Tuesday, April 30, 2013

ከ2000 ዓመት በኋላ እንደ አዲስ እንመዘገባለን፣ እንደ አዲስም እንታወቃለን


ሰሞኑን የፌድራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሃይማኖት ተቋማትን ለመመዝገብ የወጣ ረቂቅ መመሪያ› የሚል ወረቀት አስተያየት ይሰጥበት ዘንድ ለእምነት ተቋማት አሠራጭቷል፡፡ ይህ መመርያ የያዛቸውን ጉዳዮች እያንዳንዳቸውን እየነጠሉ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም ወደፊት የምናደርገው ይሆናል፡፡ ለአሁኑ ግን መመሪያውን ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ነባራዊ፣ ሉዓላዊና መንፈሳዊ ጠባያት ጋር በማዛመድ ብቻ እንመለከተዋለን፡፡
1.       መመሪያው የቤተ ክርስቲያኒቱን ልዩ ሁኔታ ከግምት ያላስገባ ነው
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላለፉት 2000 ዓመታት በምድሪቱ ላይ የኖረች፣ የሰበከች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ ክፉውንም ሆነ ደጉንም እኩል የቀመሰች፣ እንዲያውም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በመሆንዋ ብቻ ልዩ ጉዳት የደረሰባትም ናት፡፡ በጣልያን ወረራ ጊዜ የተሠውትን ጳጳሳትና መነኮሳት ማሰቡ ብቻ ለዚህ የቅርብ ምሳሌ ነው፡፡ ይህቺ ቤተ ክርስቲያን በዘመናት ሂደት ውስጥ በሀገሪቱ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሕይወት ውስጥ ልዩ የሆነና የማይተካ ሚና ተጫውታለች፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ተመሥርታ ሀገሪቱንም መሥርታለች፡፡
ይህንን ሁሉ ዘንግቶ በ2005 ዓም ላይ ቤተ ክርስቲያኒቱን እንደ አዲስ ተመዝገቢ፣ እንደ አዲስ ፈቃድ አውጭ፣ እንደ አዲስ ደንብና መመሪያሽን አምጭ ማለት እጅግ አሳዛኝም አስገራሚም ነገር ነው፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ራሱ ከፈለገ መረጃ ሰብስቦ መመዝገብና ማወቅ ነበረበት እንጂ ሰነድ አምጭ፣ ደንብ አስገቢ፣ ፈቃድ አውጭና ልወቅሽ ማለት አልነበረበትም፡፡

Tuesday, April 23, 2013

አማርኛ ከሠላሳ ዓመት በኋላ 
የዛሬ ሠላሳ ዓመት በ2035 ዓም በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች መካከል የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ውድድር ይደረጋል፡፡ በውድድሩም ከዚህ በታች የማቀርብላችሁ ወግ ‹እኔና ትምህርት ቤቴ› በሚል ርእስ ተወዳድሮ አንደኛ ይወጣል፡፡
ይህ ኦፖርቹኒቲ ስለ ተሰጠኝ ታንክዩ፡፡ አቦ ይመቻችሁ፡፡ ሀገራችን ኢቶጲያ ሚራክልየስ ሀገር ናት፡፡ አይ ሚን ነፍስ ነገር ናት፡፡ ይህንን ስል ግን ሙድ እንዳትይዙብኝ፡፡ እዚህ ሀገር ብዙ ነገር ነፍ ነው ማለቴ ነው፡፡ ዋተር ነፍ ነው፣ ኦፕን ኤይር ነፍ ነው፣ ሰን ሴትና ሰን ራይዝ ነፍ ነው፡፡ ማዩንቴይን ነፍ ነው፤ የሚደብረው ነገር ሮዶቹና ቪሌጆቹ ምልክት የላቸውም፡፡ ፎር ኤግዛምፕል የኛን ቤት ለሰው ስንነግር ‹ኒር እንትና ጫት ቤት› ነው የምንለው፡፡ ቢኮዝ እዚህ ሀገር ጫት ቤት ነፍ ነዋ፡፡ አት ዚስ ፖይንት ኤክስፕሌይን ማድረግ አለብኝ፡፡ የአያቴን ካፕ ቦርድ ስሾፍ አዲስ ዘመን የሚባል አንድ የድሮ ኒውስ ፔፐር አገኘሁና፡፡ ኮለመኑ ላይ ‹በምግብ ራስን መቻል› የሚል ነገር ሾፍኩ፡፡ ነገሩ ክሊር አልሆነልኝም ነበር፡፡ ዋት ኢዝ ‹ራስን መቻል›? ራስ ማለት ‹ሄድ› አይለደም እንዴ? መቻልስ ምንድን ነው? አንዱን ፍሬንዴን አስክ ሳደርገው ‹መቻል የሚባል ኦልድ ውሻ ጎረቤታችን አለ› አለኝ፡፡ ስለዚህ ራስን መቻል ሚን ‹የመቻል ራስ› ማለት ነው፡፡ 

