Tuesday, February 5, 2013

አቡነ ፊልጶስን ፍለጋ (ክፍል ሁለት)


አባ ፊልጶስ በመጀመርያው ስደቱ የተሻገረው የበሽሎ በረሃ
click here for pdf
እስኪ እርሱ ይርዳንና ታላቁን ሰው አባ ፊልጶስን መፈለጋችንን እንቀጥል፡፡ ‹ኅሡ ወአስተብቁዑ - ፈልጉ፣ ለምኑም› እንዲል መጽሐፈ ቅዳሴ፡፡
ገድሉ የሚሰጠን ስሞች በሀገሪቱ ውስጥ በተፈጠሩ የሕዝቦች ፍልሰትና ጦርነቶች ምክንያት ተቀያይረዋል፡፡ አንዳንዶቹም ቢሆኑ ትናንት ታላላቅ ግዛቶች የነበሩት ዛሬ የአንድ መንደር ወይም ጎጥ መጠርያ ሆነዋል፡፡ እነዚህን መንደሮችና ጎጦች ደግሞ በካርታ ላይ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ የመጀመርያው ፍለጋ የተካሄደው በመካከለኛው ዘመንና ከመካከለኛውም ዘመን በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ወይም ስለ ሀገሪቱ መረጃ ሰብስበው ካርታ ያዘጋጁ ሰዎችን መዛግብት ማገላበጥ ነበር፡፡ ጌርጌስና ሐቃሊትን በካርታቸው ላይ ለማግኘት አልተቻለም፡፡ 

