Friday, January 25, 2013

አሸንፈናል፤ ማንን? እኛንየዛሬ ሠላሳ አንድ ዓመት ኢትዮጵያን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማሳለፍ ወሳኝ የሆነውን ግብ ላገባው ተጨዋች አራት ሜትር ጨርቅ ነበር አሉ የተሸለመው፡፡ ዘመን ተለውጦ፣ ሀገርም ተለውጣ ይኼው ዛሬ ተጨዋቾቻችን በመቶ ሺ ብሮች፣ በሞባይል ስልኮች፣ በሙሉ ልብሶችና በጫማዎች ተምነሽንሸዋል፡፡ ለቀጣይ ድሎቻቸውም በዶላሮች ቃል እየተገባላቸው ነው፡፡
ግን ይህን መሰል ትርዒት እንደገና ለማየት ስንት ዓመት ይፈጅብን ይሆን? 

የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ
ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ
ማን ያውቃል?
አሉ አብዬ መንግሥቱ ለማ፡፡ የኛስ እግር ኳስ ከጅራታም ኮከብ ጋር ቀጠሮ እንዳላቸው ማን ያውቃል? እርሷ በየ75/76 ዓመቱ ምድርን ስትዞር በየአጋማሹ ነው እንዴ እኛ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የምንሄደው? የአፍሪካን ዋንጫ ለመሠረትን ለእኛ፤ የመጀመርያዎቹን ዋንጫዎች ከወሰዱት ሀገራት ተርታ ለተሰለፍን ለእኛ፣ የአፍሪካን እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ለብዙ ዓመታት ለመራን ለእኛ፣ ‹እነ ድንጋይ ኳሱ› ተብሎ ለተገጠመልን ለእኛ የአፍሪካ ዋንጫ ለምን ብርቃችን ሆነ? 
© photo from Ethiopian review
ለመሆኑ ይህንን የአፍሪካ ዋንጫ ስኬት ያገኘነው በጥረት ነው ወይስ በዕድል?
በዕድል ከሆነ ሌላ ሠላሳ አንድ ዓመት እንጠብቃለን፡፡ በጥረት ከሆነ በቀጣዩም እንገኛለን፣ ያለበለዚያም ቢያንስ አሠልሰን እንካፈላለን፡፡ በዕድል ከሆነ ለቀጣዮቹ ሠላሳ አንድ ዓመታት ታሪክ ብቻ እንተርካለን፡፡ በጥረት ከሆነ ግን ሌላም ታሪክ እንሠራለን፡፡ በጥረት ከሆነ ያልነውን እናሳካለን በዕድል ከሆነ ግን የእናታችን መቀነት እንዴት እንደጠለፈን መዘርዘር እንጀምራለን፡፡ በጥረት ከሆነ ብንሸነፍ እንኳን በምክንያት እንሸነፋለን፤ በዕድል ከሆነ ብናሸንፍ እንኳን ያሸነፍንበትን ምክንያት አናውቀውም፡፡ በጥረት ከሆነ የድሉ ድባብ ደቡብ አፍሪካ ሜዳ ላይ ይታያል፤ በዕድል ከሆነ ግን የጨበራ ድግስ መስሎ ለያዥ ለገራዥ ያስቸግራል፡፡
ያረሰማ ጎበዝ እርፍ የነቀነቀ
ወፍጮው እንዳጎራ መስከረም ዘለቀ
ይላል የሀገሬ ገበሬ ጀግናውን አራሽ ሲያሞግሰው፡፡ ሞፈር ከቀንበሩ አስማምቶ፣ ፀሐይ ቁሩን ችሎ፣ አረንቋ ጭቃውን ተቋቁሞ፣ ዕንቅልፍና ድካምን አሸንፎ ዓመቱን ሙሉ የሠራ ገበሬ በክረምት ወፍጮው ‹እርም፣ እርም›› ሲል ማንነቱ ይታወቃል፡፡ ሰነፉ ገበሬ (ሰነፍ ገበሬ በሰኔ ይሞታል እንዲሉ)
እኛስ ይችን ክረምት ወጣናት በመላ
በኩርማን እንጀራ ጎመን ተጠቅልላ
