Tuesday, August 27, 2013

ጌሾና ጫት - በአውስትራልያ

አሁን አብዛኛው አውስትራልያ የገባ ኢትዮጵያዊ በሚገኝባት የሜልበርን ከተማ ውስጥ አበሻው ሰብሰብ ብሎ በሚኖርባትና በሚሠራባት ፉትስክሬይ በተባለችው መንደር እንገኛለን፡፡ ይህች የሜልበርን ምዕራባዊ ቀበሌ የሆነች መንደር ጥንት የኤስያውያን መናኸርያ ነበረች ይባላል፡፡ ዛሬ ግን ዋናዋ የአፍሪካውያን ስደተኞች መሰባሰቢያ ናት፡፡ በዚህች ከ74000 ትንሽ ከፍ የሚል ሕዝብ በሚኖርባት መንደር ውስጥ ከ135 ሀገሮች የመጡ ስደተኞች ይኖሩባታል፤ ከ85 ቋንቋ በላይ ይነገርባታል፡፡ እንዴው መርካቶ በሏት፡፡
በአውስትራልያ ታሪክ የመጀመሪያው የእንጀራ መሸጫ ሱቅ የተከፈተው እዚህ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እዚህ ሀገር እንጀራ በዋናነት ከስንዴ ወይም ከሩዝ ዱቄት ተቦክቶ የማሽላ ዱቄት ይቀላቀልበታል፡፡ የታደሉት ደግሞ ከሀገር ቤት የመጣ የጤፍ ዱቄት ለአመል ይጨምሩበታል፡፡ ስፋቱ የአገር ቤት እንጎቻ የሚያህል ሲሆን ውፍረቱ የሰንበት ቂጣ ታናሽ ወንድም ነው፡፡ ኮከብ የመሰለ ዓይን ባያገኝም፣ ሞጭሟጫ ከመባል ለጥቂት ይተርፋል፡፡ በብዛት የሚጋገረው ከብረት በተሠራ ምጣድ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ግን ከሀገር ቤት የሸክላ ምጣድ የሚያመጡ አሉ፡፡ ሳይሰበር ከደረሰላቸው፡፡

