የሚወዱትን ሰው አጥቶ በብቸኝነት መኖር ከተስፋ ይልቅ በትዝታ ውስጥ እንድንኖር
የሚያደርግ ነው፡፡ በማኅበረሰባችን ባህል የቤት ውስጥ ሥራዎች የሚባሉትን በአብዛኛው የሚሸፍኑት ሴቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሴቶች
የተማሩም ቢሆኑ ወይም ያልተማሩ፣ ሠራተኞችም ቢሆኑ ወይም የቤት እመቤቶች የቤት ሥራ ይቀርላቸው ይሆናል እንጂ የቤት አስተዳደር
አይቀርላቸውም፡፡ እነዚህ ሴቶች ሊቃውንትም ቢሆኑ ወይም ሳይንቲስቶች፣ የሀገር መሪዎችም ቢሆኑ ወይም የታወቁ ሃሳብ አመንጭዎች
የቤት ውስጥ ጭቅጭቅ ግን አይቀርላቸውም፡፡ ጓዳ የራሱ ሳይንስ አለው፡፡ የጓዳ ሳይንስ እስከዛሬ በየትኛውም ትምህርት ቤት
አይሰጥም፡፡ የጓዳ አስተዳደር በየትኛውም የአስተዳደር ትምህርቶች ውስጥ አልተካተተም፡፡
ይህ ነው እንግዲህ ለአባቴ የመጀመርያው ፈተና፡፡ ጓዳውን ማስተዳደር፡፡ በቤታችን
ውስጥ እናታችን ካረፈች በኋላ ሦስት ዓይነት የቤት ሠራተኞችን አይተናል፡፡ የመጀመርያዎቹ ቤቱን ‹‹የወንድ ቤት ነው›› ብለው
የሚያስቡና መደፋፋት፣ ማባከንና ማዝረክረክ ይቻላል ብለው የሚገምቱ ናቸው፡፡ ወንድ ጓዳ ድረስ አይዘልቅም፤ የተጠየቀውን
ይሰጣል፣ ግዛ የተባለውን ይገዛል፤ ለምን አለቀ፣ መቼ አለቀ፣ እንዴት አለቀ አይልም ብለው የሚያስቡ ዓይነት ናቸው፡፡