እያለ ሲያዜም፤ ጎበዙ ገበሬ ግን ከነጎድጓዱ ጋር ወፍጮው ሲያስገመግም ክረምቱን ይዘልቃል፡፡ የጀግና ገበሬ መታያው መለኪያው ክረምቱ ነው፡፡
የፌዴሬሽኑም፣ የአሠልጣኙም፣ የተጨዋቹም የጥረት ፍሬ ደቡብ አፍሪካ ሜዳ ላይ እየታየ ነው፡፡ ድል ማለት በዋንጫው፣ በማጣርያው ማለፍ ብቻ አይደለም፡፡ በምርጥ ጨዋታ፣ በተጠናና በጠቀመረ ጨዋታ፣ ተመልካችን ቁጭ ብዲግ በሚያደርግ ጨዋታ ድል ይገኛል፡፡ ለአፍሪካ ዋንጫ የሚመጥን ጨዋታ ተጫውተናል፡፡ እንዲህ ሆነን የምንጠብቀው ነገር እንኳን ባይሆን ለኛ ድሉ አይደበዝዝም፡፡ አንዳንዴ አሪፍ መጽሐፍ ሳይሸጥ ሊቀር ይችላል፡፡ እንደ ዳኛቸው ወርቁ አደፍርስ፡፡ አለመሸጡና ‹በተሻለ ሁኔታ የተሸጠ›› best selling አለመባሉ ይዘቱን ላይነግረን ይችላል፡፡
ስፖርት ከውጤት ይልቅ ሂደት ነው፡፡ ከመንደር ጀምሮ እስከ ሀገር አቀፍ፣ ከታችኛው ቡድን እስከ ፕሪሚየር ሊግ፣ ከወረዳዎች ውድድር እስከ ዓለም ዋንጫ፣ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ኮሌጅ፤ ከግለሰብ እስከ ማኅበር፣ ከቡድን እስከ ፌዴሬሽን የሚያደርጉት ሠንሰለታዊ ትግግዝና ጥረት ነው እግር ኳሱ አድጓል ወይስ አላደገም? የሚለውን የሚመልሰው፡፡  አንዳንድ ጊዜ ውጤት በአጋጣሚም፣ በዕድልም፣ በተወሰኑ ሰዎች ጥረትም፣ በተቃራኒ ቡድን ድክመትም ሊገኝ ይችላል፡፡ ይህ ውጤት የሂደት ውጤት ካልሆነ ክስተት ይሆናል፡፡ ከዚያም እንደ ተአምር ይቆጠራል፡፡
ስፖርታዊ ውጤት የሂደት ፍሬ ከሆነ ተጨዋቹም፣ አሠልጣኙም፣ ፌዴሬሽኑም፣ ሕዝቡም ለምን አላለፍንም? ለምን አላሸነፍንም? ለምን አልተሳካልንም? ብለው ይጠይቃሉ እንጂ እንዴት ልናሸንፍ ቻልን? ብለው አይገረሙም፡፡ ለምን ስማችን አልተጠራም? ብለው ይገረማሉ እንጂ እገሌ የተባለ ታዋቂ አሠልጣኝ፣ ወይም ሚዲያ እንዴት ስማችን ጠራው? ብለው ብርቅ አይሆንባቸውም፡፡ የሠሩትን፣ የለፉትን፣ ያወጡትን፣ የደከሙበትን ያውቃሉና፡፡ በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ማለፋችን ለብዙ ሰው ተአምር፣ የሥዕለት ውጤት፣ ታላቅ ዕድል፣ ሆኖበታል፡፡ ለምን?
አንድ ሕንፃ ሲገነባ መጀመርያ የሕንጻው ዲዛይን በቢል ቦርድ ይሰቀላል፡፡ ሕዝቡ ምን እንደሚሠራ፣ ማን እንደሚሠራው፣ ማን እንደሚያማክረው፣ ባለቤቱም ማን እንደሆነ ያውቀዋል፡፡ መሠረቱ ሲጣል ያያል ወይም ይሰማል፡፡ ቁፋሮ ሲጀመር፣ አፈሩ ሲወጣ፣ መሠረት ሲደመደም፣ ግንቡ ሲቆም፣ ‹ቢም› ሲታሠር፣ አርማታ ሲሞላ፣ ብሎኬት ሲደረደር፣ አልቆም ሲቀባባና የውስጥ ዕቃው ሲሟላ ያያል፡፡ ስለዚህም አንድ ቀን በሠፈሩ አንዳች ልዩ የሆነ ሕንፃ ቢያይ ተአምር አይሆንበትም፡፡ ባይሆን ሥራውንና ሠሪውን ያደንቃል፡፡ የሂደቱም አካል ነበርና እንዴት ተጀምሮ እንዳለቀ ይተርካል፡፡ ምስክርም ይሆናል፡፡