በፉት ስክሬይ ከደርዘን በላይ የኢትዮጵያውያን ሱቆች፣ ከአምስት በላይ ምግብ ቤቶች እንዳሉ ይነገራል፡፡ በአካባቢው ስትዘዋወሩ ቢያነጥሳችሁ ‹ይማርህ› የሚል አታጡም ይባላል፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያን እናቶችና አባቶች ስለሚዘዋወሩበት፡፡ በርግጥ ወጣቶቹና ጎልማሶቹ እንዲህ ያለ ነገር አያውቁም፡፡ የሚገርማችሁ እንዲያውም እዚህ አካባቢ አበሻና አበሻ ሲገናኝ ቁጣ እንጂ ሰላምታ አይሰጣጥም፡፡ ሁለቱም ፊታቸውን ኮስተር አድርገው ነው የሚተላለፉት፡፡ እኔ እንዲያውም ‹እዚህ ሀገር የመጣው ያኮረፈው ተመርጦ ነው እንዴ› ብዬ ነበር፡፡
በፉት ስክሬይ የሚጠፋ ቅመማ ቅመም የለም፡፡ በተለይም ሕንድ ሱቅ ውስጥ በሀገራችን የጠፋው ቅመም ሁሉ ይገኛል፡፡ ሞያ በሜልበርን በሽ በሽ ነው፡፡ በርበሬ ከሀገር ቤት ለማስመጣት የአውስትራልያ የምግብ ሕግ ሲያስቸግር እዚሁ ሌላ በርበሬ ተፈጥሯል፡፡ ከሕንዶች ሱቅ የሚገዛ የሚያቃጥል ቀይ ቃሪያ አለ፡፡ እርሱን በኮረሪማ መፍጫ መፍጨት ነው፡፡ ከዚያ ደግሞ ቅመማ ቅመሙን ለብቻ ፈጭቶ መጨመር፡፡ በመጨረሻም አውስትራልያ ሠራሽ ምርጥ ድልህ ይሆንላችኋል፡፡
 አንድ ወዳጃችን ‹ሽሮ እኛን ስላሳደገች በክብር ጡረታ ወጥታ ትቀመጥ› ቢልም ከሀገር ሲወጡ አንዱ የሚናፍቀው ግን ሽሮ ነው፡፡ በአውስትራልያ ልዩ የሆነ የሽሮ አዘገጃጀት ተፈጥሯል፡፡ የባቄላው ዱቄት ከሕንድ ሱቅ ይገዛል፡፡ ከዚያም አመስ አመስ ይደረጋል፡፡ ለቅመማው አስፈላጊ የሆነውን ቅመምም ሕንዶቹ ያመጡታል፡፡ እርሱንም በቡና መፍጫ ፈጭቶ በመጠኑ ማመስ ነው፡፡ ከዚያም ሁለቱን በባለሞያ እጅ ደባልቆ ምርጥ የውጭ ሀገር ሽሮ ማግኘት፡፡ ችግር ብልሃትን ይፈጥር የለ፡፡
   ለኢትዮጵያውያን እዚህ አንዱ ፈተና ከሀገር ቤት ባህላዊ ምግቦችን ማስመጣት ነው፡፡ የሀገሩ ሕግ ጥብቅ ስለሆነ፡፡ ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ ግን እንደ ካልዲ(የቡናን ፍሬ ያገኘው እረኛ) አዳዲስ ቅጠላ ቅጠሎችን የሚያገኙ ኢትዮጵያውያን እዚህ ሞልተዋል፡፡ አንድ ቀን ነው አሉ፡፡ መቼም እኛ ታሪክን በጊዜና በሰዓት የመመዝገብ ችግር አለብን፡፡ (ተረቱም ታሪኩም ከዕለታት በአንድ ቀን ብሎ ነው የሚጀምረው) አንዲት የሀገሬ ሰው በግቢዋ ውስጥ ስትዘዋወር አንድ የምታውቀውን ቅጠል የሚመስል ነገር ታያለች፡፡ ጠጋ ብላ ቆረጠችውና መዳፏ ላይ አሸችው፡፡ ልክ ነው፤ እርሱ ነው፡፡ ወስዳ ለጓደኛዋ አሳየቻት፡፡ ሁለቱም ርግጠኞች ሆኑ፡፡ ጉዳዩን ወደ ልጅቱ እናት ‹ሪፈር› አደረጉት፡፡ እርሳቸውም እየተገረሙ ‹እርሱ ነው› አሉ፡፡ ለካስ ጌሾ ኖሯል፡፡ ጠላ ለመጥመቅ ችግር የነበረው ጌሾ በአውስትራልያ ምድር በቅሎ ተገኘ፡፡ ዛሬ በብዙ ኢትዮጵያውያን ግቢ ውስጥ ጌሾ በቅሎ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡
