Tuesday, June 11, 2013

ችግር ፈቺ ዜጋ


በቀደም ዕለት ከመገናኛ ወደ ሲኤም ሲ በሚወስደው መንገድ ላይ እየተጓዝን አንድ አይ ሱዙ መኪና ከጎናችን መጣ፡፡ እኛ ወደ መንገዱ ጠርዝ ተጠግተን ነበር የምንነዳው፡፡ አይ ሱዙ መኪናው የመጣው ከመንገዱ ጠርዝ ቀጥሎ በስተ ቀኝ ከሚገኘው መሥመር ነው፡፡ ወደ መንገዱ ማቋረጫ ላይ ሲደርስ ወደ ግራ ለመጠምዘዝ ፍሬቻ ማብራት ጀመረ፡፡ የነበረበት መሥመር በቀጥታ ለመንዳት እንጂ ለመጠምዘዝ የሚያስችል አልነበረም፡፡ ምክንያቱም በስተግራው ሌሎች መኪኖች ማለፍ ይችላሉና፡፡ አይሱዙው ግን መሐል መንገድ ላይ ቆሞ ፍሬቻ እያበራ አሳልፉኝ ማለት ቀጠለ፡፡ በግራ መንገዱ በኩል የማለፍ መብት የተሰጣቸው መኪኖች ከቁብ ሳይቆጥሩት ጥለውት ያልፋሉ፡፡ ከአይሱዙው ኋላ የነበሩ ብዙ መኪኖች በመቆማቸው ምክንያት መንገዱ ተጨናነቀ፡፡ ይህንን ያየ ከፊታችን የነበረው ባለመኪና ቆመና አይሱዙው እንዲያልፍ አደረገው፡፡ ያን ጊዜ መንገዱ ተከፍቶ መጨናነቁ ተፈታ፡፡ የአይሱዙው ሾፌር ግን ላሳለፈው ሰው ምስጋናም ሳያቀርብ ፈትለክ አለ፡፡

