያ ፓንክረስት የሚልከውን ጽሑፍ ሳያቋርጥ ያገኛቸውን አካላት ሁሉ የኢትዮጵያ አርበኞችን ስለመርዳትና በእነርሱም አማካኝነት ጣልያንን ድል ስለማድረግ ያማክር ነበር፡፡
ይህ ጥረቱ ውጤት በማምጣቱ የተነሣም በሜይ 1940 ሃሳቡን ተግባራዊ ለማደረግ የሚያስችል ደብዳቤ ከእንግሊዝ ወታደራዊ ባለ ሥልጣናት ደረሰው፡፡ ዊንሆልትም እየፈነደቀ በ62 ዓመት እድሜው እንደገና ወደ ውትድርና ተመለሰ፡፡ በጁን 17 ቀን 1940 እኤአ ከየመን ወደ ሱዳን ካርቱም በረረ፡፡
ምንም እንኳን ለንደን ለሚገኙት ለቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ የተገለጠ ነገር ባይኖርም እንግሊዞች ግን እያሠጋቸው የመጣውን የጣልያኖችን ኃይል ከምሥራቅ አፍሪካ ለማስወጣት ምሥጢራዊ ዕቅድ በማዘጋጀት ላይ ነበሩ፡፡ ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያን አርበኞች በማገዝ ጣልያኖችን ሰላም መንሣትና በመጨረሻም እንዲወጡ ማደረግ በብዙዎቹ ባለሞያዎቻቸው የታመነበት ዕቅድ ሆነ፡፡ ይህ ዕቅድ ዊንሆልት በተደጋጋሚ ሲወተውተው የነበረ ዕቅድ ነበረ፡፡ እንግሊዞች ይህንን ዕቅድ የተሳካ ለማድረግ በሕንድና በመካከለኛው ምሥራቅ ያገለገለውን በተለይም ደግሞ በምድረ ፍልስጤም እሥራኤልን በመርዳት የተሳከለት ሥራ የሠራውን፣ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላም ወደ ኢትዮጵያ ክርስቲን ከምትባለው ባለቤቱ ጋር መጥቶ ከአዲስ አበባ በስተ ሰሜን ኑሮ የጀመረውን ዳን ሳንፎርድን ነበር የመረጡት፡፡ ሳንፎርድ ስለ ኢትዮጵያ ማወቅ ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ ይቆረቆር የነበረ፤ ከብዙዎቹ የዘመኑ መሳፍንትና መኳንንት ጋርም መልካም ግንኙነት የነበረው፤ በንጉሠ ነገሥቱ ዘንድም መታወቅንና መከበርን ያተረፈ ሰው ነበር፡፡
ሳንፎርድና(ግራ) ዐፄ ኃይለ ሥላሴ በደምበጫ ግንባር(ጎጃም)
ዳን ሳንፎርድ አዲስ አበባን ለቅቆ ወደ እንግሊዝ የተመለሰው ጣልያኖች ኢትዮጵያን ሲወርሩ ነበር፡፡ አሁን ከጡረታ ተጠርቶ የዚህ የኢትዮጵያ ተልዕኮ መሐንዲስ እንዲሆን ተደረገ፡፡ መጀመሪያ ወደ ካይሮ ከዚያም ወደ ካርቱም በመምጣት ከሌሎች የውትድርና ባለሞያዎች ጋር ዕቅዱን ነደፈ፡፡ ዊንሆልት ካርቱም የደረሰው በዚህ ጊዜ ነበር፡፡ ዳን ሳንፎርድ በጎጃም በኩል ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ከአርበኞች ጋር ሆኖ ጣልያንን ለመውጋት ሲያስብ በደቡብ አፍሪካው የደፈጣ ውጊያ ጊዜ አንድ እጁ ጉዳት የደረሰበት ዊንሆልት እዚያው ሆኖ እርሱም ከአርበኞች ጋር ተቀላቅሎ የደፈጣ ውጊያ ለመቀጠል እየተሟሟቀ ነበር፡፡
ሳን ፎርድ በገለባት በኩል ወደ ኢትዮጵያ ለመዝለቅ የነበረው ዕቅድ ጣልያኖች ገለባትን በመያዛቸው ምክንያት ከመተማ 19 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደ ምትገኘው ሌሞና ተዛወረ፡፡ ጣልያኖችና ባንዳዎች ከቋራ እስከ መተማ ያለውን ቦታ መሽገውበት ነበር፡፡ ከእንግሊዝ የምሥራቅ አፍሪካ እዝ የመጨረሻውን መመሪያ ሲጠባበቅ የነበረው ኮሎኔል ሳንፎርድ በኦገስት 6 ቀን ዶቃ ከሚገኘው ካምፕ 54 በቅሎ፣ 36 አህዮች፣ ስድስት ገመድ አልባ መገናኛዎች፣ 13303 ጠመንጃዎች፣ 3 ሪቮልቨሮች፣ 30 አሮጌ ጠመንጃዎች፣ ከአራት የእንግሊዝ ወታደሮች፣ ከአንድ ሐኪምና ከአንድ የራዲዮ ሠራተኛ ጋር ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ተነቃነቀ፡፡ ሳንፎርድ ዊንሆልትን በዶቃ ካምፕ ትቶት ነበር የመጣው፡፡
