Thursday, June 13, 2013

ዶስሌ
አንዱ የሀገሬ ሰው በአምስት ዓመቱ የጣልያን ወረራ ጊዜ ተሰድዶ ሱዳን ይገባል፡፡ እዚያ ገዳሪፍ እያለ ትልቁ ችግሩ ውኃ ማግኘት ነበረ፡፡ እርሱ ደግሞ የተወለደውም ያደገውም ዓባይ ከጣና ተለይቶ በሚወጣባት ደብረ ማርያም በምትባለው ደሴት አጠገብ ነበርና እንዲያ በጀልባ እየቀዘፈ፣ በዋና እየሰነጠቀ፣ ዓሣ እያጠመደ፣ ጉማሬ እያሳደደ፣ ጳልቃን (ፔሊካን) መሥመር ሠርተው በሚዋኙት ዋና እየተዝናና፣ ጎመንና ሸንኮራ ተክሎ ወረታ ገበያ እያቀና ነበርና ያደገው፣ ‹ይህማ የሀገሬ ውኃ ግፍ ነው› እያለ ይጸጸት ጀመር፡፡
ዓባይ እየተገማሸረ ሲወርድ ጣና በማዕበል ሲናወጥ ከቁም ነገር ቆጥሯቸው አያውቅም ነበርና፣ ዛሬ በባዕድ ሀገር ሆኖ ሲያስታውሰው  አንገሸገሸው፡፡ ውኃ መከበሪያ ሆኖ፣ ውኃ ያለው ሰው እንደ ጌታ ሲታይ ‹የጎረቤት ጠበል የቆዳ መንከሪያ ይሆናል› የሚለው ተረት እየመጣበት ተቃጠለ፡፡ ተቃጥሎም አልቀረ ለትውልድ የተረፈ ሁለት መሥመር ግጥም ገጠመ