ካርታዎቹን በመፈለግ ላይ እያለን አንድ ባለሞያ እንዲህ ጠቆመን፡፡ ‹‹አባ ፊልጶስ በመጨረሻ ወደ አቡነ ሰላማ ነው የሄደው፡፡ እርሳቸውንም ያገኛቸው ጌርጌስ በተባለው ቦታ ነው፡፡ ስለዚህም ከሀገራዊ ምንጮች ለምን የጳጳሳትን የጥንት መናብርት በተመለከተ መረጃ አንፈልግም?›› እውነትም ይህ አንድ መንገድ ነው ብዬ ተቀበልኩት፡፡ በመካከለኛው ዘመን ከነበሩ ጳጳሳት መካከል አራቱ በሚገባ ይታወቃሉ፡፡ አቡነ ጌርሎስ፣ አቡነ ያዕቆብ፣ አቡነ ሰላማና አቡነ በርተሎሜዎስ፡፡ አቡነ ጌርሎስ በ12ኛው መክዘ የነበሩና ለብዙዎቹ አባቶች ክህነት የሰጡ ግብጻዊ ጳጳስ ናቸው፡፡ እነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ እነ አቡነ ዜና ማርቆስና ሌሎቹም ክህነት የተቀበሉት ከእርሳቸው ነው፡፡ የእርሳቸውን መቀመጫ መዛግብቶቻችን በአምሐራና በላስታ ሀገር መሆኑን ነው የሚገልጡት፡፡
በዋድላ ፍለጋ ወቅት
ላስታ ላሊበላ ያለበት አካባቢ ነው፡፡ ብዙ አባቶችም መንበራቸው በዚያ ነበረ፡፡ በአካባቢው ግን ጌርጌስና ሐቃሊት የሚባሉ ሥፍራዎች የሉም፡፡ በጥንቱ የቦታዎች ስያሜ አምሐራ የሚባለው ከሐይቅ በስተደቡብ ከወለቃም ወንዝ በስተ ሰሜን ያለው የዛሬውን አምሐራ ሳይንት፣ መርሐ ቤቴና ቦረና የያዘ አካባቢ ነው፡፡ እዚህ አካባቢ በተደረገው ፍተሻ ጌርጌስ ወይም ሐቃሊት የሚባል ያለበለዚያም ደግሞ ከእርሱ ጋር የሚመሳሰል ስም ሊገኝ አልቻለም፡፡ በርግጥ በሀገረ ሰላም የአቡነ ፊልጶስ ቤተ ክርስቲያን ይገኛል፡፡ ነገር ግን የአካባቢው ትውፊት በዚያ አካባቢ ማስተማሩን እንጂ ማረፉን አይነግረንም፡፡
በገድለ አቡነ ፊልጶስ ላይ እንደ ተገለጠውም ወደ ሀገረ ጌርጌስና ሐቃሊት ከመሄዱ በፊት አቡነ ፊልጶስ በወለቃ ነበረ፡፡ ወለቃ ማለትም የዛሬው ደቡብ ወሎ ቦረና አካባቢ ማለት ነው፡፡ አካባቢው አሁንም ይህንን ስም ይጠቀምበታል፡፡ በተለይም ወንዙ አሁንም የወለቃ ወንዝ እየተባለ ነው የሚጠራው፡፡ ከአቡነ ጌርሎስ ቀጥሎ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ቦታ የነበረው አቡነ ያዕቆብ(1330-37 ዓም) ነው፡፡ አሥራ ሁለቱን ንቡራነ ዕድ ሾሞ በመላዋ ኢትዮጵያ ያሠማራ አባት ነው አቡነ ያዕቆብ፡፡ ስለ እርሱ ያገኘናቸው መረጃዎች መንበረ ጵጵስናውን አይነግሩንም፡፡ እንዲያውም አቡነ ሰላማ መተርጉምንና አቡነ በርተሎሜዎስን በተመለከተ የተጻፉት መዛግብት ሁለት መንበረ ጵጵስና እንደነበራቸውና አንዱ በጥንቱ አንጎት በዛሬው የጁ ውስጥ ሲሆን ሁለተኛው ጌርጌስ መሆኑን ይገልጣሉ፡፡
መንደር ለመንደር ፍለጋ
አንድ ጠቃሚ ነገር አገኘን ማለት ነው፡፡ ጌርጌስ የጳጳሳት ማረፊያ የነበረች ቦታ ናት ማለት ነው፡፡ ሐቃሊትም የጌርጌስ ጎረቤት መሆን አለባት፡፡ ምክንያቱም አቡነ ፊልጶስ ወደ ጌርጌስ ሄዶ አቡነ ሰላማ መተርጉምን አግኝቷቸዋል፡፡ ያን ጊዜ ታምሞ ደከመ፡፡ እርሳቸውም ወደ ሐቃሊት ለመሄድ በዝግጅት ላይ ነበሩ፡፡ እርሱም አብሮ መሄድ እንደሚፈልግ ነገራቸው፡፡ እርሳቸውም በአልጋ አሸክመው ወደ ሐቃሊት ወሰዱት፡፡ ይህ ሁሉ ነገር ሐቃሊትና ጌርጌስ የተቀራረቡ መሆናቸውን ያሳየናል፡፡
