Thursday, March 21, 2013

<ነቢዩ ኤልያስ> በአራት ኪሎ


 click here for pdf
ሰሞኑን በከተማችን በአዲስ አበባ ‹ነቢዩ ኤልያስ መጥቷል፣ የዓለምም ፍጻሜ ቀርቧል› የሚሉ አካላት ተነሥተዋል፡፡ እነርሱ እንደሚሉትም ነቢዩ ኤልያስ መጥቶ አዲስ አበባ ይገኛል፡፡ ቤተ መንግሥቱንና ቤተ ክህነቱን ለማጥራትም ተዘጋጅቷል፡፡ ከሚያጠራቸው የቤተ ክህነት ጉዳዮች ሦስቱ ትኩረት አግኝተዋል፡፡ የመጀመርያው ‹ኦርቶዶክስ የሚባለው ስም ስሕተት ነው፤ ስማችን ተዋሕዶ ነው፤ መለበስ ያለበት ልብስ ነጭ ብቻ ነው፤ እርሱም ቢሆን ጥለቱ አረንጓዴ ቢጫና ቀይ መሆን አለበት፤ አሁን ያደረግነውን ማተብ በመበጠስም አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ማተብ ማሠር አለብን› የሚል ነው፡፡ በየአጋጣሚው ቤተ ክህነቱንና ቤተ መንግሥቱን በመንቀፍ፣ አሁን የሚታዩትን ችግሮች መሠረት አድርጎም ሕዝቡ መጥቷል የተባለውን ኤልያስ መከተል እንጂ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄዱ ጥቅም እንደሌለው እየተነገረው ነው፡፡ የሚከናወኑ ማናቸውም የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችም የኤልያስን መምጣት የሚያመለክቱ እንጂ ምእመናኑ ሊሳተፍባቸው የሚገቡ አለመሆናቸው ይነገራል፡፡
እስኪ እነዚህን ነገሮች በዝርዝር እንያቸው፡፡
ኤልያስ ማነው?