ውኃ እንደ ቁም ነገር ሰውን ካስከበረ
ዓባይና ጣና ሀገሬ ነበረ


በሀገሩ በጎጡ ያለውን ሀብትና ጥበብ፣ ታሪክና ቁምነገር፣ የኑሮ ዘይቤና ዝመና ሳያስተውለው የሚኖረው ይኼ ዘመዳችን ብቻ አይደለም፡፡ አንዳንዶቻችን የኛን ነገር ሌላ ሰው አጥንቶ ሌላ ሰው ሲተርከው በዚያ ሀገር ተወለድን ብለን ለመናገር እስክናፍር ድረስ እንደርሳለን፡፡ ከባሕር ማዶ የመጣ ነገር እንጂ እዚህ አፍንጫችን ሥር ያለውን፣ በኑባሬ ሥርዓት ከኛ ጋር ተዋሕዶ የሚኖረውን፣ የሚፈጥረው እንጂ የሚያጠናው ያላገኘውን ነገር እንደ ቁም ነገር ማየት ሐራም ሆኖብናል፡፡ በሀገሯ ስንት ዘመን ስትኖር ክብር ያላገኘች ቁንጮ፣ ፓንክ ሆና ስትመጣ መከበሯን ያየ ሀገርኛ ጥበብና ሀብት ሁሉ፣ ሐበሻ አላይና አልሰማ ሲለው፣ ባሕር እየተሻገረ ፈርንጆ ይመጣል፡፡ ይኼው 1% አይረን፣ 99% ነገር ይዛለች እየተባለች በገዛ ወገኗ ትወረፍ የነበረች ጤፍ፣ ዛሬ ነጭ ተጥቁር እየተነሣ ‹የጤፍን ነገር ለኛ ተውት› እያለ በኦን ላይን ገበያ ሲቸበችበው አይደል እንዴ በጤፋችን መኩራት የጀመርነው፡፡
ተውኝ ባካችሁ ብዙ አታናግሩኝ፤ የድኻ ምግብ የነበረው ጥቁር ጤፍ እንኳን በሀብታም ገበታ ላይ በኩራት መንቀባረር የጀመረው ምድረ ፈረንጅ ‹ዋናው ብረትማ ያለው ጥቁር ጤፍ ላይ ነው› ካለ ወዲህም አይደል እንዴ፡፡ እንዴው ለመሆኑ ፈረንጅ የተቀደደ ሱሪ ፋሽን ነው ብሎ ከመልበሱ በፊት በየቤታችን ስንትና ስንት የተቀደደ ሱሪ ነበረንኮ፡፡ እነርሱ ግን ስልት ቀየሩና ቀዳዳ ሱሪያችንን በርዳታ ከምንሰጣቸው ለምን ፋሽን አናደርገውም ብለው ሲሸጡልን፣‹ይህንን ቀዳዳ አንለብስልሽም› እያለ እናቱን መከራ ያሳይ የነበረው ሁሉ እየቀደደ መልበስ ሆነ ሥራው፡፡ ዛሬ በቢራና በድራፍት እየተተኩ እንደ ዋልያና ቀይ ቀበሮ ሊጠፉ የደረሱት የጠላ ዘሮች አንድ አፍ ያለው ፈረንጅ ስማቸውን ቀይሮ ‹ኦርጋኒክ ድራፍት› ብሎ ያመጣቸው ለት የቴሌቭዥኑ ማስታወቂያ በእነርሱ ባይሞላ ከምላሴ ፀጉር ይነቀል፡፡
ይህንን ሁሉ የምቀባጥረው ተኝቼ በሕልሜ፣ ሰው ተሰብስቦ በአዳራሽ፣ ያለበለዚያም ደግሞ ክፍል ውስጥ ለተማሪዎቼ እንዳይመስላችሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ውስጥ፣ ጎዴ ከተማ በምትገኝ አንዲት ዶስሌ ፊት ለፊት ቆሜ ነው፡፡ ዶስሌ የሶማሌ ብሔረሰብ ባሕላዊ ጎጆ ናት፡፡ በአብዛኛው በሴቶች ተሠርታ፣ በግመል ተጭና የተፈለገበት ቦታ የምትተከል ጎጆ፡፡ አራት ነገሮች ብቻ ተገጣጥመው የሚሠሯት፣ ስትገነባ ሙቀት የሚከላከል የራሷ የአየር ማቀዝቀዣ ያላት ናት- ዶስሌ፡፡ ሶማሌዎች ዶስሌን ሲገነቧት ለማኅበረሰቡ ኑሮ የሚጠቅሙ አራት መርሖችን መሠረት አድርገው ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሶማሌ አካባቢው ሙቀት ነው፡፡ ዶስሌም ይህንን ሙቀት የምትከላከልና ቀዝቀዝ ያለ የቤት ውስጥ አየር የምታመጣ መሆን አለባት፡፡ የዶስሌ አርክቴክቶች ይህንን ለማምጣት የጎጆዋን ዲዛይን በአራቱም መዓዝን ነፋስ እንዲያስገባ አድርገው በመቀመር አዘጋጅተዋታል፡፡ የቤቷን ክዳኖች ለመሥራት የተጠቀሙት ቁስ ከሣርና ዕጽዋት ውጤቶች በመሆኑ የውጭውን ሙቀት ተቋቁሞ የውስጡን ቅዝቃዜ ይዞ ለመቆየት እንዲችል አድርጎታል፡፡
ሁለተኛው የዶስሌ የዲዛይን መርሕ ለመንቀሳቀስ መቻል ነው፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብ አርብቶ አደርና ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚንቀሳቀስ ሕዝብ በመሆኑ የምትገነባው ጎጆ አርብቶ አደር መሆን ነበረባት፡፡ ሶማሌዎችም ይህንን በዲዛይናቸው አምጥተውታል፡፡ ከአራት ነገሮች ተገጣጥማ የምትሠራው ዶስሌ በተፈለገበት ቦታ በግመል ተጓጉዛ በቀላሉ የምትገጣጠም ቤት ናት፡፡ የዶስሌ አስገራሚው ነገር ለመጓጓዝ መቻሏ ብቻ ሳይሆን በጉዞ ሂደቷም አገልግሎቷን አለማቋረጧ ጭምር ነው፡፡ ግመል ላይ ተሰቅላ እንኳን የቤቱን የወግ ዕቃዎች ትጭናለች፤ ሕጻናትንና ግልገሎችን ታስጠልላለች፡፡
ፕሮፌሰር ሺፈራው በቀለ በአንድ ጽሑፋቸው ላይ አንድ ምሁር ስለ ‹ሜይንቴናንስ› ባህላችን የሰጡትን ትችት አቅርበውት ነበር፡፡ በባህላችን ውስጥ ሲፈርስ እንደገና መሥራት ወይም አፍርሶ ለሌላ መጠቀም እንጂ አንድን ነገር ሳይፈርስ፣ ነገር ግን ተጠብቆ ለአገልግሎት የማዋል ባህል እንደሌለ አንዱ ማሳያ በአማርኛችን ውስጥ ‹ሜይንቴናንስ› ለሚለው ጽንሰ ሃሳብ የሚሆን ቃል አለመኖሩ ነው ይላሉ፡፡
‹ሜይንቴናንስ› ቃሉም እንደሚያስረዳው አንድን ነገር ‹ሜይንቴይን‹ ማድረግ፣ ወይም ጥቅሙን ሳያጎድል ተከባክቦ ማኖር ነው፡፡ በአማርኛችን ውስጥ ‹ጥገና› የሚለው ሃሳብ አንድ ነገር ሲፈርስ፣ ሲበላሽ ወይም ጥቅም ሲያቆም እንደገና እንዲሠራ ማድረግን የሚወክል እንጂ ይዞታውን አገልግሎቱንና ማንነቱን ሳያጣ ጠብቆ ማቆየትን አያሳይም፡፡ ስለዚህም ልማዳችን ሲፈርስ መሥራት እንጂ እንዳይፈርስ ማድረግ አይደለም ማለት ነው፡፡
ይህ ሃሳብ በባህላችን ባለመኖሩ ምክንያት አንድን ነገር ሳይበላሽ፣ ሳይፈርስ ወይም ከጥቅም ውጭ ሳይሆን በፊት ማንነቱንና ይዞታውን ጠብቆ ለአገልግሎት ማዋል እየተቻለ ተዘንግተው የቀሩትን፣ በችኮላ የፈረሱትን፣ እስኪበላሹ የሚጠበቁትን፣ የሀገሪቱን ሀብቶች አስቧቸው፡፡ መከላከያ ኢንጂነሪንግ እስኪሰበስባቸው ድረስ ከደርግ ጋር በነበረው ጦርነት ተበላሽተውም ይሁን ተቃጥለው በየመንገዱ የወደቁ አያሌ ታንኮችና ሌሎች መሣሪያዎች አፈር ነበር ሲቀልድባቸው የነበሩት፡፡ እነዚህን ነገሮች ከጥቅም ውጭ ስለማድረግ እንጂ ስለመጠቀም ያሰበባቸው አልነበረምና፡፡