በዚህች ምድር በቅሎ የተገኘው ግን ጌሾ ብቻ አይደለም፡፡ መቼም አገር ደግ ነገር ብቻ አታበቅል፡፡ አንድ ወዳጃችን ሁል ጊዜ አንድ ቦታ እየሄደ ቅጠል ሸምጥጦ ሲወጣ ይታያል አሉ፡፡ መጀመሪያ አካባቢ ማንም ከቁም ነገር አልወሰደውም ነበር፡፡ በኋላ ግን ሸምጣጩ በዛ፡፡ የአካባቢው ሰዎችም ግራ ገባቸው፡፡ በከተማዋ ውስጥም ወሬው ተባዛ፡፡ የሚሸመጠጥበት ቦታም በአንዳንድ ሰዎች መዘውተር ጀመረ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ከሥሩ እየነቀሉ ወስደው በጓሯቸው ተከሉት፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የአውስትራልያ ፖሊሶች ጉዳዩን ሰሙትና ክትትል አደረጉ፡፡ ለካስ ያ በወፍ ዘራሽ በቅሎ አገር እየተራኮተ የሚሸመጥጠው ጫት ኖሯል፡፡ ፖሊሶቹ እዚያ ቦታ የነበረውን መድምደው አጠፉት፡፡ ችግሩ ግን እነርሱ ሳይደርሱ በፊት በየግቢው ተዛምቷል፡፡ አንዳንድ ቤት ስትሄዱ ጫት በኩራት በቅሎ ታዩታላችሁ፡፡
ፉት ስክሬይ በአበሾች ዘንድ ከምትታወቅበት ሀብቷ አንዱ ምርጥ የሆነ ቁርጥ ሥጋ መሸጫ ስለሆነች ነው፡፡ መቼም ቁርጥ እየበላን ቁርጥ ነገር አለመቻላችን የሚገርም ቢሆንም የሀገሬ ሰው የትም ቦታ ቢሄድ፣ ምንም ዓይነት ትምህርት ቢማር ሊያጣው የማይፈልገው ነገር ቢኖር ቁርጥ ሥጋ ነው፡፡ ከነአባባሉም ‹የተማረ ሰውና የተሳለ ቢላዋ ሥጋ አያጣም› አይደል የሚባለው፡፡ እዚህ ከተማ በጥሬ ሥጋ ሻጭነታቸው የታወቁ ቤቶች አሉ፡፡ ነጭ፣ ቀይ፣ ጎድን፣ ዳቢት፣ ሻኛ፣ ለቁርጥ፣ ለወጥ እያሉ የሚያስተናግዱ፡፡ እነርሱ ጋ ገብቶ አለበለዚያም ደግሞ ሰፈር ይዞ መጥቶ ቁርጥ በኅብረት መብላት እዚህ የተለመደ ነው፡፡ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ወደ አውስትራልያ ዘመድ ለመጠየቅም ሆነ ለመዝናናት የሚመጡ ኢትዮጵያውያን በአውስትራልያ ቁርጥ ፍቅር ተነድፈው ነው የሚመለሱት፡፡ አንዳንድ የአውሮፓና የአሜሪካ ወዳጆቼ ጋር ስንጻጻፍ እንዲያውም ‹የአውስትራልያን ቁርጥ ሳትበላ እንዳትመጣ› ይሉኛል፡፡ እስቲ ቀምሼ እመሰክርለታለሁ፡፡
‹አይ እኔ ማን እንደነካው የማይታወቅ ሥጋ አልበላም› ለሚሉ አለያም ደግሞ ‹የተሸረፈ ጥርስ፣ ደልደል ያለም ላት አይቶ መርጦ ተከራክሮ መግዛት› ለሚያምራቸው ወደ ገጠሩ ክፍል ወጣ ማለት ነው፡፡ ከበግ አርቢ ገበሬዎች ጋር ምን የመሰለ የደብረ ብርሃን በግ ይገኛል፡፡ ማረዱን ባይፈቅዱላችሁም መባረኩን ይፈቅዱላችኋል፡፡ እነርሱ ደግሞ ገፍፈውና ቆራርጠው ይሰጧችኋል፡፡ ከዚያ በኋላማ ‹አቤት ባለፈው ለፋሲካ የገዛሁት ምን የመሰለ በግ› እያላችሁ ሾላ ገበያ የሄዳችሁ ማስመሰል ነው፡፡ 
ሜልበርን አውስትራልያ፡፡