Tuesday, April 16, 2013

የዓመቱ ‹በጎ ሰው›

የዳንኤል ዕይታዎች ‹የዓመቱ በጎ ሰው› የምርጫ ኮሚቴ ሰባት አባላት ነበሩት፡፡ እነዚህ አባላት ከተለያዩ ሞያዎችና አካባቢዎች የመጡ ሲሆን በ‹የዳንኤል ዕይታዎች› አማካኝነት ለአንድ ወር ያህል አንባብያን ‹በጎ ሰው› የሚሉትን እንዲጠቁሙ ዕድል ተሰጥቶ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት በ159 ጠቋሚዎች 70 ግለሰቦችና ሰባት ተቋማት ተጠቁመዋል፡፡
እነዚህን 70 ኢትዮጵያውያንና ሰባት ተቋማትን አመዛዝነው አሥር ምርጦችን እንዲሰይሙ በተለያዩ ክልሎችና ሞያዎች ለሚገኙ እርስ በርሳቸውም ለማይተዋወቁ 9 ሰዎች ተሰጠ፡፡ በዚህም መሠረት ከጠቋሚዎችና ከመራጮች የተሻሉ ድምፆችን ያገኙ አሥራ ሰባት ሰዎች ተመረጡ፡፡
እነርሱም 

ዝክረ የዳንኤል ክብረት እይታዎች (፫ኛ ዓመት)ኃ/ገብርኤል ከአራት ኪሎ
የጉባኤው ድባብ
ሰላምና ጤናን የምመኝላችሁ፣ በሀገር ውስጥም በውጪም የምትገኙ የዚህ ጡመራ መድረክ እድምተኞች እንደምን ሰነበታችሁ? ዛሬ ሚያዝያ ፭ ፳፻፭ ዓ.ም ነው የዳንኤል ክብረት እይታዎች በጡመራ መድረክ ላይ መውጣት የጀመሩበትን ፫ኛ ዓመት የሚዘከርበት ቀን። ከሀገር ውጪ እና በሀገር ውስጥም ሆናችሁ በተለያዩ ምክንያቶች ይህንን ፕሮግራም ላልታደማችሁ ሁሉ ስለ ነበረው ክንውን አጠር አድርጌ ላስቃኛችሁ ወደድኩኝ። መልካም ንባብ።
እንደ ልማዴ ከ፬ኪሎ የ፳፪ን ታክሲ ተሳፈርኩኝና ጉዞ ወደ አክሱም ሆቴል ሆነ። ሆቴሉ ስደርስ ሰዓቴን ተመለከትኩኝ ልክ ፮፡፵፭ ይላል። በትክክለኛው ሰዓት በመድረሴ በመደሰት ፍተሻውን አልፌ ወደ ስብሰባው አዳራሽ አቅጣጫ ጠቋሚ በሆኑ እና ጎድግዳ ላይ በተለጠፉ ጽሑፎች አማካኝነት ፎቁን ወጣሁ። ሁለተኛ ፎቅ ላይ የሚገኘው የስብሰባ አዳራሽ ስደርስ የተወሰኑ እድምተኛች ቀድመውኝ ምዝገባ እያካሄዱ ደረስኩኝ። እኔም እንደነሱ ምዝገባዬን አከናወንኩኝና በረንዳው ላይ ቆም አልኩኝ። በአንዱ ጥግ ላይ በቅርቡ የታተመውን “የኔ ጀግና” ን ጨምሮ ሌሎች መጻሕፍትን የያዙ ወንድሞችና እህቶች አየሁና ጠጋ ብዬ የሌለኝን መርጬ ያዝኩኝ። ትንሽ እንደቆየን ወደ አዳራሽ እንድንገባ ተደረገ ቦታ ቦታችንንም ያዝን። ኤልያስም ከዲ/ን ምንዳዬ ብርሃኑ ጋር እየተመካከረ ክራሩን ለስለስ ባለ ሁናቴ የንስሃ መዝሙር ማሰማት እና ለዝግጅቱ የታደሙቱ ሁሉ እስኪደርሱ እና መርሃግብሩ አስኪጀመር ድረስ ቀድመው የመጡትን ሃሳብ ያዘ። ቀስ እያለም አዳራሹ በእድምተኞች መሞላት ጀመረ። ተጋባዥ ምሁራንና የክብር እንግዶችም የተዘጋጀላቸውን ቦታ በአስተናጋጆች አማካኝነት እንዲይዙ ተደረገ።

