Thursday, August 1, 2013

ጉዞ ወደ ምድር ጥግ (ክፍል ሁለት)

ከምሽቱ አራት ሰዓት ተኩል ላይ ወደ አውሮፕላኑ እንድንገባ ተጋበዝን፡፡ በቀኜም በግራዬም ከፊቴም ከኋላዬም የተቀመጡት የእስያ ዝርያ ያላቸው ተጓዦች ናቸው፡፡ እንዲህ ኤስያውያን በሞሉበት አውሮፕላን ስሄድ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ አስተናጋጆቹ ከዚህ በኋላ ወደ ቀጣዩ መዳረሻችን ለመድረስ የስምንት ሰዓት ከሩብ ጎዳና ይቀረናል አሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ ሌላ አውሮፕላን እንይዛለን፡፡ ድሮ ሦስተኛ ክፍል ስንማር ‹ንብ አበባ ለመቅሰም የምታደርገውን ጉዞ በአንድ መሥመር ብታደርገው ኖሮ፣ ዓለምን ትዞር ነበር› የሚል ነገር ተምሬ ነበር፡፡ አሁንም የኔ ነገር እንደዚያ ሳይሆን አይቀርም፡፡
‹ይህ ነው ምኞቴ እኔ ለሕይወቴ› የሚል የቆየ የማርሽ መዝሙር  ትዝ አለኝ፡፡ እዚያ መዝሙር ውስጥ ደግሞ
ረዥሙን ጉዞ ትግሉን ዐውቄ
ተነሥቻለሁ ትጥቄን አጥብቄ
የሚል ነገር ነበረው፡፡ ምን ይደረግ ሰው ከሀገሩ ሲወጣ ትዝታ ነው የሚተርፈው፡፡ ከወሎ መቄት ወደ አዲስ አበባ መጥተው የኖሩት አለቃ ለማ ኃይሉ አይደሉ እንዴ ቢቸግራቸው ‹‹እግር አዲስ አበባ ልቡና መቄት›› ያሉት፡፡ አንዳንድ ጊዜ ‹ሀገር ማለት ምንድን ናት?›› ያሰኛል፡፡ በሀገራችን ተሰቃየን፣ ታሠርን፣ ተንገላታን፣ ግፍ ተፈጸመብን ብለው ከሀገር የሚወጡ ወገኖቻችን እንኳን መልሰው ‹ሀገሬ› ሲሉ ሳያቸው ይህቺ ሀገር የምትባል ‹መንፈስ› ምንድን ናት? እላለሁ፡፡ አንድ ጊዜ ከዋሽንግተን ዲሲ ወደ አዲስ አበባ ስመጣ ከጎኔ አንድ በጎልማሳነት እድሜ ላይ የደረሰ ኢትዮጵያዊ ወገን ተቀምጦ ነበር፡፡ አውሮፕላኑ ሲነሣ እጁ ይንቀጠቀጣል፡፡ ያመመው መሰለኝና ዘወር ብዬ ‹‹አመመህ›› ስል ጠየቅኩት፡፡ ግንባሩን በመሐረብ እየጠረገ ‹‹ደኅና ነኝ፣ ምንም አልል›› አለኝ በእንግልጣር፡፡ አሁንም እጁ ይንቀጠቀጣልና ዘወር አልኩ፡፡