አቡነ ሰላማ መተርጉም(1341-81 ዓም) በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሁለት ነገር ይታወሳሉ፡፡ የመጀመርያው ከዐረብኛ ወደ ግእዝ እንዲተረጎሙ ባደረጓቸው አያሌ መጻሕፍት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከእርሳቸው መምጣት በፊት በአባቶችና በነገሥታት መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ችግር በዕርቅ ለመፍታት ያደረጉት ጥረት ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ሊቃውንት ስማቸው ‹ሰላማ› የተባለው  ዘመናቸው የሰላም ስለነበረ ነው ይላሉ፡፡
አቡነ ሰላማ መንበራቸው ያደረጉት ጌርጌስ፣ በኋላም አቡነ ፊልጶስን ይዘው የተጓዙባት ሐቃሊት ለእርሳቸው የትርጉም ሥራ የሚረዱ ሊቃውንት ይገኙባት የነበረች፣ ጥንት አምሐራ ለሚባለውም ሀገር ቅርብ የሆነች ወይም በውስጡ ያለች መሆን አለባት የሚል ግምት ተወሰደ፡፡ መረጃውንም ለማሰባሰብ ስለዘመኑ የተጻፉ ሌሎች ገድሎችንና ዜና መዋዕሎችንም መፈተሽ ጀመርኩ፡፡ በዚህ መካከል በዘመነ መሳፍንት በማኅደረ ማርያም በግዞት እያሉ በግራኝ የጠፋውን ታሪካችንን ከየገዳማቱና ዋሻዎቹ እያሰባሰቡ ያስጻፉትን የደጃዝማች ኃይሉ እሼቴን የነገሥታት ዜና መዋዕል አገኘሁ፡፡
ደጃዝማች ኃይሉ እሼቴ በዚህ የታሪክ መጽሐፋቸው ላይ በዓምደ ጽዮንና በሠይፈ አርዕድ ዘመን የተደረገውን የአባቶች ስደት በአንድ አንቀጽ ጠቅሰውት አልፈዋል፡፡ ዘመኑንም ‹‹የደብረ ሊባኖሳውያን ስደት›› እንደሚባል ነግረውናል፡፡ በዚሁ መረጃቸውም ላይ ‹‹የደብረ ሊባኖስ መነኮሳት ከአንቆ እስከ ግሼና ተሰደዱ›› ይላሉ፡፡ እዚህ ላይ ሁለት የቦታ ስሞችን ነው የሚያነሡት፡፡ ‹‹አንቆ›› እና ‹‹ግሼና›› አንቆን በተመለከተ ምሁራኑ ሁሉ ለመለየት ተቸግረዋል፡፡ ‹‹ግሼና››ን በተመለከተ ግን ሁለት ዓይነት አስተያየት ነበር በግርጌ ማስተዋሻዎቻቸው የሚሰጡት፡፡
የመጀመርያው ጥንት ገዳምም የነገሥታት ልጆች ወኅኒ ቤትም የነበረውን ግሼን ተራራን ነው፡፡ እውነትም ስሙ ‹‹ግሼና›› ከሚለው ጋር ተቀራራቢ በመሆኑ ሊያስብል ይችላል፡፡ ነገር ግን በግሼን ማርያም ላይ በምናገኛቸው መዛግብትም ሆነ ትውፊቶች ይህንን የሚደግፉ መረጃዎች የሉም፡፡ ‹ግሼን› የሚለው ስም ቢገኝም ጌርጌስን ግን ማግኘት አልተቻለም፡፡ በመንደርም ሆነ በጎጥ፣ በወንዝ ስምም ሆነ በተራራ ስም ላይ አይጠቀሙበትም፡፡ ሽማግሌዎችም ጥንት እንደዚህ ያለ ቦታ ስለመኖሩ የሚነግሩን ነገር የለም፡፡
ጋሼና
ሁለተኛው የምሁራኑ ግምት ከላሊበላ 50 ኪሎ ሜትር፣ ከዋላ ዋና ከተማ ከኮን 12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውና ‹‹ጋሼና›› የሚባለው አካባቢ ነው፡፡ በቦታው ላይ በተደረገው ጥናት በአካባቢው ከሚገኙት የገጠር አብያተ ክርስቲያናት በቀር ጥንት ከደብረ ሊባኖሳውያን ጋር የሚያያዝ ገዳምም ሆነ ቦታ አልተገኘም፡፡ ጌርጌስ የሚባል ስምም የለም፡፡ ለጳጳሳት ማረፊያነት ሊውል የሚችል ደብርም በአካባቢው ጥንት እንደነበረ ምልክት አይሰጥም፡፡
