Friday, June 28, 2013

ማንዴላ


click here for pdf
አንዳንዱ የሞተበት ቀን የድል ቀን ተብሎ ይከበርበታል፤ ሕዝብ የመሞቻውን ቀን የሚናፍቁለት ሰውም አለ፡፡ አንዳንዱ እንኳን ተወለደ ሳይባልለት እንኳን ሞተ ይባልለታል፡፡ አንዳንዱ እንዲሞት ይጸለይለታል፤ ሌላው እድሜው እንዲያጥር ይረገማል፡፡ ከዚህ የተለየ ነው ማንዴላ፡፡
ሚሊየኖች እንዳይሞት የሚጸልዩለት፤ ሚሊየኖች እንዲኖር የሚመኙለት፤ ሚሊየኖች ከእድሜያቸው ተቀንሶ ቢሰጠው የሚፈቅዱለት፤ ሚሊየኖች እነርሱ ሞተው ሊያኖሩት የሚሹት፤ ሚሊየኖች በየቀኑ የጤናውን ሁኔታ ከራሳቸው ጤና በላይ የሚከታተሉለት ሰው ነው ማንዴላ፡፡

Tuesday, June 25, 2013

‹‹ሥልጣን ልቀቁ?››click here for pdf
ኢትዮጵያ ከቦትስዋና ጋር ስትጫወት ተገቢ ያልሆነ ተጨዋች አሰልፋችኋልና ሦስት ነጥብ ታጣላችሁ ብሎ ፊፋ የሚባል ቡዳ አገሩን ቀወጠው፡፡ እንደ አውነቱ ከሆነ እንዲህ ዓይነት ነገር ማድረግ የሌለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ፊፋ ከአድኅሮት ኃይሎች ጋር ካልተሰለፈ በቀር ሌላ ምክንያት ሰጥቶ ኢትዮጵያን መጣል ይችል ነበር፡፡ ለኛ የኢትዮጵያ ነጥብ መቀነስ አይደለም ችግራችን፤ ነጥቡ መቀነሱን ሕዝቡ መስማቱ ነው፡፡ እኛኮ ቀስ አድርገን ‹ኪራይ ሰብሳቢዎች የሀገራችንን የስፖርት ራእይ ለማደናቀፍ ከፀረ ሕዝብ ኃይሎች ጋር በመሆን የደቀኑብን ሤራ ነው› ብለን ሕዝቡን ማሳመን እንችል ነበር፡፡
መጀመሪያ ከበላዮቻችን ጋር እንነጋገራለን፤ ሂስ ከተሰጠንም ሂሳችንን እንውጣለን፣ ግምገማችንንም እንቀበላለን፣ ዋናው ይሄ አይደለም፤ አንዴት አድርገን ለሕዝቡ እንንገረው? የሚለው ነው፡፡ ሕዝብ እንደነገርከው ነው፡፡ እንደ አሰማሙ ነው፡፡ አቀናብረን ከነገርነው አቀናብሮ ይሰማል፡፡ ግን ምን ያደርጋል፣ ፊፋ የሚባል ቡዳ ለሕዝብ መነገር የሌለበትን ለሕዝብ ተናገረና መከራ አሳየን፡፡
አሁን አዳሜ ዕድል ስታገኝ ጊዜ ‹ለምን ሥልጣን አትለቁም› ትላለች፡፡ 

Thursday, June 20, 2013

የሐረር የታሪክ አባት


ሐረር ከተማ የገባ ሰው ታሪካዊ ነገር የሚያምረው ከሆነ የከተማው ነዋሪ ወደ አንድ ቦታ ይወስደዋል፡፡ ቦታው ራስ ተፈሪ መኮንን የሐረር ገዥ በነበሩ ጊዜ ከእቴጌ መነን ጋር ይኖሩበት የነበረ ቤት ነው፡፡ ዛሬ ወደ መቶ ዓመታት እድሜ አስቆጥሯል፡፡ የበሩ መቃን ላይ በግእዝ ‹ዝ ቤት ዘደጃዝማች ተፈሪ መ. ሐረር ገዥ አውራጃ  ፩፱፻፫ ››
ይላል፡፡ ወደ ውስጥ ስትዘልቁ አንድ ከትከሻቸው ደልደል፣ ከመልካቸው ጠየም፣ ከቁመታቸው መካከለኛ የሆኑ ሰው ታገኛላችሁ፡፡ ሰውዬው የተማሩት የአካውንቲንግ ሞያ ነው፡፡ ጭላሎ አግሪካልቸራል ደቨሎፕመንት ዩኒት ከተባለ ተቋም ነበር በዲፕሎማ የተመረቁት፡፡ መጀመሪያ የሐረርጌ ክፍለ ሀገር ኦዲተር፣ ከዚያም የሐረሪ ክልል ሲመሠረት የክልሉ ዋና ኦዲተር ሆነው ሠርተዋል - ሼክ አብዱላሂ ሸሪፍ፡፡
የሐረር ሰውም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን እኒህን ሰው የሚያውቃቸው በአካውንታንትነታቸውም ሆነ በኦዲተርነታቸው አይደለም፡፡ እርሳቸው ከዚያም በላይ ከብረዋል፤ ከዚያም በላይ አገልግለዋል፣ ከዚያም በላይ ታምነዋል፣ ከዚያም በላይ በሕዝቡ ልብ ውስጥ ነግሠዋል፡፡ 