‹‹ይገርምሃል ከሀገሬ ከወጣሁ ሠላሳ ዓመቴ ነው፡፡ ወደ ሀገር ለመሄድ ሳስብ ሁልጊዜ ሰውነቴ ይንቀጠቀጣል፡፡ አንዳች ነገር መጥቶ ይወርረኛል፡፡ ልቤ ምቱ ይጨምራል፡፡ አሁንማ አውሮፕላን ውስጥ ስገባ ባሰብኝ፡፡ ውስጤ ብርድ ብርድ ይለኛል፤ እንደገና ይሞቀኛል፡፡ ምን እንደሆነ ማወቅ አልቻልኩም›› አለኝ፡፡ እያየሁት እገረም ነበር፡፡ ከሕይወቱ አብዛኛውን፤ ያውም ነፍስ ያወቀበትን ዘመን ያሳለፈው አሜሪካ ነው፡፡ ግን ‹ኢትዮጵያ› የሚለውን ሲያስበው አንዳች ስሜት፣ እርሱም የማይገባው ስሜት ይወርረዋል፡፡ ‹‹ሀገር ምንድን ነው?››
ደግነቱ አንድ ወዳጄ ‹‹ዜጋን ከሀገሩ ማስውጣት ቀላል ነው፤ ሀገርን ከዜጋው ልብ ማስውጣት ግን አይቻልም›› ብሎኝ ነበር፡፡ እኛ ልብ ውስጥ ልዩ የሆነች ሀገር አለች፡፡ ማንም የማይነካት፣ ማንም የማይወስዳት፣ ማንም የማያጠፋት፡፡ አለቃ ለማ ‹ልቡና መቄት› ያሉትኮ መቄት ከልባቸው አልወጣ ብላቸው ነው፡፡
ይህንን ሁሉ እያሰብኩ አውሮፕላኑ ተነሥቶ ወደ ሕንድ ውቅያኖስ አቅጣጫ ማምራት ጀመረ፡፡ እኔም የሕይወት ተፈራን Tower In The Sky አውጥቼ ማንበብ ጀመርኩ፡፡ ያ ትውልድ አሁንም አብሮኝ ሕንድ ውቅያኖስን ሰንጥቆ ሊጓዝ ነው፡፡ ዓላማ፣ ትጋት፣ ቆራጥነት፣ መሥዋዕትነት፣ ጽንዓት የነበረው አንድ ትውልድ ጠፍቷል፡፡
በማርክሲስት ሌኒኒስት ቀንበር ተቀይዶ፣ የሁሉንም ነገር መፍትሔ ከመጻሕፍት ውስጥ ሲያስስ፣ እርስ በርስ ተከራክሮና ተወያይቶ በመተማመን ወይም ባለመተማመን መፍታት ሲቻል፤ ተምሮ እንዳልተማረ፣ ዐውቆ እንዳላወቀ ሲጨራረስ ማየት አሳዛኝ ነው፡፡ ሁሉንም ነገር በሳጥን ውስጥ ብቻ ለመመልከት የሚተጋ ትውልድ የ‹ኢስት› ብዛት፡- ማርክሲስት፣ ማኦኢስት፣ ቾቭኒስት፣ ፌሚኒስት፣ ካፒታሊስት፣ አናርኪስት፣ ፋሺስት፣ ትሮትስኪስት፣ ኮሙኒስት፣›› የ‹ኢዝም› መዓት፡፡ ሁሉንም ሃሳቦች፣ ሁሉንም አመለካከቶች በሳጥኖች ብቻ አድርጎ የመመልከት አባዜ፡፡ ማርክስ፣ ሌኒንና ኤንግልስ የሚባሉ ሐዋርያት ያመጡት አዲስ ሃይማኖት፤ ቦልሼቪስት፣ ማኦኢስት፣ ማርክሲስት የሚባሉ ምእመናን፤ አናርኪስት፣ ትሮትስኪስት፣ የሚባሉ መናፍቃን፤ ኢምፔሪያሊስት፣ ፊውዳልና ቡርዧ የሚባሉ አጋንንት፣ ተፈጥረው አማኝና ከሃዲ ሲወጋገዙና ሲጫረሱ የኖሩባቸው ዘመናት፡፡
