click here for pdf
‹‹አንድ ቀን ነው፤ ባለቤቴ ከበረራ የምትመለሰው ሌሊት ስለሆነ በግማሽ ልቤ ተኝቼ
ስልኳን እጠብቅ ነበር፡፡ እኩለ ሌሊት ላይ ስልኬ ጮኸ፡፡ እኔም ቁጥሩን ሳላይ እንዴው በዳበሳ ስልኩን አነሣሁት፡፡ ‹ሃሎ አያ
ግርማ› አለኝ የደወለው ሰው፡፡ ‹ተሳስተዋል ጌታዬ፤ ይህ የአያ ግርማ ስልክ አይደለም› ስል መለስኩለት፡፡ ‹ኧረ እባክዎን
ፈልጌያቸው ነው› አለኝ፡፡ እኔም መሳሳቱን ደግሜ አስረዳሁትና ስልኩን ዘጋሁት፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በምሽት እየደወለ ‹አያ
ግርማ የሉም› የሚለኝ ሰውዬ ሊያቆም አልቻለም፡፡ እየቆየሁ የስልክ ቁጥሩን ሳውቀው ማንሣት አቆምኩ፡፡ ነገር ግን ልጆቼ ወይም
ባለቤቴ ስልኩን ሲያነሡት አሁንም ‹አያ ግርማ የሉም› ይለኛል ያ ሰው፡፡ ደጋግሜ መሳሳቱን ነግሬዋለሁ፡፡ ግን የሚሰማ አልሆነም፡፡
እንዲያውም ጓደኞቼ መቀለጃ አድርገውት ሲያገኙኝ ‹አያ ግርማ› ይሉኝ ነበር፡፡
አንዳንዴ ቀን፣ ብዙ ጊዜ ግን ሌሊት ይደውላል፡፡ አላነሣ ስለው በሌላ ስልክ ቀይሮ
መደወልም ጀምሮ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ባለቤቴ ከበረራ የምትመለሰው ሌሊት ስለሆነ ስልኬን አልዘጋውም፡፡ ሰውዬው አሰለቸኝ፡፡
አንድ ሌሊት በሰባት ሰዓት አካባቢ በሌላ ስልክ ደወለና እንደለመደው ‹አያ ግርማ የሉም› ሲለኝ ድምፄን አስተዛዝኜ ‹አያ
ግርማኮ ዐረፉ› አልኩት፡፡ ጩኸቱን ለቀቀው፡፡ ቤቱን ሲያደባልቀው ይታወቀኛል፡፡ ከዚያ አንዲት ሴትዮ ስልኩን ተቀበሉና ‹መቼ
ዐረፉ› አሉኝ ‹ትናንት ዐረፉ› አልኩ በተሰበረ ድምጽ፡፡ እርሳቸውም ‹በሉ አይዟችሁ እግዚአብሔር ያጽናችሁ› ብለው ዘጉት፡፡
ከዚያ በኋላ ዐረፍኩ፡›› ብሎ ያጫወተኝ አንድ ወዳጄ ነው፡፡