ለመሆኑ ስለ እግር ኳስ ስፖርታችን እንደዚህ አድርገን መተረክ እንችላለን? ዕቅዱ ምን ነበር? እነማን ጀመሩት? እነማን አማከሩ? እነማን ምን ሠሩ? ባለቤቱ ማን ነበር? መቼ መሠረቱ ተጣለ? እንዴት ተገነባ? እንዴትስ እዚህ ደረስን? አሁን ሁላችን የምናውቀው፣ የምንናገረውና አካል የሆንንበት ነገር አለን? ወይስ ሕንጻውን በድንገት ሠፈራችን ውስጥ አገኘነው?
 በትክክለኛ ሂደት የሚመጣ መጥፎ ውጤት በመጥፎ ሂደት ከሚመጣ አስደሳች ውጤት እጅግ የተሻለ ነው፡፡ አንድ ቡድን መሠረት ኑሮት፣ ተተኪ ኑሮት፣ መንገዱ ተስተካክሎለት፣ ሥልጠናው፣ ትጥቁ፣ ድጋፉና በጀቱ ተሟልቶ፣ በሚገባ ተዘጋጅቶና ዐቅዶ፣ ግን ያልታሰበና ያልተፈለገ ውጤት ሊመጣ ይችላል፡፡ ሕዝቡም፣ አሠልጣኙም፣ ተጨዋቹም፣ ፌዴሬሽኑም የሚችሉትን ሁሉ አንጠፍጥፈው፣ ግን የሚፈለገው ውጤት ላይመጣ ይችላል፡፡ ያን ጊዜ ተስፋ መቁረጥ አይመጣም፡፡ ምክንያቱም በመልካም መንገድ ላይ ያጋጠመ ዕንቅፋት እንጂ፣ በዕንቅፋት በተሞላ መንገድ ላይ የመጣ ዕጣ ፈንታ አይደለምና፡፡
ከርሞ እንገናኝ ላመት
እናንተም ሳትሞቱ እኛም ላንሞት
ብለን ከውድድሩ ሥፍራ እንመለሳለን፡፡ ከርሞ እንደምንገናኝ አምነን፤ የሠራነው ሥራ ዘላቂ እንጂ ጊዜያዊ፣ ለዓመታት እንጂ ለዛሬ፣ የጥረት ውጤት እንጂ የዕድል ጉዳይ አይደለምና፡፡ እየተማሩ መውደቅና እየወደቁ መማር ይለያያሉ፡፡ እነ አብርሃም ሊንከን በደርዘን ለሚቆጠር ጊዜ እየተማሩ፣ እየወደቁ፣ ግን ከውድቀታቸው እየተማሩ ተጉዘው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡ እነ ቅዱስ ያሬድ እየተማሩ ወድቀው፣ ግን እየወደቁ ተምረው ሊቀ ሊቃውንት ሆነዋል፡፡ እነ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ እየተማሩ ወድቀው፣ ግን ከውድቀታቸው ተምረው ያሰቡበት ደርሰዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች መንገዳቸው ትክክል ነበረ፡፡ የጥበብ መንገድም ነበረ፡፡ ግን ውድቀት አጋጠማቸው፡፡ ከውድቀቱም ትምህርት ወሰዱና ተማሩበት፡፡ ወትሮም በትክክለኛው መንገድ ላይ ስለነበሩ ውጤታቸውን አሣመሩት፡፡ ውጤታቸው የአጋጣሚ ወይም የዕድል ፍሬ አልነበረምና፤ በሥጋ ካረፉም በኋላ እንኳን ዘለቀ፡፡
አሁንም ከውጤቱ በላይ ለሂደቱ መጨነቁ፣ ሂደቱንም መልካም ለማድረግ መሥራቱ ውጤታችንን ዘላቂ ያደርገዋል፡፡ ለሂደቱ ቢታሰብ ኖሮ ሱዳንን ካሸነፍንበት ቀን እስከ ዛሬ ተረባርበን የስታዲዮም መገንቢያ ቦታ እንቀበል፣ መሥሪያ ገንዘብም እንሰበስብ ነበር፡፡ ሕዝቡን ለዘለቄታዊ የእግር ኳስ ውጤት በዘላቂ ዕቅድ እናሰልፈው ነበር፡፡ አየነውኮ፡፡ ዓለም ካሸናፊዎች ጋር ናት፡፡ ማሸነፍ ስንጀምር ርዳታው፣ ስፖንሰሩ፣ ሽልማቱ፣ ዕውቅናው ጎረፈ፡፡ ስማችን ጠርተውን የማያውቁት ስማችንን ጠሩን፡፡ 