ኤልያስ ማለት ‹እግዚአብሔር አምላክ ነው› ማለት ነው፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት በስምንተኛው መክዘ አካባቢ በእሥራኤል የተነሣ ነቢይ ነው፡፡ የተወለደው ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ ይገኙ ከነበሩት የገለዓድ ቀበሌዎች በአንዱ በቴስቢ ነው፡፡ ኤልያስ የሚታወቀው በሦስት ሃይማኖታዊ ተግባሮቹ ነው፡፡ የመጀመርያው በእሥራኤል ተንሰራፍቶ የነበረውን የበኣል አምልኮ ያጠፋና አምልኮ እግዚአብሔርን ያጸና መሆኑ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ አሕዛባዊቷን ኤልዛቤልን አግብቶ ንጉሡ አክአብ ይፈጽመው የነበረውን ግፍና ጥፋት ሳይፈራና ሳያፍር ፊት ለፊት የገሠጸና ለእውነት ብቻ የቆመ ነቢይ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ አቋሙ ምክንያትም በሰሜናዊ እሥራኤል በሚገኙ ሰንሰለታማ ተራሮች ፈፋ ለፈፋ ሲንከራተት ኖሯል፡፡ መጀመርያ ቁራዎች ሲመግቡት ኖረው በኋላም በሰራፕታ የምትገኝ አንዲት መበለት አገልግላዋለች፡፡
ይህ ቆራጥነቱና ለአምልኮተ እግዚአብሔር ቋሚ መሆኑ በእግዚአብሔር ዘንድ ባስገኘለት ሞገስ የተነሣ ኤልያስ ከኄኖክ ቀጥሎ ሳይሞት ወደ ብሔረ ሕያዋን በመወሰዱም ይታወቃል፡፡ የዮርዳኖስን ወንዝ ከደቀ መዝሙሩ ከኤልሳዕ ጋር ከተሻገረ በኋላ የእሳት ሠረገላ መጥቶ ኤልያስን ወስዶታል፡፡ ይህ ኤልያስ የሚታወቅበት ሦስተኛው ነገር ነው፡፡
ኤልያስ ይመጣል?
ከ470 እስከ 440 በኢየሩሳሌም ትንቢት የተናገረው ነቢዩ ሚልክያስ ‹‹የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩ ኤልያስን እልክላችኋለሁ›› ብሎ ትንቢት ተናግሮ ነበር፡፡ (ሚል. 4÷5) ይህንንም በመያዝ አይሁድ በፋርሶች፣ በግሪኮች፣ በሶርያውያንና በሮማውያን መከራ በተፈራረቁባቸው 400 ዓመታት ውስጥ ነቢዩ ኤልያስን ሲጠባበቁት ነበር፡፡ በየምኩራባቸውም የኤልያስ መንበር የተባለ ከፍ ብሎ የተሠራ ባለ መከዳ ወንበር ያስቀምጡ ነበር፡፡ ከክርስቶስ ልደት 6 ወራት ተቀድሞ የተወለደውና ከበረሃ የመጣው መጥምቁ ዮሐንስ በብዙ መልኩ ኤልያስን ይመስለው ስለነበር የተወሰኑት የአይሁድ ክፍሎችና በኋላም ክርስቲያኖች ይመጣል የተባለው ነቢዩ ኤልያስ እርሱ ነው ብለው ተቀብለውታል፡፡
ዮሐንስ መጥምቅ እንደ ኤልያስ ሁሉ በርኸኛ ባሕታዊ ነው፤ እንደ ኤልያስ ሁሉ ፀጉር የለበሰ ነው፤ እንደ ኤልያስ ሁሉ እሥራኤል ተስፋ በቆረጠችበት ዘመን የመጣ ነው፤ እንደ ኤልያስ ሁሉ ሄሮድስን ሳይፈራና ሳያፍር የገሠጸ ነው፡፡ በእነዚህና በሌሎችም ምክንያቶች መጥምቁ ዮሐንስ ኤልያስን ይመስለው ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ይመጣል የተባለው ኤልያስ መጥምቁ ዮሐንስ መሆኑን መስክሮለታል (ማቴ 11÷14፤ 17÷10-13፤ሉቃ 1÷17)
ስለ ኤልያስ መምጣት የሚነግረን ሌላው መጽሐፍ የዮሐንስ ራእይ ነው፡፡ የዮሐንስ ራእይ በምእራፍ 11 ላይ ዓለምን የሚያጠፋው ሐሳዌ መሲሕ ከመጣ በኋላ ዙፋኑን አደላድሎ የዓለምን ክርስቲያኖች ሲጨርስና ምስክር ሲጠፋ ሁለት ምስክሮች መጥተው 1260 ቀናት ምስክርነት እንደሚሰጡና በመጨረሻም በሐሳዌ መሲህ እንደሚገደሉ ይገልጣል፡፡ ከሁለተኛው መክዘ ጀምሮ የተነሡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ሁለት ምስክሮች ኄኖክና ኤልያስ መሆናቸውን ተርጉመዋል፡፡
ሐሳዌ መሲሕ ሲነሣና ሁሉንም እንደ ሰም አቅልጦ እንደ ገል ቀጥቅጦ ሲያጠፋ፤ ለእውነት የሚመሰክርም ሲጠፋ፣ ምእመናንም በሚደርሰው መከራ ምክንያት የሚከተሉት የእምነት መንገድ ‹ስሕተት ይሆንን?› ብለው ሲጠራጠሩ እነዚህ ሁለቱ ሳይሞቱ ወደ ብሔረ ሕያዋን ያረጉ ነቢያት መጥተው እውነትን በመመስከርና የሐሳዌ መሲሕን ነገር በማጋለጥ ምስክርነታቸውን በደም እንደሚያጸኑ የሊቃውንቱ ትርጓሜ ያብራራል፡፡
ዮሐንስ አፈወርቅ፣ አቡሊዲስ ዘሮምና ቪክቶርያነስ እንደሚገልጡት ኤልያስና ኄኖክ በኢየሩሳሌም ያስተምራሉ፣ በኢየሩሳሌም ተአምራት ያደርጋሉ፣ በኢየሩሳሌም ይገደላሉ፣ በኢየሩሳሌም ይነሣሉ፣ በኢየሩሳሌምም ያርጋሉ፡፡ ይህም ለጌታችን መምጣት የመጨረሻው ምልክት ነው፡፡ ከኤልያስና ኄኖክ መምጣት በኋላ የሚጠበቀው የክርስቶስ ለፍርድ መምጣት ነው፡፡
‹ነቢዩ ኤልያስ› በአራት ኪሎ›
በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ነቢዩ ኤልያስ መጥቷል ይባላል፡፡ የሚኖረውም አራት ኪሎ ነው፡፡ አንዳንድ ታዋቂ የሆኑ ሰዎች በተለይም አርቲስቶች ተከታዮቹ ሆነናል ይላሉ፡፡ ይህንን ሁኔታ ከቅዱሳት መጻሕፍትና ከሊቃውንቱ ትምህርት ጋር ስናነጻጽረው ትክክል ሆኖ አናገኘውም፡፡
መጀመርያ ነገር ኤልያስ ብቻውን አይመጣም፡፡ በነቢዩ በሚልክያስ ለብቻው እንደሚመጣ የተነገረለት ኤልያስ መጥምቁ ዮሐንስ መሆኑን ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ መሰከረ ሌላ ምስክር ማምጣት አያስፈልግም፡፡ በሌላም በኩል አሁን መጥቷል የተባለው በመጨረሻው ዘመን የሚመጣው ኤልያስ ከሆነ ደግሞ እንደ ሊቃውንቱ ትምህርት ብቻውን አይመጣም፤ አብሮት ኄኖክም ይመጣል፡፡ አሁን ግን ኤልያስ ከኄኖክ ተነጥሎ ነው መጣ የሚባለው፡፡
ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ነቢዩ ኤልያስ የሚመጣበት ጊዜ በራእየ ዮሐንስ ላይ በምእራፍ 11 ተገልጧል፡፡ አስቀድሞ ሐሳዌ መሲሕ ይመጣል፡፡ ዙፋኑንም በተቀደሰችው ከተማ በኢየሩሳሌም ይዘረጋል፡፡ ምእመናንም (በተለይም የስድስት ስድሳ ስድስትን አምልኮ ያልተቀበሉትን) በግፍ ይገድላቸዋል፡፡ በዚህም ጊዜ እውነት ትቀጥንና ምስክር ታጣለች፤ ኤልያስና ኄኖክ የሚመጡትም እውነትን በአደባባይ ለመመስከር ነው፡፡
ይህ ከሆነና በአዲስ አበባ እየተባለ እንዳለው ኤልያስ ከመጣ ሐሳዌ መሲሕ ቀድሞት መጥቷል ማለት ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ምእመናን በግፍ ተገድለዋል፤ በዓለምም ላይ አማኞች በአብዛኛው አልቀዋል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሲፈጸም አላየነውም፡፡ በኢየሩሳሌምም ሐሳዌ መሲሕ ገና አልነገሠም፡፡
ሌላም ሦስተኛ ነገር መነሣት አለበት፡፡ ሐሳዌ መሲሕ የሚነግሠው፣ ኄኖክና ኤልያስም የሚገለጡት ‹በተቀደሰችው ከተማ› በኢየሩሳሌም ነው፡፡ የሚሠውትም እዚያ መሆኑን ‹እርስዋም በመንፈሳዊ ምሳሌ ሰዶምና ግብጽ የተባለችው ደግሞ ጌታቸው የተሰቀለባት ናት› ብሎ ኢየሩሳሌም መሆንዋን ነግሮናል፡፡ (ራእይ 11÷8) አሁን ግን ኤልያስ ተገለጠ እየተባለ ያለው አዲስ አበባ አራት ኪሎ ላይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከተልዕኮውም ከመጽሐፉም ጋር የሚጣረስ ነው፡፡ ጌታ የተሰቀለው አራት ኪሎ ነው ካላልን በቀር፡፡  
ራእየ ዮሐንስ እንደሚነግረን ኄኖክና ኤልያስ ምስክርነት የሚሰጡት ለ1260 ቀናት ወይም ለ42 ወራት ወይም ለ ሦስት ዓመት ከስድስት ወራት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ይገደላሉ፣ ተነሥተውም ያርጋሉ፡፡ አሁን ግን አዲስ አበባ መጣ የተባለው ኤልያስ መጣ ከተባለ አራት ዓመት ሊያልፈው ነው፡፡
ምጽአትንና መሲሕን መናፈቅ
በዓለምም ሆነ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የምጽአትን ቀን የመናፈቅና የምጽአትን ምልክቶች ደርሰዋል ብሎ የመጨነቅ አዝማሚያ የሚከሰትባቸው ምክንያቶች አሉ፡፡ እነዚህም ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች ሲከሰቱና ሕዝብ ተስፋ ሲቆርጥ ነው፡፡
እሥራኤላውያን ከፋሶችና ከግሪኮች ወረራ በኋላ ሀገራቸው ስትመሰቃቀል፣ መንፈሳዊነት ሲጎድልና መንግሥታቸው ፈርሶ ተስፋ ወደ መቁረጥ ሲመጡ ‹መሲሕ እየመጣ ነው፤ ኤልያስ እየደረሰ ነው› የሚል አስተምህሮን ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ2ኛው መክዘ ጀምረው ነበር፡፡ በዚህም የተነሣ አንዳንድ ሰዎች ይመጣል የተባለው መሲሕና ኤልያስ እኛ ነን እያሉ አጋጣሚውን ሊጠቀሙበት ሞክረው ነበር፡፡ ከእነዚህ መካከል ከክርስቶስ ልደት በፊት በ2ኛውና አንደኛው መክዘ ላይ የተነሡት ቴዎዳስና ይሁዳ ይጠቀሳሉ፡፡ ቴዎዳስ አራት መቶ ሰዎችን አስከትሎ ነበር፡፡ በኋላ ግን ሐሰተኛ መሆኑ ሲታወቅ ሕዝቡ ተወው፤ ይሁዳም ሕዝቡን አስነሥቶ እስከ ማስሸፈት ደርሶ ነበር፡፡ መጨረሻው ግን አላማረም፡፡ (የሐዋ 5÷37-38)
በቅርብ ጊዜ በኡጋንዳ ኢኮኖሚው ሲደቅና የእርስ በርስ ጦርነቱ ሲባባስ፣ ይህም የሕዝቡን ማኅበራዊ ሕይወት ሲያቃውሰው ‹እኔ ክርስቶስ ነኝ› የሚል ሰው ተነሥቶ በአንድ አዳራሽ ውስጥ የነበሩ ተከታዮቹ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ሲሉ በእሳት ተቃጥለው እንዲያልቁ አድርጓቸው ነበር፡፡ በአሜሪካ የደረሰው የኢኮኖሚ ድቀት ካስከተላቸው መዘዞች አንዱ በየአካባቢው ‹እኔ መሲሕ ነኝ› የሚሉና ሕዝቡ ችግሩን ከማሸነፍ ይልቅ ችግሩን እንዲረሳው የሚያደርጉ ሰዎች መከሰታቸው ነው፡፡ በ2012 የተደረገ አንድ ጥናት ባለፉት ሦስት ዓመታት በአሜሪካ ውስጥ 132 ሰዎች መሲሕ ነን ብለው ተነሥተው ወደ 4.5 ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ አስከትለዋል፡፡
በሀገራችን ታሪክ በ15ኛው መክዘ ከተከሰተው የግራኝ ጦርነት በኋላ ሕዝቡ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተስፋ መቁረጥ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ አብያተ ክርስቲያናቱ ተቃጠሉ፣ ኢኮኖሚው ወደመ፤ መንግሥቱ ተዳከመ፤ ትዳርንና አካባቢያዊ መስተጋብርን የመሰሉ ማኅበራዊ ተቋማት ፈረሱ፡፡ ብዙ ሰዎች ሞቱ፡፡ ይህ በሕዝቡ ላይ ባስከሰተው ተስፋ መቁረጥ የተነሣ ከዚህ መከራና ሰቆቃ የሚያወጣውን አንዳች ሰማያዊ ኃይልን ይጠብቅ ነበር፡፡
በሀገራችን ታሪክ ራእየ ዮሐንስ ይበልጥ የታወቀውና በገልባጮች እጅ በብዛት የተገለበጠው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ በሚሠሩት አብያተ ክርስቲያናትም የሐሳዌ መሲሕ፣ የኤልያስና ኄኖክ፣ የአዲሲቱ ሰማይና ምድር ሥዕሎችም በብዛት ተሳሉ፡፡ ይህንንም መሠረት አድርገው እነ ፍካሬ ኢየሱስ ተጻፉ፡፡ ፍካሬ ኢየሱስ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉትን ትንቢታዊ ቃሎች መሠረት አድርጎ ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር ያዛመደ መጽሐፍ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ላይ ሕዝቡን ከችግር የሚያወጣ፣ የአንድ በሬ እሸት የአንዲት ላም ወተት እንዲያጠግብ የሚያደርግ ‹ቴዎድሮስ› የሚባል ንጉሥ ይነግሣል የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ ሕዝቡም በደረሰው ነገር ላይ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ይህንን ቴዎድሮስ የተባለ ደግ ንጉሥ እንዲጠብቅ አደረገው፡፡
ከግራኝ ጦርነት በኋላ በዐፄ ሠርጸ ድንግል ወራሾች መካከል በተፈጠረው የርስ በርስ ውጊያ ሀገሪቱ ስትታመስና ሕዝቡም በተደጋጋሚ ጦርነትና የሕዝብ ፍልሰት ሲታወክ እኔ ክርስቶስ ነኝ፣ ሕዝቡንም ከችግሩ ላወጣውና መንግሥተ ሰማያትን ላወርሰው መጥቻለሁ የሚል ሐሳዊ መሲሕ በአምሐራ ሳይንት አካባቢ ተነሥቶ ነበር፡፡ አሥራ ሁለት ሐዋርያት፣ 72 አርድእትና 36 ቅዱሳት አንስትንም መርጦ ነበር፡፡ ብዙው ሕዝብም በተስፋ መቁረጥ ላይ ስለነበር ተከትሎት ነበር፡፡ በኋላ ግን በሞት መቀጣቱን አቡነ ጎርጎርዮስ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ መጽሐፋቸው ጠቅሰውታል፡፡
በቅርቡ የሀገራችን ታሪክ ዐፄ ምኒሊክ ዐርፈው ሞታቸው በተደበቀበት ጊዜ፣ በታኅሣሥ ግርግር ጊዜ፣ በአብዮቱ ዋዜማና ማግሥት፣ እንዲሁም ኢሕአዴግ አዲስ አበባ በገባበት ጊዜ አያሌ ‹ባሕታውያን› ተነሥተው ነበር፡፡ ይህ ነገር መጣ፣ መርስኤ ኀዘን ስለ ንግሥት ዘውዲቱ ዘመን በጻፉት የትዝታ መጽሐፋቸውም ይህንን ገልጠውታል፡፡ ይህም ያም ነገር ታየ፣ ተገለጠ የሚለው ብሂልም ነባርና የሀገር አለመረጋጋትና በኑሮ ተስፋ መቁረጥን ተገን አድርገው የሚመጡ ናቸው፡፡
የኤልያሳውያን› ሁለት አስተምህሮዎች
አሁን በዘመናችን የተከሰቱት ‹ኤልያሳውያን› ሁለት ነገሮች ላይ አተኩረው እየሠሩ ነው፡፡ የመጀመርያው ‹ኦርቶዶክስ› ትክክለኛ ስም አይደለም የሚለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሰንደቅ ዓላማን ከጽድቅና ኩነኔ ጋር ማያያዝ ናቸው፡፡
ኦርቶዶክስ የሚለው ቃል የግሪክ ቃል ሲሆን ›ኦርቶ› ርቱዕ፣ ‹ዶክሳ› ደግሞ እምነት፣ መንገድ፣ ጠባይ፣ ባህል ማለት ነው፡፡ ይህንን ስም የክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት መጠቀም የጀመሩት በ325 ዓም ከተደረገው የኒቂያ ጉባኤ በኋላ ነው፡፡ ከጉባኤ ኬልቄዶን የ451 ዓም ጉባኤ በኋላ ደግሞ የምዕራብ አብያተ ክርስቲያናት ካቶሊክ ሲባሉ ምሥራቆቹ ‹ኦርቶዶክስ› የሚለውን ስም ይዘው ቀሩ፡፡ በምሥራቆቹ መካከል የጉባኤ ኬልቄዶንን ውሳኔ በመቀበልና ባለመቀበል መካከል ልዩነት ስላለ የግሪክና መሰል አብያተ ክርስቲያናት የምሥራቅ ኦርቶዶክስ ሲባሉ፣ አርመን፣ ግብጽ፣ ሕንድ፣ ሶርያና ኢትዮጵያ ደግሞ ‹ኦርየንታል ኦርቶዶክስ› ተባሉ፡፡
ኦርቶዶክስ፣ ኦርቶዶክሳዊ የሚለው ስም በሀገራችን ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በሁለት መንገድ ተገልጠዋል፡፡ በአንድ በኩል ጥሬ ቃሉ እንዳለ የተቀመጠ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ግእዙ ተተርጉሞ ‹ርቱዕ ሃይማኖት› እየተባለ ተቀምጧል፡፡ ፍትሐ ነገሥት ‹ይኩን ምእመነ ኦርቶዶክሳዌ› ይላል(42÷2)፡፡ ያዕቆብ ዘእልበረዲም ‹ሃይማኖት ኦርቶዶክሳዊት› ሲል እምነቱን ይገልጣል፡፡ በመጽሐፈ ቄርሎስም ‹ሃይማኖት ርትዕት› እያለ ተርጉሞ ይገልጠዋል፡፡
‹ተዋሕዶ› የሚለው ቃል ነጥሮ የወጣው በጉባኤ ኤፌሶን በ431 ዓም ነው፡፡ በጉባኤው የንስጥሮስን ባሕል ለማየት የተሰበሰቡት አበው በእስክንድርያው ቄርሎስ የተሰጠውን ትምህርት በመቀበል ሁለት ባሕርይ የሚለውን አውግዘው መለኮት ከሥጋ ተዋሕዶ ሥግው ቃል ሆነ የሚለውን ርቱዕ እምነት መሆኑን መሰከሩ፡፡ ይህ ቃል የእምነት መግለጫ ዶክትሪን ሆኖ ነው የኖረው፡፡ ከኬልቄዶን ጉባኤ በኋላም ይህ ስያሜ የኦርቶዶክሶቹ ዋና መጠርያ እየሆነ መጣ፡፡ በኢትዮጵያ ጥንታዊ መጻሕፍት ላይ ተዋሕዶ እምነት ሆኖ እንጂ የቤተ ክርስቲያኒቱ መጠርያ ሆኖ አናገኘውም ‹ኦርቶዶክሳዊ› የሚለውን ቃል የምናገኘውን ያህል ‹ተዋሕዶዊ› የሚል መገለጫ አናገኝም፡፡ ተዋሕዶ የሚለውን ቃል በነገረ ሥጋዌ ትምህርት ላይ በአጽንዖት እናገኘዋለን፡፡ በዚህ ትምህርት ላይ በሀገር ውስጥ የተነሣ የተለየ አስተያየት ስላልነበር መጠርያነቱ አልጎላም፡፡
በ17ኛው መክዘ ከአውሮፓ በመጡ ካቶሊካውያን ምክንያት የተፈጠረውን የእምነት ክፍፍል ተከትሎ ይህ የእምነት መጠርያ የአማንያንና የወገን መጠርያ እየሆነ መጣ፡፡ በ17ኛው መክዘ ቅባትና ጸጋ የሚባሉ ባህሎች መጥተው ነበር፡፡ እነዚህን ባህሎች የሚቃወሙትና ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ እንጂ የጸጋ ልጅ አይደለም፣ ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮት ከሥጋ በተዋሕዶ ሥግው ቃል እንጂ እንደ ነገሥታትና ነቢያት በመቀባት አይደለም ያሉት ደግሞ መጠርያቸው ከእምነታቸው ተወስዶ ‹ተዋሕዶዎች› ተባሉ፡፡ ከቦሩ ሜዳ ጉባኤ በኋላም የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ ስም ‹ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ› የሚለው ጎላ፡፡
ኦርቶዶክስ የሚለው ስም ቤተ ክርስቲያኒቱ በዓለም የምትታወቅበት የወገን ስሟ ነው፡፡ ሌሎቹም ‹የግብጽ ኦርቶዶክስ› የሶርያ ኦርቶዶክስ› የሕንድ ኦርቶዶክስ› ብለው ይጠሩና ከአካባቢያቸው ራሳቸውን ለመለየት ደግሞ ‹የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ‹፣ የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ፣ የሶርያ ያዕቆባዊት ኦርቶዶክስ› እያሉ ይጠራሉ፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ‹ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ› ትባላለች፡፡
አንዳንድ ሰዎች በዘመናውያን መዛግብተ ቃላት ስለ ‹ኦርቶዶክስ› የተሰጡ ፍቺዎችን ይዘው ይሞግታሉ፡፡ ኦርቶዶክስን ‹ከአክራሪነትና፣ ከለውጥ አለመቀበል› ጋር እያዛመዱ ይፈቱታል፡፡ በዚህም ምክያት ኦርቶዶክስ የሚለውን ቃል ለኮንሰርቫቲቭ ፓርቲዎችና አይሁድ ሲሰጡት ይታያሉ፡፡ ይህ ግን ኦርቶዶክስ የሚለው ስም ከመነጨበት ጠባይ በእጅጉ የራቀ ነው፡፡
አሁን ወደ ሁለተኛው ነጥብ እንመለስና ሰንደቅ ዓላማን እንመልከት፡፡ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያውያን መለያ ናት፡፡ ለዚህች ሰንደቅ ዓላማ ብዙዎች ውድ ሕይወታቸውን ከፍለዋል፡፡ እነዚህ ውድ ሕይወታቸውን ከከፈሉት መካከልም የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶችና ልጆች ይገኙበታል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክን ከማቆየት፣ ባህልን ከማሸጋገርና ኢትዮጵያዊነትን ከማሥረጽ ሚናዋ አንጻር ሰንደቅ ዓላማንም በማስከበርና ለትውልድ በማስተላለፍም የበኩልዋን ድርሻ ተወጥታለች፡፡
የኢትዮጵያ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ከሀገራዊ እሴትነቱ፣ መሥዋዕትነትንና ነጻነትን ከማንጸባረቁ፣ ለኢትዮጵያውያንም ከደማቸው ጋር የተዋሐደ ልዩ ምልክት ከመሆን አልፎ ግን ጽድቅና ኩነኔ ውስጥ የሚገባ፣ እርሱን ያልተቀበለና ያላደረገ ሰማያዊ ዋጋ የሚቀርበት፣ ከእርሱ ውጭ ቀለም ያለው ነገር የለበሰና ማተብ ያሠረ ኃጢአት እንደሠራ ተቆጥሮ ንስሐ የሚገባበት ግን አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ ያለ ዜጋ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባል ለመሆን የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማና ቀኖና መቀበልን እንጂ አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ባንዲራን መቀበል ግዴታው አይደለም፡፡ በኡጋንዳ ባንዴራ፣ በአሜሪካ ባንዴራ፣ በግብጽ ባንዴራ፣ በሶማልያ ባንዴራ አሸብርቆም ቢሆን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጅ መሆን ይችላል፡፡ እስካሁን ስለ ቀኖና በሚደነግጉት መጽሐፎቻችን ውስጥ ሰንደቅ ዓለማን የተመለከተ ቀኖና የለንም፡፡
በመሆኑም ሰንደቅ ዓላማችን ከኢትዮጵያዊነታችን ጋር እንጂ ከኦርቶዶክሳዊ እምነታችን ጋር የታሪክ እንጂ የድኅነት ተዛምዶ የለውም፡፡
እንደዚህ ዓይነት አመለካከቶች የሚያይሉት እንዲሁ አይደለም፡፡ በሕዝቡ ዘንድ ኢትዮጵዊ ስሜት ደብዝዟል፣ ለሰንደቅ ዓላማና ለሀገራዊ እሴቶች የሚሰጠው ዋጋ ቀንሷል ተብሎ ሲታሰብ ሰንደቅ ዓላማን የመሰሉ ሀገራዊ እሴቶች ጉልበት ያገኙ ዘንድ ተጨማሪ ሃይማኖታዊ ኃይል ይሰጣቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ የሰንደቅ ዓላማን ክብርና ትርጉም ማስተማርዋና በትውልዱ ውስጥ ማሥረጽዋ ባልከፋ፡፡ አስተምህሮው ግን ከሀገራዊ ግዴታ የሚመጣ እንጂ ከሃይማኖታዊ ግዴታ የሚመጣ መሆን የለበትም፡፡ ከሕዝብ እሴቶች እንደ አንዱ ሆኖ እንጂ ከጽድቅና ኩነኔ ጋር ተያይዞ መሆን የለበትም፡፡
ምን ይደረግ?
የሃይማኖት ትምህርት በሚገባ መሰጠት ሲያቆምና ሰዎችም በተደላደለው የእምነት መንገድ ላይ በዕውቀትና በእምነት እየተመሩ መጓዝ ሳይችሉ ሲቀሩ ‹ባለ ተስፋዎች› ብቻ ይሆናሉ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ መጀመርያ ላይ ‹በኤፌሶን ላሉት ቅዱሳን፣ በክርስቶስ ኢየሱስም ላሉት ምእመናን› በማለት የገለጠው አባባል ታላቅ ነገር አለው፡፡ ምእመናኑ በሁለት ዓለም መኖራቸውን እንዳይረሱ የሚያደርግ ነው፡፡ ‹በክርስቶስና በኤፌሶን›፡፡ ክርስቲያኖችም ምድራዊነታቸውንም ሰማያዊነታቸውንም መርሳት የለባቸውም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ምድራዊው ጎዳና ሲያቅትና ፈተና ሲበዛበት፣ የኢኮኖሚውና የፖለቲካውም ሁኔታ አልቃና ሲል፣ የምናየውና የምንሰማውም ተስፋ ሲያሳጣን፣ ምድር ላይ መሆናችንን ፈጽመን ረስተን ኅሊናችን ወደሚፈጥረው ልዩ ዓለም እንገባለን፡፡ ያንንም እጅግ ከመመኘታችን የተነሣ የደረስንበት ይመስለናል፡፡
በዚህ ጊዜ የሚሰጡ ትምህርቶችም ለሰዎች ቀላል የሆኑ፣ ንባብና ትምህርትን የማይጠይቁ፣ በቀላሉ የሚተገበሩ፣ የሚነኩና የሚዳሰሱ ይሆናሉ፡፡ ቡና መጠጣት አለመጠጣት፣ አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ማተብ ማሠር አለማሠር፣ በባዶ እግር መሄድ አለመሄድ፣ ጸጉርን ማስረዘም አለማስረዘም፣ መቁጠርያን ያለ ሥርዓቱ ማሠር አለማሠር፣ ከመምህራን ቃል ይልቅ የሰይጣንን ቃል መቀበልና ማመን፣ እየሠለጠኑ ይመጣሉ፡፡
ለዚህ ትልቁ መፍትሔው የእምነት ተቋማት የራሳቸውን ሥራ (ወንጌል ማስተማርን )ትተው በሰዎች ሥራ ውስጥ መግባታቸው ነው፡፡ ስለዚህም ተቋማቱ መጀመርያ ራሳቸውን ወደ ተልዕኳቸው መልሰው፣ በማይጨበጥ ተስፋ የሚዋልለውን ሕዝብም ወደ ትክክለኛ ኑሮና ተስፋ መመለስ አለባቸው፡፡ እዚህ ኤልያስ ነኝ፣ እዚያ ድንግል ማርያም ነኝ፣ እዚያ አቡዬ ነኝ የሚሉ በተነሡ ቁጥር ሕዝቡ ሥራና ትዳር ፈትቶ ተንከራትቶ አይዘልቀውም፡፡
 © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት የወጣ ነው፤ ደግሞ በሌላ ሚዲያ ማተም አይፈቀድም