ይህ ቀላል አጋጣሚ ልዩ ልዩ ጥያቄዎችን እንድናነሣ ቢያደርገን መልካም ነው፡፡ የአይ ሱዙው ሾፌር ለምን ለመጠምዘዝ በማይቻልበት መሥመር በኩል መጣ? ከኋላው ቆመው ጊዜና ነዳጅ ለሚያባክኑ ሌሎች ሰዎች ለምን አላሰበላቸውም? የአይሱዙው ሾፌር በተሳሳተ መሥመር ለመታጠፍ ቢመጣም በግራው በኩል የሚያልፉት ሌሎች ሾፌሮች አንዳቸው እንኳን በመቆም ለምን አላሳለፉትም? እነዚያ ሁሉ ሾፌሮች እንደነርሱ ያሉ ሌሎች መኪና ነጅዎች በአንድ አይሱዙ ምክንያት መቆማቸው እንዴት አላስጨነቃቸውም? በመጨረሻስ ከፊታችን የነበረው ሾፌር ለምን አይሱዙውን አሳለፈው? የአይሱዙው ሾፌርስ ለምን አላመሰገነውም?
ይህ ቀላል ችግር እንዲሁ የተፈጠረና እንዲሁም የተፈታ አይደለም፡፡ ሌሎች በሀገሪቱ ውስጥ የሚፈጠሩ ከባድና ታላላቅ ችግሮች በሚፈጠሩበትና ሊፈቱም በሚችሉበት ምክንያትና መንገድ የመጣና የተፈታ ነው፡፡ ችግር ፈቺ ዜጋ ባለመሆን የሚመጣ፣ በመሆንም የሚፈታ ነው፡፡ ችግር ፈቺ ዜጋ የአንዲት ሀገር የሥልጣኔዋ መሠረት፣ የዕድገቷም አቀላጣፊ፣ ብሎም የነጻነቷ አስገኚና የሉዓላዊነቷም ጠባቂ ነው፡፡ አንዲት ሀገር ገንዘብም፣ ነዳጅም፣ በቂ መሠረተ ልማትም፣ የተማረና የሠለጠነ የሰው ኃይልም ባይኖራት ችግር ፈቺ ዜጋ ካላት እነዚህን ነገሮች በአጭርና በተቀላጠፈ መንገድ ልታገኛቸው እንደምትችል ጃፓንና ኮርያን ያየ ያውቀዋል፡፡
ችግር ፈቺ ዜጋ ማለት አሳቢነት ያለው፣ ኃላፊነት የሚሰማውና ራሱን ላመነበት ተልዕኮ የሚመድብ ዜጋ ማለት ነው፡፡  አንድ ሰው ያስባል ሲባል አስገራሚ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም ሰውን ከእንስሳት ከለዩት ነገሮች ዋናው ለማሰብ መቻሉ ነውና፡፡ ስለሚያስብ ዜጋ መናገር የማያስብ ዜጋ መኖሩን በጎንዮሽ ማሳየት ስለሚሆን ነው አስገራሚ የሚሆነው፡፡ የማያስብ ሰው አለን? የሚል ጥያቄ ስለሚያስነሣ፡፡ ማሰብን ከአእምሮ የዕለት ተዕለት ሥራ አንጻር ካየነው፣ ማሰብን ከሰው ተፈጥሮ ጋር ብቻ ካመዛዘነው የማያስብ ሰው የለም፡፡ የሚያስብ ዜጋ ማለት ግን ከዚህ ይለያል፡፡ እዚህ ላይ አሳቢነት ያልነው በእንግሊዝኛው Thoughtfulness የሚለውን ነው፡፡ አሳቢነት አንድ ሰው ማንኛውንም ነገር ሲወስን፣ ሲያደርግና ሲከውን ለአካባቢው፣ ለሌሎች ሰዎች ብሎም ለሀገሩና ለቀጣዩ ትውልድ እያሰበ፣ ለእነዚህ ሁሉ መልካም ሊያደርግ በሚችልበት መንገድ ሲወስን፣ ሲያደርግና ሲከውን ነው፡፡ የአይሱዙው ሾፌራችን ከጎደሉት ነገሮች አንዱ ይኼ ነበር፡፡ እርሱ ራሱ መንገድ ማግኘቱን፣ ታጥፎ ለመሄድና የራሱን ጉዳይ ለመፈጸም መቻሉን እንጂ በአካባቢው፣ በሌሎችና በሀገሩ ላይ የሚያስከትለውን ችግር ለማሰብ ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ለምሳሌ እንዲህ ማሰብ ይችል ነበር፡፡ ከኋላዬ መንገድ የተዘጋበት አምቡላንስ አለ፤ በአምቡላንሱ ውስጥ ደግሞ ልትወልድ ምጥ የተያዘች ሴት አለች፤ ከኋላዬ ልጆቹ አደጋ ውስጥ ናቸው ተብሎ ከቢሮው የተጠራ አባት አለ፤ በአስቸኳይ ነድቶ ልጆቹን መታደግ ይፈልጋል፤ ከኋላዬ የቆሙት መኪኖች ያለ አግባብ ቆመው የሚለቅቁት ጢስ አካባቢውን እየበከለው ነው፤ እኔ መንገዱን በመዝጋቴ አውቶቡስና ታክሲ የሚጠብቁ ሰዎች በፀሐይ እየተንቃቁ ነው፤ አሳቢነት ከሌለ እነዚህን ነገሮች