ዊንስተን ቼርቺል በአንድ ወቅት አሜሪካን ሀገር በዚያ ጊዜ ሃምሳ ሺ ሕዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ ንግግር አድርጎ ነበር፡፡ የአንድን መሪ ንግግር ለመስማት ያንን ያህል የአሜሪካ ሕዝብ ሲሰበሰብ ብርቅ ነበር፡፡ ከንግግሩ በኋላ አንድ ሰው ቼርቺልን ‹‹ይህ ሁሉ ሕዝብ አንተን ሊሰማ ሲወጣ ምን ተሰማህ?›› ብሎ ቢጠይቀው ‹‹ቼርቺል አንዳች ነገር አጥፍቶ ሊሰቀል ነው ቢባል ከዚህ በላይ ሕዝብ እንደሚሰበሰብ ተሰማኝ›› ነበር ያለው፡፡
ዛሬ በድል ስንምነሸነሽ ወዳሴ የሚያዘንቡልን ሁሉ ነገ ተሸነፉ ብንባል ከጎናችን ይኖራሉ? እንዲሁ እንዳሁኑ በከፍታዎች ላይ እንዘልቃለን? ይህ ዛሬ ከሞባይሉ ቀንሶ የሚሠጠን ሕዝብ ነገስ ይለግሰናል? የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጨዋቾች የትጥቅ ችግራቸው እንደተፈታ ይቀራል ወይስ ተመልሰው ‹‹ማልያ መቀያየር ያስቀጣል›› ይባላሉ? ስፖንሰርሺፑ ይዘልቃል? ወይስ ‹በድሮ ዘመን አንድ ስፖንሰር ነ-በ-ረ›› የምንልበት ዘመን ይመጣል? ይህንን ደቡብ አፍሪካውያንንና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንን እስኪያስገርም ድረስ ትኬት የገዛ ሕዝብ ነገ የትኬቱን ገንዘብ ወደ እግር ኳሱ ዕድገት እንዲቀይረው ታስቧል? ወይስ ‹‹የዛሬ ሠላሳ አንድ ዓመት፣ ደቡብ አፍሪካ ላይ›› እያለ ተረት ወደሚተርት ሽማግሌ ይለወጣል፡፡
ከጨዋታው በኋላ አጀንዳችን ‹‹እገሌ ለምን ኳስ ሳያቀብል ቀረ? እንዴት በእገሌ እንሸነፋለን? አሠልጣኙ ምን ሆነ? እነ እገሌ ለምን አልተሰለፉም? የተዋጣው ብር የት ደረሰ? ሽልማታችን አልተሰጠንም? ከተጨዋቾች ቁጥር በላይ የቡድን መሪዎች ለምን ሄዱ? ›› የሚል ከሆነ ዋንጫ ከማጣትም፣ ማጣርያ ከማለፍም በላይ ከስረናል ማለት ነው፡፡ የምንችለውን ጨዋታ ተጫውተን፣ የሚገባንን ውጤት አምጥተን፣ የት እንደ ደረስንና ምን ማድረግ እንደምንችል ለዓለም አሳይተን፤ ‹‹ለቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ፣ እንዲያውም ለዓለም ዋንጫ ምን እናድርግ? ሠላሳ አንድ ዓመቱን በሃያ ዘጠኝ ዓመት እንዴት እንቀንሰው?›› የምንል ከሆነ ግን ማጣርያ ባናልፍም፤ ዋንጫ ባናመጣም እኛ አሸንፈናል፡፡ ከምንም በላይ አንችልም የሚለውን ተጋጣሚ አሸንፈናል፡፡ ኢትዮጵያ የትም አትደርስም የሚለውን ተቃራኒ አሸንፈናል፡፡ ስል ክፉ ጎናችን ለማውራት የሚሽቀዳደሙትን ሚዲያዎች አንደበት በውዳሴ በማሟሸት አሸንፈናል፡፡ በተስፋ መቁረጥ ላይ ፍጹም ቅጣት ምት መትተናል፡፡ ከዚህ በላይ ምን ድል አለ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ እኛ እኛን አሸንፈናል፡፡
መልካም ዕድል፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው፡፡