27 comments:

 1. wow dani great view

  yonas from dallas

  ReplyDelete
 2. ወይ ዳንኤል ዘጣና ዳር!

  ReplyDelete
 3. Wey gud ezam abesha endetekuarefe now? Ene lemejemeria gize american heger habesha sagegn betam desblogn roche heje selam alkut.lju betam gra gebaw ENDIH yale selamta keyet meta blo. mknyatum ayawqegnma.abragn yeneberechw betam sqa ayzoh atchekul hulunm tderdbetaleh alechgn.Ahun amet honognal yalechwn betegbar ayehut.heger bet hogne keakste gar menged lay sn
  hed akste yemtawqewnm yematawqewnm tnshunm tlqunm selam slemtl betam enadedbatna selamta endatabeza enegrat neber.esua gn selamta ye egzer msa ena erat now tlegn neber.ewnet now selamtaw endemn aderachhum hone walachhu melsu EGZIABHER YMESGEN now. Slezih selam yemilen sew egziabhern endnamesegnew mknyat slehone des lilen ygebal enji lnakorfew aygebam.bemengedachn lay yeqerebelnn yemsgana meswat tlen egziabhern lemamesgen betekrstiyan weym mesgid flega ymnrot egzisbher endemitazeben anzenga.

  ReplyDelete
 4. ዳኒ ወዳጄ የአውስትራሊያ ቁርጥ ልትበላ መሆንህን በዚህ የጉዞ ማስታወሻህ ላይ ነገርከኝ ቁርጡን ስታስቆርጥ አንድ ወንድማዊ ምክር ልምከርህ ከማያቆራርጠው ቁረጥልኝ በለው አለበለዚያ እኔና አንተም ፉት ስክሬ ላይ ተኮራርፈን መተላለፋችን ነው። እኔ ምለው ቁርጥ እያበላችሁ ጉድ ያደረጋችሁን የኮሚኒቲ የጀርባ ሹማምንቶች ይብላኝ ለናንተ አብልቶ ለሚበላ ሃሳብ ለተጠናወታችሁ

  ReplyDelete
 5. ሽሮ እኛን ስላሳደገች በክብር ጡረታ ወጥታ ትቀመጥ

  ReplyDelete
 6. ዳኒ በጣም የሚገርም ነው ይህማ ምን አወስትራሊያ ትለዋለህ ኢትዮጵያ በለው እንጂ ለማንኛውም ጤናህን ያብዛልን

  ReplyDelete
 7. ግሩም ነው ። በሰላም ይመልስህ።

  ReplyDelete
 8. እንብላ በሚለዉ ባህላን እንብላ ባትለንም መልካም ምግብ የተባረከ ይሁን ብለናል!

  ReplyDelete
 9. "ሽሮ እኛን ስላሳደገች በክብር ጡረታ ወጥታ ትቀመጥ"