የሚያስበውን ልቡና ስግብግብነት ስለሚጫወትበት ችግር ፈጠሪ እንጂ ችግር ፈቺ መሆን አይቻልም፡፡ አሳቢነት በሌለው ሰውና በሌላቸው ወገኖቹ ዘንድ በሌሎች ሰዎች መብት ላይ መጫወት፣ ሌሎችን ሰዎች ማታለል፣ የሌሎችን ሰዎችን ሰልፍ ጥሶ መቅደም፣ ቆሻሻን ከግቢ አውጥቶ መንገድ ዳር መድፋት፣ጊዜው ያለፈበት ምኃኒትና ምግብ መሸጥ፤ በዘመድ ቅድሚያ ማግኘትና ሌሎችም እንደ አራድነት ይቆጠራሉ፤ አድራጊዎችም ይሞገሳሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ለጊዜው የራሳቸውን ችግር እየፈቱ ይመስላቸዋል እንጂ ውስብስብ ችግር በራሳቸውም ላይ እየፈጠሩ ይሄዳሉ፡፡ አራዳነት የሚሠራው የበለጠ አራዳ እስኪመጣ ድረስ ነው፡፡ አራዳነትን የችግር መውጫ የሚያደርጉት የበለጠ አራዳ ሲመጣ ችግር ላይ ይወድቃሉ፡፡
ሰውየው ከጓደኛው ጋር ወርቅ ሊዘርፉ ይሄዳሉ፡፡ አንድ ሀብታም ሰው ቤት ገብተው ወርቅ ይዘርፉና ወደ ጫካ ገቡ፡፡ እዚያ ጋደም ብለው በየራሳቸው እንዲህ ሲሉ በየራሳቸው አሰቡ፡ ዛሬ ይኼ ሰው ባይኖር ኖሮ ይኼ ሁሉ ወርቅ የእኔ ብቻ ይሆን ነበር፡፡ እንዴት ብቻቸውን ሊወስዱ እንደሚችሉም አውጠነጠኑ፡፡ አንደኛው ለሌላኛው ‹እባክህ ከተማ ገብተህ በምታውቀው መንገድ ምግብ ግዛ› አለው፡፡ ያም ብቻውን ለማሰብ ጊዜ ማግኘቱን ሲያይ እሺ ብሎ ከተማ ሄደ፡፡ ጫካ የቀረውም ‹‹አሁን እንደመጣ በዚህ ጩቤ ሆዱን እዘረግፈውና ብቻዬን ወርቁን እወስዳለሁ› ብሎ ተዘጋጀ፡፡ ምግብ ሊገዛ የሄደውም ‹እዚህ እንጀራ ላይ መርዝ ነስንሼ እሰጠዋለሁ› ብሎ አዘጋጅቶለት መጣ፡፡
እንደተገናኙ ጫካ የቀረው ጓደኛ የወዳጁን አንጀት በጩቤ ዘረገፈና ወርቁን ወረሰ፤ ከዚያም መሬት ላይ አረፍ ብሎ ጓደኛው ገዝቶ ያመጣውን እንጀራ ብቻውን በላ፡፡ ከደቂቃዎች በኋላም እርሱም በሞት ተከተለው፡፡ ወርቁም ጫካ ውስጥ ብቻውን ቀረ፡፡ ይህ ነባር ተረት ምንጊዜም ከአራዳ የሚበልጥ አራዳ መኖሩን እንድናስብና ራሳችንን ብቻ እንዳናይ የተተረተ ነው፡፡
ከአይሱዙው በስተግራ በኩል ያልፉ የነበሩ ባለመኪኖች ይህ ጎድሏቸው ነበር፡፡ ለሰከንዶች ቆመው አይ ሱዙው የፈጠረውን ችግር ቢፈቱት አያሌ የማያውቋቸውን ችግሮች ሊፈቱ እንደሚችሉ አላሰቡም፡፡ ከኋላ ታግተው የተያዙ ከሠላሳ በላይ መኪኖችን ችግሮች እንደሚፈቱ፤ ምናልባትም ደግሞ ሳያስቡት የእነርሱንም ችግሮች አብረው እንደሚፈቱ የሚያገናዝቡበት ዐቅም አልነበራቸውም፡፡ ከኋላ ማን እንዳለ ማን ያውቃል? ሚስት? ልጅ? ወንድም? እናት? አባት? ጎረቤት?
አንድ ወዳጄ እንዲህ አጫውቶኝ ነበር፡፡ አንድ ሐኪም በሥራ መካከል ለሻሂ በሄደበት ጊዜ በድንገት ከሐኪም ቤቱ ይደወልለታል፡፡ ስልኩን ማንሣት ግን አልፈለገም፡፡ በአንድ በኩል ከጓደኞቹ ጋር ሻሂ መጠጣት ፈልጓል በሌላ በኩልም ትንሽ ሞቅ ያለ ወሬ ይዟል፡፡ ከአንድ ሰዓት በኋላ ወደ ሕክምና ጣቢያው ሲመለስ ግን ጆሮ ጭው የሚያደርግ ነገር ነበር የገጠመው፡፡ የገዛ ወንድሙ በመኪና አደጋ ተጎድቶ በድንገተኛ ነበር የመጣው፡፡ ደም ይፈስሰው ነበር፤ ነርሶቹ ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ አደረጉ፤ ነገር ግን ሕይወቱን ሊታደጓት እልቻሉም፡፡ ማን ያውቃል የሐኪሙ መምጣት የሚፈጥረው ነገር ይኖር ነበር፡፡ አሳቢነት ያለው ሰው ምንጊዜም ነገሮችን አርቆ አያስባቸውም፤ ያቀርባቸዋል፡፡ በራሱ ላይ፣ በወገኑ ላይ፣ በቤተ ሰቡ ላይ እንደተፈጸሙ አድርጎ ይቆጥራቸዋል፡፡