ቀጣዩ የጥናት መንገዳችን የነበረው ከጥንቱ ወለቃ ጀምሮ አባቶችና ነጋዴዎች ይጓዙባቸው የነበሩትን የሲራራ ነጋዴዎች መንገዶችን መከተል ነበር፡፡ በዚህም ሁለት መንገዶችን አይተናል፡፡ የመጀመርያው ከጥንቱ ሸዋ ይነሣና  በወለቃ በኩል ወደ አንጎት፣ ከዚያም በአፋር በኩል አድርጎ ወደ ትግራይ የሚሄደው ጎዳና ነው፡፡ አባ ፊልጶስ በመጀመርያው ስደቱ በዘመነ ዓምደ ጽዮን ወደ ትግራይ ሲሰደድ ይህንን መንገድ ነበር የተከተለው፡፡ በዚህ መሥመር ቢጓዝ ኖሮ በወሎና በትግራይ መረጃዎችን እናገኝ ስለነበር ትተነዋል፡፡
ሁለተኛው መሥመር ከጥንቱ አምሐራ ወደ ሸዋ ከተጓዘ በኋላ በመርሐ ቤቴ በኩል ተገንጥሎ ወደ ደቡብ ጎንደር ይጓዝ የነበረው ወደ ስናር የሚያልፈው የሲራራ ነጋዴዎች መሥመር ነው፡፡ ይህንን መሥመር ተከትለን እስኪ ፍለጋችንን እናከናውን፡፡ ጣራ ገዳም ደቡብ ወሎ በሚገኘው የአቡነ እንድርያስ ገድል ላይ አቡነ እንድርያስ ከደብረ ሊባኖስ ወደ ጎንደር የመጡት በመርሐ ቤቴ በኩል መሆኑን፣ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም በሁለተኛው የኢየሩሳሌም ጉዟቸው ከላስታ ወደ ደቡብ ጎንደር ተከዜን ተሻግረው መምጣታቸውን፤ ከዚያም ወደ ጥንቱ ሸዋ ግዛት በመርሐ ቤቴ በኩል አልፈው መሄዳቸውን ይገልጥልናል፡፡ በገድለ አቡነ መርሐ ክርስቶስ ላይም አቡነ መርሐ ክርስቶስ ከደብረ ሊባኖስ ተነሥቶ በመርሐ ቤቴ በኩል ምስካበ ቅዱሳንን አልፎ ወደ አትሮንሰ ማርያም መምጣቱን ይገልጥልናል፡፡ ከአትሮንሰ ማርያም ወደ ወለቃ ነው ቀጣዩ መንገድ፡፡ 
መርጡለ ማርያም እቴጌ ዕሌኒ ያሠራችው ቤተ ክርስቲያን ፍራሽ
ይኼ መንገድ ዓባይና በሽሎ በሚገናኙበት በኩል አቋርጦ ዦጋ በምትባለው ተራራ በኩል የሚያልፍ ነው፡፡ ከአምሐራ ሳይንት አጅባር የሚነሣው መንገድ፣ ከምሥራቅ ጎጃም መርጡለ ማርያም የሚመጣው ጎዳናና ከስማዳ ደቡብ ጎንደር ከሚመጣው መንገድ ጋር ዦጋ ላይ ይገናኛሉ፡፡ እነ ንጉሥ በዕደ ማርያም፣ እነ ንጉሥ እስክንድርና ንጉሥ ልብ ድንግል ወደ ጎጃም የተሻገሩት በዚህ መንገድ በኩል ነበር፡፡ ዛሬም ቢሆን ጎንደርና ሸዋ በዚሁ መንገድ በእግር ይገናኛል፡፡ ደጃዝማች ኃይሉ እሼቴ ታሪክ ያሰባሰቡባት ማኅደረ ማርያም የምትገኘው በዚሁ በደቡብ ጎንደር ነው፡፡ ምናልባትም ጌርጌስና ሐቃሊትም በዚህ አካባቢ ሊገኙ ይችላሉ የሚለው ግምት ተጠናከረ፡፡
ይህ በዚህ ላይ እንዳለም የቅድስት ወለተ ጴጥሮስን ገድል ሳነብብ እምነ ወለተ ጴጥሮስ አንቆ በተባለ ቦታ መመንኮሷንና ገዳማዊ ሕይወትም የጀመረችው እዚያው መሆንዋን የሚያመለክተውን አገኘሁ፡፡ ይህም አንቆ በደቡብ ጎንደር አካባቢ ልትገኝ እንደምትችል ፍንጩን አጠናከረልኝ፡፡ የሚቀረው ወደ አካባቢው መጓዝና መንደር ለመንደር፣ ተራራ ለተራራ ቦታውን እያጣሩ መፈለግ ነው፡፡ እዚያም ካልተገኘ ደግሞ ፈጣሪ ያውቃል፡፡
እነሆ ኅዳር 24 ቀን 2005 ዓም እኔ፣ ድንበሩ ሰጠ(መኪናውን እያገላበጠ)፣ ኤልያስ ደፋልኝ በምሕንድስና ሞያው ሊሠራ)ና ቀለመወርቅ ሚደቅሳ (በሕግ ዓይን ሊያይ) ወደ ደቡብ ጎንደር ጉዞ ጀመርን፡፡ መንገድ ላይ ደግሞ ሀገሩን የሚያውቀው የጎንደሩ ሙሉቀን ይጠብቀናል፡፡ መልካም ጎዳና ይሁንልን፡፡