መጽሐፉ እያሳዘናችሁ እያስገረማችሁ፣ እያበሳጫችሁም ይጓዛል፡፡ የአንድ ፓርቲ ሰዎች ትናንትም ይከፋፈላሉ፤ ዛሬም እንዲሁ፤ ተከፋፍለውም ይወጋገዛሉ፤ ዛሬም እንዲሁ፤ ተወጋግዘውም ይገዳደላሉ፤ ዛሬም እንዲሁ፤ ለአብዮቱ ሲባል፤ ለትግሉ ሲባል፤ አድኅሮት ኃይላትን ለማስወገድ ሲባል በጓዶች ላይ ርምጃ ይወሰዳል፡፡ ድመት ይመስል አብዮት ልጆቿን ትበላለች፡፡ እስካን አይጥ ለማጥመጃ ስንት መሣሪያ ሲሠራ፤ ምነው ይህቺን ልጆቿን የምትፈጅ ‹የአብዮት ድመት› ማጥፊያ መድኃኒት ጠፋ?
የዚያ ዘመን ሰዎቹ ዐልፈዋል፤ ሥርዓቱ ዐልፏል፤ ታሪኩ ዐልፏል፤ መንፈሱ ግን አለ፡፡ ‹‹ግደል ተጋደል በርታ ወገኔ›› የሚለው ዛር ግን አለ፡፡ ፖለቲካዊ ጽንፈኛነት፤ ደጋፊነትና ጠላትነት፤ ሥር ነቀልነትና ደምሳሽነት አሁንም አሉ፡፡ ይህንን መንፈስ የሚያጠፋ ትምህርት፤ የሚደመስስ ጸሎት፤ የሚያስቀር ሥርየት አልተገኘም፡፡
መጽሐፉን እንዲህ እያነበብኩ እያለ አስተናጋጆቹ ምግብ ይዘው በጎናችን መጡ፡፡ ከጎኔ ላለው ሰውዬ የሰጠችው ምግብ ስሙን የጠራችው በቻይንኛ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የነዚህ የእስያውያን ነገርኮ ምን እንደሚበሉና ምን እንደማይበሉ አይታወቅም፡፡ ቢጨንቀኝ ዓሣ አዘዝኩ፡፡ የመጣውን ነገር አልነግራችሁም፡፡ ምናልባት ምግብ ላይ ትሆናላችሁና ይቅር፡፡ አንድ ወዳጄ ‹‹እነዚህ ሰዎችኮ ሰውን ባሕር ውስጥ ቢያገኙት ዓሣ ነው የሚሉት›› ያለኝ ትዝ አለኝ፡፡ እንኳን ልበላው ኢትዮጵያ የበላሁትም ምግብ ሆዴ ውስጥ ሆኖ እንደ ኤርታሌ ይተራመስ ጀመር፡፡
ከድኜ ተውኩትና መጽሐፉን ቀጠልኩ፡፡ አይ ሕይወት እግዜር ይይልሽ፡፡ ልደታ ብስኩት ቤት፣ ፒያሳ ጮርናቄ ቤት፣ ሐረር ምግብ ቤት፣ ምናምን ክትፎ ቤት እያለች የአዲስ አበባን ምግብ ቤቶችና ሻሂ ቤቶች ትዘረዝራለች፡፡ ይህም አልበቃ ብሏት በመቀሌ መንገድ ላይ ‹‹ምን የመሰለ ዱለት በላሁ›› ትላለች፡፡ እኔ እዚህ በአንድ በኩል የሚዘጋ ምግብ ከፊቴ ተቀምጦ ይተናነቀኛል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የሀገሬን ምግብ ቤትና ምግብ እያነበብኩ ረሃቤ ይቀሰቀስብኛል፡፡ ተርቦ ስለ ረሃብ ማንበብን የመሰለ ቅጣት መቼም የለም፡፡