ችግር ፈቺ ዜጋ አሳቢነትን ገንዘብ ከማድረጉም በተጨማሪ ኃላፊነትም ይሰማዋል፡፡ ራሱን ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ይህን መሥራት ግዴታዬ ነው ብሎ ያስባል፡፡ ለነገሮች የኦሪት ፍየል አይፈልግም፡፡ የኦሪት ፍየል ፍለጋ ማለት ለአንድ ነገር የሚጠየቅ፣ የሚቀጣ ሌላ አካል ፍለጋ ማለት ነው፡፡ አይሱዙውን ያሳለፈው ሰው ይህ ነገር ሳይኖረው አይቀርም፡፡ ይህንን የተወሳሰበ የትራፊክ መጨናነቅ መፍታት ያለበት የትራፊክ ፖሊሱ ነው ብሎ አላሰበም፤ ወይም ለዚህ ሁሉ ችግር ተጠያቂው ይህ የአይ ሱዙ ሾፌር ነው ብሎ የሚያመካኝበት አካል አልፈለገም፡፡ ከዚያ ይልቅ ይህንን ችግር መፍታት የእኔ ድርሻ ነው፤ እችላለሁም ብሎ አሰበ፡፡ ስለዚህም መኪናውን አቁሞ አይሱዙውን አሳለፈው፤ ችግሩም ተፈታ፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ ይህንን መሰል ሰዎች ብናገኝ ኖሮ ‹አለቃዬ የሉም፣ መመሪያ የለም፣ እኔን አይመለከትም፣ ሌላ ጊዜ ና› የሚሉ አታካችና አድካሚ መልሶች አይኖሩም ነበር፡፡ አንድ ሰው እርሱ ራሱ ሊወስን ባይችል እንኳን ለሚወስነው ሰው ሃሳብ መስጠት፣ ወደሚወሰንበት ቦታ በትክክል ማስተላለፍ፣ መከታተል፣ መረጃ መስጠት ይችላል፡፡ መቼም ፋይሉ ራሱ ተነሥቶ ወደ አለቅዬው ዘንድ አይሄድም፡፡
ሚኒያፖሊስ የሚኖር አንድ ወዳጄ እንዲህ አጫውቶኝ ነበር፡፡ ከሥራ በምትተርፈው ጊዜ በግል መኪናው ኢትዮጵያውያንን  መኪና ያለማምድ ነበር፡፡ ሥራው  ፈቃድ ያስፈልገዋል፡፡ እርሱ ግን ፈቃድ የለውም፡፡ ፈቃድ ስለሌለውም ከአካባቢው ራቅ ብሎ በከተማ ጥግ ባሉ መንደሮች መንገድ ላይ ነበር የሚያለማምደው፡፡ ለብዙ ጊዜ ከሠራ በኋላ አንድ ቀን ስለ መኪና ማቆም አንዲትን ልጅ ለማሳየት ወደ አንድ መንገድ ዳር ይወጣል፡፡ በዚያ መንገድ አጠገብ አንድ ቤት አለ፡፡ አንዲት በእድሜ ገፋ ያለች ሴት ከቤቱ ወጣችና ወደ እርሱ መጣች፡፡ መኪናውን ተጠግታም ‹አንተ ሰው እዚህ ሠፈር ምንድን ነው የምታደርገው? የተለያዩ ሰዎች እየያዝክ ትመጣለህ፣ እዚህም ለጥቂት ጊዜ ትቆማለህ፣ በዙ ጊዜ ተከታትዬሃለሁ፣ ፎቶ ግራም አንሥቼሃለሁ፣ የተፈጠረ ችግር ስለሌለ ግን ዝም ብያለሁ፤ ለመሆኑ ምን እያደረግክ ነው?› ብላ ጠየቀችው፡፡ እርሱም ደንግጦ እኅቶቹን መኪና እያለማመደ መሆኑን ነገራት፡፡ ‹ስንት እኅቶች ናቸው ያሉህ?› አለችው ተገርማ፡፡ ከዚያ በኋላ እዚያ አካባቢ ሄዶ አያውቅም፡፡
ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ እንደዚህ ነው፡፡ አንድን ነገር ለመከታተል፣ ለማድረግ ወይም መረጃ ለመያዝ፣ በአንድ ጉዳይ ላይ የሚችለውን ለማድረግ የማንንም ማነሣሣት፣ ውክልና፣ ሹመት ወይም መመሪያ አይጠብቅም፤ እርሱ ለማድረግ መልካም የመሰለውንና፣ ሕግም የሚፈቅደውን ያደርጋል፡፡ ሀገሬን፣ ሕዝቤን፣ ወገኔና የመታደግ ኃላፊነት አለብኝ ብሎ ያምናል፡፡ ኃላፊነቱንም ራሱ ከራሱ ይቀበላል፡፡ በአምስት ዓመቱ የጣልያን ወረራ ጊዜ በየጫካው ገብተው ጠላትን ፋታ የነሡት አርበኞች ይህ ነገር ነበራቸው፡፡ የመከላከያ ሚንስቴር እንዲያሠማራቸው አልጠበቁም፣ ለሀገራቸው ነጻነት ራሳቸው ኃላፊነቱን ወስደው ተዋጉ፡፡ ምንም አልሾማቸውም፣ ራሳቸውን ሾሙ፤ ማንም አልቀጠራቸውም፣ ራሳቸውን ቀጠሩ፡፡