  ReplyDelete
 10. ወጣ ያለ አስተያየት፡-
  ዳንኤልን ከበድ ያለ ሰው ሁኖ አገኘሁት፡፡ በእርግጥ ስለእርሱ የነበረኝ እውቀት የሚጀምረው ከጮርቃ አስራዎቹ ዕድሜው ነበር፡፡ እኔ ደግሞ በዕድሜዬ ከእርሱ እንስ ብዬ ልክ ደቀ-መዝሙር ልሆን የምችልበት አካባቢ ነበርኩ፡፡ ታዲያ ምን ያደርጋል ጠላትህ እልም ይበል ኮሌጅ ከገባህበት ጊዜ በኋላ “እንትን ያረደው ወንዝ የጋረደው” እንደሚሉት አጣሁህ፡፡ እንዳለህ እየሰማሁ ፈጣሪየን ማመስገን እንጂ አንድ ቀን አራት ኪሎ ላይ ከማየት በቀር አንተን ለማግኘት ምንም ዕድል አልነበረኝም፡፡ ያኔም ግርግር በዝቶ ወዳጀን ሰላም ሳልልህ በመቅረቴ እስከዛሬ ድረስ ሆድ ሆዴን ይቆርጠኛል፡፡ መቼስ የማልረሳው ነገር ከልጂነትህ ጀምረህ ጊዜህን በቁምነገር ላይ ማዋልህ፣ አስበህ መናገርህ፣ አጥንተህ ማቅረብህ ስለሚማርኩኝ አንተ አንድ ነገር ማቅረብ ስትጀምር አፌን እንደከፈትሁ ለቀጣዩ ተናጋሪ እንኳ አፌ እንደተከፈተለት ነበር የሚቀረው፡፡
  እንደዛሬው ሁሉም ነገር በደጅ ሁሉም ነገር በእጅ ባልነበረበት በዚያን ጊዜ አንተው ጋዜጠኛዬ፣ አንተው ደራሲዬ፣ አንተው ተመራማሪዬ አንተው የልጅ ምሁሬ እንደነበርክና ወደነዚህ ነገሮች ሁሉ እንደመራኸኝ አንተ አታውቅ ይሆናል፡፡ ግን ነበርክ፡፡ መቸም በዚህ “ብሎግ” ካገኘሁህ በኋላ ልክ እንደ ጥንቱ ቅዳሜዬና እሁዴ በስስት መመልከት ጀምሬአለሁ፡፡ አንዳንዱ እጅ ያልታደለ ሁኖ ወደ ክፉ አቅጣጫ ሲጠቁም አንዳንዱ ደግሞ ሳያስብበት እንኳ ወደ መልካም አቅጣጫ ይመራል፡፡ እኔንም ወደ አንተ “ብሎግ” የመራኝ እንደዚህ ዓይነቱ እጅ ነው፡፡
  በቅርብ ቀን አንዱ በሰፈራችን ልጆች ”ፌስ ቡክ ግሩፕ” ውስጥ ያለ አንዲት ነገር “ሊንክ” ያደርግልንና እርሷን ማንበብ፡፡ የማን ትሁን ከምን ትሁን ሳላውቃት እንደጣፈጠችኝ ጭልጥ አድርጌ አንብቤ ጨረስኳት፡፡ በእግርጌዋ ላይም ዳንኤል ትላለች፡፡ ከዚያ ብዙም ሳልቆይ ዳንኤል ክብረት ብዬ ስጠይቀው ሰማዩን ሁሉ እንደሞላ¤ው አወቅሁ፡፡ ከዚያ ሙልጭ አድርጌ አንብቤ ጨረስኩልህ ብልህ ታምነኛለህ፡፡
  እኔ ግን ዛሬ እንደገና ልጽፍልህ የወደድኩት ሌላ ስብዕና ደግሞ ስላገኘሁብህ ነው፡፡ ከጥበብ ባለፈ የውስጥ ስብዕና ማበልጸግህ፡፡ በጣም ዴሞክራት ሁነሃል፡፡ ድሮ አልነበረክም እንደማለት ካልተወሰብኝ በቀር፡፡ በጣም ዴሞክራት፡፡ እንደነገርኩህ ሙልጭ አድርጌ ነው ያነበብኩት ስልህ የተሠጠህን አስተያየት ጨምሬ ማለቴ ነው፡፡ መቸስ በየጊዜውና በየወቅቱ ለተከታተለው ሰው ቀላል - እጅግ ደካማ አስተያየት ይመስላል፡፡ እንደእኔ እድሉን አግኝቶ - የጊዜ ዕድል ማለቴ ነው አስተውሎ እንደአንድ ወጥ ላነበበው፤ በጣም ዘግናኝ በጣም አሳፋሪ በጣም ተስፋ አስቆራጭ ጩ¤ቶችን ተመልክቻለሁ፡፡
  እኔን ያስደነቀኝ ይህ አይደለም፡፡ እኔን ያስደነቀኝ በ“አነኒመስ” የተሰጠህን አስተያየት በ”ፕሩፍ ሪድ” እየፈተሸህ የምትወደውን መለጠፍ የምትጠላውን ወደራሱ መመለስ ትችል የነበረበትን እድል አለመውሰድህ ነው፡፡ ከዚያም በተረፈ “ይቅርታ” ለመጠየቅ የሚያስገድድህ ጉዳይ ካልሆነ በቀር መልስ ለመስጠት ገመድ ጉተታ ውስጥ አለመግባትህም አስደንቆኛል፡፡ ስለአንተ ለመሟገት የምላስ ጩቤ የሚመዙትንም በማየት ምንያክል የማይታገሱት አስተያየት እንደሆነ እገምትና አንተ ግን ጸጥ ረጭ! ጥበብን ስታሳድግ ስብዕናንም እንዳልረሳህ አስተዋልሁ፡፡
  ይህ መወድስ ሳይሆን አስተማሪነቱን ለማግዘፍ ስለፈለግኩ ነው፡፡ በጣም ያስተምራል፡፡ በተለይ ለመሰደብ ዕድሉን ያገኙ በጊዚያዊ የግልም ሆነ የመንግስት ሥልጣን ላይ ለተቀመጡ ሠዎች ትልቅ ትምህርት፡፡ ያልተገደበ ዴሞክራሲ ማለት እንደዚህ ነው፡፡ ሠው በተፈጥሮው የመተንፈስ ባህርይ ስላለው አምላክ በከፈተለት ቀዳዳ ሁሉ ይተነፍሳል፡፡ ያ ነው ጤንነቱ፡፡ ሲታፈን ግን መርዝ ነው ሲፈነዳ ደግሞ ፍንዳታው ትልቅ ነው፡፡ እንደመጣለት የተነፈሰ ሰው ግን አስፈሪ አይደለም፡፡ ከላይ ከላዩ ስለተነፈሰው የተጠራቀመ የትልቅ ፍንዳታ ኃይሉን አባክኖታልና፡፡ በሳሎቹ ዴሞከራቶች ይህንን ሁሉ ይፈቅዳሉ እንጂ “ጡጥ” ባለቁጥር የአጸፋቸውን ደግሞ “አያንጧጡትም”፡፡
  አሁን ዳንኤል እንደተሰነዘረብህ አስተያየት ቢሆን ኑሮ ዓይንህ ተለውጦ እሳት የሚተፋ ዕሬቶ ኮከብ፣ አፍንጫህ ተቀይሮ የትልቅ መኪና ጭስ ማውጫ፣ ሆድህ ተነፋፍቶ ግዙፍ የቆሻሻ መጣያ፣ እጅህ ተቆልምሞ የዝሆን ቱምቢ፣ ጭንቅላትህ አሞልሙሎ እንደ ደራጎን፤ ከዚያ ሙሉ በሙሉ ማንነትህ ይጠፋና ድሮ የምተነግረንን ዓይነት ጭራቅ ትሆን ነበር፡፡ ነገር ግን ወይ ፍንክች! ይኸው ነው ሰው የፈለገውን እንዲተነፍስ የማድረግ ውጤቱ፡፡ አፈሩን ገለባ ያድርግላቸውና የቀድሞውም ጠቅላይ ሚኒሰትር ብዙ በሚባሉበት ጊዜና በጸጋ ባስተናገዱበት ወቅት ይለመልሙ ነበር፣ እለት በዕለት ይበስሉ ነበር፣ እያደር ያስተውሉ ነበር፡፡ “ዝም በል ” ማለት ሲጀምሩ ግን እያደሩ ውሃ የማይቋጥር ነገር መወትለፍ ጀመሩ፤ ህዝቡም ከአንጀቱ አዘነ መሰለኝ ብዙም አልቆዩ፡፡ አበስኩ ገበረኩ!
  እንግዲህ ሁሉም በየተቀመጠበት ኃላፊነቱ ልክ እንዳንተ ሆዱን አስፍቶ ሁሉንም ቢሰማ ምን ይሆናል ትላለህ?
  በል ዳንኤል ዘጣና ዳር በርታኝ፣ እኔም በጸሎት ከጎንህ እቆማለሁ!
  ከጣን ዳር

  ReplyDelete
  Replies
  1. ዓይንህ ተለውጦ እሳት የሚተፋ ዕሬቶ ኮከብ፣ አፍንጫህ ተቀይሮ የትልቅ መኪና ጭስ ማውጫ፣ ሆድህ ተነፋፍቶ ግዙፍ የቆሻሻ መጣያ፣ እጅህ ተቆልምሞ የዝሆን ቱምቢ፣ ጭንቅላትህ አሞልሙሎ እንደ ደራጎን፤ ከዚያ ሙሉ በሙሉ ማንነትህ ይጠፋና ድሮ የምተነግረንን ዓይነት ጭራቅ ትሆን ነበር፡፡
   Very impressive ...

   Delete
  2. To Daniel ze Tana Daar: Are you sure that Daniel is a democrat. As it looks like you are technologically innocent, you cannot know whether Daniel has concealed the most sensitive comments and is revealing to us only 'gebs gebsun'.

   Bekelalu metalel ayawatam - Daniel ze Tana daar!!

   Delete
  3. ወንድሜ ወይም እህቴ፡-
   እንግዲህ እኔ እስከተመለከትኩት ድረስ "ሠይጣን" ዓይነት ተደርጎ የቀረበበትን ትችት ሳይቀር ከማቅረብ በላይ የትኛውን እንዳስቀረው ማወቅ አልችልም፡፡ ምንአልባት አንተ አስተያየትህን ሰንዝረህ ካላቀረበልህ አንተ ለእራስህ ተጨባጭ ማስረጃህ ሁነህ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደዚህ ከሆነ ደግሞ እራስህን መካድ አልችልም፡፡ በትንሹ እንኩአን ይህንን አስተያየትህን እንዲቀርብ ፈቅዶ ላገኝህ እንድችል ስለፈቀደልህ ላመሰግነው እወዳለሁ፡፡ እንግዲህ ሁሉንም ጽሁፎቹን ለማንበብ ከታደልክና አስተያየቶችንም ለመፈተሸ ከቻልክ ከበሳል እሰከ ፍሬ የሌላቸው ድረስ አስተናግዶአል፡፡ የአስተያየት ሰጩ ግለሰብ የግሉ አመለካከት ሁኖ እስካገኘው ድረስ፡፡ ምናልባትም አንዳንድ አይነኬ ቃላት፣ ለጨዋ አንደበት የሚጎረብጡ፣ አልፎም ሞገስ ላላቸው አንባብያኑ የሚያስጸይፍ ቃላት ያለባቸውን አስቀርቶ ከሆነ የግል የእሴት ስርዓቱ (his value system) ስላልፈቀደለት ይሆናል፡፡ ለምሳሌ በአደባባይ "አላዋቂ ሳሚ 'ምን' ይለቀልቃል" ይባላል እንጂ እንደማይጨረሰው ሁሉ፡፡
   ዳንኤልን እንደ ጥንቱ የማግኘት እድል ባገኝ ኑሮ ያስቀረብህን አስተያየት ከራሱ ጠይቄ ብረዳው ከዚሕ የማያልፍ እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ ምክንያቱም ሌላውን ትችት ሁሉ አስተናገዶ የአንተን ለይቶ በምንም ተአምር ሊያስቀርብህ አይችልም የሚል ግምት ስላለኝ፡፡
   ለምሳሌ አሁን አንተ እኔን በጨዋ ሐረግ አንኳሰኸኛል፡፡ በእንደዚህ ዓየነት አይነት ዘይቤ ካዘጋጀኸው ከማቅረብ ወደኃላ እንደማይል ማስረጃዬ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ዓይነት "ግላዊ" ሽንቆጣ ካቀረብህም ደግሞ ቢያጣራው በእኔ በኩል ዓውዱን ለመንከባከብ ካደረገው ጥበብ ለይቸ አላየውም፡፡
   አለበለዚያ ስለዳንኤል ብቻ የሚዘግብ አንድ "ብላግ" ማዘጋጀት ትችላለህ፡፡
   በተረፈ ሁለት ወጣ ያሉ አስተያየቶች ልስጥና ልጨርስ፡፡ ሁለት ዓይነት ሰዎች አሉ፡፡ አንደኛዎቹ እራሳቸውን ችለው ማሰብ፣ መፍጠር፣ መመራመርና አልፈው ተርፈውም ለመሞከር የሚፍጨረጨሩ ናቸው፡፡ ሌሎቹ ሰዎች ደግሞ እራሳቸውን ችለው ማሰብ፣ መፍጠር፣ መመራመርና ምንም የሚሞክሩት የሌላቸው ናቸው፡፡ ታዲያ አብዛኛውን ጊዜ ሁለተኛዎቹ ሰዎች እራሳቸውን ችለው ከሚንቀሳቀሱት ሰዎች ተጠግተው ተረፈውን የሚቀጥሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ሠዎች ሌላ ጎጅ ተፈጥሮ አላቸው፡፡ ሁልጊዜ ተረፈውን መሙላት ሲመራቸው የእነዚያ እራሰቸውን ችለው የሚኖሩት ሰዎች ሾተል ይሆናሉ፡፡ መገለጫቸውም አፍራሽ ትችት መሰንዘር፣ አይጥምሽ ስሜት ማንጸባረቅ፣ ከጀርባ እየተንቀሳቀሱ ሰው ሁሉ እራሳቸውን የቻሉትን ሠዎች እንዲጠላለቸው ጭቃ መቀባት እና አሁን ልዘረዝርልህ ከምችለው በላይ ጎጅ አመል ይታይባቸዋል፡፡
   ሁለተኛው አስተያየቴ ደግሞ አሁንም ለዳንኤል ነው፡፡ ከትችት ነጻ መሆን የሚችለው ሠው "ገና ያልተወለደው ሠው ብቻ ነው"፡፡ ብትወፍርም - ዘረጦ፣ ብትከሳም - ቋንጣ፣ ብትናገር - ምላሳም፣ ዝም ብትል - ጋግርታም፣ ብታለቅስ - ነፍራቃ፣ ብትስቅ - ግልፍጥ፣ ብትማር - ትምክህተኛ፣ ባትማር - ደንቆሮ፣ ብታገኝ - ሌባ፣ ብታጣ - መናጢ መባልህ አይቀርምና ... (ላንበሳ አይመትሩም ለብልህ አይመክሩምና ሌላውን እራስህ ታውቀዋለህ... ቀጥለው) "ግፋ ወደፊት ያገሬ ጀግና"፡፡ (ከደርጉ ዘፈኖች የተወሰደ)
   ምንጊዜም ቅን ሁን፡፡ መድረሻችን ጽዩን ነው፡፡ የጽዩን መንገደኞች ሊኖራቸው በሚገባው ስብዕና በርትተህ ጉዞህን ቀጥል፡፡
   ሁላችሁም ቻው፡፡