125 comments:

 1. Replies
  1. it is good perspective keep it up!!

   Delete
 2. ለዚህ ትልቁ መፍትሔው የእምነት ተቋማት የራሳቸውን ሥራ (ወንጌል ማስተማርን )ትተው በሰዎች ሥራ ውስጥ መግባታቸው ነው፡፡ ስለዚህም ተቋማቱ መጀመርያ ራሳቸውን ወደ ተልዕኳቸው መልሰው፣ በማይጨበጥ ተስፋ የሚዋልለውን ሕዝብም ወደ ትክክለኛ ኑሮና ተስፋ መመለስ አለባቸው ..kalhywit yasmalen

  ReplyDelete
 3. thank you daniel, I always appreciate your current views. keep it up! God bless you.

  ReplyDelete
 4. tkkl bilehal diyakon danel:: yihe elias elias emilut neger mnm alamaregnim:: beeconomiw bepoleticaw ena behulu neger embi silachew bezih metu:: yaw yachin siltan lemechebet new:: hige mengistawiw serhatachin endehu woy finkich bilobachewal:: gud eko enezih yetawoku hayloch emifetsimut sera:: tebarek biruk hun yegna astemari dyakon danel::

  ReplyDelete
 5. In addition,if he is Elias,he will teach without fear.The Prophet Elias hadn't fear for the King Akaab and for the Queen Elzabet.Why did this elias hide in Arat kilo?The true Elias is not afraid of leadrers,peoples,soldiers,etc.Therefore ,this elias in Arat kilo is false elias.

  ReplyDelete
 6. በዓለምም ሆነ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የምጽአትን ቀን የመናፈቅና የምጽአትን ምልክቶች ደርሰዋል ብሎ የመጨነቅ አዝማሚያ የሚከሰትባቸው ምክንያቶች አሉ፡፡ እነዚህም ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች ሲከሰቱና ሕዝብ ተስፋ ሲቆርጥ ነው፡፡

  ReplyDelete
 7. የሃይማኖት ትምህርት በሚገባ መሰጠት ሲያቆምና ሰዎችም በተደላደለው የእምነት መንገድ ላይ በዕውቀትና በእምነት እየተመሩ መጓዝ ሳይችሉ ሲቀሩ ‹ባለ ተስፋዎች› ብቻ ይሆናሉ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ መጀመርያ ላይ ‹በኤፌሶን ላሉት ቅዱሳን፣ በክርስቶስ ኢየሱስም ላሉት ምእመናን› በማለት የገለጠው አባባል ታላቅ ነገር አለው፡፡ ምእመናኑ በሁለት ዓለም መኖራቸውን እንዳይረሱ የሚያደርግ ነው፡፡ ‹በክርስቶስና በኤፌሶን›፡፡ ክርስቲያኖችም ምድራዊነታቸውንም ሰማያዊነታቸውንም መርሳት የለባቸውም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ምድራዊው ጎዳና ሲያቅትና ፈተና ሲበዛበት፣ የኢኮኖሚውና የፖለቲካውም ሁኔታ አልቃና ሲል፣ የምናየውና የምንሰማውም ተስፋ ሲያሳጣን፣ ምድር ላይ መሆናችንን ፈጽመን ረስተን ኅሊናችን ወደሚፈጥረው ልዩ ዓለም እንገባለን፡፡ ያንንም እጅግ ከመመኘታችን የተነሣ የደረስንበት ይመስለናል፡፡

  ReplyDelete
 8. ዲያቆን ዳንኤል
  ስለዚህ ጉዳይ እንድታስተምረን ጠይቀንህ ነበር፤ ጉዳዩን ከጠየቅነው በላይ አብራርተህ ስላስተማርከን እናመሰግናለን፡፡

  ReplyDelete
 9. I agree
  ለዚህ ትልቁ መፍትሔው የእምነት ተቋማት የራሳቸውን ሥራ (ወንጌል ማስተማርን )ትተው በሰዎች ሥራ ውስጥ መግባታቸው ነው፡፡ ስለዚህም ተቋማቱ መጀመርያ ራሳቸውን ወደ ተልዕኳቸው መልሰው፣ በማይጨበጥ ተስፋ የሚዋልለውን ሕዝብም ወደ ትክክለኛ ኑሮና ተስፋ መመለስ አለባቸው፡፡ እዚህ ኤልያስ ነኝ፣ እዚያ ድንግል ማርያም ነኝ፣ እዚያ አቡዬ ነኝ የሚሉ በተነሡ ቁጥር ሕዝቡ ሥራና ትዳር ፈትቶ ተንከራትቶ አይዘልቀውም፡፡

  ReplyDelete
 10. ድያቆን ዳንኤል ስለ ሰንደቅ አለማ ያልከው ብታስብበት.
  የኖህ ምልክት ምን ልትለው ነው?

  ReplyDelete
  Replies
  1. ferst,the rainbow is not exactly the same color as GREEN,YELLOW,RED.
   Second, the rainbow is not a sign of TSIDK ENA KUNENIE, it is rather a sign of covenant between Noha/human and God.

   Delete
  2. ኪዳነ ሙሴ በ ታቦት ከያዝነው :
   ኪዳነ ኖህ'ሳ በምን ልንገልፀው ነው?

   Delete
  3. be mariam mekenet

   Delete
 11. ለዚህ ትልቁ መፍትሔው የእምነት ተቋማት የራሳቸውን ሥራ (ወንጌል ማስተማርን )ትተው በሰዎች ሥራ ውስጥ መግባታቸው ነው፡፡ ስለዚህም ተቋማቱ መጀመርያ ራሳቸውን ወደ ተልዕኳቸው መልሰው፣ በማይጨበጥ ተስፋ የሚዋልለውን ሕዝብም ወደ ትክክለኛ ኑሮና ተስፋ መመለስ አለባቸው፡፡ እዚህ ኤልያስ ነኝ፣ እዚያ ድንግል ማርያም ነኝ፣ እዚያ አቡዬ ነኝ የሚሉ በተነሡ ቁጥር ሕዝቡ ሥራና ትዳር ፈትቶ ተንከራትቶ አይዘልቀውም፡፡ kale hiwot yasemalin

  ReplyDelete
 12. Dirowus Elias ahun limeta nurwall ??

  ReplyDelete
 13. Thank u brother I always appreciated ur articles God bless u Dani anbesawe.

  ReplyDelete
 14. Danny anbesaw keep up man

  ReplyDelete
 15. ኤልያስም መጣ ተብሏል እንዴ?? “የቸገረው እርጉዝ ያገባል” አሉ እማማ…..

  ReplyDelete
  Replies
  1. sitweldebe gedel yigebal... indeya new negeru!

   Delete
 16. የሃይማኖት ትምህርት በሚገባ መሰጠት ሲያቆምና ሰዎችም በተደላደለው የእምነት መንገድ ላይ በዕውቀትና በእምነት እየተመሩ መጓዝ ሳይችሉ ሲቀሩ ‹ባለ ተስፋዎች› ብቻ ይሆናሉ፡፡tebarek dyakon danel

  ReplyDelete
 17. I think the coming of king Tewodros is invitable because it is written in so many different Church books!

  ReplyDelete
  Replies
  1. dear anonymous, I did not get what you want to say. What do you mean by the coming of king tewodros? Is Tewodros also coming again? what related this to story we are being told. Could you make it clear.

   Delete
 18. ምን ይገርማል: ETHIOPIA ውስጥ ማንም ቢመጣ ተከታይ አያጣም

  ስንቱን አየነሁ

  ReplyDelete
 19. “ጌታ የተሰቀለው አራት ኪሎ ነው ካላልን በቀር,”
  ይችን ሀረግ ውስጠ-ወይራ ናት ብየ ልመን ይሆን?

  ReplyDelete
  Replies
  1. hahaha, "anteye sew negeregna new" alech azmari

   Delete
  2. ኣይ ያአበሻ ነገር ሁሉ ነገር ለኛ ቅኔ ነው አይደል? ለምን ፊትለፊት አንረዳውም?

   Delete
  3. You are free to appreciate the way you need but i don't think what you said is deacon Daniel's intention.

   Delete
 20. endezih ayinet awonabajoch sinesu yeartodokisawi lijoch atigabi melis bemesitetachew betam des yilal.