ይህ ኃላፊነት የመውሰድ ችሎታ ነው ራስን ለተልዕኮ የሚያሠማራው፡፡ ሰው ማሰብ ከቻለ፣ ኃላፊነትንም ከወሰደ ራሱን ለአንዳች ተልዕኮ ያሠማራል፡፡ የሁለቱም ነገሮች መገለጫቸው ተግባር ነውና፡፡ ያ ከፊታችን የነበረው ሾፌር ስለሌሎች አሰበ፣ ችግሩን የመፍታት ኃላፊነትንም ወሰደ፡፡ እነዚህ ሁለቱ በሦስተኛው ነገር ባይታጀቡ ኖሮ ጥቅም አይኖራቸውም ነበር፡፡ ተልዕኮን በመውሰድ፡፡ ያ ሾፌር መኪናውን አቁሞ አይሱዙውን የማሳለፍ ተልዕኮን ራሱ ወሰደ፡፡ ከፊታችሁ ቀድመዋችሁ ከገቡ በኋላ በሩን ይዘው የሚያሳልፏችሁ ሰዎች፣ እናንተ የጣላችሁትን ቆሻሻ አንሥተው ቅርጫት ውስጥ የሚጨምሩ ሰዎች፣ ደክሟችሁ መምጣታችሁን አይተው ወንበር የሚለቁላችሁ ሰዎች፣ ታክሲ ውስጥ ሽማግሌዎች ሲመጡ የፊት ወንበራቸውን ለቅቀው ወደ ኋላ የሚጠጉ ሰዎች፣ ለነፍሰ ጡር ሴቶች ቅድሚያ የሚሰጡ ሰዎች፣ ቤታችሁ መጥተው ቁጭ ሳይሉ ቤታችሁን ማስተካከል የሚጀምሩ ወዳጆች፣ በአንዳች ነገር ተቸግራችሁ ሲያዩ የመፍትሔውን አቅጣጫ የሚያመለክቷችሁ ሰዎች፣ ለነጻነትና እኩልነት፣ ለፍትሐዊነትና ለሰብአዊ መብት ተቆርቁረው የሚታገሉ ሰዎች ሌሎች አይደሉም፣ አሳቢነትን ገንዘብ አድርገው፣ ኃላፊነትንም ወስደው ለራሳቸው ተልዕኮ የሰጡ ሰዎች ናቸው፡፡
ራሳቸውን ለተልዕኮ ያሠማሩ ችግር ፈቺ ዜጎች ናቸው የዓለማችንን ችግሮች ያቃለሉ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ሃሳቦችን ያመነጩት፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ እሳቤዎችን ጽንሰ ሃሳቦች የቀረጹት፣ ለሰላም ላይ ታች ያሉት፣ እንደ ጧፍ ነድደው እንደ መብራት ያበሩት፤ ራሳቸውን ለተልዕኮ ያሠማሩ ችግር ፈቺ ዜጎች በመኖራቸው ነው በየቢሮው፣ በየተቋማቱ፣ በየጤና ጣቢያው፣ በየቴሌ ቅርንጫፉ ቢያንስ የባሰ ችግር እንዳይፈጠር ያደረጉት፤ እነዚህ ዜጎች ናቸው ሀገራችንን የተሸከሙት፤ እነርሱ ሲበዙ ዕድገታችንና ብልጽግናችን፣ ዴሞክራሲያችንና የፖለቲካ ባህላችን፣ ማኅበራዊ መስተጋብራችንና የኑሮ ደረጃችን ይሻሻላል፡፡ እነርሱ ሲያንሱ ደግሞ ሙስናና ብልሹ አሠራር፣ አምባገነንነትና ስግብግበነት፣ ችግርና ጠኔ፣ ቀጠናና ችጋር፣ ቢሮክራሲና የዘመድ አሠራር፣ ትብትብና ውስብስብነት፣ ምሬትና ሮሮ፣ ኋላ ቀርነትና ድህነት፣ ድንቁርናና ማይምነት ሀገርን እጅ ተወርች አሥረው ይይዟታል፡፡
ችግር ፈቺ ዜጋ ባልበቀለበት ሀገር ችግር ፈቺ ፖለቲከኛ፣ ችግር ፈቺ መሪ፣ ችግር ፈቺ፣ ምሁር፣ ችግር ፈቺ የሃይማኖት አባት፣ ችግር ፈቺ  ነጋዴ፣ ችግር ፈቺ ቢሮክራት፣ ችግር ፈቺ የፍትሕ ሰው፣ ችግር ፈቺ ፖሊስ፣ ችግር ፈቺ ሐኪም፣ ችግር ፈቺ ጋዜጠኛ፣ ችግር ፈቺ ደራሲ፣ ችግር ፈቺ መሐንዲስ ማሰብ ሕልም ነው፡፡
ለዚህም ነው ጥቂቶች ችግር ፈቺ ዜጎቻችንን ‹ችግር ፈቺ ዜጎች ሆይ፣ እንደ ምድር አሸዋ እንደ ሰማይ ከዋክብትም ያብዛችሁ፤ እንደ ምድር አፈርና እንደ ሰማይ ጠል የበዛውን ችግራችንን ታስወግዱልን ዘንድ› ብለን መመረቅ ያለብን፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ስለሆነ በተመሳሳይ ሚዲያ መጠቀም ክልክል ነው