39 comments:

 1. Ye Abun Filipos AMILAK Yeradah Dani Qale Hiwoten Yasemalin Ye Ageligelot Zemenihen Yarzimlin

  ReplyDelete
 2. ደ/ን ዳንኤል
  በጣም እናመሰግናለን በእርግጥ እየሰራችሁት ያለው ሰውም ቤተክርስቲያንም ታሪክም እግዚአብሔርም የሚወደውን ነውና መድኃኔዓለም ብርታቱን ድንግል አማላጅነቷና ረድኤቷ አይለያችሁ፡፡

  ReplyDelete
 3. ደ/ን ዳንኤል
  በጣም እናመሰግናለን በእርግጥ እየሰራችሁት ያለው ሰውም ቤተክርስቲያንም ታሪክም እግዚአብሔርም የሚወደውን ነውና መድኃኔዓለም ብርታቱን ድንግል አማላጅነቷና ረድኤቷ አይለያችሁ፡፡

  ReplyDelete
 4. Wow! What happen 2 u!?

  ReplyDelete
 5. wow , God bless you all
  good work

  ReplyDelete
 6. good Job Tebareku!

  ReplyDelete
 7. እዚያም ካልተገኘ ደግሞ ፈጣሪ ያውቃል፡፡

  ReplyDelete
 8. Why do I yearn for foreign documentaries? yours is the best! and blessful!

  GOD of Israel be with you.

  ReplyDelete
 9. የድንግል ልጅ ይከተላችሁ፣ በርቱ።

  ReplyDelete
 10. ዲ ዳንኤል እያደረግህ ያለዉን ነገር ሁሉ አደንቃለሁ ነገር ግን የመርጡለማርያ ግንብን በተመለከተ በፎቶግራፉ ግርጌ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የጻፍከዉን መግለጫ በተመለከተ በአካባቢዉ ምሁራን ከሚነገረዉና በ 333 አም እንደተሰራ ከሚገልጸዉ የሊቀ ማእምራን ፋንታሁን አለሙ ጽሁፍ ጋር በእጅጉ የሚጻረር በመሆኑ ከቻልክ እርምት እንድታደርግበት ካልሆነም ማብራሪያ እንድትሰጥበት በእግዚአብሄር ስም እጠይቅሀለሁ እግዚአብሄር ስራህንና ቤተሰብህን ይባርክ

  ReplyDelete
  Replies
  1. You are incorrect. Dn. Daniel is also wrong. That wall is part of a building commissioned by Atse Susenyos. The church built by Eleni was destroyed by Gragn and later by Borena tribes.