እርሱም አልፏል ብለን እንሸነጋገልና ወደ ሌላ እንለፍ፤ በሀገሪቱ አያሌ መንገዶች በየክልሉ እየተገነቡ ነው፡፡ እነዚህን መንገዶች ለመገንባት ለሚሠማሩ ሠራተኞች በየቦታው የመኖሪያ ካምፖች ይገነባሉ፡፡ በእነዚህ ካምፖች ውስጥ መኖሪያ ቤቶች፣ ጽ/ቤቶች፣ የመጸዳጃ ቤቶች፣ አዳራሾች፣ የማምረቻ ቦታዎችና ሌሎች ግንባታዎች ይከናወናሉ፡፡ የመንገዱ ግንባታ ሲያልቅ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ለሌላ አገልግሎት እንዲውሉ አይደረጉም፤ ወይ ይፈርሳሉ፤ ወይም የቆሻሻ መጣያ ይሆናሉ፤ አንድን ነገር ጠብቀን የመጠቀም ልማድ ቢኖረን ኖሮ ሲጀመር ካምፖቹ ነገ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ሆነው እንዲገነቡ መትጋት፣ የተገነቡበትን ጊዜያዊ አገልግሎት ሲያጠናቅቁም ለትምህርት ቤት፣ ለጤና ተቋማት፣ ለመኖሪያ ቤት፣ ለአካባቢ መስተዳድሮች ቢሮዎች ወዘተ ሆነው እንዲያገለግሉ ማድረግ በተቻለ ነበር፡፡
ግና ምን ያደርጋል ‹ውኃ የለም እንጂ ውኃማ ቢኖር› ፣ ጠብቆ መጠቀም የሚባለው የለም እንጂ እርሱማ ቢኖር ስንቱ ሀብት ባክኖ አይቀርም ነበር፡፡ ይኼው በሽታ ተጠናውቶን አይደል እንዴ በየጊዜው እየተመረመርን ጤናችን ከመጠበቅ ይልቅ ስንታመም ብቻ ወደ ሐኪም ቤት የምንሄደው? መኪኖቻችን እንኳን ኪሎ ሜትራቸውን ጠብቀን ለምርመራ ጋራጅ ከመውሰድ ይልቅ ተበላሽተው እስኪቆሙ ጠብቀን የምንወስዳቸው መጠገን እንጂ ማንበር ስላልለመድን ነውኮ፡፡
ዶስሌ ግን ይህንን ክፉ ልማዳችንን ተሻግራለች፡፡ እንደ ዕቃ ዕቃ ጨዋታ እያፈረሱ ሲሠሩ፣ ሀብትና ጊዜ ሲያባክኑ ከመኖር በአንድ በተፈለገ ጊዜ ተነቅላ በተፈለገ ጊዜ እንድትተከል ሆና ዲዛይን ተደርጋለች፡፡ ይህ ዲዛይኗ ደግሞ የታደገው የሀብት፣ የጉልበትና የጊዜ ብክነትን ብቻ ሳይሆን በየቦታው ቁሳቁሶችን ከአገልግሎት ውጭ በማድረግ ከሚፈጠረው የአካባቢ ብክለትም ጭምር ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ነገሮችን እንደገና መጠቀም (ሪሳይክሊንግ) የመጣበት አንዱ ምክንያት በቁሳቁስ መጣል ምክንያት የሚመጣውን የአካባቢ ብክለት ለመከላከል ነው፡፡  ይህ ነው የዶስሌ ዲዛይን ሦስተኛ መርሕ፡፡
አንድን ግንባታ የተዋጣለት ከሚያሰኙት ነገሮች አንዱ ከአካባቢው የተፈጥሮ አደጋዎች አንጻር ያለው የመፍትሔ አዋጭነት ነው፡፡ በሩቅ ምሥራቅ ሀገሮች የሙንሱን ነፋስና እርሱም የሚያስከትለውን ጎርፍ ለመቋቋም ይቻል ዘንድ ቤቶቹ ቀላልና ከውኀ በላይ እንዲሆኑ ተደርገው ይገነባሉ፡፡ ዶስሌን ዲዛይን ያደረጓት ቀደምት የሶማሌ አበው ከተፈጥሮ አደጋዎች መካከል ዝቅተኛ ቦታዎችን የሚያጠቃውን የመሬት መንቀጥቀጥን እንድትቋቋም አድርገዋታል፡፡ ምድር እንደ ቄጠማ ስትንቀጠቀጥ ብትውል ዶስሌ አትፈራርስም፡፡ አራተኛው የዶስሌ የግንባታ መርሕ ነው ይሄ፡፡