ዘሚካኤል ትዝ አለኝ፡፡ ዘሚካኤል ኤርትራዊ ነው፡፡ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ከዐሥራ ሁለት ዓመታት በፊት ባዘጋጀው አንድ ሴሚናር ላይ ለመሳተፍ ተጋብዘን ኡጋንዳ ኢንሴንዜ የምትባል መንደር ተገናኝተን ነበር፡፡ እዚያ ከአሥራ ስድስት የአፍሪካ ሀገሮች የመጡ ወጣቶች ነበሩ፡፡ ከሁሉም የእኔና የዘሚካኤል የምግብ ምርጫ ነበር የሚገርማቸው፡፡ ከምንበላው የማንበላው ይበልጣል፡፡ አንደ ቀን ሴሚናር ላይ ውለን አምሽተን ተመለስን፡፡ እኔ ቀደም ብዬ ጨለም ወዳለው የማምሻችን ቦታ መጣሁ፡፡ እሳት ነድዶ ጨዋታው ቀልጧል፡፡ ዘሚካኤል መታጠቢያ ቤት ገብቶ ዘገየ፡፡ ስደርስ የሆነ ነገር ሸተተኝ፡፡ አሻግሬ ሳይ ጠረጲዛው ላይ ያለውን ነገር ይሻሙበታል፡፡ በጨለማው ውስጥ ያለው የእሳት ብርሃን ብቻ ስለነበር ልለየው አልቻልኩም፡፡ ራቅ ብዬ ተቀመጥኩ፡፡
ዘሚካኤል መጣና ጠረጲዛ ላይ ያለውን ነገር አየው፡፤ ‹‹ዘቢብ ሳይሆን አይቀርም›› አለኝ፡፡
‹‹አይ እኔ ይቅርብኝ አንተ ሞክረው›› አልኩት፡፡
‹‹ዘቢብ መሆን አለበት፤ መልኩ እንደዚያ ነው›› አለና ሊያመጣ ሄደ፡፡ ልክ ጠረጲዛው ጋ ሲደርስ ‹‹ቧ፣ አተ›› አለና ፈጠን ፈጠን ብሎ ወደ ማደሪያው ገባ፡፡ ምን ሆነ ብዬ ደነገጥኩና ተከተልኩት፡፡ ባንኳኳ ባንኳኳ አልከፍትም አለ፤ በስንት መከራ ሳስከፍተው ፊቱ በውኃ ርሷል፡፡
‹‹ምን ሆነህ ነው?›› አልኩት
‹‹ጉድ ሠሩኝኮ›› አለኝ
‹‹ምን አደረጉህ››
‹‹ምን እንደሆነ ዐውቀሃል››
‹‹ምንድን ነው?››
‹‹የተጠበሰ ክረምት አግባ›› በሳቅ ፈረስኩ፡፡ ለካስ እንደ ዘቢብ አምሮ የታየው እኛ ክረምት አግባ የምንለውን ሰብስበው ቆልተውት ነው››
ዛሬ የደረሰብኝ በዘሚካኤል በሳቅኩት ግፍ ነው፡፡
ከዱባይ ወደ ብሩናይ መንገድ፣ ሕንድ ውቅያኖስ ላይ