በአንድ በኩል ይህ የተደረገው እነ ሳን ፎርድ መንገዱን ከጠረጉ በኋላ ዊንሆልት እንዲከተላቸው በማሰብ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ያን ጊዜ ዊንሆልት ገና የመጓጓዣ አጋሰሶችን አላዘጋጀም ነበርና፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የዊንሆልት በዶቃ ካምፕ መገኘት ከሌላኛው መኮንን ከሮኒ ክሊችሌይ ጋር አለመጣጣም አስከትሎ ነበር፡፡ የመረጃ ሰው የሆነው ክሊችሌይ ዊንሆልት አርጅቷል ብሎ አስቧል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ለመዝለቅ ያለውን ጉጉትና ከሲልቭያ ፓንክረስት ጋር ስለሠራው ሥራ ደጋግሞ ማውራቱን አልወደደውም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እርሱ ራሱ በዚያ ጊዜ ጥቂት በእድሜ ገፍቶ የነበረው ሳን ፎርድ ዊንሆልትን ‹አርጅቷል› ብሎ በማሰብ በተልዕኮው ውስጥ ማካተት አልፈለገም ነበር፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ዊንሆልት አንድ እጁ በሚገባ አይሠራም፡፡
ዊንሆልት ግን ሁሉንም ትቶ 11 አህዮችን፣ ስድስት የታጠቁ የኢትዮጵያ ወታደሮችንና አንድ ሱዳናዊ  ምግብ አብሳይ አዘጋጀ፡፡ በ1940 እኤአ፣ ኦገስት 31 ቀን ሳን ፎርድ የሄደበትን መንገድ በመተው ዊንሆት ከመተማ በስተደቡብ ወደ ቋራ አቅጣጫ የሱዳንን ድንበር ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ጀመረ፡፡ በመንገድ ላይ የተወሰኑትን ኢትዮጵያውያን ወታደሮችና ሱዳናዊውን አብሳይ ቀነሳቸው፡፡ ሁለት አገልጋዮችንና ሦስት አህዮችን ብቻ በመያዝ ጠመንጃውን እንደ አገሬው ሰዎች በትከሻው ወደ ታች አጋድሞ ጉዞ ቀጠለ፡፡ ከመነሣቱ በፊት ሊሄድ ያሰበበት መንገድ ለጣልያን ያደሩ ባንዳዎች የሚገኙበት አደገኛ መንገድ መሆኑን ተነግሮት ነበር፡፡ እርሱ ግን አልተቀበለውም፡፡ እንዲያውም መጣቢያ በምትባል ጣቢያ 50 የጣልያን ወታደሮችና 300 የአካባቢው ተወላጅ ባንዶች ካምፕ መሥርተው አካባቢውን እየቃኙ ነበር፡፡
ጉዞ ወደ ኢትዮጵያ
ዊንሆልት ኦገስት 31 ከሌሎቹ የእንግሊዝ መኮንኖች ተለያይቶ በቋራ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ከዘለቀ በኋላ ድምፁ ጠፋ፡፡ ሳንፎርድም ዊንሆልት ወደ እርሱ ዘንድ አለመድረሱን ገለጠ፡፡ በገለባትና በካርቱም የሚገኙ የእንግሊዝ ሚሲዮኖች ዊንሆልት የት እንደገባ ለማወቅ አልቻሉም፡፡ የዊንሆልት ዜና ከተሰማ 15 ቀናት አለፉ፡፡ ሴፕቴምበር 15 ቀን 1940 ከዊንሆልት ጋር አብረው ሄደው የነበሩ ሁለት ሰዎች  በዶቃ ካምፕ ተገኙ፡፡ በካምፑ የነበሩት ቴሲገርና ላውሬ የተባሉ ሁለት የእንግሊዝ መኮንኖች የዊንሆልትን ዜና ጠየቋቸው፡፡ ኢሳ አቡ ጂያር እንደተናገረው ከሆነ ይመራቸው የነበረው ሰው የጉሙዝን አካባቢ እያቋረጡ እያሉ ጠፋባቸው፡፡ በዚህም ምክያት በመጣቢያ አካባቢ ካምፕ ሠርተው ተቀመጡ፡፡ በዚህ መካከልም አንድ ቀን በድንገት ከአራቱም አቅጣጫ ተኩስ ተከፈተባቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ዊንሆልት ጠመንጃውን ለአስተርጓሚው አሸክሞት ነበር፡፡