29 comments:

 1. Thank You Dani, አስተምሮኛል!!!

  ReplyDelete
 2. Tikikil Dani, inameseginalen, ‹ችግር ፈቺ ዜጎች ሆይ፣ እንደ ምድር አሸዋ እንደ ሰማይ ከዋክብትም ያብዛችሁ, Getaye Iyesus kirstos tsegawin yabizaleh!

  ReplyDelete
 3. You mentioned a great point here. Normally, in my opinion, the main problem we got is not the luck of wisdom, but jealousy and selfishness. Besides it is our bad habit not to allow and give power for knowledgeable people. We are seeing these problem from generation to generation. That is why many of our problems still exists. We can not build wide roads by ourselves, we can not have good communication technology, we can not have good health care officers or doctors and so on. All trained in Ethiopia but are now being exploited in other countries while we are paying for China's. That is because we do not allow the educated people to work and share his/her knowledge. Where are now the university graduates who were supposed to solve the societies problem. They have not given space to perform their jobs because they do not know how to fire a gun or kill. That is why we can not solve our problem.

  ReplyDelete
 4. ሰውየው ከጓደኛው ጋር ወርቅ ሊዘርፉ ይሄዳሉ፡፡ አንድ ሀብታም ሰው ቤት ገብተው ወርቅ ይዘርፉና ወደ ጫካ ገቡ፡፡ እዚያ ጋደም ብለው በየራሳቸው እንዲህ ሲሉ በየራሳቸው አሰቡ፡ ዛሬ ይኼ ሰው ባይኖር ኖሮ ይኼ ሁሉ ወርቅ የእኔ ብቻ ይሆን ነበር፡፡ እንዴት ብቻቸውን ሊወስዱ እንደሚችሉም አውጠነጠኑ፡፡ አንደኛው ለሌላኛው ‹እባክህ ከተማ ገብተህ በምታውቀው መንገድ ምግብ ግዛ› አለው፡፡ ያም ብቻውን ለማሰብ ጊዜ ማግኘቱን ሲያይ እሺ ብሎ ከተማ ሄደ፡፡ ጫካ የቀረውም ‹‹አሁን እንደመጣ በዚህ ጩቤ ሆዱን እዘረግፈውና ብቻዬን ወርቁን እወስዳለሁ› ብሎ ተዘጋጀ፡፡ ምግብ ሊገዛ የሄደውም ‹እዚህ እንጀራ ላይ መርዝ ነስንሼ እሰጠዋለሁ› ብሎ አዘጋጅቶለት መጣ፡፡
  እንደተገናኙ ጫካ የቀረው ጓደኛ የወዳጁን አንጀት በጩቤ ዘረገፈና ወርቁን ወረሰ፤ ከዚያም መሬት ላይ አረፍ ብሎ ጓደኛው ገዝቶ ያመጣውን እንጀራ ብቻውን በላ፡፡ ከደቂቃዎች በኋላም እርሱም በሞት ተከተለው፡፡ ወርቁም ጫካ ውስጥ ብቻውን ቀረ፡፡ ይህ ነባር ተረት ምንጊዜም ከአራዳ የሚበልጥ አራዳ መኖሩን እንድናስብና ራሳችንን ብቻ እንዳናይ የተተረተ ነው፡፡

  እግዚአብሔር ዕድሜህን ያርዝምልህ እንድትጽፍልን

  ReplyDelete
 5. እግዚአብሔር ይስጥልን ዳንኤል

  ችግር ፈቺ ዜጎች ሆይ፣ እንደ ምድር አሸዋ እንደ ሰማይ ከዋክብትም ያብዛችሁ፤ አሜን፡፡

  ReplyDelete
 6. ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ እንደዚህ ነው፡፡ Thank You Dani,

  ReplyDelete
 7. ችግር ፈቺ ለመሆን አምላክ አስተዋይ አይምሮ ያብቃን አሜን

  ReplyDelete
 8. Egziabher yistih! legnam libona yisten! abzagnochachin kerasachin wichi maseb yalemedebin nen ena!