እንደ ልማዳችን ሁሉን እናፈርንጅ ካላልን በቀር የግንባታ ጥበቦቻችን መነሻዎቻቸውን ከውጭ ብቻ ሳይሆን እንደ ዶስሌ ካሉት ሀገራዊ ጥበቦችስ ለምን አይወስዱም?አሁን እንደ ዶስሌ ሳይፈርስ የሚነሣ ቤት አዲስ አበባ ላይ ቢኖር ኖሮ ለሚሠራው መንገድና ሕንፃ ሁሉ ሠፈራችንን ስናፈርስ ከምንኖር ቤታችንን እየያዝን  የትም እንሄድ ነበር፡፡ አራት ኪሎን ነቅለን ካራ ላይ፣ ልደታን ሰበታ፣ ሠንጋ ተራን ሽሮ ሜዳ፣ ካዛንቺስን አቃቂ ወስደን እንገላገል ነበር፡፡ መንግሥትም ለማፍረሻና ለካሣ ገንዘብ ከሚያወጣ የቤት ማጓጓዣ ብቻ ይከፍለን ነበር፡፡
ምን ይኼ ብቻ፤ አንዳንዴ አንድ ሠፈር ብቻ መኖር ሲሰለቸን ዶስሌያችንን ጭነን ሌላ ሰፈር መትከል ነው፡፡ ከቦሌ ልጅነት ወደ ካዛንቺስ፣ ከአራት ኪሎ ወደ ስድስት ኪሎ ፣ ከኮልፌ ወደ ላፍቶ፣ ከአስኮ ወደ ኮተቤ እየሄዱ መኖር፡፡ ይኼ የክፍለ ሀገር ተማሪ ኮሌጅ በጥሶ ሲመጣ በየከተማው የቤት ኪራይ ተወዶበት ከሚማረር ዶስሌውን ይዞ መጥቶ ቢሻው እንጦጦ ተራራ ላይ ቢሻው የካ ላይ ተክሎ ይማር ነበር፡፡
ለመስክ ሥራ ወደ ሌላ ቦታ ስንሄድም ሻዎር ያለውና የሌለው፣ የሚመችና የማይመች እያልን ሰው በሠራው አልጋ መከራ ከምናይ ዶስሌያችን ጭነን ላጥ፡፡ ባይሆን ያን ጊዜ እንደ መኪና ፓርኪንግ የዶስሌ ፓርኪንግ ያስፈልገን ይሆናል፡፡ ይኼም ቢሆን እንደ አዲስ አበባ ፓርኪንግ ለብዙዎች እንጀራ መክፈቻ ይሆን ነበር፡፡ አንዳንዴ ክፉ ጎረቤታችሁ ምርር ሲላችሁ ‹እንዴው ይህንን ቤት ሽጬ ልብረር ይሆን› ትላላችሁ፡፡ ችግሩ በስንት  ወረፋና ስዕለት የተገኘ ኮንዶሚኒየም ተሸጦ በኋላ ‹አልበር እንዳሞራ ሰው አርጎ ፈጥሮኛል› ማለት ይመጣል፡፡ አይ ዶስሌ ብትኖር፤ አንዱን ሄዳችሁ ‹በናትህ ጎረቤት ቀይረኝ› ትሉትና  አሪፍ ጎረቤት ጥግ ዶስሌያችሁን ተክላችሁ ዕርፍ፡፡ እንዴውም ባደገው ዓለም እኔ ነኝ ያሉ ሀብታሞች ተተክሎ መኖር ሲሰለቻቸው በመኪና የሚጎተት ቤት ገዝተው አገር ሲዞሩ ይኖራሉ፡፡ ምናለ እነ ማሩ ብረታ ብረት፣ እነ ማሞ ካቻ፣ እነ መስፍን ኢንጂነሪንግ ለዶስሌ ጎማ ሠርተውላት ለዚህ ወግ መዓርግ ቢያደርሷት፡፡
እናም ኮንደሚኒየምም አልደርስ ብሎ፣ ሪል እስቴትም ዋጋው ተሰቅሎ፣ የኪራይ ቤትም የአከራዩን ጠባይና የዋጋ ጭማሪ ችሎ መኖር እያቃተን ነውና ዶስሌ ሆይ ባክሽ አዲስ አበባ ግቢና ገላግይን፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ስለሆነ በተመሳሳይ ሚዲያ መጠቀም ክልክል ነው