  ReplyDelete
 21. በእውነት በእንደዚህ አይነት የጓሮ አሉባልታ የሚሰናከል ሰው ወይም ምዕመን ካለ ሊሰናከል ይገባዋል.....በፊትም ከእኛ አለመሆናቸው ይታወቅ ዘንድ ›› ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ እንደጻፈው፡፡ መቼ ይሆን በእውቀት፣ በእምነትና በምግባር የምንመላለሰው፡፡ ጥፋትንም መወቅና መጸጸትኮ ከ ቅጣት ባያድንም ቅጣትን ሲያቀል ከብዙ ድርሳናትና ገድላት አንበናል ሰምተናል ተምረናል፡፡ እንወቅ፣ ከዛ እንመን...ምግባሩ ከነዚህ በኋላ የሚመጣ ነው….የእውቀት መጉደል ግን እንደዚህ ነፋስ በነፈሰበት እንደሸንበቆ ከመወዛወዝም በላይ የበጎ ምግባርን ዋጋ ሊያሳጣ ይችላል፡፡ ልክ የቁርባን ዋጋ ሳይገባን እንደመቁረብ ማለት ነው፡፡
  ት.ኤር 6፡16፣ ‹‹በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም የቀደመቺዪቱንም መንገድ ጠይቁ፣ መልካም የሆነችውንም መንገድ ዕወቁ በእርሷም ላይ ሂዱ ለነፍሳችሁ እረፍት ታገኛላችሁና፡፡›› እንደሚለው፡፡ መንገድ የሚለው ሊትራሊ አስፋልቱንና ኮሮኮንቹን ቢሆን ኖሮ፣ መጨረሻ ላይ ‹‹ለነፍሳችሁ እረፍት ታገኛላችሁ›› ባላለም ነበር፡፡ ስለዚህ ‹‹በመንገድ ላይ ቁሙ›› ሲል በሃይማኖት መንገድ ማለት ነው፡፡ ቀጥሎም ‹‹ የቀደመቺዪቱንም መንገድ ጠይቁ›› አለ ….በፍልስፍና ያልሆነ በሃይማኖት መንገድ ላይ ቆመን ለመከራከር ያልሆነ ለማወቅ መጠየቅ እንዳለብን ሲያስረዳ…ከዛ…‹‹ መልካሚቱም መንገድ ወዴት እንደሆነች ዕወቁ›› አለ…ጠይቀን እንድናውቅ ስለሚገባ….ከዛ..‹‹ በእርሷም ላይ ሂዱ ለነፍሳችሁ እረፍት ታገኛላችሁና›› ስለዚህ ቅደም ተከተሉ መጠየቅ፣ ማወቅ፣ በዕምነት መራመድ ነው ማለት ነው፡፡
  እኛ…እንደ እግርኳስ ደጋፊ በሞራል ብቻ ሆ! ባይ ነን እንጂ ሆ የምንልበትን እንኳ ምክንያት አናውቅም…..ስለዚህ እንደዚህ አይነት ተራ የሚዳ ነፋስ በነፈሰ ቁጥር ፍሬ ያለው እዚያው ሲቀር እኛ ግን እንደገለባ ስንበተን እንኖራለን፡፡

  ReplyDelete
  Replies
  1. EWNET BILEHAL, INTERESTING IDEA!!!

   Delete
 22. Yetebalewin neger wudk liyaderg yemichil tikkilegna metshaf kidusawi mikniyat yetekemete yimeslegnal wetarewiha lemidir welemiemenan bekalike /midir leloch haimanot teketay endihume tewahido orthodoxawian

  ReplyDelete
 23. ገልቱ! ይላል ወንድሜ…..
  በእንደዚህ አይነት የመንደር ወሬ የእውነት ኤልያስ መጥቷል ብሎ የሚያምን ካለ ሊሰናከል ይገባዋል! ብል ደስ ይለኝ ነበር ግን እኔም ያው ገልቱ ነኝ፡፡
  መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል
  ‹‹ በመንገድ ላይ ቁሙ፣ ተመልከቱም የቀደመቺዪቱንም መንገድ ጠይቁ መልካሚቱም መንገድ ወዴት እንደሆነች እወቁ በእርሷም ላይ ሂዱ፣ ለነፍሳችሁ እረፍት ታገኛላችሁና ›› ይላል፡፡ ትንቢተ ኤርምያስ የሚባል የብሉይ ኪዳን የመጽሃፍ ቅዱስ ክፍል ላይ6፤16 ፡፡
  ትንሽ እንዳብራራ እድል ከተሰጠኝ
  መንገድ እያለ የሚያወራው…የሃይማኖት መንገድ ነው…ምክንያቱም መጨረሻ ለይ ለነፍሳችሁ እረፍት ታገኛላችሁና ስለሚል፡፡ ኖርማል መንገድ ለነፍስ እረፍት አያሰጥምና፡፡
  ስለዚህ በሃይማኖት መንገድ ላይ ቁም፣ የቀደመቺዪቱንም ሃይማኖት ጠይቁ፣ መልካሚቱም ሃይማኖት ወዴት እንደሆነች እወቁ በእርሷም ላይ ሒዱ ለነፍሳችሁ እረፍት ታገኛላችሁና….
  ቅደም ተከተሉን አያችሁልኝ…
  መጀመሪያ ጠይቁ…..
  ቀጥሎም እወቁ….
  ቀጥሎ በሃይማኖት ሂዱ፣ ኑሩ ማለት ነው፡፡
  የኦርቶዶክስ አማኝ በቀላሉ በሌላ ነገር ተረቶ የሚወድቀው የነዚህን ቅደም ተከተል ስላላስተዋለ ነው ብዪ አምናለሁ፡፡ በጣም ብዙ አማኝ ያለ እውቀት ታቦት ይሸኛል፣ በኣላትን ድምቅ አድርጎ ያከብራል….ምናምን….ግን የምንንም ነገር ቫሊዩ(ዋጋ) ሳናውቅ ብናደርገው ከትርፉ ይልቅ ኪሳራው ያመዝንና እኛ በምናውቀውም ሆነ በማናውቀው መንገድ ስንጎዳና ከሃይማኖት መንገድ ስንርቅ ስንጠፋ ብሎም ቤታችን ከሞላ ምግብ ከጎረቤት እንቀላውጥና ስንጰነጥጥ እንገኛለን፡፡
  አለማወቅ ከሃይማኖት መንገድ የሚያወጣ፣ በእኛ ጊዜ ደግሞ ከፍልስፍና ጋር የሚያቀላቅልና የሚያኮናፍዝ፣ ብሎም በእምነቱ ስር እንኳ ሆነን ለምናደርገው በጎ ስራ እንኳን የሚገባውን ያህል ዋጋ የማያሰጥ በሽታ ነው፡፡ እውቀት ጥፋትን ያሳውቃል፣ ጥፋትን ሳያውቁ ደግሞ ይቅርታ መጠየቅ አይቻልም፣ ይቅርታ ደግሞ ንስሃ ነው…ያለ ንስሃ ደግሞ….ምኑን ዳንነው…
  …በእንደዚህ አይነት ኢምንት ነገር የምንበረግግ፣ በተራራ ላይ እንኳን እንዳለ ሰይሆን በሜዳ ነፋስ የምንበተን ፍሬ እንደሌለው ገለባ ዝርው ሆነን እንቀራለን….
  በየቤተክርስቲያን መጸሃፍት ላይ ያሉት የሃይማኖት ና የመንግስት ፈተና ቢመጣ ምን ሊውጠን ነው….
  ነጋቲ!

  ReplyDelete
  Replies
  1. These group (Eliyas awuyan) also quoted the same versus as you did.

   Delete
 24. when the people gave up hope on the religious institutions and when almost all our church administration politicized. this is what happening into the fellow christian members. It is the responsibility of our young theologian preachers to guide the pour Christian brothers and sisters and to get them out from this kind of wrong perceptions or misleads. Thank you Dani. And pls pass my great regards to your beloved family.

  ReplyDelete
 25. እንዴ ሰዉ ምን ሆኗል ሆሆሆሆ አሉ እትዬ ነገ ደግሞ ምን እንሰማ ይሆን ቆይ ሰላማዊ ሰልፍ ሲከለከል ጊዜ በየሰበቡ እየተሰበሰቡ ይሆናል እንጂ
  ዳኒ ግን እግዝአብሄር ቤተሰብህን ይባርክ

  ReplyDelete
 26. እግዚኣብሄር ማስተዋልና ጥበብን ይስጠን
  እግዚኣብሄር ያገልገሎጥን ዘመን ከፍ ያርግልን ኣሜን

  ReplyDelete
 27. Gud Saysema Mesekerem Aytebam Ale Ye Agere Sew Ye Cherinet AMILAK Edime Keseten Gena Bezu Enayalen Ensemalen Teru Milketa New MEDEHANIALEM Tsegawin Yabizalih Dn.Danii

  ReplyDelete
 28. በክርስቶስ የተወደድክ ወንድም ዳንኤል

  በጉዳዩ ላይ ያለህን አመለካከት አና ምን ይደረግ የመፍትሔ ሀሳብ ስላካፈልከን አናመሰግንሀለን። ግን ስለጉዳዩ ለማንሳት አልዘገየህም ወይ? ከጽሁፍህ እንደተረዳሁት ንብዩ ኤልያስ ነኝ ባዩ ከተነሳ አራት አመት አለፈው። የራሱን ካህናት መልምሎ ቅዳሴም አንደጀመረ ሰምተናል። ቤተክርስቲያን ያፈራቻቸው የሚባሉ ፥ በኢትዮጵያ ቤተክህነት እና በፖለቲካው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው ሊቃውንት ስለ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ስያሜ፥ ስለ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ እና የአንበሳው ምስል፥ ስለ ኢትዮጵያ አና እመቤታችን፥ ስለ ማተብ እንዲሁም የግብጽ ኦርቶዶክስ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን እምነት ባህልና የባእላት ቀን አቆጣጠር ላይ የመጣችውን ተጽእኖ በቁጨት በመጽሐፍ እየጻፉ በቃል አያስተማሩ ይገኛሉ:: ለምሳሌ ያክል ንቡረ እድ ኤርሚያስ ከበደን እና አባ ተስፋስላሴ ሞገስን መጥቀስ ይቻላል። በዚህም ላይ አስተያየት አንድትሰጡን ከአንድም ሁለት ሶስት ጊዜ ጠይቀን ነበር። ለጻፍነው ኢሜል ምላሸም አላገኘንም። አንተ ሁልጊዜ እንደምትጠቅሰው አነዚህ ሊቃውንት በህይወት ባሉበት እና በቃል ምላሸ መስጠት በሚችሉበት ጊዜ ስለ አስተምህሮታቸው ይጠየቁ፥ ትችትም ከሆነ ይተቹ።

  ወልደ ሥላሴ

  ReplyDelete
  Replies
  1. dear Wolde Selase, thank you so very much for saying this!!! yes, there are some fathers who are stirring believers mind here in the states! I myself have a friend who is a "follower" of Nibure Ed Ermiyas and she does not celebrate GENA as this father told her it isn't suppose to be celebrated in December rather on September first. Also, Tsome Niybeay breaks on Timqet day. so many confusing teachings. And, I can't even start to tell you how committed these people are to the teaching of this father! { it is almost a cult follower behavior!!!} Though, I don't believe it is only Dn. Daniel's responsibility to address this. But, we would benefit from his views!!! TEbareke wondeme

   Delete
 29. እረ ጎበዝ የቀደመችውንና የኌለኛዪቱን ሃይማኖት ተከተሉ::ልብ ይበሉ በአሁኑ ሰአት የሀይማኖት ድርጅት ተብለዉ እንደ አሽን ፈልተዋል

  ReplyDelete
 30. Elias endaet new aret kilo geba mefenkel mengest liyaderg new...kkkkkkk tekawami yelakew endayhon...kkkkkk

  ReplyDelete
 31. yasazinal yegna hizb bekelalu yitalelal mech yihon tenkiko sile haymanoyu yemiawkew kemetaw gar menedat endalkew ye nuro chigrina ena be amro yalemebsel yebzu neger seleba nen yasaznal Amlake kidusan tibebna mastewal yemiyastemru melaektun ende Abatachn Daniel yilakilin

  ReplyDelete
 32. Gud Saysema Mesekrem Aytebam Yelal ye Agere sew Sitert Bezihu re'es Zuriya Lela Bilog Lai Anibebe westen Sikenknegn Neber Antem MEDEHANIALEM beseteh Tsga Teru Adergeh Segelsekilen Ahunim Tsegawin Yabizaleh Le Egnam Masetewalun Yesten CHERU AMILAK edeme Keseten Gena Bezu Ensemalenim Enayalenm Teru Milketa New MEDEHANIALEM Tsegawin Yabizalih Dn. Danii

  ReplyDelete
 33. Egziabhier Amlak haymanotachinin yetebiklen amen

  ReplyDelete
 34. ስለ ኤልያስ መምጣት የሚነግረን ሌላው መጽሐፍ የዮሐንስ ራእይ ነው፡፡ የዮሐንስ ራእይ በምእራፍ 11 ላይ ዓለምን የሚያጠፋው ሐሳዌ መሲሕ ከመጣ በኋላ ዙፋኑን አደላድሎ የዓለምን ክርስቲያኖች ሲጨርስና ምስክር ሲጠፋ ሁለት ምስክሮች መጥተው 1260 ቀናት ምስክርነት እንደሚሰጡና በመጨረሻም በሐሳዌ መሲህ እንደሚገደሉ ይገልጣል፡፡ ከሁለተኛው መክዘ ጀምሮ የተነሡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ሁለት ምስክሮች ኄኖክና ኤልያስ መሆናቸውን ተርጉመዋል
  Thank you very much!
  Mamush, MN

  ReplyDelete
 35. Dani i wish u a long and blessed life. u addressed current issue which could save many soul. God will never let this country down. u r one of the most influential writer in this generation. your articles always make a difference. keep it up.