  ReplyDelete
 9. ያበርታልን!!!...በአምስት ዓመቱ የጣልያን ወረራ ጊዜ በየጫካው ገብተው ጠላትን ፋታ የነሡት አርበኞች ይህ ነገር ነበራቸው፡፡ የመከላከያ ሚንስቴር እንዲያሠማራቸው አልጠበቁም፣ ለሀገራቸው ነጻነት ራሳቸው ኃላፊነቱን ወስደው ተዋጉ፡፡ ምንም አልሾማቸውም፣ ራሳቸውን ሾሙ፤ ማንም አልቀጠራቸውም፣ ራሳቸውን ቀጠሩ፡፡

  ReplyDelete
 10. ዲ/ን ዳንኤል የተፈጠርልን የካፒታሊስት ስርዓት ችግር ይፈታል ቢባል እንኳን ሰብዓዊነት ይጎለዋል:: መሰረቱ ስግብግብነት ነዉ:: መሰረቱ ብዝበዛ ነዉ:: ጉልበት ይበዘበዛል: ሃብት ይበዘበዛል: እዉቀት ይበዘበዛል : ወዘተ:: እኔነት ነግሷል:: ያቺ ቲንሿ ጨዉ ሰዉን ምን ያህል ራስ ወዳድ እንዳደረገችን የቅርብ ግዜ ትዝታ ነዉ:: አንድ ቤት ያለዉ 2 እንዲኖረዉ 2 ያለዉ 3 እንዲኖረዉ:: መጋፋት ነዉ : ሰልፍ ነዉ:: እኔ ልቅደም እንጂ እሳቸዉ ይቅደሙ ለማለት ስርዓቱ አይፈቅድልህም:: የስርዓቱን ህግ አክብረህ መጫወት ካልሆነም እንዳንተ ደጋግ አሳቢዎች በዝተዉ ስርዓቱን መቀየር መፍተሄ ነዉ:: አንተ ግን ስለ ደጋግ ሃሳቦችህ ፈጣሪ ሚሊዮኖችን በሃሳብህ ዙሪያ ያሰልፍልን

  ReplyDelete
 11. Please send to all Addis Ababa Sub City Land Administration on their P.O.Box. I will cover the cost.

  ReplyDelete
 12. Please send this writing to all Addis Ababa sub city Administration on their P.O.Box, I will cover the mail cost

  ReplyDelete
 13. ችግር ፈቺ ጸሃፊም እንዲህ ነው።
  እግዚአብሔር ይስጥልን

  ReplyDelete
 14. ጥሩ ብለሃል!!
  "አሳቢነት አንድ ሰው ማንኛውንም ነገር ሲወስን፣ ሲያደርግና ሲከውን ለአካባቢው፣ ለሌሎች ሰዎች ብሎም ለሀገሩና ለቀጣዩ ትውልድ እያሰበ፣ ለእነዚህ ሁሉ መልካም ሊያደርግ በሚችልበት መንገድ ሲወስን፣ ሲያደርግና ሲከውን ነው፡፡"
  ከትም

  ReplyDelete
 15. weye Dani ye isuzu sufare meche cegere fetari becah sayhonue nefseh atftwem endegari ferese mgalbe becah newe yensue sera Enatane gedlo ytfaw eskzara altyazem ande amet lymolat ande wereh newe ykrate Ehzbhere lbona ysetcew antenm ybarkhe berta

  ReplyDelete
 16. ዳኔ ግሩም ምክር ነው ሰሜ ካለ ፤የዝሆን ጆሮ የስጠኝ ከልተባለ።

  ReplyDelete
 17. ችግር ፈቺ ሰው የሚታወቀው በማድረጉ ነው፡፡

  ReplyDelete
 18. Good observation ?

