በከበደ ሚካኤልኛ እንዲህ ይተረካል፡፡
አንዲት ግልገል በቅሎ እናቷን እንዲህ ብላ ጠየቀቻት፡፡ ‹‹እማዬ እኔ ግን ማነኝ››
እናቷም ገረማትና ‹አንቺማ በቅሎ ነሽ፤ ግን ለምን ጠየቅሽኝ››
ግልገሏም ጥቂት ጊዜ ዝም ብላ ከቆየች በኋላ ‹‹መጀመሪያ ግን አህያ ነበርኩ ወይስ
ፈረስ›› አለቻት፡፡ እናቲቱም አንገቷን ነቅንቃ፡፡ ‹‹እንስሳ ነሽ ልጄ፤ እንስሳ፡፡ ፈረስም አህያም እንስሳ ነው፡፡ ስንፈጠር
እንስሳ ነበርን፡፡ የቤት የዱር፣ የሸክም የግልቢያ፣ የእርሻ የሜዳ፣ የንጉሥ የባሪያ የሚለው በኋላ የመጣ ነው፡፡ አዳምኮ
ሲፈጠር ቤት አልነበረውም፡፡ ስለዚህ የቤት እንስሳ አልነበረም ማለት ነው፡፡ ሁላችንም ይህቺን ምድር እንደልባችን እንጠቀምባት
ነበር፡፡ ነገር የመጣው በኋላ ነው፡፡ ለመኖር የሚደረግ ትግል ነው ይህንን አሁን ያለንበትን ሁኔታ የፈጠረው፡፡››
‹‹ጓደኛዬ የአንቺ አያቶች ጨቁነውናል አለኝ፡፡››