  ReplyDelete
 36. yihe 8 gnaw shi sayhon 9 gnawn alfoal enedea sewu min nekaw (ene jemaneshi) zare tilant dingil maryam negni bla metachi zare elias kemeta nege henoh samnt esaru eyesus yimeta yihonal tebku

  ReplyDelete
 37. እግዚኦ ማለት ነው የሚሻለው፡፡ገና የባሰ ይመጣል!
  ዳኒ በርታ!

  ReplyDelete
 38. ለዲያቆን ዳንኤል

  በርግጥ ስለሁኔታው አስተያየት መስጠት ባልችልም ስለ ሰንደቅአላማ ያልከው ግን ስህተት እንደሆነ ከትህትና ጋር እገልጻለሁ:: ይሕም የኖህን ቃልኪዳን ሲያመለክተን ከቀስተ ደመናው ቀለማት ጎልተው የሚታዩት አርንጉዋዴ ቢጫ ና ቀይ እንደሆነ ግልጽ ነው:: እንግዲህ እነኝህ ሶስቱ ብዙ ትርጉም እንዳላቸው ተምረናል:: ከነዚህም መካከል ያንድነቱንና ሶስትነቱን፣ የነብስ ፣ የስጋ እና የምንፈስ አንድነትንና ሶስትነቱን፣ የኢትዮጵያውያን የውህደት ዘር (የካም፣ያፌት ና ሴም): የኢትዮጵያ መለኮታዊ መንግስት: ቤተ ክህነት፣ ቤተ ህዝብ እና ቤተ ምልክና ናቸው:: አባቶቻችን ይህን ሲያስተምሩን "ልክ አይደሉም" እያልከን ነው ወይንስ አንዱን ለመቃዎም ስትል ያለውን እውነት ጨፈለከው:: ማህተብም ቢሆን መታሰር የሚገባው ይህ ርቂቅ ትርጉም ያለው አርንጉዋዴ ቢጫ ና ቀዩ ነው እንጅ አንተ እንዳልከው ከጽድቅና ከኩነኔ ጋር ተገናኝቶ አይደለም:: የግብጽ ፓትርያርክ ቤተክርስቲያንን ያስተዳድሩ በነበረበት ወቅት ውዳሴ ማርያምን ሲያስተረጉሙ : ደመና በዞረ ጊዜ ጎልተው የሚታዩት ቀለማት ተብሎ ሲተረጎም የራሳቸውን ሰንድቅ አላም አስገብተው እንደጻፍ አልተረዳሃው የሆን? ይህም የግብጽ ሰንደቅ አላማ ቀይ ጥቁር እና ነጭ ነው:: ይህም ነገር እስከዛሬ ድርስ ውዳሴ ማርያም ትርጉም ላይ ያለ አይደለምን? ህሊና ያለው ሰው መቼም ከቀስተደመና ቀለማት መካከል ጎልቶ የሚታየው ቀይ ጥቁር እና ነጭ ሳይሆን አርንጉዋዴ ቢጫ ና ቀዩ እንደሆነ ግልጽ ነው:: ታዲያ ይህንን የግብጾች ደባ እና ተንኮል በግልጽ ከመቃውምና ከማውገዝ ይልቅ ሰንደቅ አላማው ምንም አይነት ሃይማኖታዊ ትስስር (ትርጉም) የለውም ብሎ የግብጽን ሰንደቅ አላማ ሃይማኖታዊ ትርጉም ስጥቶ ይህ ህዝብ አንገቱ ላይ የግብጽን ሰንደቅ አላማ (ቀይ ጥቁር እና ነጭ) አስሮ በጭፍን እንዲሄድ መተው ከእንዳንተ ያለ ኢትዮጵያዊ የታርክ ተመራማሪ የሚጠበቅ አይደለምና እርምት ቢወሰድበት ስል በትህትና እጠይቅሃለሁ::ሲሆን ሲሆን እውነቱ መግለጽ ሲገባ!

  እግዚአብሔር ይስጥልኝ::

  ReplyDelete
  Replies
  1. Brother, please read bible. Dn Daniel is right. Flag is just a sign for a country!!!

   Delete
  2. From whom do you have such an education on Flag. I want to know your teacher. I have never heard such an education before in Ethiopian Orthodox church officially.
   Especially the correlation with the Holy trinity is really new and illogical. And also do not forget how wearing the 'MATEB' comes, it is a sign of baptism and belief. Any way please tell us your source.

   Delete
  3. Ere wendmie Astewil Egziabhier eko yefeterew Ethiopian bicha aydelem. Ersu key tikur achir rejim Africawi Americawi sayil hulachininim bealem mulu yefeterenin hizbochun yiwedenal. Hulachinim endindinlet yifeligal. endih Arenguade bicha kein ke keste demena gar ayayizen bebanderachin kentu timkihit yeminmeka kehone Getachin Medhanitachin Iyesus kiristos ke Ethiopiawit Dingil teweldo bihon noroma timkihitachin yet bederese neber.

   Delete
 39. ዳኒ በመጀመሪያ ደረጃ ቃለ ህይወት ያሰማልን !!! እነደዚህ ዓይነት አዳዲስ ነገሮች ሲፈጠሩ ቶሎ የማንቂያ ደወል በማስተላልፍህ፡፡
  ነገረ ግን ዳኒ ራእየ ዮሐንስ እንደሚነግረን ኄኖክና ኤልያስ ምስክርነት የሚሰጡት ለ1260 ቀናት ወይም ለ42 ወራት ወይም ለ ሦስት ዓመት ከስድስት ወራት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ይገደላሉ፣ ተነሥተውም ያርጋሉ፡፡ አሁን ግን አዲስ አበባ መጣ የተባለው ኤልያስ መጣ ከተባለ አራት ዓመት ሊያልፈው ነው፡፡ እስካሁን ህን የመሰለ መረጃ ባለማስተላለፍህ ትንሽ የዘገየህ ስለመሰለኝ ይህን አስተያየት ለመስጠት ነው፡፡ አመሰግናለሁ

  ReplyDelete
 40. መቼም በእውነኛው ፍርድ፤ በምድር ማለፍ እና በሰማያዊው የእግዚአብሔር መንግስት መኖር የሚያምን ሁሉ ዋና ዓላማው ይህችኑ ዘለዓለማዊ መንግስት መውረስ ነው፡፡ ሌላው ሁሉ ዝግጅት ነው፡፡ እንደ ጤነኛ ሰው ማንም ሰው፤ የምንም ዓይነት ኃይማኖት ተከታይ ይሁን በራሱ ላይ ክፉ አይመኝም፡፡ አንዱ መንፈሳዊም ለሌላው ሰው ከፉን አይመኝም፡፡ ከዚህ የተነሳ ስለኤልያስያውያኑ ሀሳብ ማወቅ እፈልጋለሁ፡፡ ከላይ ከተገለጹት ኃይማኖታዊ ቁም ነገሮች ውጭ ለነዚህ ወንድሞች እና እህቶች ምን ተገልጦላቸው ይሆን፡፡ ወይም ደግሞ ምን አልገባቸው ይሆን? አስኪ ሃሳባችሁን በዚህ ብሎግ ወይም በሌላ መንገድ ቀጥተኛ እና ግልጽ በሆነ ሁኔታ ብተትገልጹ፡፡ ለማስረዳት ወይም ለመረዳት ምቹ ብትሆኑ፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ከላይ ያልኩት የ'ጤንነት' ጉዳይ ይነሳል፡፡

  ReplyDelete
 41. እግዚያብሔር ከክፉ ነገር ይሰውረን በሐይማኖታችን ጸንተን እንድንኖር የድንግል ማርያም ልጅ ይጠብቀን አሜን

  ReplyDelete
 42. እግዚያብሔር ከክፉ ነገር ይሰውረን በሐይማኖታችን ጸንተን እንድንኖር የድንግል ማርያም ልጅ ይጠብቀን አሜን

  ReplyDelete
 43. wish GOD and MARRY with u....

  ReplyDelete
 44. ወይ ጉድ!ከኤልያስያውያኑ ይባስ ያስገረመኝ ደግሞ የአንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች አተያይ፡ እስኪ አሁን ሰንደቅ አላማ ከጽድቅና ኩነኔ ጋር ምን መጋጠም አለው? የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ መለያነቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ነው እና ሌላው ዜጋ አማኝ በቅድስና ቢኖር መንግስቱን ላይወርስ ነው ማለት ነው? ለመሆኑ ቀስተ ደመናስ ቀለሙ 3 ብቻ ነው? የክርስቶስ ደም የፈሰሰው ለአለም ነው። ቤተክርስቲያንም የትኛውንም ዜጋ የምታስተናግድ የሰማያዊት ኢየሩሳሌም ምሳሌ እንጂ በቀለም እና በቋንቋ የተወሰነች ሚጢጢዬ ማዕከል አይደለችም።

  እ ና ስ ተ ው ል!

  ReplyDelete
 45. ሰንደቅ ዓላማችን ከኢትዮጵያዊነታችን ጋር እንጂ ከኦርቶዶክሳዊ እምነታችን ጋር የታሪክ እንጂ የድኅነት ተዛምዶ የለውም፡፡
  ከሕዝብ እሴቶች እንደ አንዱ ሆኖ እንጂ ከጽድቅና ኩነኔ ጋር ተያይዞ መሆን የለበትም፡፡

  እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ።
  ማስተዋሉን ይስጠን። አሜን!

  ReplyDelete
 46. ዳኔ አሁንስ አንተው ታሳዝነኝ ጀመር ። የምንሰማበት ቅን ልቦናቾን ከኛ ርቒል ። ያ :ባይሆን ሰለባንዲራ አስመልክቶ የጻፈው ወንድም ፤ ግዜውን በዜህ ላይ ባላባከነም ። መጤን : ያለበት ሙሉ መልኦክቱ ነው። አልያ አኛ በማተብ ከለር ስንከሬከር ጭሬሹን ማተብ ለማያውቁ እንዳንሰጥ እባካችሁ መልእክቱን በቅን ልቦና እንመለከተው።

  ReplyDelete
 47. dn daniel selamneh? des ymil tsihuf tsafik Egzixbher yibaRkih.

  ReplyDelete
 48. ዲ/ዳንኤል እግዚአብሔር የአገልግሎት እድሜህን ያብዛልህ በጣም ግራ አጋብተውኝ ነበር ምን የሚሉት እምነት ነው ብየ ገርሞኛል አንተም ያስቀመጥቃቸው ምክንያቶች በጣም የምስማማባቸው ናቸው ::
  እግዚአብሔር ይስጥህ::

  ReplyDelete
 49. ቃለ ሕወት ያሰማህ ። አረ የቴዎድሮስንም ቃኘው ብዙ ችግሮች አሉባቸው እነርሱም አለባበሳቸዉ እንደ ኤልያሳዉያ ኖች ነዉና ።

  ReplyDelete
 50. EGZIABIHER TESGA YEBZALEN DANIEL

  ReplyDelete
 51. Excerpt from the book Ethiopia: The Classic Case by N’bure-Id Ermias K. WoldeYesus, page 32-35

  The Second Covenant

  The second Covenant of God, by which He assured His Creation never to destroy it again by flood, with Noah, and it is perpetuated in this world through the sign of the Rainbow.
  For the Ethiopians, the rainbow, from the beginning of their existence, was not only a physical manifestation of their Creator’s presence in their midst, but was also a spiritual assertion of the imprint of the Devine Seal of the Covenant on their hearts wherein it is enshrined by faith since then. That is why the Ethiopians always looked to it outwardly and inwardly: first, as a testimony of their covenantal relationship with the Only God they worship: secondly, as an eternal assurance of His Divine Protection from the enemy and thirdly, as a guarantee of their security from total annihilation by destructive forces of nature or human perversity……….it represents the Trinity of God and that of the human race descended from the three sons of Noah: Shem, Ham and Japheth.
  The significance of the Second Covenant is effectively enhanced by the Third Covenant of God with Melchizedek the Patriarch of Ethiopianism, whose Foundation and Crown is none other than God the Son Jesus Christ Himself.

  ReplyDelete
 52. ጥያቄ አለኝ። ለመሆኑ ይህ ኤልያስ ነኝ ብሎ የመጣው ሰው ማንው? ስሙ ማን ይባላል? ታሪኩስ ምንድን ነው? አራት ኪሎ የትኛው ቤተክርስቲያን ነው ይህ ሰው ያለው? ለምን በግልፅ ለመጻፍ ሳይቻል ቀረ? በድፍኑ ከማስቀመጥ በግልፅ ቢነገረን የበለጠ ለመጠንቀቅ ጠቃሚ ስለሚሆን አንተም ባትሆን ሌሎች የሚያውቁ ካሉ ቢነግሩን መልካም ነው እላለሁ። ቢቻል ፎቶግራፉንም ወጥቶ ብናየው ተገቢ ይመስለኛል። አንተ ግን የበኩልህን ብለሃልና ልትደነቅ ይገባሃል።

  ReplyDelete
  Replies
  1. አዎን! ማርያም ነኝ ብላ የመጣችውን ታሪኳን ሰምተናል፤ መልኳን አይተናል፤ ስለዚህ በደንብ እናውቃታለንና ልንታለል አንችልም። ይህ ኤልያስ የተባለ ሰው ግን በወሬ ብቻ ስለሆነ ግራ ተጋብተናልና በዝርዝር የምታውቁ አንድ በሉን።

   Delete
  2. በስውር ይታያል ነው የሚሉት

   Delete
 53. I always get amazed why Orthodox Christians enters in religion hectic always.We have many well educated priests and written books which deals until the dooms day. Let the Church leaders have to address each and every question arise from the people, timely in organized and better prepared way, publish book, journals, conferences with a researched papers. then tekula will forced to out when the real Yebegochu Eregna come.