ሁለቱ አገልጋዮቹ ተኩሱን ሲሰሙ እየሮጡ በየአቅጣጫው ጠፉ፡፡ መሣሪያ ያልያዘው ዊንሆልት ብቻውን ቀረ፡፡ ከዚህ በኋላ ያለውን ኢሳ አቡ ጂያር የሚያውቀው ነገር አልነበረም፡፡ እርሱ አምልጦ ወደ ዶቃ ገብቷል፡፡ ሁለቱ የእንግሊዝ መኮንኖች ይህንን ሪፖርት ሲያስተላልፉ ሌላ ዘገባ ከገለባት መጣላቸው፡፡ ‹‹ሌፍትናንት ዊንሆልት በብዙ ችግር ወደ ሰራቆ ደርሷል፡፡ ፊታውራሪ ወርቁ ስንቄም አስፈላጊውን ነገር ረድተውት ወደ ጎጃም አምርቷል›› ይላል፡፡ ነገር ግን ዊንሆልት ወደ ጎጃም ዘልቆ ሊታይ አልቻለም፡፡ በኋላ እንደተረጋገጠውም የገለባቱ ዘገባ ትክክል አልነበረም፡፡
ከወራት በኋላ እንግሊዞች በአካባቢው ባደረጉት አሰሳ ዊንሆልት ይጠቀምበት የነበረውን  ሄልሜት፣ የተበጫጨቁ ልብሶቹንና ይዞት የነበረውን ቦርሳ(ኪት) አገኙት፡፡ አሳሽ ጓዱም ዊንሆልት መጀመሪያ ተመትቶ ወደ ጫካ በመግባት በዚያው ሳይሞት እንዳልቀረ ገመተ፡፡
ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የዊንሆልት ባለቤት በካርቱም ያለውን የእንግሊዝን ሚሲዮን የባሏን መጨረሻ እንዲያሳውቃት ጠይቃ ነበር፡፡ በጁላይ 8 ቀን 1941 እኤአ ከጋላባት የተነሡ እንግሊዝ ወታደራዊ አሳሾች ዊንሆልት የሄደበትን መንገድ ተከትለው እነዚያ ሁለት አብረውት የተጓዙ ሰዎች ካምፕ ሠራንበት ወዳሉት ቦታ ተንቀሳቅሰው ነበር፡፡ በአካባቢው የተገኙ መረጃዎች እንደጠቆሙት ጣልያኖች የዊንሆልትን መምጣት በማወቃቸው በመንገዱ ተከትለውታል፡፡ በመጨረሻም ካምፑን በመውረር ተኩስ ሲከፍቱባቸው ዊንሆልትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ካምፑን ጥለው ጠፉ፡፡ ጣልያኖችና ባንዶችም ወደ ካምፑ ገቡ፡፡
ከዓይን እማኞችና በጊዜው ከነበሩ የአካባቢው ሰዎች ያገኘውን መረጃ ይዞ አሳሹ ጓድ ከመጣብያ የአራት ወይም የአምስት ሰዓት መንገድ ወደሚርቀውና ከሺንፋ ወንዝ አጠገብ ወደነበረው የዊንሆልት ካምፕ ቦታ ደረሰ፡፡ በአካባቢው በተደረገው ምርመራ የአህዮች አጥንት፣ የተተኮሱ ጥይቶች ቀለሃዎችና የጫማ ቅሬቶች ተለቀሙ፡፡ በአቅራቢያውም የጥርስ መፋቂያና ቦት ጫማ ተገኘ፡፡ ካምፑ ነበረበት ከተባለው 300 ያርድ ርቀት ላይም በመበስበስ ላይ የነበሩ የሰው አጥንቶች ታዩ፡፡ ምናልባትም የቆሰለው ዊንሆልት እዚህ ድረስ ተጉዞ ይሆናል ለሞት እጁን የሰጠው፡፡
ካርቱም የሚገኘው የዊንሆልት የመታሰቢያ ሐውልት 
ይህ ሪፖርት ሲድኒ ሲደርስ የኩዊንስ ላንድ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ኦክቶበር 10 ቀን 1941 እኤአ የዊንሆልትን መሞት በይፋ ዐወጀ፡፡ ቋረኛው የአውስትራልያ ሰውም የኢትዮጵያን ነጻነት ሳያይ ቋራ ላይ ቀረ፡፡ አንደኛው ቋረኛ(ዐፄ ቴዎድሮስ) ለእንግሊዝ እጄን አልሰጥም ብሎ በጀግንነት ሞተ፡፡ ሌላኛው ቋረኛም ኢትዮጵያን ነጻ አወጣለሁ ብሎ በሀገሬው ባንዶች ተገደለ፡፡ ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር እንዲህ ነጭ ከጥቁር ዋጋ ከፍሎባታል፡፡ ኢትዮጵያ እንግሊዞች፣ ኩባዎች፣ አውስትራልያዎች፣ ዐረቦች፣ አይሁድ፣ ሱዳኖች፣ ሩሲያዎች፣ አሜሪካኖች፣ ግሪኮችና ሌሎች ዋጋ ከፍለው ሀገር ያደረጓት ሀገር ናት፡፡ እንኳን የተወለዱባትን ያወቋትን ሰዎች ሕይወት የምታስገብር ሀገር፡፡
 ከፐርዝ ወደ ሜልበርን፣ ኳንታስ አውሮፕላን ላይ