  ReplyDelete
 19. Dn.Dani,Egzabher yebarkehi

  ReplyDelete
 20. ግሩም እይታ ነው ዲያቆን ግን ምን ይደረግ ችግር ቋጣሪዎች እኮ በዛን አረ አንድ እንባባል

  ReplyDelete
 21. When I evaluate my self, some what,I am one of the" chigir fechi" people. I use rules & regulations in our organization in the way to solve problems, not as hinderance, But staffs always say me why u do this for others don't risk ur self etc... But until now nothing happened. I am free of any personal benefits.I will strengthen it. Thanks

  ReplyDelete
 22. ከሥራ በምትተርፈው ጊዜ በግል መኪናው ኢትዮጵያውያንን መኪና ያለማምድ ነበር፡፡ ሥራው ፈቃድ ያስፈልገዋል፡፡ እርሱ ግን ፈቃድ የለውም፡፡ ፈቃድ ስለሌለውም ከአካባቢው ራቅ ብሎ በከተማ ጥግ ባሉ መንደሮች መንገድ ላይ ነበር የሚያለማምደው፡፡ woyne I like this man. So respected person.There are lots of good Ethiopians.God bless them.

  ReplyDelete
 23. ሁሌም የሚያበሳጨኝን እንዲሁም የሀገራችንን ሰው ራስ ወዳድነትና አርቆ አለማስተዋልን ከሚያስገነዝበኝ ሁኔታ አንዱን በመጥቀስህ አመሰግናለሁ፡፡ ሁሌም ትራፊክ በሌለበት መስቀለኛ መንገድ መቅደም ያለበትን መኪና ለሰከንዶች ቅድሚያ መስጠት አቅቶዋቸው ለሰዓታት ተሳስረው የሚቆሙ፤ በግራ የሚሄዱበት መስመር ለደቂቃዎች ስለተጨናነቀ ባልተገባ የቀኝ መንገድ ገብተው የሌላ አቅጣጫ ተጓዥ መኪኖችን የሚያደናቅፉ አሽከርካሪዎች፤ እንዲሁም የተለያየ ጉዳይ ሰልፍ በተያዘበት ቦታ ጣልቃ እየገቡ የሚሰለፉ የግለሰቦችን ራስወዳድነት ብቻ ሳይሆን የሚያንፀባርቁት የማህበረሰባችንን አሉታዊ አስተሳሰብ ነውና ወዮ ለሀገሬ የሚያስብል ነው፡፡
  የቤቶች ምዝገባን ግርግር ማየት ለዚህ በቂ ነው፡፡ መዝጋቢዎቹ ሥርዓትን የተከተለ ማስተናገጃ ቀድመው አላሟሉ ተስተናጋጁ ሥርዓቱን ጠብቆ ለመስተናገድ ፈቃደኛ አልሆነ….. ሁሌም እኔ ብቻ ልቅደም ሁላችንንም ወደኃላ እንዳስቀረን ብንገነዘብ እንዴት መልካም በሆነ!!!

  ReplyDelete
 24. ትውልዱ ቅንነት ቅንቅን ሆኖበት ነው ያለው የአውሬው መንፈስ ገና አልተሰበረም በውስጡ ስለዚህ ቢነገር እንደ መድሃኒት በመርፊ ቢወጋ ወደ መልካምነት የማይመጣ ሰው ስላላ ምን ታረገዋለህ እግዚያብሄር ይርዳው እያልክ መፀለይ ነው እንጂ!!

  ReplyDelete
 25. Dani
  Reading this article is like seeing one's image in a mirror.

  I would like to appreciate your witty observation.

  From Dessie

  ReplyDelete
 26. ‹ችግር ፈቺ ዜጎች ሆይ፣ እንደ ምድር አሸዋ እንደ ሰማይ ከዋክብትም ያብዛችሁ፤ እንደ ምድር አፈርና እንደ ሰማይ ጠል የበዛውን ችግራችንን ታስወግዱልን ዘንድ›

  አሜን ነው የሚባለውአሜን

  ReplyDelete
 27. ችግር ፈቺ ዜጋ ባልበቀለበት ሀገር ችግር ፈቺ ፖለቲከኛ፣ ችግር ፈቺ መሪ፣ ችግር ፈቺ፣ ምሁር፣ ችግር ፈቺ የሃይማኖት አባት፣ ችግር ፈቺ ነጋዴ፣ ችግር ፈቺ ቢሮክራት፣ ችግር ፈቺ የፍትሕ ሰው፣ ችግር ፈቺ ፖሊስ፣ ችግር ፈቺ ሐኪም፣ ችግር ፈቺ ጋዜጠኛ፣ ችግር ፈቺ ደራሲ፣ ችግር ፈቺ መሐንዲስ ማሰብ ሕልም ነው፡፡

  ReplyDelete