  ReplyDelete
  Replies
  1. The devil spirit is working 24 hours to destabilise God's people and that's why there is always 'fetena' in orthodox church

   Delete
 54. Taken from Nebure-id Ermias facebook page:
  Last week, we received an e-mail from someone from Ethiopia regarding the religious movement by the name, “Nebiyu Elias is in Addis” and asked the following question:

  From S. Muluneh;

  I am a frequent reader and visitor of your website. And I know some of your teachings. Now there is some strange movement in Addis Ababa that targets the Ethiopian Orthodox Tewahdo Church by the name of "Nebiyu Elsa is in Addis". Some of the teachings and ideology look like yours; and I want to know if this movement is in relation with yours which I doubt it is yours.

  Response:

  Thank you in the Names of God and The Virgin Mary for your email message, and for visiting Our website.
  In order to help you clear your curiosity to know “if the movement by the name of ‘Nebiyu Elsa (or Elias?) is in Addis’ has a relationship with our Ethiopia: The Kingdom of God”, I say, there is none.
  However, I am glad they “targeted the Ethiopian Orthodox Tewahdo Church” because the current incumbents, including the clergy and the laity of the Church, need such incentive to wake up and realize what is going on within and around them. They still seem to be asleep or conniving and cooperating with the adversary.
  This is how The Holy Spirit works whenever circumstances are ripe and conducive. I say this because I discern that most of the teachings of the movement go in line with those of ours.
  Please let me remind you to amend your term of “ideology” if its implication is meant to include our vocation, or if its connotation involves the material or the secular aspect of its meaning only, because The Divine Truth that is revealed in the Message that we, in Ethiopia: The Kingdom of God of The Holy Covenant in the Ethiopian Tewah’do Faith are delivering has nothing to do with the human except The Divine.

  ReplyDelete
 55. very interesting discussion

  ReplyDelete
 56. ዳንኤል እንደምን ነህ ደህና ነህ ወይ ?

  የጻፍከውን በጣም ወድጄዋለሁ ነገር ግን

  በባንዲራ ጉዳይ የጻፍከው አልተቀበልኩትም

  የማርያም መቀነት እያሉ ወላጆቻችን ያሥተማሩንን

  እና ታቦታት ሰገቡ እና አዳዲስ ቤተክርስቲያን ሲከፈቱ

  ከሰማይ ቀስቱን ከቦ የሚያጅበውን የኖህ ቃል ኪዳን ምልክት

  በምን እይታ አይተኸዉ ነዉ ?

  ወለተ ሚካኤል

  ReplyDelete
 57. በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ስም የከበረ ሠላምታዬን አቀርባለሁ፡፡ በቀረበው ጽሑፍ ላይ ያለኝን አስተያየት እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡
  የጽሑፉ መረጃ አልባነት ለአሽሙርነት
  ጽሑፉ መሠረት ያደረገው “ተብሏል”፣ “ተነስተዋል” ተብለው በቀረቡ፡ አንድ እርግጠኛ ያልሆንበትን ነገር ለማቅረብ፡ በምንጠቀምበት የአቀራረብ ዘዴ ነው፡፡ ይህ ጽሑፍ፡ የበለጠ ጠቃሚ የሚሆን የነበረው፡ የተሟላ መረጃ ይዞ ሲገኝ ነበረ፡፡ ይኸውም፡
  ነብያት ነን ያሉት ሰዎች እነማን ናቸው?
  ቤተ መንግሥቱና ቤተ ክህነቱ ይጠራል ያሉት በምን መልክ ነው?
  ኦርቶዶክስ የሚለውን ስም አንቀበልም ያሉት ለምንድን ነው?
  ኦርቶዶክስ የሚለውን ስም አይሆንም ካሉ በምን ይተካ ነው ያሉት?
  ነጭ ልብስ ብቻ ይለበስ ያሉት ከምን አንጻር ነው?
  አረንጓዴ ብጫ ቀይ የሆነውን መለያ ምልክት የእውነት ከኩነኔና ጽድቅ አገናኝተውታል ወይ ካገናኙትስ በምን ሁኔታ ነው ያገናኙት?
  የሚሉትና የመሳሰሉት መረጃዎች በዝርዝር መቅረብ ይገባቸዋል፡፡ እነዚህ መረጃዎች ተጣርተው ሳይቀርቡና፡ ግራቀኙን ለማየትና ለመመርመር በሚያስችል መልኩ ባልቀረበበት አኳኃን ጽሑፉ መቅረቡ ፈጽሞ ትክክል አይሆንም፡፡
  እኔ ባለኝ መረጃ መሠረት፡ እነዚህ ከላይ የታተቱት ጉዳዮች፡ በስፋትና በጥልቀት ተዳሰው የሚገኙት ንቡረ እድ ኤርምያስ ከበደ ወ/ኢየሱስ የተባሉ የቤተ ክርስቲያናችን አገልጋይ ባዘጋጁዋቸው መጻሕፍት ውስጥ ነው፡፡ እነሱም
  ኢትዮጵያዊው በማንነቱ ፍለጋ
  ኢትዮጵያ የአለሙ መፋረጃ!
  ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት (ክፍል 1፣2፣3)
  http://www.ethkogserv.org
  የተባሉት መጻሕፍትና ድረገጽ ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር ስመለከተው፡ ምን አልባት ዲ. ዳንኤል ክብረት እንዳመነበት፡ ሓሳውያን ትምህረት ሰጪዎች ተነስተው ትክክል ያልሆነ ሥራ እየሰሩ ስለሆነ፡ ይህንን ምክኒያት በማድረግ፡ ካላይ ከጠቀስኳቸው ታላቅ የአገራችንና የአለማችን ጸሐፊ ጋር ያለውን የሓሰብ ግጭት፡ በአሽሙር የመግለጽ አዝማሚያ ነው ብዬ እንድገነዘበው አስገድዶኛል፡፡ በዚህም የተነሣ ዲ. ዳንኤል ክብረት ጽሑፉን በሚከተለው መንገድ መጻፍ ነበረበት ብዬ አምናለሁ፡፡
  1.ሓሳዊ ናቸው ተብለው የታመነባቸው ሰዎች ሙሉ ማንነትና፡ እምነታቸውና ዘዴያቸው ጭምር ሙሉ በሙሉ መቅረብ ነበረበት፡፡ ይህ ግልጽ የሆነ አካሄድ፡ እውነትን አንጥሮ ማውጣት የሚያስችልና፡ ትክክል ያልሆነውን ሓሰብ ብቻ ለማስወገድ የሚረዳ በመሆኑ፡ ዘወትር መከተል ያስፈልጋል፡፡
  2.አጸፋዊ ምላሹ በሚሰጥበት ጊዜ፡ ምላሹ የአገሪቱንና የቤተክርቲያኒቱን ቋሚ እውነታዎችን፡ እስከ መጨፍለቅ ድረስ የደረሰ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
  ጸኣዳ ነጭ ልብስ የመልበስ ኢትዮጵያዊው ባሕል
  ጸኣዳ ነጭ ልብስ መልበስ፡ ታላቁ ሃይማኖታዊ ቅርሳችን ነው፡፡ ይኸውም፡ በክርስቶስ የማዳን ሥራ ምክኒያት ዘመኑ፡ ዘመነ ምህረት፣ ዘመነ ምስራች መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡ ይኽም ሁኔታ፡ ኢትዮጵያውያን፡ እንደሌሎቹ ባሕሎቻቸውና ልምዶቻቸው ሁሉ፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተቆራኙ ለመሆናቸው፡ የክርስቶስን ትንሳኤ ያበሰሩት መላእክት፡ የለበሱትን ጸኣዳ ነጭ ልብስ ማየቱ በቂ ማስረጃ ነው፡፡
  ይህንን ምልክትነትና ምስጢር የያዘን ልብስ፡ “ልበሱ” ብሎ ኢትዮጵያዊነትን ለመጠበቅ የሚደረገውን አስተዋጽኦ መደገፍ ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ፡፡ በእርግጥ “ነጭ ልብስ” ብቻ መባሉ አሁን ባለንበት አስተሳሰብና ሁኔታ፡ ሊከብድ ቢችልም በቀደሙት ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ግን፡ ይህ ልብስ የአዘቦት ልብስ እንደነበረ፡ የተለያዩ የታሪክ ማስረጃዎች እንደሚያመለክቱ መርምሮ መረዳት ይቻላል፡፡
  አረንጓዴ፡ ብጫ፡ ቀይ ሕብረ ቀለም ያለው ያንገት ማኅተባችን
  አባቶቻችንና እናቶቻችን፡ የኖኅ ቃልኪዳን ምልክት የሆነውን ይህንን ምልክት፡ ለመጠበቅ ሲሉ በኑሮአችን፣ በሕይወታችን፣ በባሕላችንና ልምዶቻችን ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ላይ እንዲኖር አድርገውታል፡፡
  • ቤተክርስቲያንን ከጉልላቷ እስከ ቅጽሩ ድረስ በምልክቱ ማስጌጥ
  • በበዓላት ጊዜ በዓላቱን ማድመቂያ ማድረግ
  • በዕለት ተዕለት ልብሳቸው ላይ፡ በተለይም የክርስቶስን የማዳን ሥራ ዘወትር በይፋ በሚገልጸው፡ ጸኣዳ ነጭ ልብሳቸው ላይ፡ እንደ ዘርፍ አድርጎ መልበስ
  • የማርያም መቀነት ብሎ በመሠየም፡ ልጆቻቸው ሳይቀሩ በሕጻንነት ጊዜያቸው ጀምሮ በሕሊና ሠሌዳቸው ላይ ተቀርጾ እንዲያድግ በማድረግ
  • ከሁሉም በላይ ደግሞ፡ የአገራችንን ኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዚሁ መሠየምና እያንዳንዱ መዕመን፡ ከሥላሴ ልጅነት ለማግኘቱ ምስክር እንዲሆን፡ ምልክቱን የአንገት ማኅተብ አድርገን እንድንጠቀምበት ማድረጋቸው፣
  ይህንን ፈጽሞ ተረስቶና ተቀብሮ የቀረ ኢትዮጵያዊ ማኅተባችንን፡ በከፍተኛ ቆራጥነትና ተጋድሎ፡ ከተቀበረበት አውጥተው እውነታውን ያስተዋወቁን የቤተ ክርስቲያናችን አገልጋይ፡ ከላይ የጠቀስኳቸው ካህን ናቸው፡፡ ዲ. ዳንኤል ክብረት በዚህ ረገድ፡ ምን ዓይነት ሓሳብ ያላቸውን፡ ሓሳዊያን ትምህርት ሰጪዎችን እንዳገኝ በዝርዝ በይነግረንም፡ በጽሑፉ ግን ከላይ የተዘረዘረውን መለኮታዊ ውልና ስጦታ፡ ያንንም ስጦታ እናቶቻችንና አባቶቻችን ያቆዩበትን ተጋድሎዋቸውንና፡ እንዲሁም በዚህ ባለንበት ዘመን ይህ የአባቶቻችንና የእናቶቻችን አደራ፡ እንዲጠበቅና እኛም ትክክለኛውን ኢትዮጵያዊነት በመኖር፡ በዓለም ለይ በንቃትና ኩራት፡ እንድናስተዋውቀው ጥረት እያደረጉ የሚገኙ፡ የቤተክርስቲያን አገልጋዮችን ጭምር፡ “ከጽድቅና ኩነኔ ጋር አገናኝተውታል” በሚል ሰበብ አጣጥሏቸዋል፡፡
  ስለዚህ ዲ. ዳንኤል ክብረትን የምጠይቀው ጥያቄዎች አሉኝ
  1.አንተም እንደጠቀስከው: የማኅተባችን የቀለማት ኅብር: ለኩነኔም ሆነ ለጽድቅ የሚሠጠው ፋይዳ የለም፡፡ ነገር ግን ለዚህ ለታላቁና ዘለዓለማዊ ልደታችን ምልክት መሆን ያለበት ምን ዓይነት ቀለም ወይም የቀለም ኅብር ነው?
  2.አረንጓዴ፣ ብጫ፣ ቀይ የሆነው ማኅተብ፡ አሁን እየተሠራበት ያለውን የግብጽ ባንዲራ ቀለማት ኅብር፡ መተካት አለበት: የሚለው ሓሳብ ላይ ያለህ አስተያየት ምንድን ነው
  እነዚህን ጥያቄዎች ያነሳሁበት ምክንያት፡ ጸሑፉ አጠቃላይ መንፈሱ፡ እነዚህ ሓሳቦች ላይ ያተኮረ ነው ብዬ ስላመንኩ ነው፡፡
  ለኢትዮጵያውያን ወገኖቼ በሙሉ! አስተውለን እንድናየው የምፈልገው፡ የኢትዮጵያውያን ልምድ አለኝ
  ይኸውም ዘወትር ጥምቀት በመጣ ቁጥር የምናደርገው፡ አረንጓዴ፣ ብጫ፣ ቀይ ኅብር የተቀባ ዱላ የመያዝ ልምዳችን ነው፡፡ ይህንን ዱላ ለምንድን ነው ጥምቀት ላይ እንድንይዝ ልምድ የተደረገው? አሁን አሁን ግን ይህ ልምድ፡ በተለይ በወጣቱ ዘንድ እምብዛም የተለመደ አይደለም፡፡
  እንግዲህ የዲ. ዳንደኤል ክብረት ጽሑፍ፡ ይህንን ሁሉ ትኩረት ያለደረገና እንዲሁ በደፈናው ስለተጻፈ፡ የጽሑፉ ዓላማ እንደውም፡ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጠፋ ሆኖ አግኝቼዋለው፡፡ ይህንንም የምላችሁ ያለምክንያት አየደለም፣ እስኪ ራሳችሁን ራሳችሁ ገምግሙትና እውነተኛውን ምላሽ ለራሳችሁ ስጡ፣ ይህንን በዲ. ዳንኤል ክብረት የቀረበውን ጽሑፍ አንብባችሁ እንደጨረሳችሁ የሚሠጣችሁ መልእክትና የሚሰማችሁ ስሜት ምንድን ነው? ልምዶቻችንን መርምረን እንድንቀበል ሳይሆን አሉታዊ ጥርጣሬ እንዲያድርብን አይደለም?
  ሠላም እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን!