12 comments:

 1. ጎበዙ ገበሬ ግን ከነጎድጓዱ ጋር ወፍጮው ሲያስገመግም ክረምቱን ይዘልቃል፡፡ የጀግና ገበሬ መታያው መለኪያው ክረምቱ ነው፡፡

  ReplyDelete
 2. ያጣነውን ትተን ያገኘነውን እናስብ፤ የሌለንን ትተን ባለን እንጠቀም፤ ያልሆንነውን ትተን በሆንነው እንሥራበት፤ ያልደረስንበትን ትተን በደረስንበት እናፍራበት፡፡ የማይጎድል የለምና፡፡ የዚህ ዓለም ጉዞ አንዱን ጎደሎ እየሞሉ ሌላ ጎደሎ መፍጠር ነው፡፡

  ReplyDelete
 3. ከርሞ እንገናኝ ላመት
  እናንተም ሳትሞቱ እኛም ላንሞት

  ‹‹ለቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ፣ እንዲያውም ለዓለም ዋንጫ ምን እናድርግ? ሠላሳ አንድ ዓመቱን በሃያ ዘጠኝ ዓመት እንዴት እንቀንሰው?››

  ReplyDelete
 4. You are really correct Danny. kehulum belay ega egan ashenefenal.

  ReplyDelete
 5. Thank you bro!በትክክለኛ ሂደት የሚመጣ መጥፎ ውጤት በመጥፎ ሂደት ከሚመጣ አስደሳች ውጤት እጅግ የተሻለ ነው፡፡ ... How many of us think this way?‹ለቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ፣ እንዲያውም ለዓለም ዋንጫ ምን እናድርግ? ሠላሳ አንድ ዓመቱን በሃያ ዘጠኝ ዓመት እንዴት እንቀንሰው?›› የምንል ከሆነ ግን ማጣርያ ባናልፍም፤ ዋንጫ ባናመጣም እኛ አሸንፈናል፡፡ ከምንም በላይ አንችልም የሚለውን ተጋጣሚ አሸንፈናል፡፡

  ReplyDelete
 6. ዓለም ካሸናፊዎች ጋር ናት፡፡ ማሸነፍ ስንጀምር ርዳታው፣ ስፖንሰሩ፣ ሽልማቱ፣ ዕውቅናው ጎረፈ፡፡ ስማችን ጠርተውን የማያውቁት ስማችንን ጠሩን፡፡

  ReplyDelete
 7. ሐዘናችን በደስታ እንደሚቀየር እርግጠኛ ነኝ፡፡ ፈጣሪ ላያስጨርስ አያስጀምርምና ናይጀሪያን በፀሎትም ቢሆን 2-1 ማሸነፍ አለብን፡፡ በቃ አለዚያ ተቃጥዬ መሞቴ ነው፡፡ ቶሎ ብዬም የምረሳው አይመስለኝም፡፡ ዳኒ አንተም ሰባት ሰላም እለኪንና አቡነ ዘበሰማያትን ድገም፣ እኔም ከልቤ እፀልያለሁ፡፡

  ReplyDelete
  Replies
  1. don't you know for what do be prayed? what a pity you are!
   "ሐዘናችን በደስታ እንደሚቀየር እርግጠኛ ነኝ፡፡ ፈጣሪ ላያስጨርስ አያስጀምርምና ናይጀሪያን በፀሎትም ቢሆን 2-1 ማሸነፍ አለብን፡፡ በቃ አለዚያ ተቃጥዬ መሞቴ ነው፡፡ ቶሎ ብዬም የምረሳው አይመስለኝም፡፡ ዳኒ አንተም ሰባት ሰላም እለኪንና አቡነ ዘበሰማያትን ድገም፣ እኔም ከልቤ እፀልያለሁ፡፡"

