click here for pdf
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ታላላቅ ሥራ ሠርተው ነገር ግን እጅግም
ሳይታወቁ ያለፉ አባቶችና እናቶች አሉ፡፡ ዛሬ ላለንበት መሠረት የሆኑ፣ እምነታችን ሲቀዘቅዝ፣ ሞራላችን ሲናድ፣ ክብራችን
ከራሳችን ላይ ሲወርድ፤ ለልባችን ብርሃን፣ ለቀቢጸ ተስፋችን መጽናኛ፣ ለባዶነታችንም መሙያ የሚሆኑ ድንቅ ሰዎች አሉ፡፡ ዐውቀው
የሚያምኑ፤ ባመኑበት የሚጸኑ፣ ለጸኑበት የሚያስከፍላቸውን መሥዋዕትነት ሁሉ የሚከፍሉ፣ በጥብዐት የሚጓዙ፡፡ ሥልጣን ገንዘብ፣
ርስት፣ ክብርና ሹመት ያመኑበትንና የጸኑበትን የማያስለውጧቸው፡፡ የስቃይ ዓይነቶች፣ የመከራ ብዛቶች፣ የቅጣት ውርጅብኞች
ከአቋማቸው የማያስበረግጓቸው፡፡ በአንድ በኩል መንፈሳውያን ከሚመስሉ ዓለማውያን፤ በሌላ በኩል ኃይልና ሥልጣን ከጨበጡ
ነገሥታትና መኳንንት፤ በአንድ በኩል ለሆድ ካደሩ የቤተ መቅደስ ሰዎች፣ በሌላ በኩል ክብራቸውን ሽጠው ካደሩ መለካውያን ባለ ጊዜዎች ጋር የተጋደሉ አባቶችና እናቶች ነበሩን፡፡
አቡነ ፊልጶስ ዘደብረ ሊባኖስ ከእነዚህ አንዱ ነበር፡፡ በ1266 ዓም አካባቢ ለት በምትባል ቦታ የተወለደው አቡነ
ፊልጶስ ወደ ደብረ አስቦ (ደብረ ሊባኖስ) ገዳም የገባው በ15 ዓመቱ ነበር፡፡ በዚያ መጀመርያ ወደ ደብረ አስቦ ከገቡት 17 የአቡነ
ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዛሙርት አንዱ ነው፡፡ በዚያ ገዳም ቅዱሳት መጻሕፍትንና ምንኩስናዊ ሕይወትን ተምሮ ያደገው አባ ፊልጶስ ከአቡነ
ተክለ ሃይማኖት ዕረፍት በኋላ በ1306 ዓም የደብረ ሊባኖስ ገዳም ሦስተኛው እጨጌ ሆነ፡፡