   Delete
 11. abo yidlah dani tiru sew endi endante yimechew

  ReplyDelete
 12. Thank you so much our brother Daniel. Even if we didn't get chance to visit that place God gave us best brother to get information. I lerned so many thing from this site and I am always open your site to see a new thing. Today I learned that how Ethiopian creativety to have their cultural food all over the world. Preparing "Berbera" is not easy when we live abrod but our mother and sister went to other Indian's stores to create "Berbera and Shero" and the did it. know I know how to prepare our cultural food even if not avilable in Ethiopian stores. God bless you and your family brother Daniel for sharing us your day to day expriance that has been given us to know about other countries rule and regulation. If I get a chance to go Australia now I know that they don't allowed to carry "Berbera and shero" I wish you Matusalas's age with peace and pleasure. Sincerly

  ReplyDelete
 13. Hello Brother Daniel
  If this posible with Ethiopia rule and regulation could you posted on your site pleas.
  Who is Liar?
  Our world has been changing day to day with civilization, human being interest and natural disaster. At this time all unexpected things are happing without any prediction. Nobody expected about Meles Zenawi and Abune Paulos death but it happened with the same year while Menegesetu Hailemariam and Abune Markorios are in life. Three years before I read one article about former Libian leader Mohamed Gadafi that explain about his house expensive materials such as his bed cost 2,000,000 dollar that protect him any kind of gun and other dangerous chemicals, shower 100,000 dollar made from gold and expensive marbles, pistil made from gold. However, when he passed away, his dead body pulled by his people on the road, but no African leader learned from this situation, so they are still dictator to lead their people. Right now our country face difficult situation between Government and Muslim. Nine years before while Ali Abdo was Addis Abeba leader all Addis Ababa's open place covered by Mosque and they took most Ethiopian orthodoxies property with power ,in that time nobody say anything about the situation from current government. In addition that, the past twenty years our brothers and sisters killed by Muslim. However the current government didn't take action to stop the situation until we fight back. "All thieves are agreeing when they take by force but they fight when they divide the stuff." My message is to our Ethiopian orthodox leader to stop participating or involving between Government and Muslim fight.

  ReplyDelete
 14. እዚህ ሀገር የመጣው ያኮረፈው ተመርጦ ነው እንዴ› ብዬ ነበር፡፡ mengestachen yametaw cheger eko new Dany