23 comments:

 1. ......ኢትዮጵያ እንግሊዞች፣ ኩባዎች፣ አውስትራልያዎች፣ ዐረቦች፣ አይሁድ፣ ሱዳኖች፣ ሩሲያዎች፣ አሜሪካኖች፣ ግሪኮችና ሌሎች ዋጋ ከፍለው ሀገር ያደረጓት ሀገር ናት፡፡ እንኳን የተወለዱባትን ያወቋትን ሰዎች ሕይወት የምታስገብር ሀገር፡፡ ...........

  ReplyDelete
 2. Wow amazing story please keep up on dani

  ReplyDelete
 3. "እንኳን የተወለዱባትን ያወቋትን ሰዎች ሕይወት የምታስገብር ሀገር፡፡ "

  ReplyDelete
 4. ካርቱም የሚገኘው የዊንሆልት የመታሰቢያ ሐውልት What a pity no statue in Ethiopia for him

  ReplyDelete
 5. አይ ኢትዮጵያ ባዕድ እናቴ ሲልሽ
  ባትወልጅውም ለክብሽ ሲሞትልሽ
  የአለም ብርሀንነትሽን ሲያጸናልሽ
  ጥቁር ነጩ ሲቆምልሽ
  ምነዋ ዛሬ ልጆችሽ
  የስር መሰረት ብቃዮችሽ
  ባንድነትን መረጡ
  ለአረብ ሊሠጡሽ ቋመጡ???
  ምነዋ አጥር ቅጥርሽን
  አንድ ያደረገ ፍቅርሽን
  መተሳሰብ ውድሽን
  ሊንዱት ሹ ግንብሽን
  “እናትህ ናት ሀገርህ
  ሚስትህም ናት ሀገርህ
  እህትህ ናት ሀገርህ
  ልጅ ውድህ ናት ሀገርህ
  እምነት ጽናት መክበሪያህ
  ሁለመናህ መለያህ”
  ብለው ያሉት አዋጁ
  አባቶቻችን ሲበጁ
  ወደየት ገባ ሀገሬ
  ከትውልዱ ዛሬዛሬ???

  ReplyDelete
 6. አይ ኢትዮጵያ ባዕድ እናቴ ሲልሽ
  ባትወልጅውም ለክብሽ ሲሞትልሽ
  የአለም ብርሀንነትሽን ሲያጸናልሽ
  ጥቁር ነጩ ሲቆምልሽ
  ምነዋ ዛሬ ልጆችሽ
  የስር መሰረት ብቃዮችሽ
  ባንድነትን መረጡ
  ለአረብ ሊሠጡሽ ቋመጡ???
  ምነዋ አጥር ቅጥርሽን
  አንድ ያደረገ ፍቅርሽን
  መተሳሰብ ውድሽን
  ሊንዱት ሹ ግንብሽን
  “እናትህ ናት ሀገርህ
  ሚስትህም ናት ሀገርህ
  እህትህ ናት ሀገርህ
  ልጅ ውድህ ናት ሀገርህ
  እምነት ጽናት መክበሪያህ
  ሁለመናህ መለያህ”
  ብለው ያሉት አዋጁ
  አባቶቻችን ሲያበጁ
  ወደየት ገባ ሀገሬ
  ከትውልዱ ዛሬዛሬ???