29 comments:

 1. hagerawi ewuketachinin ena habtachinin Endet Metteqqem endaLebn Ke Ethiopia SomaLe wendiMochachin ena Ehitochachin talaQQ TiBeb Endinimar Limdachewun Endinqqesim YeMiyastemren....tsihuf Newu. BeEJachin Yalewun WorrQQ Endnakebrewu Endinteqqembet YemiYameLeKten.

  ReplyDelete
 2. GOOD OBSERVATION ?

  ReplyDelete
 3. ደስ የሚልአዝናጅና አስተማሪ ለአንተም እድሜና ጤና ይስጥህ አሜን


  wtbhm

  ReplyDelete
 4. Good insight indeed! Dani u always try to figure out our community problems & there solution. God bless u!

  ReplyDelete
 5. betam des yilali GOD BLESS U

  ReplyDelete
 6. really really nice. watch out there in Somalie Civil Engineers/Architects!

  ReplyDelete
 7. አንዲት ዶስሌ አግኝቼ ከዚያ ጨቅጫቃ አከራይ እና ያቺ ነገረኛ ጎረቤቴ በተገላገልኩ!

  ReplyDelete
  Replies
  1. ha ha ha ha ha ha ha ...........

   Delete
 8. Our social Engineer thanks for your critical observation!

  ReplyDelete
 9. REALLY YOU ARE WONDERFUL GUY ?

  ReplyDelete
 10. እናም ኮንደሚኒየምም አልደርስ ብሎ፣ ሪል እስቴትም ዋጋው ተሰቅሎ፣ የኪራይ ቤትም የአከራዩን ጠባይና የዋጋ ጭማሪ ችሎ መኖር እያቃተን ነውና ዶስሌ ሆይ ባክሽ አዲስ አበባ ግቢና ገላግይን፡፡

  ReplyDelete
  Replies
  1. ነገሮችን በቅጡ ለማከናወን ማንበብ አስፈላጊ ቢሆንም ሰው በህይወት ዘመኑ ሲኖር ችግሩንም መጋፈጥ እንደለበት ማስተማር ይገባናል ለ21ኛው ክፍለ ዘመን ትውልድ እንኳን እንደዚህ አይነት ቤት ወደ አገር ቤት ይምጣ ብለኸው ቀርቶ እንዲሁ በራሱ የፈጠረው ቤት አላስገባ ብሎት መከራ ያያል እባክህ አስተማሪ የሆነ ነገር ቢሆንም ተስፋው የሕልም እንጀራ እንዳይሆንበት ትውልዱን እግዚያብሔይ ይባርከው ብለን እንለምን ፡፡

   Delete
  2. good observation, but better to be realistic considering civilization,land management and social values in respect of the situation.

   Delete
 11. ሶማሌ ክልል ለምስክርነት ሄደህ ነበር'ንዴ?

  ReplyDelete
 12. ዳኔ ግሩም ነው፤ በመንገድህ የድንግል ልጅ አይለይህ። በርታ ።

  ReplyDelete
 13. ሀገራችን የብዝሀ ሃይማኖት ብሔረሰብ እና ባሕል ቋት ናት:: ይህ የራሱ ተጽእኖ ቢኖረውም ቅሉ ማዋደድና ለጥቅም ለማዋል ከተሠራበት ትልቁ የሀገር ልማት አጀንዳ መሆኑ አይቀሬ ነው:: ወንድማችን የሀገራችን ስም ከርሃብ ጋር በተያያዘ ሲነሳ እንደምትታመም ሁሉ አውቃለሁ:: እስኪ የአመጋገብ ሥርዓታችንን ከሀገር ሳንወጣ ልምዳችንን ብንለዋወጥ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስበህ ታውቃለህ? በእይታህ እይልን እስኪ

  ከባህል ልውውጥና ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንጻር ብቻ እንኳን ብናየው የደቡቡን እንሰት መሀል አገር አሽገን የምናደርሰው መቼ ይሆን? ዛሬምኮ አግድምና በመስኖ ስለ ማለስ ነው ስልጠናችን:: ያ ባልከፋ አማራጮች ጠፍተው ቢሆን ባልገደደኝ የተለያየ አካባቢዎችን ሳይ ድፍን ኢትዮጵያ አንድ ዓይነት ቁርስ ምሳ እራት አይበላም:: ሁሉም ተዋጽኦአቸው የእንስሳ አይደለም::አትክልት እንኳ ሲበላ የየራሳችን መንገድ አለን:: ማባያዎቻችን እንኳ ከሀገር ወጥተው ጉድ የሚያሰኙ ናቸው:: አገር ውስጥ ግን የትም ገበያ ላይ የሉም::

  ባሕል ሲባ ግን ቶሎ የሚመጣልን ልብስ ቡና ጭፈራ ብቻ ነው:: ከልቡ የሚይዘው ቢገኝ ግን ብዙ ልንለዋወጣቸውና በቀላሉ ለምደን ልንወራረሳቸው የምንችላቸው አካባቢያዊ አመጋገቦች አሉን:: የክትፎን መንገድ ያየ መቼም የማይሆን ነው እንደማይለኝ አምናለሁ:: ዳኒ ምን ይታይሀል?

