የዘንድሮው የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ሲከፈት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ጉባኤው ሊያተኩርባቸው ብሎም ውሳኔ አሳልፎ ሊፈጽማቸው ይገባል ያሏቸውን አራት
መሠረታዊ ነገሮች አንሥተዋል፡፡
1.
ብልሹ አሠራርን ማረምና
ማስወገድ
2.
አስተዳደሩን በአዲስ መልክ
ማዋቀር
3.
የፋይናንስ አያያዝን
ማስተካከል
4.
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን
እንደገና ማዋቀር
በመጀመርያ ፓትርያርኩ ከተለመደው መወድሳዊና ቢሮክራሲያዊ ንግግር ወጣ ብለው በቤተ
ክርስቲያኒቱ ወቅታዊና አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ ማተኮራቸው የሚያስመሰግን ነው፡፡ ከተሰየሙ በኋላ የመጀመርያቸው በሆነው የቅዱስ
ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ላይ ያቀረቡት መክፈቻ ከሁለት ነገሮች አንጻር ተገቢም ተመስጋኝም ነው፡፡