   Delete
  2. are you sure? Borena tribes? give me a historical evidence that tells it is destroyed by Borena tribes-i might accept the case of Grange's devastation on Bet Amhara particularly and the larger north Ethiopia in general-but i do not think Borena tribes destroyed for the Boran tribe expansion is in Kenya than Ethiopia.

   Delete
 11. Please, D/n, Daniel, you are making us very Egor, why not you finish it now? i can not wait a week. Please post it as soon as possible!! Ma god, really amusing and interesting!! May god be with you!!

  ReplyDelete
 12. (……አንዱ በጥንቱ አንጎት በዛሬው የጁ ውስጥ ሲሆን ሁለተኛው ጌርጌስ መሆኑን ይገልጣሉ፡፡) ምናልባትም እንዲህ ያሉ ስሞች አሁንም በአካባቢው የግለሰብ መጠሪያ ሆነው ያገለግላሉና የግለሰቦቹን ዘርማንዘር ለጥናትህ ግብኣት ብታደርጋቸው ምን ይመስልሃል

  ReplyDelete
 13. ማን ያውቃል ቦታው ተገኝቶ አንድ ቀን እኛም እናየው ይሆናል ለእናንተም ያስጀመረን የሚያስጨርስ አምላክ የትክክለኛውን ቦታ ይግለጥላችሁበአይነ ህሌናም አብናችሁ እንድንጓዝ ስላደረጋችሁ ዋጋችሁ በሰማይ ከፍ ያለ ያድርገው አሜን

  ReplyDelete
 14. መልካም መንገድ።ማስተዋልን ይስጥህ።አይዞህ ቀጥል፤የሚከተልህን እሱ ያዘጋጃል።

  ReplyDelete
 15. እግዚአብሄር ድካማችሁን ይቁጠር::
  Mamush,MN

  ReplyDelete
 16. D/N Daniel lemtsfachew menfesawi tsihufoch hulu betam kelib eyamesegenkugn sale, gin and neger tiz alegn esum Waldbban betemeleket new ye Waldbba Menekosat ketesekayeu ametat askotirewal enesum Betminas nachew mekerana sikay sidersbachew min ale silenesu yalehen maletim Egziabhier Amlak yesetehin menfesawi sira bititsf des balen neber.mekniyatum kegedamu eyewetu new hulachihum ye Orthodox menfesawi sebakiwech bemulu.new wyes lik endezihu ende Abune Filpos mejemrya yebetenu ena endegena filega yeshalal bilachihu new.Egziabhier Amlak band endisebesben yerdan Amen.

  ReplyDelete
 17. Hi Dani,

  If I am not mistake in Sodo Guragegna and the Coptic Christians call St. George, as Gergis and Girgis respectively. The pronunciation of the place you are looking for it sounds the same with those once. Who knows the name you are looking for they may used for St George's Church area...

  ReplyDelete
 18. Great Job!Deacon Daniel.
  Holy of holiness God bless you and Your family. who never know may be this is the time for us going to the holy place on a pilgrimage and appreciate our fathers' endurance for our significance church.
  (Dani, keayin yawutah eskemchereshaw yasnah!!!)

  ReplyDelete
 19. here is the great discovery of these nation and you so GOD finish it

  ReplyDelete
 20. D/n Daniel thank u very much. It is very interesting history. God bless u. other question in south Gonder area like other father history please write.

  ReplyDelete
 21. እግዚአብሔር ይርዳችሁ
  ___________________________________________
  (በነገራችን ላይ ኤልያስን አውቀዋለሁ (ደ/ዘይት ቅ/ሩፋኤል ሰ/ትቤት))

  ዐቢይ አሰፋ

  ReplyDelete
 22. angot yemibalew gezat ke hayqe seminawi eseke alamata hara wenze derese endehone be qereb yeweta ye raya hizb tarik yemil anbibalehu..minalbat girgisa betentu ye angot gizat akale behonew ye ahunu weregesa yehon endi....yehinem bitayew teru new....

  ReplyDelete
 23. Hi Dani,
  I really appreciate your work.Keep it up.

