በአውሮፓ ክርስቲያኖች ዘንድ የታወቀ አንድ የአራተኛው መክዘ ታሪክ አለ፡፡ ድኾችን
እጅግ የሚወድ፣ የተቸገሩትን ለመርዳት ምንም ነገር የማያግደው፤ ከእራሱም አብልጦ ለሌሎችን የሚሞት አንድ ሰው ነበረ፡፡ ይህ
ሰው በበጎ ምግባሩ የተነሣ ስሙ ተረስቶ ‹እኁ ቅዱስ- ቅዱሱ ወንድም› እየተባለ ነው የሚጠራው፡፡ በታሪክ ድርሳናትም
የተመዘገበው በዚሁ ስም ነው፡፡ ሠርቶ የሚያገኘውን ምንም ለሌላቸውና ለምነው እንኳን ለማግኘት ዐቅም ላነሣቸው በመስጠት የታወቀ
ነበር፡፡
አንድ ጊዜ የሚሰጠው ነገር አጣ፡፡ ብዙ ችግረኞች ደግሞ መልካም ዜናውን ሰምተው ጥቂት
ነገር ለማግኘት ወደ እርሱ ዘንድ መጡ፡፡ ምን ይስጣቸው፡፡ የሚያያቸው አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ሌላ አማራጭ የላቸውም፡፡
ብዙዎቹ ገንዘቡን ከጨረሰ በኋላ ከሩቅ ሀገር ሳይቀር በመምጣታቸው አዘኑ፡፡ መመለሻ እንኳን የላቸውም ነበር፡፡ በመጨረሻ እኁ
ቅዱስ አንድ ውሳኔ ላይ ደረሰ፡፡ ‹‹እኔን ሽጡኝና ተካፈሉ› አላቸው፡፡ እነዚያ ችግረኞችም ምን አማራጭ ስላልነበራቸው እርሱን በባርነት
ሸጡትና ገንዘቡን ተካፈሉ፡፡