   Delete
 8. ምንም እንኳን በመጀመሪያ አንድ እኩል ወጥተን ሁለተኛው ላይ አራት ለባዶ ብንሸነፍም እውነት ነው አኩርተውናል ፡፡ማነው ኢትዮጵያን እግር ኳስ አትችልም የሚል ካሁን በኋላ; የአፍሪካ እግር ኳስ ዛሬ ተጀመረ እስኪባል አንገታችንን ቀና እንድንል አደረጉን ታድያ እነዚን ጀግኖች ማነው ሚተች; ብቻ ክብር ይገባቸዋል ሰላም ይሁኑ ሁሉም ባሉበት፡፡

  ReplyDelete
 9. የምንችለውን ጨዋታ ተጫውተን፣ የሚገባንን ውጤት አምጥተን፣ የት እንደ ደረስንና ምን ማድረግ እንደምንችል ለዓለም አሳይተን፤ ‹‹ለቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ፣ እንዲያውም ለዓለም ዋንጫ ምን እናድርግ? ሠላሳ አንድ ዓመቱን በሃያ ዘጠኝ ዓመት እንዴት እንቀንሰው?›› የምንል ከሆነ ግን ማጣርያ ባናልፍም፤ ዋንጫ ባናመጣም እኛ አሸንፈናል፡፡ ከምንም በላይ አንችልም የሚለውን ተጋጣሚ አሸንፈናል፡፡ ኢትዮጵያ የትም አትደርስም የሚለውን ተቃራኒ አሸንፈናል፡፡ ስል ክፉ ጎናችን ለማውራት የሚሽቀዳደሙትን ሚዲያዎች አንደበት በውዳሴ በማሟሸት አሸንፈናል፡፡ በተስፋ መቁረጥ ላይ ፍጹም ቅጣት ምት መትተናል፡፡ ከዚህ በላይ ምን ድል አለ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ እኛ እኛን አሸንፈናል፡፡
  መልካም ዕድል፡፡

  ReplyDelete
 10. አይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ አድናቆትና አድናቂዎች፡፡ አገርን በመውደድ፣ የአገርን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድንን ውጤታማነት በመመኘትና በእውነተኛው ብቃታችን መካከል ያለውን ልዩነት አንጥሮ በማውጣት ይሄ አገራዊ ስሜታችንንና መሻታችን ነው ይሄኛው ደግሞ እግር ኳሳችን ያለበት ደካማ መዋቅራዊ አደረጃጀት ያመጣው (የአቅም የቴክኒክና የታክቲክ ብስለታችን ማለቴ) ነው ብሎ በዝርዝር ማስረዳት የሚቻለውና እውነታውን እየተጎነጩ ችግሩን እየቀረፉ የሚከደው መቼ ይሆን?

  እውነት ነው እስከ ዛሬ ካየሁት ጨዋታ በተሻለ ሁኔታ ዛምቢያ ላይ ጥሩ ነገር አድርገናል (በጨዋታ ፍሰት፣በታክቲክ አተገባበር ዛሬም ቢሆን የጋርዚያቶን የአርጀቲና ትርዒት የላቀ ጨዋታ ማየት አልቻልኩም)፡፡ ግን መረሳት የሌለበት ኢትዮጵያ የዛምቢያ ቡድንን ደጋግማ በማግኘት ረገድ አዲስ አይደለችም፡፡ ወደ ምዕራብ አፍሪካና ሰሜን ስናቀና ግን ኢትዮጵያ ጥሩ የውጤት ታሪክ የላትም፡፡

  አሁን ያለው ድጋፍና ኩሸት አገራዊ ስሜት የተቀላቀለበት ነው፡፡ እንደዚህ ከሆነ እንግሊዞች ስለ ብሔራዊ ቡድናቸው የሚያወሩትና የሚያገኙት ውጤት ዓይነት የሚዲያ ትርፍ ብቻ እንዳይሆን ብቃት ላይ የተመሠረተ ትንተና ጠቃሚ ነው ባይ ነኝ፡፡

  ReplyDelete
 11. dani i like your blog but i like this to much
  now a days if u say some thing i say it is correct no matter what it is

  ReplyDelete