አሁን አብዛኛው አውስትራልያ የገባ ኢትዮጵያዊ በሚገኝባት የሜልበርን ከተማ ውስጥ
አበሻው ሰብሰብ ብሎ በሚኖርባትና በሚሠራባት ፉትስክሬይ በተባለችው መንደር እንገኛለን፡፡ ይህች የሜልበርን ምዕራባዊ ቀበሌ
የሆነች መንደር ጥንት የኤስያውያን መናኸርያ ነበረች ይባላል፡፡ ዛሬ ግን ዋናዋ የአፍሪካውያን ስደተኞች መሰባሰቢያ ናት፡፡
በዚህች ከ74000 ትንሽ ከፍ የሚል ሕዝብ በሚኖርባት መንደር ውስጥ ከ135 ሀገሮች የመጡ ስደተኞች ይኖሩባታል፤ ከ85 ቋንቋ
በላይ ይነገርባታል፡፡ እንዴው መርካቶ በሏት፡፡
በአውስትራልያ ታሪክ የመጀመሪያው የእንጀራ መሸጫ ሱቅ የተከፈተው እዚህ ነው፡፡
በነገራችን ላይ እዚህ ሀገር እንጀራ በዋናነት ከስንዴ ወይም ከሩዝ ዱቄት ተቦክቶ የማሽላ ዱቄት ይቀላቀልበታል፡፡ የታደሉት
ደግሞ ከሀገር ቤት የመጣ የጤፍ ዱቄት ለአመል ይጨምሩበታል፡፡ ስፋቱ የአገር ቤት እንጎቻ የሚያህል ሲሆን ውፍረቱ የሰንበት ቂጣ
ታናሽ ወንድም ነው፡፡ ኮከብ የመሰለ ዓይን ባያገኝም፣ ሞጭሟጫ ከመባል ለጥቂት ይተርፋል፡፡ በብዛት የሚጋገረው ከብረት በተሠራ
ምጣድ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ግን ከሀገር ቤት የሸክላ ምጣድ የሚያመጡ አሉ፡፡ ሳይሰበር ከደረሰላቸው፡፡