  ReplyDelete
 24. Gishena is at Amhara saint now.

  Dn Daniel betam melkam ena model sira new yih filega. Bagatim ene Amhara saint woreda new tewoldje yadeghut enam zare woredaw lehulet tekfilual maletem saint (Adjibar) ena mehal saint (densa)teblo. bezih meseret gishena yetebale bot (zare yemender ena yewuha minch suyame)mehal saint densa worda, ahiyo kebele (039 kebele)hana geregera sefer(got)Ene yetewoldi sefer new.

  oral teaching about the place
  some people currently live here in Gishena were come from Begemidir, south Gonder area and are purly christian and royal family and still believe that there were some tribs immigrated named local reas like Gishena, Solebat, Girdamdo, etc all are now in Densa woreda aheyo kebele around abay river.
  i will search more info from elder and communicate with you (if you need getachewchane@gmail.com) dani since i am working at jimma university now.
  thank you really.

  ReplyDelete
 25. Dear my friends, i am very proud of you!! My God bless you and your families!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!

  ReplyDelete
 26. EM BERHAN KANTEGAR NECH MENGEDU EYEMERACH TADERSEHALECH....

  ReplyDelete
 27. Hi dani, Ethiopiawiwe jandereba hawaryawe philipose yatemekew semu mane yibalale? pls tell me

  ReplyDelete
  Replies
  1. ye Ethiopiawiwe jandereba ስም ባኮስ ነው፡፡ I call my son Bakos!

   Delete
 28. betam tiru new ktilbet

  ReplyDelete
 29. የርእሰ ርኡሰን መርጡለ ማርያም ገዳምMarch 4, 2013 at 2:45 PM

  የርእሰ ርኡሰን መርጡለ ማርያም ገዳም እንደ ጥንታዊነቷ እና እንደ ታሪካዊነቷ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ታሪኳን ማሳወቅ ቅርሶቿን ጠብቆ ለተተኪው ትውልድ ማሳወቅ እና ማስረከብ ከዚህ ትውልድ የሚጠበቅ ነው ፡፡ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት የስነ ቤተ ክርስቲያን ተመራማሪ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ታሪክ ማንነት ትውፊት ለማሳወቅ የምታደርገው ጥረት በጣም ትልቅ እርምጃ ነው ይበል የሚያሰኝ ነው ፡፡ ነገር ግን በግል መካነ ድርህ ላይ አቡነ ፊልጶስን ፍለጋ (ክፍል ሁለት) በሚለው የጉዞ ዘገባ ለይ ባስቀመጥከው ፎቶ ስር መርጡለ ማርያም እቴጌ ዕሌኒ ያሠራችው ቤተ ክርስቲያን ፍራሽ በማለት የገለጥከው አብርሐ ወ አጽብሐ ያሰሩት በሚለው ይስተካከል ፡፡ ምክንያቱም አብርሐ ወ አጽብሐ ያሰሩት ቤተ ክርስቲን በዮዲት ጉዲት ከፈረሰ በኋላ ከፍርስራሹ አጠገብ በስተምሥራቅ በኩል ሌላ ቤተ ክርስቲያን በሳር ክዳን በ፰፻፹፪ ዓ.ም የነገሰው አንበሳ ውድም አሰርቷል ፡፡ ይህንን ቤተ ክርስቲያንን ከነሐሴ ፳፮ ፲፬፻፷ ዓ.ም - ኅዳር ፲ ፲፬፻፸ ዓ.ም የነገሠው ንጉሥ ዐፄ በእደ ማርያም በ፲፬፻፷ ዓ.ም አሳድሶታል ፡፡ ባለቤቱ ንግሥት እሌኒ ደግሞ የአንባውን ዙሪያ አሰርታለች አሁንም የገዳሟ ዙሪያ የእሌኒ ውድሞ ይባላል ፡፡ አገልግሎትህን እግዚአብሔር ይባርክልህ !!!