31 comments:

 1. ዳኒ የምግቡንስ ነገር ተወው ሆዳቸው አምላካቸው የሆኑ ሕዝቦች ጥንቡንም ቢጎትቱ አይገርመንም፤ ላንተና ለመሰሎችህ የዓለምን ነገር ለመታዘብ በየምድሪቱ ለምትዞሩ ግን አዘንኩ፤ ለመሆኑ ያ የምድር ጥግ ጉዞህ ምን ደረሰ? እባክህ ናፍቆኛል አታዘግየው፤ አምላከ ቅዱሳን በመንገድህ ሁሉ ይምራህ!!!

  ReplyDelete
 2. Dani,God be with you!

  ReplyDelete
 3. <> የከሸፉ ትውልዶች! kb z Adigrat

  ReplyDelete
 4. "ደግነቱ አንድ ወዳጄ‹ዜጋን ከሀገሩ ማስውጣት ቀላል ነው፤ ሀገርን ከዜጋው ልብ ማስውጣት ግን አይቻልም' ብሎኝ ነበር፡፡

  የበዓሉን ከአድማስ ባሻገርና የብርሃኑ ዘሪሁንን የቴዎድሮስ ዕንባ ተመልከት፡፡ ከተወሰኑ የቃል ቅርጾች በቀር አገላለጹ የእነርሱ ነው፡፡

  ReplyDelete
  Replies
  1. ይህን የጻፉት የመጀመሪያው በ "ፍቅር እስከመቃብር" ውስጥ አቶ ሀዲስ ዓለማየሁ ሳይሆኑ አይቀሩም። አገላለጹን ቃል በቃል ባላስታውስም እርሳቸው "ዜጋ" በማለት ፋንታ "ባላገር" በማለት ያሰፈሩት የሚከተለውን የሚመስል ነው፦ 'ባላገርን ከአገሩ ማስወጣት እንጂ አገርን ከባላገር ልብ ማስወጣት አይቻልም'።

   Delete
 5. ክረምት አግባ ምንድነው አንጀት ነው

  ReplyDelete
  Replies
  1. Nooo Anjet Aydelem ... Be Kiremt Yemimeta Berari Nefsat New

   Delete
 6. Engede Egizabhare kantaga yehune danie.

  ReplyDelete
 7. Dani andd gizie Abune Shinoda salsawi yihchignayitu Egyptina Libunaye wustt yalechiw Egypt andd aydelum alu. Hager bemehied yemtrikat melk'amidrawi akemamett yalat bicha aydelechim. Teweldeh etibtih wedersuwa sikeber yersiwa fikir degimo belibunah wustt yikeberal. Lezih new ya yayehw sew kebizu ametat behuwala wede hageru simeles yaltaweke andach simet yetesemaw.
  Kesis Sintayehu,

  ReplyDelete
 8. Thank you Diyakon Daniel Kibret Interesting view God Bless You...የአንድ ፓርቲ ሰዎች ትናንትም ይከፋፈላሉ፤ ዛሬም እንዲሁ፤ ተከፋፍለውም ይወጋገዛሉ፤ ዛሬም እንዲሁ፤ ተወጋግዘውም ይገዳደላሉ፤ ዛሬም እንዲሁ፤ ለአብዮቱ ሲባል፤ ለትግሉ ሲባል፤ አድኅሮት ኃይላትን ለማስወገድ ሲባል በጓዶች ላይ ርምጃ ይወሰዳል፡፡ ድመት ይመስል አብዮት ልጆቿን ትበላለች፡፡ እስካን አይጥ ለማጥመጃ ስንት መሣሪያ ሲሠራ፤ ምነው ይህቺን ልጆቿን የምትፈጅ ‹የአብዮት ድመት› ማጥፊያ መድኃኒት ጠፋ?

  ReplyDelete
  Replies
  1. worenga anatam....ymnabk abiot neewww degmo....????

   Delete
 9. "ያለ በሬ ምን ያደርጋል ገበሬ" አለ ገበሬው! ያለ ሀገር ምን ያደርጋል ሁሉ ነገር አለች ዮኒ!!!!

  የሀገሬን ምግብ ቤትና ምግብ እያነበብኩ ረሃቤ ይቀሰቀስብኛል፡፡ ተርቦ ስለ ረሃብ ማንበብን የመሰለ ቅጣት መቼም የለም አልከን? ዳኒ "ጆሮ በላ ሆድ ጦሙን አደረ" የተባለው ትንቢት በአንተ ተፈጸመ።

  ReplyDelete
 10. ahunes betam asakegn, Egziabheramlak keantegar yehun
  amen

  ReplyDelete
 11. hi dani,God bless you and your journey. I am really impressed with your views. keep it up!!!!! what the amazing I haven't word to appreciated you. just I wonder.

  ReplyDelete
 12. ‹‹ምን እንደሆነ ዐውቀሃል?›
  ዛሬ የደረሰብኝ በዘሚካኤል በሳቅኩት ግፍ ነው፡:

  ReplyDelete
 13. Anten yewledech enat tadela dani,
  Lelochenm anten mesaye yeweledu

  ReplyDelete
 14. ዲ/ን ዳንኤል ወዴት ወዴት ነው ነገሩ?