  ReplyDelete
 15. ጦሱ የታል?
  ሰሞኑን ዲ/ን ዳንኤል የአውስትራሊያ ቆይታውን እያስቃኘን ያለበት ሁኔታ ነው ያለው:: {ውይ እኔም ተጋባብኝ ማለት ነው ለነገሩ ከለማበት የተጋባበት ይባል የለ::} እና ምን መሰላችሁ ያ ቅኝቱ ሌላ ጽሑ አስታወሰኝ:: “ የስደት ጦስና ተስፋ” የሚል ጽሑፍ ትዝ ይላችኋል? በነገራችን ላይ መናደድ ካማራችሁ አንብቡት
  http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-24/---mainmenu-27/1293-2013-06-26-07-45-15 መጀመሪያ ላይ ያየሁት በፌስ ቡክ ገጼ ላይ ነበር:: እናም አነበብኩት ከምር ቅር አለኝ:: ምክንያቶቼን ላቅርብ አደለ:: ይኽውላችሁ በቃ አንድም ጦስ አላየሁበትም:: የሚገርመው ከ15 ዓመት በፊት ካገር ቤት የወጣሁት በየአውደምረቱ ዐረብ አገር የምትሄጂ ወዮልሽ እየተባለ ሳለ ነው:: አጋጣሚው ይገርም ይሆናል:: ወዮላችሁ የተባልነው ወጣቶች የዚህ ዘመን ሓዋርያ ነን ባዮቹ ያላደረጉትን እንበለ ደም በዐረብ ምድር የክርስቲያን መቅደስ ተከልን:: ዛሬ ብዙ ነገር ጳጳስ ተመደበልን፣ ቀሳውስት ተላኩልን፣ ሰባኪ ካልመጣሁ እያለ ተሻማብን፣ ለገዳማት ዕርዳታ ለልማት ሥራ የአረብ ሀገራት ደብራትን የማይለምን ማን አለ? ታዲያ ጦሱ የታል?::
  አገሪቱ ምንም በድላን አልተሰደድንም:: እህል እራበን ነጻነት ጠማን፣ እኩልነት የሒሳብ ትምህርት ላይ ያለ ምልክት ብቻ ሆነብን፣ የምንተማመንበት ተቋም የለንም:: መንፈሳዊ ተቋማት የመከራችን ሰዓት መጠለያ መሆን ተስኗቸዋል:: የሃይማኖት አባቶች የነጻነት ታጋዮችን ገድል ባነበነቡበት አንደበት ለእውነት መቆም አቅቷቸዋል:: የመሰደድ ነውርን ለመስበክ የሚተጋ ሰው ታዲያ የሀገሪቱን ባያውቅ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሊመልስ በተገባው ይመስለኛል:: የተሰደድንበት ምክንያት አይታወቅም?
  ቤተ ክርስቲያንን በትምህርቷ በሥርዓቷና በሌሎች መሰል ጉዳዮች እንከን ልናገኝላት እንደማንችል እሙን ነው:: የያዙዋት ሰዎች /መሪዎችዋ ማለት ይከብዳል::/ እንዴት እየመሩን እንደሆነ ለይተው ቢያውቁ መልካም ነበር:: የስደታችን ምክንያት ሆነውም መጠቀስ ነበረባቸው:: ሀገረ ስብከት ሲቋቋምና ደብር ሲተከል ተሰደዋል ካላልን ደስ ካሰኘን በስደተኞች ባዘንን ነበር:: ቤተ ክርስቲያን ለድህነታችን ተጠያቂ አይደለችም አትሁንብን ደስ ይለናል:: እሺ ለምን ለብልጽግናችን አንጠቅሳትም:: ከመጣ መንግሥት ጋር እየተለጠፉ መንፈሳዊ ነጻነቷን ስለነጠቋት ሰዎች መናገር ነውር የምናደርግ ስለ ስደት ጦስ መናገርን እንዴት ደፈርን?
  አሥራት አውጥተን ዛሬም አጥቢያዎቻችንን እያስተዳደርን የቤተ ክርስቲያን ስም በምንም መንገድ እንዲወሳ ባደረግን ነውሩ የቱ ጋር ነው? አለ የሚባል ነውር ካለም ከነ ፈጣሪው ነዋ መናገር:: ስብከታችን እንኳ ለእውነት ዘብ ይቁም እስኪ? እንደውም የሆነ ቦታ ስትደርሱ የጽሑፉን ውል ይዞ መጨረስ ያቅታል:: ለም እንደተጻፈ ስለምን እንደሚያወራ በውል ያልለየ ጽሑፍ ግቡ ምን ይሆናል ብለን እንደምድም? አትሰደዱ ፣ ስትሰደዱ ተጠንቀቁ፣ ስደትና ተስፋው፣ ጦስን ምን አመጣው:: ዳኒ እባክህ እግረ መንገድ ይህንን ጦስ ፈልግልን?

  ReplyDelete
 16. ዳንኤል መቼስ የማታሳውቀን ነገር የለም አቦ እግዚአብሔር ይባርክህ!!!!!!!!!!!!

  ReplyDelete
 17. ዳኒ መቼስ የማታሳውቀን ነገር የለም አቦ እግዚአብሔር ይባርክህ!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!

  ReplyDelete
 18. የልቡን ሲነግሩት የኮረኮሩት ያህል ይስቃል ይባል የለ ሽሮን ብናጣት እንዴት እንደምንሆነ ገርሞኝ ነው መሰል በጣም ያስቀኛል በዓይነ ሕልና ለምታሳየን ለአንተ አምላክ ፀጋውን ያብዛልህ አሜን
  wtbhm

  ReplyDelete
 19. dc daniel you are such ,postive person and you have been such rool model for me and its a brivelage to know you ,i pray for you long life

  ReplyDelete
 20. thank you Dani, i have been here for 5 years but i didn't know the things you explain about Australia, shame on me, u are a great lecture. God bless you

  ReplyDelete
 21. ሽሮ እኛን ስላሳደገች በክብር ጡረታ ወጥታ ትቀመጥ" እንብላ በሚለዉ ባህላን እንብላ ባትለንም መልካም ምግብ የተባረከ ይሁን ብለናል!

  ReplyDelete
 22. "በዚህች ምድር በቅሎ የተገኘው ግን ጌሾ ብቻ አይደለም፡፡ መቼም አገር ደግ ነገር ብቻ አታበቅል፡፡"..........

  ወይ ጉድ ጌሾ ጥሩ ነገር ሆኖ ጫት መጥፎ ተባለ…. ወይ የወገንተኘነት አዙሪት…Double standard......

  ReplyDelete
 23. ገሾም ሆነ ጫት መጥፎ አይደሉም! መልካሙንና መጥፎን መለያት ያቀተው ሰው ነው መጥፎ!

  ReplyDelete