  ReplyDelete
 14. Dani betame dese ymtle bate beza laye atmoke ena gena selune saywe yehle kmre nebre ymslige betame ymral bmdre laye lmnor beki newe degu abate Abrhme bdnkuane noro yele fikre kale kbeki belay new Dosle tamryalsh mobile home Abo Egzbher ybarke knbtsbhe Dn.Daniel

  ReplyDelete
 15. God bless u
  Manish,MN

  ReplyDelete
 16. 40/60 gudesh fela!!! ... dosle hoy wodet nesh?

  ReplyDelete
 17. ዳኒ ቤት ይዞ መንቀሳቀሱ ቀርቶብን አምላክ ባለንበት ከክፉ በሰዉረን:: የወደፊቱን ሳይተነብዩ ይህን ድንጋይ ከምረዉ ከምረዉ ድንገት የመሬት መንቀጥቀጥ ወይም መንሸራተት ቢነሳ ያን ግዜ ዶስሌ ማሪኝ አንቺን ማደሪያ አድርጌ ቢሆን ኖሮ ማለት ይመጣል

  ReplyDelete
 18. ለመሆኑ ዲያቆን ዳኒኤል ክብረት ኣግብተዋል?

  ReplyDelete
 19. ዝም ብለው ድንጋይ ለሚደረድሩልንና ፈጠራ የሚባል ነገር ለማይታያቸው አስተማሪና ለአዲስ ፈጠራ በር ከፋች ሃሳብ ነው፡፡ ተባረክ

  ReplyDelete
 20. ውድ ዳንኤል የማደንቅህ ነገሮችን የምታይበት እይታህና ፍልስፍናህ ነውና በርታ!!! ስለዶስሌ በጻፍክ ወቅት አብሬህ ከተጓዙት አንዱ ነበርኩ የገረመኝ በዛች አጭር ጊዜ ውስጥ እንዲህ አይነት ጽሁፍ ማቅረብህ በጣም አስደንቆኝ ነበር ፊቸር አርቲክል በጻፍ እየፈለጉ ግራ ለገባቸው ጓደኞቼ እንዲማሩበት ጋበዝኳቸው እውነት እልሃለሁ ምርጥ የፊቸር ተምሳሌት ናትና ልናመሰግንህ እንወዳለን

  ReplyDelete
 21. dosile temecheshign abo!

  ReplyDelete
 22. ጎበዝ ተማሪ የተሰጠውን የቤት ስራ በጊዜ ይሰራል፡፡

  ReplyDelete
 23. እድሜ ለኢሀዴግ እኔን እና ቤትን ሊዝ እያለ አይጥና ድመት አድርጎናል::

  ReplyDelete
 24. ዳኒ መልካሙ ሁሉ ይግጠምህ ጥሩ ስልሃገራቸሂነ ብዙ የማናዉቀውን እንድናውቅ ፤ ታሪካችንን እንድረዳ በተለይም የኢትዮጵየ ኦረቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የኢትዮጵያ ታሪክ ባለቤት እንደሆነች ጭምር ለማየት ችለናል ብዛኛውን የኢትዮጵያን ክፍሎችንም ለማሳየት ሞክርሃለ ነገር ጊነ እጅግ በጣም ብዙ ያልተፃፈላቸው ታሪካዊ ቦታዎች ስላሉ እነዛነ በጥቂቱ ቢያንስ በወር አንድ ታሪካዊ ቦታን ብታስተዋዉቀን እንደ አስተያየት … በተለይ ምንም ስላልተፃፈላቻ በሸሜን ሽዋ ሀገረ ስብከት ስረ የሚገኙ በመንዝ ፤ በቡልጋ ፤ በተጉለት የሚገኙ ገዳማት ላይ ብእርህን አንስተህ የአባቶቻችንን ፅናት ፤ስብእና ፤ሃይማኖት እና አኗኗር እንዲሁም ያቆዩልንን ቅርስ ለህዝበ ክርስቲያኑ እና ነሁሉም የማሳወቅ ስራ ብትሰራ … በእግዚአብሄር ስም እጠይቃለሁ .. አመሰግናለሁ፡፡

  ReplyDelete