Monday, June 17, 2013

ይኼ ሰው ጀግና ነው

አበሻን በአንድ እግሩ ያስቆመ፤ ለሃያ አራት ሰዓታት የመግቢያ ትኬት ፍለጋ ያሰለፈ፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የብሔራዊ ቡድኑን ዐርማ የያዙ ቲሸርቶች እንዲቸበቸቡ ያደረገ፤ ሕዝብ እንደ መንጋ ንብ አንድ ዓይነት ዜማ እንዲያዜም ያስቻለ፤ ሽማግሌን እንደ ሕጻን ያስጨፈረ፤ ሕጻንን እንደ ሽማግሌ ያስተከዘ፤ የፓርቲና፣ የዘር፣ የእምነትና የባህልን አጥር አስጥሶ ወገንን በአንድነት ገመድ ያስተሣሠረ፤ ይኼ ሰው ጀግና ነው፡፡
ተረስተን ነበረ፤ ረስተንም ነበረ፤ ርቀን ነበረ፤ ተርቀንም ነበረ፤ ተርተን ነበረ፤ ተረት ሆነንም ነበረ፤ እግርን ከኳስ አውጥተን ለሩጫ ብቻ አውለነው ነበረ፤ እንዲያ በሩጫ ዓለምን አስደምመን፣ ኳስ ሜዳ ግን ዘጠና ደቂቃ መሮጥ አቅቶን ደክሞን ነበረ፡፡ ሕዝባችን ከካምቦሎጆ ኳስ ወደ ዲ ኤስ ቲቪ ኳስ ፊቱን አዙሮ ነበረ፡፡ ይህንን ቀይሮ በአፍሪካ ምድር ከ31 ዓመታ በኋላ ብቅ እንድንል ያደረገ፤ በዓለም መድረክ ‹እኛም አለንበት› እንድንል ያስቻለ - ይኼ ሰው ጀግና ነው፡፡

Thursday, June 13, 2013

ዶስሌ
አንዱ የሀገሬ ሰው በአምስት ዓመቱ የጣልያን ወረራ ጊዜ ተሰድዶ ሱዳን ይገባል፡፡ እዚያ ገዳሪፍ እያለ ትልቁ ችግሩ ውኃ ማግኘት ነበረ፡፡ እርሱ ደግሞ የተወለደውም ያደገውም ዓባይ ከጣና ተለይቶ በሚወጣባት ደብረ ማርያም በምትባለው ደሴት አጠገብ ነበርና እንዲያ በጀልባ እየቀዘፈ፣ በዋና እየሰነጠቀ፣ ዓሣ እያጠመደ፣ ጉማሬ እያሳደደ፣ ጳልቃን (ፔሊካን) መሥመር ሠርተው በሚዋኙት ዋና እየተዝናና፣ ጎመንና ሸንኮራ ተክሎ ወረታ ገበያ እያቀና ነበርና ያደገው፣ ‹ይህማ የሀገሬ ውኃ ግፍ ነው› እያለ ይጸጸት ጀመር፡፡
ዓባይ እየተገማሸረ ሲወርድ ጣና በማዕበል ሲናወጥ ከቁም ነገር ቆጥሯቸው አያውቅም ነበርና፣ ዛሬ በባዕድ ሀገር ሆኖ ሲያስታውሰው  አንገሸገሸው፡፡ ውኃ መከበሪያ ሆኖ፣ ውኃ ያለው ሰው እንደ ጌታ ሲታይ ‹የጎረቤት ጠበል የቆዳ መንከሪያ ይሆናል› የሚለው ተረት እየመጣበት ተቃጠለ፡፡ ተቃጥሎም አልቀረ ለትውልድ የተረፈ ሁለት መሥመር ግጥም ገጠመ

ውኃ እንደ ቁም ነገር ሰውን ካስከበረ
ዓባይና ጣና ሀገሬ ነበረ

Tuesday, June 11, 2013

ችግር ፈቺ ዜጋ


በቀደም ዕለት ከመገናኛ ወደ ሲኤም ሲ በሚወስደው መንገድ ላይ እየተጓዝን አንድ አይ ሱዙ መኪና ከጎናችን መጣ፡፡ እኛ ወደ መንገዱ ጠርዝ ተጠግተን ነበር የምንነዳው፡፡ አይ ሱዙ መኪናው የመጣው ከመንገዱ ጠርዝ ቀጥሎ በስተ ቀኝ ከሚገኘው መሥመር ነው፡፡ ወደ መንገዱ ማቋረጫ ላይ ሲደርስ ወደ ግራ ለመጠምዘዝ ፍሬቻ ማብራት ጀመረ፡፡ የነበረበት መሥመር በቀጥታ ለመንዳት እንጂ ለመጠምዘዝ የሚያስችል አልነበረም፡፡ ምክንያቱም በስተግራው ሌሎች መኪኖች ማለፍ ይችላሉና፡፡ አይሱዙው ግን መሐል መንገድ ላይ ቆሞ ፍሬቻ እያበራ አሳልፉኝ ማለት ቀጠለ፡፡ በግራ መንገዱ በኩል የማለፍ መብት የተሰጣቸው መኪኖች ከቁብ ሳይቆጥሩት ጥለውት ያልፋሉ፡፡ ከአይሱዙው ኋላ የነበሩ ብዙ መኪኖች በመቆማቸው ምክንያት መንገዱ ተጨናነቀ፡፡ ይህንን ያየ ከፊታችን የነበረው ባለመኪና ቆመና አይሱዙው እንዲያልፍ አደረገው፡፡ ያን ጊዜ መንገዱ ተከፍቶ መጨናነቁ ተፈታ፡፡ የአይሱዙው ሾፌር ግን ላሳለፈው ሰው ምስጋናም ሳያቀርብ ፈትለክ አለ፡፡