  ReplyDelete
 7. በጣም የሚገርም ታሪክ ነው፡፡ የዊንሆልት ታሪክ በእውነት ከአርበኞች ታሪክ ጋር አንድ ላይ ሊዘከር የሚገባው ነው፡፡

  ReplyDelete
 8. እንኳን የተወለዱባትን ያወቋትን ሰዎች ሕይወት የምታስገብር ሀገር፡፡ "
  ድንቅ ታሪክ

  ReplyDelete
 9. እንደምን ሰነበትህ ዲ/ን ዳንኤል መንገድ እንዴት ነው? እመ ብርሃን ትከተልህ
  የጻፍኸውን ጽሁፍ አንብቤዋለሁ በጣም የሚገርም ታሪክ ነው ለዚህች ሃገር ያልሞተላት የለም ለካ ግን ራሴን ባዶነት ተሰማኝ ምን እንደሰራሁላት ብጠየቅ መልስ የለኝም ይመስለኛል እስኪ ከዚህ ተምረን አንድ ነገር እንድናደርግ ፈጣሪ ልብ ይስጠን፡፡

  ReplyDelete
 10. ጥሪ
  አንዱን ከማህፀን ሌላውን ከእቅፍ፣
  አንዱን ከእረኝነት ወይም ከእርሻ ከእርፍ፣
  ሌላውን ከግንባር ከጦር ከሞት አፋፍ፡፡
  ወይ ደግሞ ከትምህርት ከምርምር ቦታ፣
  አለዚያም ከጥፉው ከሥጋ ገበታ፣
  ወይም ከጥፋት ዕቅድ ከይጥፉ ሁካታ፡፡
  ይለያል ለምህረት ያንጻል ለሕይዎት፣
  ሁን ላለለት ዕቅድ ለመረጠው ተምኔት፣
  እሽ በጄ ብሎ ታምኖ ላመነለት፡፡
  ዳንየ! እያትና ከሆነች እንደምትሆን አድርጋት

  ReplyDelete
 11. Very Amassing History. Thank you Daniel

  ReplyDelete
 12. dan silew ethiopia wst mote: yekalkidan tekafay new.

  ReplyDelete
 13. Nafesone yemarawe
  Sawe batakadasa bota yekadasale
  Dani ejehe yebarak

  ReplyDelete
 14. ለሚበረታቱብን አይስጠን እንጂ አሁንማ እንደዚህ አይነት ትውልድ የሚኖረን የልሎች አገር ዜጎችም አንደ ባለታሪኩ የሚወድቁላት አይምስለኝም ለምን ቢባል በሰው ሀገርም ሄደን አልተስማማንም

  ReplyDelete
 15. Dani I was very impressed by this story.What we did for our beloved country?Thanks Dani.I have nothing to say more than this.God bless you.

  ReplyDelete
 16. AMEN LB YSTEN. DANI BERT BESELAMA YMELSH.

  ReplyDelete
 17. it was a bravilage to know d.c daniel kibret ,i learn so much from you ,god bless you have a safe trip to your family.

  ReplyDelete
 18. SUDANOCH METASEBYA SERULET ... ETHIOPIA WEYAN GEN ENKAN HAWET MAKOMU KERTO SEMUN ENKAN BE MIGEBA ALANESANEWM ... BE EWNET ECHI HAGER KEDST NAT ... YAHULU YEHONEW ... MOLEKOTAWI SRA YELWEM BELACHU TAMNALCH ... EMBERHAN SMWA YEMSEGEN AGERWA TASKEBRALECH .... D.C DANIEL ANTE SEW NEH AMESEGNHALEW ... JEGNA WEDAJI ENDAWEK ADERGEHNGAL ENA ... YEKARAW AMBESA YEWLEDWE JEGAN NEW

  ReplyDelete
  Replies
  1. በጣም ግሩም የሆነ ዘገባ ነው

   Delete
 19. ay egna ahunm yelenem mutenal eko ygermal ke wuch meto liredan sil egnaw gedelew

  ReplyDelete
 20. This Hero really impressed me. I don't now such touching history. God may let his soul in the heaven; together with Abraham, Issac and Jacob. Amen.

  ReplyDelete