  ReplyDelete
 15. Egizabiher yibarkih asdenaki new

  ReplyDelete
 16. ዳንኤል እንደምን ነህ

  በጨዋታ መልክ እያዋዛ የሚቀርበው ቁም ነገር አዘል

  መጣጥፍ በጣም ደስ ይላል፡፡

  የንሰሀ እድሜ እና ጤናህን ይስጥህ፡፡

  ወለተ ሚካኤል

  ReplyDelete
 17. ጉዞ ወደ ምድር ጥግ (ክፍል 3)

  ReplyDelete
 18. ውድ ዳንኤል፣

  ይህ ብሎግ ከዋጋ በላይ ነው፣ ለእኔ፡፡ በዚህ ብሎግ አማካይነት ከአንተ ጋር በሃሳብ የተጠራነፍኩበት ከመቶ ዘጠና ይደርሳል፡፡ በሃሳብ የተገሸላለጥኩበትም አለ፡፡ ይህ ብሎግ ለእኔ የቦክስ ሜዳ ነው፡፡ በሃሳብ ቡጢ የምንቧቀስበት፡፡

  ብሎጉ ምርጥ ነው፡፡ ምርጥነቱ ደግሞ በሚያነሳቸው ጭብጦች ምክንያት ነው፡፡ እያንዳንዱ ርዕስ የራሱ የሆነ ልቅ የመከራከሪያ መድረክ (forum) የሚያስፈልገው ነው፡፡ በተለይም እንዲህ እንደ ጉዞው ዓይነት መጣጥፎችህ "ተራ" የሚመስሉ ግን ደግሞ ከአቶም ቦምብ የገዘፈ ኃይል በውስጣቸው አምቀው ይዘዋል፡፡ እንዲህ በዋዛ በአጭር ቃል በምስጋና፣ መልሶ በመጥቀስ፣ ወይም በዘለፋ ዓይነት አስተያየቶች ብቻ ማለፉ በቂ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡

  "ሀገር ምንድን ነው?" ፤ "የበቅሎ ጥያቄ"

  እንደነዚህ ዓይነቶችን፣ ወቅት ተኮር፣ ግን ደግሞ በጣም መሠረታዊ ጥያቄዎች ኢትዮጵያውያን ሁሉ፤ ከአንድነት እስከ መገንጠል፣ ከቋንቋ ተኮር እስከ ማኀበረ ኢኮኖሚያዊ ተኮር ፌደራሊዝም አስፈላጊነት፣ ከግለሰብ ነጻነትና መብት እስከ የቡድን መብት ተከራካሪዎች፣ ከብዙኃን እስከ ንዑሳን ተሟጋቾች፣ ከግለሰብ እስከ መንግሥት ድረስ ሊወያዩበት ሊከራከሩበት የሃሳብ ፍጭትን በተጠየቃዊና አስረጂ መንገድ አቅርበው የግራ ቀኙ ሃሳብ የሚነበብበት፣ የሚደመጥበት ብዙኃኑ በምክንያትና በማስረጃ አቋሙን በፍላጎቱ የሚያሳይበት መድረክ ልታዘጋጅ ይገባሃል ባይ ነኝ፡፡

  ኢትዮጵያ የምሑራንም የአስተሳሰብም ደሃ አይደለችም የሚባለውን በተግባር ለማሳየት ከዚህ ብሎግ ብዙ እጠብቃለሁ፡፡ መሪነትን በጋን ውስጥ ካለ መብራት እንዴት መጠበቅ ይቻላል? በአደባባይ ሃሳቡን ያልገለጠውን፣ ምክንያቱን ያላስረዳውን፣ ተከራክሮ መርታት ወይም መረታት ያልቻለውን፣ ማስረጃ አቅርቦ አሳምኖ ደጋፊ ያላፈራውን መሪነት እንዴት መሪ ብለን ልንቀበለው እንችላለን?