  ReplyDelete
  Replies
  1. I think the main point of Dn. Daniel article is about the false teaching concerning the coming of "Nebiue Elias" from religious point of view. So the aim is to inform us about the existence of this movement and,nothing else. If you has a doubt on this,you can check from other sources. They named themselves "Maheber Selassie Zdekike Elias",their sign is like "toto" letter found in Amharic alphabet,with a moon and star picture inside it. Egeziabher Yitebken.

   Delete
  2. yehulum neger meseretachen mehon yalebet metshafe keduse new enji zegenet aydelem mekeniatum Egziabhere ayadalam endeza kalen negeroch tekekel wedalhone mengede yameralu

   Delete
 58. ውድ ዳንኤል ጥሩ ትምህርትን ሰጥተኸኛል
  ከዚሁ ጎን ለጎን መረሳት የሌለባቸው የተሳቱ ወንድሞቻችን (መምህራን )በስፋት እየታዩ ነው ስሙን መጥቀስ ያልፈልግኩት አንድ መምህር አፉን ሞልቶ ሲያስተምር ሰምቼው ነበር ግን ዳሩ ይሄ ይሆናል የሚል ግምት ስላል ነብረኝ ብዙም ቦታ ሳልሰጠው አልፌው ነበር
  አሁን ግን ማንነታቸውም እንዳጠና መንደርደሪያ ህሳብና ጥልቅ ትምህርት አጊኝቻለው
  ስለ ሁሉም የልዑል እግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን
  ቃለ ህይወት ያሰማልን

  ReplyDelete
 59. Thank you Diyakon for your timely reply. but I would like to know whether it have any relations with the pool of siloam churchs.

  ReplyDelete
 60. Yehe Hulu Bete kerstiyan Asteddadari Endatache Yastawekal Betelye be Ethiopia Ortodox Ye Egziyabher fekad sayehon Yeswe fekad Eyetfesemebat New Betam Yasazenal !!!

  ReplyDelete
 61. OUR ETHIOPIANISM HAS NOTHING TO DO WITH ETHIOIAN ORTODOX CHURH. I COULD NOT FIGURE OUT HOW THEY ARE TRYING TO ASSOCIATE IT WITH RELIGION MAYBE THEY ARE TAKING ADVANTAGE OF MILLIONS ETHIOPIANS WHO ARE PROUD OF THEIR ETHIOPIANISM..SOMETHING SHOULD BE DONE TO STOP THIS MADNESS..

  ReplyDelete
  Replies
  1. የሚከተሉትን መጻሕፍት ያንብቡ


   ኢትዮጵያዊው በማንነቱ ፍለጋ (
   ኢትዮጵያ የአለሙ መፋረጃ!
   ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት (ክፍል 1፣2፣3)


   ጸሓፊውንቡረ እድ ኤርምያስ ከበደ ወ/ኢየሱስ ይባላሉ


   ወይም የሚከተለውን ሕዋ ሰሌዳ (web site)ይመልከቱ
   http://www.ethkogserv.org

   Delete
  2. Ethiopiawinet ayatsedkim menfesawinet enji. Enam Enezihin metsehaft bemanbeb gizeyachinin anatefam

   Delete
  3. ማንበብ ጊዜን ማባከን ከሆነ፡ የእርስዎን ጽሑፍ ማን ጊዜውን እያባከን እንዲያነብ ነው እዚህ ላይ የሚጽፉት፡ ይህ ትክክለኛ አባባል ስላልሆነ መታረም አለበት፡፡ ነገር ግን ስላነሱት ሓሳብ፡ የሚከተለውን አስፍሬያለሁና አስተውለው ይዩት፡-
   • በሦስቱም ኪዳናት ማለትም (ኪዳነ ልቡና፣ ኪዳነ ኦሪት፣ ኪዳነ መንፈስ ቅዱስ) ጸንታ የተገኘች ብቸኛ አገር ኢትዮጵያ ናት፤
   • እግዚአብሔር ከሰው ልጆች ጋር ያደረጋቸው ኪዳናት በሙሉ፡ ማለትም ሰባቱም (ኪዳነ አዳም ወሔዋን፣ ኪዳነ ኖኅ፣ ኪዳነ መልከ ፄዴቅ፣ ኪዳነ አብርሃም፣ ኪዳነ ሙሴ፣ ኪዳነ ዳዊት እና ኪዳነ ምሕረት) ተጠብቀው ያሉት፡ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ብቻ ነው፡፡
   • መድኃኒተ ዓለም ክርስቶስ፡ ሥጋውን ቆርሶበት ደሙን አፍስሶበት ዓለምን፡ ከኃጢአት፣ ከዲያብሎስ እና ከሞት ቁራኝነት ያዳነበት፡ ቅዱስ እፀ መስቀል በአሁኑ ሰዓት የሚገኘው፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡
   • በሕገ ልቡና መመራት ለተቸገሩት እስራኤላውያን ዘሥጋ፡ ሁለተኛ ዕድል ሆና ከእግዚአብሔር የተሰጠቻቸው፡ በጊዜው ለአማናዊዎቹ ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስና ለድንግል ማርያም ምሳሌ የነበረችው ታቦተ ጽዮን፡ በአሁኑ ሰዓት ያለችው በኢትዮጵያ ነው፤ ይኸውም የተሰጣቸውን ሁለተኛ ዕድል መጠቀም ካቃታቸው እስራኤላውያን ዘሥጋ ተወስዶ፡ ለኢትዮጵያውያን በአደራ ተሰጥታ ነው፡፡ ላለው ይጨመርለታል እንዳለ መጽሐፍ፡፡
   • በአለም ላይ ያሉ ቅዱሳን፡ ተቀባይነትን የሚያገኙት፡ ገድላቸው የሚነበበው፡ መልክአዎቻቸው የሚነበበው፣አማላጅነታቸው ሥራ እየሰራ ያለው በይበልጥ በኢትዮጵያን ላይ ነው፡፡
   • ለዓለም ሰላምና ደኅንነት ዘወትር ሳታስታጉል የሚትጸልየው ኢትዮጵያ አይደለችም? (የቅዳሴን ጸሎት ያስቡ)
   • ወዘተ….

   ታዲያ ኢትዮጵያዊነት፡ ጊዜና ቦታ ሳይለየው፡ ለዓለም ሁሉ የተሰጠ አይደለም ይላሉ?

   Delete
  4. ይህ ከ ዋናው ጽኁፍ ጋር ምን አገናኘው፡፡

   Delete
 62. ጥያቄዎች አሉኝ
  1. ትክክለኛው መጠሪያ ማህተብ ነው ወይስ ማተብ?
  2. አራት ኪሎ ላይ መጥተዋል የተባሉት ነብያት ከሶስት ዓመት ከስድስት ወር ቦሃላ እንደተነገረው ትንቢት ከሃሳዊ መሲህ ጋር አለመሟገታቸውን፣ ምስክርነት አለመቆማቸውን፣ አለመገደላቸውንና አለማረጋቸውን በደንብ ካረጋገጠ ቦሃላ መጻፉ ዘገየህ ተብሎ ዳንኤልን ያስወቅሳል?
  3. በመጨረሻው ቀን ለፍርድ የምንቀርበው በስራችን የሚያወጣንም የሚያስፈርድብንም ስራችን እንጂ በምናስረው ማተብ ዓይነት ይሆን?

  ReplyDelete
 63. +++ God Help us +++

  ReplyDelete
 64. ዲ/ን ዳንኤል ምላሽህ በጣም አስደስቶኛል፡፡

  ‹‹ በሀገራችን ታሪክ ራእየ ዮሐንስ ይበልጥ የታወቀውና በገልባጮች እጅ በብዛት የተገለበጠው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ በሚሠሩት አብያተ ክርስቲያናትም የሐሳዌ መሲሕ፣ የኤልያስና ኄኖክ፣ የአዲሲቱ ሰማይና ምድር ሥዕሎችም በብዛት ተሳሉ፡፡ ይህንንም መሠረት አድርገው እነ ፍካሬ ኢየሱስ ተጻፉ፡፡ ፍካሬ ኢየሱስ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉትን ትንቢታዊ ቃሎች መሠረት አድርጎ ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር ያዛመደ መጽሐፍ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ላይ ሕዝቡን ከችግር የሚያወጣ፣ የአንድ በሬ እሸት የአንዲት ላም ወተት እንዲያጠግብ የሚያደርግ ‹ቴዎድሮስ› የሚባል ንጉሥ ይነግሣል የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ ሕዝቡም በደረሰው ነገር ላይ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ይህንን ቴዎድሮስ የተባለ ደግ ንጉሥ እንዲጠብቅ አደረገው፡ ››
  የሚላው ግን ፍካሬ ኢየሱስ ትክክለኛ መፅሐፍ አይደለም ወደሚለው ሃሳብ አያመጣም፡፡ ይህንን ደግሞ ሊቃውንተ ቤ/ክ እና አባቶች እንዴት ያዩታል?

  ReplyDelete
 65. minim menifesawi yalihone. ... fitsum haymanotawi ....eyita new. Egziabher yirdanin ena ewinetawin yigletsilin. manew feraj?

  ReplyDelete
 66. fitsum menfesawinet yegodelew ... haymanotawi milash. "manim yekome bimesilew endayiwedik yitenikek". manew feraj?

  ReplyDelete
 67. የስላሴን ልጅነት በምናገኘኝበት ጊዜ የሚታሰርልን ማህተብ ነጭ፣ቀይ እና ጥቁር እንጂ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ አይደለም ቀለሞችም ምሳሌነታቸው ነጭ-የመንፈስ ቅዱስ፣ቀይ-በደሙ የመዋጀታችን ነው ፡፡ማህተብ ማሰር ክርስቲያን ለመሆናችን ምልክት እንጂ ከድህነት ጋር አይያያዝም ፡፡

  ReplyDelete
 68. እግዚኣብሄር ማስተዋሉን ያድለን
  ሰይጣን እየተጠቀመብን ነው

  ReplyDelete
 69. ለዚህ ትልቁ መፍትሔው የእምነት ተቋማት የራሳቸውን ሥራ (ወንጌል ማስተማርን )ትተው በሰዎች ሥራ ውስጥ መግባታቸው ነው፡፡ ስለዚህም ተቋማቱ መጀመርያ ራሳቸውን ወደ ተልዕኳቸው መልሰው፣ በማይጨበጥ ተስፋ የሚዋልለውን ሕዝብም ወደ ትክክለኛ ኑሮና ተስፋ መመለስ አለባቸው፡፡ እዚህ ኤልያስ ነኝ፣ እዚያ ድንግል ማርያም ነኝ፣ እዚያ አቡዬ ነኝ የሚሉ በተነሡ ቁጥር ሕዝቡ ሥራና ትዳር ፈትቶ ተንከራትቶ አይዘልቀውም፡፡

  ReplyDelete
 70. ዲ/ዳኒኣኤል እግዚኣብሄር ጸጋዉን ያብዛልሕ ኣይዞሕ ሁሌኣም ለቤተክርስትያን መቆም ኣለብክ ቀጥልበት።

  ReplyDelete
 71. '' ትምህርቶችም ለሰዎች ቀላል የሆኑ፣ ንባብና ትምህርትን የማይጠይቁ፣ በቀላሉ የሚተገበሩ፣ የሚነኩና የሚዳሰሱ ይሆናሉ''

  ይህ መአት ምሳሌ ሊቀርብለት ይችላል፡፡

  ReplyDelete
 72. Wondem Dani Amelak Tsegawn
  Yabezalehe LEtessasatume Lebona YEsetelgh Ytenbitu Tefetsami Endayhonu Teliyulachewu
  Ante Bretalene

  ReplyDelete
 73. Ewenet aswteway kehonen kezi neger bezu memar yecehalale eqo amelak kehulacehen gar yehun!!!