Thursday, April 11, 2013

የደረጃ ዕድገት


click here for pdf 
የዚህ መ/ቤት ሠራተኞች ዘንድሮስ አምርረዋል፡፡ ባለ ስንት አሐዝ እንደፈለጉ አይታወቅም እንጂ ዕድገት ዕድገት ይላሉ፡፡ ‹ላለፉት ጥቂት ዓመታት የደረጃ ዕድገት አላገኘንምና እንደገና ሊታይልን ይገባል› እያሉ አንዴ በስብሰባ አንዴ በደብዳቤ ይጯጯሃሉ፡፡ ለነገሩ ባለቤት ካልጮኸ ጎረቤት አይረዳም የሚለውን የሚያውቁ አዲስ ሠራተኞች ናቸው አሉ ጉዳዩን የሚገፋፉት፡፡ አንዳንዶች ነባር ሠራተኞች ግን ‹ነባሕነ ነባሕነ ከመ ዘኢነባሕነ ኮነ- ጩኸን ጩኸን እንዳልጮህን ሆንን› የሚለውን በመተረክ ነው ያለፈ ልምዳቸውን የሚያካፍሉት፡፡
ኃላፊዎቹ ደግሞ ጥያቄው በተደራጀ መልኩ እንዲቀርብ ነው ያሳሰቡት፡፡ በአነስተኛም ይደራጁ በከፍተኛ የቢሮው ሠራተኞች ግን አንዳች አደረጃጀት ይዘው ጥያቄዎችቸውን ቢያቀርቡ የተሻለ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ‹አንድነት ኃይል ነው› የሚለው መፈክር ከሠርቶ አደር ጋዜጣ መቆም በኋላ በብዛት ባይታይም የአደረጃጀቶች የውስጥ ፋይል ውስጥ ግን ሊኖር እንደሚችል አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች ገልጠዋል፡፡ 

Tuesday, April 9, 2013

ለትልቁ ዓሣ፣ ትንሽ መያዣአንዳንዴ ትልቅ ነገር እንመኛለን፣ እንሻለን፣ እናስሳለንም፡፡ ትልቅ ሀብት፣ ትልቅ ሥልጣን፣ ትልቅ ትዳር፣ ትልቅ ቤት፣ ትልቅ ዘመድ፣ ትልቅ ትምህርት፣ ትልቅ ሥራ፣ ትልቅ ቢሮ፣ ትልቅ ድርጅት፣ ከፍ ያለ እንጀራ፣ ከፍ ያለ ደመወዝ፣ ከፍ ያለ ጓደኛ፣ ከፍ ያለ ጸጋ እንመኛለን፡፡ መመኘቱ በራሱ አንድ ነገር ነው፡፡ የሀገሬ ሰው ‹ቸር ተመኝ ቸር እንድታገኝ› ይላልና፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ አፍርንጅ ሲጨምርበት ‹ጨረቃን ለመምታት ወርውር፣ እርሷን እንኳን ብትስት ከከዋክብቱ አንዷን ታገኛለህና› ይላል፡፡ አፍሪካዊ ወገኖቻችንም ‹ለንጉሥነት ብትጸልይ ቢያንስ ጭቃ ሹምነት አታጣም› ይላሉ፡፡
ቀጣዩና ዋናው ጥያቄ ግን የተመኘነውን ብናገኘው፣ ያሰብነውን ብንደርስበት፣ የፈለግነውን ብንጨብጠው፣ አያያዙን እንችልበታለን ወይ? ነው፡፡ ያገኘነውን ነገር ለማስተዳደር፣ ለመያዝና ለመከባከብ የሚያስችል ዐቅም አስቀድመን አከብተናል ወይ? ‹ሳያርሱ ዝናብ መመኘት ጎርፍ አምጣ ማለት ነው› የሚል አጎት ነበረኝ፡፡ ለምንመኘው ነገር የሚበቃ ዝግጁነት ከሌለ የሚመጣው ነገር በረከት ሳይሆን መርገም ይሆናል፡፡ ምሕረት ሳይሆን መዓት ያወርዳል፡፡ 

Wednesday, April 3, 2013

ዕሩቅ ብእሲ

<ዕሩቅ ብእሲ> በግእዙ ሰው ብቻ፣ ሥጋ ብቻ፣ የተራቆተ፣ ምንም ነገር የሌለው እንደ ማለት ነው፡፡ ቃሉ ከነገረ መለኮት ትምህርት ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ አይደለም፣ ሥግው ቃል አይደለም፣ ሰው ብቻ ነው የሚለውን ትምህርት ለመቃወም በተሰጡ ትምህርቶች ላይ ነው ቃሉን የምናገኘው፡፡ እዚህ ግን ሌላ ትርጉም ነው የምንሰጠው፡፡ ‹ዕሩቅ ብእሲ› ምንም ነገር የሌለው፣ ሥጋ ብቻ ያለው ሰው፣ ሌላ አንዳች ነገር ያልተዋሐደው፣ እንዴው ሥጋና ደም የሆነ ሰው ማለታችን ነው፡፡
ዕሩቅ ብእሲ የራሱ የሆነ ሞያ፣ ሞራል፣ ሀብት፣ ጸጋ፣ ክብር፣ ዝና የለውም፤ ዕሩቅ ብእሲ ራሱን ችሎ አይቆምም፣ እንደ ሐረግ መደገፊያ፣ እንደ እንሽላሊት መታከኪያ ይፈልጋል፡፡ እንደ ሙጫ መጣበቂያ እንደ አልጌ መሸሸጊያ ይሻል፡፡ እንደ ገደል ማሚቱ የሚያስተጋባው፣ እንደ በቀቀን የሚቀዳው ነገር ይፈልጋል- ዕሩቅ ብእሲ፡፡