  ከአዙሪታችን የመውጫ መንገዱ ዛሬም አልተገለጸልንም፡፡ እንዲገለጽልን ተአምር እየጠበቅን ይሆን? ለመሆኑ ከሰው ልጅ አዕምሮ በላይ ተአምር አድራጊ ከወዴት ይመጣል?(ከመንፈሳዊ እይታ ውጪ ያለ አገላለጽ ነው)፡፡ ሳይንቲስቶች እንደኛው ሰው ናቸው፡፡ አምላካዊ ስጦታቸውን ተጠቅመው ተአምር የምንለውን አሳዩን፣ ሠሩልን፣ ሰጡን፡፡ አሁን ከኔልሰን ማንዴላ በላይ ለእኛ ተአምር ሊያሳየን ማን ይችላል?

  እንደ እኔ እምነት ከአዙሪታችን ለመውጣት የሚያስፈልገን የመንግሥት ፕሮፓጋንዳ ወይም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥልፍልፍ የፓለቲካ ጨዋታ አይደለም፡፡ ሕዝብን እንደ ዜጋ እንደ አንድ ሕዝብ የሚያስተባብር፣ የአስተሳሰብ ፍልስፍና ነው፡፡ ከላይ እንደተቀመጡት ያሉ የፍልስፍና ጽንሰ ሃሳቦች፤ ግን ደግሞ መሠረታዊ የማንነትና የምንነት ጥያቄዎች፡፡
  እስኪ አንዳንዴ ወራትን ወይም ዓመታትን የሚያቆጥር የመከራከሪያ ርዕስ/አርእስት ላይ ችክ በል፡፡ ለምሳሌ እንዳሁኑ ዓይነት፡፡ የተበታተነውን የኢትዮጵያዊነት አካል መልሶ መገጣጠም ሳይቻል በዚህ ክ/ዘመን ሉዓላዊ ኢትዮጵያን ለመጠበቅብም ሆነ ሉዓላዊ ዜግነትን ለመጎናጸፍ ቀርቶ አሁን ያለውን ቋንቋ ተኮር የብሔር ፌደራሊዝም ይዞ ለመቀጠል ከመልካም ጎኑ ይልቅ ተግዳሮቶቹ ከደርዘን በላይ የሚቆጠሩ ናቸው፡፡

  እናም በነካ እጅህ የሚለው ለሥላቅና ለስድብ ብቻ አይሁንና በነካ እጅህ በእነዚህ ሁለት አርእስት አማካይነት ኢትዮጵያውያንን ወደ መድረኩ እንዲመጡ በማድረግ ስለነገ የሚሠሩ ዜጎች እንዲወለዱ ሥራው ዛሬ ይጀመር፡፡ ከተበጣጠሰው የገበሬ እርሻ ዓይነት አስተራረስ እንውጣና በሂደት ወደሁለት ጎራ ለመምጣት እንቻል፡፡ ያን ጊዜ ጠንካራ፣ አቋሙ የማይሸረሸር፣ በምክንያት የሚያምን፣ በምክንያት የሚደግፍ፣ በምክንያት የሚቃወም ሕዝቦች እንሆናለን፡፡ እንዲህ በመሆናችን ቢያንስ የሚከተሉት ጥቅሞችን ለአገራችንም ለፖለቲካ ፓርቲዎቻችንም እንሰጣለን፡፡

  1ኛ. የአገራችን የልማት ዕቅድ ያለምንም እንከን በሕዝቦች የልብ ፈቃድ በፈጣን መልኩ ይራመዳል፡፡
  2ኛ. የመንግሥት ፕሮፓጋንዳ ተኮር ልፈፋውና እኔን ብቻ አድምጡ አካሄድ በግድ ይቀይራል፣
  3ኛ. የፓርቲዎች እንዳሸን መፍላት ያከትምና የምክንያት ፖለቲካ ፓርቲዎች በሕዝብ ድጋፍ ገዝፈው ይታያሉ፣ ነጥረው ይወጣሉ