  ReplyDelete
 30. ሩፊኖስ ከምድር ጫፍMarch 6, 2013 at 12:50 PM

  ማስተካክያ ይደረግበት !!! ውድ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት አቡነ ፊልዾስን ፍለጋ ክፍል-፪ ላይ የርእሰ ርኡሳን መርጡለ ማርያምን ታሪክ ስትፅፍ እንዲሁም ባወጣኸው ፎት ስር በንግሥት እሌኒ እንደተሰራች የገለፅከው በጣም ስህተት ነው ::: በአብርሐ ወ አጽብሐ የተሰራችው በሚል ይስተካከል :: ይህ ጉዳይ በገዳሟ ላይ የበረደውን ንትርክ ድጋሚ የሚያስነሳ በመሆኑ በአስቸኳይ ይስተካከል !!!

  ReplyDelete
 31. ውድ ዳንኤል በፍለጋህ ዦጋ(ሾጋ) ጋሼና ብለህ የተቀስካቸው ቦታወች ደላንታ እና ዋድላ አካባቢ ያሉ በመሆናቸው ብዙ ታሪካዊ ቦታወችም እዚሁ አካባቢ በመኖራቸው(ዳውንት ዋድላ ደላንታ) ከአርባእቱ ስውራን ዋሻወች ይፋ ልሆኑም ስላሉ ብሎም ዋድላ ደላንታ እና ዳውንት በቤጌምድር ተቅላይ ግዛት አብረው የነበሩ ከመሆናቸውም ባሻገር እና የጥንቱን አንጎት መነሻ ስለያዙ ፍለጋህን እነዚሁ አካባቢወች ብታደርግ! ለሌላው ዋድላ የዶጊት ማርያም አጠገብ ጌርጊስ(ገርጊስ) እንቆ(አናቆ) በሚል የሚጠሩ ፍልፍል በተክርስቲያን እና ዋሻ ያለባቸው ተራሮች መኖራቸውን ስጠቁምህ በትህትና ነው፡፡

  ReplyDelete
 32. ውድ ዳንኤል በፍለጋህ ዦጋ(ሾጋ) ጋሼና ብለህ የተቀስካቸው ቦታወች ደላንታ እና ዋድላ አካባቢ ያሉ በመሆናቸው ብዙ ታሪካዊ ቦታወችም እዚሁ አካባቢ በመኖራቸው(ዳውንት ዋድላ ደላንታ) ከአርባእቱ ስውራን ዋሻወች ይፋ ልሆኑም ስላሉ ብሎም ዋድላ ደላንታ እና ዳውንት በቤጌምድር ተቅላይ ግዛት አብረው የነበሩ ከመሆናቸውም ባሻገር እና የጥንቱን አንጎት መነሻ ስለያዙ ፍለጋህን እነዚሁ አካባቢወች ብታደርግ! ለሌላው ዋድላ የዶጊት ማርያም አጠገብ ጌርጊስ(ገርጊስ) እንቆ(አናቆ) በሚል የሚጠሩ ፍልፍል በተክርስቲያን እና ዋሻ ያለባቸው ተራሮች መኖራቸውን ስጠቁምህ በትህትና ነው፡፡

  ReplyDelete
 33. ውድ ዳንኤል በቅድሚያ ስለምታደርገው ጥረት እያመሰገንኩ፡ በታሪክ አንጎት የአሁኑን የጁን ሊጨምር ይችል ዪናል፡፡ አሁንም ድረስ ግን አንጎት ደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ ውስጥ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት አንጎት ከ2001 ዓ.ም ከደላንታ ወረዳ ወደ ጉባላፍቶ ወረዳ /የጁ/ የተቀላቀሉትን 2 ቀበሌዎች ጨምሮ ሌሎች 3 ቀበሌዎችን በመጨመር በአጠቃላይ አሁን ድረስ አንጎት እየተባለ ይጠራል፡፡

  ReplyDelete