  ReplyDelete
 74. Selam Dn. Daniel. tiru maregagat new. Minalbat tesfa mekuret silebeza mitseat nafakiwoch bezitew yihon. gin durom endezih tihun weyim ahun ketina alawkim ewunet yekesach timesilegnalech. gin degimo kiristosim besega tegelito beneberebet wekitim yaw neberech. Betam ketikitoch beker yale bedelu kesewut neber. andandochum bizu yaderegelachew.
  Eski Yemitiketelewun sinign lakaflachihu (Sorry my amharic does not work at the moment I am pasting from other source)
  ሕሊና ተርቦ ሆድ ጠግቦ ይስቃል

  ሕሊና ተርቦ እውነትን ሲናፍቅ፣
  ሆድ በእህል ተሞልቶ በደስታ ሲቦርቅ፣
  ወደ እንዱ ስትቀርብ ሌላው ከእሷ ሲርቅ፣
  ሕይወት ተቸገረች ሆኖባት ዝበርቅርቅ፡፡
  የዕለት እውነት ስጠኝ እያለም ቢጸልይ፣
  ጩኸቱ በርክቶ የእለት እንጀራ ባይ፣
  ሕሊና ፀሎቱ ሳይደርስ ከሰማይ፣
  የጉም ሽታ ሆኖ ቀረበት መንገድ ላይ፡፡
  ከስቶና ጠውልጎ ሕሊና እውነት አጥቶ፣
  ሆድ እየወፈረ መብልን አብዝቶ፣
  ለሕይወት ቸገራት ውጥንቅጡ ወጥቶ፣
  መኖርም ተሳናት አንዱን ከአንዱ አስማምቶ
  ዮ. ሠርፀ (J. Sertse) -1994 ዓ.ም

  ReplyDelete
 75. Egziabiher yihunen

  ReplyDelete
 76. "ከኢትዮጵያ ውጭ ያለ ዜጋ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባል ለመሆን የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማና ቀኖና መቀበልን እንጂ አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ባንዲራን መቀበል ግዴታው አይደለም፡፡ በኡጋንዳ ባንዴራ፣ በአሜሪካ ባንዴራ፣ በግብጽ ባንዴራ፣ በሶማልያ ባንዴራ አሸብርቆም ቢሆን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጅ መሆን ይችላል፡፡ እስካሁን ስለ ቀኖና በሚደነግጉት መጽሐፎቻችን ውስጥ ሰንደቅ ዓለማን የተመለከተ ቀኖና የለንም፡፡
  በመሆኑም ሰንደቅ ዓላማችን ከኢትዮጵያዊነታችን ጋር እንጂ ከኦርቶዶክሳዊ እምነታችን ጋር የታሪክ እንጂ የድኅነት ተዛምዶ የለውም፡፡"

  Betam Tikikilegna ena Yemayikad Ewunet new.
  EGZIABIHER Yibarkih Dn. Daniel

  Metalem Amare from Kombolcha, Wollo

  ReplyDelete
 77. tiru melis new minim yemikerew neger yelem kale hiwot yasemalin lenesum libonan yistilin

  ReplyDelete
 78. daniel i think u give a very good explanation but how come ze church remain silent???

  ReplyDelete
 79. Who is Ethiopian leader?
  Give your judgment after you read this article.
  It was April 1, 2005 around 4am Ethiopian police went to Benishangul gumuz and they knocked the door. The time was night so nobody open the door. Them the police brake the door and inter in the room. The police asked them to leave their house and they asked him why? He told them you are Amhara so you have to leave this area as soon as possible. A single mom she has three children, they born in Benishangul and they don't understand a single Amharic word. And the argument continue like this
  Mother is Benishangul is not part of Ethiopia?
  Police Yes it is part of Ethiopia but my boss told me to do this.
  Mother, my children don't speak Amharic
  Police I know but this is my job
  Mother I have three children and my husband passed away two month ago in addition that I am six month pregnant.
  Police he started crying and he left the house.
  After one hour another police came and he asked them why they didn't leave the house and she told him the above situation
  Police I don't care about your problem, if you are Amhara, you have to leave this area.
  Mother She left her house after 27 years and she passed away while she walked in to Gojam.


  ReplyDelete
 80. God bless your ending!!!

  ReplyDelete
 81. Have you seen the recent release by Diakon Mehreteab on the then Artist Jemanesh Solomon and a "Preist" trying to make a new form of religion
  Have you seen the Cross and other images Behind Jemanesh Solomon the Preist and their followers and even printed on their dresses.
  - The cross a Circle on the top is named ANKH and it is one of the Symbols the so called Satanism religion followers use
  -The other Symbol a Hexagon star is also a symbol used by Satanism followers they belive it can make Majic
  for your information you can search the Internet about this symbols
  You can brouse writing "Satanic Symbols"
  Also look at the following links :
  http://www.exposingsatanism.org/signsymbols.htm
  ReplyDelete
 82. በመሆኑም ሰንደቅ ዓላማችን ከኢትዮጵያዊነታችን ጋር እንጂ ከኦርቶዶክሳዊ እምነታችን ጋር የታሪክ እንጂ የድኅነት ተዛምዶ የለውም፡፡
  I think this is right but minalbat abatochachen yhen flag yemertut kemitayut yenoah kelemoch mekakel selehonu lihon yechelal በመሆኑም ሰንደቅ ዓላማችን ከኢትዮጵያዊነታችን ጋር እንጂ ከኦርቶዶክሳዊ እምነታችን ጋር የታሪክ እንጂ የድኅነት ተዛምዶ የለውም፡፡

  ReplyDelete
 83. ante betam jegna sew new ..egziabher lezelalem kante gar yiun

  ReplyDelete
 84. Can anyone please translate this to English, this sect has caused my family alot of problem and I need more information on it. PLEASE help me.

  ReplyDelete
 85. bandirachin tirgum alew. ye ethiopiawian megelecha enj yedihinet melkiya aydelem

  ReplyDelete
 86. ቅዱስ፡ኤልያስን፡ወደዚህ፡ምድር፡የመምጣቱን፡እውነታ፡ማንም፡ሊሰውረው፡የማይችለው፡ነገር፡መሆኑን፡በእርግጠኝነት፡ልንነግራቸው፡እንወዳለን፡፡በእርግጥም፡የቅዱስ፡ኤልያስ፡መምጣት፡ማንም፡ምንም፡ሊጋርደው፡የማይችለው፡እንደ፡ፀሐይ፡የሚያበራ፡እውነታ፡ነው፡፡

  ReplyDelete
 87. ባለፉት ጊዜያት ስለ ነብዩ ኤልያስ መጥቷል በሚል ወሬ ህዝበ ክርስቲያኑ በእምነቱ ግራ መጋባት እንደሌለበት በዲ. ዳንኤል ብሎግ እና በሐመር መጽሄት ለማስገንዘብ ተሞክራል፡፡
  እንደኔ እምነት ይህ ብቻ በቂ አይደለም እላለሁ፡፡ምክንያቱም ህዝበ ክርስቲያኑ አሁንም ግራ እየተጋባ መሆኑን ተመለክቻለሁ፡፡ ዕለቱ ግንቦት 18/2005 ዓ.ም ቦታው ቃሊቲ ገብርኤል ከቅዳሴ በኋላ ህዝበ ክርስቲያኑ ወደ ቤቱ እንዲሄድ ከተደረገ በኋላ ከቅጽር ውጭ ከታች በኩል በአንድ ቦታ ብዙ ሰው ተሰብስቦ አየሁ፡፡ምንድነው ብዬ ስጠጋ ከወገቡ በላይ ራቅቱን ሰንሰለትና መቁጠሪያ ብጤ አሰሮ እንክርዳዱን የሚዘራ አንድ ሰው አየሁ፡፡የሚያነሳቸው ጉዳዮች ከላይ በጠቀስኳቸው ሚደያዎች ያስነበቡንን ነው፡፡ እኔ ለማሳሰብ የምፈልገው ግን ብዙው ህዝብ ለኢንተርኔትና ለመጽሄት…ወዘተ ቀርቶ ለቤተክርስቲያን እንኳን ቅርብ አይደለም፡፡ ከተመለከትሁት አንጻርም ህዝበ ክርስቲያኑ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የተነሱ ተረፈ አይሁዳዊነት መሆናቸውን አልተገነዘበም የሚል እምነት አለኝ፡፡ እኔ ወዲያውኑ ወደ ቤቴ ብሄድም ቆይቼ ስመለከት አሁንም ብዙ ሰው ነበር፡፡ ታዲያ ሰይጣንና ወዶ ዘማቾቹ ይህን ያህል ጊዜ ምእመኑን እንዲያገኙት ከፈቀድንላቸው ግራ ማጋባት አይከብዳቸውም፡፡የሚያነስትና ለማደናገሪያ የመረጡት ሃሳብም አዳማጭ እንዲያገኙ አድርጓቿል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ለመሆኑ የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደራዊ ችግሮች አለመሻሻል እስከ መቼ ድረስ ለሰነፎች ምክንያት ሲሆኑ ሊኖር ነው;
  ሰለዚህ ቤተክርስቲያናችን ምእመኗን ከመወሰድ የምተከላከልበትን የማስተማሪያ መርሀ- ግብር አዘጋጅታ ግንዛቤ ማስጨበጥ ይገባታል እላለሁ፡፡
  እግዚአብሄር ቤተክርስቲያናችንን ይጥብቅልን አሜን፡፡

  ReplyDelete
 88. kale hiwot yasemah

  ReplyDelete
 89. ድሮ ልጅ ሆኜ የሰማሁት ትዝ አለኝ። የእየሱስ ክርስቶስ ታናሽ ወንድም ነኝ ብሎ አንዱ መጥቶ ነበር አሉ። ሰዎች ግን አልተቀበሉትም። ስለዚህ ሌባ ሌባ ብለው ሲደበድቡት የሰጣቸው መልስ የሚያስገርም ነው። "ይሁን እሺ ወንድም ጋሼንም እንዲህ ነበር ያደረጋችሁት" አለ ይባላል።
  ሁሌ በተጠንቀቅ መቆየት አለብን። ዲያቢሎስ አይተኛምና።

  ReplyDelete
 90. ...የእምነት ተቋማት የራሳቸውን ሥራ (ወንጌል ማስተማርን )ትተው በሰዎች ሥራ ውስጥ መግባታቸው ነው፡፡ ስለዚህም ተቋማቱ መጀመርያ ራሳቸውን ወደ ተልዕኳቸው መልሰው፣ በማይጨበጥ ተስፋ የሚዋልለውን ሕዝብም ወደ ትክክለኛ ኑሮና ተስፋ መመለስ አለባቸው፡፡ እዚህ ኤልያስ ነኝ፣ እዚያ ድንግል ማርያም ነኝ፣ እዚያ አቡዬ ነኝ የሚሉ በተነሡ ቁጥር ሕዝቡ ሥራና ትዳር ፈትቶ ተንከራትቶ አይዘልቀውም፡፡

  Joro yalew yesema !!

  ReplyDelete
 91. I have no words to express your intellectual ability how you discuss some issue and how much you express it in detail. You are really our hero and role model. I wish you long live. God bless you. ከተመኙ አይቀር እንደ አንተ መሆንን መመኘት ነው፡፡ ማን ያውቃል እንደ አንተ ሳንደክምና ሳንሰለች ከሰራን ነገ እንደ አንተ እንሆን ይሆናል፡፡

  ReplyDelete
 92. እኔ እምለው // ከሁለተኛው መክዘ ጀምሮ የተነሡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ሁለት ምስክሮች ኄኖክና ኤልያስ መሆናቸውን ተርጉመዋል// የሚለውን ሳነበው ገርሞኛል ለምን መሰላችሁ ከፍቺው በፊት ስለ ኤሊያስና መጥምቁ ዮሃንስ የተጠቀሰው ትክክልና መጽሃፍ ቅዱሳዊ ነው ግን ሊቃውንት እኮ ሊተረጉሙት የሚገባውና የሚችሉት መጽሃፍ ቅዱስንና መጽሃፍ ቅዱስን ብቻ ተንተርሰው ነው መሆን ያለበት ያለ በለዚያ እኛ ሳንሆን እግ/ር ተናግሮናል ከሚሉት በምን እነለያለን? ለማንኛውም ማመን ያለብን የተገለፀውን እንጂ በግምትና በሎጅክ ከሆነ ተሳስተን እንዳናሳስት እንጠንቀቅ ሳይጣን ሙሉ ውሸት ነግሮን ሳይሆን ልክ ትንሽ
  መርዝ ብዙ ምግብ ውስጥ ገብታ እንደምትገድል ውሸትም እንዲሁ ነው. ሌላው መርዝ አውቀነው ጠጣነውም ሳናውቀው ጠጣነው መግደሉን አይተውምና ወገኔ ጠንቀቅ እንበል በመጨረሻም ዳኒ በጣም ደስ ብሎኛል ግን ስትፅፍ አሁንም መፅሃፍ ቅዱስን እንጂ አባቶችንና ታሪክን አታስበልጥ መጽሃፉ በራሱ ሊቆም ይችላልና

  ReplyDelete
 93. በመጀመሪያ ዳንኤል ፈጣሪ አምላክ እድሜና ጤና ይስጥህ የፃፍከው ነገር ተመችቶኛል፡፡ ነገር ግን አንድ ጥያቄ አለኝ በባንዲራ ጉዳይ የጻፍከው ትንሽ አወዛግቦኛል የማርያም መቀነት እያሉ ሲነግሩን ሰማይ ላይ የምናየው አረንጎዴ፣ቢጫ፣ቀዩስ ማለት ትንሽ ብታብራራልኝ ብተረፈ ያገልግሎት እድሜህን እግዚአብሄር ይባርክልህ እኛንም በሃይማኖቻችን የፅናን አሜን!!!

  ReplyDelete
 94. ለድም ዳኒ እውነት ለአንተ ምድነው ?

  ReplyDelete