  ሰላም
  ተስፋዬ  ReplyDelete
 19. ዳኔ በርታ! የድንግል ልጅ ይከተልህ።

  ReplyDelete
 20. ..... ‹‹ዘቢብ መሆን አለበት፤ መልኩ እንደዚያ ነው›› አለና ሊያመጣ ሄደ፡፡ ልክ ጠረጲዛው ጋ ሲደርስ ‹‹ቧ፣ አተ›› አለና ፈጠን ፈጠን ብሎ ወደ ማደሪያው ገባ፡፡ ምን ሆነ ብዬ ደነገጥኩና ተከተልኩት፡፡ ባንኳኳ ባንኳኳ አልከፍትም አለ፤ በስንት መከራ ሳስከፍተው ፊቱ በውኃ ርሷል፡፡
  ‹‹ምን ሆነህ ነው?›› አልኩት
  ‹‹ጉድ ሠሩኝኮ›› አለኝ
  ‹‹ምን አደረጉህ››
  ‹‹ምን እንደሆነ ዐውቀሃል››
  ‹‹ምንድን ነው?››
  ‹‹የተጠበሰ ክረምት አግባ›› በሳቅ ፈረስኩ፡፡ ለካስ እንደ ዘቢብ አምሮ የታየው እኛ ክረምት አግባ የምንለውን ሰብስበው ቆልተውት ነው››
  ዛሬ የደረሰብኝ በዘሚካኤል በሳቅኩት ግፍ ነው፡፡

  Hoden eskiyamegne naw yeskugne !!!!!!!!!!!! Dani!

  ReplyDelete
 21. Yimrah new yemibalew!

  ReplyDelete
 22. Yimrah new yemibalew!

  ReplyDelete
 23. ክፍል ሦሥት ምን ሆኖ ይሆን…በጉጉት እየጠበቅሁት ነበር፡፡ለካም ሲቸኩሉ ይዘገያል መሰለኝ ዉሥጤን ቀስ በል አልኩት…እና አይጻፍም እንዴ!

  ReplyDelete
 24. ውድ ዳንኤል ጋዜጠኛ ሆኜ በአንድ ፕሮግራም ላይ አንተን ሰውይይት ለመጋበዝ ብችል ስንትና ስንት ጥያቄዎች ነበሩኝ መሰለህ፡፡ ዳሩ አንተስ የት ተገኝተህ?? እኔስ እንዴት ጋዜጠኛ ሆኜ?? እንደው ጨዋታውን ማለቴ ነው እንጂ፡፡

  ReplyDelete
 25. ዳኒ እግዚአብሃር ይባርክህ!የዘር ፖለቲካ እንጂ ለሀገር የሚያስብ ከማንም ወገን ቢሆን ችግር የለመ...ደርግ መንግስት ሲልታን ሲይዝ ወላይታ ገዝህ የነበሩ ወ/ሰማያትን እንዳየገደሉ የከለክከልው ሂዝቡ ነው..እሳችው ያሰሩት ኦሞና ብላተ ድልድይ ህያወ ምስክር ነወ.ገርማመ ንዋየ እንድዝሁ./ህዝቡ ስልሚውድውቸው 'በዘፈናቸወ ሰማአት ገዝህያችን ገርማመ ወንዲማችን" ብልወታል.ወላይታ ባሀል አዳራስ ፍቶችወን ክታርካችወ አኑርላችዋል.ክሲዳማና አውሳ ታርክ ጋር ሁልም የሚንሱ ራስ ልኡል መንገስ ስዩም እንድዝሁ፤/በየካ ሚካእል ወ/ሰማያተን ብታገናችወ ብዙ ነግሮቸ ያቻወቱህል.

  ReplyDelete